ስለ ነገ…

እዮብ…

የልጅነቱ ማገር የታሠረው ከችግር ፈተና ጋር ተጣምሮ ነው። ይህን ጥብቅ ገመድ ለመፍታት በብርቱ ሲታገል ቆይቷል። ሕይወት በየአጋጣሚው እየጣለች ብታነሳውም እጅ ሰጥቶ አያውቅም። ሁሌም የኑሮን ፈታኝ አቀበት በመውደቅ መነሳት ያልፈዋል።

አዲስ አበባ፤ ሰፈረ – ተክለሃይማኖት ለእዮብ ተወልደመድህን መኖሪያው ብቻ አልነበረም። ለእሱ መልከ ብዙ ሆኖ ይገለጻል። በዚህ ሥፍራ የልጅነት ቀለሙ ተቆጥሯል። የወጣትነት ትጋቱ ታይቷል። በጉልምስና ዕድሜው በትዳር ተባርኮ ፣ ልጅ ወልዶ የሳመው ከሰፈሩ ሳይርቅ ነው።

እዮብ በልጅነቱ የመጀመሪያ ዓመታት ደስተኛ፣ ሳቂታና ተጫዋች ነበር። ዛሬም የዛኔውን ሕይወት በመልካም ያስበዋል። በጊዜው ከቤተሰቡ ጋር በፍቅር ኖሯል። እንደታላቅነቱ ታናናሾቹ ታዘው፣ እናት አባቱ አክብረውታል። አፈር ፈጭቶ ውሃ ተራጭቶ ባደገበት ተክሃለሃይማኖት ብዙ ትዝታዎች አሉት፡ አስራአንደኛ ዓመቱን እንደያዘ እናትና አባቱ በፍቺ ተለያዩ። ይህ አጋጣሚ በብዙ የሕይወት መንገዶች ሊያመላልሰው ምክንያት ሆነ። ጅምር ልጅነቱን ከቤተሰቡ አላጣጣመም። ከእናቱ ተነጥሎ፣ ከእህት ወንድሞቹ ርቆ ወደ አሰበ ተፈሪ ተጓዘ። ኑሮው ከአባቱ ጋር ቢሆንም የልጅነት ጫንቃው ክፉ ደግ ሊሸከም ግድ ነበር።

እዮብ ለቤቱ የመጀመሪያ ነውና እንደአዋቂ ያስባል። ስለእናቱ ኑሮ ፣ ስለ እህት ወንድሞቹ ሕይወት ይጨነቃል። ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ቢሆንም ከአካባቢው ሊላመድ አልዘገየም። የአባቱ የሥራ ባህርይ ከቤት አያውልም። ጠዋት ወጥተው አምሽተው ይመለሳሉ። ብቸኛው ብላቴና ከአዲስ አበባ ርቋል። አሁን እንደ ቀድሞው እናቱ ጎኑ የሉም። ቤተሰቦቹ ውል ባሉት ጊዜ በናፍቆት ይሰቃያል። የልጅነት ማንነቱ በጥንካሬ መዋዛት ጀመረ። ብቸኝነትን ለመደ። ችሎ ማደርን አወቀ። ፍቅር በሚያሻው ዕድሜ የልቡን ማጣቱ እያስከፋው ነው። የአባቱ ለዓይን መራቅ ብዙ ያስቃኘው ጀምሯል፡፡

ትንሹ ባይተዋር …

ቀኑን ሙሉ ሱቅ እየዋለ ቤት እንዲጠብቅ የተፈረደበት ልጅ ታዛቢ የለውም። ትንሹ ባይተዋር አሁን ብዙ እያሰበ ነው። ከአጠገቡ ማንም የለም። የት ይዋል ፣ የት ይደር ፈቃጅም ከልካይም የለውም። ዘወትር ዓይኖቹ ብዙ ይቃኛሉ፣ ዓእምሮው አርቆ ያስባል። አሰበተፈሪ የመጣ ሰሞን እንደ እኩዮቹ ትምህርት ጀምሮ ነበር። አልገፋበትም። ትምህርቱን ትቶ በትልቁ ቤት ብቻውን መዋል ማደር ግዴታው ሆነ።

