ራስወርቅ ሙሉጌታ
ጀቤሳ ደበላ ይባላል ውልደቱም እድገቱም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል አካባቢ ነው። ጀቤሳ ከአንደኛ እስከ አስረኛ ክፍል ትምህርቱንም የተከታተለው በተወለደበት አካባቢ ሲሆን የአስራ አንደኛና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን ደግሞ ከወንድሙ ጋር ወደ አዲስ አበባ በማቅናት አደይ አበባ አካባቢ አጠናቋል።
በ2005 ዓ.ም የአስራ ሁለተኛ ክፍልን ካጠናቀቀ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በቂ ነጥብ ያስመዘገበ ቢሆንም ገና የአስር ዓመት ልጅ እያለ በፖሊዮ ምክንያት በእግሩ ላይ የደረሰበት የአካል ጉዳት ያሰበውን ለማሳካት በጀመረው ጉዞ ላይ ፈተና እየጋረጠበት የልጅነት ህልሙንም እያጨለመበት መምጣት ይጀምራል።
ጀቤሳ ከልጅነቱ ጀምሮ አካል ጉዳተኝነቱ ሳይገድበው ራሱን ለትምህርት አስገዝቶ የኖረው የጤና ትምህርት በመማር ዶክተር ለመሆን የነበረውን ህልም ለማሳካት ከዛም የራሱን ህይወት ለመምራት ነበር። ነገር ግን በቂ ነጥብ አምጥቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ቢችልም ያሰበውን የትምህረት መስክ መቀላቀል ግን አልቻለም።
ይህም ሆኖ ግን ጀቤሳ ፈታኝ የነበሩትን ጉዞዎች በማለፍ ዛሬ ለብዙዎች አርአያ ለመሆን በቅቷል። «በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ስማር አካል ጉዳተኝነቴ ካሰቡክት ነገር ያደናቅፈኛል ብዪ አስቤ አላውቅም ነበር፤ በኋላ ግን ነገሮች እየተወሳሰቡብኝ መጡ» ጀቤሳ በድል ያሳለፋቸውንና ለዛሬ ውጤት የበቃባቻውን የፈተና ዓመታት እንዲህ ያስታውሳቸዋል።
ጀቤሳ የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ወስዶ ጥሩ ውጤት በማምጣቱ የህክምና ትምህርት ክፍልን ለመቀላቀል ወደ ተመደበበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲያቀና ሃላፊዎች «ትምህርቱ ላይከብድህ ይችላል ነገር ግን ስትማርም ሆነ ስራ ስትገባ ህመምተኞችን ማገላበጥ ማንቀሳቀስ የሚጠይቅ በመሆኑ ላንተ አስቸጋሪ ስለሚሆን መስክህን ልትቀይር ይገባል» የሚል ምከር ሀሳብ ከዩኒቨርሲቲው ሃላፊወች ይቀርብለታል።
በመጀመሪያ ምላሹ የዓመታት ህልሙን የሚያጨናግፍ ቢመስለውም ደጋግሞ ካሰበበት በኋላ ነገሩ አሳማኝ ሆኖ ስላገኘው የእነሱን ሀሳብ ተቀብሎ እዛው ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክት ትምህርት ለመማር ይወስንና ወደዛው ያቀናል።
በተመሳሳይ የዲፓርትመንቱ ሃላፊም ያለውን ችግር በመረዳት በተጨማሪም ተመርቆ ሲወጣም በስራው አለም በርካታ መሰናክሎች ሊገጥሙት እንደሚችል በመንገር ሀሳቡን ተቀብለው ያሰናብቱታል። እዛም የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና በጥሩ ውጤት ለማለፍ ቢበቃም በገቢው ለመማርም ለመተኛም በተለይ ደግሞ ለመጸዳጃ የተዘጋጁት ቤቶች ለእሱ የማይሆኑ በመሆናቸው ሌላ የትምህረት መስክ መፈለግ እንዳለበት ይወስናል። ለነገሩ እንደው ልሞክረው በማለት እንጂ የመጀመሪያ ቀንም ለፈተና የወጣው በሸክም በመሆኑ እንደማይቀጥል ውስጡ እየነገረው ነበር።
