የሪል ስቴቱ ውስጣ ውስጥ ሲፈተሽ!

ክፍል ሁለት

በአማላይ ማስታወቂያዎች የተሸፈኑ የማይፈጸሙ ውሎች እና የዜጎች እንባ

በክፍል አንድ ጽሑፋችን፣ “ የሪል ስቴቱ ውስጣ ውስጥ ሲፈተሸ! “ በሚል ርዕስ፤ የሪል ስቴትን ምንነት፣ የሀገራት ተሞክሮ እና በኢትዮጵያ ያለውን ገጽታ ለማመላከት ተሞክሯል። የሪል ስቴት ዘርፉ በኢትዮጵያ እንዲተገበር ሲደረግ ምንም አይነት የሕግ ማዕቀፍ እንዳልተዘጋጀለት፤ የአሰራር ሥርዓት እንዳልተበጀለት፤ እገሌ የሚባል ተቋም ይምራው ተብሎ እንኳን ባለቤት እንዳልተሰጠው ያመላከተ ዘገባ አቅርበናል።

በዘገባችን ምንም እንኳን የሪል ስቴት ዘርፍ የቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ አስተዋጽኦ እያበረከተ ቢሆንም ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን፤ በተለይም ለዜጎች እንግልትና ብዝበዛ፣ ለጥቂቶች ደግሞ የመክበሪያና በአቋራጭ መበልጸጊያ ሰፊ ሜዳ ሆኖ መከሰቱን ጠቁመናል።

ለመሬት ወረራ፣ ለከተሞች ፕላንና ገጽታ መበላሸት፣ ሰፊ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ከዚህም አለፍ ያሉ ሥነልቡናዊ ችግሮችን እያስከተለ፤ ከፍ ሲልም ለካፒታል ገበያው ትልቅ ፈተና ስለመሆኑ በመጠቆም፤ ችግሮቹን በቀጣይ ክፍሎች በዝርዝር እንደምናስነብብ ቃል ገብተን ነበር። እነሆ ዛሬ በቃላችን መሰረት የችግሩ አንድ ማሳያ የሆነውን፤ ክፍል ሁለትን አሰናድተናል።

“የባንክ ብድር ተመቻችቷል፤…”፣ “…ኑሮ ቀለል ይላል፤”፣… “ምቾት ስጋ ለብሶ ቅንጡ ቤት ውስጥ ነዎት፣…”፣ እና ከመሰል የማስታወቂያ ማስዋቢያ ሀረጎች በስተጀርባ የሚነገሩ የማይጨበጡ ጉም ቃላት፣ ብዙ ቤት ፈላጊዎችን ተስፋ አልባ አድርገዋል። ምክንያቱም፣ በእነዚህ ቃላት ተከሽነው አምረውና ተውበው የቤት ፈላጊዎችን ቀልብ ገዝተው የሚቀርቡ ማስታወቂያዎች፣ የሪል ስቴት ዘርፉ በማይፈጸም እና በሳቢ ማስታወቂያዎች ማኅበረሰቡን በማማለል ልባቸውን የሚያሸንፉበት፤ በደካማ ጎናቸው ገብተውም የቤት ባለቤት እንሆናለን ብለው የቆጠቡትን አንጡራ ሀብት የሚበዘበዙበት፤ ሕይወታቸውንም ለከፋ ችግር የሚዳረጉበት ስልትና መንገድ እንደሆነ የሚታየው እውነት ይመሰክራል።

ከላይ ለአብነት የተጠቀሱት የማግባቢያ ቃላቶች አንድ አዝማሪ፣ ‹‹የወለዱት ባይሞት ያመኑት ባይከዳ፣ አባይ ቁልቁለቱ ይሆን ነበር ሜዳ…›› ሲል ያዜመውን ያስታውሱናል። መተማመን ቢኖር በአማላይና ሳቢ ቃላት የተዋቡ የቤት ማስታወቂያዎች ቤት ፈላጊዎችን ባለቤት ባደረጉ፤ ሰው የሚወደውን ባላጣ እና ውጣ ውረዱ፤ አስቸጋሪውና የማይቻል የሚመስው ሁኔታ ሁሉ ቀላልና ቀና እደሚሆን ያሳየበት ነው። በማር ተለውሰው የቀረቡ ማስታወቂያዎች ታምነው ቤት ቢሆኑ መሠረታዊ የሆነውን የቤት እጦት ችግር በማቃለል አስተዋጽኦው ከፍተኛ በሆነ ነበር። ዳሩ ግን ችግሩን ከማቅለል ይልቅ የብዙዎችን ተስፋ ከማጨለም ባሻገር ለእንግልት ዳርጓቸዋል።

