የቤተሰብ እቅድ ሁለት ጥንዶች መቼ እና ስንት ልጅ መውለድ እንዳለባቸው ለመወሰን የሚያስችላቸው መንገድ ነው። ይህም የልጆችን ቁጥር መወሰንና በልጆቹ መካከል ሊኖር የሚችለውን የዕድሜ ርቀት ይጨምራል። የቤተሰብ እቅድ የስነ ተዋልዶ ጤናንም ያበረታታል። የቤተሰብን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ጉዳዮችን አቅዶ ለመንቀሳቀስ ያግዛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሴቶችንና የልጆችን ሕይወት ከመታደግ ባለፈ ጤናቸውንና ደህንነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በመጠነ ሰፊና የረጅም ግዜ ጥቅሙ ምክንያት የተነሳ በቤተሰብ እቅድ ሴቶች፣ ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ማሕረሰብና ሀገርም ጭምር ተጠቃሚ ይሆናል። ለዛም ነው ብዙ ሀገራት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን በስፋት ጥቅም ላይ እያዋሉ የሚገኙት።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ውጤታማ በማድረግ ረገድ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀመው የወሊድ መከላከያ ነው። የወሊድ መከላከያዎች እርግዝናን ለመከላከል የሚጠቅሙ ዘዴዎች ሲሆኑ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች፣ ኮንዶም፣ በክንድና በማሕፀን የሚቀመጡ እንዲሁም ተፈጥሯዊ የወር አበባ ኡደትን ተከትሎ ተግባራዊ የሚሆኑ ናቸው። ከዚህ አንፃር የወሊድ መከላከያዎች እንደ አንድ የቤተሰብ ዕቅድ መሳሪያና ውጤታማ የጤና ኢንቨስትመንት ሆነው ይቆጠራሉ። በዚህም የተነሳ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የወሊድ መከላከያ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
እንዲያም ሆኖ ግን ከቤተሰብ እቅድ ጋር በተለይም ከእርግዝና መከላከያ ጋር በተያያዘ አሁንም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የተዛቡ አመለካከቶች አሉ። ለምሳሌ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት መካንነትን ያስከትላል፣ የእርግዝና መከላከያ የወሲብ ፍላጎትን ይቀንሳል፣ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች በሠውነት ውስጥ ተከማችተው የጤና ጉዳት ያስከትላሉ የሚሉና ሌሎችም የተዛቡ አመለካከቶች በማሕበረሰቡ ውስጥ በስፋት ይደመጣሉ።
ምንም እንኳን እርግዝናና ወሊድ ተፈጥሯዊ ቢሆንም አንዳንዴ በተለያዩ ምክንያቶች በሴቶችና በልጆቻቸው ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በቅርብ የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 ከመቶ የሚሆኑት እርግዝናዎች የሚከሰቱት ሳይታቀዱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 22 ከመቶ ያህሉ ባልተፈለገ ውርጃ የሚጠናቀቁ ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2023 ባወጣው ጥናት መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ2015 እስከ 2019 ድረስ 121 ሚሊዮን ያልተፈለጉ እርግዝናዎች ተከስተዋል። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 61 ከመቶው ባልተፈለገ ውርጃ ተጠናቋል። በኢትዮጵያም እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2019 ድረስ 4 ሺ 920 እርግዝናዎች በየዓመቱ ተከስተዋል። ከእነዚህ መካከል 2 ሺ 60 ያህሉ ያልተፈለጉ ወይም ያልታቀዱ እርግዝናዎች ናቸው። 632 ሺ ያህሎቹ ደግሞ ባልተፈለገ ውርጃ የተጠናቀቁ ናቸው።
ስለአልተፈለገ እርግዝና ሲነሳ ታዲያ በቀዳሚነት ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትና የወሊድ መከላከያ ነው። ምክንያቱም አብዛኛው ያልተፈለገ እርግዝና የሚከሰተው የቤተሰብ ዕቅድንና የእርግዝና መከላከያን በአግባቡ ባለመጠቀም ነው። ይህ ችግር ደግሞ ከግንዛቤና አመለካከት ማነስ ይመነጫል። ይኸው ችግር ዛሬም ድረስ የቀጠለ መሆኑ ይነገራል።
