አሊሴሮ
ሟች ከመሞቱ በፊት ያንቀዠቅዠው ነበር። በተለይ በሕዝብ አመጽ ተገፍቶ መቀሌ ከገባ ጀምሮ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ፤ልዩ ኃይል እያደራጀ ፤ዕድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናትን መሳሪያ አስታጥቆ ትርኢት እያሳየ በአጠቃላይ በእብሪት ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ፤ለያዝ ለገናዥ አስቸግሮ ነበር።
የህወሓት ቡድን እብሪት የጀመረውና በገሃድ የታየው በሃዋሳ ከተማ ነበር። በሐዋሳ ከተካሄደው የመጨረሻው የኢሕአዴግ ጉባዔ ጀምሮ የፓርቲውን ርዕዮተ ዓለም ለመለወጥና ግንባሩን ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመቀየር የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ቢሆንም፣ በተለይ ህወሓት ብልፅግና ፓርቲ ተብሎ የተመሠረተው ፓርቲ ውስጥ ላለመሳተፍ ከወሰነ ወዲህ ህወሓትና ብልጽግና ላይገናኙ እስከዘለቄታው ተለያይዋል። አቡሆይ ስብሃት በተያዙበት ወቅት እንደተናገሩትም ህወሓት የሞተው ኢህአዴግ ሲፈርስ ነው።
ከሃዋሳው ጉባኤ በኋላም ህወሓትና ወደ ብልጽግና ፓርቲ እያመሩ በነበሩት ፓርቲዎች መካከል የነበረው እሰጥ እገባ እየተካረረ መጥቶ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሙጥኝ ባለው በህወሓትና ከርዕዮተ ዓለማዊ እስረኝነት ተላቅቄ ለሁኔታዎች የሚስማሙ ውሳኔዎችን በምክንያታዊነት አራምዳለሁ በሚለው የብልፅግና ፓርቲ መካከል የቃላት ጦርነቶች እየበረቱ መጥተዋል።
እነዚህ የቃላት እሰጥ እገባዎች በወቅቱ ትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህወሓትና የተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች በሚያስተዳድረው ብልፅግና መካከል ወደ ግልጽ ልዩነት ያመሩትና በድርጊት የሚገለጹ መካረሮችን የፈጠሩት፣ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ታቅዶ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ የቀረውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ነው።
በ2012 በነሐሴ ወር መጨረሻ ታቅዶ የነበረው ምርጫ በሕገ መንግሥታዊ ትርጉም በተሰጠ ትንታኔ የኮሮና ወረርሽኝ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት መሆኑ ሲያበቃ እንዲካሄድ ውሳኔ ቢተላለፍም፣ ህወሓት ምርጫው መራዘም የለበትም ሲል አሻፈረኝ አለ። ማንም አይዳኘኝም በሚል እብሪት ምርጫ ቦርድ ፤የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ጭምር በአንድነት ምርጫው መራዘም አለበት ብለው ውሳኔ ቢያሳልፉም በትግራይ የምርጫ ዝግጅት እንደሚደረግና ክልላዊ ምርጫም እንደሚከናወን አስታወቀ፣ በድፍረትም ምርጫውን ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በማከናወን አዲስ ምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚ አቋቋመ።
በማናለብኝነት ብቻውን ተወዳድሮ አሸነፍኩ ባለው ዝቅተኛውን የምርጫ መስፈርት የማያሟላ እና በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የዕድር አባላት ምርጫን እንኳን የማይመጥን ‹ምርጫ› ብለው የጠሩት ምርጫ በዓለም ላይ ከተካሄዱ በምርጫ ስም ከተቀለደባቸው ትዕይንቶች አንዱ ነበር። ይህንንም አሳፋሪ ቅሌት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው እንዳልተደረገ የሚቆጠርና ተፈጻሚነት የማይኖረው ይሆናል ሲል አስታወቀ።
