ጽጌረዳ ጫንያለው
ለአገራችን ወቅታዊ ችግሮች መንስኤዎቹ የተሳሳቱ ትርክቶች፣ የታሪክ ንግርታችንና የህግ አፈጻጸም ሁኔታዎች እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። የህገመንግሥት ጉዳይም እንዲሁ ችግር መሆኑ ይጠቀሳል። በእነዚህ ጉዳይ ላይ ለዓመታት ሲሠሩ የቆዩና በሙያው ልምድ ያላቸውን በኮተቤ መልቲፖሊታል ዩኒቨርሲቲ የህግና ታሪክ መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌን ስለጉዳዩና መፍትሔው እንዲያወጉን ጋብዘናቸዋል። ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታም እንደሚከተለው አቅርበነዋልና ተከታተሉን።
አዲስ ዘመን፡– ህግና ታሪክ እንዴት ይሰናሰላሉ?
ዶክተር አልማው፡– ታሪክ ማለት ሰው ባለፉት ዓመታት ከነበረው አካባቢ ማለትም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ የህግ መስተጋብሩ እንዴት ተከወነ የሚለውን የምናይበት ነው። ነገር ግን ሁሉንም መጻፍ አይቻልምና በተጻፈ መልኩ ለማስቀመጥ የተቻለው እንደህግና ፖለቲካ ዓይነቶቹን በመሆኑ በየፈርጃቸው ጽፈንና አስቀምጠን ተተኪው እንዲረዳው ተደርጓል። ስለሆነም ህግም እንዲሁ አንዱ የታሪክ አካል ሆኖ በመቀመጡና ለትውልድ በመተላለፉ ከታሪክ ጋር ይሰናሰላል ማለት እንችላለን።
ታሪክ ትናንት ነው። ትናንት ምን አለ፣ ምን ጉዳት ነበር፣ ለዛሬ ቢመጣ ምን ይጠቅማል የሚለውን ማያም ነው። ታሪክ የትናንቱን ማወቂያ፣ የነገ ማቀጃና የዛሬ መኖሪያም ነው። ምክንያቱም ትናንትን ያላወቀ ዛሬ ሊኖር አይችልም። ትናንት እውቀት ነው፣ ትናንት ማንነት ነው፣ ትናንት መረጃ ነው፤ ትናንት ትምህርት ቤት ነው። በመሆኑም ትናንትን በሚይዘው ታሪክ ውስጥ ህግ ይታያል፤ ይተገበራል፤ ለትውልድም ይሻገራል።
በዚህም ነው ህግና ታሪክ የተቆራኙ ናቸው የሚባለው። ነገር ግን አሁን ነገሮች ተቀይረው ኢኮኖሚውን፣ ማህበራዊውን፣ ህጉን ትቶ ፖለቲካ ብቻ ሆነና ብዙ ነገሮች ተረሱ። ታሪክ ለብቻው ህግም ለብቻው መጓዝ ጀመሩና ምንነታቸውን ረሱ። በዚህም በፖለቲካው ብቻ መመራት ተጀመረ። እንደ አገር በስርዓትና በምርምር እንዲሁም በእውቀት የተጻፈ ታሪክን ይዞ መቀጠል ቀረ። ከ1960ዎቹ ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ምርምር ጥናት የተጻፉ ታሪኮች አይደለም ኢትዮጵያን ሌሎችን ከፍ የሚያደርጉ ነበሩ። ሆኖም ቦታውን ፖለቲካ ስለያዘው አልተቻለም። እንደውም የመባያ መንስኤ አደረጓቸው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታሪኮችን በሦስት መልኩ ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን፤ የመጀመሪያው ተጓዦቹ ሚሲዮኖች የጻፉት ነው። ባህሉን፣ ቋንቋውን እንዲሁም ህዝቡን ሳያውቁ ያዩትንና የፈለጉትን ይጽፉ ነበር። ሁለተኛው ገድል ጸሐፊዎች ሲሆኑ፤ የነገስታትን ጨምሮ ሌሎች በቅርብ የሚያውቋቸውን ሰዎች የሚጽፉት ናቸው።
ዋና ግባቸውም ስልጣንን ማረጋገጥ እንጂ ህዝቡና መንግሥት በመረዳት ሳይንስ ማቀራረብ አይደለም። ለዚህ ማሳያው በማይረዱት መንገድ ታሪክን መጻፋቸው ነው። ለምሳሌ ህዝብ ለታላላቅ ሰዎችና ለሚፈሯቸው ሰዎች ‹‹አባ›› የሚለው ስያሜ ይሰጣሉ ብለው የመነኩሴውን አባ ፣ አባገዳን ጠቅሰው አባ ጨንገሬን ይጨምራሉ። ይህ ደግሞ ካለማወቅ የመጣ እንደሆነ እንረዳለን። ነገርግን በዚህ ሥራቸው ህብረተሰቡን አደናብረውታል።
ሦስተኛው የአጻጻፍ ዓይነት የልምድ ጸሐፍት የጻፉት ሲሆን፤ በታሪክ አጻጻፍ እውቀት ያተቃኙ፣ የሚያመጣውን ችግር የማያውቁ፣ ለህዝቡ ምን ይጠቅመዋልና ምን ያስተምረዋልን በአግባቡ የማይረዱት ናቸው። በዚህም የታሪኩ መረጃ በሚፈለገው መልኩ እንዳይደርስ ሆኗል። የተበላሹ ትርክቶችም የተቀመጡት በዚህ የተነሳ ነው። ያልገባውን ህዝብ ለማተራመስ መሰረት የሆኑትም ለዚህ ነው። ጽሑፎቻቸው ፖለቲካ አዘል ሲሆን፤ መሰረት የሌለው ትውልድን ለመፍጠር አስችሏል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ ከፖለቲካው ውጪ ያላየ፣ ሰሜን ተኮር የሆነና ሌሎችን ያልዳሰሰ በመሆኑ ዛሬ ድረስ የሁሉ ነገር መሰረት ቢሆንም እንዳንታይ አድርጎናል። ሞልቶ የፈሰሰው ስለ ገዢዎችና አገዛዛቸው ብቻ መሆኑም ሌላ ተወቃሽነቱን ያመጣ ነው። መንግሥት ሲያጽፈው ክፍያና ስልጣን የሚፈልጉ ጸሐፍት ደግሞ የመንግሥት አቀንቃኝ እንጂ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም። በዚህም ፖለቲካው ከሚገባው በላይ ፈርጥሞ ምህዳሩን ሞልቶት ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በታሪካቸው እንዳይታወቁ አድርጓቸዋል።
ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ህግን ጨምሮ ሌሎችን አንኳር አገር የሚገነቡ የታሪክ አካላት እንዳይታዩና እንዳይፈጸሙ ሆነዋል። በዚህም እኔ አልተጻፍኩም የሚለው አካል ብቅ ብሎ ዱላ እንዲያነሳና ለዚያ መክፈል ያለበት ብሔር አለ ብሎ እንዲያስብም ሆኗል።
አለ የሚባለው ከ1960 ጀምሮ የነበረውም ታሪክ በእንግሊዝኛ የተጻፈ፣ ለህዝቡ ተደራሽ ያልሆነ በመሆኑ ህዝቡ የሚያውቀውና እየኖረበት ያለው ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች የጻፉትን እንዲሆንም መሰረት ጥሏል። ይህ ደግሞ ታሪክን በአግባቡ የሚረዳ አካል እንዳይኖር አድርጎታል። በኃይለሥላሴ ታሪኩ ሞአ አንበሳ እምዘነገደ ይሁዳ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የሚል መልክ እንዲይዝ ተደርጎ የተጻፈ ነው፣ በደርግ ደግሞ የሶሻሊዝም ከየት ወዴትን የሚያቀነቅን መልዕክት የያዘ ነበር። በኢህአዴግ ደግሞ ታሪክ ሙሉ ደብዛው ጠፋና ብሔር ብሔረሰቦች ከየት ወዴት የሚል ፖለቲካ አዘል መልዕክትን የሚያ ስተላልፍ ነው። በዚህም ታሪክ ሥራውን ሳይሠራ እስከዛሬ እንዲዘልቅ ሆኗል።
በተለይ በ27 ዓመታት ውስጥ የታሪክ ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ ደብዛቸው ጠፍቷል። መምህራንም ከሥራቸው ተፈናቅለዋል። የታሪክ መጸሐፍትም ሆኑ ጽሑፎች ከገበያ እንዲወጡ፣ በትምህርት መልክ እንዳይሰጡና ማጣቀሻ ጭምር እንዳይሆኑም ታግደዋል።
ስለሆነም ትውልድ ትናንቱን በሚገባ እንዳይረዳና ነገን አቅዶ እንዳይንቀሳቀስ ተፈርዶበታል። ስለ አገሩም ማሰብ እንዳይችል በሩ ተዘግቷል። ስለዚህ የጋራ ምንም የሌለው ዜጋ ሆኖ ህግ የማያከብር ፣ ታሪክ የማያውቅና ጥላቻና መበጣበጥ ምግባሩ ተደርጎ ለብሶታል።
አዲስ ዘመን፡– የታሪክ ምሁራን እርስ በእርሳቸው ባለመስማማታቸው ትውልዱ ታሪኩን እንዳያውቅና ለተተኪ እንዳያስተላልፍ ሆኗል ይባላል። ምክንያቱ ምን ይሆን?
ዶክተር አልማው፡- አንድን ነገር ለመረዳት ያደግ ንበት ማህበረሰብ፣ ቤተሰብ፣ አኗኗራችን፣ ኢኮኖሚው፣ ሃይማኖቱ፣ የትምህርት ደረጃችን፣ የምንከተለው ፖለቲካ እንዲሁም የተማርነው ትምህርት ወሳኝነት አለው። በዚህም የታሪክ ምሁሩም ስምምነቱ በዚህ ሁኔታ ላይ ይመሰረታል። በእርግጥ በቋሚው ነገር መስማማት አለ። ልዩነቱ ማብራሪያ አሰጣጡ ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ መሰረታዊ ነገር ጣልቃ ገብነቶች ናቸው።
ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናው፣ ልዩ ፍላጎቱ ፣ የውጭ ስፖንሰሩ ወዘተ ታሪክ በስምምነት እንዳይነገር ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ከውጭ አገራት የሚደረጉ ታሪክ የማጥፋት ዘመቻዎች ትልቅ ችግር ፈጣሪ ናቸው። መጥፎ ታሪክ የሚጽፉ አካላትን ስፖንሰር እስከማድረግ ይደርሳል።
እንደ አገር የፈረንጅ ወዳጅ የለንም። ምክንያቱም የሴራ ፖለቲካ አለበት። ከአደዋ በኋላ ኢትዮጵያ የሠራችው ገድል ዘመን ተሻጋሪ ከመሆኑም በላይ ፈረንጆችን ያሸማቀቀ ነው። አይሸነፉምንም ቢሆን አጥፍቷል። ይህ ደግሞ ለፈረንጆቹ ከባድ ሽንፈትና የፈለጉትን እንዳያገኙ ያደረገ ነው። እንደፈሯትም እንዲኖሩ ያስቻለ ነው። በመሆኑም አሁንም ድረስ የእርሷን ማደግና መበልጸግ ስለማይፈልጉ ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ አካላትን ሁሉ ይደግፋሉ።
