ደረሰኝ ላለመቁረጥ ይህን ያህል ጩኸት ለምን አስፈለገ ?

ግብር በመሰብሰብ ከአፍሪካ ቀዳሚዎች ነን። በሀገራችን ከአክሱማውያን ዘመን መንግስት ጀምሮ ግብር ይሰበሰብ ነበር። ግብር ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ የነበረው አበርክቶ ምን ይመስል እንደነበር ለታሪክ ባለሙያዎች እንተወውና ትናንት ለነበረው ኃያልነታችን ትልቅ አቅም ሊሆን እንደሚችል ግን ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

በዘመናዊዋ ኢትዮጵያ ግብር በመሰብሰብ ለኅብረተሰቡ የመሠረተ ልማት፤ መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ ፖሊስ ጣቢያ የመሳሰሉ ተቋማት ግንባታዎችን ማካሄድ ከምዕተ ዓመት በላይ እድሜ እንዳለው የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ። ይህም ሆኖ እስከዛሬ የግብር ስርዓቱ ፍትሀዊ እና ዘመናዊ መሆን አልቻለም።

እንደ ሀገር ግብር በትክክል እየከፈለ ያለው የመንግሥት ሠራተኛው ነው፤ ይህም መክፈል እና አለመክፈል በእሱ ውሳኔ ውስጥ ስላልሆነ፤ መንግስት በራሱ ጊዜ ቆርጦ የሚወስድበት አሰራር በመኖሩ ነው። ከዚህ ውጪ ያለው ግብር ከፋይ ዜጋ በአንድም ይሁን በሌላ የሚጠበቅበትን እየከፈለ አይደለም።

አሁን አሁን ችግሩ የሀገርን እድገት ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ ሕይወት አደጋ ውስጥ በሚከት ደረጃ ደንድኖ የመጣበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው። አብዛኛው በሚባል ደረጃ ግብር መክፈል የሚገባው ዜጋ የሚጠበቅበትን ለመክፈል ፈቃደኛ አይደለም።

ግብይቶች በደረሰኝ እንዲካሄዱ ለዓመታት በሚመለከታቸው አካላት የተለያዩ መግለጫዎች ቢወጡ፤ ሕጎች ተረቀው ተግባራዊ ቢሆኑም ችግሩ ሊፈታ አልቻለም። እንዲያውም ችግሩ የማኅበረሰቡን አጠቃላይ ሕይወት ፈተና ውስጥ መክተት የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው። ችግሩን ለመከላከል በየወቅቱ የሚደረጉ ጥረቶችም ከእነዚሁ ሕገወጦች በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮት የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በያዝነው ሕዳር መባቻ በመርካቶ አካባቢ የሚስተዋለውም ግርግር ከዚሁ እውነታ ጋር የተያያዘ፤ የመንግስትን ጥረት ለማምከን የሚደረግ የተለመደ ውንብድና ነው። የግብር አሰባሰብ ሥርዓን ለማስተካከል እየተወሰደ ያለውን እርምጃዎች ለማደናቀፍ እና እንደቀደመው ባልተገባ የንግድ ስርዓት ውስጥ ለመቆየት የሚደረግ ያልተገባ አካሄድ ነው።

የመስተዳድሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚነግሩን፤ በመርካቶ ገበያ ያለው ግብይት በአብዛኛው ያለ ደረሰኝ የሚካሄድ ነው። በተለይ ትላልቆቹ አስመጪ፣ አምራችና አከፋፋይ ነጋዴዎች ግብይታቸው ጤናማ አይደለም። ችግሩን ለመከላከል ቁጥጥር የሚያደርጉ ከሦስት እስከ አምስት አባላትን የያዙ 58 ቡድኖች በአካባቢው ተሰማርተዋል። ይህም የደረሰኝ ግብይትን መስመር ለማስያዝ እንደ አንድ የመፍትሄ መንገድ የተወሰደ።

