ማህሌት አብዱል
አቶ ተስፋዬ አለማየሁ ይባላሉ፤ ኮኽያ በተባለ የትግራይ አካባቢ ነው የተወለዱት፤ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት አዲግራት ፅንተአለም ማርያም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ነው፡፡
አባታቸው የአውራጎዳና ሹፌር ስለነበሩ በሥራው ምክንያት መላው ቤተሰቡ ወደአድዋ በመዛወራቸው የአድዋ ወንጌላዊት ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍልን አጠናቀቁ፡፡ በ1968 ዓ.ም ላይ በወቅቱ የነበሩ ታጋዮች የአባታቸው መኪና በመወሰዱ እንደገና ወደአዲግራት ተዛወሩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አጋዚ በተሰኘ ትምህርት ቤት በንግድ ሥራ ትምህርት ተከታትለው ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡
ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ገብተው በታሪክ ትምህርት ዲፕሎማቸውን አገኙ። ኢሉባቡር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተመደቡ። ለ11 ዓመት በመምህርነት ካገለገሉ በኋላ በአካባቢው ይንቀሳቀሱ በነበሩት የኦነግ ክንፎች በሌሎች ክልል ተወላጆች ላይ ያደርሱት በነበረው ዛቻና ማስፈራሪያ ሳቢያ ሥራቸውን ለቅቀው ከደምቢዶሎ ወጡ።
አዲስ አበባ መጥተውም ትምህርት ሚኒስቴር አመልክተው ትግራይ ክልል ቢመደቡም በወቅቱ ክልሉ በጀት የሌለው በመሆኑ በዓመቱ መጨረሻ እንዲመለሱ ይነግሯቸዋል። ይሁንና ያለሥራ መቀመጡን ስላልወደዱት ወባን በመከላከል ሥራ ላይ በተሰማራ ድርጅት ውስጥ ሰልጥነው ተቀጠሩ። በመቀጠልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ በሚከናወነው በሕዝብ ቆጠራ ሥራ የጂኦግራፊካል ማፕ ተቆጣጣሪ ሆነው በክልሉ ተሳተፉ።
በተመሳሳይ ወቅት በአድቬንቲስት ሁለተኛ ደረጃ መምህርነት አመልክተው ስለነበር የሕዝብ ቆጠራውን ትተው በታሪክ መምህርነት መስራት ጀመሩ። ነገር ግን በዚያም አልገፉበትም፤ ከአንድ ወር በኋላ በአስጎብኚነት በተቋቋመ የግል ድርጅት ተወዳድረው ወደ አዲስ አበባ መጡ።
አምስት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ግን በህወሓት ሰዎች በተቋቋመው በዚሁ አስጎብኚ ድርጅት ውስጥ የነበሩ ኃላፊዎች የእሳቸው እውቅና ተወዳጅነት ያላስደሰታቸው በመሆኑ ጫና ያሳድሩባቸው ጀመር። በዚህ ምክንያት ሥራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለቀው ወጡ። በግላቸው ለዓመታት በአስጎብኚነት ሥራ ሲንቀሳቀሱ ከቆዩ በኋላ በቅርቡ ደግሞ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን ተቀላቅለዋል።
በአሁኑ ወቅት የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ያሉት እኚሁ የታሪክ ሰው፤ በነበራቸው የአገር ፍቅር ስሜትና በአገር ወዳድነታቸው ምክንያት በህወሓት ሰዎች ከፍተኛ ጫና ደርሶባቸዋል።
በተለይም ደግሞ የማያምኑበትን ደፍረው የሚናገሩ በመሆናቸው ምክንያት እሳቸውም ሆነ መላ ቤተሰባቸው ‹‹ባንዳ›› የሚባል ስያሜ በዚሁ ኃይል አጋፋሪዎች ተሰጥቷቸዋል። ከዚህም ባሻገር ከትውልድ ቀያቸው እስከመሰደድ ድረስ ከፍተኛ እንግልት ደርሶባቸዋል።
የዛሬው የዘመን እንግዳችን አቶ ተስፋዬ አለማየሁ፣ የህወሓት ጁንታ እንደእሳቸው ባሉ ለአገር ቅን አሳቢዎችና ታሪክ ወዳዶች ላይ ያደረሰው በደል በምንም የማይተካ እንደሆነ ያምናሉ።
አሁን ላይ የመጣው ለውጥም በተለይም በጭቆና ቀምበርና በድህነት አረንቋ ሲዳክር ለኖረው የትግራይ ሕዝብ ከድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑን ያነሳሉ። ከእንግዳችን ጋር በእዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነው ውይይት እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ከንግድ ሥራ ትምህርት ወደ ታሪክ ትምህርት የገቡበት የተለየ ምክንያት ካለ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ተስፋዬ፡– በመጀመሪያ ደረጃ እነበዓሉ ግርማ፣ እነ ሙሉጌታ ሉሌን፣ ስብሃት ገብረግዚአብሔርንና ማዕረጉ በዛብህን ባፈራው አንጋፋ የአገራችን ጋዜጣ ላይ እንግዳ ተደርጌ በመቅረቤ የተሰማኝን ደስታና ከበሬታ መግለጽ እወዳለሁ። ወደ ጥያቄሽ ስመለስ እንዳልሽው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት
በንግድ ሥራ ወይም ቡክ ኪፒንግ በተባለ ትምህርት ነው። ዲፕሎማም አግኝቼ ነው ወደ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የተመደብኩት። ነገር ግን በወቅቱ የደርግ መንግሥት የንግድ ሥራ ትምህርት የሙያ ትምህርት በመሆኑና በዚያ እንዲማሩ የሚፈለገው በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት ላመጡ በመሆኑ ወደታሪክ ትምህርት ክፍል ገብቼ ታሪክ አጠናሁ።
ለነገሩ ቀድሞውንም ቢሆን አባቴ የአገሬን ታሪክ ጠንቅቄ እንዳውቅና እንድወድ አድርጎ ያሳደገኝ በመሆኑ ለታሪክ ትምህርት የተለየ ቦታ አለኝ። እውነቱን ለመናገርም በትምህርት ቤት ካገኘሁት እውቀት በላይ አባቴ ያስተማሩኝ ትምህርትና የአገር ፍቅር ስሜት አሁን ላለሁበት ማንነት ትልቅ አሻራ አሳርፏል የሚል እምነት አለኝ።
አባቴ ምንም እንኳን የተማረው እስከ ሦስተኛ ክፍል ቢሆንም በታሪክ ጥልቅ እውቀት ነበረው። አያቴም ቢሆኑ ለአገራቸው አንድነትና ህልውና መቀጠል በአርበኝነት እየተዋጉ ነው የሞቱት። በመሆኑም እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ስለሀገራችን ታሪክ ጠንቅቅን የምናወቅ፣ ታሪክንም ሆነ አገራችንን የምንወድ ነን።
አባቴ ጣሊያኖች ቤት አስመራ ያደገና ሹፌርነትም የሰለጠነው በእነሱ ድጋፍ ቢሆንም፤ የአገር ጉዳይ ሲመጣ ‹‹ኢትዮጵያ ወይም ሞት›› ብሎ ኤርትራ ከ70 ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ካደረጉት ሰዎች መካከል ስሙ የሚጠቀስ ነው። ከዚህም ባሻገር ኮተቤ በተማርኩት ትምህርት ከፍተኛ ደስታ ነው የሚሰማኝ።
የነበሩት መምህራኖችም ለታሪክና ለአገራቸው ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው በመሆናቸው እኔም ያንኑ እንድወርስ አድርገውኛል ብዬ አምናለሁ። ኢሉባቡር ዲዲላሎ በምትባል ትንሽ ወረዳ ላይ ለማስተማር ከተመደብኩኝ በኋላም ያገኘኋቸው መጽሐፎች አሁን ላለው ማንነቴ ትልቅ መሠረት ጥለውልኛል። እነዚያ መጽሐፎች ባሳደሩብኝ መልካም ተፅዕኖ ዛሬም ድረስ ከመጻሕፍት ሳልላቀቅ እንድኖር አድርገውኛል።
