ኃይለማርያም ወንድሙ
በቀደሙት ዘመናት የነበሩት ትምህርት ቤቶቻችን ከመደበኛ ትምህርት በተጓዳኝ የክህሎት ትምህርትና ስልጠና ይሰጡ ነበር። ስነጽሁፍ፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ ስዕል፣ ድራማ፣ ዘፈንና ውዝዋዜ፣ የመሳሰሉትን ማለት ነው።
በዚህም ተሰጥዖቸውን በማዳበር ከመደበኛ ትምህርት ውጪ ሲሰጡ በነበሩ ተጨማሪ የክህሎት ስልጠናዎች ፍሬያማ የሆኑ በርካታ ናቸው። ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በተለያዩ የክህሎት ስልጠና ይሰጡ የነበሩ ቀደምቶች አሁን ላሉት ታዳጊዎችና ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለትምህርት ቤቶችም ጭምር ምሳሌ ናቸው።
ከትምህርት ቤት ውጪ ለወጣቶች የስነምግባር መገንበያና ክህሎት ማሳደጊያ ይሆኑ ዘንድ ከጥቂት አመታት በፊት ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ወጣት ማዕከላት የታለመላቸውን ዓላማ በትክክል ተወተዋልን የሚለው ጥያቄ በማንሳት በትዝብት መልክ ያሉበት አጠቃላይ ሁናቴ በዛሬው የጋዜጠኛው ቅኝት አምዳችን ለመዳሰስ እንሞክራለን።
ወጣት ማዕከላቱ በዓለም ደረጃ የተከሰተውና በብዙ መልኩ መደበኛ ተግባርና እንቅስቃሴን ባወከው ኮቪድ ምክንያት ተዘግተው የቆዩ ቢሆኑም ዛሬ ላይ አንዳንድ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ባሉ ወጣት ማዕከላቱ በመገኘት ቆይታቸውን የተሻለ ለማድረግ ይጥራሉ። ነገር ግን እነዚህ ወጣቱን ያንፃሉ የትርፍ ጊዜ ቆይታውም የተሻለና ውጤታማ በሆነ መልክ ይገሩታል የተባሉት ወጣት ማዕከላት ዛሬ ላይ ቀድሞ የታሰበላቸውን ዓላማ መወጣት በሚያስችላቸው ቁመና መገኘታቸው አጠራጣሪ ያደርገዋል።
ወጣት ማዕከላቱ በየአካባቢው ያለው ስራ አጥ ወጣቶችን በመሰብሰብና ምቹ መዋያ እንዲሁን የተላያዩ ክህሎት መቅሰሚያ ይሆኑ ዘንድ ቢታሰብም ትኩረት ሰጥቶ ያሉበት ሁኔታ በትኩረት የተመለከተ የለም። ወጣቶቹ በልዩ ልዩ መልኩ ተደራጅተው የክህሎት ስልጠናና ትምህርት የሚያገኙበት መንገድ ማመቻቸት ሲገባ ችላ ተብለዋል። አንዳንድ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ወደ ማዕከላቱ ተመላልሰው ውሎና ቆይታቸው የተሻለ ለማድረግ ፍላጎት ቢኖራቸውም ወጣት ማዕከላቱ ያሉበት ሁኔታ ምቹ አለመሆን ያለሙት እንዳያሳኩ አድርጓቸዋል።
ወጣቶች ክህሎታቸውን ሊያሳድጉ ብሎም ሊያወጡና የሚችሉባቸው ማዕከሎች (የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት) እያሉ ወጣቶቹ በልዩ ልዩ መስክ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አላስቻላቸውም። መንግሥት የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት መገንባቱ አንድ እርምጃ ነው፤ ነገር ግን ማዕከላቱ ወጣቱን የሚጣሩ ሳይሆን የሚያባርሩ ይመስላሉ። የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላቱ ለወጣቱ የሚሆን የረባ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታዩም።
ለወጣቱ የሚበጅ ስራ ካልተሰራና የተሻለ እንቅስቃሴ ከሌለ ወጣቱ ተስፋ ሊያስቆርጠው ይችላል። ማዕከል ስላለ ብቻ የወጣት ስብዕና አይገነባም፤ በርግጥም ለወጣቱ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል። በጉዟችን የታዘብነው ትልቅ ማሳያችን እዚህ ጋር መጥቀሱ ተገቢ ነው።
በአራዳ በአዲስ ከተማና በኮልፌ የቃኘሁዋቸው የተወሰኑ ማዕከላት በክፍያ የደከመ ምግብ ቤት፣ የወጣቶች መጫወቻ፣ የገላ መታጠቢያ አገልግሎትና በአዳራሾቻቸው የአገር ውስጥና የአውሮፓን ኳስ ያሳያሉ፤ ቤተመጻህፍቶቻቸውም በወጉ የተደራጁ አይደሉም አሉ ከሚል ይልቅ የሉም በሚባልበት ደረጃ ላይ ናቸው።
