የሞተር ስፖርትን ወደ ቀድሞ ዝናው የመመለስ ጥረት

የሞተር ስፖርት በኢትዮጵያ ቀደምትና ግማሽ ክፍለ ዘመን ካስቆጠሩት ጥቂት ስፖርቶች አንዱ ነው። የሞተር ስፖርት ውድድሮች በኢትዮጵያ በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ በውጪ ሀገር ዲፕሎማቶች አማካኝነት ይካሄዱ እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለያየ መልኩ በአዲስ አበባና በአንዳንድ አካባቢዎች ተደራጅቶም ይካሄድም ነበር። በአሶሴሽን ተደራጅቶ እንቅስቃሴ ከጀመረም ስድስት አስርተ ዓመታትን ሊያስቆጥር የወራት እድሜ ብቻ ይቀሩታል።

በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ አሁን የሚገኝበት ደረጃ የደረሰው የኢትዮጵያ የሞተር ስፖርት እንቅስቃሴ ዛሬም በብዙ እንቅፋቶች ሲፈተን ይታያል። ስፖርቱ በባሕሪው ከአንዳንድ ሀገር አቀፍ ሕጎች፣ ከማዘውተሪያ ስፍራ እጥረትና በፖሊሲ ማነቆዎች ምክንያት የአንጋፋነቱን ያህል ማደግ እንዳልቻለ ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ። የሞተር ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅና ቢሊዮን ዶላሮች የሚንቀሳቀሱበት ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ተቀዛቅዞና ተዘውታሪነቱ ቀንሶ ይገኛል።

ስፖርቱ ከውጪ በሚገቡ ተሽከርካሪዎችና የመለዋወጫ ቁሳቁሶች የሚፈልግ እንደመሆኑ ጠንካራ ፋይናንስ ይሻል። ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት ተሽከርካሪዎችንና መለዋወጫዎችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው ለስፖርቱ ለመጠቀም ደግሞ ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ሕጎች ይፈተናሉ። ይህን ቢያልፉም ከማዘውተሪያ ስፍራ ጋር የተያያዘ ሌላ ፈተና መኖሩ ስፖርቱ ሊዳከም ችሏል።

በዘርፉ በአውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግና አውቶማሪን ኢንጂነሪንግ ባለሙያነት የሠሩት የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ አዲስ ዓለማየሁ፣ ስፖርቱ አንጋፋ ቢሆንም ከባሕሪው አንጻር ውጤታማነቱንና እድገቱን የሚወስነው የግል ብቃትና ስኬት ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂ ሽግግር ጭምር መሆኑን ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ አንፃር ስፖርቱ በመንግሥታት መቀያየር ምክንያት ከቀረጥ ጋር ተያይዞ የፖሊሲ ማሻሻያዎች የተደረጉ ቢሆንም፣ አሁን ያለው ፖሊሲ ባለመከለሱ ስፖርቱ ላይ ጫና መፍጠሩን ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት በከፍተኛ ቀረጥ የመወዳደሪያ መኪናዎችንን እና ሌሎች ቁሳቁሶች ከውጪ አስገብቶ ለመወዳደር ፈታኝ ሆኗል። ይህም ስፖርቱ በተወሰነ ደረጃ እንዲቀዛቀዝ አድርጋል።

የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት በዓለም ደረጃና በተለያዩ ሀገሮች ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውና አቅም የነበረው መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ከስፖርትነቱም በላይ የኢንጂነሪንግና አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ማሳያ በመሆን የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫና በቡድን አደጋን ተከላክሎ መወዳደር የሚለካበት እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ያስረዳሉ።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፣ ከዚህ ቀደም ትልልቅ መኪና አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ድጋፍ በማድረግ ትልልቅ ውድድሮች ይካሄዱም ነበር። ነገር ግን በደርግ ዘመነ መንግሥት ስፖርቱ እንደ ቅንጦት በመታየቱ የተነሳ ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም፤ አሁንም የፖሊሲ ማሕቀፉ ባለመሻሻሉ እንቅፋት ሆኖ ይገኛል። ለስፖርቱ ፍላጎትና ፍቅር ያላቸው አካላት ትልልቅ ወጪዎችን አውጥተው የሚወዳደሩት በርካቶች ናቸው። የስፖርት መኪኖችን በከፍተኛ ወጪ ከውጪ አምጥቶ ለመወዳደር ፖሊሲው አበረታች ባለመሆኑ የተነሳ ግን እንቅስቃሴው ተቀዛቅዟል።

