ሰላማዊት ውቤ
በአዲስ አበባ ከተማ በድለላ ሥራ የተሰማራው ሰው ቁጥር በርክቷል።በየጊዜው ስራ ፍለጋ ከገጠር ወደ መዲናዋ ከሚፈልሰው ወጣት ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው በድለላ ሥራ የሚሰማራ ነው ።
ከነዚህ ውስጥ ሊስትሮ፣ ጫኝ አውራጅና ሌሎች ቀለል ያሉ ሥራዎች እየሰራ የድለላ ሥራን ደርበው የሚሰሩም ብዙዎች ናቸው። ከእነዚህም አልፈው በመንግስትና በግል ስራ ውስጥ ያሉ ሰራተኞችም ይሄንኑ የድላለ ስራ ተደራቢ ስራ አድርገውታል።
ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በድላለ ስራ ላይ ከተሰማሩት መካከል አብዛኞቹ ህጋዊ ፍቃድ ያላቸው አይደሉም።ሥራውን የሚሠሩት ተደብቀውና እየተሸሎከለኩ ነው።
በዚህ ምክንያት በሕብረተሰቡ ዘንድ በከተማዋ በስፋት እንዳሉ ቢታወቅም ትክክለኛው ቁጥራቸው ግን አይታወቅም። ነገር ግን በግምት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መሆናቸውን ለማረገጋጥ በየትኛው የመዲናዋ ጫፍ በሚካሄዱ የንግድ ስፍራዎች በተለይ የቤት፣የመኪና፣የዕቃ መሸጫ ስፍራዎች፤ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እንዲሁም ሥራና ሠራተኛ አገናኛለን በሙሉ አካበቢዎች ብቅ ብሎ ማረጋገጥ ይቻላል።
ደላሎቹ በከተማዋ ነዋሪ ላይ የሚያሳድሩት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን በነዋሪው ላይ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መገንዘብ ይቻላል፡፡እንደ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ በተለይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር በቤት ሰራተኝነት ለመቀጠር ከገጠር የሚፈልሱት ሴት ወጣቶች የደላላ ዋንኞቹ ሰለባዎች ናቸው።ወጣት ሴቶቹ ህጋዊ በሆኑት ሳይሆን በህገወጥ ደላሎች ነው የሚጠለፉት፡፡
አንዳንድ ጊዜ በህጋዊ የሥራና ሠራተኛ አገናኝም ለችግር የሚጋለጡበት ሁኔታ አለ።ሆኖም የድለላ ሥራ በጎም መጥፎም ጎን አለው። አስተያየታቸውን የሰጡን የመዲናዋ ነዋሪዎችም ከላይ የተነሱትን ሀሳቦቹ ተጋርተዋቸዋል።
የግንባታ ክትትል ባለሙያ ፍሰሀ ዘርዓ ብሩክ በዚህ ይስማማሉ። ‹‹ደላላ በከተማው ላይ በተለያዩ ቦታዎች በብዛት ይታያል፤ ሆኖም ግን የድለላ ስራ አሉታዊም አወንታዊ ጎን አለው››ይላሉ።እሳቸው ሥራቸው በሚሰሩበትና ቁልፍ ርክብክብና ውል መዋዋል በሚፈፀምበት ወቅት ደላሎች በስፋት እንደሚያስተውሉም ይገልፃሉ።በዚህ ምክንያት የቤት ዕድለኛ ባላሰበው ወይም ደግሞ እነሱ በተመኑለት ዋጋ ሀብቱን ሊያስተላልፍ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል።
‹‹የጋራ መኖሪያ ቤት ደርሶኝ ውል ለመዋዋል ሄጄ በርካታ የደላላ አድራሻ ካርድ ተቀብያለሁ›› ያሉን ወይዘሮ ጥበብ በየነ እንዳሉን በደላሎች ወከባና ግርግር በጉያቸው የነበረ ቦርሳ ወድቆ ጠፍቶባቸዋል።
ሳያስቡትና ሳይፈልጉ በደላሎች ግፊት ቤታቸውን ለመሸጥ የተገደዱና በኋላ ቁጭትና ችግር ላይ የወደቁ ሰዎች መኖራቸውን አስተውለዋል። ወይዘሮዋ ቤት ሲያሻሽጡ ያይዋቸውን ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ሆነው ያገኙበት አጋጣሚ በመኖሩ ደላሎቹ የማይገቡበት የስራ ዘርፍ የለም ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ 22 አካባቢ ነዋሪ የሆኑትና ሥራና ሠራተኛ አገናኝ እናት ኤጄንሲ ውስጥ አገናኝ ሆነው የሚሰሩት አቶ አንዱ ዓለም የኔነህ እንዳጫወቱኝ ኤጄንሲው ወደ ሥራ የገባው በ2008 ዓ.ም ቢሆንም እሳቸው በስራው ላይ የቆዩት ለአራት ወራት ነው፡፡
ስለኤጀንሲው አገልግሎት እንደገለፁልን በሚፈጥረው የሥራ ዕድል በሀገሪቱ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር እጅግ ይቀንሳል።እርሳቸው በአብዛኛው የሚያውቋቸው ሥራ ፈላጊዎች ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ሴቶች እንደሆኑና በደላሎች እንደሚዋከቡ ተናግረዋል፡፡አልፎ ተርፎም ለተለያየ ችግር ይጋለጣሉ። አብዛኞቹም ሥራ ፈላጎዎች ከ30 አመት ዕድሜ በላይ የሆኑና ለረጅም ጊዜ የሥራ ዕድል አጥተው የቆዩና እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው።
