ወርቅነሽ ደምሰው
ባለፈው ታኅሣሥ 7 ቀን 2013 ዓ.ም እትማችን ‹‹አንዲት ዛፍ መቁረጥ ያቃተው የወረዳ አስተዳደር እና የነዋሪዎች የዘመናት እሮሮ›› በተሰኘ ርዕስ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ስሙ ርግብ ሆቴል አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የአንድ መንደር ነዋሪዎች የደረሰባቸውን ችግር የሚመለከት ዝግጅት ይዘን መቅረባችን የሚታወስ ነው።
እነዚህ ነዋሪዎች በወቅቱ ያጋጠማቸውን ችግር አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍሉ ባደረጉት ጥቆማ መሠረት ቦታው ድረስ በመገኘት የነዋሪዎች እሮሮ አስመልክቶ ያዘጋጀነውን ዘገባና የአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ 4 ጽሕፈት ቤት ምላሽ የሚያስቃኝ ጥንቅር ለአንባቢያን አቅርበናል።
በወቅቱ በቀረበው ጽሑፍ የአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ 4 ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱልጀሊል መሀዲ ‹‹የነዋሪዎቹን የዘመናት ችግር አስተዳደሩ ያውቀዋል ወይ?›› ተብለው ሲጠየቁ በወቅቱ የሰጡት ምላሽ ‹‹ኧረ በፍጹም አሁን ገና መስማቴ ነው።
እኔ እዚህ ወረዳ ከመጣሁ አንድ ወር ሆኖኛል፤ ነገር ግን ይህንን ችግር ያደረሰኝም አካል ሆነ የደረሰኝ ማመልከቻ የለም፤ የቀረበም ቅሬታ የለም›› ብለው። ‹‹ሆኖም ግን ከእናንተ እንደሰማሁት የነዋሪዎች ችግር ከባድ በመሆኑ ችግሩ ውሎ ማደር የለበትም፤ አሳሳቢ የጤና ጉዳይ የሚያስከትል በመሆኑ ስለዚህ አሁኑኑ እናንተ እያላችሁ ኮሚቴ በማዋቀር ጉዳዩን ለመፍታት እንሰራለን›› ብለው እንደነበር ይታወሳል።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ይህንን ካሉ በኋላ እኛ እዚያው እያለን ለሚመለከታቸው ሠራተኞች ሁሉ ስልክ ደውለው እንዲመጡ ካዘዙ በኋላ ባለሙያዎች ወዲያውኑ መምጣታቸውንና አቶ አብዱልጀሊል ለባለሙያዎች ወዲያወኑ ቦታ ድረስ በመሄድ ችግሩን አጣርተው በቪዲዮና በፎቶ የታገዘ መረጃ ይዘው እንዲመጡ ትዕዛዝ ካስተላለፉ በኋላ ነዋሪዎቹን ከሦስት ቀናት በኋላ ቅዳሜ ጠዋት 3፡00 ለመነጋገር ቀጠሮ እንዲያዝላቸው ማድረጋቸውን ተመልክተን እንደነበር በወቅቱ ዘገባችን አቅርበናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ነዋሪዎቹን ለምሬት የዳረገው የፍሳሽ አገልግሎት የሚሰጠው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ነዋሪዎቹ የፍሳሽ አገልግሎት ለመስጠት የተመደበው መኪና የመጸዳጃ ቤቱን ፍሳሽ አገልግሎት ለመሰጠት በተደጋጋሚ ከአንድም ሁለት ጊዜ ተመላልሶ በመንገዱ ዳር ላይ ያለው ዛፉ አያስገባኝም ብሎ መመለሱን ነዋሪዎች ገልጸው ነበር።
ሆኖ ግን የውሃ ፍሳሽ ጽሕፈት ቤት አገልግሎት ለመስጠት መስከረም ወር በትንሿ መኪና ተገብቶ ፈሳሹን ማንሳት ቢችልም መኪናዋ የምትይዘው መጠን ትንሽ በመሆኑ መጸዳጃ ቤቱ ተመልሶ ወዲያውኑ መሙላቱን ነበር ነዋሪዎቹ የተናገሩት።ከዚያ በኋላ ከሁለት ወር በፊት ፈሳሹን ለመምጠጥ የመጣችሁ ትንሿ መኪና በትግል መግባቷን ገልጸው፤ ‹‹በር ላይ ያለው መግቢያ ቅጠሉ (አትክልቱ) ወጣ ያለ ስለሆነ፤ ከዚህ በፊት መጥተን ተመልሠናል፤ በአባከንነው ነዳጅ ምክንያትም ተቀጥተናል፤ አሁንም በመከራ ነው የገባነው መብራት እስፖኪዮውን ሰብሮብናል። ለሚቀጥለው ይህ ካልተነሳ የማንሠራ መሆኑን ይወቁልን›› የሚል በ25/01/2013 ዓ.ም የተጻፈ ማስታወሻ እንደተሰጣቸው የሚያሳይ መረጃን አካተ አቅርበን ነበር።