ገቢ ማግኘትን ብቻ ታሳቢ ያደረጉ የሪል ስቴት ማስታወቂያዎች ሰፊ ችግር የተስተዋለባቸው ናቸው። በዚህ መልኩ በዘርፉ በተከሰቱ ችግሮች ቤት ይኖረናል ብለው ተስፋ ይዘው ተስፋቸው ከንቱ እንዲሆን ከሆነባቸው ተጠቂዎች መካከል ወይዘሮ ሳራ ዮሃንስ (ስማቸው ለዚህ ጽሑፍ ሲባል የተቀየረ) አንዷ ናቸው።

ወይዘሮዋ፣ ነዋሪነታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን፤ የቤት ባለቤት የመሆን ትልቅ ሕልማቸውን ለማሳካት በማስታወቂያ በተነገራቸው መረጃ መሰረት ወደ አንድ ታዋቂ ሪል ስቴት ጎራ ይላሉ። ሪል እስቴቱም ቤት ለመገንባት የሚያስችለውን ሁሉ መስፈርት እንዳሟላ እና ቤት ለመግዛት የሚፈልጉ ሰዎች ተገቢውን ክፍያ ሲከፍሉ ገንብቶ እንደሚያስረክብ ተስፋ በመስጠት፤ በሽያጭ ባለሙያዎች በኩል ክፍያውን እንዲፈጽሙ ያግባቧቸዋል፤ ያሳምኗቸዋልም።

ወይዘሮ ሳራ፣ ብቸገር እሸጠዋለው፤ ዕድሜዬ ሲገፋም እጦርበታለው፤ እኔ ሳልፍ ደግሞ ለልጅ ልጆቼና ለቤተሰቦቼ ቅርስ ይሆናል በማለት ካለቻቸው ጥሪት ላይ ቤት ለመግዛት በቅርብ ጓደኞቻቸው አማካኝነት አክሲዮን ገዙ። በዚሁ መሰረት 20 በመቶ የሚሆነውን ከፍለው ቀሪውን በየወሩ 38 ሺህ ብር እየከፈሉ ቤታቸው መጠባበቅ ጀመሩ። እንደ ወይዘሮ ሳራ ሁሉ የቤት የባለቤትነት ተስፋን የሰነቁ ሌሎች 27 ሰዎችም ከቤት ሻጭ ሪል እስቴቱ ጋር ውል ተዋውለው የሁልጊዜ ምኞታቸው የሆነውን ቤት ለመረከብ በተስፋ ይጠባበቁ ያዙ።

ስለ ጉዳዩ ያስረዱን እነዚህ የቤት ተስፈኞች እንደሚሉት፤ አብዛኛዎቹ ሰዎች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ማስታወቂያ እንዳዩና አክሲዮን እንደገዙ ይናገራሉ። ሪል እስቴቱም ለገዥዎች በሰጠው ተስፋ መሰረት እና ከቤት ፈላጊዎች በሰበሰበው ብር የተወሰነ ግንባታ ጀመረ። የግንባታው መጀመር ደግሞ ለገዢዎቹ የበለጠ ቤት የማግኘት ተስፋቸውን ከፍ አደረገው። ይሁን እና ቤቱ እያደገ እና ቤቱ ይደርሰናል ወደ ማለት ደረጃ ላይ ሲደርስ፤ ወይዘሮ ሳራን ጨምሮ ሌሎች ቤት ፈላጊዎችን ተስፋ ያስቆረጠ የቤት ሕልማቸው ያደረቀ ነገር አጋጠማቸው።

“ግንባታው ከተጀመረ በኋላ፣ የከፈሉበትና በገንዘባቸው እየተሠራ ያለውን ቤት ሪል እስቴቱ ለሌላ ሪል እስቴት በውል እና ማስረጃ ተዋውሎ ሸጠው።” ይህ ደግሞ የቤት ባለቤት እንሆናለን ብለው የሰነቁትን ሕልም የነጠቀ አጋጣሚ መሆኑን ነው ባለጉዳዮቹ የሚያስረዱት። ወይዘሮ ሳራ ስለጉዳዩ በቁጭት ሲያስረዱ፤ ይሄ የሆነው እርሳቸውና እና ሌሎች 27 ቤት ፈላጊዎች የመጀመሪያ ገዥዎች ስለነበሩ እንዲሁም የቤቱ ግንባታ ያልተጠናቀቀ ስለነበር፤ የግዥ ውል የፈጸሙት በመንደር ውል ስለነበረ ነው።

ለዚህም ነው ግንባታው ተጀምሮ የይዞታ ማረጋገጫ ሲወጣለት ሪል እስቴቱ ጅምር ቤቶቹን ግንባታ ጨርሶ ለእነርሱ ከማስረከብ ይልቅ በሰነዶች ማረጋገጫ ጽ/ቤት በኩል ለሌላ ሪል ስቴት የሸጠው። በእነርሱ ገንዘብ የተሰራውን ቤት የገዛው ሌላኛው ሪል ስቴት ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ለሌሎች ቤት ለሚፈልጉ ሰዎች ሸጦታል። ይህ የሆነው ደግሞ ሪል እስቴትን የተመለከተ ሕግ ባለመኖሩ እንደማንኛውም ቤት ሽያጭ በውልና ማስረጃ መሸጥ የሚችልበት ክፍተት ስለነበር ነው።