በቋሚነት እንዳትረጋጋም ይጥራሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የታሪክ ምሁራን የተጣመመ አስተሳሰብ ትልቁ የፍላጎታቸው ማሳኪያ ሲሆን፤ ጽሑፎቻቸውን ኢትዮጵያን በሚያባላ መልኩ እንዲያደርጉ ይከፍሏቸዋል። የትምህርት እድልም እየሰጡ በሚፈልጉት መልኩ ያሰለጥኑና የፈለጉትን መልዕክት እንዲያስተላልፉ ያደርጓቸዋል። ይህ ደግሞ አለመስማማትን በሚገባ ያመጣል።
ትውልዱም የአገሩን ሳይሆን የውጪውን የሚናፍቀ ውና የሚመርጠውም በተማረው ታሪክ የእውቀት ሚዛን የውጪዎችን አድርጎ ስለሚወስድ ነው። ስለዚህ ምንም ትክክል ነገር ቢነገረው የማያምነው ለዚህ ነው። በተለይ በታሪክ እነ ኦነግና ህውሓት ብዙ ፖለቲካዊ ጨዋታ ስለተጫወቱ ብሔራዊ ጀግኖችን ይዞ የሚጀግን ዜጋ እንዲጠፋ ሆኗል።
ብሔራዊ ጀግና ጠለሸና የለም ማለት አገር ወደቀ፣ ማንነት ተጥላላ፣ አገር የሠራችው ድልና ገድል ጠፋ ማለት ነው። ስለዚህም ይህ እየሆነ ይገኛልም። ለዚህ ነው ዛሬ የጋራ ራዕይ ይዞ በመስማማት አገርን ለማሳደግ የሚጥር የጠፋውም።
ታሪክ ሲበላሽ ብሔራዊ እሴቶችም አብረው ይበላሻሉ። ለምሳሌ ባንዲራ፣ ገንዘብና በዓላት የተለየ መልክ የኖራቸውም ከዚህ አኳያ መሆኑ ግልጽ ነው። ሁሉም በየሰፈሩ ባንዲራን ፈጥሯል፤ የሚሟገተውም ለብሔሩና ለሰፈሩ ልጅ ነው። ከዚያ ውጪ አይወክለኝም፣ አይመለከተኝም ባይነት ሰፍኗል። ስለዚህም እንደተባለው በታሪኩ ማብራሪያ የታሪኩ ምሁር መለያየትና አገርን ለማውደም የተሠሩ ሥራዎች ይህንን ሁሉ አስከትለዋል። አሁንም ቢሆን መሰረታቸው ከእንደገና እንዲመለስ ካልተሠራ በቀላሉ አይፈታም።
ምክንያቱም የጋራ በዓላት በትውልዱ ዘንድ የጭቆና እንደሆኑ ይታሰባሉ። ለአብነት ዓደዋ የዓለም መሆኑ ቀርቶ የአማራ ተደርጎ ተወስዷል። እናም አሁን ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚያጠለሽ ምሁር እየወሰዱ ሁለተኛና ሦስተኛ ድግሪ እየሰጡ የማስተማራቸው ምስጢር ማክሰም ይገባል። የተሳሳቱ ትርክቶችን የሚዘሩ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ መጀመር ያስፈልጋል። ታሪክ አገርን እንደሀገር የሚያስቀጥል ሳይሆን የግለሰብን ጥቅም የሚያስከብሩ ሆኗልና ይህንን ከመሰረቱ ማድረቅ ላይ ሁሉም መረባረብ አለበት። ብሔር ያለአገር ይጓዝ ይመስል የብሔር ልዕልናን እያስከበሩ ብሄር ተኮር አገርንም የሚፈጥሩ አካላትን ሀይ ማለት ቅድሚያ መሰጠት ይገባል።
የእስከዛሬዋ አገር በመላዕክት የተገዛች አልነበረችም። ገዢዎች በጠመንጃ ገዝተዋት ያውቃሉ። ስለ ፍትህ ፣ ስለ ዴሞክራሲ የማያውቁ ገዢዎችም ሲገዟት ኖረዋል። ስለዚህም ህዝብ ተጨቁኖ ፈተናን አሳልፏል። ነገር ግን የተግባሩ ባለቤት ገዢዎች እንጂ ህዝቦች አልነበሩም። ዛሬ እንደሚባለው አማራው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞውና ሌላው ህዝብ አንዱ አንዱን አልጨቆነም። በባለስልጣናቶቹ የስልጣን ጥም የሆነ ነው እንጂ። ገዢው መደብ ግዛቱን ለማስፋፋትና አልገዛም ያሉትን ለማስገዛት የተሳሳቱ ትርክቶችን ትተን ተግባሩን ፈጽሞታል። በግለሰቦቹ ጥፋት አንድ ብሔር ላይ ይህንን በደል ያለ አግባብ መጫን ተገቢነት የለውም። አንድን ብሔር ለብቻው የተሰበረ አድርጎ መውሰድም አይገባም።
ሁሉም ህዝብ የጉዳት ሰለባ የሆነበት ጊዜ ነበረው። እናም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ይህንን ማየት ይገባናል።
አገሪቱ ውስጥ ጥግ የያዘ ድህነት አለ። ፍትሐዊነት የለም። ብልሹ አስተዳደሮች በሰፊው ይታያሉ። የፖለቲካ ባህላችን የሰለጠነ አይደለም። ልዩነትን በቀናነት ማስተናገድ ያመናል። በዚያ ላይ ሥራ አጡ ብዙ ነው። ተደራሽ የሆነ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ፖለቲካ፣ የሃሳብ የበላይነትም የለም። በተለይም በብሔር ላይ ተመርኩዞ የሚመሰረት የፖለቲካ ፓርቲ አግላይና አንገዋላይ ነው።
እናም እንደ ህዝብ ተመርጦ መፈናቀል፣ ተመርጦ መግደል፣ ተመርጦ መቀማት አለ። እናም ይህንን ለማስወገድ አንድነት ብቻ ነው መፍትሔው። የቀደመና መልካሙ ታሪካችን ብቻም ነው የሚያሻግረው። ስለሆነም ትውልዱ ታሪኩን በሚገባ እንዲረዳ ከተፈለገ ይህንን ማድረግ ግድ ይላል።