እነዚህ ሁለት ጽሕፈት ቤቶች የሰጡትን ምላሽ ያቀረብነው ያለምክንያት አይደለም። ቀደም ሲል የነዋሪዎቹ ቅሬታ ለአንባቢያን ስናቀርብ የአብዛኛው ቀበሌ ቤቶች ነዋሪዎችን ጓዳ ጎድጓዳ የሚያሳይ በመሆኑ ችግሮች ተባብሶ ሥር ሳይሰድ በእንጭጩ ለመቅረፍ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚፈጠሩ ችግሮች ከወዲሁ በመቅረፍና የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት በየኅብረተሰቡ ችግር ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ በማሰብ ነው።
በተለይ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ በቀበሌ ቤት የሚኖሩ ነዋሪዎች አቤቱታ የት ደረስ ስንል እውን የወረዳ ምክትል ኃላፊ በሰጡን ፈጣን ምላሽ መሠረት ችግራቸው ተቀርፏል ወይስ ችግራቸው ተባብሶ ቀጥሎ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል የሚለው ለማየት የታለመ ነበር። ሆኖም ግን እነዚህ ነዋሪዎች አቤቱታ ሰሚ አልባ ጩኸት ሆኖ እስከ ዛሬ ችግራቸው ሳይቀረፍ ለባስ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል።
የዝግጅት ክፍላችንም የነዋሪዎቹ ጥቆማ ከተደረሰው በኋላ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ዕለቱ አርብ ታኅሣሥ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡30 ላይ ወደ ጥቆማው ቦታ ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ስሙ ርግብ ሆቴል አካባቢ ደረስን በዓይናችን ያየነውን የነዋሪዎች አቤቱታ በጥቂቱ ማስዳሰሳችን የሚታወስ ነው።
በዚህም መሠረት የዝግጅት ክፍላችንም የእነዚህ ነዋሪዎች ችግር እስከዛሬ ለምን መፍታት አልቻለም የሚለውን በመመልከት የነዋሪዎቹን ቅሬታና የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ምላሽ ያቀረበ ሲሆን፤ ፍርዱን ለእናንተው በመተው፤ የቅሬታ አቅራቢዎቹን እሮሮና ምሬት በማዳመጥ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየትና ምላሹን ጨምረን እንደሚከተለው ልናስቃኛችሁ ወደድን።
ከቅሬታ አቅራቢዎች አንደበት
የዚሁ ሰፈር ነዋሪ ከሆኑት መካከል አቶ ያደቴ ሁሬሳ ከ30 ዓመት በላይ በግቢ ውስጥ መኖራቸውን ይናገራሉ። ቅሬታ አቅራቢ ትልቁ ችግራቸው የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ምክንያቱ መኪና የሚገባበት መንገድ መታጣቱ መሆኑን ይናገራሉ። ከውሃና ፍሳሽ የመጸዳጃ የፈሳሽ አገልግሎት የሚሰጠው ትልቁ መኪና በመምጣት ፈሳሹን ለመምጠጥ ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ዛፍ ካልተቆረጠ መስታወት ይመታብኛል ብሎ በመናገር ወደ መጣበት የተመለሰ ሲሆን፤ ‹‹ዛፉ ከተቆረጠ በኋላ ጥሩኝ ›› ብሎ እንደሄደ ይናገራሉ። በድጋሚም ለውሃና ፍሳሽ ካመለከትን በኋላም መኪና ተመልሶ በድጋሚ ቢመጣ ለመግባት ስላልቻለ መመለሱን ይናገራሉ።
