ግርማ መንግሥቴ
ከማንምና ከምንም የጤና ጉዳይ የበላይ ነው። ያለ እሱ ምንም የለም፤ ማንም የለም፤ ሁሉም የለም። “ዋናው ጤና” ሲባልም በሌላ መንገድ መልዕክቱ የጤናን አስፈላጊነት፣ ወሳኝነትና አሳሳቢነት መግለፅ ነው። በመሆኑም ያነጋግራል፤ ያወያያል፤ ያሳስባልም።
በነጮቹ ዘንድ አንድ የተለመደ አባባል አለ፤ “ተደሰት፤ ምክንያቱም ጤና ደስታ ነው”ና (Be happy because Health is Happiness.) የሚል። ምንም የማይወጣለት እውነት ነው። የእኛውም ሥነቃልም ሆነ ሌላው (ለምሳሌ ዘፈኑ …) ከዚህ ከፍ ባለ መልኩ፤ ለዛውም በልዩ ልዩ አገላለፅ የሚለው ብዙ አለው።
አንዳንድ አገላለፆች ደግሞ አሉ፤ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ጤናን የሚሰብኩ፤ አስፈላጊነቱን የሚያፀኑ፤ “ጤናችን በእጃችን” መሆኑን የሚያሳብቁ። ከእነዚህም አንዱ “ሰው ሆዱን ይመስላል” የሚለው ሲሆን ትርጓሜውም የሰው መልኩም ሆነ ወዝና ወዘናው፤ ቅጥነቱም ሆነ ውፍረቱ፤ መታመሙም ሆነ ፈጥኖ የማገገሙ ጉዳይ፤ አስተሳሰቡም ሆነ አተያዩ፤ ተግባሩም ሆነ እንቅስቃሴው ወደ ሆዱ በሚያስገባው (በሚመገበው) የምግብ አይነትና ጥራት የሚወሰን መሆኑን መግለፅ ነው።
ትርጓሜው ይሄ ከሆነ የተናጋሪው የጤና ፍልስፍና (“philosophy of health”፤ ጥናቱ “Philosophy of Healthcare” ነው፤) ደግሞ ከብዙዎች የሚለይና “ከእነሙሉ ጤንነት፣ አስተሳሰብ፣ አቅም፣ አተያይ ወዘተ ለመኖር ካስፈለገ የተመጣጠነ ምግብ መብላት ይገባል” (ባጭሩ) የሚል ሆኖ ይገኛል። (እዚህ ላይ ግን “ሆድ”ንና “መብላት”ን ስናነሳ “ሆዱን ያለ ሆዱን ተወጋ” ከሚለው ጋር የማይገናኝ መሆኑን መግለፅ ተገቢ ነው።)
“የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም” የሚለውም ስፋትና ጥልቀቱን ባናውቀውም የራሱ የሆነ፤ “በበሽታ ተይዞ ከመውደቅ በፊት በሚገባ መመገብ” ተገቢ መሆኑን አስመልክቶ የሚለው አያጣም። እንዲህ እንዲህ እያልን ስንሄድ ከጤና ጋር በተያያዘ ብዙ የተነገሩ ጉዳዮች መኖራቸውን እንረዳለን። አሁን ወደ ዓለም አቀፍ ጉዳያችን እንሂድ።
የዓለማችን የእስከዛሬ ህይወት፣ ሂደትና አመጣጥ ከጤና አኳያ ለዘርፉ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች እንጂ ለእኛ፣ ለተራዎቹ ለጊዜው ብዙም አይደለምና ስለ መጪው፤ የተፈራው እንነጋገር።
ከጤና አኳያ ይህ ጥሩ፣ ይህ መጥፎ ነው ብሎ ከወዲሁ አንድ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም። እንኳን ለራሳቸው ለእኛም ይተርፋሉ ላልናቸውም ብልጭ ሳይልላቸው ነው ኮቪድ ድንገት ከች ብሎ የሚሊዮኖችን ህይወት ቀጥፎ አሁንም አለማችንን እያስጨነቀ ያለው።
ይሁንና ግን አሁን አሁን ደግሞ የኮቪዱን ሳንገላገል ከወደ “የዓለም ጤና ድርጅት” (WHO) የሚሰማው ወሬ ማስጠንቀቂያ በማስጠንቀቂያ ሲሆን በመልዕክቱም ሁላችንም ከወዲሁ እንድናስብበት፤ ማድረግ የሚገባንን እንድናደርግና የመከላከል አቅማችንን እንድናጎለብት፤ በዚህም ሊደርስ የሚችለውን የከፋ አደጋ ከወዲሁ እንድናስቀር፤ ማስቀረት ባይቻል እንኳን እንድንቀንስ የሚያደርግና ለዚህም ዓለም አንድ ሆኖ እንደ አንድ በጋራ ተቀናጅቶ እንዲሰራ (“Integrated approach” ይለዋል ተቋሙ) የሚያሳስብ ነው።
ድርጅቱ ይህን ሲለን ዝም ብሎ አይደለም፤ በምክንያትና “አስጊ” እና “አሳሳቢ” ያላቸውን በስም በመዘርዘር ነው።
እንደ ድርጅቱ ጥናትና ማሳሰቢያ የሚቀጥሉት አስር ዓመታት ከ13 በላይ የበሽታ አይነቶችና ለተለያዩ በሽታዎች የሚያጋልጡ (ተፈጥሯዊና ተፈጥሯዊ ያልሆኑ) ሁኔታዎች ዓለማችንን ይፈታተኗታል፤ የሰው ልጅም ከወዲሁ መላ ካልዘየደ የከፋ አደጋ ይጠብቀዋል።