ይህ አጋጣሚ ንቁውን ልጅ ብዙ ያሳየው ያዘ። አካባቢውን ለመምሰል የዕድሜው ማነስ አልገደበውም። ያለታዛቢ ብቻውን የቆመው ልጅ በማንነቱ ለማዘዝ የራሱ አለቃ ሆነ። ሁሉን በእጁ ሁሉን በደጁ ለማድረግ ‹‹ተው እረፍ ባይ›› እንደሌለው አሳምሮ ያውቃል። ትንንሽ እጆቹ በርከት ያለ ገንዘብ፣ መቁጠር ሲጀምሩ ያሻውን ጣፋጭ መብላት ፣ የፈለገውን መርጦ መጠጣት ልምዱ ሆነ።

እዮብ ከእኩዮቹ የሚውልበት ዕድል ጠባብ ነበር። እንደ አካባቢው ለመምሰል ፣ ታላላቆቹን በልጦ ለመታየት አልዘገየም። ያለ ዕድሜው በሻካራማው፣ የሕይወት መንገድ እየተንጋደደ በተጓዘ ጊዜ እንደ ልጅ አይቶ ‹‹አደብ ግዛ›› ያለው አልተገኘም። ልጅነቱን ያለታዛቢ እንዳሻው አዘዘበት። በቀላሉ ሁሉን አወቀ፣ ሁሉን ተረዳ። ለእሱ እያንዳንዱ ጉዳይ ከዓእምሮው በታች አልሆነም። የታዳጊነት ዕድሜው እንደዋዛ አንድ ሁለት ብሎ ተቆጠረ ። በቁጥሮቹ መሀል የተረገጡት የሕይወት አጥፋቶች ግን ‹‹እዮብ›› ለተባለው አንድ ሰው አይፈዜውን የማንነት ንቅሳት አኑረው ነበር።

የአፍላነት መዘዝ…

እነሆ ! የእዮብ ፈታኝ የልጅነት ጊዜ እንደ ማታ ጥላ ውልብ ብሎ አለፈ ። በብቸኝነት፣ በቤተሰብ ናፍቆትና በብዙ ልማዶች መሀል የተራመደው ልጅ አሁን በዕድሜው መብሰል፣ መጎርመስ ይዟል። የልጅነቱ ክፉና ደግ ፣ ጊዚያቶች፣ የሳቅና ዕንባ ቀናቶች በትናንቱ ታሪክ ‹‹ነበር›› ተብለዋል።

1983 ዓ.ም። በመላው ሀገሪቱ የለውጡ ትኩሳት ተጋብቷል። በየሥፍራው የሚሰማው ዜና የደርግ ሥርዓት ማክተሙን፣ በምትኩ ሌላ መንግሥት መመሥረቱን ነው። እዮብ ይህ ጊዜ ከወጣትነት ዕድሜው የተጨባበጠበት ነበር። ማንነቱ በአዲስ ጉልበት ተገንብቷል። የውስጡ ግለት በትኩስ እንፋሎት ይፋጃል። አሁን ልጅነቱ ከእሱ የለም። ራሱን በራሱ የሚጠብቅበት፣ የሌሎችን እገዛ የማይሻበት መሀል አፍላነት ላይ ቆሟል።

ከቀናት በአንዱ እዮብ ተወልዶ ወዳደገበት ሰፈሩ ሊያቀና ግድ አለው። ለእሱ የተክለሃይማኖትና አካባቢው ትዝታዎች ብዙ ናቸው። ልጅነቱን ፣ ሳቅ ጨዋታውን ያስታውሱታል። ካደገበት አካባቢ ያስለቀቀው ግን የሠፈሩ ናፍቆት አልነበረም። የለውጡ አጋጣሚ እዮብን በመልካም አልተቀበለውም። በክፉ የሚያዩት ዓይኖች በዙ። የሚያሳድዱት እግሮች በረከቱ።

ክፉ ቀናት…

እዮብ ልጅነቱን በገፋበት ሰፈር እንደ ፀጉረ ልውጥ መታየቱ ልቡን ሰበረው። በቀላሉ እጅ አልሰጠም። እንዲያም ሆኖ ሰበብ ፈልገው የሚያሳድዱት፣ ሰዎች ድርጊት በነጻነት ላደገው ልጅ አልተመቸም። የዛኔ ጊዜ አመጣሹ አጋጣሚ ብዙ ነበር። የሚሮጥ፣ የሚደናበር ሰው ቢኖር በሌባ ስም የጥይት ሰለባ ሊሆን ይችላል።

