መልካሙ ተክሌ (melkamutekle@gmail.com)
ሰሞኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕገወጥ ተግባር ተፈጽሞባቸዋል ብሎ ጥናት ያካሄደባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች፤ የመሬት ወረራና የቀበሌ ቤቶችን የተመለከተ መረጃ ለሕዝብ ይፋ ካደረገ በኋላ በከተማዋ ዋና መነጋገርያ ሆኗል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም በዚህ መልኩ በሕዝብ ላይ የተፈጸሙ በደሎችን ለማጋለጥ የሄደበት ዕርቀት ከበርካታ ወገኖች አድናቆትን አስገኝቶለታል፡፡ ሆኖም ግን በጥናቱ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ብልሹ አሠራሮች አለመዳሰሳቸው ግን ጥናቱን ሙሉ እንዳይሆን ያደረገው ይመስለኛል፡፡
ለስድስት ዓመታት ከቆጠብን በኋላ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም በወጣው የሁለተኛ ዙር የአዲስ አበባ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ እንደወጣልን ስናውቅ በብዙ ሺህ የምንቆጠር ዜጎች ደስተኛ ሆነን ነበር፡፡ ሆኖም ከመጀመሪያም ግልጽነት በጎደለው አሠራር ስሙ 40/60 ሆኖ ሳለ መቶ በመቶ የቆጠብን ሳለን ለሌሎች እንዴት ወጣ በሚል ክስ ተመስርቶም እንደነበር ይታወቃል፡፡
ይህ ሁለተኛ ዙር ዕጣ ከወጣ ከአምስት ወር በኋላ በነሐሴ ወር አንድ ቦታ ብቻ በተለጠፈ ማስታወቂያ ኑ እና ውል እሠሩ ተባልን፡፡ ቤቶቹ ቶሎ ባለመጠናቀቃቸው የተደረገውን ዋጋ ጭማሪ አካቶ መቶ በመቶ የከፈልን ዕጣ የወጣልን ሰዎች ካርታችንን፣ 40 በመቶ እና ከዚያ በላይ የከፈልን ደግሞ 9.5% ወለድ የሚታሰብበት የብድር ውል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተፈራረምን፡፡ በቤቶቹ መኖር ሳንጀምር የባንክ ዕዳ መክፈላችንም በምን ሕግ ልክ እንደሆነ ባይገባንም፡፡
በዓመቱ ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ ቁልፍ ተረከቡ ተባልን በመላ አዲስ አበባ አንድ ቦታ ብቻ በተለጠፈ ማስታወቂያ፡፡ በጋዜጣችሁ ጥያቄ የቀረበላቸው አንድ የቤቶች ማስተላለፍ የሥራ ኃላፊ ግን ካሁን ቀደም ለጋዜጣችሁ በሠጡት ምላሽ ለእያንዳንዱ ደውለን ነግረናል ብለዋል፡፡
