ራስወርቅ ሙሉጌታ
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱትና ዛሬም ድረስ ብልጭ ድርግም እያሉ ያሉት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በርካቶችን ለህልፈተ ህይወት በመዳረግ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎችን ለመፈናቀልና ለስደት ዳርገዋል። በተለይም በአንዳንድ ቦታዎች የተፈጸሙት እንኳን ለተመልካች ለነጋሪ የሚዘገንኑ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያን የሚወዱትን ሁሉ አንገት ያስደፋ ያሳዘነም ነበር።
እነዚህ በጥቂት ርኩስ ዓላማ ባነገቡ ቀስቃሾች ተጠንስሰው ነገሮችን ለማገናዘብ ጊዜ ባልነበራቸው ወጣቶች ሲፈጸሙ የነበሩ ኢሰብአዊ ድርጊቶች የበርካታ ቤተሰቦችን ህይወት አመሰቃቅለዋል ልጆችን ያላአሳዳጊ ሽማግሌዎችንና አሮጊቶችንም ያለጧሪና አለሁ ባይ አስቀርተዋል። በርካቶችንም ያለጥሪት በማስቀረት ለከፍተኛ ድህነት ተረጂነትና አንዳንዶችንም ለጎዳና ህይወት እየዳረጉም ይገኛሉ።
የዛሬዋ የቤተሰብ አምድ እንግዳችንም በሰው ልጅ የማይታሰቡ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳቶች የደረሱባት ቢሆንም ለራሷ በገባችው የአልሸነፍምና አልንበረከክም ባይነት ከመጨረሻው የህይወት ምእራፍ በመነሳት ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ የቻለች ናት።
ወይዘሪት አበባ ታፈሰ ትባላለች ትውልድና እድገቷ በጅማ ከተማ አካባቢ በምትገኝ ሊሙ ገነት በምትባል አንዲት ትንሽ የገጠር ከተማ ነው። አበባ የልጅነት ጊዜዋን እንደማንኛውም ህጻን እየተጫወተች ቦርቃ ያሳለፈች ቢሆንም ነፍስ እያወቀች ስትመጣ ግን በአካባቢዋ ይፈጠሩ የነበሩት ነገሮች ጤናዋንም ሰላሟንም እየተፈታተኗት መምጣት ይጀምራሉ።
ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው የነበረው ብሄርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ከጥላቻ የተነሳ በቂም የተጠነሰሰ ግጭት ነበር። አበባ ገና በልጅነት እድሜዋ በትምህርት ቤት በሰፈርና በአንዳንድ ተቋማት ታያቸው የነበሩ ጥላቻና ቂም አዘል ንግግሮችና ተግባራት አንድ ቀን ወደ ተግባር ከተገባባቸው እሷና እሷን መሰሎች ብዙ መስዋእትነት ሊከፍሉ እንደሚችሉ ትገምት ነበር።
እውነትም ግምቷ ትክክል ነበርና ነገሩ እየተካረረ ሄዶ በአንዲት ያልታሰበች ለአበባ የኀዘን ካባን ያከናነበች ቀን በ2002 ዓ.ም እንደፈራችው በሌሎች አካባቢዎች በተደጋጋሚ ሲከሰትና ብዙዎችን ለመከራ ሲዳርግ የነበረው ግጭት ወደ እነሱም ቤት ይገባል።
በእለቱ አበባና እናቷ አገር ሰላም ብለው በተቀመጡበት የአካባቢው ወጣቶች እየጨፈሩና እየጮሁ በሰፈሩ ካሉት ቤቶች የነአበባን ጨምሮ ማንነትን መሰረት አድርገው በተመረጡት ላይ የአካባቢው ጎረምሶች ገጀራና ዱላ ድንጋይና ስለት ይዘው እጅግ ዘግናኝ የሆነ እርምጃ መውሰድ ይጀምራሉ። በዛች ቀን በርካቶች ይህቺን ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብተው የሄዱ ሲሆን የአበባ እናት የከፋ ጉዳት ባይደርስባቸውም አበባን ግን የህይወቷን መስመር ያጨናገፈ አደጋ ያጋጥማታል።
በወቅቱ የአንድ ልጅ እናት የነበረችው አበባም ከአስር ቦታ በላይ በአካባቢው አጠራር (አርባ ገራፊ) በሚባለው የመጨረሻው ትልቁ ገጀራ እንዲሁም በስለት ከፍተኛ ጉዳት ያደርሱባታል። ከሁሉም በላይ ሁለቱም እግሮቿ ላይ ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ተካሂዶባት ስለነበር ከአጥንት መሰበር ባለፈም የጉልበቷ ሎሚ ለመፍሰስ ይበቃል።
ከዚህ በተጨማሪ ጭንቅላቷን ትከሻዋንና ጀርባዋን በገጀራ ከደበደቧት በኋላ ምን አልባትም አትተርፍም በማለት ራሷን ስታ በወደቀችበት ትተዋት ይሄዳሉ። ወጣቶቹ ርኩስ የጥፋት ተልእኳቸውን ፈጽመው አካባቢውን ትተው ከሄዱና ነገሩ ከበረደ በኋላ የአካባቢው ሰዎች እንደምንም አፋፍሰው አበባን አዛው አካባቢ በሚገኝ ሆስፒታል ይወስዷትና ተስፋ አስቆራጭ በነበረ ሁኔታ ህከምናዋን መከታተል ትጀምራለች።