ይህ ዓይነቱ እውነት ለፈጣኑ ወጣት ፈተና ሆነበት። ‹‹አውቃቸዋለሁ›› በሚላቸው የቅርብ ዘመዶቹ ጭምር ተሳደደ። እዮብ እንደ ክፉ ጊዜያት የመዘገባቸውን ቀናት አንገቱን ደፍቶ ሊያሳልፋቸው ሞከረ። አልቻለም። አሰበ ተፈሪን ትቶ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።

አጋጣሚው ለማንነቱ ታላቅ ትምህርት ነበር። የሆነበትን ሁሉ ባይረሳም ከሁኔታዎች ብዙ ተማረ። ነገን ለማቀድ፣ ወዳጅ ዘመድን ለይቶ ለመራመድ ምክንያት ሆነው። ዓይኑን ጨፈኖ አርቆ አለመ፣ ርምጃውን ለክቶ ውሳኔውን ቆረጠ። ትናንትና ዛሬ ላይ አቁሞ ነገን ወለል አድርጎ አሳየው።

የግርግሩ ጊዜ አልፎ ሁኔታዎች ሲረጋጉ እዮብ ለዓመታት ከራቃቸው ቤተሰቦቹ ተቀላቅሎ ሕይወትን መልሶ አጣጣማት። የሚቆጨውን የልጅነት ዘመኑን መልሶ ላያስታውሰው ረሳው። ዳግም የተወለደ ያህል ውስጡ ለመለመ፣ መንፈሱ ታደሰ።

እንደገና…

እዮብ ከቤተሰቦቹ ሲገናኝ ውስጡ በረታ። ተመልሶ ቀለም መቁጠር ዕውቀት መገብየት አማረው። ያሰበው አልቀረም። ትምህርት ቤት ተመዝግቦ ዓእምሮውን አዘጋጀ። ገና ከጅማሬው እንደ እኩዮቹ መራመድ ያልቻለው ተማሪ ውጤቱ አሽቆለቆለ። ማርፈድና መቅረት አበዛ ። ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን ደጋግሞ ወደቀ። አጋጣሚው አላስከፋውም። ከሕይወቱ ብዙ እንዲማር በር ከፈተለት። የትምህርቱን መዝገብ ለመዝጋት አልቸኮለም። አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት አልዘገየም።

እዮብ በየጊዜው የሕይወትን ጣፋጭና መራር ጣዕም ቢቀምስም ‹‹ከእንግዲህ በቃኝ›› ሲል ተሰምቶ አያውቅም። ፈተና ባገኘው ቁጥር ሁሌም ጉልበቱ እንደንስር ነው። የጣለውን ታግሎ፣ በአሸናፊነት ድል ይመታል። እንዲህ በሆነ ቁጥር ስላለፈው ትናንት አይጨነቅም። የኋላውን ትቶ የፊቱን ያልማል። በትምህርቱ ይህን ተገበረው።

ለትምህርቱ ትኩረት ሰጠ። የጣለውን ደብተር አንስቶ በጥናት ታተረ። ስሙን ቀይሮ የስንፍና ታሪኩን ለመፋቅ ቆረጠ። ያሰበው ተሳካለት። ዳግመኛ የስምንተኛ ክፍልን ተፈተኖ በአመርቂ ውጤት አለፈ። ዘጠነኛ ክፍል እንደገባ ግን የቤቱን ጎዶሎ አይቶ ማለፍ ከበደው። ገና በጠዋቱ የእናት አባታቸው መለያየት የከፋ ችግርን ጥሎ አልፏል። በቀላሉ ታክሞ ያልዳነው ድህነት ዛሬም ከነስሩ እንደተንሰራፋ ነው።