እኚህን ባለጉዳይ ጨምሮ ሌሎች ለቤቶቹ የተዋዋሉ ሰዎች አይሆንም ብለው ጠይቀው ተቃውሞ ቢያቀርቡም ምንም ማድረግ ሳይችሉ እንደቀሩ የሚናገሩት ወይዘሮዋ፤ ክስተቱ ከገንዘባቸው አሊያም የዘወትር ሕልማቸው ከነበረው ቤት ሳይሆኑ እንዳስቀራቸው ይናገራሉ።

“እኔ ከሪል ስቴት ቤት ለመግዛት ያሰብኩት ውጣ ውረድ የሌለበት እና በቀላሉ ቤት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ነው ብዬ ስለተማመንኩኝ እና በተለይም በትልልቅ መገናኛ ብዙሃን የሚነገረው ማስታወቂያ አምኜ ነበር። ይሁን እና ያሰብኩት ሳይሆን ያላሰብኩት ነገር ነው የገጠመኝ” ሲሉም ነው ወይዘሮ ሳራ ብሶታቸውን የገለጹት።

ወይዘሮ ሳራ፣ የሪል ስቴት አልሚዎችን የማስታወቂያ ማስነገርና የሌሎችን ልብ የመግዛት አካሄድን፣ የውል አሰራርንና ሌሎች ጉዳዮችን ሲያስረዱም፤ የሪል ስቴት ዘርፉ በዋናነት የተወሰኑ ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ሌሎች ተስበው በመግባት እዲከስሩ የሚደረግበት፤ ግለሰቦች ያለምንም የሕግ ልጓም ዜጎችን የሚበዘብዙበት መንገድ ነው ይሉታል።

ውሉን ከመዋዋላቸው በፊት የሽያጭ ባለሙያዎችን አናግረው፣ “በየወሩ የሠራተኛ ክፍያ ይጨምራል፤ ነገር ግን ቢጨመር በመቶ ብር የሚቆጠር ነው። ስለዚህ ሊደርስቦት የሚችለው ክፍያ በጣም ትንሽ ነው፤” የሚል የማታለያ ማብራሪያ በመጠቀም የሽያጭ ባለሙያዎች እንደነገሯቸውና ትንሽ ብር ከሆነ አይጎዳም በማለት በሀሳቡ ተስማምተው ውሉን መፈረማቸውን ነው ወይዘሮዋ የሚያስረዱት።

ለመሆኑ የሪል ስቴት ዘርፉ እንደ ሀገር ለምን በአሳሳች ማስታወቂያዎች፣ ማብራሪያዎችና በማይፈጸሙ ውሎች ታጅቦ የዜጎች መበዝበዣ መስክ ሆነ የሚለውን በተመለከተ፤ የተለያዩ ባለሙያዎች የየራሳቸውን አስተያየትና ብያኔ ይሰጣሉ። ኢንጂነር ደሳለኝ ከበደ፣ የ“ሪል ስቴት ኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ግብይት” የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፣ ዘርፉ በትክልል ቢመራና ቁጥጥር ቢደረግበት የቤት ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር መንግስት በዘርፉ ማግኘት የሚገባው ገቢ በትክክል እንዲሰበስብ ያስችለው ነበር። ነገር ግን ይህ ባለመሆኑ ምክንያት መንግስት ከፍተኛ ገቢ ከማጣቱም ባሻገር፣ ዘርፉ ሀይ ባይ አጥቶ ቤት እናገኛለን ብለው አክሲዮን የገዙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እንዲበዘበዙ እያደረገ ነው ይላሉ ።

በኢትዮ-አሊያንስ አድቮኬሲ ማኅበር የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቃለ-እግዚሐብሔር ጎሳዬ እንደሚያስረዱት፤ ዘርፉ በአግባቡ ሕግ ወጥቶለት ባለመመራቱ በማስታወቂያዎች እየተታለሉ የቤት አክሲዮን የገዙ ዜጎች ያሰቡት ቤት ደብዛው ጠፍቶ ቀርቷል። ዘርፉ ትርፋማ እና ብዙ ገንዘብ የሚገኝበት ነው። ሆኖም የዜጎች ተስፋ ከመሆን ይልቅ የሚጎዱበት እና ተስፋቸውን የሚያጡበት እየሆነ ከመጣ ከርሟል። በመደበኛው የሚዲያ ተቋም ሳይቀር ማስታወቂያ ሰምተው የሚጭበረበሩበት፤ የሚበደሉበትና ለበደላቸውም ፍትህ የተነፈጉበት/ያጡበት ዘርፍ ነው።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ዳኛ በኃይሉ ተዋበ በበኩላቸው፤ ማጭበርበሩ ማስታወቂዎችን ከማስነገር እንደሚጀምር ተናግረው ጥንቃቄው ከዚህ መጀመር አለበት ይላሉ። ማስታወቂያዎች ሲሠሩና ሲነገሩ በእውነት ላይ የተመረኮዙ እና ተጨባጭ መሆን አለባቸው። ይሁንና በተግባር የሚታየው ግን የሌለን ነገር ያለ አስመስሎ ማስታወቂያ መስራትና ማስነገር ነው። ሕዝቡም በመንግስት ሚዲያዎች ማስታወቂያው መተላለፉን በማየት እነዚህ ሰዎች ያሉት እውነት ነው ብሎ ተቀብሎ ገንዘቡን ካወጣ በኋላ በማስታወቂያ የተነገረው ነገር ሳይሆን እየቀረና ዜጎች እየተበዘበዙ ነው።

