አስቴር ኤልያስ
በአገሪቱ በህትመት ሚዲያው ዘርፍ ቀዳሚውን መስመር የያዘው አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዛሬም ግንባር ቀደምትነቱን በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛል። ላለፉት ስምንት አስርት ዓመታት በየቀኑ በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋሉና የሚካሄዱ ክስተቶችን እየዘገበ ወደህዝብ ሲያደርስ እንደቆየ ሁሉ ዛሬም በነባር ማንነትና በአዲስ መንፈስ ይበልጥ ራሱን እያዘመነና ብዝሃነትን እያሰፋ ይገኛል፡፡
በቅርቡም በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ የድርጅቱን የሚዲያ ባለሙያች ወደስፍራው በመላክ ትክክኛ መረጃ ወደህዝቡ እንዲደረስ ማድረጉ ይታወቃል።
የሚዲያ ባለሙያዎቹ በስፍራው ተገኝተው የሠሯቸውን ዘገባዎችና ያስቀሯቸውን ምስሎች የሚዘክር የፎቶ አውደ ርዕይም ከጥር 22 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከፍቶ ለህዝብ በማሳየት ላይ ይገኛል።
“ዘመቻ ለፍትህ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ይህንን የፎቶ አውደ ርዕይ የኢፌዴሪ የባህር ሃይል ዋና አዛዥና ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አወሉ አብዲ እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በጋራ የከፈቱ ሲሆን፣ በዕለቱ የባህር ሃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ያሰሙትን መልዕክት አዲስ ዘመን እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፤ መልካም ንባብ።
ጦርነት የፖለቲካ ፍላጎት የመጨረሻ የሰላ ጫፍ ነው
በአገራችን ተቃጥቶ የነበረውን አደገኛ አገር የመበተንና የማፍረስ አደጋ ተሻግረን በዛሬው ዕለት “ዘመቻ ለፍትህ” በሚል በተዘጋጀው የፎቶ ኤግዚቢሽን ላይ የአገር መከላከያ ሚኒስቴርን ወክዬ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ፡፡
እንደሚታወቀው ባለፉት ሦስት ወራት ያለፍንበት የአገራችን ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና አስፈሪም የነበረ፣ የቅርብም የሩቅም ወዳጅ ይሁን ጠላት በየራሳቸው አንፃር መጥፎውንም ጥሩውንም የተመኙበትና ሥጋታቸውን ያንፀባረቁበት አደገኛ የሆነ አገራዊ ስህተት አጋጥሞን ያለፈ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የገጠመን ብሔራዊ አደጋ መነሻው ምንድን ነው የሚለውን ማየቱ መልካም ነው፡፡
ፍትህ የማስከበር ዘመቻውን አንዳንዶች ጦርነት ሌሎች ደግሞ ውጊያ ይሉታል። ለእኔ የሚመቸውና ትክክለኛ ነው ብዬ የማስበው ውጊያ ብል ነው።ስለውጊያ ታዋቂ የዘርፉ ሰዎችና ፈላስፋዎች ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በርካታ ነገር ጽፈዋል። ከእነዚህ አንዱ ታዋቂው ወታደራዊ ፋላስፋ ‹ጦርነት የፖለቲካ ፍላጎት የመጨረሻ የሰላ ጫፍ ነው› ይላሉ።ይህም ማለት ሁለትና ከሁለት በላይ የሆኑ ኃይሎች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማሳካት ሲያቅታቸው ይህንን ፍላጎት በኃይልና በአመጽ ለማሳካት ወደ ጦርነት ይገባሉ።
በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎችም የማህበራዊ ሳይንስ ጠበብቶች እንደ እነ ፕሉቶና አርስቶትል ያሉ ደግሞ ‹ግጭት ከሰው ልጆች ማህበራዊ ኑሮ ጋር የተቆራኘ የማይቀር የታሪክና የማህበረሰብ ሂደት አካል ነው› ብለው ለሁሉም አይነት ግጭቶች ወይም ውጊያዎች ወይም ጦርነቶች መንስዔው ያሏቸውን ሦስት ነገሮች ያስቀምጣሉ፡፡
እነርሱም ፍርሃት፣ ፍላጎት እና ክብር የሚባሉ ማህበራዊ እሴቶች በአንድ አገር ወይም በአንድ ማህበረሰብ ወይም በአንድ ቡድን ውስጥ ለግጭት አሊያም ለውጊያ መንስኤ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚታመን ይናገራሉ። ከዚህ አንፃር እኛን የገጠመን ችግር የትኛው ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ጸሐፍት እንዲሁም አጥኚዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች የራሳቸውን ምልከታ የሚያስቀምጡ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በእኔ አተያይ ግን የገጠመን ችግር የሦስቱ ማህበራዊ ክስተቶች ውህድ ውጤቶች ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
እንደሚታወቀው ጦርነቱ የትግራይ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጦርነት አይደለም። ይህ ጦርነት ወይም ግጭት የህወሓት እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግጭት/ውጊያ ነው። ይህን ያልኩበት ምክንያት ህወሓት የተባለው የፖለቲካ ድርጅት በእድሜ ዘመኑ ጀምሮ ሦስቱንም ማህበራዊ ክስተቶች ላይ ፈላስፋዎች ያሏቸውን በማሟላቱ ነው።እንዲህ የምልበት ደግሞ የራሴ ምክንያት ስላለኝ ነው፡፡
አንደኛ ፍርሃት የሚለው ህወሓት ሲፈጠር ጀምሮ ከፍርሃቱ የተነሳ ጠላትና ወዳጅ በማለት በመፈረጅ የኖረና እንደዛ ካላደረገ መኖር እንደማይችል የተገነዘበ ድርጅት ነው። ውጭያዊ ጠላት እንኳ ቢያጣ በውስጡ ያሉትን ደጋፊና ተቃዋሚ የሚል ፍረጃ የሚከተል ነው።
ህወሓት ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በከፍተኛ የፍርሃት ችግር ውስጥ ስለነበር በአንድ በኩል ከኤርትራ የሚመጣብኝ ችግር አለ በማለት ሲፈራ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አጎራባች ክልሎች በተለይም ወንድማማች ሕዝብ የሆነውን የትግራይና የአማራ ሕዝብን ለማጋጨት የሚጠቀምባቸው ስልቶች መነሻ በማድረግ ከጎረቤት የሚነሳ ችግር አለ ብሎ በሥጋት ውስጥ ያድራል።
ሦስተኛ ከፌዴራል መንግሥት የሚነሳ ሥጋት አለ፤ ሌሊትና ቀን በአንድ ወገን አሃዳዊ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ጨፍላቂ እንዲሁም የተለያዩ ስሞችን እየለጠፈ ጠላት እየፈጠረ የሚያድር ስለነበረ ከሁሉም አቅጣጫ የሚነሳውን የሥጋት ሥነ ልቦና ወደከፍተኛ የሆነ የፍርሃትና የጭንቀት ችግር ውስጥ አስገብተውት ነበር ብዬ እስባለሁ።
በሌላ በኩል ህወሓት ያለበት ችግር ፍላጎት ነው። ፍላጎት የሚባለው ነገር ሰብዓዊ ነው፤ በተለይ ለሰው ልጅ መሻት ወይ መፈለግ ባይኖር ኖሮ ማህበራዊ ኑሯችንና መስተጋብራችን አላስፈላጊ ነው፤ ፍላጎት በራሱ ችግር አይደለም። ግን መጠን ይኑረው ነው።