በደህናው ቀን በውጭው ዓለም አካል ጉዳተኞች አውሮፕላን ሲያበሩና ሌሎች ስራዎችን ሲሰሩ ይመለከት የነበረው ጀቤሳ የአካል ጉዳተኝነት ከምፈልገው የትምህርት አለም ያርቁኛል ብሎ ስላላሰበ በወቅቱ በጣም ውስጡ ይረበሽበትና ለሁለት ሳምንት ያህል ተስፋ በመቁረጥና በብስጭት እቤት ውስጥ ለማሳለፍ ይገደዳል።
ከወደፊቱ ተስፋ ማጣት በላይ እስካሁንስ ለምን ስማር ቆየሁ? እስካሁን የተማርኩትስ ምን ፋይዳ አለው? ወደማለት ይመለሳል። ያለበትን ሁኔታ የተረዱት ቤተሰቡና ጓደኞቹ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት በመንገር ሲያበረታቱት ከቆዩ በኋላ ጀቤሳም እቤት መቀመጡ ምንም እንደማይፈይድለት በመረዳትና መቼም ቢሆን ተስፋ ላለመቁረጥ ለራሱ ቃል በመግባት ሌሎች አማራጮችን ማማተሩን ይቀጥላል።
«እናም ለረጅም ዓመት ስመኘው የነበረውን ነገር ማሳካት ባልችል እንኳ በሆነ የትምህረት መስክ እዛው ዩኒቨርሲቲ ገብቼ መማርና መመረቅ አለብኝ ብሎ» ይነሳል። እናም ወደ አምስት ኪሎ ኢንጂነሪንግ ፋኩልቲ ያቀናል።
እዛም ማንን ማማከር እንዳለበት ግራ ገብቶት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት አካባቢ ሲንቀሳቀስ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና አካዳሚክ ዲን የነበሩት ዶክተር ጀሎ ኡመር ባጋጣሚ ያገኛቸውና የገጠመውን ነገር ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያዋያቸዋል። እሳቸውም አሁን የተጀመረ ላፕቶፕ ብቻ የሚያስፈልገው የትምህርት መስክ አለ ላፕቶፕም ከሌለህ እኔ እገዛልሀላሁ ብለው ከተጀመረ ገና ሁለት ዓመት ብቻ የሆነውን የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት እንዲከታተል ያደረጉታል።
እዛም ከገባ በኋላ ግቢ ውስጥ ያሉት የመፀዳጃና የመኝታ ክፍሎች ሌላ ፈተና ይሆኑበታል። እናም ጀቤሳ የቀድሞ የትምህርት ሚኒስቴር የነበሩትና የወቅቱ የአምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ዲን ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ዘንድ በመቅረብ ችግሩን ሲነግራቸው ምቹ ሁኔታ ወዳለበት ስድስት ኪሎ እንዳዲስ ትምህርቱን ቀይሮ እንዲሄድ ይመክሩታል።
ነገር ግን ጀቤሳ ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀርና ስድስት ኪሎ እያደረና እየተመገበ አምስት ኪሎ እየተመላለሰ መማሩን ይቀጥላል። ሽንት መሽናት ሲፈልግ ከአምስት ኪሎ ስድስት ኪሎ ድረስ መጓዝ፤ ፎቅ ላይ ትምህርት ሲኖር በልመና በተማሪዎች ሸክም መውጣት፤ ምግብ ቤቱ ፎቅ ላይ በመሆኑ ተማሪዎች እያመጡለት መመገብ የየእለት ስራው ሆኖ ለአንድ ዓመት ያህል ይቆያል።