አሁን የእዮብ ሃሳብ ትምህርቱ ብቻ አይደለም። ለመላው ቤተሰብ የዕለት ጉርስ ማሰብ መጨነቅ ይዟል። ዘጠነኛ ክፍል ከሚማሩት መሀል በጉብዝናው የሚለየው እዮብ ሌላ ችግር እየፈተነው ነው። በባዶ ሆዱ ትምህርት ቤት መመላስ ከብዶታል። በኑሮ አቻ ካልሆኑ ጓደኞቹ እኩል መራመድ አልቻለም። እህል ባልሻረ አፉ ውሎ ይገባል። ቤት ሲደርስ ቁራሽ እንጀራ አያገኝምም። ይህ እውነት የእሱ ብቻ አይደለም። የመላው ቤተሰብ ሆኗል።

አሁን እዮብ ከራሱ ሙግት ይዟል። ትምህርቱን ማቆም ለቤተሰቡ መድረስ አለበት። እንዳሰበው ሆነ። በቀን ሥራ ውሎ ቤተሰቦቹን ማሳደር ጀመረ። ጠዋት ማታ በእናቱ ምርቃት የሚባረከው ወጣት የእጁ ገቢ መልካም ሆነለት። የመጀመሪያው ቀኑ ክፍያ አስር ብር ነበር። ደስታው ወደር አጣ ። የእጁን ሳያጎድል ለእናቱ አስረከበ። የዛን ቀን መላው ቤተሰብ ቁርስ ምሳውን በልቶ ዋለ።

ሥራን ለሰሪው…

1988 ዓ.ም እዮብና ሥራ ፊትለፊት የተገናኙበት ጊዜ። ከዚህ በኋላ የመለሰው አልተገኘም። በስራ እየደከመ፣ ከሆዱ እየቆጠበ ገንዘቡን ቆጠረ። የሳምንት ክፍያው አርባ ብር ሲገባ የውድ እናቱን የጓዳ ጎዶሎ አሟልቶ ለቀጣይ ቀናት ተዘጋጀ።

እሱ ከሻይና ብስኩት በቀር ለሆዱ ፊት አይሰጥም። አንዳንዴ ለእናቱ ሰጥቶ የምትተርፈውን በኪሱ ይይዛል። ውሎ አድሮ ግን የምግብ ደረጃው አደገ። ዳቦ በለስላሳ መብላት ያዘ። በዚህ የተጀመረ ዕድገት እያደር ከፍታው ጨመረ። ከቢራ፣ ከድራፍቱ መንደር ታየ። በባልንጀሮቹ ሲጋበዝ መሳቀቅን ተወ። በምላሹ ኪሱን መዳበስ ልምዱ ሆነ።

አሁን ዓመታት የኋልዮሽ ተጉዘዋል። የእዮብ ክፉ ደግ ቀናት ትዝታዎቹ ናቸው። በበሰለ ዓእምሮ፣ በበረታ ዕድሜ በቆመ ጊዜ የሕይወት ርምጃዎቹ ቀጠሉ። ጥንካሬው በሥራ ተገለጠ። በአንድ የእንጨት መሰንጠቂያ ውስጥ ብርቱ ሠራተኝነቱ ታየ። ደመወዙ እያደር ሲጨምር የኑሮ ለውጡ አደገ።

በተራመደባቸው መንገዶች ሁሉ ትናንት የሆነበትን አልረሳም። የጎዱትን ሊበቀል ያሠበበት ጊያዜት ብዙ ናቸው። ሁሉን ትቶ ወደሥራ ተመለሰ። ለውጡን ተከትሎ በተደራጀው የወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ሆኖ መዝለቁ ከእውቅና አላራቀውም። ሀሰትን ተጸይፎ ስለ እውነት ሲሟገት ቆየ።

ውሎ አድሮ ግን የፖለቲካ ቆይታው ሰለቸው። ከጊዜያት በኋላ በሜጋ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ ራሱን ሲያገኘው ጥሩ የእጨትና የአልሙኒየም ባለሙያ ሆኖ ነበር፡ ፡በወቅቱ ለበርካታ ታዋቂ ድርጅቶች የእጅ ሙያውን አስመሰከረ። ራሱን ችሎ በበረታ ጊዜ ግን በፈተናዎች ሊጠለፍ ግድ ሆነ ። ጫት መቃም፣ ከልጅነቱ የሚያውቀው ነው። ገንዘብ ሲያገኝ ሀሺሹን አክሎ ያለገደብ ገፋበት።