በጀብድ የተሞላው የህወሓት አመራር እራሱን የዴሞክራሲና የሕገ መንግስት ጠበቃ በማድረግ የህወሓት አምባገነን ባለስልጣናት በክልሉና በህወሓት የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት፣ ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የፌዴራል መንግሥት ምርጫ አድርጎ ሥልጣኑን አድሶ እንደ አዲስ መቋቋም የነበረበት ጊዜ በመሆኑና ይኼም ባለመሆኑ ሕገወጥ መንግሥት እንደሚሆን፣ ፓርላማው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሙሉ ሕጋዊ ውክልናቸውና ሥልጣናቸው እንደሚያበቃ ብሎም የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎችና ሕጎች ተቀባይነት የሌላቸውና በትግራይም ተፈጻሚነት የማይኖራቸው እንደሚሆኑ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የፌዴራል መንግስትን ለማሳጣትና ተቀባይነቱን ለመግፈፍም ህወሓት ባደራጃቸው ሚዲያዎቹና በፌስቡክ ተቀላቢዎቹ አማካኝነት ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም የሚል ዘመቻ ተጀመረ።
የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎትና አጀንዳ ያላቸውም ግለሰቦች ይህንኑ በማስተጋባት የአመጽ ጥሪ ማስተላለፍ ጀመሩ። ጎን በጎንም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አመጾችን በማስፋፋት ሰዎች በማንነታቸው እንዲገደሉ፤ እንዲፈናቀሉና ንብረታቸው እንዲወድም አደረጉ።
በመተከል፤በምዕራብ ወለጋ፤ በኮንሶ፤በሶማሌ፤ በአዲስ አበባ፤በቡራዩ በአጠቃላይ በአራቱም አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን የደም ምድር ለማድረግ ተመሙ። ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርትና የዕውቀት ማዕከላት ከመሆን የተማሪ ሬሳ የሚወጣባቸው ጦር ሜዳዎች ሆኑ። በየቦታውም ሕገወጥ መሳሪያ እንደአሸን በማሰራጨት ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው እንዲተላለቁ መንገድ አመቻቹ።
በእነሱ ልክ የሰፏቸውን ቡድኖች ‹የፌዴራሊስት ኃይሎች› በሚል ስም በማደራጀት የብሔር ብሔረሰብ ጠበቃ መስለው ለመታየት ሞከሩ። አንድ ሁለት ጊዜ በመቀሌ ስብሰባ በመጥራት ፌዴራል መንግስትን አሃዳዊ ብለው ከሰሱ። ሆኖም ጋብቻው በእውነትና በመተማመን ላይ የተመሰረተ አልነበረምና ‹‹የፌዴራሊስት ኃይሎች›› የተሰኘው ጥምረት እንደጉም ለመበታተን ጊዜ አልፈጀበትም ነበር።
ብዙዎች የፌዴራሊስት ኃይሎች የተባሉት አካላት ህወሓት አሁንም ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ መቀጠል ይፈልጋልና ጋብቻችንን አፍርሰናል የሚል መግለጫ አወጡ። የህወሓት ዕጢም ዱብ አለ።
ሶስቱ ሰኔዎች የሚል የጥፋት ዕቅድ በማውጣትም ሀገሪቱ ወደለየለት ትርምስና መበታተን እንድትገባ ሴራ አበጁ። ሰኔ 16 /2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ ከከሸፈ በኋላ ሰኔ 15/2011 ለሌላ ጥፋት ተዘጋጁ። ባህርዳርንም የጥፋት ማዕከላቸው አድርገው ሾሟት።
ቀድሞውንም የአማራ ብሄርን እንደጥላት በመፈረጅ ከትግል ሜዳ እስከስልጣን መንበር የዘለቀው የህወሓት ቡድን ክልሉን በሕገወጥ የጦር መሳሪያ በማጥለቅለቅ አርሶ አደሩ በሬውን ሸጦ መሳሪያ እንዲገዛና በእራሱ ላይም ድህነት እንዲያውጅ በርካታ የሴራ መረቦችን ሲዘረጉ ቆይተዋል።
ሰኔ 15 በብርጋዴል ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ፊት አውራሪነት ከክልሉ አልፎ ለሀገር የሚጠቅሙ ዶክተር አምባቸውን ጨምሮ ጐምቱ ባለስልጣናት በከንቱ ተገደሉ። በአዲስ አበባም ጄኔራል ሳዕረ መኮንን በተመሳሳይ በሰው እጅ ሕይወታቸው አለፈ። የጁንታው የደም ጥማትም ለጊዜው የረካ መሰለ።