ይህንን የመንግስት ጥረት ተከትሎም፤ በሕገወጥ ነጋዴዎች የሚነዱ ውዥንብር ነዥዎች መንግስት በመርካቶ ‹‹ንብረት ይወረሳል›› የሚል የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት በአካባቢው አለመረጋጋት ለመፍጠር ሞክረዋል፤ በዚህም እጅግ የበዙ አሉባልታዎች ተደምጠዋል። አንዳንዱም በስማ በለው የተሳሳቱ መረጃዎችን ተቀብሎ ባልተገባ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል።

ነገሩን ለማረጋጋት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በዕለቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ በመርካቶ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ከማድረግ ያለፈ ንብረት የመውረስ ዕርምጃ እንዳልተወሰደ ገልጾል፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ፤ ከዚህ በፊትም በመርካቶ በሕገወጥ ነጋዴዎችና በሕገወጥ ግብይት ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ፣ ሰሞኑን የተጀመረውን የቁጥጥር ዕርምጃ ለየት የሚያደርገው አዳዲስ ተቆጣጣሪዎች እንዲሰማሩ መደረጉ ብቻ መሆኑን አስታውቀውም ነበር።

ቀደሞ በመርካቶ ገበያ ቁጥጥር እንዲያደርጉ የተሰማሩ ተቆጣጣሪዎች ከነጋዴዎች ጋር በመላመድና ጉቦ በመቀበል ወቀሳ ይቀርብባቸው እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው። እነዚህን የቁጥጥር ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ከዚህ ሥራ እንዲወጡ በማድረግ በአዲስ መተካታቸው የሚደገፍ ነው።

በመሠረቱ እኔ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ግብርን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት ከሚያደንቁ አንዱ ነኝ። በግብር ከፋዩ ዘንድ የሚታዩ ሕገወጥነቶች የሆነ ቦታ ማንቂያ ሊኖራቸው ይገባል። ማጭበርበር ዋጋ የሚያስከፍል ሕገወጥነት መሆኑን የነጋዴው ማኅበረሰብ የሚረዳበት ጠንካራ እርምጃ ያስፈልጋል።

እዚህ ላይ ስለ ገበያ ስናነሳ ስለሸማቾች፣ ስለነጋዴዎች ስናነሳም እንዲሁ ስለደላሎች እያነሳን ስለመሆን ልብ ማለት ይገባል። ከመጣንባቸው ያልተገሩ የገበያ ስርዓቶች አኳያ ገበያችን ሥርዓት የለውም ብቻ ሳይሆን ቅጥ አምባሩ የጠፋው ነው። የተወሰኑ ነጋዴዎቻችን ደርሰው ባለፀጋ የሆኑና የከበሩ ናቸው። የቀሩት ደግሞ የእነሱን ፈር ተከትለው ለመክበር ይጥራሉ።

ማንም ሰው ነጋዴዎቻችን ነግደው ማትረፍ እንዳለባቸው ያምናል። ንግዳቸው ግን የሆነ የትርፍ ወለል ሊኖረው ይገባል። የእኛ ነጋዴዎች ግን ከዚህ በተጻራሪ የሚታሰቡና የብዙ ብዙ እጥፍ ለማትረፍ የሚተጉ ናቸው። ለኔ ወለል አልባ በሆነ የትርፍ ሕዳግ እየነገዱ ማትረፍ ንግድ አይመስለኝም። ለማትረፍ ተደራጅቶ እንደመዝረፍ ነው።

አብዛኞቹ ነጋዴዎቻችን የማትረፍ ካባ ደርበው የመዝረፍ ደባ የሚፈጽሙ ናቸው። ማሕበረሰባዊ ኃላፊነት የማይሰማቸው ከመሆናቸው የተነሳ፣ ኃይማኖት (እምነት) ያላቸው አይመስለኝም። ይህን ያህል ምን አስጨከናቸው ? የዘወትር ጥያቄዬ ነው። ከዚህ ባለፈም ግብር ላለመገበር ያላቸው ደንዳና ልብም የሚገርም ብቻ ሳይሆን የሚያበሳጭ ነው።