አዲስ ዘመን፡- በግል ሕይወትዎ ህወሓት ያደረሰብዎትን ጫና እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ተስፋዬ፡- የእኔና የህወሓት ልዩነት የተፈጠረው ቀድሞ ነው። በተለይም የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት እንደተጀመረ ባለቤቴ አስመራ በመወለዷ ምክንያት እዚህ ያሉትን የሻቢያ ተቃዋሚዎች መደገፍ አለብሽ በሚል አለመግባባት ተፈጥሮ ከሥራ እስከመባረር ድረስ ከፍተኛ እንግልት አድርሰውባታል። የባለቤቴ አባት የአፄ ኃይለሥላሴ ሻለቃ ነበሩ። እንደነገርኩሽ እሷ ተወልዳ ያደገችው አስመራ ውስጥ ነው። ነገር ግን ደግሞ ጅማ እርሻ ኮሌጅ ነው ትምህርቷን የተከታተለችው።
ከዚያ በኋላም እኔ ወዳለሁበት ቦታ ተመድባም ሰርታለች። ወያኔዎቹ ከመጡ በኋላ ግን በኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ ላይ አልተሳተፈችም፤ ለኤርትራ መዋጮም አታደርግም፤ የኤርትራ መንግሥትም አያውቃትም ነበር።
በሥራዋ የትምህርት ሰውና ሥራዋንም የምታከበር ሰው ነች። ሆኖም በነበራት ችሎታ ምክንያት የህወሓት ሰዎች በቅናት ተነሳስተው ‹‹ኤርትራዊ ናት›› ብለው ከዚህ ሊያባሯት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር።
በኋላም እነሱ ከሚያሰለጥኗቸው የኤርትራ ተቃዋሚዎች ጋር መሆን አለብሽ ሲሏት ‹አይሆንም ብዬ ቅሬታዬን በወቅቱ ከፍተኛ አመራር ለነበሩት ለአቶ ገብሩ አስራት አመልክቼ ነበር። የመንግሥት ቃልአቀባይ ለነበረው አቶ ኃይሌ ኪሮስም
በተመሳሳይ አቅርቤ ነበር።፡ ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ ከጥቅምት 1992 ዓ.ም እስከ ግንቦት 1998 ዓ.ም ድረስ ከሥራ እንድትታገድ አድርገዋት ነበር። የስድስት ዓመት ደመወዝ አልሰጧትም።
ከዚያ በኋላም ቢሆን እንኳን የተከማቸውን ደመወዟን ሊሰጧት ይቅርና ዋናውን ደመወዟን እንኳን ከሌላው አካባቢ ካሉ ሠራተኞች ያነሰ አድርገውት ነበር። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከመጣ ወዲህ በሕይወቴ በተለይም በኢኮኖሚዬ ላይ ከፍተኛ ጫና ነበር ሲያደርሱብኝ የነበረው።
ነገር ግን ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁንና ባለቤቴን እንደገና መልሰዋት ሥራ ጀምራ ነበር። የሚገርምሽ ግን 40 ዓመት በላይ አገልግላ ሳለ ለእነሱ ወሬ አቀባይና ታዛዥ የሆኑትን ወጣቶች ከተማ ላይ አስቀምጠው ፈረስማይ የሚባል ገጠርና ለኑሮ አስቸጋሪ የሆነ ስፍራ ልከዋታል። እኔን ይፈልጉኝ እና ያሳድዱኝ ሰለነበር መስከረም ወር ላይ ነው ወደአዲስ አበባ የመጣሁት። ከሌላ ሰው ጋር አዳብለውም ከሰውኛል።
አዲስ ዘመን፡- ምን ስላደረጉ ነው የተከሰሱት?
አቶ ተስፋዬ፡- እንደነገርኩሽ ከሌላ ሰው ጋር አዳብለው ነው የከሰሱኝ። የክሱን ዝርዝር ገና አላየሁትም። ነገር ግን እንደሰማሁት ፀረ ወያኔ መሆኔን፣ ባንዳና ብልፅግና ነህ የሚል ነው። እኔ ሸሽቼ አዲስ አበባ ብመጣም ባለቤቴ በአሁኑ ወቅት ያለችበትን ሁኔታ አላውቅም። ስልክ ባለመኖሩ የምንገናኝበት ሁኔታ የለም።
በእርግጥ ሁለቱ ልጆቼ ከሽሬ ሰው ልከው ‹‹ደህና ነን፤ አታስብ›› ብለውኛል። እናም እንደነገርኩሽ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ በጣም እጋፈጣቸው ስለነበር ከፍተኛ ጫና ነበር ሲያደርሱብኝ የነበረው። በተለይም ዶክተር አብይኝ እደግፍ ስለነበርና በዚህ ጉዳይ ላይም እፅፍ ስለነበር ሐምሌ 14 /2010 ዓ.ም ላይ ወደ ቤቴ ስገባ ማጅራቴን አስመቱኝ። እፅፍበት የነበረው ህዋዌ ሞባይልም ስለቀሙኝ ከዚያ በኋላ መፃፍም አልቻልኩም። እዛው ግን በፕሮፖጋንዳው ረገድ እቃወም ነበር።
ለምሳሌ ምርጫ ባከናወኑበት ጊዜ ተመዝግበን ካርድ ወስደናል። ያንን ያደረግሁትም በምክንያት ነው። በዲሞክራሲ ሂደት ውስጥ ያሉትን አማራጮች መጠቀም ይገባል ብዬ ስለማምን ነው። በመመዝገብሽ የሚቆጭሽ ነገር የለም። የማትፈልጊያቸውም ከሆነ ያለመምረጥ መብትሽ ነው።
እኔ ግን ወረቀቱን እንዳይጠቀሙበት አድርጌ አጣጥፌ ነው ኮሮጆ ውስጥ የከተትኩት። ስለዚህ ድምፄ የለም። በመሆኑም ማንኛውም ሰው ሊገነዘብ ይገባል ብዬ የማምነው የዲሞክራሲ ሂደት እንዲመጣ ከተፈለገ መንግሥት ምንም ይሁን ምን የተፈጠረውን ዕድል መጠቀም ይገባል።
በአጋጣሚ እኮ ሊመረጥ የሚችል ኃይል በስተመጨረሻ ቢመጣ እንኳን የመምረጥ ዕድሉ ይኖርሻል። ለመወሰንም ሆነ ላለመወሰን ካርዱን መያዝ ያስፈልጋል። እርግጥ ነው ምርጫው መካሄዱን አልደግፍም ነበር። ነገር ግን ያልተመዘገበ እንደሚታሰርና እንደሚፈረድበት አውጀው ስለነበር ሕዝቡ ምንም አማራጭ አልነበረውም። ነገር ግን ይህንን ባያደርጉ ምርጫውን ተመዝግቤ የእኔ ምርጫ አለመሆናቸውን በድምፄ ለማሳየት ነበር የማስበው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ፖለቲካ ፓርቲ አባልነት የገቡበት አጋጣሚ ምን ነበር?
አቶ ተስፋዬ፡- በመጀመሪያ ደረጃ መናገር የምፈልገው የትዴፓ መሪዎች በኢትዮጵያዊነታቸው የሚደራደሩ አይደሉም። በቅርብ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ያውቁታል። ቁርጠኛ አቋም ያላቸው በመሆኑ ነው በሴራ ከመሰረቱትና ደማቸውን ካፈሰሱለት ፓርቲ የተገለሉት።
በተለይ ዶክተር አረጋዊ በርሄና ኢንጅነር ግደይ ዘራፂዮን ህወሓት ውስጥ በነበሩ ሰዎች ምቀኝነትና ሴራ ከፓርቲው እንዲወጡ መደረጉን የማውቅ በመሆኔ ትግሉን ለመቀላቀል ወሰንኩ። እነዚህ ሰዎች የህወሓት ጁንታ ስማቸውን ባጠለሸው መልኩ ሳይሆን ስለኢትዮጵያዊነታቸውም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ ነፃነት በከፈሉት ዋጋ በቀደሙት የህወሓት መስራቾች ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ የነበራቸው ሰዎች ናቸው።
የእነሱን ስም በዋናነት ሲያጠለሹ የነበሩት እነ አቦይ ስብሃት፣እነጀነራል ፃድቃን የመሳሰሉት ሰዎች ናቸው። ይህንን ያደርጉት የነበረውም በነበራቸው ከፍተኛ የስልጣን ጥማት ነው። እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ የማንበብ ዕድሉ ስለነበረኝ ያደርጉት ስለነበረው ብርቱ ትግል ጠንቅቄ አውቃለሁ።
በአጋጣሚ ከዶክተር አረጋዊ ጋር በአንድ ስብሰባ ላይ ተዋወቅና ተወያየን። በውይይታችንም እንደሚባለው ሳይሆን ቀለል ያለ ምስኪን ሰው መሆኑን ለመገንዘብ ችያለሁ። ከእነሱ ጋር ሆኜ እንድረዳው ስለጠየቁኝም ተስማምቼ ፓርቲውን የተቀላቀልኩኝ። ባለችኝ ቀሪ ዘመኔ ሥልጣን ለመያዝ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ በህብረት የቆመችውን ይህችን አገር ለማስረከብ ካለኝ ብርቱ ፍላጎት የተነሳ ነው። ልምዳችን ተሞክሮችንና ቅንነትና ለአገር ፍቅር ስሜት ለትውልዱ ለማስተላለፍ የምሻም በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ምሁራን የኢትዮጵያ ታሪክ የነገስታት እንጂ የሕዝቡ አይደለም ብለው ያምናሉ። ሌሎቹ ደግሞ የአንድ ብሔር ታሪክ ብቻ ነው ይላሉ። እርሶ እንደታሪክ ሰው በእነዚህ ሃሳቦች ይስማማሉ?
