በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
( ክፍል ሁለት )
የትህነግ /ህወሓት የውድቀት ቁልቁለት አሀዱ ብሎ የጀመረው የብሔር ጥያቄን ከመደብ ጭቆና አጃምሎ በውልውል ደደቢት የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም በ11 አንጋቾች በርሀ የወረደ ጊዜ ነው። በዓመቱ በ1968 ዓ.ም በማኒፌስቶው የአማራን ሕዝብና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የትግራይ ሕዝብ ጠላት አርጎ ሲፈርጅ መሻገሪያም መመለሻም ድልድዩን አፈረሰ።
ውሎ ሳያድር ከብሔርተኛ ድርጅትነት ወደ ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግነት ግራ ኋላ ሲዞር በተፈጠረ የርዕዮት ዓለም ልዩነትና አለመግባባት ሶስት የድርጅቱ መስራቾች እነ ግደይ ዘራፂዮን ፣ አስፋሃ ሀጎስ እና አረጋዊ በርሄ ቀኝ ኋላ ዞሩ። እነ መለስም የአክራሪ ብሔርተኝነት ሸሚዛቸው ላይ የአለማቀፍ ሕብረተሰባዊነትን ሽርጥን አንገታቸው ላይ አደረጉ።
ወለፈንዲዎችን አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ዲሞክራሲያዊ ማዕከልነትን እንደ ኩታ ከላይ ጣል አደረጉ። የማይታረቁ ፅንሰ ሀሳቦችን ማለትም አብዮት ብሎ ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ ብሎ አብዮት፤ ዴሞክራሲ ብሎ ማዕከላዊነት፣ ማዕከላዊ ብሎ ዴሞክራሲያዊነት፤ በማዛነቅ ማደናገሩን ተያያዘው። አብዮትና ዴሞክራሲ፣ ማዕከላዊና ዴሞክራሲ፤ አብረው አይኖሩም ። አይሄዱም።
እንደ እንግሊዙ የግሎሪየሰ እና የፈረንሳይ አብዮቶች ዴሞክራሲን ሊያዋልድ ይችላል እንጅ ከዴሞክራሲ ጋር በአብሮነት አይዘልቁም። ለዚህ ነው በአለማችን ከተካሄዱት ህልቁ መሳፍርት ከሌላቸው አብዮቶች ዴሞክራሲን ያዋለዱት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ የሆኑት። በማዕከላዊነት የዕዝ ጠገግ መመሪያን ከላይ ወደ ታች እያወረዱም። ለዚህ ነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ያልተባረኩ አስመሳይ ጋብቻዎች ናቸው የምለው ።
ትግራይን በመዳፉ ሲያስገባ የትግራይን ሪፐብሊክ ጭምብል አወለቀና በህልሙም በእውኑም እመራታለሁ ብሎ ያላሰባትንና አምርሮ የሚጠላትን ሀገር ስለመግዛት መተወን ጀመረ ። እንዲህ በማምታታት ፣ በፈጠራ ትርክትና ቁጭት ያሰባሰባቸው ጭፍራዎቹ ትግራይ ነጻ ከወጣች ከዚህ በኋላ አንዋጋም ሲሉት ደግሞ የሀውዜን ዘግናኝ ጭፍጨፋ አቀነባብሮ በገበያ ቀን በርካታ ንጹሐን እንዲገደሉ በማድረግ ፤ አንዋጋም ያሉትን ታጋዮች ትግራይ ነጻ ብትወጣም ደርግ ካልወደቀና መላ ኢትዮጵያ ነጻ ካልወጣ ነገ እንደሀውዜን እንጨፈጨፋለን ብሎ በማስፈራራትና በማታለል ብዙዎቹን መልሶ ከጎኑ ማሰለፍ ቻለ።
አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ደግሞ የአልባንያን ሶሻሊዝም አሽቀንጥሮ ጥሎ ነጭ ካፒታሊስት ነኝ ብሎ አረፈው። ከ70ሺህ በላይ ታጋዮች የተሰውለትን አላማ ጠልፎ የስልጣኑ ማደላደያና የጥቂቶች መክበሪያ አደረገው። ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ነጻነት በለየለት ፈላጭ ቆራጭነት፣ ጭቆናና ግፍ ተተካ። ደርግን ጥሎ ዳግማዊ ደርግ ሆነ ።
