ወርቅነሽ ደምሰው
አበው ‹‹ጠላቴን እኔ እጠብቀዋለሁ፤ ወዳጄን አንተ ጠብቅልኝ ›› ብለው የተናገሩት በምክንያት ነበር:: ጠላት የሚባለው አካል ከወዳጅ የሚለይበት የራሱ መለዮ ያለው ነው:: ጠላት አሳቻ ጊዜና ቦታ ጠብቆ ሊያጠቃ ይችላል የተባለ አካል ነው:: ጠላት አለኝ ብሎ የሚያስበው ወገን ደግሞ ጠላቱን ከለየ በኋላ ለመከላከል የሚቻልበት ዘዴ አስቀድሞ ይቀይሳል:: የጠላት መግቢያና መውጫ ቀዳዳ በመለየት ሊደርስበት ከሚችለው ጥቃት አስቀድሞ እራሱን ለመከላከል ዝግጁ ይደረጋል::
በጠላቱና በእርሱ መካከል ያለውን ድንበር አልፎ ደፍሮ ሊያጠቃው የመጣበት አካል ካለ አቅሙን አጠናክሮ በተጠንቀቅ በመቆም ለመከላከል የሚችለውን ያህል በመፍጨርጨር ለመከላከል ያለ የሌለ ኃይሉን አሟጦ ይጠቀማል :: ይህም ሆኖ ከአቅሙ በላይ የሚሆን ከሆነና የሌሎችን አጋር አካላት እርዳታ በመጠየቅ ካለበትም እንደዚያ አጋሮቹን ከጎኑ በማሰለፍ ያጠቃል፤ ይከላከላል :: ወዳጅ ግን ፍጹም የተለየ ነው ::
በመተማመን ግንብ ላይ መሠረቱን የጣለ በመሆኑ በሁለት ወዳጆች መካከል ያለው ወዳጅነት የጠነከረ ነው:: ወዳጅ ሚስጥር አዋቂ፣ ገመና ሸፋኝ ፣ በሀዘንም በደስታ ጊዜ ከወዳጁ ጎን ቆሞ በማፅናናት ወዳጅነቱን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው::
ይህ የጠነከረ ወዳጅነት ደግሞ መተማመንን በመፍጠሩ ጥርጣሬ ተወግዶ ለሰላም፤ አብሮነትና አንድነት ለመሰለፍ ያስችላል:: በአብሮነት ውስጥ አንዱ ለአንዱ ከለላ በመሆን ያለስጋት በሰላም የመኖር ተስፋም የሚያጭር ነው ወዳጅነት ::
ታዲያ ወዳጅነት ክፋቱ ምን ላይ ሆኖ ነው ወዳጄን ጠብቅልኝ የሚባለው ማለታችን አይቀርም:: ወዳጅ ውስጣዊ ሚስጥር ገመናን አዋቂ በመሆኑ ወዳጅነት ወደ ጠላትነት ከተቀየረ በኋላ ምንም አይነት ማምለጫ አይኖርም:: በፍጥነት በደካማ ጎኑ በመግባት አስብቶ ለማረድ የሚመች መሆኑ ክፉ ያደርገዋል ::
የወዳጅን ጥቃት እጅግ ከባድና አንገብጋቢ የሚያደርገው አጋጣሚን ጠብቆ ልብ ሲመኘው የኖረውን ሁሉ በሚፈልገው መንገድ ማድረግ መቻሉ ነው::ወዳጅ ምንም አይነት ክፋት ያስባል ተብሎ ስለማይጠበቅ ከሱ የማይጠበቅ ያልታሰበ ጉዳት በመፈጸም ያልሆነው ሆኖ ሲገኝ ለመናገር ይከብዳል፤ ለሰሚው ግራ ይላል ::
እናም ወዳጆቼ እስኪ ልብ በሉ፤ ጆሮ ሰጥታችሁ አንዴ አድምጡኝ ! ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ መሆኗን በአደባባይ ስትናገር አልነበርም እንዴ ! እኔ ኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት የሚያጠናክር ዲፕሎማሲ እየገነባሁ ነው እያለች ታውጅ አልነበረም እንዴ :: አሁን ምን የሚያሳፍር ነገር ገጠማት ይሆን:: አይኗን በጨው እንዲታጥብ ያደረጋት ::
ታዲያ ለምን አፈረች! ምን ይሆን ሚሰጥሩ እንዲህ በአንዴ ወደ ወራሪ ጠላትነት የቀየራት :: በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አኩርፋ ነው እንዳይባል የሚዋዥቅ አቋሟ እንኳ ቢሆን እንደግብጽ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚያሰኝ የሚል ሳይሆን ለኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል እንደነበረ የሚታወስ ነው::
በሱዳን ተደራዳሪዎች በኩል ሲቀርቡ የነበሩት ምክንያቶች ግልጽ የሆኑ አልነበሩም፤ በሰበብ የተሞሉ ነበሩ :: ከዚህ ባሻገር ግን ግንኙነት በማጠናከር የሚያስችል ጥረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ የወዳጅነት ግንኙነት ያላቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ትስተዋላለች ::
ድንቄ ወዳጄ አሉ እማማ! ከሰሞኑ ይቺ ገራሚ ሀገር የበላችበትን ወጭት ሰባሪ መሆኗን እያሳየች እያስገረመችን ነው:: ‹‹ ጉድና ጅራት ወደኋላ ነው›› እንዲሉ ያ ሁሉ የአደባባይ የወዳጅ ነኝ ባይ ጩኸት መልኩን ቀይሮ ከች ማለቱ የሚደንቅ ነው :: በሦስትዮሹ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ እንኳን እንደግብጽ በመጮኽ ፋንታ ሰከን ብለን ማሰብ ይሻለናል ከኢትዮጵያ ጋር በመስማማት የጋራ ጥቅማችንን ለማስከበር ያስችለናል አሳብ እንዳላት እንጂ በመሆኑ ከግብጽ ተሽላ ታይታናለች ::