አቶ ተስፋዬ፡– በመጀመሪያ የተፈጥሮ ሳይንስና የሶሻል ሳይንስ ትምህርቶችን በተናጠል ብናያቸው ደስ ይለኛል። በተፈጥሮ ሳይንስ አንድና አንድ ሲደመሩ ሁለት ነው። በኅብረተሰብ ሳይንስ ከጂኦግራፊና ከኢኮኖሚክስ ሥነ ትምህርት ውጪ አከራካሪ ናቸው። ምክንያቱም በሰው አእምሮ የሚመዘኑ ናቸው።
ደግሞም እኔ ባየሁበት መንገድ አንቺ የማታይበት፣ አንቺ ያየሽበት መንገድ እኔ የማላይበት ሊሆን ይችላል። ግን ደግሞ በእኔ አፃፃፍ ላይ ቅሬታ ካለብሽ መፃፍ ነው እንጂ ያለብሽ ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ መተቸትና መኮነን ከአዋቂ ተርታ አያስመድብሽም። ተቀባይነትም አይኖረውም።
አንቺ እኔን ለመውቀስ ከፈለግሽ ተመራምረሽ የደስሽበትን በመፃፍ ነው እንጂ እንዲሁ በዋዛ የ110 ሚሊዮን ሕዝብን ታሪክ ጥቂቶች ስላልተቀበሉት ብቻ ‹‹ታሪካችን አይደለም›› ማለት አትችይም። ይህችን ሰፊ የሆነች አገር፣ ብዙ ዋጋ የተከፈለባትን ተማርን የሚሉት ጥቂቶች ታሪኳን ሲያኮስሱት ማየት በእርግጥም እንደታሪክ ሰው ያማል።
የእነዚህ ሰዎች የትምህርታቸው ፋይዳ ምንድን ነው? ይሄ ሕዝብ እኮ ከመቀነቱ ፈቶ ነው ያስተማራቸው። በመሆኑም እንደምሁር የተጋነነ ታሪክ ካለ ያንን በማስረጃ መንቀፍና ሚዛኑን የጠበቀ አስተያየት መስጠት ይቻላል እንጂ በደፈናው ብዙኃኑ የሚያውቀውና የሚያምነውን እውነት መካድ አይቻልም። ሁለት ጫፍ ይዞ ይዞ መጓተትም ለማንም አይበጅም።
ምሁርነት የሚያጣላንና የሚለያየንን መረጃ መሰብሰብ አይደለም። ዋነኛው ትርጉሙ የባህሪ ለውጥ ማምጣቱ ላይ ነው። ከአካባቢው ከለገሰው ተፈጥሮና ባህላዊ ትውፊትን መርምሮ እውነታውን መገንዘብና ይሁንታ ያለውን ነገር ማቅረብ ነው እንጂ ይሄኛው ታሪክ የእኛ አይደለም ማለት ውሃ አያነሳም። በመሰረቱ የኢትዮጵያ ታሪክ የእነሱ ካልሆነ እነሱ ታዲያ የማን ዜጋ ናቸው? አገራቸውስ የት ነው?
በእርግጥ ታሪክ ያለፈ ማንነታችን ነው። ነገር ግን ታሪክ የምናውቀው ካለፈው ስህተት ለመማር እንዲሁም ያለፈውን ጥንክሬ ለማስቀጠል ብቻ ነው። ዛሬን ልንገነባበት፣ ነገን ደግሞ ልናይበት እንዲሁም ትውልድን ልንቀርፅበት እንጂ የራሳችንን ብቻ ሳይሆን የነገውን ትውልድ ተስፋ ልናጨልምበት አይደለም። ታሪክ ለየትኛውም አገር እድገት መሠረት ነው።
ስለዚህ ባለፈ የታሪክ ስህተት ላይ የሙጥኝ ብሎ እሱኑ አዝሎ መኖር በሽታ ነው ። መቀየም፣ ክፉ ክፉን ማዘል በማህበረሰብ ሳይንስ በስነልቦና ጭምር የሚያመጣው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም። ስትቀየሚ እኮ አይንሽ አያይም፤ ክፉ ነገር ስታስቢ እኮ ጆሮሽም አይሰማም። እንደአጠቃላይ ማህበራዊ ሳይንስ ቀመር የሌለው በመሆኑ በመካከላችን አለመግባባት መፈጠሩ ተፈጥሯዊ ነው። ፍፁም ነው የሚባልም ታሪክ የለም።
ለምሳሌ በታሪክ ውስጥ አፈታሪክ፣ የጽሑፍ መረጃ፣ ጂኦሎጂካል ቁፋሮ ሥራዎች አሉ። ስለዚህ በአፈ ታሪክ ረገድ ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን አስቆጥሯል። አብዛኞቹ ታሪኮቻችን ከትውልድ ትውልድ በአፍ ቅብብሎች ነው እዚህ የደረሰው። በዚህ ሂደት አንድም ተጋኖ፣ ወይም እየተረሳ አልያም እየተዛባ ይመጣል።
ጽሑፉን በሚመለከት ደግሞ ኢትዮጵያ ታሪኳ በአብዛኛው የህልውና እና የነፃነት ጉዳይ ስለነበር ብዙ ጦርነቶች በኖሩ ቁጥር ብዙ መረጃዎች የጠፉበት ሁኔታ ነው ያለን። እዚህም ላይ አዳዲስ ነገስታት ሲመጡ የቀድሞውን መንግሥት ታሪክ እያጠፉ ነው የሚሄዱት።
ስለዚህ ከታሪካችን አንፃር በዓለምአቀፍ ጦርነቶች ከ1928ዓ.ም ወደኋላ መቶ ዓመት ስንመለስ 32 ዓለምአቀፍ ጦርነቶችን አካሂዳለች። ይሄ እኔ የምለው አይደለም፤ ዓለምአቀፍ ጸሐፍት የፃፉት ነው። ከዚህም ባሻገር በእነ ዮዲት ጉዲትና ዘመነ መሳፍንት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ ሁላችንም የምናውቀው ነው። የሚቃጠሉና የሚጠፉ እንዲሁም የሚዘረፉ መጽሐፍቶች አሉ።
አሁን ላይ ተነስተን ባለፈው ታሪክ ይሄና ያ ተደርጓል እያልን እርስ በርስ ከምንባላ ይልቅ አሁን ለቆምንበት ነባራዊ ሁኔታ ነው መጨነቅ ያለብን። የቀደሙት አባቶቻችን ስህተትም ይስሩ አይስሩ አሁን ቆመን የምንናገርባት አገር አስረክበውናል። ይሄ እንደአንድ ትልቅ ፀጋ መቆጠር ሲገባው ያለፈውን ሁሉ በዜሮ እየደመሩ መውቀስና መባላት ነው የተያያዝነው።
በመሠረቱ እንዲህ ብሎ የሚናገረው የት ላይ ቆሞ ነው? ምንስ ነው የሚፈይደው ይሄ ታሪክ የእኛ ነው፤ አይደለም ብሎ መሟገት?። የእኔ ታሪክ አይደለም ማለትና አለመቀበል ይቻላል። አዋቂ ከሆነ፣ ለታሪክ ተቆርቋሪ ከሆነ፣ የታሪክ ባለሙያ ከሆነ ይፃፍና ያሳየን። እኛም እንገረም።
ለምሳሌ ‹‹በምኒልክ ዘመን አምስት ሚሊዮን ኦሮሞ ተጨፍጭፏል›› ብሎ የፃፈ አለ፣ እውነታው ግን በዚያ ጊዜ ጠቅላላ የኢትዮጵያ ሕዝብ 25 ሚሊዮን ነበር፣ እናም በምን አግባብ ነው ያን ያህል ሕዝብ ሊጨፈጨፍ የሚችለው? ምንድነውስ ማስረጃው? ይሄ ሁሉ የሚባለው ክፉ ትርክት አንደኛ አያስፈልገንም።
ሁለተኛ የዚያ ጊዜ ተፈጠረ በሚባለው ትርክት አሁን ያለው ትውልድ ለምንድን ነው የሚወቀሰው? ለምንድን ነው የሚጨፈጨፈው? ለምንድን ነው የሚገደለው? የአሁኑ ትውልድ መጠየቅ የሚገባው እንደማንኛው አገር ዜጋ አገሩን ከካደ፣ የአገሩን ምስጢር አሳልፎ ከሰጠ፣ ከጠላት ወገን ከተሰለፈና በአገሪቱ ሕግ መሠረት ወንጀል ከሰራ ነው።
ከዚህ ውጪ አሰብክ፣ ታሪክ አዛባህ ተብሎ ለዚያውም ላልኖረበት ዘመን፣ ዕዳ ለሌለበት ሁኔታ አዲሱ ትውልድ ሊወቀሰም ሊጠየቅም አይችልም። አብዛኞቹ ታሪክን የሚቃወሙት አሜሪካና አውሮፓ አገር ሄደው የመጡ ናቸው።
በነገራችን ላይ በአሜሪካ የባሪያ ንግድ ታሪክ እስከአሁን እየተጻፈ ነው። ስለዚህ እኛም አገር እውነት አለኝ የሚለው አካል ማስረጃን መፃፍ ነው የሚጠበቅበት። ሌላ የአጻጻፍ መንገድ ካለ ያሳዩን። ያለዚያ ዝም ብሎ መተቸት፣ ገንዘብ ለማግኘት እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ተጽፏል ለመባል ከሆነ እርባና የለውም።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የነገስታቶች ታሪክ ብቻ ነው በሚለው ይስማማሉ?