እነዚህ የዓለም ጤና ድርጅት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ለዓለም እጅግ ሥጋት የሆኑት የበሽታ አይነቶች ልክ እንደ ኮቪድ ሁሉ ምንም አይነት ቦታ፣ ዘር፣ ቀለም፣ እድሜ፣ ፆታም ሆነ ሃይማኖት የማይመርጡ ለሁሉምና በሁሉም ቦታ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እኩል ስጋት ናቸው። በመሆኑም የሚያስፈልገው በጋራ ዕቅድና ተግባር ላይ የተመሰረተ የጋራ እንቅስቃሳሴ ነው።
እነዚህ የተባበረ ክንድን የግድ የሚሉት በሽታዎችና ሁኔታዎች በቁጥር 13 ሲሆኑ እያንዳንዳቸው የሰውን ልጅ ለሞት አሳልፎ የመስጠት ከፍተኛ አቅም ያላቸው፤ በሰው ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ላይም ከፍተኛ አደጋና ተጽዕኖን ማስከተል የሚችሉ ናቸው።
ድርጅቱ የመጀመሪያ ብሎ በ1ኛ ደረጃ ያስቀመጠው በአየር ለውጥ ምክንያት የሚከትለውን ቀውስ (Climate crisis) ሲሆን፤ በስሩም በርካታ ገዳይ ችግሮችን ዘርዝሯል። ከእነዚህ ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰው የአየር ብክለት ሲሆን በዓመት በአማካይ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች በዚሁ ችግር ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።
በአጠቃላይም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 25 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ ህይወቱን የሚያጣው ማለትም በዓመት ከሚመዘገበው ሞት ውስጥ ሩቡ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትላቸው የተለያዩ ቀውሶች ምክንያት ነው። በመሆኑም ይህ አደጋ እየከፋ ከመሄዱ በፊት የሰው ልጅ በመተባበርና ባንድነት አስፈላጊውን ሁሉ ሊያደርግ፤ መንግሥታትም ፖሊሲያቸውን መልሰው ሊያዩና ሊከልሱ ይገባል።
ሁለተኛው በዓለማችን ግጭቶችና ቀውሶች ዕለት በዕለት እየተስተናገዱ መገኘታቸው ግልፅ መሆኑና እነዚህ ግጭትና ጦርነቶች በሰው ልጅ ጤና እና የጤና አገልግሎት አቅርቦት ላይ የሚያስከትሉት ተጽዕኖ ነው። የእነሱ መከሰት ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸውና ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረስ እንዳይቻል ያደርጋል፤ አድርጓልም።
ለምሳሌ በ2019 ብቻ በ11 አገራት ለዕርዳታ በተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች ላይ 978 ጥቃቶች ተሰንዝሮውባቸው ለ198 ባለሙያዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። ይህ ብቻም አይደለም ግጭቶቹና ቀውሶቹ በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለስደት ስለሚዳርጉና በዛም ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች ስለሚጋለጡ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል።
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎችም የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መገንባት ስለማይቻል ሰዎች ህይወታቸውን እንደዋዛ እያጡ ነው፤ ይህም ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። ይህ አገራት ወደ ግጭት መሄዳቸውን አቁመው ወደ ድርድርና ውይይት በመምጣት ችግሮችን ሊፈቱ፤ ወይንም በአስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን ሊሰጡ ይገባል።