መሻትና ፍላጎት ችግር ውስጥ የሚያስገባ መሆን የለበትም። የህወሓት ፍላጎት ባለፉት ሃያና ሃያ አምስት ዓመት በቃኝን ባለመቀበል ወይም አልበቃኝም ባለ ቁጥር በማጣቱ ምክንያት አሁንም በ90ዎቹ፣ በ80ዎቹና በ70ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ ሆነውም ቢሆን ኢትዮጵያን በድጋሜ ለማስተዳደርና በዚያውም ቁሳዊ ጥቅምና ፖለቲካዊ ሥልጣንን ለማሟላት የሚደረግ ጥረት ማሳያ መሆኑ ፍላጎቱ ገደብ ያጣ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡
ሦስተኛው ክብር የሚለው ወይም ደግሞ ለራስ የሚሰጥ ዋጋ የሚባለውን ነገር ስናይ ማንም ሰው ለራሱ ዋጋ መስጠት አለበት። ለራሳችንም ክብር ካልሰጠንና ለሌላውም ክብር ካሰጠን ሌላውም ለእኛ ክብር አይሰጥም። ይህ በበጎ ጎኑ የሚታይና መኖር ያለበት ማህበራዊ መስተጋብር ሆኖ ሳለ ነገር ግን ለራስ ከሚገባው በላይ ዋጋ መስጠት እና ራስን ከሚገባው በላይ መተመን የሚያስከትለው አደጋ በትክክል ተንፀባርቋል ብዬ አስባሁ።
እኛ የተለየን ነን፤ ምሥራቅ አፍሪካን መምራት እንችላለን፤ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው።እኛ የሌለንባት ኢትዮጵያ ልትኖር አትችልም ብለው ራሳቸውን በዛ አንፃር የሚተምኑ ቡድኖች ለራሳቸው የሰጡት ዋጋና ቦታ ራሳቸውንና አገራቸውን ወደችግር አስገብቷቸዋል፡፡
በእኔ አተያይ እነዚህ ሦስት ማህበራዊ ክስተቶች ህወሓትን ከራሱ በላይ ኢትዮጵያን አሳንሶ በማየት ራሱን ከኢትዮጵያ በላይም ከትግራይ ህዝብም በላይ አድርጎ በማየት ለኢትዮጵያም ሆነ ለትግራይ ህዝብ በማያስብ መልኩ በፍፁም ሊጠበቅ በማይችል ምናልባትም ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የመጨረሻው ምሽግ ነው እያልን የምንዘምርለትን መከላከያ ባልታሰበ ጊዜና ሰዓት የጥቃት ሰለባ እንዲሆን አድርጎናል።
ይህ ከመጠን ያለፈ ፍርሃት እና ስግብግብነት እንደዚሁም ከሚገባው በላይ ለራስ ዋጋ መስጠት ነው። ሌላው እንዲረሳ ማድረግና ራስን ከሌላው በላይ በመለየት ስሎ ማየት ወደአጠቃላይ የድርጅት ቀውስ፤ ከድርጅቱ ቀውስ ባሻገር ደግሞ አገራችንን እና ተቋማችን መከላከያ ወደከፍተኛ ቀውስ እንድንገባ ያስገደደ ነው። የጦርነት አደጋ ለአገራችን፣ ለሠራዊታችንና ለሕዝባችን ደቅነውብን ቢሆንም በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን፣ በአማራና በአፋር ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ የማያቋርጥ ድጋፍና የወኔ ስንቅ ማንም ከሚገምተው በላይ ባጠረ ጊዜ ጦርነቱን ለማሸነፍ በቅተናል፡፡
ታሪኩ ተደብቆ እንዳይቀር
ይህን ዛሬ ላይ ሆነን ስናስተውለው ሲናገሩትም ሲያዳምጡትም ቀላል ይምሰል እንጂ የተደገሰልን አደጋ በአጭር ጊዜ አልቆ አሁን ባለንበት ቁመና ልንገናኝ እንችል ይሆናል ብሎ ለማሰብ በፍፁም ይከብደኛል። ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ኩራቴና ክብሬ ተነክቷል ብሎ ባሰበ ጊዜ ሁሉ በሚያሳየው አንድነትና ቆራጥነት የተጋረጠብን አደጋ ሌሎች እንደተመኙልን ሳይሆን እኛ መሥራት እንደቻልነውና የኢትዮጵያ ሕዝቦች መሥራት እንደቻሉት በአጭር ጊዜ ለመቋጨትና ወደመጨረሻው ምዕራፍ የተቃረብንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ይህ ውጊያ ትግራይ ውስጥ ያጋጠመን ችግር ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በህወሓት እና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል እንጂ አደጋው ሲያጋጥም የነበረው መጠንና የአደጋው ስፋት በተለይ ቦታው ላይ የነበርን የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት ጉዳዩን ከምንናገረው በላይ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይገነዘቡታል ብዬ አስባለሁ።