በርካታ ሪል ስቴት አልሚዎች ማስታወቂያ የሚያስነግሩት የሕንጻ መሰረት እንኳን ሳይጥሉ ነው። ይሄንን የሚከታታልና የሚከለክል ደግሞ የለም። የሌለን ነገር አለ ብሎ መናገር ማጭበርበር ስለሆነ ጉዳዩ ከፍትሐ ብሔርም በተጨማሪ በወንጀልም የሚያስጠይቅ ነው።

ለምሳሌ የሌለውን መሬት ይህ ይዞታ የኔ ነው፤ ቤት ገንብቼበት ልሸጥ ነው ብሎ ሰዎችን አታልሎ ገንዘብ ቢቀበል በወንጀል ያስጠይቃል። በዚህ ምክንያት (የተባለው እና የከፈሉበት ነገር የተለያየ ሆኖ ችግር ገጥሟቸው) ወደ ፍርድ ቤት ሲሄዱም፤ ችሎቱ የሚታየው በፍትሐ ብሔር ነው።

በዚህ መልኩ ደግሞ የተታለሉ ሰዎች ገንዘባቸውን ለማስመለስ ጥያቄ ሲያነሱ፣ ያጭበረበረው አካል ዋስትና ስለሌለው ለማስፈጸም ችግር ይገጥማል። ምክንያቱም ውሉ ችግር ያለበት ከመሆኑ ባሻገር፤ አልሚው መሬት እንኳን ሳይኖረው ቤት ገንብቼ እሸጣለሁ እያለ ማስታወቂያ የሚያስነግርበትና ከዜጎች ገንዘብ የሚሰበስብበት አግባብ መኖሩ ነው።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር (አሁን የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ) ዶክተር ብሩክ ታዬ እንደተናገሩት፤ በሪል ስቴት ዘርፉ ዙሪያ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ማስታወቂዎች ሳቢ እና አጓጊ ከመሆናቸው የተነሳ በርካታ ሰዎች እንዲሳሳቱና እንዲበዘበዙ አድርጓል። አንዳንዶች ቤት ይሁን አክሲዮን ምን እንኳን እንደሚሸጡ ሳያሳውቁ ነው ዜጎች በተሳሳተ ማስታወቂያ እየበዘበዙ ያሉት።

ችግሩን በመገንዘብ መፍትሄ የሚሆን መንገድ ለመከተል ተሞክሯል። በተለይም በካፒታል ገበያ በኩል ያለው ኃላፊነት በሼር የሚቋቋሙ ማናቸውም ድርጅቶች እንደመሆናቸው፤ ለመነገድ ተቋቁሞ ገበያ ላይ ወጥቶ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚፈልግ ማንኛውም ሼር ካምፓኒ ወይም አካል መጀመሪያ ወደ ካፒታል ገበያ መጥቶ የኢንቨስትመንት መግለጫ እና ደንበኛ ሳቢ መግለጫ አስገብቶ ያ ደንበኛ ሳቢ መግለጫው ላይ በካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዕይታ ኑሮት ከተፈቀደ በኋላ ነው ወደ ሕዝብ የሚደርሰው።

ይሁን አንጂ አሁንም ድረስ የተቋቋምንበትን አዋጅ  ካለማወቅ፣ ከመዘናጋት፣ አለበለዚያም መመሪያዎችን ካለማየት የተነሳ ቁጥጥር ያልተደረገባቸው ማስወቂያዎችን በሚዲያ ሲያስተዋወቁ አሁንም እየተስተዋለ ነው።

ያለፈውን መመለስ ባይቻል እንኳን አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍም ሆነ በቀጣይ መሰል ችግር እንዳይከሰት ከመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ጋር በመነጋገር፣ ማንኛውም ማስታወቂያ (በተለይ የአክሲዮን ሽያጭ ከሆነ) በካፒታል ገበያ ባለስልጣን ታይቶ ፈቃድ ሲያገኝ ብቻ እንዲነገር የሚያደርግ አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በእስካሁኑም ትግበራ በቴሌቪዥን እየወጡ ይህን ያህል ሚሊዮን ብር ታተርፋላችሁ እያሉ የሚያጭበረብሩትን አደብ እንዲገዙ አድርጓል። በተመሳሳይ የሪል ስቴት ካምፓኒ ይሁን የአክሲዮን ካምፓኒ በማይታወቅበት ሁኔታ የተዘበራረቀ ማስታወቂያ እያስነገሩ፣ ገንዘብ ብቻ የሚሰበስቡትንም ከገበያ እንዲወጡ ማድረግ አስችሏል።