አቶ ተስፋዬ፡– አልስማማም። ምክንያቱም ከሦስቱም የታሪክ ምንጮች አንጻር፤ ከአፈ ታሪክ፣ ከጽሑፍ መረጃዎችና አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የሚባሉ መረጃዎች አሉ፣ አሪኪዩሎጂካል ቁፋሮ ሲደረግ ሁለት መለኪያዎች አሉ ከሚሊዮን ዓመት በላይ ለሆነው መለኪያዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ይህንን እያገኘች ነው። አብዛኛው የእኛ ታሪክ ከተወሰኑ ጥቂት ሰዎች በስተቀር ፈረንጅ ነው የጻፈው።
ሙሉ በሙሉ እንቀበላለን ማለት አይደለም። ስልጣኔው፣ ታሪኩ አለ። ስለነገስታቱም እኮ ነግረውናል። አጴ ቴዎድሮስ አንበሳ የነበራቸው መሆኑን በዓይናቸው አይተው ሲገስጿቸውና ሲጠሯቸው አይተው እኮ ነው የነገሩን። እኛ ግን እንኳን በዓይን ያላየነውን የኖርንበትንም እንክዳለን። የእኛስ ሚና ምንድን ነው? እየወቀስን መኖር ነው? በደሃው ኪሳራ መኖር ነው። ደሃው መስዋዕትነትን ይከፍላል፣ የአገር ነጻነትና ድንበር ያስከብራል።
እኛ ግን ተምረን የድርሻችንን አልተወጣንም። ሥራቸውን ሳይወዱት፣ የሥራ ሰዓትን በአግባቡ ሳይጠቀሙ እንዴት ነው ምሁር ነን የሚሉት? አገርን ሳይወድ ሕዝቡን ሳይወድ እንዴ ዓይነት ትችት ማቅረብ የሚችሉት? በመሆኑም ሁሉም ትችቱን ያቁም። ከቆምንበት፣ አሁን ካለንበት ተነስተን ሥራ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27 ዓመታት ትውልዱ ትክክለኛ ታሪኩን አውቆ እንዲኖር ከማድረግ አኳያ የነበሩት ክፍተቶች ምንድን ናቸው ይላሉ?
አቶ ተስፋዬ፡- አንደኛው ያለፉት 27 ዓመታት ወያኔ ኢህአዴግ የገዛበት ምክንያት የኢትዮጵያውያን ጥፋት ይመስለኛል። ከእራሴ ጀምሮ። ወያኔ እዚህ እንዲመጣ ያደረገው ድምር ውጤታችን ነው። አለመደማመጣችን፣ አለመነጋገራችን ነው። እንደፈለገ እንዲያደርገን ዕድል የፈጠረለትም ይኸው ነው። መንግሥታት ሲነገራቸው ከማኩረፍ አልፈው ወደ መግደል መሄዳቸው ነው።
ብዙ ያልተጻፉ ታሪኮችን በተራ ታሪክ ልንናገረው የማይገባን የሚባሉ አሉ። ይሄንን እንደ ታሪክ ምሁር ማስተጋባትም አይገባኝም። በተቻለኝ መጠን ማጣራት ነው የሚገባኝ። ስለዚህ በቤተ መንግሥት የነበሩ ሰዎች በኃይለ ሥላሴ ጊዜ ቢሆን የመከሩት ምክር ተሰምቷል? እነ ራስ አበበ አረጋይ፣ እነ ጀነራል መርዕድ መንገሻ፣ ግርማቸው ተክለሃዋርያት እኮ ላንጋኖ ድረስ ሄደው በምስሊር ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ሕገ መንግሥታዊ፣ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት አርቅቀው ለጃንሆይ አቅርበውላቸው ነበር።
ጃንሆይ እነዚህን ምን አደረጓቸው ግርማቸው ተክለሃዋርያት በግዞት መልክ ወደ ኢሉባቦር ነው የተላኩት። ጀነራል መርዕድ መንገሻ ከዋናው ሚኒስትርነታቸው ዝቅ ወደአለ ማዕረግ ነው የወረዱት።
መንግሥቱ ኃይለማርያምን ውሰጂ እነ ምኒልክን፣ እነ አጼ ቴዎድሮስን፣ እነ አጼ ዮሐንስን አሁን ባለንበት አይን እያየን እኮ ነው እየፈረድንባቸው ያለነው። እነዚህ ሰዎች ዘመናዊ ትምህርት ሳይኖራቸው፣ ካርታ ሳይኖራቸው፣ ጂፒኤስና ኮምፓስ ሳይኖራቸው ይሄንን ሰፊ አገር አስረክበዋል። ከቤተ ክህነት ወጥተው። ማሳነሴ አይደለም።
የቤተ ክህነትን ትምህርት የተማሩ ሰዎች ናቸው ኢትዮጵያን በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ጥበብ፣ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ያሳደጉት። በእኛ ዓይን ባለንበት ዘመን ምኒልክን መፍረድ፣ ዮሐንስን መፍረድ፣ አጼ ቴዎድሮስን መፍረድ ዋጋ ያለው አይመስለኝም።
ከስህተታቸው እንማር መልካም፣ ደግነታቸውን እንውሰድ። አለበለዚያ በነጭ ወራሪ ያልተደፈረችን አገር ያስረከቡንን ጀግኖች ምን አድርጉ ነው የምንላቸው?።
ስለዚህ እንደኔ እንደኔ ወያኔ የኢትዮጵያ ታሪክ ድምር ውጤት ነው። ይህንን ስል ምንም የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ባህል በሌለበት በ1966 ዓ.ም የፈነዳው አብዮት እንደኔ እንደኔ ባይፈነዳ ይሻል ነበር። ያለፍርድ ሰው የሚገደልበት፣ በቀይ ሽብር፣ በነጭ ሽብር ፍትህ፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት እፈልጋለሁ ያሉ ፓርቲዎች ያለቁበት ነው።
ሕዝብን በማስገደል የተጫወቱት ሚና፣ እርስ በእራሳቸው የሆኑትን ታሪክ ስታነቢ ይዘገንናል። በእውነቱ ይሄ የኢትዮጵያውያን ባህሪ ነው። እውነት ይሄ ይገባን ነበር፣ እውነት የኢትዮጵያ እናት ይሄ ይገባታል። ስለዚህ ያለመደማመጣችን፣ የመጻፍ መብታችን ውስን ስለነበረና ያለመነጋገራቸን ወያኔ አልፎ እንዲመጣ አደረግን። እውነቴን ነው ራሳችን ነን ያመጣነው።
እኔ ቅድም እንዳልኩሽ አጼ ኃይለስላሴ ባይወርዱ ይሻለኝ ነበር። ምክንያቱም እየሰለጠንን ሄደን ፖለቲካዊ ባህሪያችን እነ ኢህአፓ፤ መኤሶም ማቋቋም አስችሎ ነበር። በአንድ በኩል እንደ ኢህአዴግ ወያኔ ቶምቦላ የደረሰው እዚች አገር አልነበረም። ደርግ የሚወደው አልነበረም፣ በርግጥ ለደርግም ፋታ ሳይሰጡ ወደ እዚህ ጣጣና ፈንጣጣ የከተቱት እነርሱና የወቅቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።
