ምህረት ሞገስ
በዓል ሲደርስ ከአዲስ አበባ ወደ የትኛውም ክልል የሚደረጉ ጉዞዎች ውጣ ውረድ የበዛባቸው፣ የሚያንከራትቱ እና አሰልቺዎች መሆናቸው ባያጠያይቅም ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ መሄድ ግን እጅግ ከባድ እና የተለየ መሆኑን የሚናገሩት በከተማዋ ተወልደው ያደጉት አቶ መልካሙ ተክሌ ናቸው፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ በአዲስ አበባ አውቶብስ ተራ ወደ አምቦ የሚጭን መኪና ለማግኘት ትልቅ ፈተና ነው። ከአዲስ አበባ አምቦ መስመርን በሚመለከት በሁለተኛ መናሃሪያነት የሚጠቀሰው የአስኮ አውቶቢስ ተራም ቢሆን በቀላሉ ወደ አምቦ የሚሄድ መኪና ማግኘት አይታሰብም። ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ ለመሄድ ወትሮም ቢሆን ከአንድ ሰዓት ተኩል እስከ ሦስት ሰዓት ወረፋ መጠበቅ የግድ ነው።
አቶ መልካሙ፤ በመስቀል የበዓል ሰሞን ከኢሬቻ ጋር ተያይዞ ከስምንት ሰዓት በላይ ወረፋ በመጠበቅ መኪና ማግኘት አለመቻላቸውን ያጋጠማቸውን በመጥቀስ ያብራራሉ ።‹‹ ከአዲስ አበባ አምቦ ቅርብ ነው›› በሚል የመስቀል ሰሞን ለበዓል ወደ ቤተሰብ ለመሄድ የተነሱት 4 ሰዓት ከ30 ላይ አውቶቢስ ተራ መናሃሪያ ደርሰው ወረፋ ቢይዙም እስከ 12 ሰዓት መኪና ማግኘት አልቻሉም።
የተለመደው ታሪፍ 60 ብር ቢሆንም ሰዎች ለአንድ ሰው እስከ 350 ብር በመክፈል ወደ አምቦ መሄድ የቻሉ መሆኑን በመስማት፤ ደላሎችን ጠይቀው በሁለት መቶ ሃምሳ ብር ‹‹ ሃይ ሩፍ ወይም ዶልፊን መኪና ታገኛላችሁ›› ተብለው ቢጠብቁም ወደ አምቦ መሄጃ መኪና ሳያገኙ መቅረታቸውን ያስታውሳሉ ።
‹‹እኔ በአጋጣሚ አልቀረሁም፤ በቤተሰብ መኪና ብሔድም አብረውኝ የነበሩት ሰዎች ግን የአምቦ መኪና ማግኘት እንደትልቅ ነገር ከባድ ጉዳይ ሆኖባቸው ተሰቃይተው የቀሩ ብዙ ናቸው›› ካሉ በኋላ፤ እጅግ በጣም የገረማቸው መመለስ በራሱ ትልቅ ፈተና ሆናባቸው የነበረ መሆኑ ነው ። ለመስቀል ብቻ ሳይሆን ለገና በዓልም ተመሳሳይ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ለገና በዓል ተመሳሳይ እጥረት ሲያጋጥም እርሳቸው እና ሌሎች ሰዎች ተሰባስበው በአውቶቢስ ተራ ስምሪት ክፍልን በማነጋገራቸው፤ ወደ አምቦ 60 ሰው የሚጭን ትልቅ መኪና ተመድቦ ተመላሽ ስለሌለ በአንድ ሰው 100 ብር በመክፈል መሄዳቸውን ያብራራሉ ።
አምቦ ብቻ ለምን እጥረት ይኖራል? በማለት የሚጠይቁት አቶ መልካሙ የአስኮ አውቶብስ ተራ መናኸሪያ የሚሻል መሆኑን፤ ቀድሞ በመናኸሪያነት ለአምቦ መስመርም ያገለግላል የተባለው የአሸዋ ሜዳ መናሃሪያ ሙሉ ለሙሉ እንደማይሰራ እና በመርካቶ አቶቢስ ተራ ደግሞ ከፍተኛ መንገላታት መኖሩንም ይገልፃሉ ።
ምንም እንኳ አቶ መልካሙ ለበዓል ወደ አምቦ የሚሄዱ ቢሆንም ከበዓል በኋላ በሚሄዱበት ጊዜ የትራንስፖርት ሁኔታውን ሲያጣሩ እና ከተሳፋሪዎች መረጃ ሲያሰባስቡ ሁልጊዜም ወደ አምቦ የሚደረግ ጉዞ የትራንስፖርት እጥረት የሚታይበትና ወረፋ የበዛበት መሆኑን እንዳረጋገጡ እና በሌሎች ልክ እንደአምቦ ተቀራራቢ ርቀት ባለባቸው አካባቢዎች ማለትም ወሊሶ፣ ደብረብርሃን እና አዳማ ለመሄድ የትራንስፖርት ወረፋ እንደማይጠበቅ እንደውም በግድ በጥሪ መኪናዎች የሚሞሉ መሆኑን ያስረዳሉ ።
