በጋዜጣው ሪፖርተር
‹‹በውጪ ሀገር የደከምኩበትን ጉልበት ግማሹን ያህል በሀገሬ ላይ ብሰራ ምንያክል ውጤታማ መሆን እንደምችል ስለተረዳሁ ነው ወደ ሀገር ቤት የመጣሁት። እዚህም ከመጣሁ በኋላ ምን ብሰራ የት ቦታ ብሰራ ያዋጣኛል የሚል መጠነኛ ጥናት አደረኩ ። ብዙ የሥራ ቦታዎችንም ተመልክቻለሁ። ሆኖም ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ተመሳሳይ የሆኑ ስራዎች ናቸው የሚበዙትና የሚሰሩት ።
ለምሳሌ አንድ ሰው የጀበና ቡና ለመነገድ ሥራ ከጀመረ ሌላውም በቅርብ ቦታ ላይ ተመሳሳይ ሥራ ይጀምራል። አንድ አይነት ሥራ በአንድ አካባቢ ላይ ሲኖር ተጠቃሚዎች አማራጭ ስለሚያገኙ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአንድ አካባቢ ላይ ተመሳሳይ ሥራ ከበዛ ደግሞ በስራው ላይ ለተሰማራው አካል የገበያ እጥረት ይፈጠራል።ስለዚህ ይሄንን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው ለንግድ የሚሆን አካባቢና የምነግደውን ስራ መወሰን የቻልኩት›› ትላለች ወይዘሪት ጸሀይ ታሪኩ።
ወጣት ፀሀይ ለረጅም ዓመታት የስራ ቦታዋን ያደረገችው ግብጽ ሀገር ነበር። እዛ በነበረችበት ወቅት ቀን ቀን በቤት ሠራተኛነት እየዋለች ማታ ደግሞ ከሌሎች አራት ጓደኞቿ ጋር ሆነው በተከራዩት ቤት ኑሮን ይገፋሉ ። በዚህ ሁኔታ ስምንት ዓመታትን አሳልፋለች።
የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቅቃ ወደ ግብጽ ከመሄዷ በፊት ግን የነበራት ዓላማ በከፍተኛ የትምህርት ተቋሟት መግባትና መማር ነው። ሆኖም ግን በወቅቱ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያገኘችው ውጤት ለዚህ ብቁ ስላላደረጋት ምርጫዋን ወደ ውጪ ሀገር መሄድና ሰርቶ ገንዘብ ማግኘትን አድርጋለች ። በዚሁ መሰረት ግብጽ ሀገር ሰው ቤት ሰርታ ያገኘችውን ገንዘብ ቋጥራ ወደ ሀገሯ ተመለሰች።
ወጣቷ ታዲያ ቀድሞውንም ቢሆን ራስን መቻል፣ ሰርቶ መለወጥ ወይም ተምሮ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚል ውስጣዊ ፍላጎትና ምኞት አላትና ለፍታና ሰርታ ባገኘችው ገንዘብ መገናኛ አካባቢ የህጻናት ልብስ መሸጫ ሱቅ ከፈተች።
የንግድ ስራ ጠንካራ መሆንን ይጠይቃል። ስልቹ ሰው፣ ደከመኝ የሚል፣ ጊዜውን ከስራው ውጪ የሚያባክን ነጋዴ መሆን አይችልም። ንግድ ሙሉ ጊዜን ይጠይቃል። ጠንካራ ሰራተኛ የሆነ ሰው ደግሞ ውጤታማ ይሆናል፤ በአጭር ጊዜም ያድጋል ትላለች ። ነገር ግን ብዙ ሰዎች ንግድ መነገድ ይፈራሉ ምክንያቱም መጀመሪያ አካባቢ ደንበኛ እስኪኖር እና ሰዎችም ቤቱን እስኪያውቁና እስኪለምዱት ድረስ ኪሳራ አለው።ወጪ እንጂ ገቢ አይታሰብም። ስለዚህ እከሌ ከስሮ ነው ከንግድ የወጣው ሲሉ ይሰማል።