‹‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ አሉ ›› ለካ ይህ ሁሉ ማስመሰል አስብቶ ለማረድ መሆኑን ማን በነገረን አወይ ያለመጠርጠር ጊዜ ጠባቂዋ ሀገር ! ምቹ ጊዜና ሰዓት በመምረጥ የወዳጅነቷ ልክ በአደባባይ አስመስክራለች:: ትጠብቀው ታልመው የነበረውን የጎረቤቷ ጎደሎ ቀን ለመጥፎነት ለመጠቀም በማሰብ የመቶ ዓመታት ህልሟን እውን ለማድረግ በቅታለች::
ጎረቤቷ ወዳጄ ናት ብላ አምና የሰጠቻትን እምነት አፍርሳ በተከፈተላት በር ሰተት ብላ በመግባት ወታደሮቿን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በማስጠጋት የኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ከቦታቸው በማፈናቀል ከ20 እስከ 40 ኪሎ ሜትሮች ድረስ ዘልቃ ድንበር ጥሳ በመግባት ከተቆጣጠረች በኋላ የራሴን ድንበር እያካለልኩ ነው ማለቷ እጅግ ያስገርማል :: ይህንን ሰምተን ለትዝብት ነው ትርፉ ለማለት ብቻ ልናልፋት አንችልም::
ወዳጆቼ! ይቺ ሀገር ከፈጸመች የድንበር ዘለል ወረራ ባሻገር እጅግ የከፋው ደግሞ እያቀረበች የምትገኘው እዚህ ግባ የማይባል አጥጋቢ ያልሆነ ምክንያት እጅግ ገራሚ ያደርጋታል:: እኔ መሬት አልወረርኩም ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገ ስምምነት ነው ቦታው የያዝኩት ስትልም መደመጧ እጅጉኑ ቢያስገርመንም ለዚህ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሰጡት አጥጋቢ ምላሽ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል ::
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጥር 12 ቀን 2013 ዓ. ም በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ እንድትጠብቅም ሆነ መሬት እንድትይዝ የተደረሰ ስምምነት እንደሌለ የተናገሩበት ማስታወስ የግድ ይላል::
እንደ ቃለ አቀባዩ ገለጻ፤ መንግሥት ህግ ማስከበር በሚለው ወታደራዊ ዘመቻ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባቀናበት ወቅት ድንበር አካባቢ ሊከሰቱ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን በተመለከተ ከሱዳን ጋር መግባባት የተደረሰ መሆኑን አስታወሰዋል::
“ድንበር አካባቢ የሁለቱን አገሮች ደህንነት የሚጎዳ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በኛ አመራር ለሱዳን መንግሥት አደራ ተሰጥቷል” ያሉት ቃለ አቀባዩ አክለውም ሆኖም “ድንበሩን አልፈው አገራችን ግቡ መሬት ይዛችሁ ጠብቁልን የሚል አይነት ሊኖር የሚችል አይደለም፤ አልነበረም” ብለው መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ከሰሞኑ የሱዳን ምክር ቤት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ሱዳን ሠራዊቷን ወደ ድንበር ያስጠጋችው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ አህመድ ጥያቄና ፈቃድ ነው መባሉ መዘገቡ የሚታወስ ነው::
ለዚህ ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር)፣እንደተናገሩት “ቅዠት ነው” ካሉ በኋላም “አጥፊ ኃይሎች የናንተን ድንበር ተጠቅመው ወደኛ ድንበር እንዳይገቡ ማለት ኑና ገብታችሁ ጭራሽ ያልተከለለና መቶ ዓመት በዚሁ ሁኔታ ይሁን ተብሎ የቆየውን መሬት ድንበር የኛ ነው በሉ ማለትም አይደለም” ብለው ማለታቸው እንዲሁ የምናስታውሰው ጉዳይ ነው።
ወይ ወዳጅነት ! ይህንን ምን ማለት ይቻላል ወዳጅነት ገመና ሸፍኖ ክፉ ቀን በመተጋጋዝ ማለፍ እንጂ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆን አይደለም:: እንግዲህ ሱዳን አደራዋን ቅርጥፍ አድርጋ በላችው::
ለኛ ታዛቢዎቹ እንኳን! ‹‹በፈረስ የፈለጉት በእግር›› እንዲሉ ሆኖ ስታሰብና ስታልም የነበረው ተሳካላት እንጂ ድንገተኛ አለመሆኑ ድርጊቷ አስገንዝቦናል::የእስካሁንም መቆየቷ አጋጣሚ እየጠበቀች እንጂ እውነተኛ ወዳጅ እንዳልነበረች ፍንትው አድርጎ ያሳየን ሃቅን በመሆኑ ልናቆለጳጵሳት መረጥን፤ አይ ጀግኒት ሀገር:: እንዲህ አይነት አደራ ጠባቂ ሀገር የት ትገኛለች::