ፍራቻው ፣ ገበያው ላይ ያለው ፖለቲካ፣ የፖለቲካው አደረጃጀት፣ የህጉ አደረጃጀት፣ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ የታሪክ ምሁራን ማህበር እንዳይቋቋም መታገዱ፣ ነፃ ተቋም ያለመኖሩና መሰል ችግሮች በታሪክ ምሁራን መካከል መቀራረብ እንዳይኖርና አገር በታሪክ እንዳትሠራ ያደረገ ሌላው ምክንያት ነው። ሆኖም አሁን በመጣው መንግሥት መነጋገር ተጀምሯል። ማህበሩ ከተፈቀደ ደግሞ ይበልጥ የምርምር፣ የስርጸትና መሰል ክፍሎች ስለሚኖሩት ገበያ ላይ ከሚወጡትና ለህትመት ከሚቀርቡት መጽሐፍት ጀምሮ ተገምግመው ለህዝብ እንዲደርሱ ይደረጋል። ህዝብም መርጦ አንባቢና ታሪኩን አዋቂ ይሆናል።
የሚነበቡ ታሪካዊ መጽሐፍትን የሚፈልጉ በርካታ በመሆናቸው ግራ መጋባትን ያስቀርላቸዋል። የተሳሳቱ ትርክቶችም ቦታ አይኖራቸውም። በተለይም ለሁሉ ነገር መነሻው ትምህርት በመሆኑ የታሪክ ትምህርቶች በአግባቡ የሚሰጡበትን ሁኔታ ያመቻቻል። አገራዊ ራዕይ፣ አገራዊ አጀንዳና ህዝባዊ ብልጽግናን የማይፈልጉ ወረበሎች ተሰብስበው የመሰረቱትን ታሪክም ከምድረገጽ ማጥፋት ያስችላል።
አንደኛ ደረጃ ብሔር ነን በአገር ደረጃ በፍጹም መታሰብ እንዳይኖርም ዕድል ይሰጣል። ምክንያቱም ያልተጋባና ያልተዋለደ የለምና ሁሉም ታሪኩን መርምሮ እንዲረዳ ይሆናልና።
አዲስ ዘመን፡– ታሪክ ለአገር ግንባታ ምን አስተዋፅኦ አለው፤ ከህግ አንጻር የሚታይበት ሁኔታ አለ? በተለይ በፌዴራልና በክልል ህገመንግሥት?
ዶክተር አልማው፡- የኢትዮጵያ ታሪክ በፖለቲካው የተበላ ነው። ምክንያቱም ከፖለቲካ ውጪ 100 በመቶ የሚታይ አንድም ነገር የለም። ኢኮኖሚው እንኳን በሁለተኛ ደረጃ ነው የሚታየው። እንደ ታሪክ ዓይነቶቹ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ጠፍተዋል። ነገር ግን ታሪክ አገር ሲገነባ ሥራውን ሠርቶ እውነቱን ለህዝብ በማሳየት ነው። ማን መጥፎ ማን ጥሩ ሠራ በሚገባ ያሳያል። እያስተማረ ከችግሮች ትምህርትን ሰጥቶ ነገን የተሻለ እንዲያደርጉ የሚጠቁምም ነው። ታሪክ ዛሬ መኖሪያ አይደለም። ትናንት ምን ነበር ያለው የሚለውን ያሳያል እንጂ። እናም ሰው በፖለቲካ፣ በህግ፣ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ ወዘተ እንዴት ኖረ የሚለውን በእውቀት ያስጨብጣል። ለቀጣይ ህይወቱም የተሻለውን ያመቻቻል።
ነገር ግን የታሪክ ምሁሩና ፖለቲከኛው ቦታ ተቀያይሮ ትክክለኛው ታሪክ እንዳይደርስ ሆኗል። በዚህም ዳቦ ሳይሰጡት ነገ እንሰጥሀለን እያሉ በማስጎምዡት አብሮነቱን ቀምተው ታሪኩን ከህጉ ነጥለው አሳዩትና ህግ አክባሪ፣ ታሪክ ሠሪ ትውልድ እንዳይፈጠር ሆነ። ትናንቱን ያላወቀ ዛሬን አይጠይቅም። ዛሬን ያልኖረም ነገን አያውቅም። በዚህም ህግ ያለማክበር መብትና ልምድ ተደረገ። የሚረቀቁ ህጎችም ቢሆኑ መሰረታዊ መብቶችን የሚያስከብሩ እንዳይሆኑ ሆኑ። በዚህም ታሪክ ከህግ አንጻር ገደብ የለሽ ነበር ብሎ ማንሳት ይቻላል። አገር ላይ በነፃነት መኖር ታሪክ ተቆርጦ በመጣሉ ነው።
በታሪክ ሁሉም ብሔር በአብሮነት ይኖር ነበር። አሁን በተፈጠረ ህግ ግን በአንድ ክልል ውስጥ ከብሔሩ ውጪ ተጠቃሚ፣ ባለሀብት፣ የመኖር መብት ያለው አካል የለም። ፈላጭ ቆራጩ የክልሉ ተዋላጅ ብቻ ነው። በዚህም በታሪክ የነበረው በአብሮ መሥራት፣ በአብሮ ማደግና አገርን ማስቀጠል ቦታቸውን ለቀቁ። በተለይ አመራሩ የአገር ቢሆንም ከሰፈር እንዳይዘል ተደረገ። በመሆኑም ከፌዴራል እስከ ክልል ያለው ህገመንግሥት አግላይ አንገዋላይና ሰፈርን የማስከበር ሥራ የሚሠራም ሆነ። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ህውሓት ሲሆን፤ 27 ዓመት ሙሉ ሠርቶበት አንድ ትውልድ ስላፈራበት ነው።
አዲስ ዘመን፡– 27 ዓመታትን ስልጣን ላይ የቆየው ህወሓት በፖለቲካው ላይ የፈጠረው መዘበራረቅ አሁን ላለንበት ቀውስ አድርሶናል። ከዚህ አኳያ ያለውን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አልማው፡– ህወሓት መራሹ መንግሥት ከጫካ ጀምሮ ሁለት የተጻረረ ሃሳብ ይዞ የመጣ ነው። አብዮታዊ ዴሞክራሲን ያቀነቅናል። ነገር ግን የራሱን ጥቅም ያስከብራል። በተለይ ኢትዮጵያን ማፍረስ ዋነኛ ግቡ ነበር። አዲስ ፖለቲካና አዲስ አገር መመስረት መሰረታዊ ጉዳዩ ነው። አገራዊ እሴት፣ አገራዊ ጀግና እና አገራዊ ታሪክ ሳይኖር አገር ወዳድ ትውልድ ሊኖር አይችልም። ስለዚህም ከ27 ዓመት በላይ በተሠራው ሥራ ብሔር እንጂ አገር የሚለው እንዳይታሰብ ሆኗል። ብጥብጥና ጥላቻም የዚሁ ውላጅ ናቸው።
