ለምለም መንግሥቱ
አንድ ወዳጄን ለአረንጓዴ ስፍራዎች ያለውን ስሜት ጠየኩት። መልሶ ‹‹ስለየትኛው አረንጓዴ›› ብሎ ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰ። እንኳን በከተማ ውስጥ በገጠሩም በአረንጓዴ ልማት ምትክ ቤቶች እየተገነቡ አረንጓዴ ማየት ምኞት እየሆነ መምጣቱን ግን ከመናገር አልተቆጠበም።
ውልደቱና ዕድገቱ ገጠር በመሆኑ ቦርቆ ያደገበትን፣ በክረምቱ ከሚደርሰው የመኸር ወቅት ጋር ተዳምሮ አረንጓዴ የለበሰው መሬት ላይ የተንከባለለበትን ያዘመንና የነበረው ውበት ዛሬም በአይነህሊናው እንደሚመጣ ነበር ያጫወተኝ። በበጋውም ቢሆን መሬቱ የተራቆተ እንዳልሆነ ያስታውሳል።
እርሱ ባለው ግንዛቤ የአረንጓዴ ልማት የአካባቢ ሥነምህዳርን ከመጠበቅም ያለፈ ጥቅም አለው። ዋርካ፣ ጽድና ሌሎችም ዛፎች ማህበራዊ ኩነቶችን በማስተናገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው። ሰዎች በዛፍ ጥላው ሥር ሰብሰብ ብለው ይጫወታሉ። ሽማግሌዎች የተጣላን ለማስታረቅ ይጠቀሙበታል። ኃይማኖታዊ ኩነቶችም እንዲሁ ይፈጽሙበታል። ድካምንም አረፍ ብለው ይወጡበታል።
ወዳጄ በልጅነቱ የሚያውቀው አይነት ልምላሜ አሁን ላይ አለማየቱ ያስቆጨዋል። አልሚውም፣ አጥፊውም ሰው በመሆኑ ቆም ብሎ ማሰቡ ለሁሉም ይበጃል ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ወዳጄ ልክ ነው። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሰው ልጅ በደን ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። እንደሀገርም የኃይል አቅርቦቱ ከ34 በመቶ በላይ ያላደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ለማገዶ የሚውለው የደን ውጤት ነው። ለቤትና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉት ቁሳቁሶች በሌሎች ግብአቶች ባለመተካታቸው በደን ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።
ሰዎች ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት የልማቱ ተሳታፊ ከመሆን ይልቅ በአንዳንድ አካባቢ ለእርሻ፣ ለግጦሽና ለተለያዩ አገልግሎቶች በማዋል የለማውን ማጥፋት በስፋት ይስተዋላል። በተለይ በፓርኮች እና ጥብቅ ደን ባሉባቸው አካባቢዎች ጥፋቱ የከፋ እንደሆነም ተደጋግሞ የተነሳ ጉዳይ መሆኑ አይዘነጋም።
ከከተማ ወጣ ብለን አረንጓዴ የለበሰ መሬት ሥናይ እንዴት ሀሴት እንደምናደርግ እማኝ መጥራት አያስፈልግም። አንዱ ስላየው ድንቅ ተፈጥሮ ለሌላው በአድናቆት ሲገልጽ፣ አንዳንዱም በብዕሩ በጽሁፍ አስፍሮ ለሕዝብ ጆሮ ሲያደርስ ታዝበናል። ይህ ደግሞ አረንጓዴን የመፈለግ ስሜት ከፍተኛ መሆኑን ያረጋግጣል።
ነገር ግን አረንጓዴ ልማትን እንደምናደንቀው በመንከባከብና የጠፋውን መልሶ በመተካቱ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ዝቅተኛ ነው። የአረንጓዴ ልማት ሥራ እየቀነሰ ሲሄድ ጉዳቱም በዚያው ልክ የከፋ ይሆናል። ያልተለመደ የአየር ፀባይ መለዋወጥ ማጋጠሙ አንዱ ማሳያ ነው።
የሰሞኑን የአየር ፀባይ ለውጥ ለአብነት ብንጠቅስ እንኳን ቅዝቃዜው በርትቷል። ከጥር 11 በኃላ አየሩ መሞቅ እንደሚጀምር ይነገራል። ይሁን እንጂ በተግባር ይሄ እየሆነ አይደለም። ቅዝቃዜው በማየሉ የፀሐይ ሙቀት እየተናፈቀ ነው።
አካባቢን በአረንጓዴ ልማት ማስዋብ፣ጥብቅ ደኖችን ተንከባክቦ ማቆየትና ጎን ለጎንም ችግኞችን በመትከል የመተካቱን ሥራ ማጠናከር እንደሚገባ የሚመከረው ለሰዎች ጤና እና ሰላማዊ የሆነ ኑሮ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ አይደለም። ምርትና ምርታማነትም እንዲጨምር፤ የውሀ ሀብት እንዳይነጥፍ የአረንጓዴ ልማት ሥራ አስተዋጽኦው ከፍተኛ በመሆኑ ነው።
