ሞገስ ጸጋዬ
ለአንድ ሀገር እድገትና መበልጸግ አስፈላጊ ከሆኑ መሰረታዊ ነገሮች መካከል መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ፣ በጥቂቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዋናነት ግን የመንገድ መኖር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በመንገድ አለመኖር ምክንያት በርካታ አርሶ አደሮች ለዘመናት ወደ ከተማ ሳይመጡ ይቀራሉ፡፡ ትምህርት ሳያገኙ እድሜያቸውን ይፈጃሉ፣ ያመረቱትን ለገበያ ማቅረብ ሳይችሉ ይቀራሉ፡፡
በአንፃሩ ደግሞ የመንገድ መሰረተ ልማት ሲሟላ ጎንደር፣ ጂማ፣ ጋምቤላና ቦረና በአጠቃላይ ከሀገሪቱ የትኛውም ጫፍ የተመረተው ምርት በቀላሉ አዲስ አበባ እና ሌሎች ትልልቅ ከተሞች ማጓጓዝና መሸጥ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የተሳለጠ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንኙነት እንዲኖር ትልቅ ጠቀሜታ አለው። አምራቹንም ሆነ ተጠቃሚውን በማገናኘት ገበያን ከማረጋጋት አንፃር አይተኬ ሚና ይኖረዋል፡፡
የውጭ ሀገር ባለሀብቶች አንድ ሀገር ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሲፈልጉ በመጀመሪያ ታሳቢ የሚያደርጉት የመንገድ ሽፋንን ነው፡፡ የተሟላ የመሰረተ ልማት አለወይ ቀዳሚ ጥያቄያቸው ነው። ምክንያቱም በሚሰማሩበት ዘርፍ የሚያመርቱትን የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ውጤት ወደ ገበያ ለማውጣት ዋናው የመንገድ መሰረተ ልማት መኖር ነው። ከዚህ አንፃር የመንገድ መሰረተ ልማት የችግሮች ሁሉ ማስተንፈሻ ነው ማለት ይቻላል:: አንድን ከተማ ከተማ ነው ለማለት አለም አቀፍ መስፈርቶች ያሉ ቢሆንም ሀገራት የተለያዩ መስፈርቶችን በማስቀመጥ ይህን ያክል ህዝቤ በከተማ ይኖራል እያሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
የህዝብ ብዛት አንዱ መለኪያ መስፈርት ነው። ነገር ግን የመንገድ መሰረተ ልማት ግን ሁሉም የሚስማሙበትና አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ነው፡፡ በርካታ ሀገሮች ከተማ ሲመሰርቱ በጥልቀት የሚጨነቁትና ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለመንገድ ነው፡፡
ያደጉ ሀገሮች ለመንገድ ልዩ ትኩረት ሰጥተው የገጠሩንና የከተማውን ህዝብ በስፋት በማገናኘት እንደ ሀገር አንድነት እንዲፈጠር፣ የንግድ ልውውጦች የተሳለጡ እንዲሆን፣ አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ በጊዜ በማድረስ ተጠቃሚ እንዲሆንና የከተማ ነዋሪዎችም የሚፈልጉትን ምርት በጊዜ እንዲያገኙ በማድረግ ጤናማ የሆነ የገበያ ስርአትና ትስስር ፈጥረዋል፡፡
ታዲያ ይህ የመንገድ ግንባታ ያመጣው ትሩፋት ነው፡፡ በእርግጥ በእኛና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ይህ ነገር አይስተዋልም፡፡ በከተማ ውስጥ የሚሰሩ ግንባታዎች መንገዶችን ታከው በመሆኑ ለተሽከርካሪዎችና ለመንገደኞች ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር አድርጎታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያም ለዜጎቿ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮቿን ለማሳለጥ ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ የመንገዶችን መሰረተ ልማት በማስፋፋት ላይ ትገኛለች፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት ብዙ መልካም አጋጣሚዎች ይፈጥራል፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት ሲኖር አርሶ አደሩ የሰበሰበውን ሰብል በቀላሉ ወደ ከተማ አምጥቶ በመሸጥ መለወጥ ይችላል::
ኑሮውን ከሚያቀሉለት ቁሶች ጋር በቀላሉ በመላመድ ወደ ተሻሻለ የኑሮ ደረጃ እንዲያድግ ያደርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የህክምና፣ የመብራት፣ የትምህርትና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን በፍጥነት ያገኛል፡፡ በኛ ሀገር ከተሜነት በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉበት ሲሆን በፕላን የወጣ መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት ህብረተሰቡ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ይጋለጣል፡፡ ሰዎች በቀላሉ ወደ ስራ ቦታቸው ለመሄድና ለመምጣትም ሆነ ሌላ ጉዳዮቻቸውን ለመከወን ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ ከግለሰብ አልፎ እንደ ሀገር ለዘርፈ ብዙ ችግሮችና እንግልቶች አለፍ ሲልም ለኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች ይዳርጋል፡፡