በፊት ላይ ዴሞክሪያሲያዊና ህዝብን የሚጠቅም ባይሆንም አገር የሚለው ስብዕና ግን አልጠፋም። ለዚህም ማሳያው ጠላት ሲመጣ ልዩነታቸውን ለነገ ትተው አገርን አሻግረዋል። ህወሓት መራሹ መንግሥት ሲመጣ ግን አንዱ ብሔር ከሌላው ብሔር ጋር የት ቦታና እንዴት ሊጣላ ይችላል የሚለውን እያቀደና በተግባር እየተረጎመ 27 ዓመት ሙሉ የሠራ በመሆኑ አገር መውደድ ብቻ ሳይሆን አገርን መጥራት እንዳይቻልም ነው የሆነው። አገሬ የሚል አካል ከተገኘ ሁሉ ነገር ያከትምለታል።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የተሻሉ ነገሮች ቢመጡም አሁንም የተተከለው ተክል በብዙ መንገድ እየሠራ አይደለም። ለአብነት የክልሎች፣ የዞኖችና የወረዳዎች አወቃቀር የህውሓትን ሥራ በተወ መልኩ አይደለም። በዚህም ማዕከላዊ መንግሥቱ ያልተጠናከረና ክልሎች የፈረጠሙ እንዲሆኑ አድርጓል። ስለዚህም ምርጫ ማካሄድን፣ የፈለጋቸውን መግደልን እንድናይ ሆነናል። ህወሓት ባለስልጣኑን ሳይቀር በምርጫ የተቀመጠ መንግሥት ስለሌለ ነገ ይህ ቢወድቅ በሚል መንፈስ ሁለት አምላኪ አድርጎታል።
በዚህም የክልልና የፌዴራል አሠራሮች ተለያይተው ህዝቡ እንዳይረጋጋ መንገድ ጠርጓል። ከዚያ ውጪ አዲሱ መንግሥት ከህወሓት የተረከባቸው ባለስልጣናት ስላሉም ጥቅማቸውን ከህዝብ ስለሚያስበልጡ ሸምጋይና ሲያደርጉት የቖዩትን መተው ስለማይፈልጉ አለመረጋጋቱ እንዲቀጥል ሆኗል።
በሌላም በኩል መንግሥት በህወሓት ጥፋት ብዙ ችግሮች ተጋርጠውበታል። ከእነዚህ መካከል ግንኙነቱ አሁንም ድረስ ከጽንፈኛው ጋር የሆነ ብዙ አመራር መኖሩ፤ አገር በብዙ እዳ ውስጥ መሆኗ፤ ታችኛው ክፍል ላይ ያለው አመራር በአብዛኛው የተጨመላለቀና በአሠራር እንኳን በብዙ መልኩ ያልጸዳ መሆኑ፤ በገንዘብ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደሚቻል የሚያምን መሆኑ፣ የህዝብ ጠባቂ ተብሎ የተሰየመውም አካል ለመኖር ሲል ያለ አግባብ ሰውን እየገደለ መቀጠሉ፤ ነፃ ተቋማት አለመፈጠራቸው በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎችም ቢሆኑ የጁንታው ምልምሎችን ያካተተ መሆኑ መረጋጋት እንዳይመጣ አድርጓል። ስለዚህም ይህንን እስኪያጸዳ ድረስ በአመራር ዘንድም ሆነ በዜጋው ላይ ትልቅ ፈተና ጥሏል ማለት ይቻላል።
የህወሓት ጁንታ ህግን ሳይቀር የዘወረ ነው። እንዴት ከተባለ በዋናነት በአምስት መንገድ አበላሽቶታል። አንደኛው ሰዎች ሙስና ውስጥ እንዲዘፈቁ በማድረግ ሲሆን፤ ነፍስህ በእጃችን ነች በማለት የፈለጉትን ማስደረጋቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመጠቀም በብሔር መለያያና ችግር መፍጠሪያ ማዕከል አድርጎ መሥራቱ ነው። ለዚህ ደግሞ የማይመረቁ የደህንነት ሰዎችን ሳይቀር ይጠቀም ነበር። ሦስተኛው ስፖርትን ከፖለቲካ ጋር ማስተሳሰሩ ሲሆን፤ አጀንዳ ተሰጥቷቸው ህዝብን እንዲበርዙና ከህግ ውጪ እንዲሆኑ ያደረገበት ነው።
አራተኛው ኢኮኖሚውን ማናወጥ ሲሆን፤ ህዝብ የሚፈልገውን ከገበያ በማጥፋት ሲንጫጫ ይቆይና እኔ እያለሁ በማለት ከመጋዘን አውጥቶ ያቀርብና እርሱን ብቻ እያመኑ እንዲቀጥሉ ያደረገበት ነው። የብሔር ተኮር ግጭቶችን በተለያየ መንገድ በመፍጠር መሥራቱ ሌላው ህግ ማስጣሻ ነበር። በግጦሽና በውሃ ምክንያት ውጊያ እንዲያደርጉ አንዱን ወገን በመደገፍ አስጨርሶ የእንትና ብሔር በእንትና ተጠቃ እያለ ሽማግሌ እየሆነ ስልጣኑን ከህግ ውጪ ማራዘሙ ነው። ሚዲያውን ወጥሮ በመያዝ እነርሱ ከሚፈልጉት ውጪ እንዳይዘገብ ማድረጉ፤ የክልል ህገመንግሥት እንዲኖር መፈቀዱና ዜጎች በፈለጉበት ቦታ እንዳይኖሩ መገደቡም ህጉን ሳይቀር እንደዘወረው የሚያሳይ ነው።
ብሔርና ሃይማኖት እንደ ኢትዮጵያ ደምና አጥንት መሆኑን ስለሚያውቅ ሥራውን ከህግ ጋር አያይዞ ሴራውን ደግሞ ከህግ ውጪ እየፈጸመ መቆየቱ ችግሮች በቀላሉ መፍትሔ እንዳያገኙ ያደረገበት ነው።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ህግ እንዴት ይታያል፤ በህግ የመመራቱ ሁኔታስ እንዴት ይገመገማል ?
ዶክተር አልማው፡– መጀመሪያ መስማማት የሚያስፈልገው በምድር ላይ ሙሉ ፍትህ እንደሌለ ነው። ምክንያቱም ህግ ለጉልበተኛ፣ ለገንዘበኛ፣ ለሹመኛ፣ ለመልከኛ ያደላል። እነዚህ አካላት ፍርድቤት ሳይሄዱ ፍርዳቸውን ያስጨርሳሉ። ክፍተት ተጠቅመውም ልክ እንዳልሆነ ያሳምናሉ። ስለዚህም ፍትህ በኢትዮጵያ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለምም ክርክርን ማሸነፍ ነውና ከባድ ነው። ስለ እውነት ሳይሆን ስለክርክር ማሸነፍ ብቻ የሚያቀነቅን ነው። ከዚያ ውጪ ሲታይ ግን በአገር ደረጃ ምን ዓይነት ህግ የማስከበር ሥራ አለ የሚለውን መመልከት ይቻላል።
እንደ ኢትዮጵያ ህግ ከፍትህ ተቋሙ ጀምሮ ችግር ያለበት ነው። ምክንያቱም ገለልተኛነት ይጎለዋል። ህጉ በሹመኞች የሚመራ ነው። ዳኛው ፍርዱን ሲሰጥ ሁለት ዓይነት አቅጣጫን ተከትሎ ነው። የመጀመሪያው በማስታወሻ የሚሠራው ሲሆን፤ የፖለቲካ ውሳኔ በሚል የሚከናወነው ነው። የእንትና ሚኒስቴርና ክፍለከተማ ይጽፍና ሞት የተፈረደበትን ሰው ልቀቁ ይባልበታል። ነፃ የሆነው ደግሞ ይታሰር ይባላል።
ስለዚህም የማስታወሻ ማስፈጸሚያ ህግ የሚከወንበት ነው። ሌላውና ሁለተኛው ጥቂት ሀቀኞችን ትተን ስንት ትከፍላለህ ተብሎ የሚፈረድ ፍርድም ያለበት ነው። ስለዚህም እንደ አገር ያለው የህግና ህግ መከበር በተለይ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሹመኛና በጥቅመኛ የሚሠራው አካል ውሳኔ ፍርድ ነው። በዳኝነት ሥራ ላይ በተሳተፍኩባቸው ጊዜያት ደግሞ ይህንን አረጋግጫለሁ።
በአገር ውስጥ በህግ የመመራቱ ጉዳይ አገራዊ ራዕይና ህዝባዊ አገልግሎትን ያነገበ አይደለም። ገና ብዙ የሚጠራ ነገርን ይፈልጋል። ገለልተኛ የፖለቲካ ድርጅት፣ ገለልተኛ ተቋምም እስካልተመሰረተለት የባለስልጣናት አገልጋይ መሆኑ አይቀርም። እስከ አሁን ድረስም ህዝብንና እውነትን የሚያገለግል ተቋም አልተመሰረተም። አሁን ያሉት ጅማሮዎች እንዳሉ ሆነው።
በህግ መመራትን ለማምጣት አገር የሚያሻግር ህገመንግሥት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ያለአግባብ የገቡ ህጎች አሁን በተጀመረበት ሁኔታ እየተስተካከሉ መሄድ ይገባቸዋል። ከግለሰብ የጀመረ ሥራንም ይጠይቃል። መብቱ የተነካ ሰው ሁሉ መጮህ አለበት። በጋራ ጉዳይ ላይ መደራደርም አይገባም። አድርባይነትን ማስወገድ፣ ሌሎች ክልሎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች ሲመጡ እንደ ወራሪ አድርጎ የሚያየው የክልሎች አግላይ የሆነ ህገመንግሥትና የአወቃቀር ስርዓት በህግ መስተካከል ይኖርበታል። ህብረ ብሔራዊነትን በህገመንግሥቱ ማሳየት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚፈጸሙ የህግ ጥሰቶች ንጹሐንን እየማገዱ ይገኛሉ። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ፈር ለማስያዝ ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር አልማው፡– አሁን ያለው ችግር ለዘመናት የተሠሩ ሥራዎች ውጤት ነው። ዘመናችን ያለፈው በቂም፣ በበቀል፣ በጥላቻና በቁርሾ ነው። አንድም አገርን ሊያሻግር የሚችል ፣ አብሮነትን ሊያጠናክር የሚችል ነገር አልተሠራም። ስለዚህም ያበበውና የጎለመሰው ዘር እንጂ አገር አይደለም። ይህ ደግሞ በቀላሉ የሚጠፋ አይሆንም። አሁንም ብዙዎችን በግፍ ያጣነው ለዚህ ነው። ነገር ግን በተወሰደው የህግ ማስከበር ሥራ ጁንታው ተይዞ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ድል ተገኝቷል። ሁሌ ነዳጅ የሚያርከፈክፍና ክብሪት የሚጭር እጅን ማሰር ተችሏል። በዚህም ማሰቢያ ጊዜ ተገኝቷል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም እሳቱ ይለኮሳል ሳይሆን የተለኮሰው እንዴት ይጠፋል ላይ ለመሥራት ያግዛል።
