ይቤ ከደጃች.ውቤ
አስተምሮ የሚያልፍ፤ ቁም ነገርን የሚያስጨብጥ ቀልድ ይናፍቃል። እናንተዬ ሳቅ ናፈቀን አይደል። የት ሄዶ ነው ግን። ከትከት ተብሎ የሚሳቅበት ሆድ ተይዞ የሚንቆራጠጡበት ሳቅ ቀን ከወዴት ሄዶ ነው? ስለ ቀልድ ስናነሳ አለቃ ገብረሃና ከማንም ቀድመው ይታወሱናል።
አለቃ ገብረሃና ሲባል «ብላቴና» እያለን ተረት ተረት እንጂ በዕውን ዓለም የተከሰቱ ሰው መስሎ አይታሰበንም ነበር። አለቃ ገብረሃና በቀልዳቸው የሚታወቁ ቢሆንም በትምህርታቸውም ምጡቅና ሊቅ ነበሩ ይባላል።
በቁመትም በአመለካከትም እየጎለበትን ስንሄድ አለቃ ገብረሃና በዕውኑ ዓለም እንደነበሩ ተረዳን። አለቃ ገብረሃና ለቀልዳቸው ዕውቅና ተሰጥቷቸው፤ በቤተመንግሥት የዳግማዊ ቴዎድሮስ፣ የዐፄ ዮሐንስ እና የዳማግዊ ምኒልክ አጫዋች ሆነው ነበር።
በዘመናቸው የሦስቱ ነገሥታት አጫዋች ቢሆኑም በዳግማዊ ቴዎድሮስ ዘመን ግን ከንጉሡ ጋር ብዙም መዝለቅ አልቻሉም፤ ኮስታራውና ቆፍጣናው ዐፄ ቴዎድሮስ ቀልድ ሲበዛባቸው አባረሩዋቸው፤ ምክንያቱ ደግሞ አለቃ ገብረሃና ሲቀልዱ በነገር ሲጎነትሉ ንጉሥ ነው ጭሰኛ፤ ገባሪ ነው አስገባሪ የሚባል ነገር አልነበረባቸውም።
አለቃ ገብረሃና የተወለዱት በደቡብ ጎንደር ፎገራ መንደር ነው። አንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለን ፎገራ በከብቶች ምርት ታዋቂ ነበረች፤ የፎገራ ከብት ተብሎ ሲጠራ አስታውሳለሁ፤ እንደ ሐረር ሰንጋ ማለት ነው።
ፎገራ በከብት ብቻ የምትታወቅ አይደለችም ከ1977ቱ ድርቅ ወዲህ አካባቢው በውሃ የረሰረሰ በመሆኑ ለሩዝ ምርት አመቺ ሆና ተገኘች። ዛሬ ፎገራ በከብት ብቻ ሳይሆን በሩዝ ምርትም ታዋቂ ነች። ወዳጆቼ ፎገራ በከብትም በሩዝ ምርትም ታዋቂ ናት ስላችሁ ዋናውን ነገር ዘነጋሁላችሁ።
ከላይ አለቃ ገብረሃና የተወለዱት ፎገራ ነው እንዳልኩት የአዲስ አበቤ አራዳዎች የሚቀልድን የሚተርብን ሰው በአራዳ ቋንቋ ፎጋሪ እያሉ ይጠሩታል፤ ፎጋሪ የቃሉ ምንጭ ተረበኛው አለቃ ገብረሃና ከተወለዱበት ፎገራ ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ።
ለምሳሌ በገጠር የሰው ሀብት የሚለካው ባለው የጋማ እና የቀንድ ከብት ቁጥር ነው። ብዙ ከብት ካለው ባለከብት ይባላል፤ ቀስ በቀስ ባለከብት የሚለው ባለሀብት ወደሚለው ተቀየረ። ሀብት የሚለው ቃል ምንጩ ከብት ከሚለው ቃል ነው የሚሉ ጽሑፎች ማንበቤን አስታውሳለሁ።
ሌላው ካነሳን ዘንዳ ሳልጠቅስ የማላልፈው የከብቶች ተረፈ ምርት ወይም እዳሪ ነው፤ እንደ ፋንድያ እበት የመሳሰሉት ጠዋት ከከብቶች በረት በእጅ ተዝቀው በቁና በምናመን ተወስደው አንድ ቦታ እንዲከመር ተደርጎ በመሬት ተጠፍጥፎ ማገዶ ይሰራባቸዋል። ኩበት የምንለው ማለት ነው፤ ስናጠቃልለው ከብት የሚለው ቃል የኩበትና (የማገዶ) ምንጭ ነው፤ የስነቃል ተመራማሪዎች ደግሞ የሚሉንን እንጠብቅ።
አንድ ዘመዴ ከገጠር መጥታ ልብስ አጋዛኝ ብላ ጠየቀችኝ፤ እኔ ግን በሌለኝ ብር አጋዛኝ ስትለኝ ግዛልኝ ያለችኝ መስሎኝ ተናድጄ ነበር። ጆሮዬ አንዳንዴ ያሳልፋል፤ የምትገዛውን ስጠይቃት ለበረኛ የሚሆን ልብስ አለችኝ።
የስፖርት ልብሶች የሚሸጥባቸው ቦታ ወሰድኳት፤ የምትኖርበት አካባቢ ዳገት፣ ቁልቁለት፣ ዐለት ቋጥኝ፣ የድንጋይ ጠጠሮች የበዙበት ስለሆነ ቦታው ለእረኛ እንጂ ለበረኛ (ለኳስ) የሚመች ነገር የለውምና የስፖርት ልብሱን ምን ልታደርገው ነው? እያለ ውስጤ ይጠይቅ ነበር።
