አዲሱ ገረመው
ጤና ይስጥልኝ! እንደምን ሰነበቱልኝ? ዛሬ ከመገናኛ ፒያሳ በትምህርት ሚኒስቴር አጥር ሥር እያለፍን እናውራ። ለአንድ ሀገር እድገትና ብልጽግና የተማረ የሰው ሀይል ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የመምህራን ሚና የጎላ ነው።
መምህራን ከሚያበረክቱት አስተዋጽዖና ድካም አንጻር የሚገባቸውን ያህል መጠቀምም አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። በቅርቡ ለአዲስ አበባ መምህራን ይከፈል የነበረውን የቤት አበል ከብር 850 ወደ ብር 3ሺ እንዲሻሻል መውሰኑም የዚሁ ማሳያ ነው።
በእርግጥ በአሁኑ ሰአት የገጠር እና የከተማ መምህር የሚባል የለም በሁሉም የኑሮ ውድነት አለ። እውን ግን ሁሉም መምህራን ትውልድን በመልካም ከመቅረጽና የእውቀት ባለቤት ከማድረግ አንጻር ሚናቸውን በሚገባ እየተወጡ ነውን? ነገሩ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይቆየን።
ጎበዝ የመምህራን ጉዳይ ከጤፍ መወደድ በላይ እያሳሰበኝ ነው። መምህር ማነው? የሚለው ጥያቄ የማይረባ ጥያቄ ሊመስል ይችላል። ጥያቄው ግን ተገቢ ይመስለኛል። መምህራን በአንድ የትውልድ ማዕቀፍ የቀለም ቡርሽ ይዘው በትውልድ ውጥር ሸራ ላይ አሻራቸውን ሊያሳርፉ የሚታትሩ ናቸው።
በተለያዩ ጊዜ ከሚያጋጥሙኝ የመምህራን ግምገማ መድረኮች እንዲሁም ምሁራን በተለያዩ አውዶች ከሚሰነዝሩት አስተያየቶች ብዙ ነገሮችን እንዳስተዋልኩት ይህ ብያኔ በወረቀት ላይ የቀረ ይመስላል። አንዳንዱ መምህር ኃላፊነቱ የሚመስለው የራሱን ሰዓት ጠብቆ ክፍል ውስጥ መግባት እንጂ፤ የተማሪዎቹ መምጣት አለመምጣት፣ የአስተማራቸውን ትምህርት መረዳት አለመረዳት፣ የአእምሮአቸውም መልማት አለመልማት ቅንጣት አያስጨንቀውም።
እነዚህ መምህራን ነገን የማያዩ ናቸው። ሁልጊዜም የሚያስቡት የዛሬን ብቻ ነው። አስተሳሰባቸው ከእጅ ወደ አፍ (የዕለቱን ብቻ የሚያስቡ) የሆኑ መምህራን እንደ አባይ በሬ ቆመውም ሆነ ተቀምጠው የሚያሰሉት ትምህርት ተዘግቶ የሚያርፉበትን ቀን ነው።
አጼው የወደቀበት፣ ደርግ የገባበት፣ መንጌ የወጣበት፣ መሌ የሞተበት ወዘተ እየተባለ ሙሉው የትምህርት ዘመን በበአል ሰበብ ቢዘጋ ደስታው ወደር የላቸውም።
ክፍል ውስጥ የገቡት መምህራንም ቢሆኑ እንኳን መብራት ሄደ፣ ኮምፒዩተሬ አይሠራም፣ ፕሮጀክተሩ ተበላሸ ወዘተ. የሚል ተልካሻ ምክንያት ከሚያስተምሩበት ይልቅ የማያስተምሩበት ጊዜ ይበዛል። ክፍል ውስጥ ያልከረመን ተማሪ የሚፈትኑ፣ ያልተፈተነን ደግሞ ወደ ቀጣይ ክፍል የሚያሳልፉ፣ ያልተማሩትን አንድ ላይ ሰብስበው የሚያስመርቁ መምህራን ትውልድን የሚገድሉ እንጂ አገር ተረካቢ ትውልድን የሚያፈሩ አይደሉም።
ጀግናና እውቀት ተኮር መምህራን ቢበዙልን ተማሪዎች ማለፍ መውደቅ ከሚል ነፍስና ሥጋን ከሚለይ ስጋት ነጻ በሆኑ ነበር። ዳሩ ግን ነገሩ ወዲህ ነው። መኮፈሱ በማን አለብኝነት መንጠራራቱ፣ ጥቅምን ብቻ ማሳደዱ ለተማሪዎች ግድ አለማለቱ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል።