በመጨረሻም በሦስተኛው ጊዜ የመጣችው ትንሿ መኪና ገብታ በስንት መከራ ፈሳሹን ከመጠጠች በኋላ በግድ የወጣች ሲሆን፤ ሹፌሩ ይህ ዛፍ ካልተነሳ ሁለተኛ እንዳትጠሩኝ ዳግም አልመጣም ብሎ መሄዱን ጠቁመው፤ በዚህ ሁኔታ እንደምታዩት መኪና መግባት አይችልም ብሎ ማስታወሻ ጽሑፍ እንደሰጣቸው ተናግረዋል። አቶ ያደቴ እንደሚሉት፤ የግቢው ነዋሪዎች ከ12 በላይ አባወራዎች ከነቤተሰቦቻቸው በአጠቃላይ ከ60 ሰዎች በላይ የሚኖሩበት ሲሆን፤ መጸዳጃ ቤቱ በርካታ ተጠቃሚዎች ስላለው ወር ሳይሞላ ወዲያውኑ እንደሚሞላ ይገልጻሉ።
በዚህ የተነሳ መጸዳጃ ቤቱ ሞልቶ የሚፈሰው ፍሳሽ ከእኛ በታችኛው በኩል ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋ በቀጥታ ስለሚሄድ ሁልጊዜ እንደሚከሷቸው ተናግረዋል። ‹‹እኛም ይህ መጥፎ ሽታ የእኛን ጤና የሚያውከው አንሶ የሌላውን ነዋሪ ሕይወት ለአደጋ እንዲያጋልጥ አንፈልግም።›› ሲሉ ችግሩ ለብዙዎች መትረፉን ያስረዳሉ።
አክለውም የዚህ ግቢ አብዛኛው ነዋሪ አቅመ ደካማ ነው። ‹‹እኔን እንደምታየኝ አንድ እግሬን ያመኛል፤ በክራንች ነው የምሄደው። ተንፏቅቄም ቢሆን ወረዳ መሄድ አያቅተኝም ነበር። ወክለን የላክናቸው ሰዎች ሆነ በየጊዜው እየመጡ የሚመለከቱት የወረዳው ሰዎች መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ ነጋ ጠባ መመላለስ ሥራቸው ሆኗል›› በማለት በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 አስተዳደር ችግራቸውን እንዳልፈታላቸው ይናገራሉ።
የውሃና ፍሳሽ ሠራተኞች እንዳሉት፤ ‹‹ይሄ ዛፍ ካልተነሳ አልገባም ብራችሁን በከንቱ አታወጡ፤ ዝም ብላችሁ አትድከሙ ብለውናል። የግድ መኪና ገብቶ ፍሳሹን እንዲያስወግድ ከተፈለገ ዛፉ እንዲቆረጥ እና መንገዱ ክፍት እንዲሆን የሚያስፈልግ መሆኑ ጠቁመው፤ ዛፉን የተከለውን ሰው እንዲቆርጥ ቢጠይቁትም ቆርጫለሁ ብሎ ቅጠሉን ነካ ነካ አድርጎ ትቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ያደቴ ገለጻ፤ ከዚህ ሌላም ትልቅና ዋና አሳሳቢ ስጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ። የሰው ልጅ በሕይወት እንዳለ በተለያዩ አጋጣሚዎች ውስጥ ማለፉ የግድ ነው። ለምሳሌ ድንገት የእሳት አደጋ ቢከሰት የእሳት አደጋ መኪና እንዲገባ፤ በድንገት የታመመ ሰው ኖሮ አምቡላንስ ቢያስፈልግ፤ እንዲሁም ሰው ቢሞት አስከሬን እንኳን ለማውጣት መኪና የማይገባበት በመሆኑ ከችግርም በላይ የሆነ ችግር ነው የገጠመን ይላሉ።
ከሁለት ወር በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የመጣችውን ትንሿ መኪና እንኳን መግባት ያልቻለችውን እንዴት ትልቅ፣ መኪና መግባት ይችላል ብለው ይጠይቃሉ። ስለዚህ መፍትሔ ከጤናና ከማህበራዊ ሕይወታችን የሚበልጥ ነገር የለምና ቢታሰብበት ጥሩ ነው። የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ሌላኛዋ ከ50 ዓመታት በላይ በዚህ አካባቢ እንደኖሩ የሚናገሩት ወ/ሮ አየለች አበበ በበኩላቸው፤ እነዚህ ቤቶች የቀበሌ ቤት በመሆናቸው መፀዳጃ ቤት የጋራ ስለሆነ በተደጋጋሚ እንደዚያ ዓይነት ችግር ይገጥመናል።
ይሁን እንጂ በየጊዜው መጸዳጃ ቤቱ ሲሞላ ለማስመጠጥ ችግር አልነበረብንም። የአሁን ችግሩ ባስ እንዲል ያደረገው ግን፤ የሁለቱ መጸዳጃ ቤት ፍሳሽ በአንድ ላይ መምጣቱና ለማስመጠጥ ያልቻሉበት ሁኔታ በማጋጠሙ እንደሆነ ይናገራሉ። መኪናው በበር ላይ የተተከለ አበባና ዛፍ ምክንያት አድርጎ አለመግባቱና ከአንዴም ሁለትና ሦስት ጊዜ አትክልትና ዛፉ በማደጉ ምክንያት ብንለምናቸውም ዛፉ ካልተቆረጠ አልገባም ብሎ መሄዱን ችግሩን እንዳባባሰውና ዞሮ ዞሮ ችግሩ አለመቀረፉን ተናግረዋል።