መንገድ ለአንድ ከተማ ዕድገት የጀርባ አጥንት ነው፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት ማለት ጥራትና ስፋትን ያማከለ ሲሆን ከተማን የመፍጠርና የማስፋፋት እድሉ ሰፊ ነው:: ከተማን ከከተማ ጋር በማገናኘት ሀገራትን የትላልቅ ከተማዎች ባለቤት እንዲሆኑ ያግዛል፡፡ የሰዎች የአኗኗር ደረጃ በፍጥነት ይቀየራል፡፡ አገልግሎቶች በፍጥነት ይዘምናሉ በጥቅሉ የሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ በእጅጉ የተቀላጠፈ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ከተሜነትን ለማስፋፋትና መላ የሀገሪቷን ህዝቦች ለማስተሳሰር በርካታ የመንገድ ስራዎችን እየከወነ ይገኛል፡፡ በቅርብ ግንባታቸው አልቆ ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑት መንገዶች መካከል በአፋር ክልል ባሳለፍነው ሳምንት የተመረቀው የዲቼቶ -ጋላፊ- በልሆ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ሲሆን መንገዱ የአፋር ገጠር ከተማዎችንና ቀበሌዎችን ከክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ ጋር እንዲሁም ኢትዮጵያን ከአሰብ ወደብ ጋር በማስተሳሰር ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፡፡ በርካታ ሰዎች የመንገዱን መጠናቀቅ ተከትሎ የመንገዱን አቅጣጫ በመከተል መስፈር ጀምረዋል፡፡
መንገዱ አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር በመጠናቀቁ ብቻ ድንበር ተሻጋሪ የከባድ ጭነት ሹፌሮችን ታሳቢ በማድረግ ሻይ ቡና፣ የምግብ አገልግሎት፣ የሻወር አገልግሎትና በሸራ የተሰሩ ግሮሰሪዎች በስፋት ተሰርተዋል፡፡ እንዲሁም የመሬት ሽያጭ ጡፎል፡፡ ይህ ሁሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ያመጣው ውጤት ነው፡፡ ነባር ከተማዎች የመስፋትና አዳዲስ ከተማዎች የመፈጠር እድላቸው ላቅ ያለ ነው፡፡ ህብረተሰቡም ከግብርና ወደ ንግድና አገልግሎት መስክ በመሰማራት መተዳደር ይጀምራል፡፡ ለብዙ ሰዎች በተለይ ደግሞ ለአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድሎች ይፈጠራሉ፡፡
ይህም የመንገድ መሰረተ ልማትና ከተሜነት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች መሆናቸውን ያመላክታል፡፡ ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ እስከ አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከጋላፊ ከተማ ጀምሮ በኤሊዳር ከተማ እና ሞሎዶኒ የገጠር ቀበሌ በማድረግ በኢትጵያና እና በጅቡቲ ጠረፍ በሆነችው የገጠር ቀበሌ በልሆ የሚያስተሳስር ነው፡፡ በዚህ እርቀት ሁሉ የአካባቢው ሰው ወደ ከተሜነት የመለወጥ ሰፊ እድሎች ይኖራሉ፡፡
የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የነገሩኝ ነገር ቢኖር ≪ማረፍ ስንፈልግና ሲደክመን አንኳን በአካባቢው ሰዎች ስለሌሉ አናርፍም፤ ቢጠማንና ቢርበን መብላት አንችልም። ያለን አማራጭ ከጂቡቲ ተነስተው ረዘም ላለ ጊዜ መጓዝ ነው≫ይላሉ፡፡ መንገዱ አጠቃላይ 78.37 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮንክሪት አስፋልት ግንባታ ፕሮጀክት ሲሆን የግንባታ ስራው የተጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2015 ዓ.ም ነው፡፡
የዲቾቶ – ጋላፊ መገንጠያ – ኤሊዳር – በልሆ መንገድ መገንባት አዲሱን የታጁራ ወደብ በአማራጭነት ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር በነባሩ ጅቡቲ ወደብ ይፈጠር የነበረውን የትራንስፖርት ጫና እና መጨናነቅ የማቃለል ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
ህብረተሰቡን የንግድ ተጠቃሚ በማድረግ ለሀገር እድገትና ዘመናዊነት ያለውን ሚና ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህ መንገድ አገሪቷ የወጪ ገቢ ንግድ የሚካሄድበት ኮሪደር በመሆኑ በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ሰዎች ይንቀሳቀሱበታል፡፡ ይህ ደግሞ በአካባቢው የንግድ ለውውጥ እንዲነቃቃና ከተሜነት እንዲስፋፋ ያደርገዋል፡፡
የመንገዱ ፕሮጀክት ተወካይ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ቢንያም ተስፋዬ እንደገለፁት የኮንክሪት መንገዱ ውፍረት 40 ሳንቲ ሜትር ሲሆን ስፋቱ በገጠር 7 ሜትር በከተማ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 14 ሜትር የሚሸፍን ነው።
