በሄኖክ ጥበቡ
መገናኛ እንደለመደችው የሥራ፣ የሌብነት፣ የልመናና የትራፊክ ግርግሯን በጠዋቱ ጀምራለች። እኔም የዘወትር ግርግር የመጥላት ምሬቴን አምቄ ያቺን የምወዳትን ልጅ ሞልቃቄን ከኋላ እየተከተልኩ፤ ‹‹አቤት ቁመና፤ ወየው ደም ግባት፤ አይ አረማመድ›› እላለሁ በውስጤ።
ድንገት የሆነ አካል ጉዳተኛ ወጣት መንገድ ዳር ተቀምጦ ‹‹እጅ የለኝ እግር የለኝ። ወገን እርዱኝ። እህቴ ስለ እመብርሃን !›› ሲላት ቆም አለችና ቦርሳዋን ፈትሻ ለማኙ ያላሰበውን አንድ መቶ ብር መለመኛ ምንጣፉ ላይ ዱብ ስታደርግለት የእኔም እጢ አብሮ ዱብ። ተከትያት ሄጄ ‹‹ሞልቃቄ (ለምን እንደሆነ አላውቅም ግን ሞልቃቄ ነው የምላት።
አትሞላቀቅም እኮ!) መልስ አለሽ !›› ልላት አሰብኩና እሷ የምታደርገው በጎ ነገር ሁሉ ስለሚያስደስተኝ ‹‹ሁ ማይነስ ሁ›› በሚል ወደለማኙ ተጠግቼ የአንድ ብር ሳንቲሜን ወረወርኩለት።
መስጠቴን፤ ለጋስነቴን እንዲያውቅና እንዲመርቀኝ ብዬ ነበር ምንጣፉ ላይ ያሉ ሳንቲሞች በሞላ ኪልኪልታቸውን በደንብ እስኪያሰሙ የአንድ ብር ሳንቲሙን አጩኬ የወረወርኩት። ለማኙ… እንኳን የሳንቲም ጩኸት ሊሰማ ሞልቃቄ የጣለችለትን መቶ ብር እንኳ ከጤፍ ሳይቆጥር አንገቱን ቆልምሞ፤ ዓይኑን ጎልጉሎ የሞልቃቄን ዳሌ እየተመለከተ ‹‹ይች ፖፖሊና ጭን›› ሲል በድንጋጤና በብሽቀት ሰማሁት።
አድናቆት ይሁን ምርቃት ግራ ገብቶኝ በድንጋጤና በብሽቀት ድጋሚ ለረጅም ጊዜ ስገላምጠው ሞልቃቄ በግርግሩ መሀል ዱካዋ ጠፋብኝ። አሁን አሁንማ ስድብ የአዘቦት ልብሳችን ከሆነ ሰነባብቷል።
አንዳንድ ቀናቶች ከሚገጥሙን ሁነቶች የተነሳ የሳምንት ያክል ይሆናሉ፤ ሞልቃቄ በግርግሩ ተሰውራብኝ የሥራ ፈት ነገር፤ በለማኙ እየተናደድኩ ተመልሼ ከመገናኛ የአራብሳ ታክሲ ያዝኩ። አራብሳ እንግዲህ ወጣቶችና ኤርትራውያን ወንድሞቻችን የሚበዙበት አዲስ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንደር ነው። በዚህ የኮንዶሚኒየም ሕንፃ በደረቅ ሌሊት ግድግዳ የሚቆፈቁፉ እንግዳ ጎረቤቶቼ ግራ ያጋቡኛል።
‹‹ኧረ እንተኛበት›› ስላቸው የሚሰጡኝ ምላሽ ‹‹እኛ አይደለንም፤ ወይም ደግሞ ልብስ እያጠብን ነው›› የሚል ነው። ይኸው ደግሞ እነርሱ እዚያ ሰፈር ከመጡ ጀምሮ የቤት ኪራይ ጣራ ነክቷል። በዚህም ምክንያት አከራይ በየወሩ ነው ኪራይ የሚጨምረው፤ በዚህ ላይ ደሞ! በተከራዮችና ቤት ደርሷቸው የኮንዶሚኒየም ባለቤት ሆነው በሚኖሩት መካከል ያለው የተከራይነትና የአድራጊ ፈጣሪ ኮሚቴነት ስሜት ይገርማል።