አክለውም፤ የዛፉ ባለቤቶችም የዚሁ የመጸዳጃ ቤቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ የእነሱ ቤት መግቢያ በር ላይ ከዳር በኩል ላይ በመሆኑም ሽታው ስለማይደርስባቸው እኔን ካልነካኝ በሚል ስሜት ለመቁረጥ ውዝግብ መፍጠራቸውን ይናገራሉ።
‹‹ እኛ የመጸዳጃ ቤቱን ፈሳሽ ለማስመጠጥ ገንዘብ አሰባስበን ስንሄድ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ተቀጥተናል። የተቀጣንበትም ምክንያት ዛፉን ሳታስቆርጡ ለምን ውሃና ፍሳሽ መኪናን ትጠራላችሁ በሚል ነው። ስለዚህ በአንዲት ዛፍ ምክንያት ሕይወታችን እየታመሰ ነው›› ሲሉ ምሬት የተቀላቀለበት ሀሳብ ሰንዝረዋል። በተመሳሳይ ደግሞ የኛ የመጸዳጃ ቤት ፈሳሽ ደግሞ ወደ ሌላ ግቢ እየፈሰሰ ይገኛል የሚሉት ወ/ሮ አየለች፤ ፈሳሹ የሚፈስባቸው ሰዎች እኛን እየከሰሱን እያስቀጡን ነው።
‹‹ለምን አላስመጠጣችሁም፤ ማስመጠጥ አለባችሁ ተብለን ተከሰናል።›› በሌላ በኩል ከሌላ ቦታ ግቢው የሚፈሰው የመጸዳጃ ቤት ፈሳሽ ያለ ሲሆን፤ እኛን የተጠላለፈ ችግር ውስጥ እንደሆንን ሊታወቅ ይገባል። መፍትሔ የሚሰጠን አካል አጥተናልና የመፍትሔ ያለህ እንላለን።
እስካሁን የደረሰብን ችግር እጅግ በርካታ ነው በቃ ልንባል ይገባል›› በማለት በምሬት ይናገራሉ። መጸዳጃ ቤቱ በሁለት በኩል ሞልቶ በሰው ላይ እየፈሰሰ በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ይሰጠን ዘንድ እንጠይቃለን ሲሉ ተናግረዋል።
ሌለኛዋ ለ10 ዓመታት ያህል በግቢው ነዋሪና የወረዳው የቀጣናው ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ምንትዋብ ታምሩ በበኩላቸው፤ ይህንን ያጋጠማቸውን ችግር በተደጋጋሚ ማመልከታቸውን ይናገራሉ።
አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት አካባቢ የሚመለከታት ጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛ መጥታ በማየት ችግሩን መፍታት ስላልቻለች ከአቅሜ በላይ ነው ብላ ለወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ማስተላለፏን ትጠቁማለች። ሌሎችም የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ቦታው ድረስ በተደጋጋሚ በመምጣት ቢያዩም፤ መፍትሔ የሰጣቸው አካል እንደሌለ ምንትዋብ ትናገራለች።
በዚህም ምክንያት ሕፃናት ልጆች መታመማቸውንና እሱንም ሄደው ለወረዳው ማስታወቋን ትናገራለች። ሕፃናቱ በየቀኑ በጉንፋን የሚታመሙ በመሆኑ ወደ ሀኪም ቤት ማመላለስ የተሰላቹበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁማ፤ ወደ ህክምና ተቋም በሚወሰዱበት ጊዜ ይድናል እንደገና ተመልሶ ይነሳል። በመሆኑም ሀኪሞቹም ችግራቸው አላርጂክ መሆኑን ተረድተው ሽታ ካለበት ቦታ አርቋቸው የሚል ምክር ይሰጡናል፤ እኛ ግን ልጆቻችንን የት እናድርሳቸው ስትል የችግሩን አሳሳቢነት ታስረዳለች።
አክላም በግቢው የሚኖሩት ነዋሪዎች ደካሞች አቅም የሌላቸው አዛውንቶችና ሕፃናት የሚበዙበት ግቢና መኖሪያ አካባቢ በመሆኑ ዋናው ችግራቸው መፀዳጃ ቤት ሞልቶ የመፍሰሱ ጉዳይ ቢሆንም፤ ፍሳሽ በበራቸው ላይ በቤት ውስጥ የሚያልፍበት ሁኔታ መኖሩን ታስረዳለች።
