በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
የአለማችን ቁጥር አንዱ ቢሊየነር እና የመጀመሪያው ባለትሪሊዮን ዶላር ካፒታል ለነገሩ አሁን ላይ ወደ 1ነጥብ 5ትሪሊዮን ዶላር ያደገው አማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞ ንብረት የሆነው “ ዋሽንግተን ፓስት “ባለፈው እሁድ፤ “ The pandemic will not end unless every country gets the vaccine “ በሚል ርዕስ እንደ ሁል ጊዜው የፋሪድ ዘካርያን ማለፊያ መጣጥፍ አስነብቧል ። ጭብጡ ጎልቶ እየታየ ያለውን የክትባት ብሔርተኝነት ይሞግታል። ሁሉም ሀገራት ክትባቱን በፍትሐዊነት ካላገኙ በስተቀር የኮቪድ ወረርሽኝን መከላከል አይቻልም። አሜሪካ ፣ እንግሊዝ ፣ እስራኤልና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለዜጎቻቸው ክትባቱን እየሰጡ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የመጀመሪያውን ብልቃጥ ሰጥተው ለሁለተኛው እየተዘጋጁ ነው ።
የክትባቱ መገኘት የተስፋ ጎህ ቢቀድም ለሁሉም በተመሳሳይ ጊዜ ተደራሽ ሊሆን አለመቻሉ ደግሞ ስጋት መደቀኑ አልቀረም ። በዚህ የተነሳም አለማችን ከወረርሽኙ ነጻ የሚሆንበትን ጊዜ አራዝሞታል ። በመሆኑም ቫይረሱ ራሱን እየቀያየረ መስፋፋቱን ይቀጥላል ሲል ፋሪድ ስጋቱን ያጋባል ። ወረርሽኙ እንደ አዲስ ሊያገረሽ ከተሞች ሙሉ በሙሉ መልሰው ሊዘጉ አልያም በርካታ ሰዎች ሊያልቁ ይችላል። መሠረታዊ ችግሩ ክትባቱ እየተሰራጨበት ያለው አግባብ ነው ።
ቅድሚያ መዳረስ ላለበት ሀገራት ሳይሆን ገንዘብ ላላቸው ያደላ ነው ። ባለጠጋ ሀገራት ከሚያስፈልጋቸው በላይ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ብልቃጦች አስቀድመው ከፍለዋል ። ካናዳን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ይላል ፋሪድ ፤ የሚያስፈልጋት የክትባት ብልቃጥ 38 ሚሊዮን ሆኖ እያለ ቅድሚያ የከፈለችበትና ያዘዘችው ግን ከዚህ አምስት እጥፍ 190ሚሊዮን ብልቃጥ ነው። ይሁንና 200ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ናይጀሪያም ሆነች 105ሚሊዮን ያላት ኢትዮጵያ አንዲት ብልቃጥ አላገኙም ። የበለጸጉ ሀገራት ከአለም ሕዝብ ያላቸው ድርሻ 16በመቶ ሲሆን የከዘኑት ክትባት ግን የአቅርቦቱን 60በመቶ መሆኑን በመጥቀስ ፋሪድ ዘካሪያ በመጣጥፉ ይወቅሳል ። ቶማስ ቦሊኪና ቻድ ቦውን ሰሞኑን “ ፎሪን አፊርስ” መጽሔት ላይ ባስነበቡት መጣጥፍ አውስትራሊያና ካናዳ ከአለማችን የቫይረሱ ተጠቂዎች የእነሱ ድርሻ 1በመቶ ቢሆንም በእጃቸው ያስገቡት የክትባት ብልቃጥ ግን ለላቲን አሜሪካና ለካሪቢያን ሀገራት የሚበቃ ነው ።
የሚያሳዝነው ይላል ፋሪድ ዘካርያ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በክትባት ግኝቱ ሒደት በሙከራው የተሳተፉ ቢሆንም ክትባቱን ማግኘት ላይ መድሎዎና መገለል ተፈጽሞባቸዋል ። የዱክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ታዳጊ ሀገራት እስከ 2024 እኤአ ድረስ ክትባቱን ሙሉ በሙሉ አያዳርሱም ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል ። ይህ ማለት ቫይረሱ የመባዣና የመሰራጫ ተጨማሪ ጊዜ ያገኛል ። እስከ 2021 እኤአ መጨረሻ ድረስ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ከአምስቱ አንዱ ብቻ ክትባት እንደሚደርሰው ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ አስታውቀዋል። አክለውም ወደዳችሁም ጠላችሁ ሁላችንም በአንድ ጀልባ ላይ ነን ሲሉ የበለጸጉ ሀገራትን ሸንቆጥ አድርገዋል።