እራሳቸው እየገደሉ እራሳቸው የሚያለቅሱት የጁንታው አባላት የአዞ እንባ ማንባት ጀመሩ። ሕዝብ አለቀ ሲሉ ተሳለቁ። በሰኔ 15 ጥፋትና ዕልቂት ያልረኩት የህወሓት ቡድን አባላት ለሌላ ዕልቂት ተዘጋጁ።
ሰኔ 23/2012 አሳዛኝ ጥፋት ተፈጸመ። ኢትዮጵያውያን በሙሉ የሃዘን ማቅ ለበሱ። ጀግናው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በጁንታው ቡድን አቀናባሪነት ህይወቱን ተነጠቀ። ቀድሞውንም የህወሓትን ቡድን ሲያወግዝና ፊትለፊትም ሲዋጋ በነበረው ጀግናው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ ቂም ቋጥሮ የነበረው የህወሓት ቡድን አንድም ሃጫሉን በማጥፋት ቂሙንም ለመወጣት ሁለትም አማራ ነው ያስገደለው የሚል ትርክት ቀድሞ በመንዛት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው እንዲተላለቁ ለማድረግ ረጅም እጁን ዘረጋ።
ትልሙም ለጊዜውም ቢሆን ተሳካለት። ሻሸመኔን በመሳሰሉ ከተሞች የንጹሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ፤ለዘመናት በልፋት የተጠራቀመ ንብረት በአንድ ጀንበር የእሳት እራት ሆነ። ሻሸመኔም የሶርያዋ አሊፖ ሆነች። ጽንፍ የወጣ ብሔር ፖለቲካና ጥላቻ ሀገርን እንደሚያፈራርስ ቋሚ ምስክር ሆና እስከዛሬ አለች።
አስተዋይ በሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ኢትዮጵያ ከሶስቱ ሰኔዎች ጥፋትና መበታተን ለጥቂት አመለጠች። በነዚህ ሁሉ ጥፋቶችና ሴራዎች መሃል የኢትዮጵያ መንግስት እልክ አስጨራሽ ትዕግስቱን እያሳየ እስከ 11 የሚጠጉ ሽምግልናዎችን ጭምር በመላክ የጁንታውን ሴራ በብልሃትና በጨዋነት ለማለፍ ሞክሯል። ትዕግስት ፍራቻ የመሰለው የጁንታው ቡድን አባላትም ያደራጁትን ልዩ ኃይል በመተማመን የወንድ ያለህ አሉ። እኛን ሊወር የሚመጣ ትግራይ መቀበሪያው ትሆናለች ሲል ተሰሙ።
ይባስ ብሎም ተራራውን ያንቀጠቀጠ የሚለውን አሮጌ ትርክት በመደጋገምና የ1980ዎቹን የቆረጣ ውጊያ በመተማመን ከእኔ በላይ ጀግና ለአሳር ሲሉ ተደመጡ። ሽማግሌዎቹም የህወሓት ቡድን አባላት ብድግ ብለውም ‹‹ኮር አፍርሰን ኮር እንገነባለን›› ሲሉ ተመጻደቁ።
ይህው እብሪት ጣራ ነክቶም ለ21 ዓመታት ዳር ድንበር ሲጠብቅና የትግራይ ሕዝብን ሲያገለግል የነበረውን የሰሜን ዕዝን ከኋላው በመውጋት ታሪክ የማይሰራው ጥፋት ሰሩ። መቀበሪያቸውንም ማሱ። ኢትዮጵያውያንም ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተቆጡ። መንግስትም ትዕግስቱ ተሟጧልና በህወሓት ቡድን ላይ ሕግ ማስከበር ዘመቻውን በይፋ መጀመሩን አበሰረ።
እዚህ ጋር አበሰረ ማለቴ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ27 ዓመታት ያህል በደረሰበት በደልና ጭቆና ትከሻው ጎብጦ ስለነበር መንግስት ይህን አጥፊ ሃይል ለመደምሰስ የሚወስደውን እርምጃ ሁሉ በደስታ ነበር የተቀበለው። አብዛኛው ሕዝብም ከመከላከያ ጎን በመሆን ገንዘቡን በማዋጣት፤ ደም በመለገስና አንዳንዱም ዘመቻውን ለመቀላቀል ጭምር ጥያቄ በማቅረብ ደጀንነቱን አሳይቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሕግ ለማስከበር በተንቀሳቀሰባቸው በተለይ የመጀመሪያዎቹ ቀናት የሽንፈትን ጽዋ ገና በጠዋቱ መጎንጨት የጀመረው የህወሓት ቡድን በማይካድራ ሰላማዊ ሰዎችን በመጨፍጨፍና የዘር ፍጅት በመፈጸም አለም አቀፍ ሽብርተኝነቱን በገሃድ አረጋግጧል።