ከዓመት በኋላ ግን ነገሮች የሚቀየሩበትና የጀቤሳም መከራ የሚቀንስበት አጋጣሚ ለመፈጠር ይበቃል። ጀቤሳ በአንዲት የተመረጠች ቀን የወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳነት የነበሩት ፕሮፌሰር ዶክተር አድማሱ ጸጋዩን ቢሯቸው ገብቶ ሲያናግራቸው ሁሉም ነገር እንዲመቻችለት ያደርጉለታል። ከዛን ጊዜ ጀምሮም ጀቤሳ የሚማርባቸው ክፍሎች፤ ላብራቶሪውን ጨምሮ በሁለት ሳምንት ውስጥ ምድር ቤት እንዲሆኑ ያደርጋሉ።
ጀቤሳ ለእሱ የተከፈተለትን በር በመጠቀምም ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ምቹ ያልሆኑ ነገሮች እዲስተካከሉ ለማስደረግም እድሉን ያገኛል። ይህንን ትግሉን ያስተዋሉ አካል ጉዳተኞች የማህበራቸው ተወካይ እንዲሆን ይመርጡትና ለሁለት ዓመት በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግል ይቆያል።
በዚህ ሁኔታ የአምስት ዓመት ቆይታውን ካጠናቀቀ በኋላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ለመያዝ ይበቃል። ዩኒቨርሲቲውም በተለያየ መስክ ሲያደርግ የነበረውን አስተዋጽኦ መነሻ በማድረግ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህረት እድል በውድድር ሰጥቶት ስለነበር ሁሉተኛ ዲግሪውን ደግሞ በኮምፒውተር ሳይንስ እዛው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መከታተል ይጀምራል።
ጀቤሳ በትምህርት ዓለም የገጠመውን ፈተና በአሸናፊነት ለመወጣት ቢበቃም ቀሪውና ከባዱ የህይወት ፈተና ከፊቱ እንደሚጠብቀው የተረዳው ውሎ ሳያድር ነበር። በአንድ ወቅት ቤት ለመከራየት ሲንቀሳቀስ በገጠመው ነገር ማህበረሰቡ ውስጥ ያለው አመለካከት አለመቀየር ብዙ ሊያስከፍለው እንደሚችል በመገመት ጠንካራ ልብ ሊኖረው እንደሚገባ ለራሱ ቃል ገብቶ ነበር።
በተጨማሪ የቅጥር ሁኔታ ላይሳካ እንደሚችል፣ ቢሳካ እንኳን ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል በመገንዘቡ ከትምህርቱ በተጓዳኝ የሞባይል ጥገና ተምሮ ነበር። እንደፈራውም ስራ ፍለጋ ወደ ተቋም ሲሄድ አንዳንዶቹ ለምጽዋት የሚመጣ እየመሰላቸው ሊመልሱት ሲሞክሩ ሌሎቹ ደግሞ ካላንዳች ጥያቄ አትችልም የሚል ምላሽ እየሰጡ ሲመልሱት ይቆያሉ።
በዚህ አይነት የቅጥር ስራ ነገር አስቸጋሪ መሆኑን የተረዳው ጀቤሳ ሐበዝግጅቱ መሰረት ከትምህርቱም ሳይርቅ የራሱን የገቢ ምንጭ ለማግኘት አራት ኪሎ ሥላሴ ህንጻ አንዲት ክፍል በመከራየት የሞባይልና ኮምፒውተር ጥገናውን መስራት ይጀምራል። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ መንግስት ለቴክኒክና ሞያ መምህርነት የስራ ማስታወቂያ ያወጣና ተወዳድሮ ያልፋል። ግን ሃላፊዎች ተቋሙ ያለበትን ሁኔታ በማየት ከመምህርነቱ ይልቅ የቢሮ ስራ ቢሰጠው እንደሚሻል ሀሳብ ያቀርቡለታል።