አጠቃላይ 2 ነጥብ 3 ቢልዮን ብር በጀት ተይዞለት የግንባታ ሂደት 99 በመቶ መድረሱን አንስተዋል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ጠቀሜታውም ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡና የሚወጡ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የተሳለጠ እና በአካባቢው ያለውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡
ቀሪ የሚባሉ ስራዎችን መንገዱ አልፏቸው በሚሄዱ ከተማዎች የእግረኛ መንገድ እና የዲሾች ከደና ሥራ ብቻ መሆኑን እና እነዚህንም ቀሪ ስራዎች በአጭር ጊዜያት እንደሚጠናቀቁ ተጠቁሟል፡፡ የመንገድ ግንባታው የአፋር ክልልን በተለይ ለአካባቢው ማህበረሰብ ያለው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡
በተለይም በአፋር ክልል እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም እና በቀጣይ የአገሪቱ የመንገድ ልማት ውስጥ የክልል መንገድ ባለስልጣናት የሚኖራቸውን ሚና ከፍተኛ መሆኑንንም አብራርተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በመንገድ ግንባታ ሂደት ውስጥ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታና በቀጣይ ከሚኖረው ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፍላጎት አንፃር የክልሎችን አቅም ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ በስፋት ተሳታፊ ሆነው ለሀገር እድገትና ለዘመናዊነት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ ክልሎች በስፋት በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እና ጥገና እንዲሳተፉ እድል በመፍጠር መሰረተ ልማቶች እየተፋጠኑ ይገኛል፡፡
በየጊዜው እየጨመረ ለመጣው የህብረተሰቡ የመንገድ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ በመስጠት ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርለት እየተደረገ ነው፡፡ የህብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ መንገድ አይነተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ የሀገራችንን የመንገድ አውታር በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት ለመከወን እቅድ እንዳለ አንስተዋል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር ድኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ ወደፊት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ብልጽግናዎችን ለማጎናጸፍ የመንገድ ዘርፉ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር አለበት፡፡
ለዚህ ደግሞ ክልሎችም ተሳታፊ ሆነው እንዲሰሩ መንግስት መጠነ ሰፊ ስራዎችን ይሰራል፡፡ በተለይም የክልሎችን ሚና እና ሃላፊነት በግልጽ አስቀምጦ ይበልጥ የሚያጠናክር በመሆኑ የነበሩ ውስንነቶችን በመቅረፍ ለሀገራዊ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው ከኤርትራ የአሰብ ወደብ ጋር የሚያስተሳስረው የሜሎዶኒ መገንጠያ – ማንዳ – ቡሬ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በይፋ ወደ ስራ መግባቱም በገጠር ይኖር የነበረውን ህብረተሰብ ከተማ ከሚኖረው ህብረተሰብ ጋር በማገናኘት ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ ይረዳል፡፡ አካባቢው ቀደም ሲልም ቀላል የማይባል የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት በመሆኑ ከመንገዱ ግንባታ በኋላ የአካባቢው ህብረተሰብ በቀላሉ ተጠቃሚ እንደሚሆን ተገልጧል፡፡ ወደ አሰብ ወደብ የሚዘልቅ መንገድ እንደመሆኑ ለኢትዮጵያ የተሻለ የወጪ ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ መሳለጥ አይነተኛ ሚናውን ይጫወታል፡፡
የአካባቢውን ነዋሪ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቀላሉ በመገናኘት የንግድ ትስስራቸውን ያሳድጋሉ፡፡ 71 ነጥብ 65 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ይህን ፕሮጀክት በብር 2 ቢሊየን 085 ሚሊየን 985 ሺህ 162 በሆነ ወጪ ጨረታውን አሸንፎ ግንባታውን የሚያከናውነው ሻንዶንግ ሊኪኖ ግሩፕ የተባለ የውጪ የስራ ተቋራጭ ድርጅት ሲሆን ኢትዮጵያ ለምታደርገው የልማት ስራ መንገድ ዋነኛውንና አይነተኛውን ሚና ስለሚሆን በተባለው ጊዜ ከጥራት ጋር ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013