ፖለቲካው አሳታፊ ከመሆን ይልቅ አስመሳይና አግላይ ሆነ። የፖለቲካ ምህዳሩ እንደተከረቸመ ቀረ። ኢኮኖሚውም ፍትሐዊና አካታች ከመሆን ይልቅ ብዙኃኑን የበይ ተመልካች አደረገው። ሙስና ገነገነ። ዘረፋ ሙያ ሆነ ። ትህነግ ላለፉት 46 ዓመታት ለስልጣን ሲል ያልሆነውና ያልሄደበት መንገድ የለም። በክህደት፣ በሴራ፣ በደባ በቅጥፈት፣ በጥላቻ፣ በዘረፋ፣ በጭካኔ፣ በጉግማንጉግ ፣ ወዘተረፈ ተወልዶ አድጎና ጎልምሶ ሞቷል። ፖለቲካዊ ሞቱን ከምስረታው እኩል ጀምሯል የምለው ለዚህ ነው። ከስብሀት ጋር የማልስማማውም በዚህ የተነሳ ነው። “እኛ የሞትነው ስማችን (ህወሓት/ኢህአዴግ) ወደ ብልፅግና የተቀየረለት ነው ።
አሁን ቀብራችንን ነው እያስፈጸማችሁ ያላችሁት፤ “ቢልም ፤ ለእኔ ግን ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደሞከርሁት ትህነግ መሞት የጀመረው በግልብና ድቡሽት ትንተናው ላይ ክህደትንና ሴራን ለንጥቆ ከተመሠረተባት ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ዕለት ጀምሮ ነው።
በክፍል አንድ መጣጥፌ ፖለቲካዊ ትንተናው በአመክንዮና በተጠየቅ ሳይሆን በስሜትና በግዓብታዊነት የተቃኘ መሆኑ ፤ ለችግሮች ሀገረኛ መፍትሔ አለመሻት እና የተረክና የታሪክ ምርኮኛ መሆን ለትህነግም ሆነ በ60ዎቹ እንደ እንጉዳይ ፈልተው ለነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውድቀት በምክንያት መጠቀሳቸው እንዳለ ሆኖ።
ኮምኒዝም እንደተንኮታኮተ በ20 ዓመታት ውስጥ በቼክ ፣ ስሎቫክና ሀንጋሪ 37 የፖለቲካ ፓርቲዎች በየሀገራቱ አሸንፈው ፓርላማ ገብተው ነበር። በ2012 እኤአ ግን በምርጫ 5በመቶ ድምጽ ባለማግኘታቸው ብዙዎች ተሰርዘዋል። ፓርቲዎች ለመራጮች የገቡትን ቃል ኪዳን ሳይፈጸሙ ሲቀር፤ ፕሮግራሞቻቸውና ፖሊሲዎቻቸው ሲከሽፉ መራጩ ፊት ስለሚነሳቸው ይሰረዛሉ።
ይህ ቀናው ከፖለቲካ የመሸኛው መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በሀገራችን ይህ ነው የሚባል የርዕዮት ዓለም ወይም የፕሮግራም ልዩነት ሳይኖራቸው እንደ አሸን የፈሉ ፓርቲዎችን ለማንገዋለል ከድህረ ምርጫ በኋላ ይህን መስፈርት ስራ ላይ ማዋል። እንደ አማራጭ ስልት ሊያገለግል ይችላል። አሁን ለመወዳደር ከተለዩት 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከ5በመቶ በታች ድምጽ ያገኘውን ማሰናበት እንደ ማለት ነው ።
ትህነግ/ህወሓትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለውድቀት ከሚዳረጉ ፈተናዎች አምስቱ ግንባር ቀደም ናቸው። እነሱም ፦1ኛ. ጥርት ያለ የፖለቲካ ፕሮግራም አለመቅረጽ፤ 2ኛ. በሕገ ወጥ ተግባር ወይም ወንጀል ተሰማርቶ መገኘት፤ 3ኛ.የመወዳደሪያ ስትራቴጂ መክሸፍ፤ 4ኛ. በፓርቲዎች ውስጥ የሚፈጠሩ መከፋፈሎች የሚፈቱበት አግባብ ፤ 5ኛ. የፓርቲው የአደረጃጀትና አወቃቀር ጥንካሬ ናቸው። እያንዳንዳቸውን በወፍ በረር ስንመለከታቸው፤