መጸዳጃ ቤት የጋራ በመሆኑ በርካታ ሰዎች የሚጠቀሙበት ሲሆን፤ ቶሎ ቶሎ የሚሞላበት ሁኔታ መኖሩን የምትገልጸው ምንትዋብ፤ ከላይ በኩል መጸዳጃ ቤት ፈንድቶ በቱቦ በኩል ወደ ግቢ እየፈሰሰ ያለ ፈሳሽ መኖሩን አመላክታለች። ይሁን እንጂ በየቀኑ የደንብ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በመምጣት የሚያዩት ቢሆንም፤ ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊሰጡና አጥጋቢ የሚሆን መልስ ሊሰጣቸው እንዳልቻሉ ትናገራለች።
በግቢው የሚገኙ በርካታ ልጆች በአላርጂክ እየቆሰሉ የጤና እክል እየገጠማቸው ቢሆንም፤ የተወሰኑ ተወካዮችና ሁለት እርጉዝ እናቶች ወደ ወረዳ ሄደው ችግራቸውን ቢናገሩም መፍትሄ አላገኙም። በዚህ ምክንያት ልጇ አላርጂክ እየታመመ የተቸገረች እናት ቤቷን ለቃ ተከራይታ እየኖረች መሆኗን ገልጻ፤ ልጆቹ በተደጋጋሚ ሳል ስለሚይዛቸው በየጊዜው ወደ ህክምና በማመላለስ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ትጠቁማለች።
‹‹እኔ የቀጣና ኮሚቴ እንደመሆኔ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ለወረዳው በየስብሰባ በመናገር፤ የማሳወቅና መጥተው እንዲያዩ ማድረግ ሥራ ሰርቼ ነበር መፍትሔ ይዞ ባይመጣም የምትለው ምንትዋብ፤ በተለይ ኮቪድ ወረርሽኝ ሀገራችን ከገባ በኋላም እንኳን በጣም እየፈሰሰ ስለነበር በጣም ስጋት ውስጥ እንደነበሩም ታስረዳለች።
በቅርብ እንኳን ‹‹መፍትሄ መስጠት የማትችሉ ከሆነ የምናመለክትበት መንገድ አሳዩን ብለን ሄደን ነበር›› ብላ የምትናገረው ወ/ሮ ምንትዋብ እስካሁን ግን አንዳች መፍትሄ እንዳላገኙ ታስረዳለች።
የደንብ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች መጥተው በሚያዩበት ጊዜ ፈሳሽ የሚመጣበት ቦታ ባለቤት የሆኑት ሴት የኔ አይደለም በቱቦ ከሌላ ቦታ የመጣ ነው በማለት የሚከራከሩ ሲሆን፤ ይህንን ከየት እንደሚፈስ የሚመረምር ባለሙያ እንልክላችኋለን ብለው ከሄዱ በኋላ በዚያው የውሃ ሽታ ሆነው እንደሚቀሩ ነው የምትናገረው። መጸዳጃ ቤት ፈሳሽ ችግር ከወረዳ አቅም በላይ ሆኖ አይደለም የምትለው ወ/ሮ ምንትዋብ፤ ይህ የሚያሳየው የመልካም አስተዳደር ችግር ከወረዳ ጀምሮ መኖሩን ነው።
ወረዳው ይህንን መፍታት የሚችል ወረዳ ከመሆኑም በላይ በጣም ቀላልና እጁ ላይ ያለው ነገር ነው። ደንቦች በተደጋጋሚ መጥተው ያዩታል ተነጋግረው ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ችግራቸው ባለማድረጋቸው ኅብረተሰቡ በስቃይ ለመኖር ተገዷል። የችግሩ ተጠቂ ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል በዚህ ፈሳሽ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ወላጆች መካከል ወ/ሮ ሽሙ መንግሥቱ አንዱ ናት።
ሕፃን ልጅ ይዛለች። ‹‹ልጄ ከተወለደ ከስድስት ወር በኋላ ነው የጤና እክል የገጠመው አሁን የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ልጅ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ በመታመሙ ምክንያት ወደ ህክምና ተቋም ስወስደው አላርጂክ ነው ይሉኛል ›› ትላለች። ‹‹አካባቢያችሁ ላይ ሽታ ያለው ነገር አለ ወይ›› ብለው ሀኪሞች እንደሚጠይቋት ጠቅሳ፤ የመፀዳጃ ቤቱ ፈሳሽ በፈጠረው ችግር ምክንያት ልጁ እግር ላይ የወጣ ቁስል አላርጂክ እጅግ የከፋና ሁልጊዜ የሚያሳክከው መሆኑን ትገልጻለች። በዚህም ምክንያት በርካታ የህክምና ተቋማት ይዛ ብትሄድ ለልጇ ስቃይ መፍትሔ አለማግኘቷን ጠቁማ፤ በዚህም የተነሳ የልጇ ስቃይ የዘወትር ስቃይ በመሆኑ እረፍት እንደነሳት ትናገራለች።