አሁን ያለው አመራር ብዙ ድክመቶች ቢኖሩትም አገር ወደማለት የመጣ ስለሆነም መፍትሔዎች መምጣታቸው አይቀርም ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ይህንን ይዞ የተሻለውን ለማምጣት የእያንዳንዱ ዜጋ ጉዳይ መሆን አለበት። እሳት ለኳሹ ህወሓት ብቻ ስላልሆነም እየለዩ ወደ ህግ ማቅረብ ላይም የህዝቡ ተሳትፎ መላቅ ይኖርበታል። በተለይ ከህወሓት ጋር ክርስትና የተነሳሱ፣ ጡት የተጠባቡ እንዲሁም ፍቅር እስከመቃብርን የተፈራረሙ አሉና እነርሱን አሳልፎ ከመስጠት አንጻር ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል።
በህወሓት መመታት ድንኳን ቤታቸው ጥለው ኀዘን ውስጥ የተቀመጡ በርካቶች ናቸው። ስለሆነም ጊዜ ይጠብቃሉና ለአገር ደህንነት ሲባል እነርሱን ማሳፈር ይገባል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት እያደረገ ያለው ነገር የሚያስመሰግነው ነው። መቼም ቢሆን በአገር ተስፋ አይቆረጥምና ማንም ምንም ያድርግ ለአገር ታማኝ መሆን ከሁሉም ይጠበቃል። ስለዚህም ያለችውን ተስፋ አሟጦ መጠቀምና ወደፊት መራመድ ያስፈልጋል። ጉዳዩ አገርን የማዳን እንጂ የፓርቲና የብሔር ጉዳይ እንዳልሆነ ማሰብም ይገባል። ወቅታዊ ሁኔታው ደግሞ ብሔርና ፖለቲካን ብቻ ያነገበ በመሆኑ ከእርሱ መራቅና ስለሰው ልጅ ማሰብ ከምንም በላይ ስንቃችን ይሁን። አሁን ያለው መንግሥት በግብጽ፣ አውሮፓ ህብረትና መሰል አካላት ስለተወጠረ ህዝብ ሊያግዘው ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– የህግ ማስከበሩን ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
ዶክተር አልማው፡- ህወሓት የትግራይን ህዝብ በልቶ የጨረሰ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ የሚልን ህዝብ በብዙ ነገር ገሎታል። ውስጡ እንደ ካንሰር ሆኖ ሲገለው ለትግራይ ህዝብ እስከአሁን አልደረስንለትም የሚል እምነት አለኝ። ስልጣን ከያዙ በኋላ ደግሞ ከቅምጦቻቸው እስከ ቤተሰባቸው የደረሰ ድርጅትና ሀብት ሲያከማቹ ቆዩ እንጂ ድሃዋ የትግራይ እናት እጅ ላይ የገባ ነገር አልነበረም።
ሁሉም ሲረዳ የነበረው መከላከያ ሠራዊቱ ከኮቾሮው ላይ በቀነሳት ገንዘብ ነው። ትምህርትቤት፣ ጤና ጣቢያና ሌሎች የአገልግሎት ተቋማትም ቢሆኑ የተሠሩት በእርሱ ገንዘብና ጉልበት ነው። ግን እኔን አልፎ ለምን በሚል ቅናት ደጉን የአገር መከታ ተኩሶበታል። ስለዚህም የማይወዳጁትን ህወሓትን ልክ ማስገባቱ ትክክል ነው። ወደፊትም ይህ ነገሩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። የትግራይ ህዝብም ቢሆን ትውልዱን፣ ዘመኑን፣ ንብረቱንና ማንነቱን የቀማውን የህወሓት ጁንታ መቼም መታገስ የለበትም። ከህግ ማስከበሩ ጎን መቆም አለበት።
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ የፍትህ መዘግየቶች ይታያሉ። ይህ ደግሞ ለወንጀል መባባስ መሰረት ጥሏል ይባላል። ይህንን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አልማው፡– እውነት ነው። ብዙ ጊዜ የሚተቸውም በዚህ ነው። እንደውም የዘገየ ፍርድ እንዳልተፈረደ ይቆጠራል ይባላል። ቆይቶ የሚወሰድ ዕርምጃ ብዙ ነገር ያሳጣል። ከምንም በላይ ደግሞ ቂም ይፈጥራል። የራስን ፍትህ ወደመውሰድ እንዲያመራም የሚያደርግ ነው። መንግሥት በደህንነቱ አማካኝነት ማን ምን እንዳደረገ ያውቃል። ሆኖም ዕርምጃው ዘግይቶ ይወሰዳል። በእርግጥ ይህ የሆነበት በቂ ምክንያት ይኖር ይሆናል። ባለፈው በፓርላማ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ዓይነት ችግር። ከዚያ በተጨማሪ የጸዳ አመራር አለመኖርም እንዲሁ። ስለሆነም ከበጣም መጥፎ መጥፎ እንዲወሰድ ሆኖ የፍትህ መዘግየቶች ተፈጥረው ችግሮች እየተባባሱ እንዲሄዱ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይ የህግ የበላይነትን ለማስፈንና አገር አሁን ካለችበት ችግር እንድትወጣ ምን ይደረግ?