በጤና ሚኒስቴር የቤተሰብ ዕቅድ፣ ስነ ተዋልዶ ጤና፣ የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ገነት ድረስ እንደሚናገሩት፤ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2023 ባወጣው ጥናት መሰረት 121 ሚሊዮን ያልተፈለጉ እርግዝናዎች ተከስተዋል። ይህ ቁጥር በአብዛኛው የሚያመለከተው ኢትዮጵያን ጨምሮ ገና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ነው። በነዚህ ሀገራት በቂ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ባለመኖሩ፣ የግንዛቤ እጥረት፣ ሴቶች የትምህርት እድል አለማግኘት፣ ያለእድሜ ጋብቻና ሌሎችም ችግሮች በመኖራቸው ያልተፈለገ እርግዝና በከፍተኛ ቁጥር ይከሰታል። ያልተፈለገ ውርጃ ይስፋፋል።
በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከሚከሰቱ እርግዝናዎች መካከል አብዛኛዎቹ ያልታቀዱና በወጣቶች ላይ የሚታዩ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚጠናቀቁትም ባልተፈለገ ውርጃ ነው። ለዚህ ችግር ዋነኛ መንስዔዎች ደግሞ በወጣቶቹ በኩል ሰፊ የእውቀት ክፍተት መኖር፣ የቤተሰብ እቅድና የጤና አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን፣ በሕብረተሰብ በኩል የተዘባ አመለካከት መኖር ናቸው። በመሆኑም በተለይ ወጣት ሴቶች ያልታቀደ እርግዝና ይገጥማቸዋል።
ወጣቶች እድሜያቸው ገና እንደመሆኑ ያልታቀደ እርግዝና ሲገጥማቸው በቤተሰባቸውና በማሕበረሰቡ በኩል ተቀባይነት አይኖራቸውም። ስለዚህ ወደ አልተፈለገ ውርጃ ያመራሉ። ይህም ሕይወታቸውን እስከማሳጣት ሊያደርሳቸው ይችላል። በቂ እውቀትና ግንዛቤ ቢኖራቸው ግብረ ስጋ ግንኙነት ሲኖር እርግዝና እንደሚፈጠር ካወቁ ግንኙነት ከማድረግ ሊቆጠቡ ይችላሉ። ካደረጉ ደግሞ እርግዝናን በምን መከላከል እንዳለባቸው ግንዛቤው ካላቸው እርግዝናን መከላከልና ራሳቸውን መጠበቅ ይችላሉ። ነገር ግን በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባሕልና ሃይማኖት ተፅእኖ ተጨምሮበት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነቱና የእውቀቱ ደረጃ ያን ያህል አይደለም። ከዚህ አንፃር በርካታ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል።
ባለሞያዋ እንደሚያስረዱት፤ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነትና የእውቀት ደረጃ ከክልል ክልል ይለያያል። እንደየክልሉ ባሕል፣ እምነትና የእውቀት ደረጃ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ በጤና ሚኒስቴር በኩል እየተከናወነ ነው። ምክንያቱም ስለ ቤተሰብ ምጣኔ እውቀቱ ኖሮ አገልግሎቱ ከሌለ ጥቅም ስለማይኖረው ነው። በተቃራኒው አገልግሎቱ ቀርቦ እውቀት ከሌለ ደግሞ ተጠቃሚዎች ላይመጡ ይችላሉ። የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት መንግስት ለመድሃኒቶች ከፍተኛ ዋጋ እያወጣ ለሕብረተሰቡ በነፃ የሚያቀርበው አገልግሎት ጭምር ነው። በመሆኑም ተደራሽነትንና ግንዛቤን ማጣጣም ያስፈልጋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ራሱን የቻለ የእናቶች ስራ ክፍል በጤና ሚኒስቴር ተቋቁሟል። ከእርግዝና፣ ከወሊድና ከወሊድ በኋላ ያለው አገልግሎት ምን ምን እንደሚያስፈልግ የሚሰራ ክፍል አለ። ለምሳሌ አንድ እናት ሳታቅድ ማርገዝ የለባትም። ማሕፀኗ ለእርግዝና መዘጋጀት አለበት። የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አለባት። ሌሎች ዝግጅቶችም ያስፈልጋታል። ይሄ ከእርግዝና በፊት የምታገኘው አገልግሎት ነው። ካረገዘች በኋላ ደግሞ እስክትወልድ ድረስ ለስምንት ግዜ ያህል የእርግዝና ክትትል ታደርጋለች። በዚህ የእርግዝና ወቅት በምታደርገው ክትትል በወሊድ ግዜ ብዙ ደም እንዳይፈሳትና በፅንስ አፈጣጠር ላይ ችግር እንዳይፈጠር መድሃኒቶችን ትወስዳለች። ልትውልድ ስትል ደግሞ በሰለጠነ ባለሞያ አገልግሎቱን ማግኘት አለባት። ከወለደች በኋላም ክትባት ይወስዳሉ፤ ሌሎችም አገልግሎቶችን ማግኘት ትችላለች። የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚም ትሆናለች።
አንድ ልጅ ከወለደች በኋላ ሌላ ልጅ ለመድገም መራራቅ አለበት። ምክንያቱም በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ቀናት የተወለደው ልጅ ጡት በመጥባትና ስድስት ወር ላይ ደግሞ ተጨማሪ ምግብ እየተመገበ የአእምሮ እድገት እንዲኖረው ስራ መስራት ስለሚያስፈልግ ነው። ይህን በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ የእናቶችና የልጆችን ሞት መቀነስ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ያስፈልጋል።
እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በሕፃኑ የአእምሮ እድገት ላይ ስራ ይሰራል። ከዚህ በኋላ ደግሞ በአፍላ ወጣቶች ላይ የስነ ተዋልዶ ጤና ስራ ይሰራል። በአመጋገብ ዙሪያም በተለያየ የእድሜ ደረጃ ትምህርት ይሰጣል። አስራ ስምንት ዓመት እድሜ ሲደርሱና በተለይ ሴቶች መውለድ ሲፈልጉ ደግሞ የቤተሰብ አቅድ እና የጤና አገልግሎት ከቅድመ እርግዝና አንስቶ እስከ ወሊድ ድረስ ያገኛሉ።
አንድ ሰው ምንም አይነት እውቀትና ግንዛቤ ሳያገኝ የባሕሪ ለውጥ ማምጣት እንዲሁም የእናትና ልጅ ሞትን መቀነስ አይቻልም። ያልተፈለገ እርግዝናና ውርጃንም መከላከል አዳጋች ነው። ስለዚህ በተለይ ወጣቶች በቤተሰብ እቅድና በእርግዝና መከላከከያ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙና ይህን አውቀው ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰፊ ስራ መስራት ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ በተለይ የመገናኛ ብዙሀን ትልቅ ድርሻ አለው። በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከቤተሰብ ዕቅድ ጋር በተያያዘ ትክክለኛና ታማኝ መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ በማቅረብ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት ማስተካከል ይቻላል።
ስለዚህ የሕብረተሰቡ ግንዛቤ ባደገ ቁጥር መብቱን መጠየቅ ይጀምራል። የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቱ ያስፈልገኛል ብሎ ለሚጠይቅ ሕብረተሰብ በአካባቢውና በቅርበት ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል። አገልግሎቱን ካላገኘ ደግሞ ለሚመለከተው አካል የመጠየቅ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። በዚህ አይነት መልኩ ሕብረተሰቡን የመቀስቀስ፣ የማስተማር፣ ግንዛቤ የመፍጠር የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊነት አለባቸው።
በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ዙሪያ ለማሕበረሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተለያዩ ስራዎች በተለያየ መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከጎሳ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ለሕብረተሰቡ ወሳኝ የሆኑ የፖለቲካ አመራሮችና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚገኙባቸው እስከ ቀበሌ ድረስ የሚደርሱ የሕብረተሰብ የውይይት መድረኮች አሉ። እነሱን ያማከለ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ይዘጋጃሉ። እያንዳንዱ የፓርላማ አባል በተመረጠበት አካባቢ በመሄድ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ማሕበረሰቡ እንዲጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫና የውትወታ ስራ ይሰራል።
የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በመንግስት ብቻ ሳይሆን በግሉ ዘርፍም ጭምር እየተሰጠ ይገኛል። አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ጤና ተቋማት ተስፋፍተዋል። በዚህም በርካታ ስራዎች ተሰርተው ውጤቶች ተመዝግቧል። በ2000 ዓ.ም የነበረው የ8 ከመቶ የእርግዝና መከላከያ ተጠቃሚነት አሁን ላይ ወደ 36 ከመቶ ከፍ ማለት ተችሏል። ይህም በሕብረተሰቡ በኩል የግንዛቤ ለውጥ መምጣቱን ይጠቁማል። ሆኖም ግን እአአ በ2030 የእርግዝና መከላከያ ተጠቃሚነትን ወደ 55 ከመቶ ለማድረስ ሰፊ ስራ መስራት ይጠይቃል።
በአንፃሩ የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶች በአንድ አካባቢዎች ላይ እጥረት ያጋጥማል። ይህም ካለው ፍላጎት ጋር ሳይጣጣም ይቀራል። በየዓመቱም እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ለመድሃኒት ግዢ ወጪ ይደረጋል። ይህን ወጪ የሚሸፈነው በመንግስት ነው። ስለዚህ ማሕበረሰቡ አገልግሎቱን በአግባቡ መጠቀም ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም