ለምለም መንግሥቱ
ኢትዮጵያ ዕምቅ በሆነ የተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር ናት:: ይሁን እንጂ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ሳቢያ የአካባቢና የደን ሀብቷ ለጉዳት እየተጋለጠ ይገኛል:: ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩና ሰፋፊ መሬት ለእርሻ መዋል፣ ለማገዶና ለግንባታ የሚውል የእንጨት ፍላጎት መጨመር ፣ የደን ቦታን ለግንባታ ማዋል በምክንያትነት ይጠቀሳል::
በተለያየ ጊዜ ደግሞ በደን ላይ ቃጠሎ መከሰት፣ለደን ሀብት መጥፋትና መመናመን ከመንስዔዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው :: ይህ ደግሞ አፈር ለምነቱን እንዲያጣ ፣ አፈር እንዲከላ፣መሬትም እንዲጎሳቆል፣እንዲሁም የብዝሐ ሕይወት እንዲመናመን፣የዝናብ ስርጭት መጠን መዛባት ፣ተደጋጋሚ የሆነ ጎርፍና ድርቅ እንዲፈጠር፣ የመሬት ሙቀት እንዲጨምር፣ በረሃማነት እንዲስፋፋ ፣ ዝርያዎች እንዲጠፉ ያደርጋል::ይህ ደግሞ የከፋ ድህነትን ያስከትላል::
ችግሮቹ ሰፊ ቢሆኑም መፍትሄም እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ::ከኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት የ2010ዓ.ም የውጤት ተኮር ዕቅድ ላይ ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው፤አካባቢን ከብክለት፣ደንን ከመመናመን ለመታደግና ዘላቂ በሆነ መንገድ መልሶ ለመተካት፣ለማልማት ፣ ለመንከባከብና ለመጠቀም የሚያስችል በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ የምርምር ሥራ ማካሄድ እንዲሁም በሀገሪቱ የሚካሄዱትን የልማት ሥራዎች፣ዘላቂ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ፣የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀምን የሚያረጋግጡ በማድረግ የታቀደውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ ግብን ማሳካት ያስፈልጋል::
ስለሆነም የአካባቢ፣የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የተራቆቱ ቦታዎች መልሰው እንዲያገግሙና የበረሃማነት መስፋፋትን ለመከላከል ከፍተኛ ድርሻ አለው::ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ሀብቷ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ በሚያረጋግጥ ሁኔታ የተቀናጀ እና ወጥ የሆነ በተጠቃሚዎች ፍላጎት ላይ ያተኮረ ምርምር በማካሄድ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ማስገባት፣ ማላመድ፣ ማፍላት፣ መረጃዎችን ማውጣትና ለባለድርሻ አካላት ማድረስ እንዲሁም በሰፊው የማስተዋወቅ ሥራዎች መሥራት ይጠበቃል::
የኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት በ2009ዓ.ም የሀገሪቱን የልማትና የትኩረት አቅጣጫዎች ያገናዘበ የምርምር ሥራዎች አከናውኗል::278 የምርምር ሙከራዎች ያካተተ 68 የምርምር ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ማድረጉን በወቅቱ የወጣው ሪፖርት ያመለክታል::በምርምር በተከናወነው ሥራም ስድስት ነጥብ 88 ቶን ጥራት ያለው የዛፍ ዘር ለተጠቃሚዎች ተሰራጭቷል:: የአካባቢ ጥበቃውና የአረንጓዴ ልማት ሥራው እንዲህ በምርምር ታግዞ ሲከናወን ቢቆይም አሁንም መጠናከር እንዳለበት በመሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያመለክታል::
የአረንጓዴ ልማቱ የሰብል ልማትና የተለያዩ ተክሎችም አስተዋጽኦ ጭምር እንደሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ:: የአካባቢ ሥነምህዳርን በመጠበቅ ሚና ካላቸው መካከል የቡና ተክል ይጠቀሳል::
የዘርፉ ተመራማሪዎችሚናውን አጉልተው ይናገራሉ:: ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬከተር ዶክተር ግርማ ኃይለሚካኤል ጋር እንደነገሩኝ የቡና ልማት ያለጥላ አይታሰብም::ጥላ ሆኖ የሚያገለግለው ደግሞ ዛፍ ነው::
ማዕከሉ በየዓመቱ ከ25 ሺህ እስከ 30ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የቡና ተክል ለቡና አብቃይ አርሶአደር ያሰራጫል:: በየዓመቱ በዚህ መልኩ የቡና ተክል ሲከናወን ለጥላ የሚሆን የተመረጠ የዛፍ ችግኝ ተከላ ጎን ለጎን ይከናወናል:: ለዚህም ነው የቡና ተክል የአየር ሚዛንን በመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው የሚባለው::
