አብርሃም ተወልደ
የሰው ልጅ አዕምሮ እጅግ ብዙ ሃሳቦችን የማፍለቅና ታላቅ ሥራ የማከናወን ችሎታ አለው አንዳንድ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ትላልቅ ሥራዎችን ለመሥራት የቻሉት አዕምሯቸውን በመጠቀማቸው ነው እመነኝ አንተም የአዕምሮ ችሎታህን ማሳደግ ትችላለህ አዕምሮ ማደግ የሚችለው ሳያቋርጥ ሲሠራ ብቻ ስለሆነ ልታሠራው ይገባል።
ታዲያ አዕምሮህን እንዴት ነው የማሳድገው የሚል ጥያቄ ሊኖርህ ይችላል አዕምሮህን የምታሳድግበት መንገድ አንዱ መማር ነው፤ መማር እውቀትን ይጨምራል፤ ያሳፋል አዕምሮንም አንዲሁ፤ ይህን እውቀት ለማግኘት ደግሞ መደበኛ ትምህርት ገብቶ መማር አንደኛው ነው በተለያ መርሐ ግብር የሚሰጡ ትምህርቶችን ማለትም የማታ የተልዕኮ … ለመማር የዕድሜ ገደብ የለውም በህይወት እስካለ ድረስ ሰው ሁሉ መማር ማደግ ይችላል።
መማር የምትችልበት ሌላው መንገድ ማነበብ ነው የምታገኘውን ጽሑፍ ሁሉ አንብብ ነገር ግን የሚጻፈው ሁሉ መልካም ስላልሆነ ክፉን መለየት መቻል ይኖርብሃል ገንዘብ ስታገኝ ሰው “አለቆችህን”ጋብዘህ ወዳጅ አድርገህ በእነርሱ ለመሸሸግ ከመሞከር ይልቅ መጽሐፍ ግዛ በእውቀትህ ተማመን ማንም ቢሄድ ደግሞም ቢመጣ ካለህበት የሚነቀንቅህ አይኖርም።
ሌላኛው ከመጽሐፍ የምታገኘው እውቀት የተሻለ ሀብት ነው ከአንድ ግለሰብ ስር ስር ብለህ ከምታገኘው ፍርፋሪ ይልቅ፤ ዋናው እና መሰረታዊ ነገር ግን የማያነብ ሰው አዕምሮ ሊያድግ አይችልም መጽሐፍ ገንዘብ መሆኑን አንዳንዶች ላያስተውሉ ይችላሉ።
ለማደግ ግን አቋራጭ መንገድ የለም ዕድገት ረጅም የህይወት ጉዞ ነው አንተ ግን አቅም የሌላቸው “ተለጣፊ“ ሰዎች በሄዱበት ብትሄድ ለጊዜው የተጠቀምክ በአቋራጭም አንዳች ነገር ያገኘህ ሊመስልህ ይችላል ወዳጄ በህይወት አቋራጭ መንገድ የለም ፤ ብዙዎች በዚህ መንገድ ሄደው መመለሻው ማጣፊያው ያጠራቸው ብዙ ናቸው።
ለምሳሌ ሌቦች አንድ ሰው ቤት ገብተው የከበረ የሚሉት ቁሳቁስ ወርቅ ብር …ሌላም ሌላም ይወስዳሉ እኔ በዕድሜ መጽሐፍ የሰረቀ ሌባ አጋጥሞኝም ሰምቼም አላውቅም ምክንያቱም “የሌቦቹ” ፍላጎት በአቋራጭ ሀብታም መሆን ስለሆነ መጽሐፍ አንብበውና እውቀት አግኝተው ለማደግ የሚያስችል ትዕግስት የላቸውም።
ትኩረታቸው እውቀትን መሰረት ያደረገ ዘለቄታዊ እድገት ሳይሆን ቶሎ የሚገኝ ጊዜያዊ ሀብት ነው በአቋራጭ ሀብት፣ ዝና፣ ክብርና ሹመት ለማግኘት በተለያዩ መንገዶች የሚሄዱ ሰዎች የራሳቸው ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ህይወት ያናጋሉ፤ አገኘዋለው ላሉት ጉዳይ መሰናክል ከሆንክ ሊያጠፉህ፣ ሊገሉህ …. ብዙ ክፋታ ሊያደርጉ ይችላሉ በግል ህይወታቸውም ቢሆን ሰላም እና እርካታ አይኖራቸውም።
እውቀት ለአንድ ግለሰብም ሆነ ለአገር ወሳኝ ነው ስለሆነም የማንበብ እና የማወቅን ልማድ ልናሳድግ ይገባል የማንበብ ልምዳችን ካልዳበረን በቀር ድህነትን የምንዋጋበት መሳሪያችን ደካማ ይሆናል በአገራችን እንደሚታወቀው ብዙዎቻችን የመናር እንጂ የማነበብ ልምድ ብዙም የለንም ይህ ልምድ ግን መለወጥ አለበት መጋቢ አዲስ አለማየሁ አንዴ በአንድ የቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ስለንባብ ያላቸውን ሃሳብ ካካፈሉ በኋላ እንዲህ አሉ “የማያንብ ሰው የሌላ ሰው ሃሳብ መስጫ ሳጥን ነው” ይህ ደግሞ ሀቅ ነው።
አንባቢ ሰው ጸሐፊ ነው፤ ጸሐፊም ሲጽፍ ተራ ነገር ሳይሆን የሰውን ህይወት የሚለውጡ እና የሚያሻሽሉ ሰውን ከሰው ጋር የሚያቀራርቡ ሰላምን የሚያሰፍኑ እና እድገትን የሚያፋጥኑ ጽሑፎችን ማበርከት ይኖርብናል ኖሮ ኖሮ ሞተ ከመባል ቢያንስ ይህን አሊያም ያን ሠርቶ አለፈ መባል ምንኛ መልካም ነው!