የኢትዮ-አሊያንስ የጥብቅና መስራችና የክርክሮች ኃላፊ ጠበቃ አዲስ ሳዲቅ እንደሚያስረዱት፣ የኮንዶሚነየም ቤት የራሱ አዋጅ ኖሮት፣ የሚያስተዳድረው አካል ኖሮ፣ የቤቶች አስተዳደር የሚባል አዋጅ ተቀርጾለት ነው የተጀመረው። ይሁንና ይሄ ሕግ መንግስት የገነባቸውን ቤቶች ከማስተዳደር በዘለለ በግል ዘርፉ አማካኝነት የሚለማውን የሪል ስቴት ዘርፍ የሚያስተዳድር አይደለም።

የሪል ስቴት ዘርፉ የሚመራበት ሕግና አሰራር ባለመኖሩ ማንም አካል ሪል እስቴት እየገነባሁ ነው የሚል ማስታወቂያ በማስነገር፤ ዜጎችን ለመበዝበዣ ተጠቅሞበታል። በአጠቃላይ ዘርፉ የሚመራበት ሕግ እና የሚቆጣጠረው ተቋም ባለመኖሩ ዘርፉ መርህና ባለቤት አልባ ሆኗል። በዚህም ቃላቸውን ጠብቀው የገነቡትን ቤት ለከፈለው ማኅበረሰብ ያስተላለፉ ታማኝ የሆኑ ሪል ስቴት አልሚዎች ያሉ ቢሆንም፤ ዘርፉ ባለቤት የሌለው በመሆኑ ሪል እስቴት ብለው አቋቁመው ከኅብረተሰቡ ገንዘብ ሰብስበው የቤቱ መጨረሻ ሳይታይ ገንዘቡን ይዘው የሚጠፉ በርካቶች ናቸው።

ጠበቃ አዲስ እንደሚሉት፤ ለሪል ስቴት ዘርፍ ተብሎ የሕግ ማሕቀፍ ባለመኖሩ ምክንያት የውል ሕጉ እንደሚዋዋሉት ሰዎች አቅምና በሪል እስቴቱ ብልጠት ላይ የተወሰነ ሆኗል። አንድ ሪል ስቴት አልሚና ቤት ፈላጊ ግለሰብ ውል የመገንዘብ አቅም ደግሞ እኩል አይደለም። በዘርፉ የማኅበረሰቡ የቤት ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ ገንዘብ አለኝ ብሎ የመጣን ሰው ሁሉ በማግባባት ውል እንዲገባ የማድረግ ልምድ አለ። ለዚህ ደግሞ በርካታ የሪል ስቴት አልሚዎች የሕግ አማካሪ ስላላቸው ያለውን ክፍተት እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው አውቀው የራሳቸውን ጥቅም ያስጠብቁበታል።

ጠበቃ አዲስ፣ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በክርክር ሂደት ከገጠማቸው ጉዳይ ጋር አገናኝተው ሲያስረዱ፤ አንድ ሪል ስቴት አልሚ ነኝ ባይ ለሃያ ሰባት ሰዎች ቤት ገንብቶ ለመሸጥ የመንደር ውል ያስርላቸዋል። በገዥዎች ገንዘብም የቤት ግንባታውን ጀምሮ ለሌላ ሪል ስቴት ጅምር ቤቶቹን በውልና ማስረጃ ይሸጠዋል። ይሄን ያደረገው ሪል ስቴት አልሚ ታዲያ፣ ከሃያ ሰባቱ ሰዎች ጋር በመንደር ውል ሽያጭ ውል የያዘ ሲሆን፤ ለሪል እስቴቱ ግን በውል እና ማስረጃ በሕጋዊ መንገድ ነው የሸጠለት።

ምክንያቱም፣ ቀደም ሲል ለገዢዎቹ ሲሸጥ ቤት ስላልተገነባ ነው በመንደር ውል ያደረገው። ለሌላኛው ሪል ስቴት ሲሸጥ ግን ቤት ተገንብቷል፤ ካርታም አለው፤ ጅምር ቤት ስለሆነም መሸጥ ይቻላል። በዚህ ሂደት የቀደሙት ገዢዎች ቤቱን አልገዙም አይባልም። ምክንያቱም የመንደርም ውል ቢሆን መግዛታቸውን የሚሳይ ሰነድ አላቸው።