ወረርሽኙ ከጤና ቀውስ በላይ ነው ። የአለማችን ኢኮኖሚ ከ1ነጥብ5 እስከ 9ነጥብ 2 ትርሊዮን ዶላር ያጣል ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ በላዩን የሚያጡት የበለጸጉ ሀገራት መሆናቸውን የአለም ንግድ ምክር ቤት አስታውቋል ። ትንሽ መንደር በሆነችው አለም ኢኮኖሚው በእጅጉ የተሳሰረ ስለሆነ ወረርሽኙ የሚያስከትለው ዳፋ በአንድም በሌላ መልክ ለሁሉም ይተርፋል ። የበለጸጉ ሀገራት ክትባቱ ለድሀ አገራት እንዲደርስ ቢያደርጉ እነሱም እኩል ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር ። ክትባቱ ለድሀ ሀገራት እንዲደርስ አንድ ዶላር ቢያወጡ በምላሹ አምስት ዶላር ያገኛሉ የሚባለው ለዚህ ነው ። መሬት ላይ ያለው ሀቅ ይህ ቢሆንም የክትባት ብሔርተኝነቱ ግን እየተባባሰ ነው ።
የአውሮፓ ሀገራት በአንድ በኩል የፋይዘር ክትባት ወደ ሌሎች ሀገራት እንዳይላክ እገዳ ልንጥል እንችላለን እያሉ ዘወር ብለው ደግሞ አስትራዜኔካ የተሰኘውን ክትባት አምራች ከአውሮፓ ሕብረት ይልቅ ለብሪትን አድልቷል በማለት ለክስ እየተዘጋጁ ነው ። የበለጸጉ ሀገራት ሕዝባቸውን ቅድሚያ የማስከተብ ፍላጎት እንዳላቸው የሚታወቅ ቢሆንም ክትባቱን ሳይከዝኑ በምክንያታዊነትና በሰብዓዊነት ለሁሉም ቢያዳርሱ ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል አስተዋጾ ማበርከት ይችላሉ ።
ቦሊኪና ቦውን ከፍ ብዬ በጠቀስሁት “ ፎሪን አፊርስ”መጽሔት አሜሪካ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከል የተጫወተችውን የመሪነት ሚናና ትብብር አሁን መድገም ትችላለች ሲሉ የማርያም መንገድ ይመራሉ ። 180 ሀገራትን ያቀፈና ለታዳጊ ሀገራት ክትባት ለማዳረስ የሚተጋ ኮቫክስ/COVAX/ የተሰኘ ጥምረት ተመስርቶ እየተንቀሳቀሰ ቢሆን ቀኝ አክራሪው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሪፐብሊካኑ ትራምፕ ጥምረቱን አልቀላቀልም ብሎ አሻፈረኝ በማለቱ ግቡን እንዳይመታ እንቅፋት ቢሆንበትም እሱን የተኩት 46ኛው ዴሞክራት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግን የትራምፕን ውሳኔ ሽረው የጥምረቱ አጋር እንደሚሆኑ ለጥምረቱ አረጋግጠዋል ።
የኮቪድ 19 ክትባት መገኘት የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አምነው በተስፋ በሚጠባበቁ ወገኖች ላይ በህልምም ሆነ በእውን ያልጠበቁት ስጋት ከፊት ተደቅኖባቸዋል። ወረርሽኙን ለመከላከልም ሆነ ለመቆጣጠር ተቀናጅቶና ተናቦ መስራት ወሳኝ ሆኖ እያለ ፤ አንዳንድ መሪዎች፣” ቅድሚያ ለሀገሬ ! “ በማለት መከዘን መጀመራቸው የክትባት ብሔርተኝነትን ጎንቁሏል ። የክትባት ብሔርተኝነት በመሰረቱ ኢሞራላዊ ከመሆኑ ባሻገር ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው ። የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በአለማቀፍ ደረጃ መከላከልና መቆጣጠር ሳይቻል ፤ በዘመነ ሉላዊነት አለም ትንሽ መንደር ሆና ሳለ አንድ ሀገር ለብቻው ክትባት መከዘንና መከተብ ስለቻለ በዘላቂነት ነጻ ሊሆን አይችልም ።
ከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች ባሉባቸው እንደ አፍሪካ ፣ ላቲን አሜሪካ ፣ ብራዚል ፣ ሕንድ ፣ ራሽያ ፣ ወዘተረፈ ባሉ ሀገራት ወረርሽኙን መቆጣጠር ካልተቻለ አንድ ሀገር ክትባቱን በቅድሚያና ለብቻው ስለተጠቀመ ብቻ ሊድን አይችልም ። ወረርሽኙ እንደገና ማገርሸቱ አይቀርምና። ኮቪድ 19 አለማቀፍ ንግዱን እና የሎጅስቲክሱን ሰንሰለት ስለሚያስተጓጉለው በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለውን ጫናም ከባድ እንደሚሆን ከፍ ብሎ ለመጥቀስ ተሞክሯል ። ክትባቱን የማሰራጨት ጉዳይ በአለማቀፍ ተቋማት ፊታውራሪነት ሊመራ ይገባል ሲሉ የሀርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው ዘጋቢዎች ሬቤካ ዌንትትራውብ፣ አሳፍ ቢቶናንድና ማርክ ሮዝ ሲወተውቱ ቢባጁም እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው ። አንዳንድ ሀገራት ወረርሽኙን ለመከላከል ከፍትሐዊና የጋራ ተጠቃሚነት ይልቅ የተናጠል መንገድን መርጠዋል ።
የአውሮፓ ሀገራት ፣ የቢልና የሚሊንዳ ተራድኦ እና የዌልካም መረዳጃ በአንድ ላይ ለኮቪድ 19 ቁሳቁስ ድጋፍና ለክትባት Access to Covid-19 Tools (ACT) ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ መድበው እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም አሜሪካ ፣ ራሽያና ሕንድ የዚህ የትብብር ማዕቀፍ አባል መሆን አልፈለጉም ። ምክንያቱም የትብብሩ አካል ከሆኑ ከሚያራምዱት የክትባት ብሔርተኝነት አቋም ጋር ይቃረናል ። የሳኖፊ የመድሀኒት ፋብሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓል ሀድሰን ፣ “ የአሜሪካ ባዮሜዲካል ከፍተኛ ምርምር እና የልማት ባለስልጣን ( ቢአርዲኤ) ፤ አሜሪካ ከኩባንያቸው ጋር ባለፈው የካቲት በገባችው የኢንቨስትመንት ስምምነት መሰረት ክትባቱን ቀድማ ማዘዝ ትችላለች ። “ በማለት የአሜሪካንን የክትባት ብሔርተኝነት ለማስፈጸም ቃጥቷቸው ነበር ። የአውሮፓ ፕሮፌሰሮች ደርሰው ባያስቆሟቸው ኑሮ ። ሆኖም እነዚሁ ፕሮፌሰሮችም ሆነ ሌሎች አካላት ፤ የህንድንና የእንግሊዝን የክትባት ብሔርተኝነት ማስቆም የተሳናቸው ይመስላል። ሴራም የተሰኘው በአለማችን ትልቁ የሕንድ ክትባት አምራች ተቋም ፤ “ ክትባቱ ለውጭ ገበያ ከመዋሉ በፊት ለሕንድ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ፤ “ ዋና ስራ አስፈጻሚው እቅጩን ነግረውናል ። አስትራዜኔካ ይፋ እንዳደረገው የእንግሊዝ እና የአሜሪካ መንግስታት እንደ ቅደም ተከተላቸው 79 ሚሊዮን እና 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ለክትባት አምራቹ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ቀድመው ኢንቨስት ስለአደረጉ ካለፈው ወር ጀምሮ 30 ሚሊዮን ብልቃጥ ለእንግሊዝ ፤ 300 ሚሊዮን ደግሞ ለአሜሪካ ቅድሚያ በመስጠት ማቅረብ ጀምሯል ።