ምሽት ላይ ድንገት ኮሚቴ መሳይ የኮንዶሚኒየም ባለዕድል ተብዬዎቹ ሁለት ሦስት ይሆኑና ‹‹የውጭ መብራት አብሩ። በኋላ በጥበቃዎቹ እንዳታማርሩ።›› እያሉ ሲጮሁ ትሰማለህ። በቀጣዩ ምሽት የሌላው ሰው የውጭ መብራት ሌቱን ሙሉ ሲንቀለቀል የነዚህ ኮሚቴ ቢጤ ሰዎች በረንዳ ጨለማ ሆኖ ያድራል። የእነሱና የእኛ የመብራት የስለትና የእንጀራ ልጅ ይመስል። መቼስ ስድብ የአዘቦት ልብስ ሆኖ የለ።
ደሞ በድንገት አንዷ መሬት ላይ የምትኖር የኮንዶሚኒዬም ዕድለኛ ትነሳልህና እስከ ሁለተኛ ፎቅ ያለውን የጋራ የውሃ መክፈቻና መዝጊያ ጥርቅም ታደርግልሀለች። ውሃ ከሳምንት አንድ ቀን መጥታ ሰው ሁሉ ሲቀዳ እኛ ብሎክ ላይ አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ያለን ተከራዮች ቁልጭ ቁልጭ።
‹‹አውሮፕላን ሲበር ይላል ብልጭ ብልጭ፣
ደንገለው ሲያገባ እኔ ቁልጭቁልጭ›› ዓይነት ነገር።
የውሃ ነገር ሲነሳ ሞልቃቄ መገናኛ ላይ ከዓይኔ ተሰውራብኝ ወደ አራብሳ ተመልሼ በተለምዶ ጨርቆስ አደባባይ ተብሎ የሚጠራው የታክሲው የመጨረሻ ፌርማታ ወርጄ ወደ አሰለፈች ማርያም አቅንቶ ኮንዶሚኒዬሞቹ ሲያልቁ አብሮ በሚያልቀው አስፓልት ስወርድ ድንገት የመገናኛው ለማኝ ሞልቃቄን ‹‹ይች ፖምፖሊና…›› ብሎ ከተሳደበው የበለጠ አሰቃቂ ስድብ ሰማሁ ሳይሆን ባይኔ በብረቱ ተመለከትኩ። ስድብ የአዘቦት ልብስ ሆኗል።
ከአንድ ዓመት በፊት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች በአገሪቷ በቢሊዬኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ሲተከሉ የአራብሳ ነዋሪዎችም በየደጆቻቸውና በአስፓልቶች ማካፈያ ያሉ መሬቶች ላይ ችግኝ ተክለዋል። የጸደቀው ጸድቆ የደረቀው ደርቆ በዚህኛው ዓመትም በዘመቻ ችግኞች ተተከሉ።
ያስተዋልኩት ነባር እውነታ ግን አስፓልቶች ማካፈያ ላይ ባሉ መሬቶች የሚተከሉ ችግኞች ተተክለው ክረምት እንኳ ሳይወጣ ለአዘቦትና ዓመትባል ገበያ በሚወጡ ግለሰቦች፤ የጋማና የቀንድ ከብቶች ተረግጠውና ተቀነጣጥበው መለመላ ግንዳቸው ብቻ ደርቆ እስኪቀር ተቆርቋሪ ማጣታቸው ነበር።
አሁን ግን በድንገት አናታቸው ያለቅጠልና ቅርንጫፍ ቀርቶ ከደረቁ በኋላ ‹‹ለወገን ደራሽ ወገን!›› ብሎ ተቆርቋሪ ደረሰላቸው። ምን ቢሆን ጥሩ ነው?። ስድብ የአዘቦት ልብስ ሆኗል።
ምን ቢሆን ጥሩ ነው?… ክረምቱ አልፎ በጋው እስኪጋመስ በሰውና እንስሳት ኮቴ ተሻሽተውና በውሃ ጥም ተቃጥለው የደረቁት የዛፍ ችግኞችን ግንድ ከፕላስቲክ የውሃ ኮዳ ጋር እያሰሩ፤ ኮዳዎችን ውሃ እየሞሉ ማገዶ ቆጣቢ ውሃ የማጠጣት ዘመቻ የጀመሩ ሴቶች እህቶቻችንን አስተዋልኩ። ‹‹ምንድን ነው?›› ብዬ አንዱ ወዳጄን ስጠይቀው ‹‹ሴቶቹን አደራጅተው የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ነው¡›› አለኝ በስላቅ።