ህወሓቶች ሲያስቡ ሠራዊቱን አንደኛው አማራጭ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ በማስፈታት እንዳይሠራ በማድረግ ሥርዓቱንና አገራዊ ማንነቱን መጠበቅ የሚያስችል ኃይል አድርጎ ወደፈለጉት የስልጣን ማማ ላይ ለመውጣት የሚያስችላቸውን መንገድ መጥረግ ሲሆን፣ ይህ ካልተሳካ ‹‹ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም፤ 70 በመቶ 80 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ወታደራዊ አቅም ዕዝ ነው፤ የሥርዓቱ እና የአገሪቱ የመጨረሻ ኃይል ነው የሚባለው መከላከያ እንዳይዋጋና እንዳይሠራ ማድረግ ከቻልን መንግሥት መንግሥትነቱን ያጣል።ስለዚህ እኛ የሌለንበት አገር፣ እኛ በአመራሩ ላይ የሌለንበት መንግሥትና ሕዝብ ብትንትኑ ይውጣ›› በሚል ነው እየተጫወቱ የነበረው።
ይህ ጦርነት ሲያጋጥም የነበረበትን ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን ማንሳቱ ጠቃሚ ነው። ታሪኩም ተደብቆ እንዳይቀር ነው እንጂ የበቀል ዘር ለመዝራት ታስቦ አይደለም።ስህተትን በድጋሜ ላለመሥራት በመሆኑ ‹‹ዘመቻ ለፍትህ›› በሚል መሪ ሐሳብ የቀረበውም የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ዓላማ እሱ ነው። ይህን ጉዳይ ሳይዛባ በትኩሱ ታሪክ ለሚሰንዱ፣ ለሚጽፉ፣ ለሚመራመሩ የተወሰነ መረጃ መስጠት ጠቃሚ ይመስለኛል።
የጦርነቱ ማዕከል
ጦርነቱ እንደተጀመረ የጦርነቱ ማዕከል የነበረው ሰሜን ዕዝ ነው። ህወሓት ሰሜን ዕዝን በማጥፋት ወደስልጣን መምጣት ይቻላል ብሎ ሲያስብ አሁንም እያሰበ ያለው የ1960ዎቹና 1970ዎቹ እሳቤን ነው፡፡ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ያደረጉትን በ21ኛው ክፍለ ዘመን እናደርጋለን ብለው አስበው ስለነበር ምናልባትም ውድቀታቸውን ያፋጠነው ይኸው አስተሳሰባቸው ይመስለኛል። የመከላከያ ሠራዊቱ የተገነባበት ማህበራዊ እሴቶች ግምትና ዋጋ ባለመስጠት ከ25 እስከ 30 ሺህ የሚጠጋ የሰሜን ዕዝን በአንድ ጊዜ ከሥራ ውጭ በማድረግ ወደስልጣን እንመጣለን ብለው ነው ያሰቡት።
ይህን ሲያስቡ እንደ ወታደር ያቀዷቸው ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ ሰሜን ዕዝን ባለበት፣ ሥራ በዋለበት፣ ግማሹ አጨዳ ሲያጭድ በዋለበት፣ ገሚሱ ደግሞ አንበጣ ሲያባርር በዋለበት፣ ሌላው ደግሞ የዕለት ተዕለት ሥራውን ምሽግ ቁጭ ብሎ የአገሩን ድንበር እየጠበቀ መደበኛ ሥራውን እየሠራ ባለበት ጥቃት ሲፈጽሙበት፤ ሌላኛው ከትግራይ ክልል ውጭ ያለው ኃይል ደግሞ ምን ያደርጋል የሚል ነገር ለማሰብ ሞክረዋል።
ይህን አስተሳሰብ ማንሳታቸው እንደወታደር ትክክል ነው። ነገር ግን ግምገማቸው ችግር ነበረበት። ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለመንግሥት ያላቸው ግምት የተሳሳተ ነበር። ቢያንስ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንኳ በምን ያህል ፍጥነት ኃይል ማንቀሳቀስ የሚችል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወታደር እንደሆነና የወታደር አመለካከት እንዳለው እንኳ ቦታ ሊሰጡት አልቻሉም። እናም ዕቅዳቸው ሰሜን ዕዝን በዕቅዳቸው መሠረት ‹‹ከጥቅም ውጭ እናደርጋለን፤ ትጥቅ እናስፈታለን፤ የሚማረክ ይማረካል። አመራሩን እናስራለን።ወታደሩ እጁን ይሰጣል፤ ካልሰጠ እንወጋለን፤ ይህን ስናደርግ ምዕራብ ዕዝ፣ ደቡብ ዕዝ፣ ምሥራቅ ዕዝ ምን ሊያደረግ ይችላል›› ብለው የተሳሳተ ግምገማ መያዛቸውን ዕቅዳቸውን በኋላ ላይ ስናገኘው አስቀምጠዋል፡፡