ያሉትን መፅሀፍት የሚያነብ ወጣት በዚህ ተሰላችቶ አልያም በሌላ ምክንያት የለም፤ አንዳንዶቹ ማዕከላት የአይሲቲ አገልግሎት እንደነገሩ ሲሰጡ ይታያሉ፤ በደምብ የተደራጁ ግን አይደሉም። ወጣቶች በመልካም ስነ ምግባር እየተቀረጹ ሳይሆን በተቃራኒው እየቦዘኑ ናቸው። ማዕከላቱም ተሰጥኦን የሚያዳብሩ ሳይሆን ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ ሆነዋል።
ሁኔታውን አይቼ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥበቡ በቀለ አናገርኳቸው። በከተማዋ 113 ወጣት የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት እንዳሉ፤ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ መሆናቸውና፤ አንዳንዶቹ ሞዴል ሁለገብ ፣ መለስተኛ እና አነስተኛ መሆናቸው እንደ መረጃ ጠቆሙኝ።
ነገር ግን አንዳንዶቹ ማዕከላት ከመሠረተ ልማት ጋር በተለይ በከተማ የሚገኝ ወጣት ማዕከል ሊኖረው የሚገባው አገልግሎት ለማሟላት ችግር እንዳሉም አወጉኝ።
እነዚህን ችግሮች ከመፍታት አንፃር ቢሮው በዘንድሮ ዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ብር ለማዕከላት በማስመደብ ያለባቸውን ክፍተት በመለየት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑ ሲነግሩኝ ካለው የከፋ ችግር አንፃር በቂ ባይሆንም የሚታዩ የገዘፉ ችግሮችን ግን ከመፍታት አንፃር አንድ እርምጃ ነው ብዬ እንዳስብ አደረገኝ።
ማዕከላቱ ዓላማቸው ለወጣቱ ሳቢና ማራኪ በማድረግ እየተሰበሰበ ተሰጥኦውን ከማዳበር አንፃር የተለያዩ ክበባት እየተቋቋሙ ነው። እስካሁን በክበባት የተደራጁ ወደ 15ሺ ወጣቶች መኖራቸው ከሀላፊው የሰማሁትም ሌላ መረጃ ነበር። በቅኝቴ የክበባቱ የጎላ እንቅስቃሴ ባይታየኝም።
በወጣት ማዕከላቱ የሙዚቃ፣የኪነት፣የኤች አይቪ ኤድስ ክበብ፣ የጅምናስቲክ ፣ የሳይንስና ፈጠራ ክበብ የመሳሰሉ በተለያየ አግባብ በማዕከላቱ ውስጥ ተቋቁሟል። በነዚህ ክበባት አማካኝነት ወጣቶች መጥተው የራሳቸውን ተሰጥኦ የሚያዳብሩበት ዕድል ነበር በትክክልና በአግባቡ ቢሰራበት ኖሮ።
ዛሬ ላይ ሚዲያዎቹ እንደመብዛታቸው ወጣት አንባቢ እንዲፈጠር ማዕከላቱ ተደራጅተው ከጋዜጦች ከህትመቶች በማንበብ ወጣቱን ስነጽሁፍና ጥበብ አፍቃሪ ሲያደርጉት አይታይም። በሌላ በኩል ወጣቱም አጋጣሚውን ለመጠቀም ጥረት አያድርግ፡ ወጣቶች የተፈጠረላቸው ልዩ ልዩ ዕድል ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር ዕድለኛ ቢሆንም ያለው ሁኔታ ለራሳቸው ምቹ አድርገው ሲጠቀመበት ግን አይታይም።
ወጣቱ በተገነቡት ማዕከላት በመገልገል ውጤታማ መሆን ይገባዋል። ማዕከላቱም ወጣቶቹ በሚፈልጉትና ምቹ በሆነ መልክ መልሶ ማደራጀትና ተገቢ የሆነ አገልግሎት መስጠት ይገባቸዋል። ማዕከላቱ ወጣቱ የሚፈልገውና የሚጠይቀውን ጥያቄ አይተን ፍላጎቱን መነሻ ያደረጉ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል።
ለወጣቱ መፃይ ህይወት የተሻለ ዕድል የሚያቀርቡት እነዚህ የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በማጠናከር ወጣቱ በስነምግባርና በጥበብ ለማነጽ ጥረት ይደረግ ዘንድ ይታሰብበት። የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላቱ ለወጣቱ የሚበጁ ዘመኑን በዋጁ መልኩ ይደራጁ መልዕክታችን ነው፤ አበቃን።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013