የምናደንቀውን አረንጓዴ ሥፍራ ተንከባክቦ ለማቆየትም ሆነ ተጨማሪ ልማት ለማከናወን ከእያንዳንዱ ዜጋ የውስጥ ተነሳሽነት ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር እያንዳንዱ በየአካባቢው የአረንጓዴ ልማት ሥራ በማከናወን ኃላፊነቱን እንዴት እየተወጣ ነው? ለዛሬ የሲዳማ ክልልን የአረንጓዴ ልማት ሥራ ዳስሰናል።
በጉዳዩ ላይ በክልሉ በአካባቢ ጥበቃ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን በደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የደን ውጤቶች ዝውውር፣ ቁጥጥርና ክትትል ባለሙያ አቶ ጌታቸው ባሬ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ አረንጓዴ ልማት ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው ግንዛቤ ገና ቢሆንም ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ሥራ ከተሰራ ግን በአጭር ጊዜ የበለጠ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተሞክሮዎች ያሳያሉ። የደን ልማቱና ኢኮኖሚያው ትስስሩ በህብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ አልገባም።
ደን ማልማትና መጠበቅ የመንግሥት ስራና ኃላፊነት ብቻ አድርጎ የማየት አስተሳሰብ ጎልቶ ይታያል። በያገባኛልና በእኔነት ስሜት የሚንቀሳቀስ ህብረተሰብ በመፍጠር የጥቅም ተጋሪነቱንም በማሳየት ተከታታይነት ያለው ሥራ በመሥራት ክፍተቶችን መሙላት ይጠበቃል።
በአስፈጻሚው አካል በኩል ደግሞ የዳበረ ዕውቀት ያለው ባለሙያ በመመደብና መዋቅሩን እስከታች የመዘርጋት እንዲሁም የደን ልማቱን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር አስተሳስሮ እንደራስ አድርጎ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት የግብዓትና የቴክኖሎጂ ውጤትም አናሳ መሆን፣ችግሮች ለሥራው ውጤታማነት በእንቅፋት ይጠቀሳሉ።
አረንጓዴ ልማቱ በእነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ ከ2007ዓ.ም ወዲህ የደን ሽፋኑ ቀደም ሲል ከነበሩት ዓመታት የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል። በህብረተሰብ ተሳትፎ በችግኝ ተከላ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል።
በክልሉ ከ96 ሄክታር በላይ ስፋት ባለው ወይሾ እንዲሁም በሀሮሬሳና ጭሮ 482 ሄክታር የሚሸፍን የተፈጥሮ ጥብቅ የደን ልማት ለአብነት ይጠቀሳል። የተለያየ ይዘት ያላቸው ቢሆኑም የክልሉ 11 ወረዳዎች የተሻለ የደን ሽፋን ያላቸው መሆኑን ይናገራሉ።
በወይሾ ጥብቅ ደን ውስጥ ዕድሜ ጠገብና ሀገር በቀል ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 26 የሚሆኑት ተለይተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዝግባ፣ ቀረሮ፣ ብሳና፣ኮሶ፣ ጥቁር እንጨት ይጠቀሳሉ።
ገረባ ተራራ በሚባለው አካባቢ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ እንደሆነ የሚነገርለት የቀርከሀ ዝርያ አለ። ይሄን ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል አሁን ጊዜው ገና ቢሆንም ወደፊት ተስፋ ተጥሎበታል። መጠኑ ከአካባቢ አካባቢ ቢለያይም በሁሉም ቦታዎች የተለያዩ ዝርያዎች ይገኛሉ።