በእርግጥ የልጆቹ በደንብ አለመማር፣ ትምህርቱን ሳይጨርሱ ፈተና ላይ መቀመጣቸው የሚያሳስበው መምህር አለ። እንዲህ አይነቱ መምህር ደግሞ ዘመን የማይሽረውን አሻራ ለትውልድ እያስተላለፈ ነው።
እነዚህን መሰል መምህራን ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ከሚል ስግብግብነት ነጻ ስለሚሆኑ ያላቸውን ሁሉ ለተማሪዎቻቸው ያለንፍገት በለጋስነት ይሰጣሉ። የእነርሱ ማነስ (በምድራዊ ኮልኮሌ ማለቴ ነው) ሳይሆን የልጆቻቸው ማደግ ያስደስታቸዋል።
በመልካም ስብዕና የተቃኙ መምህራን መምህርነታቸው የቀለም (ብቻ) ስላልሆነ እኔ የምናገረውን እንጂ የምሠራውን አትመልከቱ እያሉ ተማሪዎቻቸውን አይሸነግሉም። መምህርነታቸው ከቀለም አልፎ የሕይወትም ስለሆነ ለእያንዳንዱ ተግባራቸው ጠንቃቃዎች ናቸው።
ሆድ አደርና ሁልጊዜ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚያስብ መምህር ግን እርሱ ያስተማረው ተማሪ እንዲበልጠው ስለማይፈቅድ በሥርዓት አያስተምርም ፤ ቢያስተምር እንኳ ለትውልዱ የሚያስተምረው ልማትን ሳይሆን ጥፋትን ነው።
እንዲህ አይነት መምህራን ዕውቀታቸውን ሌሎች አካላት ከአወቁባቸው የእነርሱ ዕውቀት እንደ ቡዳ መድኃኒት የሚሻር ስለሚመስላቸው ዕውቀታቸውን (ካላቸው ማለቴ ነው) ይዘውት ወደ መቃብር መውረድን ይመርጣሉ።
ዕውቀታቸውን እንደ ሐበሻ መድኃኒት ሁልጊዜ ምሥጢር አድርገው መያዝ ይቀናቸዋል። እና እነዚህ ናቸው እንግዲህ ከሚለፉ መምህራን እኩል 3ሺህ ብር የቤት አበል እንዲከፈላቸው የተደረጉት። ግድ የለም ትምህርት ቢሮው ባያያችሁ ፈጣሪ ያያችኋል።
አንዳንድ መምህራን ተማሪዎችን የሚመዝኑት በእውቀት ሳይሆን በነጥብ ብቻ ነው። ጎበዝ መምህር እኮ የአገርን ገጽታ መለወጥና ተማሪዎች በእውቀታቸውም በምግባርም እንዲጎለብቱ ማድረግ አለበት። ለነገሩ አሁን ላይ የተገላቢጦሽ የሆነ ውጤት እያየን ነው።
የክብር ዶክተሩም ሀኪሙም እኩል ክሊኒክ ከፍተው ይሰሩ የለ። ይህን ያመጣው የትምህርቱ ውጤት አይደለምን? በስፖርት ተመርቆ እንግሊዝኛ አስተማሪ የሚሆነስ ቁጥሩ ትንሽ መሰላችሁ።
ክፍሉ ውስጥ ገብቶ “ኢዝ…ዎዝ…ዚስ” እያለ ጭንቅ ብሎት ተማሪውን የሚያስጨንቅ መምህር የለም ነው የምትሉት? “ዛሬ ስለ ቨርብ ነው የምንማረው” ብሎ እንግሊዝኛን በአማርኛ ለማስረዳት የሚለፋ መምህር ከኢትዮጵያ ወዲያ ከቶ የት ሊገኝ፤ ይሁን ግድ የለም የቤት አበሉም ይጨመርለት፤ ግና ፍቅረ ነዋይነት እንደሚያሳስባቸው ሁሉ የተማሪዎች እውቀት መገብየትና የአገር እጣ ፈንታም ጉዳያቸው ሊሆን ይገባል።
ሁል ጊዜ ካልተጠቀምኩ ከቶውንም ምን አገባኝ ሳይሆን ልክ እንደወታደር እየተጎዱ እውቀትን ሳይሰስቱ መስጠት የክብር ኒሻን ያሰጣል።
በእኔ እምነት ሁሉም ሙያ ከፍቅረ ነዋይ በሽታ ነጻ በሆነ ሙያተኛ መፈጸም ቢኖርበትም ቅሉ በተለይ መምህርነት ደግሞ ከሁሉም የበለጠ ትኩረት ይሻል። ይህንን ሁሉ የምለው አብረን በምንኖርባት ኢትዮጵያችን ላይ ያለው የኑሮ ውድነት ጠፍቶኝ እንዳይመስልህ። መፍትሄውን ለባለ ድርሻው ሰጥቶ የሚፈለገውን መስራት ከባለቤቱ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013