ምንም እኮ ፋታ አላገኘም። 1966 አመጽ ተደረገ፣ 1967 መስከረም ሁለት ተያዘ፣ 1968 እና 1969 ሶማሊያም፣ ኤርትራም ወረሩን። ምንድን ነው ሃሳቡ፣ ምንድን ነው እቅዱ የሚለውን ነገር ያወቀው የለም። በደፈናው ወታደር ነው ተብሎ ነው ያ ሁሉ ዘመቻ ሲካሄድበት የኖረው።
በእነዚህ ወታደሮች ግን ስንት ሊቃውንት ነበሩ የምናውቃቸው። የእርሻ ምሁራን፣ የሥነ ሕንፃ ምሁራን፣ ሐኪሞች የነበሩ። እናም በጥቅሉ ደርግ ፋታ አልተሰጠውም፤ ነገር ግን ፋታ አለመሰጠቱ ብቻ ሳይሆን እርሱም ፋታ ለማይሰጡ ሰዎች መንገድ ከፈተላቸው።
ለምሳሌ 60ዎቹን ባለሥልጣናትንና ኢትዮጵያውያንን ያለ ፍርድ ገደለ። ከእዚያ በኋላም በእራሱ ላይ የሚመክሩትንም መግደል ጀመረ። እንቅስቃሴውን የመሩትን እነ አጥናፉ አባተ ተገደሉ፡ እነዚህ እውቅ ኢትዮጵያውያን ጀነራል አማን አምዶም ሚካኤልና ተፈሪ በንቲ ተገደሉ። ስለዚህ እነርሱ ይህችን ይፈልጉ ነበር።
መንግሥቱንም ለመግደል ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ጥረት አድርገዋል። እንደእነ ጌታቸው ማሩና ኃይሌ ፊዳ የመሳሰሉ ፖለቲከኞች ሕዝብን እናስተምር፣ እድገት በህብረት እንዝመት የሚሉ፣ ግድያ ይቃወሙ ነበረ።
ነገር ግን የራሳቸው ድርጅቶችም ችግር ፈጣሪዎች ነበሩ። ስለዚህ ፋታ አልተሰጠውም፣ ከጭካኔውና ካሳለፍነው ሁኔታ ከኢኮኖሚውና ከሰብአዊ ሁኔታ የተሻለ መንግሥት ይመጣል እየተባለ ነበር። ምክንያቱም እነዚህ በረሃ ላይ ውሸታቸውን በሚያሳዩት ሥነ ምግባርና ባህሪ ነው።
አሁን ያለው የዶክተር አብይ መንግሥት የተሻለ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ወያኔ ነግሶ እስከሄደበት ድረስ ኢትዮጵያውያን ነገ ይሻል እንጂ ዛሬ ይሻላል ያልንበት ጊዜ የለም። አሁን ባለው ተስፋ አለኝ በእዚህ ምንም ጥርጥር የለኝም። ዋናው እንዲታገሱና ወደ ሕዝቡ ወርደው የሕዝቡን ፍላጎት፤ በተለይ በሰላምና በፍቅር ረገድ የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢኖሩ ጥሩ ነው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ወያኔ ትውልዱ አገር አፍቃሪ እንዳይሆን፣ ሥነ ልቦናው ውጭ ናፋቂ እንዲሆን ያደረገው ለታሪክ የተሰጠው ዋጋ ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ። ይህስ ምን ያህል ተቀባይነት አለው?
አቶ ተስፋዬ፡– ጥሩ ጥያቄ ነው። እኔ በእዚህ ረገድ አዎ ትክክል ነሽ አጠያያቂ አይደለም፣ እኔም አይቼዋለሁ። በተለይ በትግራይ የሚጻፉ የትግራይ ሲቪክስ መጽፎች በመጠኑም ቢሆን አይቻለሁ፣ አንብቤያለሁ።
ስለኢትዮጵያ ክብር፣ የነጻነት ተጋድሎ አሞግሶ እና አክብሮ የተናገረ የእነርሱ መሪ የለም፤ አላደረጉም፣ አልሰሩበትም። ይሄ ምን ማለት ነው እነዚህ ሰዎች እኔና አንቺ እስከምናውቃቸው ድረስ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የሌላ አገር ዜግነት ፓስፖርት ያላቸው አይመስለኝም። በተለይ ደግሞ የእኔ አገር ሰዎች ናቸው።
ለምንድነው ይህንን ያደረጉት እኔ ሁለት ጥርጣሬ አለኝ። አንደኛው ጥርጣሬ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን መልእክተኞች ናቸው። ደግሞ በጣም የሚገርምሽ የሚያደርጉትን ነገር ይነግሩሻል። ሲሰድቡሽ እነርሱ የሆኑትን ነው የሚነግሩሽ አያፍሩም።
ባንዳ ሆነው ባንዳ ይሉሻል፣ ቅጥረኛ ሆነው ቅጥረኛ ይሉሻል፣ አሸባሪ ሆነው አሸባሪ ይሉሻል። እነዚህን እኮ ከባህላዊ ሽፍትነት የሚለያቸው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሽፍቶች ስለሆኑ ብቻ ነው። ባህላዊው ሽፍታ ጾም ካለ እንኳን ብታቀርቢለት አይበላም።
ለእምነቱ የኖረ ነው። እነዚህ ያገኙትን የሚገፍፉ ገፋፊዎች ናቸው። ሰብስበው አይበቃቸው፣ በልተው አይበቃቸው፣ ጠጥተው አይረኩ። ሽፍታ በአገራችን ይከበራል። ሥነ ሥርዓት አስከባሪዎችም ነበሩ። ፍትህ የሚሰጡ ተፈሪ ሽፍታዎች ነበሩ። የእነዚህ ከባህላችን አንጻርም የለም። እነዚህ እንግሊዝኛ ተናጋሪ አሸባሪ ሽፍቶች ናቸው። የትግራይን ሕዝብ ሲያንቀሳቅሱ በችግሩ፣ በስስ ብልቱ፣ በቅንነቱ፣ በደግነቱ ኪሳራ አሰባሰቡበት።
ትኩረት የምሰጠው ፊተኞቹ ላይ አይደለም። ኋለኞቹ እስከዛሬ የገዙትን ነው። እነዚህ ስልጣን ጥመኞች፣ ቅጥረኞችና ባንዳዎች የምላቸው የትግራይን ስስ ብልት በመነካካት እነርሱ ሳይነኩ ሥልጣን ያዙ። የእኔን ወንድም ሰለሞን አለማየሁ የሚባለውን ጨምሮ ብዙዎች በረሃ ላይ ቀሩ።
ከእዚያ በኋላ ትግራይ ላይ ከተገባ በኋላ የእነርሱ ዘር፣ አሽቃባጭ፣ ተላላኪና ዘራፊ ብቃት የሌላቸውን አሰባሰቡ። ብቃት ያላቸውንና የአገር ፍቅር ያላቸውን እንደመቅጠር በምትኩ ብቃት የሌላቸው ተላላኪዎችን አሰለፉ። በግልጽ እኮም ተናግረዋል።