ችግሩ ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ፤ በግብር ሰብሳቢው ተቋም በመረጃ ማጣትና ዝርክርክነትም የተከሰተ ሊሆን ይችላል። ግን እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ፤ ነጋዴዎቻችን ይህን ያህል በገዛ ሕዝባቸው ላይ የሚያስጨክን ምን እርግማን ወረደባቸው፤ የሚሰበስቡት ሀብት ትርጉም የሚኖረው አጠቃላይ ከሆነው ሕዝብ ኑሮ ጋር ተሳስሮ ትርጉም ሲፈጥር እንደሆነ ለምን ማወቅ ተሳናቸው የሚለው ጥያቄ የኔ ብቻ እንደማይሆን እገምታለሁ።

የበለጸገው ዓለም የደረሰበት መድረስ፣ ወደ ብልጽግና ጎዳና መሮጥ የሚቻለው ግብርን በአግባቡ በዘመናዊ መንገድ መሰብሰብ ሲቻል ነው። የሠራ ሲገብር ለሀገሩ ግዴታውን እየተወጣ ነው። ለሰላምና ለደኅንነት ኃይሎች እየከፈለ ነው። መቼም በመነገድ ውስጥ መንገዳገድ አለ። ይህም ሆኖ ግን የግብር አሰባሰብ ስርዓቱ በሕገወጥነጥ ከታጠረ ይዘገያል እንጂ ሀገር እና ሕዝብን ይዞ መውደቁ የማይቀር ነው።

ነጋዴዎቻችን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ብቻ ሳይሆን የእለት ተእለት ሕገወጥ ተግባራቸውን በሀገር እና ሕዝብ ላይ ይዘውት ከተጓዙ ሊመጣ የሚችለውን ተገማች አደጋ በአግባቡ የተረዱ አይደሉም። በሕገወጥነት የሚሰበስቡትን ሀብት ለመብላት ሰላም ሊኖር እንደሚገባ፤ ሀገር እንደ ሀገር መቆም እንደሚገባት ሊረዱ ያስፈልጋል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ለዘመናት ያከማቹት ሀብት የዜሮ ድምር መሆኑ የማይቀር ነው።

ነጋዴዎቻችን መነገድ ብቻውን ግብ አለመሆኑን ማጤን ይጠበቅባቸዋል፤ በመነገድ ውስጥ ማገልገልም እንዳለ ማወቅ አለባቸው። በመነገድ ውስጥ ሰብአዊ ትርፍ እንዳለም ሊረዱ ያስፈልጋል። ሕዝቡ በማትረፍ ስም መዝረፍ በብዙ መልኩ ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው። ለሁሉም እንደ አንድ ሀገር ዜጋ ብንተሳሰብ አይሻልም ?

ለዚህ ደግሞ እዛው መርካቶ ውስጥ ውጥንቅጡ የወጣውን ኅብረተሰብ ኑሮ ማየቱ ተገቢ ነው። በድህነትና በጉስቁልና የሚሮሩ የመርካቶ ነዋሪዎች ከመርካቶም እምብዛም ያተረፉት ነገር የለም። የመርካቶው ነጋዴ መርካቶ “ እየነገደ“ ኑሮው አምሮና ሰምሮ ይኖራል። በመርካቶ ኑሯቸውን ላደረጉ የተወሰኑ ድሆች ግን ቤታቸውን አድሶ ለመሥራት፤ ኑሮዋቸውን ለመደጎም ሲንቀሳቀስ አይታይም። በዚህ ጉዳይ ላይ አንዳች የሚሰማው ኃላፊነት የለም። ከዚህም እልፍ ያሉ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል።

እንደሚታወቀው የአንድ አገር የምጣኔ ሀብቱ ዋልታና ማገሩ ግብር ነው። በግብር በኩል የሚጠበቅብንን ስንወጣ ሀገር ትጠነክራለች፤ ታድጋለች፣ ለእኛም የጋራ ብሔራዊ ክብር ምንጭ ትሆናለች። ለዚህ ደግሞ የግብር ሥርዓታችን ማዘመን ወሳኝ ነው። ሰርቶ የሚያተርፍ ዜጋ ሁሉ ከትርፉ የሚጠበቅበትን ለመንግስት መክፈል ይጠበቅበታል።