ነገር ግን በውልና ማስረጃ የጸደቀ (ማለትም ሶስተኛ ወገኖች መቃወሚያ ሊያደርጉት የሚችሉት) ውል አይደለም። የሸጠላቸው ሪል ስቴት አምኖ እስካልፈጸመ ድረስ፤ የውልና ማስረጃውን ስምምነት ለመፈጸም ይገደዳሉ፡ ምክንያቱም ሦስተኛ ወገን ውልና ማስረጃ ሄዶ የገዛው ሕጋዊ ማስረጃ አለው። በመሆኑም በዘርፉ ብዙ ተስፋ አድርገው የነበሩ ዜጎች በዚህ አይነት መንገድ ተበዝብዘው ተስፋቸውን አጥተው ቀርተዋል።

ተበዳዮቹ በፍርድ ገንዘባቸው ይመለስ የሚባልበት አግባብ ቢኖር እንኳን ከ10 ዓመት በፊት ሰድስት ሚሊዮን ብር ያወጣ ሰው፣ ከአስር ዓመት በኋላ ስድስት ሚሊየን ብሩን ምን ያደርግበታል? የሚለው ሲታይ፤ ኮንዶምንየም ቤት እንኳን ላይገዛለት ይችላል። “የፐርፐዝ ብላክን “ ጉዳይ ለአብነት በመውሰድ ጉዳዩን ለማስረዳት የሞከሩት ጠበቃው፤ የተጠቀሰው ድርጅት ቤት የሚገነባበትን መሬት እንኳን በአግባቡ ሳይዝ በባዶ ሜዳ ድርጅት አቋቁሞ ቤት

አክሲዮን እሸጣለሁ እያለ ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙሃን ያስነገረበት ሁኔታ ማሳያ መሆኑን ይጠቁማሉ። ይህ ሁሉ የሆነበት ዋናው ምክንያት ዘርፉ አዋጅና ሕግ የሌለው በመሆኑ፤ ይህን ተከትሎም የሚቆጣጠርና የሚመራ በገልጽ የሚታወቅ ተቋም ባለመኖሩ ነው።

ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በባዶ ሪል ስቴት ማቋቋም ቀላሉ ገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴ ሆኗል። ምክንያቱም የዘርፉ ቢዝነስ በአንድም በሌላ መንገድ ትንሽ መሬት ከያዙ በኋላ ተስፋ በመሸጥ ገንዘብ መሰብሰብ ነውና። የዜጎች ተስፋ ግን ጉም ሆኖ፣ ብዙ ተስፋዎች እንዲጨልሙ አድርጓል። ዘርፉ በሕግ ቢመራ ግን አልሚው በትክልል ገንብቶ ለተጠቃሚው ስለማቅረቡ ዋስትና ያቀርብ ነበር።

በዚህ መልኩ የሚደረጉ የግዢ ውሎች ገዥዎችን ሜዳ ላይ የሚያስቀሩ ናቸው። ለምሳሌ፣ መሬት አለ ተብሎ የተፈጸመ ውል፣ አፈጻጸም ላይ ሲመጣ መሬቱ በሌላ አልሚ ተይዟል፤ ብሩም የለም። ገንዘብ ሲቀበሉ በሁለት ዓመት እንጨርሳለን ቢሉም፤ በሁለት ዓመት አያሳኩትም። በዚህም ምክንያት አንድ ሚሊዮን ከፍሎ ቤት ለማግኘት የተስማማ ሰው፣ ይህ ሳይሳካ ቀርቶ በፍርድ ቤት ከ20 ዓመት በኋላ አንድ ሚሊየኑ ከወለድ ጋር ይመለስለት ቢባል፤ ይህ ገንዘብ እንኳን ቤት ተራ መኪና ላይገዛበት ይችላል። ጠበቃ አዲስ እንደገለጹት፤ ከአፍሪካ ኬንያ፤ የአውሮፓ ሀገራት፤ አሜሪካ፤ ሕንድና መሰል ሀገራት በሪል ስቴት ዘርፍ ውጤታማ ሆነዋል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ሕግና ስርዓት በማበጀት በመሥራታቸ ነው።

ኢንጅነር ደሳለኝ ከበደ እንደ ሕንድ ባሉ ሪል ስቴትን በተገቢው መንገድ ውጤታማ ያደረጉ ሀገራት የስኬታቸው ሚስጥር ምንጭ የግብይት ወይም የሽያጭ ባለሙያዎች በዘርፉ የሰለጠኑና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝቡ በማድረሳቸው ነው ይላሉ። ቤት ፈላጊው ማኅበረሰብ የነቃና ያወቀ በመሆኑም መረጃዎችን አገናዝቦ ስለሚገዛ ብሎም ዘርፉ በአሠራር እና በመመሪያ በመደገፉ ዜጎቻቸውን ከብዝበዛ ታድገዋል።