ምንም ዓይነት የሥራ ዕድል ሳያገኙ ስምንተኛ ክፍል ጨርሰው ለረጅም ጊዜ የተቀመጡም የገኙበታል።ለነዚህ ዜጎች የሥራ ዕድል መክፈት እንደ ትልቅ ቁም ነገር ነው የሚቆጥሩት።እነዚህን ዜጎች መርዳታቸው የህሊና እርካታ ይሰጣቸዋል፡፡በከተማዋ ውስጥ ባሉ ህገወጥ ደላሎች ሀሳባቸውን ከዳር ሳያደርሱ ለችግር የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት አስተያየት ሰጭው ሥራ ፈላጊዎቹ ለችግር የሚዳረጉት ህጋዊ ኤጄንሲዎች በነፃ እንደሚልኳቸው ሲነግሯቸው ስለማያምኑ ገንዘብ ከፍለው ለመሄድ በሚሞክሩበት ወቅት
እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ከጎጃም በረንዳ መጥታ በካዛንቺስ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያገኘናት ወጣት ምህረት ተክሊላ ሀሳቡን ትጋራዋለች።በድለላ ሥራ ላይ የተሰማሩት አብዛኞቹ ወንዶች መሆናቸው ችግሩን እንዳባባሰው ትናገራለች፡፡እናታቸው፣እህታቸው ሴት መሆኗን እንደዘነጉ ትናገራለች፡፡ሴቶች ከሚደርስባቸው ጫና በማገዝ ተባባሪ መሆን ሲገባቸው በደል ማድረሳቸው አግባብ እንዳልሆነ በምሬት ተናግራለች፡፡ደላሎች ህጋዊ ሆነው እንዲሰሩም መደረግ እንዳለበት መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡
ህገወጥ ደላሎች ከገጠር ወደ አዲስ አበባ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሥራ የሚመጡ ሴቶች ላይ የሚፈጥሩት ችግር እንደሚበረታ የገለፁልን ደግሞ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ኤጄንሲዎች ፈቃድ መስጫ ቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ይጥና ናቸው ።
አቶ እሸቱ አንዳሉት፤ ተቋማቸው የሚገኘው ከአዲስ አበባም ብዙ ሁከትና ግርግር በበዛበት ካዛንቺስ አካበቢ ነው። ታድያ ከአንድ የሀገሪቱ ገጠር አካባቢ የመጣች ወጣት ለውጪ ሥራ በኤጄንሲ ለመቀጠር ወደ ተቋሙ ታመራለች።
ወደ ተቋሙ ሳትገባ ደላላ ይጠልፋታል።በኤጄንሲ ተቀጥሮ መሄድ ረጅም ጊዜ እንደሚፈጅና እሱ በቀላሉ ዱባይ እንደሚልካት አታሎና አሳምኖ 15 ሺ ብሯን ይወስዳል።ውሸት መሆኑን ስትደርስበት በሰው ጥቆማ ወደ ቢሯቸው ዘልቃ የደረሰባትን ችግር ትናገራለች።
በከተማዋ ባለ ህገወጥ ደላላ እንደዚህ ዓይነት ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ተቋሙ መጥተው አቤት የሚሉ ብዙ ከገጠር የሚመጡ ወጣት ሴቶች አሉ። በነዚህ ደላላዎች አንዳንዴ በህጋዊ መንገድ ሥራና ሠራተኛን በሚያገናኙ ኤጄንሲዎችም የወሲብ ጥቃት ይጋለጣሉ፡፡ተገደው በሚፈጸምባቸው ጥቃትም ሳይወዱ በግድ የልጅ እናት ይሆናሉ፡፡እንዲህ ላለ ችግር የተጋለጡትም ጥቂት የሚባሉ አለመሆናቸውን ይናገራሉ።
በህገወጥ መንገድ ከሀገር ከወጡ በኋላም የኢትዮጵያ ኢምባሲ ስለማያውቃቸው ብዙ ችግር ይደርስባቸዋል። ደላሎቹ ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙት በህገወጥ በመሆኑ ቶሎ ደርሶ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ጊዜ እንደሚወስድ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡በህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ደላሎች በቁጥር ለማወቅም አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ችግሩንም የሚያውቁት ፖሊስ ወደ ችግር መኖሩን ሲያሳውቃቸው ብቻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ተቋማቸው በየጊዜው የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ችግሩን ለማስተካከል ጥረት ያደርጋል፡፡የጉዞ ሰነድም በአካባቢያቸው እንዲጨርሱም ይመክራል፡፡ችግሩን ለመቅረፍ ከፖሊስ፣ከፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት ሥራዎችን ይሰራል፡፡በስልጠና ወቅትም ስለነዚሁ ደላሎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ይሁንና የድለላ ሥራ ህጋዊ ሆኖ ለሚሰራ ሰው ጥቅሙ እንደሚያመዝን ይናገራሉ።እርሳቸው እንደሚሉት በደፈናው አጭበርባሪ ብሎ መፈረጀም አይገባም።ምክንያቱም ደላሎች ለዜጎች ሥራ ፈጣሪዎች ናቸው።ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ያስገባሉ።ግብር ከፋዮች ናቸው። የሚልኳቸው ሴቶች የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ይዘው ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ።
በአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ጉዳይ ቢሮ የሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪት ቡድን አስተባባሪ አቶ በላይ ተሰማ በዚሁ ጉዳይ ላይ እንደገለፁልን ቢሮው በሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪት ውስጥ ሥራና ሠራተኛ የሚያገናኙ ድርጅቶች የሚላቸው በሁለት ይከፈላሉ። አንደኞቹ ከሦስተኛ ወገን ተቀብለው ሥራን የሚሠሩ ሠራተኞችን ቀጥረው የሚያስተዳድሩ አካላት ናቸው።
ሁለተኞቹ ደግሞ አገናኝተው የሚወጡ ወይም በዘልማድ ቢሮውም ሆነ ሕብረተሰቡ ደላላዎች ብሎ የሚጠራቸው ሲሆኑ የሁሉም ቁጥር 800 ነው። ከነዚህ መካከል 325ቱ ለተቋማት የጥበቃ ፣የፅዳት አገልግሎት የሚሠጡና ሥራና ሠራተኛ የሚያገናኙ ድርጅቶች ናቸው።እነዚህ በቢሮው ስር ተመዝግበውና ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። በከተማዋ ላይ ግርግርና ችግር ሲፈጥሩ የሚታዩት ህገወጥ ደላሎች ናቸው።በተለይ በከተማዋ ውስጥ ባሉ በሀገር ውስጥ ሥራ ፈላጊ ወጣት
ሴቶች ችግር እንደሚያደርሱ ይሰማል። ከዚህ ቀደምም በህገወጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች ነበሩ።በእርግጥ አሁን ላይ ቁጥራቸው ለመጨመሩ ማስረጃ የላቸውም።ሆኖም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ በተሰጠው አዋጅ መሰረት እነዚህ አካላት የብቃት ማረጋገጫ ወስደውና ፈቃድ አግኝተው መሥራት እንዳለባቸው ያምናሉ።
እንደ አቶ በላይ ማብራሪያ ብቃት ማረጋገጫውን የሚሰጠው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የፌዴራል ፖሊስ ነው።ከዚያ ውጪ ጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ኮሚሽንና እንዲሁም በሕብረት ሥራ ማህበር በመደራጀት ወደ ሥራ የገቡ ይገኛሉ፡፡እነዚህም በተለያየ መልኩ ሠራተኛ ላይ የተለያዩ በደሎች የምያደረሱበት ሁኔታ አለ ።
በተለይ ከፍተኛ የሥራ ጫና የደረሰባቸው ሠራተኞች አጋጥመዋቸዋል።ይሄን ችግር ለመፍታት በከተማ ደረጃ የተዋቀረ ግብረ ኃይል ሥራ ጀምሯል።ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የበላይ ሰብሳቢ ነው።ከፌዴራል ፖሊስና ከከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ፣ከንግድ ቢሮ፣ከሠላምና ፀጥታ፣ከአቃቢ ሕግ ጋር በጋራ በመሆን እየተሠራ ይገኛል።ሥራው በ325 ድርጅቶች እየተከናወነ ሲሆን፣ከእነዚህ ውስጥ ደረጃውን ጠብቀው የሚሄዱ ድርጅቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሁኔት ተመቻችቷል።
ህገወጥ ድርጅቶችም የአሠራር ስርዓታቸውን አስተካክለው ወደ ህጋዊ ማዕቀፍ የሚገቡበት ስርዓት ተዘርግቷል። በህግ የሚጠየቁም ሲያገጥሙ በፍትሀ ብሄር በወንጀል የሚጠየቁበት የአሰራር ስርዓት ውስጥ ተገብቶ እየተሰራ ይገኛል።የአሰራሩ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ጥር 30 ለከተማውና ለቢሮው ይቀርባል።
ከጥር 30ቀን 2013 በኋላም ተቀምሮ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከሚመለከተው አካል ጋር የውሳኔ ሀሳብ ቀርቦ በውሳኔው መሰረት ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል። ይሄን ጊዜም ገቢ ውጪውም ሆነ ነዋሪውና ሥራ ፈላጊው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በህገወጥ ደላሎች የሚደርስበት ችግር ይቀረፋል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013