እዮብ ከሥራና ሱስ ጋር ብዙ ታገለ። ሱስ እያሸነፈው እጁን ይሰጥ ጀመር። በሥራው ከፍ ያለ ዕውቅናን እያገኘ ነው። የገባበት መንገድ ግን ክብሩን አስጥሎታል። ለዛሬ እንጂ ለነገ አያስብም። በዚህ መሀል ደጋግሞ ይጨንቀዋል፣ ጭንቅላቱን፣ ዓይኑን ያመዋል። መድሂት እየወሰደ ራሱን ለመርሳት ታገለ።

1995 ዓ.ም እዮብ ጤናው የተቃወሰበት፣ ብዙ አግኝቶ የበተነበት ጊዜ ሆነ። ቆይቶ ደግሞ በታላላቅ ሥራዎች በረታ። ዓመታት በሥራ ትጋትና በፈተናዎች ተዋዝተው የኋልዮሽ አለፉ። መልካም ትዳር ይዞ ልጆች ወለደ። የመጀመሪያ ልጁን አቅፎ እንደሳመ መካከለኛ ባለሀብት ሆኖ ተመዘገበ።

አሁን ብስለትና አርቆ ማሰብ መገለጫው እየሆነ ነው። ሱስ ይሉትን እርግፍ አድርጎ ትቷል። ውሎው ሥራ፣ ትኩረቱ ቤተሰቡ ብቻ ሆኗል። እንዲያም ሆኖ ጤና አይሰማውም። የደም ግፊት፣ የራስ ምታትና የልብ ህመም ያሰቃየዋል። መድሃኒቶች ቢወስድም እየተሻለው አይደለም።

የእዮብ ኩላሊቶች…

ከቀናት በአንዱ እዮብ ከሀኪም ፊት ቀረበ። ምርመራውን ያከናወነው ዶክተር ገጽታው ጥሩ አልነበረም። በእጁ ውጤቱን እንደያዘ አስቸኳይ ትዕዛዝ ሰጠው። ፈጥኖ ወደ ሌላ ሆስፒታል መሄድ ነበረበት። በሥፍራው ሲደርስ ያገኘው ሀኪም ገጽታ ጥሩ ሆኖ አልታየውም። ሀኪሙ የታካሚው ሁለቱም ኩላሊቶች መድከማቸውን ሲነግረው እጅግ አዝኖ ነበር።

እዮብ ቢደነግጥም ለመረጋጋት ሞከረ። ሀኪሙ ጊዜ ወስዶ አነጋገረው። ስለንቅለ ተከላ፣ ዲያሌሲስና ስለሚያስፈልገው የህክምና ወጪ ዘርዝሮ አስረዳው። ይህ አይነቱ እውነት ለእዮብ አዲስና ዱብዳዕዳ ነበር።2006 ዓ.ም በህመምና በጭንቅ ተጀመረ።

በወቅቱ ያስፈልገው የነበረ ገንዘብ 400 ሺህ ብር ነው። ይህ ገንዘብ በእጁ ይገኛል። አውጥቶ ከመታከም ግን ለሚስቱ መተው መርጦ መድሃኒቱን ብቻ መውሰድ ጀመረ። በህመም መሰቃየቱ ቀጥሏል፤ ያገኙት ሀኪሞች ህክምናውን እንዲጀመር እየወተወቱት ነው። እሱ ዛሬም ልቡ አልፈቀደም። የሚስቱ የልጆቹ ሕይወት እያስጨነቀው ዝምታን መርጧል።

እዮብ ‹‹ሞቴ ላይቀር ቤተሰቤን አልበትንም›› ሲል በአቋሙ ጸንቷል። ጊዜው እየገፋ ህመሙ እየጠና ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን ባለቤቱ አታውቅም። ሚስጥሩን ለራሱ ይዞ ጊዚያትን መግፋት ቀጠለ። ውሎ አድሮ ሁሉም ታወቀ። በብዙ ውትወታ ህክምናውን ጀመረ። ከእሱ ይልቅ ግን የሌሎች ስቃይና ድህነት ያሳስበው ያዘ። እንደእሱ ዲያሌሲስ የሚያደርጉ አብዛኞች ምስኪን የሚባሉ ናቸው። ከልብ አሳዘኑት። ራሱን አበርትቶ ፊርማ ማሰባሰብ ጀመረ፤ ተሳካለት።