ችግሩን ለዘለቄታው ለመቅረፍ ዜጎችን የግብር መረብ ውስጥ መክተት፤ በደረሰኝ የሚገበያዩበትን ስርዓት ማበጀት የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ መስተዳድሩ አሁን ላይ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ እና ሀገርን ለማበልጸግ ከተያዘው ሀገራዊ መነቃቃት ጋር አብሮ ሊታሰብ የሚገባው ነው።

በ2009 መጋቢት አጋማሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ገቢ ማስገባት ከሚገባው አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ሁኔታውን ለመለወጥ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ የተሳካ ሥራ መሥራቱን አስታውቀው ነበር። በእርግጥም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር መረዳት እንደሚቻለው ሀገሪቱ በየዓመቱ የምታገኘው ገቢ እየጨመረ መጥቷል። ነገር ግን እንደ ሀገር የሚጠበቀውን ግብር እየሰበሰብን አይደለም። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የምናስባቸውን የልማት ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ ትልቁ ተግዳሮት መሆኑ አይቀርም።

የሀገራችን ነጋዴዎች ሀገራችን በኅልውና ዘመቻ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሳይቀር ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ ሕዝባችንን ለከፋ ችግር ለማጋለጥ የሄዱበት እውነታ የሩቅ ትዝታ አይደለም፤ በዚህ ደረጃ የሚገለጥ ያልተገባ መንገድ ላይ ቆመው ለመሄድ የሚፈልጉ ናቸው።

አሁን የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት መልክ እና ስርዓት ለማስያዝ በደረሰኝ መነገድን ነጋዴዎች ባሕል ማድረግ ይገባቸዋል። ሸማቾችም ልብስም ሆነ ቁሳቁስ ነገር ሲገዙ ደረሰኝ ጠይቆ መያዙ ይበጃቸዋል። ሰሞኑን የመርካቶ ነጋዴ በደረሰኝ መገብየት ልመድ ሲባል ለመንጫጫት የሞከሩት ለረጅም ጊዜ ያለደረሰኝ ይገበያዩ ስለነበረ ነው። ሌላ ምክንያት የለውም። ይህ ደግሞ በብዙ መልኩ አዋጥቷቸዋል።

በደረሰኝ መገበያየቱ የሕጋዊነት መጀመሪያ ነው፤ በግብይት መሀከል ሊከሰቱ የሚችሉ ሕገወጥነቶችን መከላከል ያስችላል። በደረሰኝ መገበያየት የነጋዴው መብት ሊሆን አይችልም። ነጋዴው የመነገድ መብት አለው ግን ያለ ደረሰኝ ነው የምገበያየው ብሎ ማላዘን ሸማቹን ብዘርፈው መንግሥት ምንቸገረው? እንደማለት ይመስለኛል። መንግሥት ደግሞ የሸማቹ ጉዳይ ያገባዋል። ለዚህ ነው በደረሰኝ ተገበያዩ የሚለው።

ከዚህ የሚከፋው ደግሞ መንግስት የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ እንዲቆርጡ ኃላፊነት የሰጣቸው የንግድ ተቋማት ሳይቀሩ የሰበሰቡትን ሀብት ለመንግስት ገቢ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑበት ሁኔታ መኖሩ ነው። ይህ ደግሞ የተለመደ ሕገወጥነት እየሆነ ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በአጠቃላይ አሁን ላይ የንግድ ሥርዓቱን ለዘለቄታው መስመር ለማስያዝ፣ ነጋዴዎች በደረሰኝ እንዲነግዱ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በኩል የሚደረገውን ጥረት የሚበረታታ እና የሁሉንም ነዋሪ ድጋፍ የሚጠይቅ ነው። ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ለጀመረችው ብልጽግና ጉዞም ሆነ ንግዱን ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት ስትራቴጂክ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።

ይቤ ከደጃች.ውቤ

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You