ታምራት ተስፋዬ
የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ የተጀመረው በየካቲት ወር 2007 ዓ.ም ነው። ፕሮጀክቱ ከአዋሽ-ኮምቦልቻና ከኮምቦልቻ- ሀራ ገበያ በሚል በሁለት ምዕራፍ የሚሠራ ሲሆን አጠቃላይ 390 ኪሎ ሜትር ይረዝማል፡፡
በአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገነባው ይህ ፕሮጀክት በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ ቢታቀድም በእቅዱ መሰረት ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱ አልተሳካለትም፡፡አስቀድሞ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጪ ከውጭ መንግሥታት በብድር ይገኛል የሚል እሳቤ ቢኖርም ገንዘቡም አልተገኘም፡፡
ከመንግሥት ወጪ እንደሚደረግ የታሰበው ቀሪ ድርሻም በሚፈለገው መጠን ባለመገኘቱም ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር፡፡ይሄ ውስንነትም የባቡር መስመሩ ግንባታ በሚፈለገው ልክ እንዳይቀላጠፍ ሲጎትተው ቆይቷል፡፡
የኃይል አቅርቦት በታሰበለት ጊዜ አለማግኘትም ሌላኛው የፕሮጀክቱ ፈተና ነበር፡፡በተለይ የአዋሽ ኮምቦልቻው መስመር ሙከራ በማድረግ ለትራፊክ ክፍት ለመሆን ዝግጁ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል ሲጠባበቅ ሥራ መጀመር አልቻለም።
የኃይል አቅርቦት ጥያቄው ያልተመለሰው በገንዘብ አቅርቦት ችግር መሆኑን በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢው መስሪያ ቤት መካከል በነበረ እሰጣ ገባም ችግሩ እልባት ሳያገኝ ረጅም ጊዜ እንዲያስቆጥር ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
የካሳ ክፍያ ጉዳይም ፕሮጀክቱ ባለበት እንዲረጋገጥ ካደረጉት ምክንያቶች በዋነኝነት የሚነሳ ነው፡፡የካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮችም ፕሮጀክቱ ላለፉት ስምንት ወራት አስተጓጉሎት ቆይቷል፡፡በአሁኑ ወቅትም ይህ ችግር መፍትሄ በማግኘቱ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ሥራ መቀጠሉ ታውቋል፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም መሃመድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁትም፣ ከአዋሽ-ኮምቦልቻ የሚዘረጋው የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ 99 በመቶ ተጠናቋል፡፡ከኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ያለው 122 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ አጠቃላይ ሥራ 82 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡ቀሪውን ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ሥራ አስኪያጁ፣ በአጠቃላይ ከኤሌክትሪክ አቅርቦትና ከከሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በሁለቱም ምዕራፎች የባቡር መስመር ዝርጋታ ሥራው ለስምንት ወር እንደተስተጓጎለ ገልፀዋል፡፡የፕሮጀክቱ አካል የሆነውና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቆ ያለአገልግሎት የቆየውን የአዋሽ ኮምቦልቻ የባቡር መስመር በቅርቡ ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ እንደሆነ ያመላከቱት ሥራ አስኪያጁ፣የሁለተኛው ምዕራፍ ከኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ያለው 122 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታም ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት ሥራው ተስተጓጉሎ መቆየቱን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
በመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታው 99 በመቶ ተጠናቆ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ወደ ሙከራ ሳይገባ የቆየውን አዋሽ – ኮምቦልቻ የባቡር መስመርን ሥራ ለማስጀመር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ይናገራሉ።
ችግሩን ለመፍታት በመንግሥት በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ለ480 አርሶ አደሮች 100 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ የካሳ ክፍያ በቅርቡ በመከፈሉ በሁለተኛው ምዕራፍ ተስተጓጉሎ የነበረው የ50 ኪሎ ሜትር መስመር ዝርጋታ ካለፈው ወር ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ነው የገለጹት።
82 በመቶ አፈፃፀም ላይ የሚገኘውና ከኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ የሚዘልቀውን ዝርጋታ ቀሪ ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ያመላከቱት ሥራ አስኪያጁ፣‹‹የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቱ በጊዜ መራዘም ምክንያት ተጨማሪ ወጪ እንዳይጠይቅ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተሰራ ይገኛልም ነው›› ያሉት፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ፕሮጀክቱ በቱርኩ ዓለም አቀፍ ተቋራጭ ‹ያፒ መርከዚ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን› የሚሠራ ነው። መነሻውን አዋሽ አድርጎ መዳረሻውን ሃራ ገበያ የሚያደርገው የባቡር ፕሮጀክቱ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ከሃምሳ በላይ ድልድዮች፣ 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 12 ዋሻዎችና 827 የውሃ ማፋሰሻዎች አሉት።
ስምንት የኃይል ማስተላለፊያና አስር የባቡር ጣቢያዎችም አሉት። ባቡሩ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። የባቡሩን አጠቃላይ ኦፕሬሽን ሥራና እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ማዕከል በኮምቦልቻ ከተማ እየተገነባለት ይገኛል፡፡ግንባታው ሲጠናቀቅ 26 ባቡሮች ይኖሩታል። 20ዎቹ የዕቃ መጫኛ ስድስቱ ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻ ይሆናሉ። አንዱ የሰው ማጓጓዣ ባቡር በአንድ ጊዜ 720 ሰዎችን ያጓጉዛል። ባቡሮቹ በቀን 4 ሺህ 320 ሰዎችን ማመላለስ ይችላሉ።
አንዱ የዕቃ ማመላለሻ ባቡር ደግሞ 1 ሺህ 350 ቶን የመሸከም አቅም አለው። አንዱ የዕቃ መጫኛ ባቡር 30 ተጎታቾች ይኖሩታል። አንዱ የዕቃ መጫኛ ባቡር 30 መኪኖች ከነተሳቢያቸው የሚጭኑትን ጭነት በአንድ ጊዜ የመሸከም አቅም አለው።የባቡር ትራንስፖርቱ አገልግሎት ሲጀምር ከአዋሽ ሀራ ገበያ ለመድረስ ከ4:30 እስከ 6:30 ይወስድበታል። ፕሮጀክቱ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለመድረስ የሚወስደውን ጊዜ 50 በመቶ ይቀንሳል።
ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘረጋው የአፍሪካ የምድር ባቡር መረብ አካል የሆነው ይህ ፕሮጀክት ለመካከለኛውና ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ቀጠና የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ እንደሀገር የገቢና ወጪ ምርትን የማሳለጥ፤ ከተሜነትንና ልማትን የማፋጠን ተስፋ እንዳለው ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013