ሦስተኛው የ”ፍትሐዊነት” ጉዳይ ሲሆን ይህም በቀጥታ ከአገራት፤ ባጠቃላይም ከዓለም ምጣኔ ሀብት ጋር ግንኙነት ያለውና ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን የተመለከተ አድሏዊ አሠራር ነው። እንደ አንድ የጤና ችግርና መንስኤም ሆኖ የሚታይ ሲሆን ይህን ኢፍትሐዊነት ለማስቀረትና ሁሉም እኩል የጤናው ዘርፍ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ይላል የዓለም ጤና ድርጅት (አጤድ)።
እንደ አጤድ ከሆነ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ችግር አለ። ይህም በሰዎች መካከል ከፍተኛ የደረጃና ሌሎች ልዩነቶችን ፈጥሯል። ለምሳሌ በአንድ በማደግ ላይ ባለ አገርና በበለፀገ አገር መካከለ የሰዎች የእድሜ ጣራ በስምንት ዓመት ይለያያል። ማለትም በሀብታም አገራት ደሀ አገራት ካሉት በስምንት ዓመት የበለጠ ይኖራሉ ማለት ነው።
የዝቅተኛና መካከለኛ አገራት ዜጎች ለተለያዩ በሽታዎች የሚጋለጡ ሲሆን ካንሰር፣ ዲያቤቲክስና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከፍትሀዊነት፣ ከሥርዓተ ፆታ እኩልነት፣ ከእናቶችና ህፃናት ደህንነት፣ ከተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት፣ ከንፅህና አጠባበቅ፣ ከንፁህ ውሃ መጠጥ ወዘተ ጋር ሁሉ የተገናኘ ስለሆነ የጉዳት መጠኑ ከፍተኛ ነው። በመሆኑ ድርጅቱ ይህ ችግር እንዲቀረፍ በእሱ በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን በየአገራቱ የሚገኙ ተቋማትና መንግሥታትም በዚሁ ልክ እንዲሰሩ አሳስቧል።
ሌላው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና አቅርቦት ሲሆን ይህም ልክ እንደ ላይኛው ሁሉ የዓለም ህዝብ ጤናን ለመከላከል የሚያስችሉ ምርቶችንና እና ለመሳሰሉት ውጤቶች እጥረት የተጋለጠ ነው። ወይም አያገኝም። የእነዚህ እጥረት አለ ማለት ደግሞ ሰዎች ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋለጡ ማለት ነውና ሁሉም ችግሩን ለመፍታት በጋራ መንቀሳቀስ ይገባዋል ይላል ዓለም አቀፉ አጤድ። ወደ ተላላፊ በሽታዎች እንሂድ።
ተላላፊ በሽታዎች ገዳዮች ናቸው። በመሆኑም እነሱን መከላከልን የተመለከተው ሥጋት አንዱ የመጪዎቹ ዓመታት የሰው ልጅ የጤና ስጋት ሲሆን በተላላፊ በሽታዎች ምክንያትም በዓመት በአማካይ አራት ሚሊዮን ህዝብ እንደሚሞት፤ የመከላከሉ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ ካልቀጠለ ይህ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ እንደሚችል አጤድ ሰግቷል። በመሆኑም ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ መግሥታትም በፖሊሲዎቻቸውና እነዚህኑ ፖሊሲዎች ተግባራዊ በማድረግ በኩል ተጋግዘው እንዲሰሩ አጤድ አሳስቧል።
ሌላውና አጤድ “አይቀሬው” (inevitable) ሲል የገለፀው የቫይረስ ወረርሽኝ ሲሆን ይህን ለመከላከል የሚደረግ ዝግጅት (Epidemic preparedness)ን በተመለከተም አገራት በፍፁም ችላ ሊሉ አይገባም። ይህንንና ድንገተኛ (የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ) አደጋን ከመከላከል አኳያ አገራት (በተናጠልም ሆነ በጋራ) እያደረጉት ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባል።