ለስንት ሺህ ሰው እንደደወሉ እነሱ ያውቃሉ- አልደወሉም እንጂ! ማስታወቂያውን ለተጠቃሚ ያስተላለፉት ግን ራሳቸው ተጠቃሚዎች ናቸው እንጂ ስልክ አልተደወለም፡፡ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን አልተነገረም፡፡ በጋዜጣም አልተጻፈም ማስታወቂያው። በግልጽ ለሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ስላልተነገረ ዕድለኛ ሆነው ምዝገባ ያለፋቸውን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡
ወደ ነሐሴ 2012 ዓ.ም ቁልፍ ርክክብ ስንመጣ ሦስቱ ሕጋዊ አካላት አንድ ሕጋዊ ያልሆነ ሥራ እንደሠሩ እንገነዘባለን፡፡ ቁልፍ ሳንረከብ እንዴት ተረከብን ብለን እንፈርም ስንል ለደንቡ ነው ቁልፉ ከሁለት ወር በኋላ ቤቱ ተጠናቆ ይሠጣችኋል ተባልን፡፡
ይህንንም ያሉን በስንት ልምምጥ ነው፡፡ ያም ሆኖ የሕንፃ ተቋራጩ፣ የአሠሪው እና የአማካሪ ድርጅቱ ማኅተም ያረፈበት ወረቀት በቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ካሟላቸው ያላሟላቸው የሚበዙ በቴክኒካዊ ሥሞች ስለተሞላም ግልጽነት የጎደለውም ነው፡፡
በርክክቡ ወቅት የነበሩ ባለሙያዎችን ለመጠየቅ ስንሞክር ግን ካሁን በኋላ ቤታችሁ ነው እየመጣችሁ ለውጡን ማየት ትችላላችሁ፣ ተሟልቷል የተባለው ዕቃው ባይገጠምም ማዕከል ተገዝቶ ስለተቀመጠ ነው ቢሉንም በተጨባጭ ግን ይህ አልሆነም፡፡
በዚህ የተነሳ ፕሮጀክት ኃላፊውን ለማነጋገር ስንሞክር እኛን ለማናገር ፈቃደኛ እንኳን አልሆኑም፡፡ ገፍተን በመሔድ የግድ ልናናግር ብንሞክርም በምስክሮች ፊት እናንተ ስለጥራት ምን ታውቃላችሁ ብለው ሸኝተውናል፡፡
ፕሮጀክቱ ቦታ ያሉ የአማካሪ ድርጅቱ ተወካይ ግን ሕገወጥ እና ጥራቱን ያልጠበቀ ተሠርቶ ከሆነ እናስፈርሳለን ቢሉም በስብርባሪ ዕብነበረድ በቦሌ ቡልቡላ ሎት አንድ ሕንጻ ቁጥር 29 እየተሠራ ያለው ግን እስካለፈው ሳምንት ድረስ ከሚያስፈልገው የሠራተኛ መጠን እጅግ ባነሰ ሠራተኛ እየተሠራ ነው፡፡ አማካሪ ማንም ሳይነግረው መሥራት ግን ነበረበት፡፡ ለዚህ ሁሉ በቦታው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የወጣልን የከተማይቱ ነዋሪዎች የፎቶግራፍ እና የሰው ማስረጃ አለን፡፡
ለጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በግል የቤት (ሕንፃ) ቁጥር ውል ብንገባም ቤቶቹ ላይ ያለውን ለውጥ ለማየት ስንሔድ ግን በሁለተኛ እኛ ሦስተኛ ፎቅ መካከል ባለ ደረጃ የቆርቆሮ አጥር ታጥሮ ማለፍ ክልክል ነው በሚል ተጨባጭ እንቅፋት ገጥሞናል፡፡ ቤቱ የራሳችን ከሆነ መከልከልን ምን አመጣው?