ጀቤሳ ግን የመምህርነቱን ነገር ባይሳካለትም ዩኒቨርሲቲም እያለ ሞክሮት ስለነበር በመምህርነቱ ለመቀጠል በመወሰኑ እነሱም ፍላጎቱን በመቀበልና የሚፈልገውን የማስተማሪያ ተቋም እንዲመርጥ በማድረግ በአሁኑ ወቅት በንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኮምፒውተር ሲስተም መምህር በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
በትምህርትና በስራ ከከፈለው መስዋዕትነትና ካገኘው ውጤት በተጓዳኝ ሁል ጊዜም ትዳር መስርቶ የቤተሰብ ሃላፊ ለመሆን ያስብ የነበርው ጀቤሳ በዩኒቨርሲቲ እያለ በአንድ አጋጣሚ የዛሬ የትዳሩ አጋር የሆነችውን ለማግኘት ይበቃል አጋጣሚውም እንዲህ ነበር።
በአንድ ወቅት ጀቤሳ ሞተር ሳይክሉን እየነዳ ወደግቢው ሲገባ ሴቶች መኝታ አካባቢ ከሌሎች ሴቶች ጋር ኳስ የምትጫወትን አንዲት መልከ መልካም ልጅ ያያል። ዓይኑ አርፎባት ስለነበር ተሽከርካሪውን ያቆምና በደንብ አስተውሏት ያልፋል። በሌላ ቀን በተመሳሳይ ግቢ ገብቶ ዊልቼሩን ከሞተር ላይ የሚያወርድለት አጥቶ በአይኑ ረዳት ሲፈልግ ያቺኑ ወጣት ከአንድ ጥግ ተቀምጣ ይመለከታታል።
ውስጡ ትንሽ ስጋት ቢፈጥርበትም እየፈራ እየተባ እንድትተባበረው ጥያቄ ያቀርብላታል። ወጣቷ በታላቅ ደስታ ጥያቄውን በመቀበል የፈለገውን ታደርግለታለች። ከቀናት በኋላ ጀቤሳ ከትምህርት ክፍሉ ወደ አልጋው ሲመለስ ከሌላው ጊዜ በተለየ ክፍሉ ጸድቶ ያገኘዋል። ያልተለመደ ነገር ስለነበር ጓደኞቹን እንዲህ ያደረገው ማነው ሲል ይጠይቃል። እሷ መሆኗን ይነግሩታል።
ጀቤሳ ከጓደኞቿ ስልኳን ይቀበልና ቀስ በቀስ ግንኙነቱን እያጠናከረ ይመጣና በአካል መገናኘት ይጀምራሉ። እናም አንድ ቀን በድፍረት ጓደኛ እንዳላትና እንደሌላት ያንንም አስከትሎ ፍቅረኛው መሆን ትችል እንደሆን ጥያቄ ያቀርብላታል። እሷም ብዙ ሳታንገራግር ትቀበለውና የጓደኝነት ጎዟቸውን ሀ ብለው ይጀምራሉ።
አልፊያ መሀመድ ተወልዳ ያደገችው በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ነው። በተወለደችበት አካባቢ እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ ከተማረች በኋላ ቀሪ ህይወቷን ያሳለፈችው በአዲስ አበባ ነው። አልፊያ ከቤተሰቧ ተለይታ አዲስ አበባ ከመጣች ጀምሮ ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ገጥመዋት የነበረ ቢሆንም ባላት መንፈሰ ጠንካራነት የተጋረጡባትን ፈተናዎች ስትሻገራቸው ኖራለች።
የአስራ ሁለተኛ ክፍልን ካጠናቀቀች በኋላ ግን ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያበቃ ነጥብ ስላልነበራት በግል ትምህርት ቤት ለመማር ስራ መስራት ስለነበረባት ፈላልጋ አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ትቀጠራለች። በዚህ ጊዜ ነበር ጀቤሳ የማስተረስ ዲግሪውን እየተማረ ሳለ ለመገናኘት የበቁት። አልፊያ ጀቤሳን ካወቀችው በኋላ የፍቅር ሀሳብ ባይኖራትም ያለበት ሁኔታ ያሳዝናት ስለነበር ለመተባበር ስትል መኝታ ቤቱን እየሄደች ታጸዳለት ነበር።