የጤና ሥርዓታቸውንም እንደገና በመፈተሽ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ዝግጅት ከወዲሁ ካላደረጉና ሥራ ላይ ማዋል (evidence-based practices) ካልቻሉ ልክ እንደ አሁኑ ኮቪድ ሁሉ በመጪዎቹ ዓመታት ህዝባቸውን ለሌላ እልቂት ይዳርጋሉ በማለትም ያስጠነቅቃል። (ይህን ማስጠንቀቂያ መንግሥታት እስካሁን ይስሙ ወይም አይስሙ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።)
ሌላውና የመጪው አስር ዓመት ሥጋት ደህንነታቸው ያልተጠበቁ የምግብ አይነቶችና መድሃኒቶች ጉዳይ (Unsafe products) ሲሆን እሱም ጥራትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች በሰው ልጅ ላይ የሚያደርሱትን አደጋ የሚመለከት ነው። እንደ አጤድ ጥናት በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ የሰውን ልጅ ከሚያጠቁ በሽታዎች መካከል አንድ ሦስተኛው በዚህ እና መሰል ችግሮች አማካኝነት የሚመጣ ነው።
እንደ ድርጅቱ አተያይ መፈናቀል፣ ረሃብ፣ የምግብ ዋስትና ያለመረጋገጥ ጉዳይ መከሰታቸው ያለ፣ የነበረና የሚኖር ነው። በዚህ ላይ የሚመረቱት እንኳን ጥራታቸውን የማይጠብቁ ከሆነ ውጤቱ የከፋ ይሆናልና የሚመለከታቸው ሁሉ ከወዲሁ በተጠንቀቅ ሊቆሙና ችግሩን ለመከላከል ሊዘጋጁ ይገባል።
ይህ ብቻም አይደለም፤ እንደ አጤድ ጥናት ከሆነ በዚህ ሥር ሌሎች በርካታ የጤና ችግርችም አሉ። በቅባት (ስብ) ምግብ፣ ክብደት መጨመር፣ ሲጋራ ማጨስና በመሳሰሉት ምክንያቶች የሚከሰቱ ህመሞች መኖራቸው፤ ስኳር፣ ግፊት … እና የመሳሰሉት ሁሉ ከልክ በላይ እየጨመሩ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል (እዚህች ጋ መግቢያችን አካባቢ ጠቆም ያደረግነውን “Philosophy of Healthcare” ያስታውሷል፤ ተግባራዊም ያደርጓል)።
በመሆኑም እነዚህን የጤና ጠንቆች (በባለሙያዎቹ ቋንቋ “health risks”) ለመከላከል ከወዲሁ ሊታሰብባቸው ይገባል፤ መንግሥታትና የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላትም ፖሊሲዎቻቸውን ከዚሁ አኳያ እንደገና ሊቃኙ፤ ሊመረምሩም የግድ ይላል። አሁን ወደ ባለሙያዎች ጉዳይ እንዝለቅ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ የባለሙያዎች እጥረት አለ። ባለሙያዎችን ለማፍራት መዋዕለ ንዋይን የማፍሰስ ችግርም በከፍተኛ ደረጃ አለ። እነዚህ ሁለቱ በመኖራቸውም የጤናው ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ፤ የሰዎች የጤና አገልግሎት የማግኘት መብትም በእጅጉ እየተነፈገ ይገኛል። በመሆኑም ችግሩ ፋታ የማይሰጥ ብቻ ሳይሆን እንቅልፍ የሚነሳ ሁሉ ነው።
እንደ አጤድ ማስረጃ በ2030 በቂ የጤና ባለሙያ ይኖር ዘንድ አለማችን ሌሎች ተጨማሪ 18 ሚሊዮን የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት የግድ ይላታል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ የሚፈለገው የህብረተሰብ ጤናን የመጠበቅ ደረጃ ላይ መድረስ አይቻልም፤ እቅድና ፍላጎቱም ፕሮፓጋንዳ ሆኖ ይቀራል ማለት ነው።
የወጣቶችን ደህንነት የተመለከተው ጉዳይ ሌላው አሰሳቢ የመጪው ዘመን የጤና ጉዳይ ሲሆን፤ በየዓመቱ እድሜአቸው ከ10 እስከ 19 የሆኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች (Adolescent/teens) ይሞታሉ።