የደን ልማት ከሆነው አንዱ የቀርከሀ ተክልን ክልሉ በስፋት በማከናወን ላይ ይገኛል። ከሶስት አመት ወዲህ የደጋና የቆላ ቀርከሀ ልማት ላይ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በዕቅድ እየተከናወነ ያለው ሥራ ተጠናክሯል።
በዚሁ መሰረትም በክልሉ ስድስት ወረዳዎች የተከናወነው የቆላ ቀርከሀ ዝርያን የማላመድና የማስፋፋት ሥራ ወደ 11 ወረዳዎች ማሳደግ ተችሏል። የደጋ ቀርከሀ ልማትም እንዲሁ በተደራጀና በተቀናጀ አሰራር በ10 ወረዳዎች ለማስፋት ችግኝ ጣቢያ ተዘጋጅቶ ዘር የማፍሰስ ዝግጅት ላይ ይገኛል።
ተክሉ የአካባቢ ሥነምህዳርን በመጠበቅና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም በማስገኘት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ክልሉ እንዲህ ባሉ ምርት ሰጪና ጥብቅ ደኖች ዙሪያ በትኩረት እየሰራ ነው።
የቀርከሃ ልማቱ ትኩረት የተሰጠበት ሌላው ምክንያት የደን ይዞታ የነበረ መሬት በጣም በመቀነሱ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የክልሉ ሕዝብ ፍላጎቱ ወደ ግብርና ሥራ በማመዘኑ ነው።
የባህርዛፍ ተክል በስፋት ቢኖርም ባህርዛፍ በባህሪው መሬት የማድረቅና የመሬት ውስጥ የውሃ ይዘትን በመቀነስ ጉዳት የሚያስከትል ሆኖ መገኘቱ ሌላው ምክንያት ነው። የባህርዛፍ ዝርያ ከውጭ የሚመጣ መሆኑም ተጽዕኖ አለው። ከውጪ ዝርያ ይልቅ የሀገር በቀሉ በስፋት ጥቅም ላይ ቢውል ለውጤታማነት የተሻለ በመሆኑ ይመረጣል።
በክልሉ እየለማ ያለው ቀርከሀ በሀገር ውስጥ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ችግኝ ሲሆን፣በየትኛውም የአየር ሁኔታ የሚለማ ተስማሚ ዝርያ ነው። ቀርከሀ ሥነምህዳርን በመጠበቅ፣እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው። ምንጮች እንዳይደርቁ፣መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ አስተዋፅዖ አለው ።
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የቀርከሃ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ በመምጣቱም የደን ኢንቨስትመንቱ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት እንዲያሟላ ጎን ለጎን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም ማሳደግ የሚጠበቅ በመሆኑ ትኩረት መሥጠቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የቆላ ቀርከሀ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በስፋት ይገኛል። ይሄንን ዝርያ በሲዳማ ክልል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው። የቆላ ቀርከሀ በአካባቢው የተለመደ ባለመሆኑም አዲስ ዕቅድ ተነድፎ እየተሰራ ያለው የልማቱ ሥራም በችግኝ ጣቢያዎች በማፍላት ለግለሰብና ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ በማሰራጨት ልማቱን ለማስፋፋት በዕቅድ እየተሰራ ይገኛል ።
በቀጣይም ህብረተሰቡ የራሱ አድርጎ እንዲይዘው ፣ አልሚዎችም እንዲበረታቱ፣ በደን ይዞታም በስፋት እንዲለማ የማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።