የህወሓት ጨካኝና ከሃዲ ቡድን የሴቶችን ጡት በመቁረጥ ጭምር በታሪክ የሰማናቸውን ነውሮች በዚህ በሰለጠነ ዘመን በአይናችን በብረቱ እንድናይ አድርጓል። አጸያፊ በሆኑ ተዘርዝረው በማያልቁ ድርጊቶች በኋላ ቀር አስተሳሰብ የተሞላ ጨካኝ ቡድን ሆኑ ይፋ ወጥቷል። ቡድኑ በባዶ እጃቸው ያገኛቸውን የመከላከያ ሰራዊት በረሃብ በማሰቃየት፤ በታንክ በመጨፍለቅና በመኪና በመደፍጠጥ ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ጥላቻ ያሳየ ነውረኛ ቡድን ነው።
ቡድኑ በደረሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች ጭምር በሽንፈት ላይ ሽንፈት እየተከናነበ ወደ መቀሌ እግሬ አውጪኝ አለ። የትግራይ መሬት የወራሪዎች መቀበሪያ ትሆናለች ሲል በነበረበት አፉ እራሱ መቀበር ጀመረ።
በለፈለፉ ይጠፉ የሚለውም ተረት ተፈጸመበት። ትንታጉ ጄኔራል አበባው እንዳለውም የህወሓት ቡድን በውሸት ተፈጥሮ በውሸት ያደገ በመሆኑ ሁለት እግሩ መቃብር አፋፍ ሆኖ ጭምር አሸንፌያለሁ፤ አውሮፕላን ጥያለሁ፤ ጄኔራሎችን ማርኬያለሁ፤ ወዘተ እያለ ጅል ተከታዮቹን በውሸት ያሞኝ ነበር።
በተለይም በመጨረሻዎቹ ቀናት ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን በወሰደው ብርቱ እርምጃ እንደአሸዋ የተበታተኑት የጁንታው አባላት በየጥሻውና በየጉድባው በመደበቅ ነፍሳቸውን ለማዳን ማሰኑ። በተከበሩበት ሀገር እንደዝንጀሮ እና እንደሸለምጥማጥ በየስርቻው ተገኙ። ከትንታጉ መከላከያ ሰራዊት አይንና ጆሮ የተደበቀ ሚስጥር የለምና የቡድኑን መሪ አቶ ስብሃትን ከዝንጀሮ ገደል ውስጥ ተሸክሞ አወጣቸው።
የተቀሩትንም ከየቦታው መዘዛቸው። እምቢ ያሉትንም ጨረሳቸው። በአሜሪካና በአውሮፓ ቀለብ የሚሰፈርላቸውና ዶላር የሚቆረጥላቸው ሎቢስቶችና ጋዜጠኛ ተብዬዎች የጁንታው አባላት በደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት ቅስማቸው ቢሰበርም አፋቸው ግን አልሞተም። የበላ አፍ አያርፍምና ዛሬም ህወሓትን ከሞተበት ለመቀስቀስ አምላካዊ ኃይል ተጎናጽፈው የቀን ቅዠታቸውን እየቃዡ ይገኛሉ።
የህወሓት ታሪክ መሆን ያሳመማቸውም በሀገር ውስጥ የግጭትና ሴራ ፖለቲካ ጥቅም ተጋሪ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ሀዘን መቀመጣቸውን እያየን ነው። የሆኖ ሆኖ ግን ለ27 ዓመታት በህወሓት የግፍ ቀንበር ሲሰቃዩ የነበሩ ምስኪን ኢትዮጵያውያን የነጻነት አየር መተንፈስ ጀምረዋል። አለም ተለዋዋጭ ናትና ግፈኞች ሲያለቅሱ ለምስኪኖች ቀን ወጥቶላቸዋል።
በተለይም ደግሞ ለ45 ዓመታት በጭቆና ቀንበር ውስጥ ለመኖር የተገደደው የትግራይ ሕዝብ ዛሬ የነጻነት አየር መተንፈስ ጀምሯል። በህወሓት ሴራ ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላምና በፍቅር እንዳይኖር ተሰምሮ የቆየው ቀይ መስመር ተሰብሮ ዛሬ በዘንባባ ዝንጣፊ ታጅቦ የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል። ህወሓት በቆሰቆሰው ጦርነትም የተጎዳው የትግራይ አካባቢንና ሕዝብን ለማቋቋም ሕዝቡ ያለውን እያካፈለ ነው።
እንደ ፈርኦን በእብሪት አንገቱ የደነደነው እፉኝቱና ከሀዲው የህወሓት ቡድን አንድ ጊዜ ከጸሐይ በታች የሚረታን ኃይል የለም ሌላ ጊዜ ጦርነትን መስራት እንችላለን ሞቅ ሲለው ተጎምጸጽ ላይ ሆኖ ጦርነት ባህላችን ነው እያለ በማንአህሎኝነት ራሱን ይኮፍስና ‹‹ትግራይ መቀሌ የገባ ጠላት ሁሉ አይወጣም መቀበሪያው ይሆናል›› እያለ በዘረፈው የሀገር ሀብት በገነባቸው ሚዲያዎቹ ሲሸልል፣ ሲፎክርና ሲያቅራራ ከርሞ ራሱ ሊቀበርበት አንድ ሀሙስ ቀርታዋለች። ይህ ከሀዲ ስብስብ መቐሌ በጀግናዊ መከላከያ ሰራዊት ነጻ ከወጣች በኋላ የሞተ ሲሆን ቀብሩ በዚያው ሰሞን ተፈጽሟል። ነፍስ ይማር¡
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013