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በተለያየ መንገድ እየተከሰተ ባለው የአየርንብረት ለውጥ በቡና ተክል ላይም ተጽዕኖ በማድረስ ላይ ይገኛል::ተጽዕኖው ተክሉ ከነበረበት ወይንም ምቹ ከሆነበት ሥነምህዳር እየለቀቀ ይሄዳል የሚል ሥጋት እየፈጠረ ነው ::
የአየር ንብረት ለውጡ ባስከተለው ተጽዕኖም በቡና አብቃይነት የማይታወቁ እንደ ምዕራብና ደቡብ ሸዋ ፣ ወሊሶና ሌሎችም አካባቢዎች ሳይቀር የልማት ተሳትፎው እየጎለበተ መጥቷል:: ምንም እንኳን በተጽዕኖ ልማቱ ከነበረበት እየወጣ ቢሆንም በሌላ በኩል በመልካም
አጋጣሚ ይወዳል:: እየሆነ ያለው ነገር ግን የአየርንብረት ለውጡን አሳሳቢነት ያሳያል:: ሆኖም የምርምር ማዕከሉ ችግሩን በቸልታ አልተመለከተውም ።ቡና በአየርንብረት ተጽዕኖ ምክንያት ከነባር የልማት ሥፍራዎች ሙሉ ለሙሉ ለቅቆ እንዳይወጣ በምርምር በመታገዝ ለቡና ጥላ የሚውሉ የዛፍ ችግኞችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በመትከል ሰፊ ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል ::
በሌላ በኩልም በተጽዕኖ ምክንያት ቡና አልሚ አርሶ አደሮችና ለሌሎችም በዘርፉ የተሰማሩ ልማቱን በሌላ በመተካት የቡና ምርት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ መጠንቀቅ ይገባል:: አረንጓዴ ወርቅ እየተባለ የሚጠራውና የሀገሪቷ ትልቅ የገቢ ምንጭ ሀብት የሆነው የቡና ልማት ጠብቆ ለማስቀጠል የአረንጓዴ ልማት ሥራው ላይ ማዕከሉ ከሚያደርገው ጎን ለጎን ባለድርሻ አካላትም ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል::
እንደሀገር ባለፉት ሁለት ክረምቶች የአረንጓዴ ልማት አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር ተከናውኗል:: በአንዱ የክረምት ጊዜ (በ2011 ዓ.ም )አራት ቢሊየን፣በሁለተኛው ዙር ማለትም በ2012 ዓ.ም ደግሞ ከአምስት ቢሊየን በላይ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች በኅብረተሰብ ተሳትፎ መከናወኑ ይታወሳል::
እነዚህ ዛፎች ለመልከዓምድሩ ውጤታማነት ብቻም ሳይሆን ጎን ለጎንም ለህብረተሰቡ በምግብነት የሚያገለግሉ ጭምር ናቸው። እንደ ቡና ላሉት ደግሞ ጥላ በመሆን የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው። የዛፍ ጥላ ለቡና ተክሉ በጎ አስተዋጽኦ ቢያበረክትም በዚህ ሳይዘናጉ ተክሉን ማዕከል አድርጎ ለጥላ የሚውል የችግኝ ተከላ ማከናወን ይጠበቃል::
የጅማ የግብርና ምርምር ማዕከል ቅርንጫፎቹ በሚገኙበት በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ውስጥ ሀሩና ሙዲ፣በኢሊአባቦራ ፣ መቱ ፣ አጋሮ ጌራ እና በሌሎችም በእያንዳንዳቸው የንዑስ ማዕከላት በያዝነው በጀት ዓመት ከግማሽ ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ተዘጋጅቷል::
ችግኞቹን ወደ አልሚው የማሰራጨት ሥራ ሲከናወን ጎን ለጎን ለቡና ጥላ የሚሆን የዛፍ ችግኞች ተከላ እንዲከናወን ግንዛቤ በመፍጠር ጭምር ማዕከሉ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል::ቡና አልሚው የዛፍን ጥቅም የሚረዳ መሆኑ ቢታወቅም ተከታታይነት ያለው በሥልጠና ግንዛቤ መፍጠርና መደገፍ ያስፈልጋል::
ቡና አልሚው ለዛፍ የሚውለውን ችግኝ በክልል በየደረጃው በተዘረጉ መዋቅሮች የግብርናና የአካባቢ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ አማካኝነት የሚቀርብ ሲሆን፣ የግብርና ባለሙያዎችም እገዛ ያገኛሉ :: በቡና ለቀማና ጉንደላ ወይም በነቅሎ ተከላ የዕድሳት ወቅትም የቡና ልማት ምርታማነት ቀጣይነት እንዲኖረው ታሳቢ ያደረገ ሥራም ከማዕከሉ ተግባራት ተደርጓል ::
በነባር የቡና ዛፎች ጉንደላ ወቅት አስፈላጊው የኬሚካል አጠቃቀም ጥቅም ላይ ውሎ በጥንቃቄ ካልተከናወነ የቡና ተክሉን ሙሉ ለሙሉ ወይንም በከፊል የሚታጣበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል:: ይሄ ደግሞ የሀገሪቱ የቡና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሽቆለቁል ስለሚያደርግ ልማቱ የሚከናወነው እነዚህን ሁሉ ግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ እንደሆነ ዶክተር ግርማ ያስረዳሉ::
የማዕከሉ የምርምር ሥራ ገበያ ተኮር በሆኑ የቡና እና በተለያዩ የሰብል አይነቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ቢሆንም በሥሩ ባደራጀው የተፈጥሮ ሀብት የሥራ ሂደት ክፍል ተስማሚ የሆነ የአፈር ልማት እንዲሁም አፈር እንዳይከላ የጥናት እና የዕቀባ ሥራዎችን በማከናወን ለአካባቢ ሥነምህዳር መጠበቅ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል::
አዲስ ዘመን ጥር 20/2013