ነፍሳቸውን ይማርና አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ወይዘሮ ገነት ዘውዴ ትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ያቀረቡት ሃሳብ ከስር መሰረቱ ጠለቅ ብለሽ ከመረመርሽው ወይንም በትምህርት ዝግጅት አልቀጥርም፣ ሥልጣን የምሰጠው የኢህአዴግን አላማ እስካስፈጸመ ነው።
በአገር መሪ ደረጃ ብዙ ያነባል፣ ያውቃል ተብሎ የሚነገርለት ነው። ለነገሩ የውጭ አገር ሰዎች የሚያደንቁሽ የእነርሱን ፖሊሲና ፍላጎት ካሳካሽላቸው የምትደነቂ ነሽ። ብሔር ብሔረሰበ ክፍፍል እኮ ጣሊያን በአራት ቦታ ከፋፍሎ ነው የሄደው።
ጣሊያን ሌሎቹም 32 ዓለም አቀፍ ጦርነቶቹ የተከላከልናቸውና ነፃነታችንን ጠብቀን የኖርነው በመሣሪያ ብዛት አይደለም። በአገር ፍቅር ስሜት፣ በወኔ ነው። ከእነዚህ ታሪካዊ 32 ጦርነቶች በየቦታው ታክቲካዊ ማፈግፈግ የተደረገባቸው ስምንት ብቻ ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በጠብመንጃም፤ በሮኬትም አልቻሉንም። የገዛ ልጆቻችን ቀጠሩና በነፃትና በዴሞክራሲ ስም ላኳቸው።
ብዙ ሰዎች መለስን የገደሉት ኢምፔያሊስቶች ናቸው ይሉኛል። ለምንድን ነው የሚገድሉት?። እንደ መለስ በኢትዮጵያ ላይ የፈለጉትን ያስፈጸመላቸው አለ እንዴ? እንደወያኔ ኢህአዴግ ያስፈጸመላቸው ሰው አለእንዴ? ትናንትናም ዛሬም የሚታገሉት ለገዛ ጥቅማቸውና ሥልጣናቸው ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይናቸው እያየ አካሉ የጎደለ፣ ፈንጂ የረገጠ፣ በአውሮፕላን ጭንቅላቱ የተመታውን የትግራይን ሕዝብ አልረዱትም። በጣም የሚገርምሽ ነገር በረሃብተኞች ኪሳራ የኖሩ ናቸው። በረሃብተኞች ሀብት የፈጠሩ ናቸው። ስለዚህ የትኛው አገር መልዕክተኞች እንደሆኑ ነው እንጂ የማላውቀው ቅጥረኞች ናቸው። ቅጥረኞች ስለሆኑ፣ በሥልጣን ለመቆየት የሚፈልጉ፣ የሚዘርፉ የስብሃት ስርወ መንግሥት ገንብተው የነበሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች የራሳቸው ስርወ መንግሥት ሲያጠናክሩ የኖሩ ናቸው።
አንደኛ በባህሪያቸው ሲታዩም ለአገር ቀርቶ ለተወለዱበት አካባቢ ሕዝብም የማይጠቅሙ ናቸው። ስብሃት ነጋ አሁን እንኳን ፍርድቤት ገብቶ በእንግሊዝኛ ነው የምናገረው አለ። በረሃብተኞች ኪሳራ በተመሳሳይ ለሕዝብና ለአገር ያለውን ንቀት እንደልቡ ሲናገር ነበር። የኢትዮጵያ ታሪክ የትግራይ ታሪክ እያላችሁ አትጨቅጭቁን ነው ያለው።
በእሱ እምነት በኢትዮጵያም ሆነ በትግራይ ከ1968 ዓ.ም ነው ታሪክ መሰራት የተጀመረው፤ ይህንንም ይናገራል። ይህም በኢትዮጵያ ላይ ያለው ጥላቻ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ያሳያል።
ሁለተኛ ትግራይ ልማት ድርጅቶችና ኢፈርት ኩባያዎች ለሕዝብ በአክሲዮን ይሸጥ ሲባል ሕዝብ ምን አገባው አለ። የወያኔም አይደለም አለ። ይሄ በሚዲያ የወጣ ነው የምነግርሽ። እነዚህ ድርጅቶች የሥራ አስፈፃሚው ብቻ በመሆናቸው ከእኔ የምታገኙት ነገር የለም በሚል ነው ምላሽ የሰጠው።
ሌላው ግን ሃሳቡን እንዲገልፅ አይፈለግም፤ አንዲገደልና እንዲጠፋ ያስደርገዋል። እሱ ሲናገር ማንም ‹‹ሃይ!›› የሚለው የለም። ከእድገት እስከሽምግልና የማይለወጥ መጥፎ ማንነት ያለው ሰው ነው።
በጣምያዘንኩትና የተገረምኩት ያን ሁሉ በደልና ምዝበራ በሕዝብና በአገር ላይ ሲፈፅም ኖሮ በቀደም ከዚያ ገደል ውስጥ በመከላከያ ኃይላችን ሲያዝ አትግደሉኝ ማለቱ ነው።
ዕድሜ ልኩን ሊኖር ይፈልጋል። ሰዎችንም አስገድሎ፤ የገዛ ልጁ ሞቶበትም አሁንም የራሱ ሕይወት ነው የሚያሳስበው። ይህ ሰዎች በዕድሜ አዛውንት ቢሆንም ከራሱ በቀር ለማንም የማያስብ፣ ግለኛ እና ሴሰኛ ስስታም ነው። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በአንድ ጀንበር ሙልጭ ብሎ ቢያድር ጉዳዩ አይደለም።
ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ቅጥረኞች በመሆናቸው ትውልዱ የአገሩን ታሪክ አውቆና ለአገሩና ሕዝቡ ፍቅር ኖሮት እንዲያድግ አይፈልጉም። ለዚህም ነው ባለፉት 27 ዓመታት የተንሻፈፈና እርስበርስ የሚያባላንን ሃሰተኛ ትርክት እየተመገበ እንዲያድግ የተደረገው። አሁን ላይ እኮ አንደእነሱ ምኞት የዓለምአቀፍ ጠላቶቻችን መናኸሪያ ሆና፣ ኢትዮጵያውያን ተበታትነን ማየት ነበር ናፍቆታቸው።
ፈጣሪ ክብሩ ይስፋና እንደምኞታቸው አልሆን። አገራችን ኢትዮጵያ ተደጋሚና አስከፊ አደጋ ቢያጋጥማትም በፈጣሪ እርዳታና በሕዝባ የማይነጥፍ ወኔ ዛሬም እንደጥንቱ በህብረት ከገባንበት ለመውጣት እየታተርን ነው።
እንዴት አንድ ሰው የወላጆቹን ቤት ለማፍረስ በዚህ ልክ ለክፋት ይተጋል? ለዚያውም የኢትዮጵያ ታሪክ እምብርት ከሆነች አገር የወጡ፣ በኢትዮጵያዊ ባህል ያደጉ፣ ኢትዮጵውያን የቀለበቻቸው፣ ያስተማሯዋቸው፣ ለዚህ ያደረሳቸው እንደዚህ ዓይነት ክህደት ሊገባኝ አይችልም። ከየት እንደመጣ፤ ከማን እንደወረሱት፣ እዚህች አገር ላይ ከሌላው በተለየ ምንስ እንደተበደሉ አላውቅም። ማን ምንስ ቢደርስበት ነው ይህንን ያክል አገርን ክዶ ቅጥረኛ እስከመሆን የሚደርሰው?