የወረዳ 4 ጽሕፈት ቤት ምላሽ
በአራዳ ክፍለከተማ የወረዳ 4 ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ አብዱልጀሊል መሀዲ እንደሚናገሩት፤ የኅብረተሰቡን ችግር ካወቁ ጊዜ ጀምሮ በቦታው በመገኘት ችግሩ ከሥር መስረቱ ለመረዳት ይቻል ዘንድ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን በሚገባ ተረድቶ ለመፍታት ብዙ ርቀቶችን ለመሄድ ተችሏል።በመጀመሪያ ቅሬታ አቅራቢ ነዋሪዎች በዚህ ጉዳይ እጅግ በመማረራቸው ምክንያት እርስ በርስ አጉል እሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት አለመግባባቶችና ለተለያዩ ቅራኔዎች ተዳርገው የነበረበት ሁኔታ መኖሩን አስታውሰው፤ እነዚህ አካላት በመግባባት ሥራቸውን መጀመራቸውን ይናገራሉ።
ሌላው ለዚህ ሁሉ መነሻ ከሆነው ዋንኛ ችግር አንዱና ኅብረተሰቡ ሲያነሳ የነበረው ቅሬታ የፍሳሽ አገልግሎት የሚሰጠው መኪና እስፖኪዮ ይሰበራል በማለት አገልግሎት ሲያደናቅፍ የነበረው አትክልት ጉዳይ በመሆኑ ገልጸው፤ ይህንን አትክልት ቅርንጫፍ ለማስቆረጥ እንዲቻል ከሚመለከታቸው የአረንጓዴ ልማት ጽ/ቤት ጋር ለመፍታት በሚያስችል ሁኔታ ላይ የተመታቸ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የኅብረተሰቡ እሮሮ የነበረው ከፍሳሽ ቱቦ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ሴክተር ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመሆን ኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ተካሂዶ እንደነበር አስረድተዋል።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ እንደሚሉት፤ በውይይቱ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ በኅብረተሰቡ ዘንድ እስካሁን የቆየ ቅሬታ እንደሌለው የተረዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን በዚህ ምክንያት በሰዎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተናግረዋል።
ሁለተኛው የፍሳሽ ማንሻ መኪና በቀላሉ ገብቶ አገልግሎት መስጠት እንዲችል መጀመሪያ የመንገዱን ስፋት በመለካት ሥራ የተሰራ ሲሆን፤ አሁን ያለው የመንገዱ ስፋት ከ3 እስከ 4 ሜትር እንደሚደርስ ገልጸው፤ የፍሳሽ አገልግሎት የሚሰጠውን መኪና አላስገባ ያለው ችግኝ እዚያው ኅብረተሰቡ ባለበት በባለሙያ ድጋፍ በጋራ ቅርንጫፉን በመቆረጥ ተከርክሞ ወደ አጠር እንዲጠጋ መደረጉ ይናገራሉ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ እነዚህን ተግባራት ካከናወኑ በኋላ የውሃና ፍሳሽ ጽሕፈት ቤት የፍሳሽ አገልግሎት ሰጪ መኪናዎች የሚያቀርቡት ቅኔታ መፈታቱን አረጋግጠው ኅብረተሰቡ ወደ ውሃና ፍሳሽ ጽሕፈት ቤት በመሄድ ጉዳዩ መፈታቱን አመልክተው አገልግሎት እንዲያገኙ ነግረዋቸው እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖ ግን ኅብረተሰቡ ሄዶ ቢያመለክትም የፍሳሽ አገልግሎት ሊሰጥ የመጣው መኪናው ዳግም የተለመደውን ዓይነት ምላሽ በመስጠት የነዋሪዎቹን ጥያቄ ችላ ብለው ጥለው መሄዳቸውን ገልጸዋል ።