በአንድ በኩል የክልሉ የደን ሽፋን መሻሻሉን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው የኃይል አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመዳረሱ ለደን መመናመን መንሥኤ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ይናገራሉ ። ይሄ ሀሳብ እርስ በእርሱ አይጋጭም እንዴ ስንል ጥያቄ አቅርበንላቸውም ነበር። ‹‹እርስበርሱ የማይጋጨው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከግል ይዞታ ጀምሮ በየደረጃው ይካሄዳል።
ለምሳሌ አምና 140ሚሊዮን 594ሺ ችግኝ ተተክሏል። አጠቃላይ የተከላ ዕድገቱ 80 በመቶና ከዚያ በላይ ሆኗል። ለገበያና ለማገዶ የሚውለው ሙሉ ለሙሉ ምንጣሮ በማካሄድ ሳይሆን እየተተካም በመሆኑ ነው ሽፋኑ ጨምሯል የተባለው። የደን ሽፋኑ ጨመረ ሲባል ደግሞ ጥብቅ ደኖች ባሉበት እንዲቆዩ የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን በማጠናከር የደን ጭፍጨፋውን የማስቆም ሥራ በመሰራቱ የደን ውድመትን ማስቀረት ተችሏል።
ይህ ማለት የደን ስፋቱን የሚጨምር ሳይሆን ባለበት እንዲቆይ የማድረግ ተግባር ነው። ለደን የሚሆኑ ዝርያዎችን የመለየትና ወደ ደንነት የሚቀየር ተጨማሪ ሥራ ገና በመከናወን ላይ ነው››ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ፤ አረንጓዴ ልማትን ለመታደግ ደን ያልሆኑና ደን የሆኑትን ተረፈምርቶች ለማገዶ ለማዋል ከዚህ ቀደም በተጠናከረ መልኩ የተከናወነ ተግባር አልነበረም። አሁን ግን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ስለሚያስገድድ በከሰል መልክ የሚዘጋጁ ብሪኬት የተባለ ማገዶ ለማምረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ እንዲሁም ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት ለመሥራት ታቅዷል።
እነዚህ ሥራዎች ሲጠናከሩ የአረንጓዴ ልማቱ የበለጠ ይጠናከራል። በአረንጓዴ ልማቱ ዙሪያ እስካሁን በተሰራው እና የደን ጥበቃና ክትትሉን በማጠናከር ስራው የንብ ማነቡን ስራ ማስፋፋት ተችሏል።
በከፍታ ቦታዎች ላይ ሳር እንዲበቅል አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ደግሞ አርሶአደሩ ለከብት የግጦሽ ሳር እንዲያገኝ አግዞታል። ከብት አድልቦ ለመሸጥ አበረታቶቷል። ይሄ ጅምር አርሶአደሩ ደኑን ዝም ብሎ እንዲጠብቅ ብቻ ሳይሆን ፣ ጎን ለጎን ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። የተገኘውን ውጤትም ለነዋሪው በተግባር በማሳየት ተነሳሽነቱ እንዲጨምር ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የአረንጓዴ ልማት ሥራው የውዴታ ግዴታ በመሆኑ ክልሉ የተጠናከረ ሥራ ይሰራል ያሉት አቶ ጌታቸው ፤በ30 ገጠር ወረዳዎች፣ ሰባት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚስተዋሉትን ጉድለቶች ለቅሞ በመያዝ፣ ለችግሩ መፍትሄ በመስጠት፣ ጠንካራውንም በማጎልበት፣ ቅድሚያ በሚሰጠው ላይም ትኩረት በማድረግ፣ ከላይ እስከታች መዋቅሮችን በመዘርጋት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራን ጨምሮ በጥናት የታገዘ ሥራ ለመሥራትም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋርም ትስስር በመፍጠር የተጠናከረ ሥራ ይከናወናል ብለዋል። ተስፋ ያለው የክልሉ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ውጤታማ እንዲሆን እንመኛለን።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013