የስፖርት መኪናዎች ተለይተው የራሳቸው ታርጋ ወጥቶላቸው ለስፖርቱ ብቻ እንዲውሉ የሚያደርግ መመሪያና ፖሊሲ እንዲወጣለት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ የአሶሴሽኑ ቦርድ አመራር ስፖርቱን በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል እቅድ ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።

ይህም የስፖርት ማዘውተሪያና የጉምሩክ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለመፍታትና ስፖርቱን ለማሳደግ ከሚከናወኑ ሥራዎች አንዱ ቢሆንም፣ የመወዳደሪያ መኪኖች፣ ሞተር ሳይክል እና ጎሕ ካርቶች ከውጪ የሚገቡት ለስፖርት ተብሎ ከቀረጥ ነፃ ማስገባት የሚቻልበት መንገድ ባለመኖሩ አበረታች አልሆነም። ይህ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ አምጥቶ ስፖርቱን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ማነቆ በመሆኑ ይሄን ለመቀየር ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እንደሚዘጋጅ ይናገራሉ።

ስፖርቱ በዓለም ደረጃ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅስ እንደመሆኑ እንደነኬንያ ያሉ ሀገራት በዓመት አንድና ሁለት ውድድሮችን እያዘጋጁ ከበርካታ ሀገራት ተሳታፊዎች መጥተው ይወዳደራሉ። በኢትዮጵያ ግን ስፖርቱ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሆነና ትልቅ የውጪ ምንዛሪን እንደሚያመጣ ግንዛቤው አላደገም። ስለዚህም ግንዛቤ እንዲፈጠር የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። በቀጣይ በየሳምንቱ ስለ ስፖርቱ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር ኅብረተሰቡን በማስተማር ለስፖርቱ ያለውን ግንዛቤና ፍቅር ከፍ ለማድረግም ታቅዷል። በተጨማሪም ስፖርቱን ለሚመሩና ለሚወዳደሩ የአሶሴሽኑ አባላት ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎችን ለመስጠትና እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዷል። በዚህም ስፖርቱን ሌሎች ሀገራት የደረሱበት ደረጃ ለማድረስ ጥረት እንደሚደረግ ፕሬዚዳንቱ ያስረዳሉ።

የሞተር ስፖርትን ለመወዳደር መኪናውና አሽከርካሪው መሠረታዊው ነገር መሆኑን የሚጠቅሱት የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለመወዳደር ብቁ የሚያደርግ የስፖርት መኪና አለመኖርና ተሽከርካሪውን ከቀረጥ ነፃ ለማስመጣትና ለማስገባት የሚያስችል የሕግ ማሕቀፍ አለመኖሩ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ሁሉንም የአየር ንብረትና መልክዓ ምድር በመያዟና ለውድድር ምቹ በመሆኗ አሶሴሽኑ ይሄንን ችግር በመቅረፍ አሕጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት እየሠራም ይገኛል።

ውድድሮችን በሀገር ውስጥ ማካሄድ ከዓለም አቀፉ ማኅበር የቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎችን የማግኘትና መንግሥት ስፖርቱን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ድጋፍ እንዲያደርግ ተነሳሽነትን እንደሚፈጥር ይታመናል። ስለዚህም በቀጣይ አንድና ሁለት ዓመታት ስፖርቱን አሁን ካለበት ችግር በማላቀቅ ወደ ቀደመው ትልቅነቱ ተመለሶ ሀገር የሚያስጠራ ለማድረግ አሶሴሽኑ ጥረቱን ቀጥላል። አሶሴሽኑ በመጪው መጋቢት 60 ዓመት የምሥረታ በዓሉን የሚያከብር ሲሆን ዓለም አቀፍ ውድድር ለማካሄድም እቅድ አለው።

ዓለማየሁ ግዛው

 

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You