ዶክተር አልማው፡– ህዝብ እንደ ህዝብ አገሩን ማስቀጠል አለበት። አገር ሲቀጥል ዴሞክራሲ ይኖራል፣ ማደግ ይቻላል። ወንጀለኛ ሁሌም ወንጀለኛ ነውና ሊታገሰው አይገባም። ቤተሰቡም ቢሆን አሳልፎ መስጠትን መለማመድ አለበት። የሞራል ዝቅጠት የሌለበትና በውስጡ ስነምግባሩ ያበበ ትውል.ድ መፍጠር ላይም ሊሠራ ይገባል። ወጣቱ ደግሞ ዘመኑን ማስበላት የለበትም። በፊሽካ የሚሰለፍ ሰው ፈጥሬያለሁ ሊባል አይገባውም። በእውቀትና በማስተዋል መመራት ይጠበቅበታል። አገሩ ከፈረሰ ስደተኛ፣ ዘመንና ራዕይ የሌለው እንደሚሆን ማሰብ ይኖርበታል። ፖለቲከኛው በበኩሉ አገር ስትኖር መምራት እንደሚችል ማመን አለበት። በውድድርና በሃሳብ ልዕልና የሚያምን፤ ለአሸናፊ ሃሳብ የሚገዛና ዴሞክራሲያዊ ውድድር የሚያደርግ እንዲሁም አቃፊ ፖለቲካ የሚያራምድ መሆንን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
በመንግሥት በኩል መሠራት ያለበት ያለ ሥራ የተኮለኮሉ ተቋማትንና አመራሮችን ማስወገድ፤ አገዛዝን የሚያገለግሉ ሠራተኞችን መለየት፤ ዘመን ተሻጋሪና በእውቀት የሚመራ ፖሊሲ፣ ሠራዊት መፍጠር ነው። የፋይናንስ ስርዓቱንም በሚገባ መመርመር ይገባዋል። በሰንሰለት የተያዙ ውሾች መሳይ ተቋማትን ማፍረስና በራሳቸው ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ ማድረግም አለበት። ለአገር፣ ለህዝብና ለትውልድም ባለውለታ የሚሆንበትን አሠራር መዘርጋት ዋነኛ ተግባሩ ሊሆን ያስፈልጋል።
የፖለቲካው አካሂድ፣ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መፍጠርም ይገባል። ይህ ማለት ውሸትን የሚጸየፍና ስለእውነት ራሱን ጭምር አሳልፎ የሚሰጥ ህብረተሰብ መፍጠር ያስፈልጋል። በደልን የማይቋቋም ማለትም በራሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ላይ የሚሆነውን የሚቃወም ዜጋ ማፍራትም ተገቢ ነው። ዴሞክራሲያዊ መሪ መፈጠር፣ በምርጫ መጥቶ ህዝቡ ያስቀመጠውና ህዝቡ የሚፈልገውን መሪ ማስቀመጥም ይገባል።
እንደ ዝንጀሮ አባት ተከታዮችን እያሳደደ የሚያጠፋ ሳይሆን ተተኪ መሪዎችን በዴሞክራሲያዊ ስርዓትና በእውቀት ቃኝቶና አሳድጎ ማፍራትም አለበት። ቋንቋ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት የማይወስነው ፖለቲካ መፍጠር፣ ፖለቲካ ውድድር ሀብት፣ ሃሳብ ፣ ሙግትና በእውቀት ማሸነፍ ያለበት መሆኑን ማሳየትም ይኖርበታል። በተለይም ፖለቲካው እንደ ኳስ ወደ መሀል ገብቶ የሚችል የሚጫወትበት ማድረግ ላይ በስፋት መሥራት አለበት። ይህ ነገር ሲፈጠር ደግሞ መረጋጋት ይመጣል። ሳንጃው ወደ ልማት ይቀየራል። የጦር መሳሪያ ላይ የሚወጣው ገንዘብም አገር ይገነባል። የሚሞተውም ሰው ሀብት ይሆናልና እነዚህን መሥራት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰ ግናለን።
ዶክተር አልማው፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 24/2013