ተበድለው ቢሆን እንኳ ከክፋት እኮ ደግነት መስራት ይቀላል። ስለዚህ ይህ ባህሪያቸው የሥልጣን ጥመኝነታቸውን ነው የሚያሳየው። በትግራይ ምድር በትምህርቱ ረገድ ካለእነሱ በላይ አዋቂ አልነበረም። ግን በየጉራንጉሩ አሉ። ግን እነዚህ ሰዎች ለአገራቸው ቀንዓዊ ስለነበሩ አይፈለጉም ነበር።
ከአገር እንዲሰደዱና እንዲጠፉ ነበር ሲደረጉ የነበሩት። ሌላው ይቅርና ዕድል ገጥሞሽ ገበሬውን ብታናግሪ ከእነሱ የላቀ ልበ ብርሃን ሆኖ ነው የምታገኚው። ግን «ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ጠቢቡ ሰለሞን» የእነሱ ገበና አሁን ላይ ገሃድ ወጥቷል። ፀሐይ ሞቆታል። ለዘመናት እናቶች ሲያነቡ የነበሩት እምባ አንድ ቀን ይደርቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ፖለቲካ በታሪክ ላይ ሲቆምር በመኖሩ ምክንያት ቢያንስ አንድ ትውልድ ጠፍቷል የሚሉ የታሪክ ሰዎች አሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ተስፋዬ፡- እውነት ነው። እንዲያውም ከወደፊቱ የተበደርነውና ያበላሸነው ትውልድ እንዳለም ነው የማምነው። ምክንያቱም የፖለቲካ ቁማሩን ለወደፊትም እንዲተርፍ አድርገን ነው የቆመርነው። ጥቂት የማይባው አዲሱ ትውልድ ሆድ አደር እንዲሆን ነው አድርገው የቀረፁት።
ይህም ማለት አንቺ የእኔ የፈጠራ ትርክት ተቀባይ ከሆንሽ ለዘላለም በባርነት ስር እንድትኖሪ ነው ያደረኩሽ ማለት ነው። ያ የሃሰት ትርክት ደግሞ ያለገንዘብና መደለያ ሆኖ ማንም አይቀበላቸውም ነበር። ሥራ አጡም፣ የተቸገረውም፣ በረንዳ አዳሪውንም በገንዘባቸው ገዝተው የሃሰት ትርክት ባሪያቸው አድርገውታል።
ድህነት እኮ መከራ ነው። ድህነት ሳትፈልጊው ባርነት ውስጥ ይከትሻል። ድህነት ፈሪና ስጉ ያደርግሻል። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች አሁን ላይ በየቦታው ያሰማሩት በገንዘባቸው የገዙት ነው። እነዚህ እኮ ባህልና ወግ እፍረት የማያውቁ በእህቶቻቸው ሰውነት የሚሸቅጡ ቅሌታሞች ናቸው።
አሁን ላይ ቺቺኒያ የሚባለውን ሰፈር የፈጠሩትና ሴተኛ አዳሪነት እንዲስፋፋ ያደረጉት እነዚሁ ነውር የማያውቁ የህወሓት ጁንታዎች ናቸው። ለአገርና ለወገን ስንት ትጠቅማለች የተባለች ወጣት ከዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አቋርጣ ሴተኛ አዳሪ እንድትሆን አድርገዋታል።
ስለዚህ በገንዘብ ትርክቱ እንዲሰርፅ አድርገዋል። ለገንዘብ ሳይሆን ለእውነት ያደሩት ግን በህወሓት ስርወ መንግሥት ከምድረገፅ እንዲጠፉ ተደርገዋል። በነገራችን ላይ አሁን ላይ የበለፀጉ የምንላቸው አብዛኞቹ አገራት ካለፈ ታሪካቸው ተምረው በሰሩት ሥራ ነው ውጤታማ የሆኑት።
በእኛ አገር ጨካኞች እንደነበሩ ሁሉ እንግሊዝም ሆነ ፈረንሳይ አሜሪካም ሆነ ጣሊያን አገርም ጨካኖች ነበሩ። ከሁሉ በላይ ለአገር ባደርጉት መልካም ሥራ ነው የሚታወሱት። እነሱ ያለፈውን ስህተት እያረሙና ጥንካሬውን እያስቀጠሉ እዚህ ደርሰዋል። ታሪኩንም እየፃፉ ትውልድ ቀርጸውበታል፤ አብሮነት ፈጥረውበታል።
የእኛ ፖለቲከኞች ግን በመጀመሪያ ደረጃ የኢትየጵያ ታሪክ በሚገባ አንብበው እሱን በሚመጥን፣ ማህበረሰቡን በሚመጥን ፣ የማህረሰቡን የልብ ትርታ ባዳመጠ መልኩ ፍላጎትና ራዕይ የተመሰረተ ፖለቲካ አልነበረም ሲያካሂዱ የቆዩት። ትውልድን ለበጎ ነገር ከማሰለፍ ሕዝብን ሲያባሉ፤ እርስበርስ እንጨፋጨፍና እንዲታኮስ ሲያደርጉ ነው የኖሩት። ስለዚህ ፖለቲካው በኢትዮጵያ ታሪክ አንድምታ ሊኖረው ይችላል።
ዋናውና አሁን ሊጠየቅ የሚገባው ጉዳይ በታሪክ ውስጥ ስላልተስማማን እኛ ኢትዮጵያውያን ምን እንደሆንን ነው። እየተገደልንም ሊሆን ይችላል፡፤ ነገር ግን እርስበርስ እንድንባላ፤ እንደተሴረው ሴራ ቢሆን ኖሮ እኔና አንቺ እዚህ ቁጭ ብለን ማውራት ባልቻልን ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲከኞቹ ባጠፉት እሱ እየተቀጣ፣ ፈጣሪን ጠዋት ማታ ይቅርታ እየጠየቀና እየተማፀነ ነው እየኖረ ያለው። የእኛ ሕዝብ እየተገደለም፣ እየታረደም የእኔ ሃጥያት ነው ብሎ ችግሩን ለፈጣሪ የሚሰጥ እንጂ እንደእነሱ በሃጥያት ተነክሮ በእብሪት የሚፋንን አይደለም።
በነገራችን ላይ የመከላከያ ሰራዊቱን ሲመቱት ድል እንደርጋለን ብለው እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ። ድል እንደማደርጉ ቀድሞውንም ያውቁታል። ነገር ግን የተበተነ ሕዝብ፣ የፈረሰ አገር ለመፍጠር ነው።
ያን ዓይነት ጉድጓድ ሲምሱ የኖሩት ለዚህ ነው። ዋና አላማቸውም እኛ ትግሬዎች በመሆናችን ተጠቅተናል የሚል አስተሳሰብ እንዲፈጠር ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የተነሳ ነው። ሌላው የእኛ ተገዢ ባለመሆኑ የመጣበት ነገር ብሎ በማሰብ እነሱን የሙጥኝ ብሎ፤ እንዲደግፍ በማሰብ ነው።
እንደአጠቃላይ ግን በትምህርት ሥርዓቱም ሆነ እንደአገር ታሪኩን የማያውቅ እና አገር ወዳድ የሆነ ትውልድ እንዳይፈጠር ዋነኛውን ድርሻ የያዘው ወያኔ ቢሆን ከመሰረቱ ወያኔ የሚባል አምባገነን ኃይል እንዲመጣ ያደረግነው በገዛ ፈቃዳችን ነው። እኛ እርስበርስ ባለ መደማመጣችንና ባለመግባባታችን ነው፤ ይሄ ክፉ ኃይል እንደፈለገ እንዲናኝብን ዕድል የሰጠነው። በዚህ መልኩ ነው እኔ የማቸው።
አዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ ከተፈለገ ፖለቲካ ለታሪክ ቦታን መልቀቅ አለበት የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ይህስ በእርስዎ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት አለው?
አቶ ተስፋዬ፡– እኔ በዚህ ሃሳብ አልሰማማም። ምክንያቱም ሁለቱም አብረው ሊጓዙ የሚችሉ ነገሮች ናቸው ብዬ ስለማምን ነው። ፖለቲካ ከታች ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በሳይንሳዊ መንገድ ማስተዳደር ማለት ነው። ሁላችንም ገዢ ልንሆን አንችልም። ከተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ ፍትህ የሚሰጥበት፣ ልማት የሚመጣበት አስተዳደር የሚዋቀርበት ፖለቲካው ነው።
በተመሳሳይ ያለታሪክ በፖለቲካ ብቻ መኖር አንችልም። አሁንም ደግሜ መናገር የምፈልገው ፖለቲከኞቹ ይወገዱ፣ ቦታን ይልቀቁ ሳይሆን ታሪካቸውን አውቀው ያስተዳድሩን ነው። ምክንያቱም የታሪክ ሰዎች ሊያስተዳድሩን አይችሉም። ሁለቱ አካላት አንዱ ለአንዱ አጋዥ እንጂ ባላንጣ አለመሆኑን መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው።
በተጨማሪም በአገራቸው ታሪክ ላይ ተሟግተውም ሆነ ከልሰው አንድ መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው ባይ ነኝ። ይሄ ነው የኢትዮጵያ ታሪክ ብለው ሦስተኛ ታሪክ ሊያሳዩን ይገባል። ራሳቸው ሚዛናዊ ሆነው ያሳዩን። ነገር ግን ፖለቲካው ለታሪክ ቦታ መልቀቅ አለበት የሚለው አስተሳሰብ የማያዋጣን ነው።
ሊሆንም የማይችል ነው። ስለዚህ ታሪካችን ለነገው እኛነታችን ወሳኝ በመሆኑ ታሪክ ጸሐፊው ያስፈልገናል፣ አገር ለማስተዳደርም ፖለቲካው ይኑርልን። ምክንያቱም እያንዳንዱ የራሱ ፀጋና ሥራ አለው። አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፖለቲከኛውም ሆነ የታሪክ ምሁራን ጽንፍ ረገጠው ተፋጠዋል።