1ኛ. ጥርት ያለ የፖለቲካ ፕሮግራም አለመቅረጽ፤ ትህነግን ለውድቀት ከዳረጉት ዐበይት ምክንያቶች ቀዳሚው በአመክንዮና በተጠየቅ የተተነተነ ወጥ የፖለቲካ ፕሮግራም መቅረፅ አለመቻሉ ነው። ይህ አልበቃ ብሎት ፕሮግራሙን በፈጠራ ትርክትና ጥላቻ መለሰኑ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲሰነጣጠቅ ፤ መስራች አባላቱ በጥርጣሬ እንዲተያዩና አንጃ መጎንቆል ጀመረ። መስራቹ አረጋዊ በርሔ በአርፋጁ ስብሀት ሲተካ፤ ገሰሰ አየለ/ስሁል/ በመሰሪው ስብሀት ሴራ ተገደለ።
የብሔር ጥያቄን ከመደብ ትግል ጋር እያፈራረቀና እያጃመለ የጠራ ፕሮግራም ሳይቀርጽ እስከ 1971 ዓ.ም በአፈተት ከዘለቀ በኋላ የትግራይ ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ /ትማሌሊ/ ይዞ ብቅ አለ። ከአክራሪ ብሔርተኝነት ወደ ኮሚኒስትነት ተቀየረ ። የሚገርመው ከምስራቅ አውሮፓዊ አልባኒያ የቀላወጠው ፕሮግራም ማህበራዊ መሰረቱ ላቭ አደሩ ሲሆን በጊዜው አይደለም ላቭ አደር ጠግቦ የሚያድር አርሶ አደር እንኳ ብርቅ ነበር።
የአልባኒያም ሆነ የትግራይና የኢትዮጵያ ሕዝብ የልቦና ውቅር ደግሞ በቅድም ሆነ በስፌት ሊገናኝ አይችልም ነበር። ሌላው ለትግራይ ሪፐብሊክ ምስረታ እታገላለሁ ብሎ ጀምሮ በርሀ ከወረደ በኋለ ድንገት እንደ እስስት ተቀይሮ ራሱን የብሔር ብሔረሰቦች ቃፊር አደረገ ። ወደ አራት ኪሎ ሲቃረብ ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲንና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን አስቀድሞ ነጭ ካፒታሊስት ሆኛለሁ አለ።
ውሎ ሳያድር ደግሞ ልማታዊ መንግስት ነኝ አለ። ይህ ሁሉ መቅበዝበዝ የጠራ ፕሮግራም እንዳልነበረውና ግቡም ስልጣን፣ ዘረፋና በቀል እንደነበር የሚያሳይ ነው። የመክሰሚያና የመለወጫ መንገድ ወይም የመውጫ ስትራቴጂ ስላልነበረው መጨረሻው ራስን በራስ ማጥፋት ሆኗል።
2ኛ. በሕገ ወጥ ተግባር ወይም ወንጀል ተሰማርቶ መገኘት፤ ትህነግ ውልደቱም እድገቱም ጉልምስናውም ሆነ ሞቱ በዘረፋ፣ በግድያ፣ በሴራ፣ በደባ፣ በቅጥፈት፣ በውልስትና፣ በክህደት፣ በስልጣን ጥመኝነት፣ በራስ ወዳድነት፣ ወዘተረፈ ያለፈ ነው። ባንክና ሀገር ዘርፏል፤ በትግል ጓዶቹም ሆነ እንደሱ በርሀ በወረዱ ድርጅቶች ላይ ክህደት ፈጽሟል፤ ከ20 ዓመታት በላይ በሀሩርና በቁር በቀበሮ ጉድጓድ ሆኖ ሲጠብቀው፤ በደስታውም በሀዘኑም ከትግራይ ሕዝብ ጎን የነበረውን፤ አለኝታው፣ መከታውና አጋዡ የነበረውን፤ ከትግራይ ሕዝብ ጋር የተጋባውንና የተዋለደውን የሰሜን ዕዝ ክዷል። በሰራዊቱ ላይ ለመስማት የሚሰቀጥጡ፣ ለማየት የሚዘገንኑ ግፎችን ፈጽሟል። የዕዙን የጦር መሳሪያ ዘርፏል።
አውድሟል። ሀገርን ከአንድም ከሁለት ሶስት ጊዜ በላይ ከድቷል። የኢፌዴሪን ሕገ መንግስት በተደጋጋሚ ጥሷል። የሀገሪቱን የምርጫ ሕጉን ጥሶ ምርጫ አካሂዷል። እጁን በደም ታጥቧል፤ የትግራይ ሕዝብ በርሀብ እንደ ቅጠል እየረገፈ የነፍስ አድን እህል ሽጦ የጦር መሳሪያ የገዛ አረመኔ ነው። ትህነግ ከጸሐይ በታች ያልጣሰው ሕግ፤ ያልፈጸመው ወንጀል የለም። በሀገሪቱ የወንጀልም ሆነ የፍትሐብሔር ሕጎች መጠየቁ እንዳለ ሆኖ፤ ትህነግ በአመጽ ተግባር ተሰማርቶ መገኘቱና ኢሕገ መንግስታዊ ምርጫ በማካሄዱ ሕጋዊ ሰውነት ተሰርዟል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው፤ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ሕወሓት/ “የአመፅ ተግባር ላይ ተሰማርቷል ወይ?”የሚለውን ሁኔታ ለማጣራት በፓርቲው የተሰጡ መግለጫዎችንና በይፋ የሚታወቁ ጥሬ ሀቆችን በማቅረብ፣ ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፅ ተግባር ላይ መሳተፉን አረጋግጧል፡፡