በኋላ ላይ ሳስተ ውል በተደራጁ ሴቶች ውሃ የማጠጣት ዘመቻው በሁሉም የአስፓልት ማካፈያ መሬት ላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የዛፍ ችግኞቹ አህያና ፈረስ እስኪንከባለልባቸው፣ ጠውልገው እስኪደርቁ ሴቶቹን ያደራጀው አካል የት ነበር? እኛ የአካባቢው ማህበረሰብ ተብዬዎቹስ የማንን ጎፈሬ ስናበጥር ነበር? ችግኞቹ ያለቅጠልና ቅርንጫፍ መለመላቸውን ከቀሩ በኋላ ውሃ ማጠጣቱ የአረንጓዴውን አሻራ ዓይን አውጥቶ ከመሳደብ የዘለለ ምን ፋይዳ ሊኖረው ይችላል?
እያልኩ ስፈላሰፍ ‹‹ኤሎ! ጁንታው ትቆያለህ ወይስ ልለፍ ?›› ብሎ አንዱ ቄንጠኛ የቤት መኪና የያዘ አሽከርካሪ ከገባሁበት ሀሳብ አናጠበኝ። ለካስ መሀል አስፓልት ላይ ተገትሬ ነበር ሕዝቤን የማብጠለጥል።
‹‹አሳልፈኝ ማለት አንድ ነገር ነው። ጁንታው ማለትን ግን ምን አመጣው?›› ስል እያጉረመረምኩ ነገር ግን ስድብ የአዘቦት ልብስ ስለሆነ …. ብቻ ወደ ዳር ወጥቼ መንገዴን ቀጠልኩ።
ስድብን እንደ አዘቦት ልብስ እየለመድነው ነው። ከአናታቸው እስከታች ግንዳቸው የደረቁት ዛፎች ዳግም ቢለመልሙና ለኛም ተስፋ ቢሆኑን ምንኛ ምኞቴ ነው!›› ሲል ተክዞ እኔንም አስቆዘመኝ። ትንሽ ቆይተን ግን በድንገት መገናኛ ላይ ከዓይኔ የተሰወረችውን ሞልቃቄና የምስጋና ቢስ ለማኙን ‹‹ይች ፖምፖሊና…›› የሚለውን ነገር አንስቼ ሳወራለት ወደቀድሞ ሳቅ ጨዋታችን ተመለስን። ያው ስድብ ልብሳችን ሆኗል፤ ሊቁም ደቂቁም ለምዶታል።
ለዚህም ማጠናከሪያ ይሆነኝ ዘንድ አንድ በአገራችን የተከሰተ ሁነት ልጨምር፤ እኛ ከሌለን ሀገር ይፈርሳል ብለው የሰረቁትን ሲካፈሉ ተጣልተው ሀገር አንድ ስትሆንባቸው ‹‹አራት ኪሎ ያለው ሕገወጡና ከሀዲው ቡድን›› እያሉ መቀመቅ ስለወረዱት።
ምን ተረፈ? የተረፈን ነገር ቢኖር ደሀ እናቱን መጦር ሲገባው ለሌቦች ሲል ነፍሱን የሰጠ ምስኪን ወጣት እሬሳና በባእድ አገር እንደ ጣረሞት የሚንከባለሉ ተቆርቋሪ ነኝ ባይ «የቺክን» እና «የበርገር» ቅልቦች እንቶ ፈንቶ «ፐሮቴስት» ነው።
መፍትሄው በእጃችን እያለ ነጮች ተሰባስበው ስለኛ እንዲመክሩ መፈራገጥ ለእኔ ‹‹ስድብ የአዘቦት ልብስ ሆኗል።›› የሚለው ድምዳሜ ላይ አድርሶኛል። ይቅርብን… ብሎም … ይቅር ይበለን!።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013