‹‹ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር ››እንዲሉ በድርጊቷ እሷ ሳታፍር በምትኩ ኢትዮጵያ አፍራለች፤ አደራዋን የተነጠቀች ሀገር ግን ማለቷ አልቀረም :: እንደራሷ ሌላን በማመኗ ያደረገችው ነው:: በኢትዮጵያዊያን ባህልና እምነት አደራ እኮ ከሁሉ በላይ ከባድ ነው:: የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ይባል የለ::
የአደራ ከባድነት ከልጅ ጋር ተያይዞ ይገለጻል:: ሱዳን ግን እያመናት ከዳተኛነቷን አሳይታን እንኳን አላረፈችም :: ቃለ አቀባዩ እንዳሉት አይነት “ቅዠት ” በመቃዠት አቋም የለሽ መሆኗን አረጋግጣለች:: የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ከመግባቷ በላይ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ታማኝነት ለማግኘት ቀን ከሌት እየተጋች ትገኛለች::
ወዳጆቼ ! ሀገሬ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን ሱዳን ድንበሬ ዘላ ገብታ ዓለም አቀፍ የድንበር ህግን ጥሳ ታጠቃኛለች ብላ አስባ አታውቅም ::ይልቁን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደሚያሳየው ሱዳን ከኢትዮጵያ እጅግ በርካታ በኢንቨስትመንት፤ በውጭ ንግድ ወዘተ በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ነው::
አቋም የለሽው ሁልጊዜ በሚዋዝቀው መንፈስ የምትመራ ወላዋዩ ሀገር ፤ ዘው ብላ ገብታ ያለ ከልካይ የሰው ድንበር መውረሯ ሳያንሳት የኢትዮጵያን ጩኸት ቀምታ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እያሰማች ነው::
ኢትዮጵያ ከፕሬዚዳንት አል በሽር መውረድ በኋላ ሱዳን ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዳትገባ ከፍተኛ ሚና እንደነበራት፤ በዳርፉር በነበረው ችግርም ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ወደ ሱዳን በመላክ ሰላሟን ለመጠበቅ ያደረገችው ተነሳሽነትና በሰሜንና በደቡብ ሱዳን መካከል በተፈጠረው ግጭት አቢዬ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት፣ ኢትዮጵያ ብቻዋን ሠራዊቷን ልካ መስራቷ ከሱዳን ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት የሚያሳይ ነው ::
ታዲያ ማነው አለች ሱዳን! ይህንን ሁሉ ወደ ጎን በመተው ዛሬ ላይ ወርቅ ላበደረ ጠጠር ማለቷ ለምን ይሆን:: የሌሎች ሀገራት እንደ ግብጽ ያሉ ሀገራት ግፊት ያለበትም መሆን የሚያሳዩ ማመላከቻዎች አሉ::
እናንተዬ! ምናልባት ኢትዮጵያውያን በውስጥ ችግራቸው ተዳክመዋል ብላ አስባ ከሆነ የተሳሳተች መሆኗን ለማሳየት ጊዜ መስጠቱ ጥሩ ነው:: ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም ለመኖር በምታደርገው ጥረት በዲፕሎማሲ ጥበብ ማሸነፍ አለባት ::
ሱዳን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብታ የያዘችውን መሬት በህግ የሚያስጠይቃት መሆኑን ማወቅ አለባት:: የድንበር ጉዳይ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: በ1972 የተደረሰውን ስምምነት እንድታከብር በመጠየቅ በአስቸኳይ ለቃ ወደ ነባራዊ ሁኔታዋ መመለስና እንድታከብር መጠየቅ የግድ ነው::
ይህ ሲባል ደግሞ መጠኑን ያጣ ትዕግስት መታገዝ ይገባል የሚል እምነት መኖር የለኝም:: እሷ በተራመደችበት መንገድ ተራምዶ ፤ የመዘዘችውን ዱላ መምዘዝ እንደማያቅተን ማሳየትና ማሳወቅ ይገባል:: አሳብ ሩቅ አላሚ ሱዳን የጎረቤቷ ፍርጣማ ክንድ ታውቀዋለችና አርፋ ብትቀመጥ ይሻላታል ::
ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን ለጠላት እጅ የማትሰጥ መሆኗ እየታወቀ የወደፊት ጉዞዋን ለማደናቀፍ ያሰበን አካል እጅ ከሀገሬ ላይ ያንሳ:: መልካሙን ሁሉ ለኢትዮጵያ፡፤
አዲስ ዘመን ጥር 20/2013