አሀዱ ያለው እንቅስቃሴ በፖሊስ ማርሽ ታጅቦ በአደባባይ ወጣ። ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ›› ሲል ያወጀው ቃል ትኩረት አግኝቶ ማህበር አቋቋመ። አቅም የሌላቸው ወገኖች በየባዛሩ ሳጥን ተቀምጦላቸው መታገዝ ጀመሩ። ከታሰበው በላይ ከፍ ያለ የሚዲያ ሽፋን ተቸረው። በማህበሩ ማዕድ እያጋራ፣ ጎዶሎን እየሞላ አብሯቸው ተጓዘ። እዮብ ቃል ለገባለት ዓላማው ያልሆነው የለም።

የማህበሩ አቅም አንሶ እጅ ባጠረ ጊዜ በልማት ተነሺነት ያገኘውን ኮንዶሚኒየም አስከመሸጥ ደርሷል። የታዘዘለትን መድሃኒት ለሌሎች አሳልፎ ሰጥቷል። ለራሱ በቂ ትኩረት አለመስጠቱ ግን ዋጋ ማስከፈሉ አልቀረም። እዮብ በኩለሊት ህመሙ አጥንቱ ሳስቶ፣ እግሮቹ ዛሉ። በዱላ ሲውተረተር ቢቆይም አልቻለም። በአስር የስቃይ ዓመታት ብዙ ተፈትኗል። ውጭ ሀገር ሄዶ ለመታከም ቢሞክርም በጀርባ መተኛት ብርቅ አስኪሆንበት ተቸገረ። ከወገቡ በታች ፓራላይዝድ ሆኖ መንቀሳቀስ እስኪሳነው ስለዓላማው እጅ አልሰጠም።

ስለ እዮብ በሸራተን…

ይህ ብርቱ ሰው ዛሬ አስር ዓመታትን በታገለበት የኩላሊት ህመም የወገኖቹን እገዛ እየጠየቀ ነው። በቅርቡ ስለ እዮብ በሸራተን አዲስ በተካሄደው መርሀግብር ያጋጠመው የአጥንት መሳሳት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ መንቀሳቀስ ከማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጧል። ህክምናውን ለማድረግም 50 ሺህ ዶላር ወይም /ከ6ሚሊን/ብር በላይ ያስፈልጋል።

እዮብ ይህን ክፍያ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያግዘው እየጠየቀ ነው። ቀደም ሲል ‹‹ባለራዕይ አይቆምም›› ሲል ያሳተመው መጽሀፍ በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚኛ፣ በትግርኛ፣ በእንግሊዝኛና በአረብኛ ተተርጉሙ ለህትመቱ እየተጋ ይገኛል። ቀድሞ ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ›› ሲል የመሠረተው ማህበር አሁን ‹‹ሰላም ጤና ለኢትዮጵያውያን›› በሚል ስያሜ ተቀይሯል።

የማህበሩ መስራች እዮብ በዕለቱ ከጎኑ ቆመው ለነበሩ ሁሉ ምስጋናውን ችሯል። ለሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን፣ ለአቶ ጀማል አህመድ፣ ለአርቲስት ጥላሁን ጉግሳ፣ ለኮሜዲያን እሸቱ መለሰና ለአቶ ዳዊት ናትናኤል ‹‹ከልብ አመሰግናለሁ›› ብሏል። ለእዮብ ያለፈው ትናንት ታሪኩ ነበር። የሚኖርበት ዛሬ ደግሞ ሕይወቱ። ስለ ነገ የሚሆነውን አያውቅምና ብዙ ያልማል።

በዕለቱ የአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት አቶ ሰይድ መሀመድ ለእዮብ የህክምና ወጪ ይሆን ዘንድ አንድ መቶ ሺህ ብር አበርክተዋል። ትናንት ከነብዙ ችግሮቹ ለብዙሃን ይደርስ የነበረው እዮብ ዛሬ ‹‹ድረሱልኝ›› እያለ ነው። ሁሌም ለወገን ደራሽ ወገን ነውና እነሆ! መልዕክቱ ይድረስ ብለናል።

መልካምሥራአፈወርቅ

 አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You