አክለው፤ ውሃና ፍሳሽ የአገልግሎት ሾፌሮች ስፖኪዩ ይሰበርብናል በሚል ጥለው ሲሄዱ የቆዩ ሲሆን አሁንም መንገዱ ከተስተካከለ በኋላም ምክንያታቸውን እንዳላቆሙ የሚናገሩት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ያለምክንያት ሕዝብ ማንገላታት ተገቢ አይደለም ይላሉ።
ከዛሬ ከ40- 50 ዓመታት በፊት የተቆፈረ መጽዳጃ ቤት እና እስካሁን ለበርካታ ዓመታት ያለምንም ችግር አገልግሎት እየተሰጠ እንደነበር ነው መረጃ የሚያሳየው። ነገር ግን በቅርብ ጊዜ የተቀየሩት የውሃና ፍሳሽ የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ፍሳሽ አገልግሎት የሚሰጡ ሹፌሮች ለሁለት ጊዜያት ወደ አካባቢው ቢሄዱም ምንም ዓይነት መለኪያ ሲያደርጉ በማየት ብቻ ይህ ችግኝ እስካለ ድረስ መግባት አንችልም፤ መኪናው አዲስ ነው በዚህ በኩል አይገባም እያሉ ምክንያት እየደረደሩ የሕዝብን ችግር ከግምት ውስጥ ባለማስገባት በማንአለብኝ ስሜት ሕዝብ ወጥቶ እየለመናቸው የሚመለሱበት ሁኔታ መኖሩ ቅሬታ አቅራቢው ሕዝብ ለወረዳው ማቅረቡ ነው የሚናገሩት የወረዳው ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱል ጀሊል ።
ወረዳው አሁን ላይ የወሰደው እርምጃ ለአዲስ አበባ ከተማ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ በ19/05/2013 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ የሕዝቡ አቤቱታና ቅሬታ እንዲፈታ አሳውቆ እስካሁን ድረስ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አቶ አብድል ጀሊል ይናገራሉ።
ሦስተኛው ኅብረተሰቡ አቤቱታ ያቀረበበት የመጸዳጃ ቤቱ የሚመነጭበት ሁኔታ ጉዳይ ነበር የሚሉት ምክትል ኃላፊው፤ ፍሳሹ ከግል ቤት የሚወጣ ቢሆንም፤ የፍሳሽ መውረጃ ቱቦውን ደፍኖ የሰራው ከአቤቱታ አቅራቢ ነዋሪዎች መካከል የሆነ ግለሰብ ነው።ይህንን ግለሰብ የሲሚንቶ፣ የአሸዋና የመሬት አጠቃላይ ነገር የጉልበት እራሱ ችሎ በማሰራት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችል ሁኔታ ሁለቱ ግለሰቦች ተስማምተው የጊዜ ገደብ አስቀምጠው የፈረሙበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ ።
ወረዳው ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተቻለውን ቢሰራም የውሃና ፍሳሽ መስሪያ ቤትን ለማዘዝ አይችልም፤ ነገር ግን ተቋሙ ይህንን ችግር በአስቸኳይ የማይፈታው ከሆነ ወደ በላይ አካል ለአዲስ አበባ ውሃና ፈሳሽ ባለስልጣን ለማሳወቅ ጥረት እናደርጋለን ያሉት አቶ አብዱል ጀሊል፤ ሆን ተብሎ ኅብረተሰብ እንዲማረር የሚያደርግ አካል ካለ እየተጋለጠ የሚሄድበት አሠራር በመዘርጋት ተጠያቂ የሚሆነው አካል ይጠየቃል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምላሽ
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የደንበኛች ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ዳዊት ታረቀኝ እንደሚናገሩት፤ የአራዳ ክፍለ የወረዳ 4 ጽሕፈት ቤት የሚገኙት የማህበረሰብ ክፍሎች የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ማግኘት አልቻልንም በሚል ወደ ጽሕፈት ቤቱ በመምጣት ማመልከታቸው ገልጸዋል።