በተጨማሪም ፓርቲው መልስ የመስጠት ዕድል እንዲኖረው በማሰብ በፓርቲውና በቦርዱ መካከል አገናኝ በመሆን ይሠሩ የነበሩትን የፓርቲውን የአዲስ አበባ ቢሮ የቀድሞ ተወካይ ለማነጋገርጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ተወካዩም ፓርቲውን መወከል እንደማይችሉ ገልጸዋል። በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 98/1/4/ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ሰርዟል።
የአየለ ጫሚሶው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የመሥራች አባላት ዝርዝር የቦርዱም ሆነ የፖሊስ ኮሚሽኑ የማጣራት ሥራ የሚያሳየው ፓርቲው እያወቀ ወይም ማወቅ እየተገባው በቃለ-መሀላ በተረጋገጠ ሰነድ ያቀረበው የመሥራች አባላት ስም ዝርዝር የተጭበረበረ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ገልጾ ስለዚህ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 98/1ሠ/ መሠረት የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ እንዲሰረዝ ተወስኗል፡፡
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ፤ ” ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/”፤ ትግራይ /ባይቶና/”፤ ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ሳወት/”በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሒደት ላይ እያሉ፤ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በተካሄደ ሕገወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸውና የፓርቲዎቹ አመራሮች በአመፅ ተግባር መሳተፋቸው ለቦርዱ መረጃ በመድረሱ፤ስለ እንቅስቃሴያቸው ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱን የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል።
ደጋግሜ ለመግለጽ እንደሞከርሁት የትህነግ/ህወሓት ጉዳይ ሰፊና ጥልቅ ጥናት የሚጠይቅ ከመሆኑ ባሻገር በራሱ ዳጎስ ዳጎስ ያሉ በርካታ መጽሐፍት የሚወጣው ስለሆነ በዚህ አምድ ሁሉንም ማስተናገድ ስለማይቻል ቀጣዩን ሶስተኛውንና ምን አልባትም የመጨረሻ የሚሆነው ሶስተኛ ክፍል እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ይዤ እመለሳለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
አሜን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 24/2013