በእኛ ሀገር ሁኔታ ግን ይህ አልሆነም። እናም አልሚዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አማራጮች ተጠቅመው ካስተዋወቁ አብዛኛው ሰው ያምናል። እንደ ኢቢሲ፣ ኢቢኤስ፤ ዋልታና ፋናን መሰል ትልልቅ የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ማስታወቂያዎች ሲነገሩ የሚሰማ ቤት ፈላጊም፣ መገናኛ ብዙኃኑን ስለሚያምን አልሚዎችን አይጠራጠርም። ሆኖም ሪል ስቴት አልሚው የሚያቀርበው ማስታወቂያ፣ የቤት ፈላጊውን ድክመት በተረዳ የማስታወቂያ ስትራቴጂ ነው። በቅርቡ የተከሰተው የፐርፐዝ ብላክ ማስታወቂያም ለዚህ ጥሩ አብነት ነው። ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግም በትልልቅ ሚዲያዎች ጭምር አስነግሮ፤ አሁን ላይ ምን ደረጃ እንዳለ ይታወቃል።

ሕጋዊ ሳይሆኑ ሕግን ያከበሩ በማስመሰል በሕግና በአሰራር በሚመሩ መገናኛ ብዙሃን ማስታወቂያዎችን ከማስነገር ጋር በተያያዘ “የማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2004 ክፍል ሦስት አንቀጽ ስድስት ንዑስ ቁጥር አንድ ሀ እስከ ሰ ማንኛውም ማስታወቂያ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴት፤ የሚያከብር የሸማቹን ማኅበረሰብ የማይጎዳ መሆን እንዳለበት ይገልጻል።

በዚሁ አዋጅ ክፍል አምስት አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ አንድ ማስታወቂያ ለማሰራጨት የተቋቋመ የብሮድካስት አገልግሎት ካልሆነ በስተቀር በብሮድካስት አገልግሎት ተጓዳኝ በፕሮግራም መልክ የሚሰራጭ ማስታወቂያን፤ የስፖንሰር አድራጊውን ስም፤ ዓላማ፤ አገልግሎት፤ ምርትና መሰል መልዕክቶችን እንዲሁም የምስጋና መግለጫን ጨምሮ ለማንኛውም ማስታወቂያ የሚመደበውን ጊዜ ይደነግጋል። በዚህ ምዕራፍ ንኡስ አንቀጽ ሀ ላይ እንደተመላከተው ከዕለቱ ፕሮግራም ወይም አንድ የተለየ ፕሮግራም የስርጭት ጊዜ ውስጥ 20 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ነው።

በአዋጁ ክፍል ሰባት ላይ የማስታወቂያ አስነጋሪ፤ ወኪልና የማስታወቂያ አሰራጭ ግዴታዎች አንጽ 27 ንኡስ አንቀጽ አንድ ሀ እና ለ እንደተመላከተው በማስታወቂያ እንዲሰራጭ በማስታወቂያ አስነጋሪ የቀረበለትን መረጃ ትክክለኛነት የማረጋገጥ እና ማስታወቂያው በቀረበው መልኩ ቢሰራጭ ሕግን የመተላለፍ ውጤት የሚያስከትል ከሆነ ለማስታወቂያ አስነጋሪው እንዲያስተካከል የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

ይሄን ጉዳይ የመቆጣጠርና ችግሩን የመከላከል ኃላፊነት ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን እንደመሆኑ፤ በዚህ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የማስታወቂያ ክትትል ዴስክ ኃላፊ አቶ ዮናስ ፋንታዬ፣ የሚከተለውን ብለዋል።

የማስታወቂያ ዘርፉ በሕግና በስርዓት መመራት ስላለበት፣ እንደ ተቋም የማስታወቂያ ሥራ የሚከናወነው በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን እንደመሆኑ፣ በአዋጅ ቁጥር 759/2004 መሰረት ያስፈጽማል። እንደሀገር በነበረው ተሞክሮ ደግሞ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪው በልምድ የሚዘወር፤ ሙያው በሌላቸው አካላት ጭምር የሚሠራ ነበር። በርካታ ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ምርትና አገልግሎታቸውን በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በኅትመት ሚዲያውም የማስተዋወቅ ልምድ አልነበራቸውም፤ ቢኖርም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

ማስታወቂያ ማስነገር ሲባል የራሳቸው ግሳንግስ ምርት እንዲጭኑበት አይደለም የሚሉት አቶ ዮናስ፤ ማስታወቂያ በባህሪው ኢንዱስትሪ እንደመሆኑ የንግድ ውድድሩ ፍትሃዊ ሆኖ ለኅብረተሰቡ ትክለኛ መረጃ ማድረስ ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባው ነው የጠቆሙት። ይህ በመሆኑ ከተለያዩ የመንግስት ተቆጣቀጣሪ አካላት (ለምሳሌ፣ ከደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን) ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ምርትና አገልግሎቶች ደረጃቸው የጠበቁ እና የደረጃ መስፈርት ያለፉ ስለመሆናቸው፤ ማስታወቂያው በሚዲያ ሲሰራጭም ጥንቃቄ እንዲደረግ በጋራ ይሠራል።