ልብሶቹን በመስታወት ስታየው ሳቀችና አይደለም እኮ ምንድነው የምታሳየኝ? ብላ ለዘበኛ የሚሆን ጨርቅ እንደምትፈልግ አስረዳችኝ። አባቷ የአንድ የግል ድርጅት በረኛ እንደሆነ ስትነግረኝ ጥበቃ እንደሚሠሩ የገባኝ ዘግይቶ ነው።
ሕፃናት ተማሪዎች እያለን ትምህርት በራዲዮ ይተላለፍ ነበር፤ መምህራን ማስተማር ሲደብራቸውና የሬዲዮ ሰዓቱ ከሚያስተምሩት ትምህርት ከፍተው አዳምጡ ብለው ይደርቡልናል ይደበሩብናል። አንድ ሳይንስ መምህራችን አንዳንዴ ሬዲዮ ይዘው መጥተው አዳምጡ ይሉናል።
ቲቸር ሬዲዮኑን ከከፈቱ በኋላ ክፍል በረንዳ ላይ ሲጃራቸውን ሲመጡ አስታውሳለሁ፤ በመስኮት ስከታተላቸው ሲጃራቸውን ሲመጡ ጭስ ከአፋቸው ሲያወጡ ቀለበት ነገር እየተሠራ ሲወጣ ዐያቸው ነበር። ሲጃራቸውን ሲጨርሱ ይገቡና ትምህርቱን አዳመጣችሁ? በጣም ጥሩ ተማሪዎች፤ ዛሬ አልጠይቃችሁም ነገ አስረዳችኋለሁ።
የመግቢያውን ሙዚቃ ግን የሚዘፍንልኝ ሰው እመርጣለሁ አሉ። እኔን መረጡኝና ወደሳቸው እንድመጣ ጠሩኝ። እንዴት እንደመረጡኝ አላውቅም። በትምህርት ውጤትም ያን ያህል ውጤታማ አልነበርኩም ነበር። በመልክም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል መልክ የለኝም፤ ምናልባት ግን ከመልከ ጥፉዎች የተሻለ መልከ ጥፉ ስለሆንኩ ይሆናል።
መግቢያውን ሙዚቃ አንዴ ዝፈንልን አሉኝ። ደስ እያለኝ ዘፈንኩ፤ተማሪዎቹም ይስቃሉ እሳቸውም ይስቃሉ በጣም ሙቀት ስለተሰማኝ በዘፈኑ ተደስተው የሚስቁ መስሎኝ ነበረ፤ በእንከን የተሞላ ዘፈን እንደነበረ የተረዳሁት ዘግይቶ ነው። በወቅቱ ስዘፍነው ያልኩት ጀባ ልበላችሁና እናንተም ፈገግ በሉ። የዘፈኑ ዜማ ግን በጣም ደስ ይለኝ እንደነበር ስናገር ለግጥሙና ለዜማው ደራሲዎች ምስጋና በማቅረብ ጭምር ነው።
…. ሳይንስ ሳይንስ መድኃኒቴ
አስጨነቀኝ ሰውነቴ (ዘፈኑ ግን የሚለው አስጨነቀኝ ጤንነቴ ነበር)
ቁርሴን ታጥቤ
ፊቴን ስበላ
በህልሜ ታየ ሳይንስ ማታ … ዜማውን በጽሑፍ የመግለጽ አቅም ቢኖረኝ ኖሮ አስደምጣችሁ ነበር፤ የተፈጠረው ቴክኒክ ብልሽት እያያችሁ ባለማየት እንድታልፉኝ እማፀናለሁ።
አህያ ተጭና ስትሄድ ባጋጣሚ የተጫነችው ማዳበሪያ ተቀደደና ለንግድ ይሁን ለድድ (ለመብል) ባላውቅም እህሉ በትንሹ ፈሰሰ። አህያ ነጂውም በያዘው አለንጋ ከነረታት በኋላ ሊያቆማት ሞከረ። ስትቆምም መታትና ማዳበሪያውን ለመያዝና ገመዱን ፈቶ እህሉን ለማቆም ሲንቀሳቀስ አንድ አዛውንት አይዞክ አትናደድ ተረቱም እኮ «በሬ ያርሳል አህያ ምርቱን ያፈሳል» ነው የሚለው አሉት።
በቦታው ስለነበርኩ ሳቄ መጣብኝና በትንሹ ተንከተከትኩ፤ አይደለም አባቴ ተረቱ የሚለው «በሬ ያርሳል አህያ ምርቱን ያፍሳል» ነው ምናልባት እርስዎ ሲያነቡ ያፍሳል የሚለውን ያፈሳል መስሎት ሊሆን ይችላል፤ አልኳቸው። በርግጥ የሚያነብና የማያነብን በዐይን በማየት መለየት አይቻልም።
ሳያቸው ግን ማንበብ የሚችሉ ስላልመሰለኝ ስህተቱን ለመንገር አዛውንቱን ማሞካሸት ስለነበረብኝ ነው። የማያውቁትን ተረት ተርተው አህያዋን ሊያጣጥሉ ሞከሩ። ስንቱ ይገጥመኛል መሰላችሁ፤ አይቼ ማለፉን ለመድኩ እንጂ።
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013