እሱን እንደምንም አልፈን ብንሔድም አስቆሚ አካል ይገጥመናል፡፡ በተለይ በጋዜጣችሁ የኅዳር 2 ቀን 2013 ዓ.ም እትም ጋዜጠኛ ሰሎሞን በየነ ጅምር ሕንፃው ያለበትን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ የገለጸው ሕንፃ ቁጥር 29 ላይ ይህ በስፋት ይታያል፡፡ አካባቢውን በጎበኘበት ወቅት ጋዜጠኛችሁን የት ነው? ምንድነው? ብሎ ያስቆመው አካል ይኑር አይኑር ባናውቅም እኛን የጋራ መኖሪያ ሕንፃ/ቤት/ ባለቤቶች የተባልን ዜጎችን ግን በተደጋጋሚ አስቁመውናል፡፡ ከነዚህም አንዱ ጥቅምት መጨረሻ ላይ (ጋዜጠኛ ሰሎሞን አካባቢው ከጎበኘ በኋላ) እስቲ ለውጥ ካለ እንይ ብለን ሰባት የሕንፃው ባለቤቶች ሔድን፡፡
የሕንፃ ተቋራጩ እህት የሆነች ግለሰብ ማየት አትችሉም ሕንፃው የኔ ነው አለችን፡፡ እንግዲህ የሕንፃው ባለቤት እኛ እንሁን ቤቶች ኮርፖሬሽን ይሁን፣ ሕገወጥ ሠፋሪዎቹ ይሁኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይሁን፣ ሕንፃ ተቋራጩ… አልለየም እንደማለት ነው፡፡ ባለቤት የሌለው ደግሞ መባከኑ አይቀርም፡፡
መጎብኘት አትችሉም ያለችን ግለሰብ እንደምንችልና በራሳችን ቤት ሕገወጥ ካልሽን ያንቺን ሕጋዊነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ አምጪ ለእኛ ሕገወጥነት ፖሊስ ጥሪ አልናት፡፡ ይህን ባለማድረጓ የሥራ እንቅስቃሴ ካለመኖሩ የተነሳ ኦና የሚመስለውን ሕንፃ አይተን ወጥተናል፡፡ ይህ በሰባታችን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጎረቤቶቻችን ላይም እየተፈጸመ ነው፡፡ ተመሳሳይ የአጨራረስ ችግር ባለባቸው ሕንፃዎችም ይንጸባረቃል፡፡
የሥራ እንቅስቃሴ አለመኖሩን የነገርናቸው፣ የተሠሩትም ጥራት እንደሌላቸው የገለጽንላቸው እና ጋዜጠኛችሁ በኅዳር 2ቱ ዘገባ በሥም የጠቀሳቸው የቦሌ ቡልቡላ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት የሥራ ኃላፊ «እናንተ ስለ ጥራት መናገር አትችሉም፡፡ ጥራት የለውም ትላላችሁ፡፡ ሰው ቆንጆ የሚባለው ምን ሲያሟላ ነው» ብለው ከርእሱ ጋር ያልተያያዘ ነገር በመናገር ያለ ምላሽ ሸኝተውናል፡፡
እኝህኑ የሥራ ኃላፊ አናግረን ምላሽ ስናጣ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 12 መሠረት መረጃ ለመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ብናስታውሳቸውም አለቆቼን ጠይቁ ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡
የሕንፃ ግንባታ አማካሪ ድርጅቱ (ለሕንፃ 29) የሳይት ባለሙያዎች ግን በትህትና ቢያስተናግዱንም እኛ ሳንጠቁማቸው ማስፈረስ የነበረባቸውን ጥራት የሌለው ግንባታ እኛ ከጠቆምናቸው በኋላም አላስፈረሱም፡፡
ይህ በአሰሪው በቤቶች ኮርፖሬሽን የ40/60 ቤቶች አስገንቢው የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ በሕንፃ ተቋራጩ እና በአማካሪው ድርጅት የሳይት ሠራተኞች እና ኃላፊዎች መካከል ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሦስት ጎናዊ ያልተገባ ግንኙነት ይኖር ይሆን በሚል ጥርጣሬ ውስጥ ከቶናል። በዚያ ላይ ዕጣ ያልወጣባቸው አንደኛ እና ሁለተኛ ፎቆች ላይ የሚኖሩ ሕጋዊ ያልሆኑ ነዋሪዎች በአግባቡ የተሰናዳ መጸዳጃ ባለመኖሩ ይመስላል በየፎቁ ስርቻ ለመጸዳዳታቸው ምልክት እየተዉ የሚሔዱት፡፡
ስለዚህ ቀዳሚውን ዘገባ ለሠራው አቶ ሰሎሞን በየነ ያለን አክብሮት እና ምስጋና እንዳለ ሆኖ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራ ጋዜጠኞች ይበልጥ ጉዳዩን ቢመረምሩት ለሌሎች የሕዝብ ሮሮዎች ትምህርት ይሠጣሉ ብለን እናምናለን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013