በዚህ አካባቢ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት እንዲሰጡ የተመደቡት ሠራተኞች አገልግሎቱን ለመስጠት ወደ ውስጥ ለመግባት እንዳልቻሉ ለጽሕፈት ቤቱ አስረድተዋል።ለዚህም እንደምክንያት ያቀረቡት አንዱ መጸዳጃ ቤቱ ከመንገድ ርቀት ያለውና ገብቶም ለመምጠጥ አስቸጋሪ መሆኑን ነው።
በውሃና ፍሳሽ ጽሕፈት ቤት ሕግ መሠረት አገልግሎት ለመስጠት የተቀመጠው ከመንገድ ያለው ርቀት እስከ 30 ሜትር ቦታ ላይ ነው፤ የአቤቱታ አቅራቢዎቹ የፍሳሽ አገልግሎት የጠየቁበት ቦታ ከመንገድ ላይ ያለው ርቀት 37 ሜትር የሚጠጋ ነው። ሆኖ ግን ጽሕፈት ቤቱ በተቀመጠ ሕግ ብቻ ተወሰኖ የሚቀር ሳይሆን፤ ከጎረቤትም ቢሆን መንገድና ማስገቢያ ምቹ ሁኔታ ካለ ተገብቶ የሚሰራበት ሁኔታ አለ።
በተለይ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆኑ የፍሳሽ አገልግሎት ከሌላ ቦታ ለማግኘት ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅና ያንን አገልግሎት ከፍለው ለማግኘት አቅሙ ስለማይኖራቸው፤ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ለማገልግል ለየት ያለ ትኩረት የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል።
አክለውም የጽሕፈት ቤቱ የፍሳሽ አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች እንዳመለከቱት፤ ወደነዋሪዎቹ በመሄድ አገልግሎት ለመስጠት ሲሞክሩ ወደ ውስጥ በሚወስደው መንገድ ላይ ያለው ኤሌክትሪክና ቅጠላ ቅጠሎች መኪናውን ወደ ውስጥ ለመግባት እስፖኪዮ የሚገነጥልና ወደ ውስጥ ዘልቆ ለመግባት አስቸጋሪ በመሆኑ ለመግባት ሳይችሉ መመለሳቸው እንደተናገሩ አብራርተዋል።
እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፤ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ጽሕፈት ቤት የተጻፈ ደብዳቤ ወደ እኔ የተመራ ሲሆን፤ ዛሬ ቀን 21/5/2013 ዓ.ም ወደ አካባቢው ባለሙያ በመላክ ሁኔታውን ማስመርመራቸውን ጠቁመው፤ እንደባለሙያ እይታ ከሆነ አሁን ላይ የመኪናውን እስፖኪዮ ሲሰብር የነበረው የቅጠል ቅርንጫፍ የተነሳ ቢሆን፤ የቀረውን የኤሌክትሪክና የስልክ ገመድ መኪና እንዲገባ ለማድረግ ገመዶች በእንጨት ከፍ በማድረግ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበት ሁኔታ የሚመቻች መሆኑ ገልጸዋል።
ነገር ግን የእነዚህ አቤቱታ አቅራቢዎች የፍሳሽ አገልግሎት ጥያቄ በጽሕፈት ቤቱ ከተቀመጠው ከመንገድ 30 ሜትር በላይ በመሆኑ የተለየ አድርጎ ለኮሚቴ ውሳኔ በማቅረብ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመጨረሻም ይህ ጉዳይ የቆየና ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የመጣን ጉዳይ ነው። የእናንተ ጽሕፈት ቤት ይህንን ዓይነት አሠራር ካለው ለምን በዚህ መንገድ ሳይፈታው ቆየ? እስካሁን እርስዎ እንዴት ሳይወቁት ቀሩ ስንል ለአቶ ዳዊት ላቀረብንላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ‹‹እኔ ቦታው ላይ የተመደብኩ በዚህ ወር አጋማሽ ላይ ነው፤ ለጉዳዩ አዲስ ነኝ›› ያሉት ኃላፊ ይህንን ችግር ለመፍታት ጊዜ የሚፈጅ ጉዳይ ስላልሆነ በፍጥነት ለመፍታት የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013