ከማድመጥ ከማየት እና ከመስማት እና ከአንባቢ ሰዎች ጋር በመሆን ብዙ ነገር መማር ይቻላል የምትሰማቸውን እና የምታያቸውን ነገሮች አስተውል “ከእነዚህ ከምታያቸው እና ከምትሰማቸው ነገሮች ምን ልማር እችላለሁ ብለህ ራስህን ጠይቅ፤ የተማርካቸውን መልካም ንግግሮች ደግሞ እንዴት በተግባር ማዋል እንደምትችል አስብ የማሰብ ጊዜ ደግሞ ሊኖርህ ይገባል።
መጋቢ በቀለ ሻንቆ እንደሚሉት አዕምሮ ካላሰበ እንደልተሞረደ ስለት ሊደነዝዝ ይችላል አዕምሮ ከደነዘዘ ጥፋተኛው አንተ እንጂ ማንም አይደለም፤ ይህ እውነት ነው ብዙዎች በአቋራጭ ለአሰቡት መንገድ አንድ ጊዜ እንኳን ማሰብ አይፈልጉም እንደ ደራሽ ውሃ ከፊታቸው ያለውን መልካሙንም ሆነ ክፉውን ሰው እየጠራረገ ማለፍ ነው የሚፈልገው ማንበብ ማስተዋል ለራስህም ለሌላውም ሰላም እና ዕረፍት ዋና ጉዳይ ነው።
አንዳንድ ሰዎች ከሥራ ጡረታ ሲወጡ ቶሎ ያረጃሉ ፤ለዚህ ምክንያ ደግሞ “አሁን ጡረታ ወጥቻለው” ከማለታቸው የተነሳ አዕምሯቸው በሥራ ስለማይጠመድአካላቸውም ያለ ጊዜው ማርጀት ይጀምራል አዕምሮ ጡረታ ከወጣ አካልም ጡረታ ይወጣል ጡረታ ወጥተሃል ማለት በአንድ መስሪያ ቤት የነበረህን የሥራ ኮንትራት ጨርሰሃል ማለት እንጂ አዕምሮህ ሥራ ጨርሷል ማለት አይደለም ጡረታ መውጣት እንዲያውም ብዙ ጊዜ በሆነ ጊዜ ልትሠራ ያሰበከውን በጊዜ ማጣት ያስቀመጥከውን የምትሠራበት ነው።
ትምህርትን ከሁሉ ሰው መማር እንደምትችል ከላይ ጠቅሻለሁ ነገር ግን “ሁሉ” ማለት ማንኛው ሰው ትምህርት ቢኖረውም መልካሙን እና ክፉውን መለየት ግን ግድ ይላል ከአንዳንድ ሰዎች አብሮ በመሆን ብቻ ብዙ ትምህርት ልታገኝ ትችላልህ ታዲያ ወደእረሱ በመጠጋት መማር የምትችለውን ሁሉ ተማር በተጨማሪ ትምህርት የምታገኝባቸው አጋጣሚ እጅግ ብዙ ስለሆነ ማስታወሻ እና ብዕር ሁሉ በትይዝ መልካም ነው።
ያኔ ስታወራ ያምርብሃል የሰው ሳይሆን የራስ ሃሳብ ይኖርሃል ፤አቋራጩን ሳይሆን በቀጥታ እና በትዕግስት ያሰብከውን ልትደርስበት የተመኘኸውን ታደርጋለህ ከአቋራጩ መንገድ ግን ህይወት ቆራጭ ነው በሰላም፣ በተድላ የማንም ባሪያ ሳይሆኑ ለመኖር አንብቦ ተምሮ ከተለጣፊነት በመውጣት ራስ የሆነ ስብዕናን በመገንባት ህይወትን መምራት አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው፤ አሊያ የተለጠፍክበት ሰው ሊጠቅምህ የሚችለው አንድም ለእርሱ የምትሰጠው ነገር እስካለህ ድረስ ነው፤ ያ ሰው የሚፈልገውን ከአንተ ያጣ ዕለት አሊያም ሳት ብሎህ እርሱ የማይፈልገውን ነገር ያደረግ ለታ በአቋራጭ ያገኘሃትን በቅጽበት ታጣታለህ፤ ቅድሚያ እድገት ለአዕምሮ ይሁን። አበቃሁ!
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013