30 እና 40 ዩኒቨርሲቲ ቢገነባም ምሁራንን የሚያዳምጥ ብቃት ያለው ተማሪ ማፍራት አልቻሉም። ስለዚህ ፖለቲካው ለታሪክ ቦታ ይልቀቅ ሳይሆን ከምሁራንና ከሳይንስ ጋር ይታረቅ ነው። እዚህም እዚያም ዩኒቨርሲቲ ገነባሁ እያሉ ድንጋይ መከመር ምንም ዋጋ የለውም። ሁሉም በየአካበቢው ያለውን ፀጋ ማወቅ መቻል አለበት።
ከደሃ እናቶች ተነጥቆ የተገነባ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ለድሀ እናቶቻችን የሚበጅ ሥራ ለመስራት መትጋት ይኖርበታል። አገራዊ ፋይዳና ዋጋ ያለው ውጤት ማምጣት ከእነዚህ አካላት ይጠበቃል። እኛ እንዳንፋታ ሆነን ነው የተፈጠርነው። ብናስብም እንኳ አንዳችን ካንዳችን ልንነጣጠል አንችልም።
አዲስ ዘመን፡- የለውጡ መምጣትና የጁንታው መወገድ በተለይ ለትግራይ ሕዝብ ምን ዓይነት በጎ አንድምታ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ተስፋዬ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ክስተቱ በተለይ ለትግራይ ሕዝብ ትንሳኤ ነው። ጁንታው ለዘመናት በከርሰ መቃብሬ ካልሆነ በስተቀር ከእኔ ወዲህ ሌላ ስልጣን አይዝም ሲል እንደፎከረው ሁሉ የተመኘውን አላጣም። ትግራይ ውስጥ በትግርኛ ‹‹እግዚአብሔር ሲጣላሽ ከወያኔ ጋር ትጣያለሽ›› የሚባል አባባል ነበር።
ይህን አባባል በየቦታው ትሰሚዋለሽ። አንድ ጓኛዬን አንተ ፈሪ ስለሆንክ እኮ ነው እየተገዛህላቸው የምትኖረው ስለው ‹‹የዝንጀሮ ጥፍር የማያውቅ ውሻ እየተመመ ወደ ዝንጀሮ ይገባል›› አለኝ። ጥፍራሞች ናቸው ማለቱ ነው። ከወጡ በኋላ ያተራመሱንን፣ ያሳጡንን ንጹህ ዜጋ፣ ያስለቀሱትን እናት፣ ያለቀውን ሕፃን አስቢ፣ እጃቸው የደረሰበትን እይው። ሴራቸው ምን ያህል እንደገባቸው የሚያሳይ ነው። እኛ ካላስተዳደርናት ይቺ አገር ትፈርሳለች አሉ።
ይህ እንዳለ ሆኖ ሕዝብ ሲመክርና ሲያለቅስ፣ ገዳማት መነኮሳት ሲያነቡ፣ እስላሞች ድምጻችን ይሰማ ብለው ሲያለቅሱ በእኛ ከርሰ ምድር ነው ይሄ የምትፈልጉት ነገር የሚሆነው ነው ያሉት። ስለዚህ ትግራይን በባርነት ቁጥጥር ስር አድርገውት ስለነበረ አሁን ትልቅ ትንሳኤ ነው።
የእነዚህ ሰዎች መወገድ ለኢትዮጵያም ትልቅ ትንሳኤ ነው። በኢኮኖሚው የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የፖለቲካ አባል ሳይሆኑ የፓርቲ መዋጮ በየወሩ በግዳጅ ይከፍላሉ።
እንደ ትግራይ ሕዝብ አንድም ቀን የዕለት ገቢውን ያላገኘ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ከመጡ ጀምሮ የማህበረ ትግራይ መዋጮ፣ የሃውልት፣ የአባልነት መዋጮ፣ የቦንድ —ወዘተ ሕዝቡ በአስገዳጅ ሁኔታ ይከፍላል። ግን የፈየዱለት ነገር የለም። በስተመጨረሻው ባንኮችን ዘርፈው መሰረተ ልማት አጥፍተው ሄዱ።
እነዚህ ናቸው የሕዝብ ታጋይ ሲባሉ የነበሩት። ስለዚህ ትልቅ ትንሳኤ ነው፤ ነገር ግን አሁንም ሊነጋጋ ሲል ይመሻል እንደሚባለው፣ እየሞቱም ስለሆነ እንኳ እነርሱ ዶሮ፣ በግም ፍየልም ልታርጂው ስትይ ይንፈራገጣል። ይሄ የመፈራገጥ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ተስፋ አጭራለች። ሚዛናችን መጠበቅ የእኛ የልጆቿ ጉዳይ ነው። ካለፈው መማር ከጁንታው መማር ካልቻልን ተስፋ የለንም። መቶ በመቶ ይሄ ለውጥ ይሳካል ብዬ አምናለሁ።
አጋነንክ እንዳትይኝ እንጂ ሚሊዮን ጊዜ ይሳካል። ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል እንደሚባለው እያንዳንዳችን እንዳያመልጠን ከግል ጥቅማችን አንጻር ሳይሆን ሀገር ለልጅ ልጆቻችን እንዲተላለፍ፣ ውርሳችን ትክክለኛ እንዲሆን ከማሰብ አንጻር የምንደማመጥ፣ የምንከባበር፣ የምንነጋገር፣ ከዚህም የምንከስረው ነገር እንደሌለ ስናውቅ ይህች አገር ትቀጥላለች። እነዚህ ሰዎች የእኛ አይደሉም፤ የእኛ ስህተት ድምር ውጤቶች ናቸው። በአዲስ ኃይል፣ ምዕራፍ፣ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይኖርብናል።
ትችት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የሚሰራውን ካከበረ፣ ካፈቀረ፣ ሰዓቱን ካከበረ፣ ባግባቡ ሰርቶ ከወጣ መልካም ነው። ከሕዝብ እና ከመንግሥት ጊዜ እየሰረቁ፣ ገንዘብ እየሰረቁ ከጂ ሆነው አገሬ አገሬ ማለት ምንም አይጠቀውምም። ተግባራዊ ርምጃዎቻችን የአገራችንን ችግር የሚፈቱ፣ የወደፊትን ብሩህ ተስፋ የሚያሳዩ፣ ብልጽና የሚያመጡ መሆን አለባቸው።
እያንዳንዱ ከጂ ሆኖ፣ እያንዳንዱ ፖለቲከኛ ሆኖ አያዛልቅም። በአብዛኛው በንግዱ፣ በህክምናው፣ በትምህርቱ፣ በትራንስፖርት ዓለም እየተጨቆንን እኮ ነው። ለአገራዊ ፋይዳ የሚጠቅሙ ሥራዎችን እየሰራን አይደለን። ነጋዴው ይሄ ገንዘብ ምንም ይሁን ምን የኔ ካልሆነ ብሎ ካላግባብ የሚበዘብዝ ከሆነ፣ አገልግሎት ሰጪው ንጉስነትሽን ረስቶ እኔ ብቻ ንጉስ ልሁን ካለ በየዘርፉ እይው —ምን ይዞብን እንደሚመጣ አስቢው ?
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ ችግሮች ተጋርጠውበታል፤ ችግሩን ለመሻገር ምን ይጠበቅበታል?
አቶ ተስፋዬ፡– ከባድ ፈተና ነው ያለበት። ሕዝቡ ከቆየበት ሁኔታ፣ አሁን በተፈጸመ፣ ትናንትም ድህነት ላይ ነው ያለው አሁን ይሄንን ጨምረውበት ሲሄዱ ድርቅ አለ ድህነት አለ። በትግራይ የመሰረተ ልማት፣ የግብርና፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የውሃ ልማት መረጃ ሙልጭ አድርገው አቃጥለው ነው የሄዱት።
የተለያዩ የደንብ ልብሶችን አምርተውና በትነው በመሄዳቸው ትግራይ በጠራራ ፀሐይ ሴት ልጅ የምትደፈርበት፣ ማጅራት የሚመታበት፣ ንብረት የሚዘረፍበት ሆኗል። እስረኞችን ለቅቀው ነው የሄዱት። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ አገር ያሉትን እያስፈታ ሲመጣና በአገር ውስጥ ያሉትን ሲያስፈታ ትግራይ ውስጥ በሦስት ዓመት የተፈታ እስረኛ አልነበረም።
እስረኞችን ፈትተው ትግራይ ሕዝብ እየተዘረፈ ነው። አሁን ትንሽ እየተሻሻለ ነው። የትግራይ ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእዚህ ጁንታ ይላቀቃሉ ብዬ ዕድሜ ልኬን ስታገል ስናገር በሌላ ጁንታ እንዲተኩ አይደለም።
የመንግሥትንም ሥራ የሚያበላሽ ጁንታው ነው፣ ጸጥታን የሚያደፈርስም ጁንታው ነው። አሁን ያለው አስተዳደርም እጥረት አለበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሊረባረብ ይገባል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ድሎች ተጎናጽፋለች፤ ከብዙ ድሎቿ በኋላ ግን ብዙ ድሎችን መፈጸም አልቻችም። ድል መጥቷል፣ ለትግራይ ሕዝብ ትንሳኤ ነው።
ግን በቶሎ በሁሉም መንገድ ካልደረስንለት እንደገና እነርሱ ወደፈለጉት መስመር እንዳይሄድ ወይንም እንዳይሳብ እሰጋለሁ። ስለዚህ መንግሥት አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ አለበት። በትግራይ ኢትዮጵያዊነት የሚያምን ሁሉ ተረባርቦ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሊተባበር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ተስፋዬ፡- እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ! ክብረት ይስጥልኝ።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013