‹‹ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ስንፈፅም ምዕራብ ዕዝ በቦታው ለመድረስ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን የሚፈጅ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል›› ሲሉ ነው ያስቀመጡት። ለዚህም ምክንያት ብለው ያስቀመጡት ሸኔ አለ፤ የአካባቢው በረሃማነት አለ ብለው ነው። መንግሥትም ቢሆን ሰላም በማረጋጋት ላይ ነው ያለው። ቀጣናው በራሱ ችግር ያለበት ነው።ስለዚህ ይህን የምዕራብ ዕዝ ወደውጊያ ለማስገባት ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ይፈጃል ብለው ነው ያሰቡት፡፡
ደቡብ ዕዙን ከሞያሌ አንስቶ መቀሌ ለማምጣትና ወደውጊያ ለማስገባት ከአስር ቀን ያላነሰ ጊዜ ይፈጃል የሚል እንዲሁም ምሥራቅ ዕዝን ደግሞ ከአምስት ቀን እስከ ሰባት ቀን ይፈጃል ብለው ነው ያሰቡት። ይህን ሲያስቡ የሚያስቡት የራሳቸውን የግምገማ መነሻ እነሱ የሚያውቁት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን አንድ የሳቱት ነገር መንግሥት መንግሥት እንደሆነና በቦታው እንዳለ፤ መንግሥት ብዙ ሀብት እንዳለው፤ ጦርነት ሲነሳ ሁሉም ሀብት ወደጦርነቱ እንደሚተም ቦታ አለመስጠታቸውን ነው።
እነሱ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ይፈጅበታል ያሉት ምዕራብ ዕዙ ውጊያ በቀን 24 ሌሊት ላይ ተነስቶ በቀን 26 ማታ ጎንደር አልፎ በቀን 27 ንጋት ላይ ሶሮቃ ውጊያ ውስጥ ገብቷል። 24ኛው ክፍለ ጦር ውጊያ ገብቷል፤ በቀን 28 እና በ29 15ኛው ክፍለ ጦር ከጅማ ተነስቶ ውጊያ ገብቷል። ምሥራቅ ዕዝ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ይፈጅበታል የተባለው እግረኛ ክፍለ ጦሮች በከፍተኛ ፍጥነት ወደግንባር በመገስገስ በአራተኛው ቀን ደርሰዋል፡፡
ከተለያየ የሱማሌ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ላይ ተሰባስበው በአጭር ጊዜ ህብረተሰቡ አይሱዙ ያለው አይሱዙውን፣ ከባድ የጭነት መኪና ያለው እሱኑ መኪናውን፣ አውቶቡስ ያለው አውቶቡሱን ያለኮንትራት፣ ያለስምምነት፣ የኢንሹራንስ ጉዳይ ከግምት ሳይገባ በተገኘበት ‹‹ይኸውላችሁ ተጠቀሙ›› ነው ያለው። ይህን ያሉት ባለሀብቶቻችን ቁጥራቸው ብዙ ነው። መስተዳድሮችም እጅግ ብዙ ናቸው፡፡
በዚህ ፍጥነት እነሱ እንዳሰቡት ‹‹ከአምስት እስከ ሰባት ቀን እነሱ እስከሚጓዙ በሑመራ ግንባር ያለው ጎንደርንና ማክሰኚትን ተቆጣጥሮ ይቆማል። በደቡብ ግንባር ያለው ወልዲያ ተቆጣጥሮ ይቆማል። ከዚያ በኋላ ፌዴራል መንግሥትን አስገድደን ወደ ድርድር እናስገባዋለን። ተመልሰን አራት ኪሎ እንገባለን›› በሚል ነው ያሰሉት። ይህ በየትኛውም የወታደራዊ እሳቤ አላቸው በሚባሉ የውጊያ ሊቆች ነን ከሚሉ ወታደራዊ አዛዦች በበላይነት ከሚያስተባብሩ የውጊያ ድግስ በተዓምር ሊጠብቅ የሚችል አይደለም፡፡
የሳቷቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። አገራዊ አቅም የሚባል፣ የህዝብ ሥነ ልቦና የሚባል፣ የመንግሥት አቅም የሚባል ዋጋ አልሰጡትም፤ ባለመስጠታቸው በውጊያው ተሸንፈዋል ብቻ ሳይሆን እጅግ በፈጠነ ጊዜ የሚይዙት፣ የሚቋጥሩት የሚፈቱትን ለማየትና ለመለየት ጊዜ ባላገኙበት ሁኔታ ውጊያውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ዕድል ሰጥቶናል። የእነሱ ድክመት ለእኛ ዕድል ሰጥቷል። አንዱ ለድላችን መፍጠን የእነሱ የግምገማ ችግር እንደ አንድ ግብዓት መወሰድ አለበት፡፡
ሁለተኛው የሠራዊታችን ጀግንነት ነው። ሠራዊታችን ምንም እንኳ በተኛበት ሳይዘጋጅ ጥቃት ይድረስበት እንጂ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ዋጋ አልሰጡትም።የተበተነ፣ ትጥቁን የተቀማ ሠራዊት አይዋጋም ብለው ነው ያሰቡት። ሠራዊታችን ግን ሌሊት ላይ ድንገት ስለሆነ በነጠላ ጫማ፣ አንዳንዱ እጁ ላይ የምትገኘዋን መሣሪያ ይዞ፣ ሌላው የጓደኛውን መሣሪያ እያነሳ የቻለ እየተዋጋ ያልቻለ ባለበት ምሽግ ውስጥ ለቀናት እና ለሳምንት የሚጠጋ ጊዜ እየተዋጋ የክፍላቸውን ክብር ያስጠበቁ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያስመሰከሩ በጀግንነት የተሰው፣ በጀግንነት እየተዋጉ ወደአጎራባች አገር ድንበር ወጥተው እንደገና ተደራጅተው ደከመን፣ ይህ ጎድሎናል የሚል ጥያቄ ሳያነሱ ተመልሰው አገራዊ ክብራችንን ለማስመለስ ኢትዮጵያን ለማዳን፣ መንግሥታችን በሁለት እግሩ ቆሞ እንዲቀጥልና አገርና ሕገ መንግሥት ለማስከበር ነው የመጨረሻ ዓላማችን እና እሱን መወጣት አለብን ብለው የተዋጋው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ለድሉ መፍጠንና አሁን ላለንበት ቁመና ለመገኘት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
በዚህ ውጊያ ውስጥ ጸሐፊዎች ሊጽፉት የሚገባ፣ ታሪክ አጥኚዎች በደንብ ሊያጠኑት የሚገባ ትልቅ ጀብዱ ተፈጽሟል። በጣም የማይረሳ ኢትዮጵያውያን አንዱ ባህሪያችን ለጠላት አለመማረክ ነው። ይህን በዓለም መድረክም አድርገነዋል፤ በብዙ ጦርነቶች አድርገነዋል። አለመታደል ሆኖ እርስ በእርስ ጦርነቶቻችንም ጊዜ አድርገነዋል። የእርስ በእርስ ጦርነት አካል በሆነውም በአሁኑ ጦርነት የሁለት ዓመት የውትድርና አግሎግሎት ያላቸው ሁለት ሴት ወታደሮች 31ኛ ዓድዋ ክፍለ ጦር ውስጥ እየተዋጉ ጥይታቸው ሊያልቅ ሁለትና ሦስት ጥይት ሲቀራቸው ‹‹በጠላት አንማረክም፤ እኛ ምሽግ ቁጭ ብለን ተወልደው ባደጉ ኢትዮጵያንና ታሪኳን በማያውቁ በስመ ልዩ ኃይል የተደራጁ ወታደሮች እጅ ሰጥተን እነሱ እጅ ላይ ከምንወድቅ ራሳችንን እናጥፋ›› ብለው ነው የወሰኑት። ጥይት እያለቀ ነው፤ የሚያቀርብ ረዳት የለም፤ የጠላት ኃይል ደግሞ እየጨመረ ነው። የወገን አቅም በአንፃሩ መዳከም አለ፤ መዳከሙ በቁጥርም በተተኳሽም ነው።ከማንም በላይ ደግሞ የተተኳሽ ችግር ነው።መጨረሻ ላይ ሴት ወታደሮቹ የወሰኑት ውሳኔ ‹‹ለጠላት መማረክ ስለሌለብን አንቺ እኔን ግደይኝ፤ እኔን ከገደልሽ በኋላ ራስሽን አጥፊ፤” እስከመባባልና ተግባራዊ እስከማድረግ የደረሱበት ሁኔታ ነበር የነበረው።
ስኬቱ የተገኘው የሁለት ዓመት አገልግሎት ያለው ወታደር የተለየ ስልጠናና ብቃት ስለፈጠረ አይደለም።ኢትዮጵያዊ የመሆናችን ውጤት ማሳያ ነው።የዚህ አጋጣሚ አሳዛኙ ገጽታ ሁለቱ ወታደሮች ራሳቸውን ካጠፉ ከአምስት ደቂቃ በኋላ የመጣው የጠላት ኃይል መቀጠል ወደማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ተሸንፎ ከሞትና ከመቁሰል የተረፉት የክፍላቸው አባላት እንደገና ቁመናቸውን አደራጅተው ወደኤርትራ ድንበር ወጥተው ማትረፍ ቻሉ። አምስት ደቂቃ ታግሰው ቢሆን እነዛ ጀግና ሴት ወታደሮች በህይወት ሊኖሩ ይችሉ ነበር።ነገር ግን ፈጥነው ወሰኑ።
የዚያን ያህል ነው ጀግንነት የተፈፀመው። የሁለት ዓመት የውጊያ ልምድ ምን ያህል በራስ ላይ መስዋዕትነት መክፈል እንዳለብንና ለዓላማ፣ ለሙያ ክብርና ለሰንደቅ ዓላማ መሰዋዕትን የሚያሳይ ነው። ጁንታው ከአንድ ሺህ 290 በላይ መኮንኖቻችንን አስሮ፣ አንገላቶ፣ በእግር ስንት በርሃ እያስጓዘ ባሰቃየበት ወቅት ከመኮንኖቻችን ጋር የታሰሩ የበታች ሹማምንትና ወታደሮች በጋራ የእግር ጉዞ እያስጓዘ ስለነበረ መኮንኖቹን ለብቻ ጁንታው ሲፈልጋቸው ወታደሩ ‹‹እኛን ገድላችሁ ጨርሱን እንጂ ለብቻ ነጥላችሁ መኮንኖቻችንን አትወስዷቸውም›› እያለ ጁንታው ከመኮንኖቹ ጋር እንዲገናኝ የሚያስችል ጊዜ እንዳይኖር ሲያደርግ የነበረውን ጥረት ወታደሩም፣ የበታች ሹማምንቱም በደንብ ተሰንዶ ሊያዝ የሚገባ ታሪክ ነው። ወታደሩ ራሱ ይኑር ይሙት በማያውቅበት ሁኔታ ስለመሪዎቹ ይጨነቅ ነበር። እርሱ ራሱ ትጥቁን ፈትቶና ተማርኮም በጠላት እጅም ወድቆ ስለመሪዎቹ ደህንነት ነበር ሲያሳስበው የነበረው።
በሌሊትም ይሁን በቀን መኮንኖቹ የተለየ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በእያንዳንዷ እንቅስቃሴ አብሮ የነበረና ስለእነሱ የሚሟገት ጀግና ወታደር ነው የነበረን። በጁንታው ቁጥጥር ሥር የገባውም ይህን ገድል ይሠራል፤ እየተዋጋ የወጣው ደግሞ ጀግና አመራሮች፣ ጀግና ተዋጊ ወታደሮች፣ ጀግና መከላከያ ነው። በእርግጥም ከምንለው በላይ በተግባር ተመስክሯል። የማንም አገር ሠራዊት አራትና አምስት ቀን ተጉዞ፣ ተርቦና ተጠምቶ እንዲሁም ተንገላቶ በተነፃፀሪም በደህንነት ቦታ ላይ ነኝ ቢል እንኳ ራሱን ያስታምማል እንጂ ወደቦታችን መልሱን ወደውጊያው አስገቡን ብሎ የሚለምን የማንም አገር ወታደር አይኖርም። የኛ ወታደር ግን ለምኗል።
እኔ በነበርኩበት፣ ጄኔራል አበባው በነበረበት ሽራሮ አካባቢ ኤርትራ ድንበር ላይ ተሰባስበው አራት ክፍለ ጦሮች የጠየቁት ይህንን ነው። እነዚህ ክፍለ ጦሮች አራት አምስት ቀን በእግራቸው ተጉዘውና ተርበው ተጠምተው የሁለቱ አገር ድንበር ላይ ከደረሱ በኋላ አመራሮች ሄደን ስናገኛቸው ምክንያቱም ብዙ አመራሮች ታስረዋል፤ ተንገላተዋል።ግን ደግሞ ጀግና አመራሮች ስለነበሩ ስለራሳቸው ድካምና እንግልት አልነበረም የተጨነቁት። ደህንነቴን አረጋግጫለሁ አልነበረም ያሉት። ደህንነቴ አሁንም አልተረጋገጠም፤ አገርና መንግሥት አደጋ ላይ ነውና እባካችሁ መልሱን፣ አገር አደጋ ላይ ናት ነበር ያሉን። ይህን የሚያደርግ የማንም ሠራዊት የለም። በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ስለሆንን ያደረገግነው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
የትግራይ ሥዝብና ህወሓት አንድና ያው ያለመሆናቸው በግልጽ የታየበትከዚህ በተጨማሪ ይህ ሁሉ በደልና ጥቃት ሲደርስብን የትግራይ ህዝብ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለውን ሚና ሳያነሱ ማለፍ ደግሞ ተገቢ አይደለም። የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው የሚለው የህወሓት ትርክት ፉርሽ መሆኑ የተረጋገጠው በዚህ ጦርነት ነው ብዬ አስባለሁ። በመቶ ሺዎች የሚገመት የጦር መሣሪያ መተኮስ ለሚችል እድሜው 18 ዓመት በላይ ለሆነ ሁሉ አስታጥቆታል። መደበኛ ፖሊስና ልዩ ኃይሉን ትተን ህዝቡ ተገዶም ቢሆን መሣሪያውን መውሰድ ነበረበት።
