ይቤ ከደጃች . ውቤ
ሰሞኑ የገጠመኝ አንድ ገጠመኝ እንካችሁማ ።ወጌን በዚያ አጣፍጬ ልጀምር ። አንድ ሽማግሌ “ጎበዝ እንደምን አላችሁ… እእ.. አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ… የሚባል ተረት ታቃላችሁ?” ብለው አንድ ሞቅ ያላቸው ሽማግሌ ድንገት ከቃያችን በተኮለኮልንበት መጡና ጠየቁን ።
ምላሻችንን ሳይጠብቁ “ዳሩ እናንተ ምን ታቃላችሁ? የታሪክ አተላ! ያሳደጋችሁ፤ መንግሥታችሁ ሲፈልግ እያቀፈና እየደገፈ ሲፈልግ እየተጠየፈ፣ እየነቀፈ እና እየገረፈ ጭምር ያኮላሻችሁ አይደላችሁ? አሉን ። ሰውየው፤ የደርግ ወታደር ሆነው ያገለገሉ ሃምሳ አለቃ እንደነበሩ ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡
ከእኛ ምላሽ ሳይጠብቁ ድጋሚ ለጠየቁን ጥያቄ ሲመልሱ “ይኸውላችሁ “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” ሲባል አውቃለሁ፤ በቃል ብቻ ። በትክክል ግን እንደተረቱ ዳኛም ሆኖ ያገለገለ ቀማኛም ሆኖ የተገለገለ ወያኔ ነበረ አሉን ።አንድ ወዳጄ እንዴት ብሎ አላቸው? የጎሪጥ ዕያዩን ሲራመዱም እየተንገዳገዱ ነበር፤ ይቅርታ አሉ እጃቸውን እያወዛወዙ፤ ስካር ነገር ስላለ ሲናገሩ አፋቸውን ያዝ ያዝ አድርጓቸዋል ።
ሀገር አስተዳዳሪ ሆኖም ንብረት መዝባሪም ሆኖ ጠቀመ ።“ አሉና ግንበራቸውን ወደ ሰማይ ቀና አደረጉ እጃቸውን አፋቸው ላይ ደርበው፤ “አይ የኔ ነገር ጠቀመ አልኩኝ አይደለ? ተጠቀመ እላለሁ ብዬ እኮ ነው ።
ለነገሩ ምን ችግር አለው? መርፌ የራስዋን ቀደዳ ሳትጠቅም የሌላውን ትጠቅማለች ይባል የለ? ሞኞች ተላሎች እኮ ናችሁ ።እነሱ በዱር በገደሉ የተዋጉት እናንተን ሊጠቅሙ ነው እንዴ ታዲያ? ሊጠቀሙ ነው ።አያችሁ ለዚህ ነው ዳኛም ቀማኛ ነበር ያልኩዋችሁ አሉን። አንዱ ጓዋደኛችን ተናዶ ሊያስተምሩን ነው እንዴ የመጡት? ሂዱ በቃ! እኛኮ ፖለቲካ ሰለቸን አለ
።ሰውየውም “ አታምኑኝም እንዴ? አውነት አውነት! የጁንታውን ቀን ይስጠኝ! “ ብለው ሁላችንንም አሳቁን፤ቀጠሉና “እናንተ ምን ታቃላችሁ? ቃና ላይ ተቸክላችሁ እና ይሄን ሞባይል እየጎረጎራችሁ የሚመዘበር ብር አይደለም የሚዘረዘር ብር የላችሁ ።የተናገርኩት እውነት ነው፤ እውነት ስለሆነ ጎመዘዛችሁ አይደል? አንዱ ወሮበላ ደግሞ መጥቶ የኪስ ሰጥቶ በአሸባሪነት አሰማርቶ እንደ ከብት ነድቶ ጫካ ይወስዳቹኋል፤ ትንሽ ትንሽ መጻፍ ለማየት ሞክሩ ፤ማንም የጎበዝ አለቃ ነኝ ባይ እንደ ከብት እንዳይነዳችሁ!” አሉን፡፡
“ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” እንደሚባለው ተረትና ምሳሌ ሰውየው በሞቅታ ውስጥ የተናገሩት ነገር እውነትነት እንዳለው ተረዳነው ።የወያኔ ሥርወ መንግሥት በለስ እየበላ ታግሎ በለስ ቀናውና ሥልጣን ጨበጠ ።ይሄን ሳስበው እኔም በግሌ ማለቴ ነው፤ የሥልጣን ጥማት ስላለብኝ፤ በለስ ከበላው በለስ ቀንቶኝ በትረ ሥልጣን እጨብጣለሁ እንዴ? ብዬ
አሰብኩኝ፡፡ማሰብ ሃሳብን መግለጽም ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ስለሆነ እርግጠኛ ነኝ ማንም አይቃወመኝም አይቀየመኝም ።የሚቃወመኝ ካለ ግን ሃሳቡን መግለጽ እንዲችል እፈቅድለታለሁ፤ መድረኩ ክፍት ነው ለማለት ፈልጌ ነው እንጂ በግሌ ፈቃጅም ከልካይ አይደለሁም፤ እኔም ሃሳቤን እንድገልጽ በራሴ ጥረት ጽፌ ነው ።ሕገ መንግሥቱ ያጎናጸፈውን ዴሞክራሲያዊ መብት ተጠቅሞ ማለቴ መሆኑ ይሰመርበት፡፡