ከበዓል ሰሞን ባሻገር በቅርቡም የታመሙ ሰዎች ሳይቀሩ ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት መቸገራቸውን በማስታወስ፤ አንድ የቤተሰብ አባላቸው ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ከለሊት 11 ሰዓት ተነስቶ መኪና ያገኘው ጠዋት 2 ሰዓት ላይ መሆኑን በመጠቆም፤ ‹‹እባካችሁ ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው፤ የሚመለከተውን አካል ጠይቁልን›› ብለዋል ።
በኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ባለስልጣን የትራንስፖርት አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ ለማ እንደሚናገሩት፤ ጥያቄው ትክክል ነው። በክልሉ 13 ሺህ የትራንስፖርት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች አሉ ።
3ሺህ 500 የትራንስፖርት መመላለሻ መስመሮች አሉ ።እነዚህ የክልሉን ህዝብ በመደበኛ ፍሰት ለማገልገል ይበቃሉ ማለት አይቻልም ።ጥያቄ የቀረበበት ከአዲስ አበባ አምቦ መስመር አልፎ አልፎ በበዓል ጊዜ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥሪ ሲያቀርቡ እጥረት ያጋጥማል ።
በጥምቀት ወቅት እንደዚህ አይነት እጥረት በማጋጠሙ በፌዴራልም ሆነ በክልሉ ትራንስፖርት መመሪያ የተፈቀደውን በመጨመር ለማጓጓዝ ጥረት ተደርጓል ።ይህ የተደረገው በአቅርቦት እና ፍላጎት መካከል ሰፊ ክፍተት መኖሩን በማየት ነው ። ብዙ ሰው በአንድ ጊዜ የሚንቀሳቀሰው በተመሳሳይ ጊዜ ነው ።
ለምሳሌ የበዓል ሰሞን ወደ አምቦ የሚሄደው ብዙ ሲሆን ተመላሽ የለም ። መኪናው ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ መሄዱ ችግር ይፈጥራል። ሌላው ግን አገር አቋራጭ እና ሌሎች አማራጮችንም በመጠቀም ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል።
‹‹በተረፈ በመደበኛነት በቀን በአምቦ መስመር ከ500 መኪና በላይ ይሰማራል›› የሚሉት አቶ ዓለሙ፤ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በቂ ናቸው ማለት ባይቻልም ያለውን ችግር የሚያቃልሉ ናቸው ።በተረፈ ፍሰቱ ሲጨምር ለማስተናገድ የአቅም ውስንነት መኖሩ የሚካድ አይደለም ብለዋል ።
ጥያቄ አቅራቢው ታማሚ ሳይቀር በትራንስፖርት ችግር እየተንገላታ ነው በሚል ላቀረቡት ሃሳብ፤ አቶ ዓለሙ በሰጡት ምላሽ በሽተኛ ሰው ከሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር አብሮ በህዝብ ትራንስፖርት መሄድ የለበትም።
ኮንትራት ወይም ሌሎች አማራጮችን መውሰድ እንዳለበት እና የሌላው ተሳፋሪ ደህንነት መጠበቅ እንደሚገባው ጠቁመው፤ ሰሞኑን ችግሩ የተፈጠረው የሠርግ ሰሞን በመሆኑ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል ።ከዚህ በኋላ ግን መኪና ተሳፋሪ አጥቶ እየጠራ መዋሉን ማረጋገጥ እንደሚቻል ይገልፃሉ ።
አቶ ዓለሙ እንደተናገሩት፤ የጠያቂውን ያህል የከበደ ፍላጎት ቢኖር ኖሮ የተሽከርካሪ ባለንብረቱም በሌላ መስመር ቆሞ ከመዋል መስመሩ ላይ መሰማራቱ እንደማይቀር በመጠቆም፤ የክልሉ የትራንስፖርት ባለሥልጣን በተቻለው መጠን ለተገልጋዩ ህብረተሰብም ሆነ ለአሽከርካሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አገልግሎቱ የተሻለ እንዲሆን ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ነው የጠቆሙት ።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013