ታዲያ በአንድ ወቅት ከሴት ጓደኞቿ ጋር ሆና ስትጫወት እንደ ቀልድ በክራንችም በዊልቸርም ስለሚሄዱ አካል ጉዳተኞች ወሬ ይጀመርና በክራንች የሚሄዱት የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ፤ ማግባትም መውለድም ይችላሉ፤ በዊል ቼር የሚሄዱት ግን ይህንን ያደርጋሉ ወይ? የሚል ጨዋታ ይነሳል።
አካል አድርገውም ጓደኞቿ ስለጀቤሳ አንስተው አሁን ይሄንን ማን ያገባዋል? ሲሉ ይጠይቃሉ። አልፊያ ውስጧ ምንም የተፈጠረ ነገር ባይኖርም በማታውቀው ሁኔታ እኔን ቢጠይቀኝ ግን አገባዋለሁ ስትል ትመልሳለች። በወቅቱ ጓደኞቿ እሷም በንግግሯ ተሳስቀው ነገሩን እንደ ቀልድ ያልፉታል።
አልፊያ የእሱን ክፍል በማጽዳትና በአንዳንድ ነገሮች ትተባበረው እንደነበር ሁሉ ጀቤሳና ጓደኞቹም እሷን የከበዳትን ትምህርት ያስጠኗት ነበር። አንድ ቀን የሚከብድሽ ነገር ካለ ደውይ ብሎ ስልኩን ሰጥቷት ስለነበር ስራ ከለቀቀች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ትደውልለታለች። ስትደውል ግን ውስጧ ፍራቻ ስለነበር ስልኩን ካነሳው በኋላ ተሳስቼ ነው ብላ ትዘጋበታለች።
ከወራት በኋላ በድጋሜ በቴሌግራም ያገኛትና መገናኘት ይጀምራሉ። በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የጀቤሳና ፍቅረኛው አልፊያ የፍቅር ግንኙነት እያደገ ይመጣና ትዳር ለመመስረት ወደማሰብ ይሸጋገራል። ነገር ግን ጀቤሳ በውስጡ በርካታ ስጋቶች ነበሩበት፤ ቤተሰቦቿ ምን ይሉ ይሆን? አንዳንድ ለትዳር የሚያስፈልጉ ነገሮችስ እንዴት ይሟላሉ እያለ ሲያወጣና ሲያወርድ ቆይቶ ለአልፊያ ጭንቀቱን ያጋራታል።
ጀቤሳ ያነሳቸው ነገሮች በሙሉ በእነሱ መካከል ላለው ግንኙነት ኢምንት መሆናቸውን አልፊያ እንዲህ በማለት ትነግረዋለች «አንተና እኔ እስከተፈቃቀድን ድረስ ሌላ የሚመለከተው አካል አይኖርም። ለቤተሰቦቼም እንዲያውቁ እነግራቸዋለሁ እንጂ መፍቀድ አለመፍቀድ የእነሱ ጉዳይ አይሆንም፤ ቤት የማሟላቱም ነገር በቀላሉ ባለን አቅም የሚሆን ስለሆነ የሚያሳስብ አይደለም።
የአንተ አካል ጉዳተኝነት ለእኔ አይታየኝም፣ ፍቅሬንም አይቀንሰውም፤ አብሬህም ለመሆን ወስኚያለሁ፣ ዋናው ነገር አንተ ከእኔ ጋር ለመሆን ከልብህ መፍቀድህና መወሰንህ ብቻ ነው።» በዚህ ምላሽ ከፊቱ እንደ ተራራ የተጋረጠው ሀሳብ የተወገደለት ጀቤሳ አልፊያን በማመስገን ዝግጅቱን ይጀምራል።
አልፊያም የራሷን ነገር አጠናቃ ጠብቃው ስለነበር ጥር አስራ ሰድስት ቀን 2013 ዓ.ም ድምቅ ባለ ሰርግ በመጋባት የሶስት ጉልቻን ህይወት አሀዱ ብለው ለመጀመር ይበቃሉ። ዛሬ ጀቤሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ጥናት የጀመረውን ሁለተኛ ዲግሪውን በማጠናቀቅ ላይ ሲሆን አልፊያ ደግሞ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የአካው ንቲንግ ተማሪ ናት።
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013