ወያኔ በበረሃ በሸንተረርና በዱር በገደል እየታገለ ደርግን ደምስሶ ለሦስት አሥርት ዓመታት ሥልጣን ተጎናፀፈ፡፡ምን ዋጋ አለው ታዲያ ደርግን ደምስሶ ሲያበቃ ከደርግ ብሶ ተገኘ ።በአገዛዙ እየተንገሸገሹ ብዙዎች ስለተማረሩ “ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ” እያሉ የሚማረሩ ነበሩ ።
በአጠቃላይ በቆየበት የሥልጣን ዘመናቱ ከላይ ሽማግሌውም እንደተናገሩት ዳኛውም ቀማኛውም የወያኔ ሥርወ መንግሥት ሆኖ ተገኘ ።ስኳር ፋብሪካ እገነባለሁ ብሎ የመዘበረው ከ70 ሚሊዮን በላይ ብር ፤በአዲስ አበባ በሊዝ የተሸጠው መሬትና ገንዘቡ መጠኑን ማን ያውቀዋል፤ በከተማው ቁልፍ ቁልፍ ቦታ የተገነቡት የእነእንትና ናቸው የሚባሉት ህንፃዎች ምኑ ቅጡ ብንዘረዝረው ደግሞ ምን ሊያመጡ ይሉናል ፡፡
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ1953 ዓ.ም ታኅሣስ ላይ ብራዚል ለጉብኝት ሄደው ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይና ገርማሜ ንዋይ በገነተ ልዑል ቤተመንግሥት መፈንቅለ መንግሥት አካሄዱ፤ከሸፈና ብዙ ሰው ሞተ፤ወቅቱም የታኅሣስ ግርግር በመባል ይታወቃል ። በተካሄደው እና በከሸፈው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተመልሰው ወደ ገነት ልዑል ቤተ መንግሥት ለመግባት አልደፈሩም፡፡ግቢው ሸሹትና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ
ዩኒቨርሲቲ ሆነ፤አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምንለው 6ኪሎ የሚገኘው ዋናው ግቢ ማለት ነው፡፡
ተማሪዎች ገብተው ተማሩበት ተመራመሩበት የሰከኑት ነገር ተወራወሩበት ያልሰከኑት ጠጠር ተወራወሩበት ያደጉት (መሣሪያ የማግኘት የቻሉት ማለቴ ነው) ደግሞ ጥይት የተወራወሩበት አሉ፡፡ኢህአፓንና ደርግን ያስታውሷል። ንጉሡ ግቢውን ቢሸሹትም ቆይቶ የግቢው ተማሪ በአመፅ ተከታላቸው፤ ወሎና የትግራይ ድርቅ የአመፁ ማቀጣጠያ ሰነድ ሆነ፤ ተማሪው ንጉሡ ይውረዱ ብሎ ተቃውሞ አነሳሳ ቀጥሎም አብዮቱ ፈነዳ፡፡ የምሁራኑን አመፅ ተከትሎ ወታደሩ ንጉሡን ከሥልጣን አወረደ ።
ከቀደሙት ትውልዶች ይልቅ ስክነትን ከስኬት ጋር አጣምረው መያዝ ሲገባቸው እርስ በርስ ተላለቁ፤ ጥይት መተኮስ ደም ማፍሰስ መደበኛ ሥራቸው ሆነ። ለዚህም በር ከፋቹ ኢህአፓ ነበር፡፡ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ተከታይ የነበሩት ደርግ እና ኢህአፓ በእናቸንፋለንና በእናሸንፋለን በሸ እና በቸ ፊደል የልዩነት ሰበዝ እየመዘዙ እርስ በርስ ተጠዛጠዙ፡፡
ደርግ ተገርሥሶ ወያኔ ሥልጣን ሲይዝም የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ቤተ መዘክር እንዲመሠረት አደረገ፡፡ምን ዋጋ አለው ከደርግ ብሶ የብዙኃኑን ደምና እንባ አፍሶ የሽብር አስተዳደር ፈፀመ ።አሁንም ያንኑ አስጸያፊ ታሪክ ካልደገምን የሚሉ ወያኔ ጭራ ኦነግ ሸኔ የመሳሰሉ አሉ፡፡የትህነግ ጭራ የነበሩት እነ ሳምሪ በማይካድራ የፈፀሙት ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል መሆኑ መገናኛ ብዙኃኑ የዘገቡት ነው ።በመተከልም የተተከለው ዕኩይ ድርጊት ለመንቀልና ለመጣል ጥረት ይደረግ፡፡የሚመለከታቸው አካላት በተለይ ቸልተኞቹ የዞኑና የክልሉ አመራሮች የሚሞቱና የሚፈናቀሉ ወገኖች ለመታደግ ይንቀሳቀሱ ።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013