ለማስታወቂያ አስነጋሪው/ ባለሀብቱ፤ ማስታወቂያ አዘጋጁና ማስታወቂያውን ለሚያሰራጨው ሚዲያ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይከናወናል። ምክንያቱም እነዚህ ሦስቱ አካላት በየደረጃቸው ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ ስላለ ነው፤ በዚህም የተወሰኑ ለውጦች ታይተዋል። በተለይ ሚዲያው በማኅበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እዲፈጠር በማድረግ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት የሚሉት አቶ ዮናስ፤ በእርሱ ሥራ ምክንያት ችግር ሲፈጠር በሕግ መጠየቅ አለበት። በመሆኑም ሚዲያዎች ማስታወቂያዎችን ሲያሰራጩ በባለቤትነት ስሜት ለሀገርና ለሕዝብ ወግነው መሥራት አለባቸው እንጂ፤ ገንዘብ ስለተከፈላቸው ብቻ ማሰራጨት የለባቸውም።

የሪል ስቴት ኢንዱስትሪው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የእውቀት እና የሕጋዊነት ጉዳይ ክፍተቶች ነበሩ። ገና ጅምር ኢንዱስትሪ ስለሆነ የሚስተዋሉ ጥፋቶችን ለማረም መጀመሪያ የሕግ ማሕቀፉን መሥራትና ግንዛቤ መፍጠር ተገቢ ነው። ምክንያቱም ሚዲያዎቹ በአዋጁ ልክ እርምጃ ይወሰድባቸው ወይም ይኮርኮሙ ቢባሉ ኖሮ እስካሁን አይኖሩም ነበር። ስለዚህ ዘርፉ ገና ጅምር ስለሆነ ማደግ ስላለበት ሆደ ሰፊ ሆኖ እንደሀገርና እንደተቋምም መስራት ስለነበረብን ይሄ ሲሠራ ቆይቷል። አሁን ላይ ግን የሚጠየቁበትን የሕግ ልኬት አውቀዋልና ክትትልና ተጠያቂነት ይኖራል።

እንደ ተቋም ጥፋት መኖሩና አለመኖሩ የሚለካው ማስታወቂያው ከተሰራጨ በኋላ ነው። ፕሮግራምና ማስታወቂያ ከተሰራጨ በኋላ ጉዳዩ ይታያል። መሬት ላይ ወይም ገበያ ላይ የሌለን ነገር ማስተዋወቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ጭምር ነው። ስለዚህ የማስታወቂያ ወኪሉም ሆነ አሰራጭ ሚዲያውም ምርቱ አለ ወይ? ብሎ የማረጋገጥ ኃላፊነት አለብህ የሚል ጥያቄ በማንሳት ተጠያቂ የሚሆንበት አግባብ አለ። እስካሁን ከካፒታል ገበያ ባለስልጣን ጋር በተሰራው ሥራም ብዙ ነገሮች ቆመዋል፤ ተስተካከልዋል።

አሁን ላይ የማስታወቂያ ወኪሎች ከባለስልጣኑ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፤ ወደ ሚዲያ ሲሄዱ ይህንን ሳያሳዩ አይስተናገዱም። ምርቱ ወይም አገልግሎቱ ፈቃድ አለው፤ የለውም ? የዘመኑን ፈቃድ አድሷል፣ አላደሰም? የሚለውን ይታያል። ይህንን ማስታወቂያ ያዘጋጀው አካል ሕጋዊ ነው ወይ? ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ አለው ወይ? የሚለው ሁሉ በሚገባ ይፈተሻል።

ከሪል ስቴት ወይም ደግሞ የመዋዕለ ንዋይ ገንዘብ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት የተሳሳተ አካሄድ ነበረው። በራሳቸው ድክመት ወይም ተነሳሽነት ማነስ ሳያረጋግጡ ማስታወቂያውን ሲያሰራጩ ኑረዋል። በዚህ ሳቢያም ሕዝቡ ለአላስፈላጊ ብዝበዛ እንዲዳረግ ሆኗል። የአክሲዮን ሽያጭ ገዥ እንዲመጣ ሲያስተዋውቅ የሚፈተሽ ጉዳይ አለው። ዛሬ ላይ በካፒታል ገበያ ተመዝኖ አልፎ የሚመጣ በመሆኑ መሬት ላይ ያለው ምንድን ነው? ተብሎ ሳይረጋገጥ ማስታወቂያው ወደ ስርጭት አይሄድም። ከዚህ የተነሳም ከማስታወቂያ ጋር የተያያዘ ከዚህ በኋላ የሚመጣ የማኅበረሰብ ስርቆት እና እንግልት የለም። ብር ሰብስቦ መጥፋትም አይቀጥልም።

ክፍል ሶስት ይቀጥላል

(በመልካም አስተዳደርና የምርመራ ዘገባ ቡድን)

አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You