በቅርብ አመታት እንኳ የበለጸጉ ሀገራት በሚያራምዱት ብሔርተኛ አቋም የተነሳ ድሀ ሀገራት ላይ ተመሳሳይ ጫና ሲያደርጉ ይህ ሁለተኛው መሆኑ ነው ። እአአ በ2009 ኤች1ኤን1 ወይም ስዋይን ፍሉ የተባለው ወረርሽኝ በአለም 284ሺህ ሰው ገሏል ። የሚያሳዝነው ወረርሽኙ እንደተከሰተ በሰባት ወር ክትባት ተገኝቶለት ነበር ። የበለጸጉ ሀገራት እንደ ዛሬው ክትባቱ በታላላቅ የመድሀኒት ፋብሪካዎቻቸው እንዲመረት በማድረግ ራሳቸውን አስቀድመዋል ። አሜሪካ ለድሀ ሀገራት ክትባቱ እንዲደርስ ድጋፍ አደርጋለሁ ብትልም በተግባር ግን ራሷን በማስቀደሟ ያልታደሉት ድሀ ሀገራት ዜጎች እንደ ቅጠል እንዲረግፉ ተፈረደባቸው ። የክትባቱ ስርጭት በወረርሽኙ ስፋት ልክ መሆን ሲገባው በገቢ መጠን መሆኑ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነስቶ ነበር። የሚያሳፍረው የበለጸጉ ሀገራት ዛሬም የትናንቱን ስግብግብነት ፣ ራስ ወዳድነትና ብሔርተኝነትን መድገማቸው ነው ።
ፖለቲከኞች ሳይሆኑ የተላላፊ በሽታ ባለሙያዎች፣ የቫይረስ አጥኝዎች እና የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዝ ሳይንሳዊ ስልት እንዲ ቀይሱ የሚወተውተው የክትባት ብሔርተኝነት በማስቀረት ለወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑ ሀገራትን ለመከላከል በማለም ነው ። ውጤታማ የማይሆኑ የተናጠልና ብሔርተኛ አካሄዶችን ለማስቀረት የተማከለና ተቀባይነት ያለው የአመራር ስርዓት መዘርጋት ፍትሐዊ የካፒታል ፣ የመረጃና የግብዓት ፍሰት እንዲኖር ያስችላል ። ረጂ አካላት ስራ ላይ የዋሉትን የኮቪድ 19 ክትባት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሀገራት ተደራሽ እንዲሆን ከአሁኑ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸው ተስፋ የሚጣልበት ነው። እአአ በ2007 የቤልና የሜሊንዳ መረዳጃ እንዲሁም አምስት ሀገራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማሰባሰብ የሳንባ ምች መከላከያ ክትባት በብዛት እንዲመረት በማድረግ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ሀገራት እንዲደርስ ማድረጋቸው አይዘነጋም። ዛሬም ተመሳሳይ ድጋፍንና ቅንጅታዊ አሰራርን ይጠይቃል።
እንደ መቋጫ
የአለም የጤና ድርጅት የክትባት ብሔርተኝነት ኮቪድ 19ን የመከላከል ጥረቱን እያስተጓጎለው መሆኑን ይገልጻል። በየትኛውም ሀገር ያለ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋቱ ለሁሉም ነውና ። ማንኛውም ክትባት ለሁሉም መዳረስ ያለበት ለዚህ ነው። የበለጸጉ ሀገራትም ይህን ሰብዓዊ መርህ ሊያከብሩ ይገባል። አለም ፈጥኖ ከወረርሽኙ ማገገም እንዲችል ፤ ክትባቱን በፍትሐዊነት መጠቀም ያሻል ። ኢኮኖሚው እጅግ የተሳሰረና አለማቀፋዊ ስለሆነ አንድ ሀገር ክትባቱን ቀድሞና ለብቻ በመጠቀሙ ከወረርሽኙ በዘላቂነት ሊያገግም አይችልም። ድርጅቱ በማከልም የትም ያለ አደገኛ የመተንፈሻ አካል በሽታ በማንኛውም ቦታ ለሚኖር የሰው ልጅ የጤና ስጋት ነው ። የበለጸጉ ሀገራት ወረርሽኙን የመከላከልም ሆነ ክትባት የማዳረሱን ጥረት ባገዙ ቁጥር ሊከተል የሚችለውን ዳፋ መቀነስ ይቻላል ። ይህ ምፅዋት አይደለም ። ድጋፍ የሚያደርጉት ለራሳቸው ብለው ነውና ። የቀረው አለም ፈጥኖ ሲያገግም እነሱም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ስለሚያገኙ እንጂ ። የተለያየን ብንሆንም ሁላችንም በአንድ ፈለክ ወይም ፕላኔት የምንኖር የሰው ዘር ስለሆነ ደህንነታችን እርስ በርሳችን የሚደጋገፍ ነው። ሁሉም ከኮሮና ቫይረስ ነጻ እስካልሆነ ድረስ አንድ ሀገር ለብቻው ነጻ ሊሆን አይችልም ።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያን ከዚህ ወረርሽኝ ይጠብቅ !
አሜን ።
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013