አንድ ሰው አንድ ንግድ ቤት ሲከፍት የመጀመሪያውን ዓመት የስራ መለማመጃና የኪሳራ እንደሚሆን አውቆና አምኖ መሆን አለበት ። እሷም ይሄንን ሥራ ስትጀምር በዚሁ ሂሳብ ነው። ገበያ ሳይኖርም የቤት ኪራይ መክፈል የግድ ነው። ሌሎች ሌሎች መንግሥታዊ ወጪዎችም ይቀጥላሉ። ‹‹መገናኛ አካባቢ ያሉ ቤቶች ኪራይ ውድ ናቸው። ስለዚህ ቢያንስ ለአንድ ዓመት የቤት ኪራይ ያለ ሥራ ልከፍል እንደምችል አምኜ ለዚህም የሚሆነኝን ጠቀም ያለ ገንዘብ አዘጋጅቼ ነው ሥራ የጀመርኩት ።
በእኔ ሥራ ዛሬ እሁድ ነው፤ በዓል ነው፤ መሸ ብሎ መዝጋት አይቻልም። ምክንያቱም ብዙ ገበያተኛ የሚመጣው ከስራ ሰዓት ውጪ አመሻሽ ላይ ነው። በእረፍት ቀን ቅዳሜና እሁድ ነው የልጆች ልብስ ለመግዛት፣ ለልደትና አራስ ለመጠየቂያ ልብስ ለመግዛት ሸማቾች የሚመጡት።ስለዚህ ሁልጊዜ ሱቄ ክፍት መሆን አለበት። ››ትላለች ያለ እረፍት እየሰራች መሆኗን ስትገለጽ።
ወጣት ጸሀይ እንደምትለው፤ የሱቅ ሥራ ብዙውን ጊዜ ከባድ የሚሆነው ለብቻው ለሚሰራ ሰው ነው። አሁን ባለሁበት ሁኔታ ሠራተኛ ለመቅጠር አቅም የለኝም። ስለዚህ እቃ ማቅረቡንም ሱቅ መክፈትና መሸጡንም ማታ ማምሸቱንም ሁሉ ችዬ እሰራለሁ። አጋዥ ሰው ቢኖር በጣም ጥሩ ነው።
አንድ ሰው ዕቃ ለማምጣት ገበያ ሲሄድ ሌላው ሰው ደግሞ ሱቅ ሳይዘጋ ሽያጩን ያከናውናል። በዚህ መልኩ ውጤታማ መሆን ይቻላል። አንድ ሰው ብቻውን ሁሉንም ሥራ ራሱ ብቻ የሚሰራ ሲሆን ግን ትንሽ ይከብዳል። ቢሆንም ግን በሰው አገር ከመልፋት በሀገር ላይ እንደመስራት የሚያስደስት ነገር የለም ።
ብዙ ወጣቶች ከሀገራቸው የሚወጡት በውጪ ሀገር የተሻለ ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ ነው። ነገር ግን በሀገር ውስጥ ወጣቱ የብድር አገልግሎት የስራ መነሻ ገንዘብ ማግኘት ከቻለ በሀገር ውስጥ እንደመስራት የሚያስደስት ነገር የለም በማለት ነው ጠንክሮ በሀገሩ ተሯሩጦ የሚሰራ ሰው ውጤታማ እንደሚሆን ወጣት ፀሀይ የተናገረችው ።
የመገናኛ አካባቢ ሳምንቱን ሙሉ አመሻሹ ላይ ከፍተኛ በሆነ መልኩ የጎዳና ላይ ንግድ ደርቶ ይታያል። ከአዋቂ እስከ ህጻን ፣ የሴት እና የወንድ አልባሳት፣ የህፃናት መጫወቻ ሳይቀር በየአይነቱ ሽያጩ የሚደራበት ነው። አላፊ አግዳሚውም በአጋጣሚ ያየውን ያጋጠመውን ሁሉ እየሸመተ ያልፋል። ይሄ በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ትልቅ ጫናን የሚያስከትል መሆኑን ወጣት ፀሀይ ትናገራለች።
የጎዳና ላይ ንግድ በሱቅ ውስጥ ከሚሸጡ ልብሶች በጥራትም በዋጋም ያንሳል።ሆኖም ግን ሰዎች የዋጋውን መቀነስ ብቻ አይተው ይገዛሉ። በሌላ መልኩ ደግሞ በሱቅ ላይ የሚገኙ ልብሶችም ቢሆኑ ጎዳና ላይ ሲሸጡ ዋጋቸው ዝቅተኛ ነው።የዚህ ዋናው ምክንያት የጎዳና ነጋዴዎች የቤት ኪራይ የለባቸውም።
ከመንግሥት ግብርም ሆነ ሌሎች ወጪዎችን አይጠየቁም ።በዚህ ምክንያት ከህጋዊ ነጋዴው ባነሰ ዋጋ ይሸጣሉ። ይሄ ደግሞ ፍትሀዊ ውድድር እንዳይኖር ከማድረጉም ሌላ ህጋዊው ነጋዴ ገበያ በማጣት እንዲከስር ያደርገዋል። ስለዚህ ሁሉም ሰው ተወዳድሮና ሰርቶ የልፋቱን ተጠቃሚ እንዲሆን ህጋዊ መስመሩን መከተል አለበት ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
አዲስ ዘመን ጥር 24/2013