የሞታቸው ምክንያቶችም ኤችአይቪ/ኤድስ፣ የመንገድና ትራፊክ አደጋዎች፣ ራስን ማጥፋት፣ በመጠኑ ያነሰ የመተንፈሻ አካል ችግር፣ በእርስ በርስ ግጭት፣ ከመጠን ያለፈ አልኮሆል መጠጥ፣ ጥንቃቄ በጎደለው ልቅ ወሲብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግ እና የመሳሰሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በመሆኑም በዚህ ዙሪያ በወጣቱ ላይ በከፍተኛ ደረጃ የባህሪይ ለውጥ ለማምጣት እሰራለሁ በማለት የተሰማሩትም ሆኑ ሌሎች አካላት ትንሽም ቢሆን ያልዘገየ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል የሚለው የወቅቱና የወደፊቱን ያማከለ ጥሪ ሆኖ ቀርቧል።
የጤና ባለሙያዎች በተገልጋዩ ማህበረሰብ ዘንድ ታማኝነታቸው እንዲጨምር በሚገባ መስራት እንደሚገባም የአሁኑ ወቅት አጣዳፊ ከሆኑት የጤና ጉዳዮች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ይህም በአብዛኛው የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ማህበረሰቡን ከባለሙያው የመለየት ሥራን የሚሰሩ መኖራቸው፣ መድሃኒት አትውሰዱ የሚል ዘመቻ ድረስ የመሄድ ሁኔታ መኖሩ እና የመሳሰሉት በጤና አገልግሎቱ ዘርፍ በከፍተኛ ችግርነት የተጋረጡ ናቸው።
በአንዳንድ በባለሙያዎች ዘንድም ያለው ሙያዊ ስነምግባርም እንደዛው። በመሆኑም አገራት፣ መንግስታት፣ የጤና ተቋሟት፣ ባለሙያዎችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ይህንን ችግር በመዋጋት በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ሊያደርጉና መጪውን ትውልድ ከወዲሁ ሊታደጉ ይገባል ስንል መነሻችን አጤድ መሆኑን በመግለፅ ነው።
የጤናው ዘርፍ ቴክኖሎጂ ጠል ነው፤ አይናፋርነቱ ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። የቴክኖሎጂ ፎቢያ አለበት፤ እራሱ ቴክኖው ሲጠራው እንኳን ሲሽኮረመም የጉድ ነው እየተባለ መታማት ከጀመረ (ዛሬ አይደለም) ቆይቷል። “ድሮና ዘንድሮ ልዩነቱ ምንድን ነው?” ከተባለ ግን ዘንድሮ በጤናው ዘርፍ ቴክን መጠቀም የግድ እየሆነ መምጣቱና ለተግባራዊነቱ ቁርጠኝነት (እውነት ከሆነ) መታየቱ ነው።
አሁን ግን ይህ አይሰራም ተብሏል። ለምን? በሚቀጥለው 10 ዓመት ውስጥ የሚያጋጥሙ የጤናው ዘርፍ ተግዳሮቶችን በሚፈለገው ደረጃ ለመፍታትና በጤናው ዘርፍ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት የላቀ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማዳበር የግድ ነው ተብሏልና ነው። ተላላፊ በሽታዎችንም ከወዲሁ ለማስቀረት (ካልተቻለ ለመቀነስ) መፍትሄው ይሄው መሆኑም ተሰምሮበታል።
በዓለማችን በቢሊዮን የመቆጠሩ ሰዎች ንፅህናው ባልተጠበቀ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው። ይህ ደግሞ በተለያዩ በሽታዎች ለመጠቃት ዋናው መንስኤ ነው። ለምሳሌ በዓለም ላይ ካሉት የጤና ተቋማት አንድ አራተኛዎቹ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሌላቸው ናቸው።
ባጠቃላይ በሚቀጥለው አስር ዓመት ውስጥ የጤና አገልግሎቱን ዘርፍ የሚፈታተኑ፤ የዓለምን ህዝብ ለከፍተኛ የጤና እክል የሚያጋልጡ፣ በተለይ በታዳጊ አገራት የሚኖረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚያናጉ ወዘተ የጤናው ዘርፍ ችግርች ከፊት ለፊት ተደቅነዋል። ጥያቄው “እነዚህን ሰብአዊ ቀውሶች እና ችግሮችን ለማስቀረት ምን ያህል ተዘጋጅተናል?” የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ አይደለም ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013