የሑመራ ግንባርን ለብቻ ትቼ በምዕራብ ግንባር ከመጀመሪያዋ ሽራሮ ከተማ ጀምሮ መቀሌ እስከምንገባ እና ከመቀሌ አገረ ሰላም ከአገረ ሰላም ተንቤን፣ ተከዜ፣ ቆላ ተንቤን እስክንገባ የትግራይ አርሶ አደሮች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች በሠራዊታችን ላይ አንድ ጥይት አልተኮሱም። እሱ ብቻ አይደለም፤ የወለደች የወታደር ባለቤት መኖሯን የሰሙ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሰባስበው ለአራሷ የሚገባትን አድርገው ካምፕ ላይ ጥቃት እንዳይደርስብሽ ብለው ቤታቸው ወስደዋታል። ገበሬዎች ያሉት የከተማ አካባቢ ስለነበር አሁንም ደህንነቱ ስላላስተማመነ አራሷን ከነልጇ ገጠር አካባቢ ወዳለው ቤት ወስደዋታል። ኢትዮጵያዊነት ማለት እሱ ነው። በዛ ጦርነትና ጭንቅ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እያሰቡ ነበር፡፡
ሽሬ ስንገባ እንኳ የከተማው ነዋሪ የሚበላ ይዞልን ነው የመጣው። ወታደሩ ግን አልራበንም፤ አያፈልገንም አለ፤ በእርግጥ ደህና እንዳልሆነና እንደተራበም ህዝቡ ያውቅ ነበርና ‹‹አይ ምን እንደፈራችሁ ገብቶናል፤ የበሰለውን እንተው አሉና ያልበሰለውን እንቁላል ይዘው መጡ። በመቶዎች የሚቆጠር እንቁላል ይዘው መጥተው ‹‹በሉ ይህን ሠርታችሁ ብሉ፤ እንቁላል መቼም ምንም ልናደርገው አንችልም›› ሲል ገበሬው ተናገረ። ይህ የሆነው ታድያ ገና ሽሬ እያለን ነው፤ ህወሓት ይቀጥል፤ ይሸነፍ ወይም ይደምሰስ በማያውቁበት ሁኔታ ነው እንዲህ መልካምነትን ሲያሳዩ የነበረው። በያለፍንባቸው ከተማዎች ገበሬው ሲያድርግ የነበረው ይህንኑ ነው። ተዋርደናል የሚል ነገር ነው ከነዋሪው ስናደምጥ የነበረው።
‹‹እግዚአብሔር ይርዳችሁ፤ እኛንም ገላግሉን›› ሲል ነበር። ስለዚህ ለጦርነቱ መፋጠንና ቶሎ ለድል ለመብቃታችን የሠራዊታችን ጥንካሬ፣ ብርታትና ጀግንነት፣ የሕዝባችን የማያቋርጥ ድጋፍ የሞራል ስንቅ ሆኖን ብቻ ሳይሆን ልክ በማይሆን ሁኔታ ውስጥ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ የነበረው የትግራይ ህዝብም በማብላትና በማጠጣት እንዲሁም የሞራል ስንቅ በመሆን ጭምር አግዞን ስለነበር ነው።
ስለዚህም በትግራይ ሕዝብና በህወሓት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ያስፈልጋል፤ ህወሓት መሸሸጊያ ላደረገው የትግራይ ሕዝብ አንድ እና ያው ናቸው የሚለው ትርክት ሕዝብን በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ እድሜ፣ ወርድና ቁመት የሚለካ ፀረ ሕዝብ እሳቤ መሆኑ በተግባር ታይቷል፤ ህወሓት ሲጠፋ የትግራይ ሕዝብ አለ፡፡
የኢትየጵያ ፕሬስ ድርጅት ጥሩውንም መጥፎውንም የማንተወው የታሪካችን አካል እስከሆነ ድረስ ትውልድ እንዲማርበትና መጥፎው የታሪካችንን ሁነት መደገም የለበትም በማለት ታሪካችንን ሰንዶ በማቆየት የወሰደውን ተነሳሽነትና የሠራዊታችንን ገድሎች ለትውልድ ለማስተላለፍ ያደረገው ጥረት እንዲሁም ይህንን ታሪክ በግንባር ዘምታችሁ ሳይዛባ ሰንዳችሁ ለመጣችሁ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የሚዲያ ባሙያዎች በራሴና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የአገር መከላከያ ሠራዊት ስም ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013