የህክምናዋ ጉዞ ግን የደረሰባት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ እንዲህ ቀላል አልነበረም በመሆኑም በአካባቢው ያለው ሆስፒታል ከጊዜያዊ እርዳታ የዘለለ ምንም ሊያደርግላት ስለማይችል ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በከፍተኛ ስፔሻሊስት ሀኪሞች መታየት እንደሚኖርባት ይወሰናል።
ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ወደ አዲስ አበባ ለከፍተኛ ህክምና መንቀሳቀስ እንዳለባት ተወስኖ አምቡላንሰ ከተዘጋጀ በኋላ ግን ከአዲስ አባባ ህክምናና ትምህርት ለመስጠት የተላኩ የእሷን ጉዳይ ሊያዩ የሚችሉ ጀርመናውያንና ኢትዮጵያውያን የአጥንት ስፔሻሊስት ዶክተሮች በእለቱ ስለደረሱ የአዲስ አበባው ጉዞ ይሰረዝና እዛው ህክምናዋን እንድትከታተል ይደረጋል።
ይህ ሁላ ነገር ሲከናወን አበባ የደረሰባት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ራሷን ስታ ስለነበር የምታውቀውም የምታስታውሰውም ነገር አልነበራትም። በዚህ ሁኔታ አስፈላጊው ህክምና እየተደረገላት ለሁለት ወራት ያህል በሆስፒታል ከቆየች በኋላ ትረፊ ያላት ነፍስ ትሆንና በህይወት ከመዳኗም ባሻገር በዊልቸር መንቀሳቀስ የምትችልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ከሆስፒታሉ ወጥታ በውጭ ህክምናዋን መከታተል ትጀምራለች። ከዚህ በኋላ የነበሩት ጊዜያት ግን ለአበባ ትልቅ የፈተናም የመከራም ወቅቶች ነበሩ።
በአንድ ወገን ከዚህ በኋላ ጤናዪ ተመልሶ እንደልብ ተንቀሳቅሼ ራሴን ችዪ መኖር አልችልም የሚለው ስጋት የፈጠረባት ጭንቀት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ራሷን ችላ ትንቀሳቀስ ስላልነበር ቤተሰብና ጓደኛን ማሰልቸቱ ትልቅ ራስ ምታት ፈጥሮባት ቆይቷል።
ይህም ሆኖ የአካባቢው ሰው ከእናቷ ጎን በመሆን ጥሩ ድጋፍ፤ ክትትልና እንክብካቤ ያደርግላት ስለነበር ከወራት በኋላ ዊልቸሩን በመተው በክራንችና በድጋፍ ለመንቀሳቀስ ትበቃለች። ከዓመታት በኋላ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ጤናዋ ወደነበረበት ባይመለስም ራሷን ችላ መንቀሳቀስ ብሎም ቀለል ቀለል ያሉ ስራዎችን ለመስራትም ትበቃለች።
አበባ በትውልድ ቀዪዋ በወግ በማዕረግ በሰርግ ተድራ የሶስት ጉልቻን ጉዞ የጀመረች ቢሆንም በባህሪ አለመስማማት ከትዳር አጋሯ ጋር አብራ ለመቆየት አልቻለችም ነበር። አበባ ሊሙ ገነት እያለችም አስረኛ ክፍልን ካጠናቀቀች በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀት ብስኩት በመጥበስ ዳቦ በመጋገርና ሻይ በመሸጥ ህይወትን ለማሸነፍ ስትታር የቆየች ቢሆንም ይህ ችግር ሲከሰት ግነ ከጎኗ የሚቆም ባለመኖሩ የእሷንም የሁለት ልጆቿንም ህይወት ሃላፊነት ወስደው ያሳድጉም ይንከባከቡም የነበሩት እኗቷ ናቸው።
በዚህ መከራ ውስጥ የነበሩትና አንድ ቀን ችግሩ ሊደገም ይችላል የሚል ስጋት የነበራቸው የአበባ እናት እያንዳንዷን ቀን በሰቀቀን ከማሳለፍ ለምን ወደ ትውልድ ቀየዪ ተመልሼ «ያገሬ ጅብ አይበላኝም» ብለው በመወሰን ከፍተኛ ብር ሊያወጣላቸው የሚችለውን ቤታቸውን እዚህ ግባ በማይባል ርካሽ ብር ሸጠው ከዘመናት በፊት በልጅነታቸው ለቀውት ወደነበረው የትውልድ ስፍራቸው ወደሆነችው የደብረ ማርቆስ ከተማ ለማቅናት ይገደዳሉ።
ነገር ግን የአበባ እናት ማርቆስ ከደረሱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በማረፋቸው አበባ በእሳቸው ድጎማ አይዞሽ ባይነትና አበረታችነት ታሳድጋቸው የነበሩትን ሁለት ልጆቿን ይዛ ለመቀጠል ሌላ ፈተና ይጋረጥባታል። ደብረ ማርቆስ የእናቷ የልጅነት አገር ቢሆንም እሷ ረጅሙን እድሜዋን ያሳለፈችው ጅማ ሊሙ ገነት በመሆኑ የምታውቀው አይዞሽ የሚላትና የሚደግፋት የቅርብ ሰው በማጣቷ የቀን ጨለማ ወርሷት በየቤቱ እየተሽከረከረች ልጆቿን በየሰው ቤት እያስቀመጠች ተቀጥራ የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን በሽታዋን ከማስታመም በተጓዳኝ መስራቷን ትቀጥላለች።
ነገር ግን በአንድ ወገን በደረሰባት አደጋ ሁለቱም እግሯና ጀርባዋ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት የጉልበት ስራ የመስራቱ ነገር የማያዛልቅ እየሆነ ሲመጣ በሌላ በኩል ደግሞ እንደዛም ሆና የምታገኘው ገቢ እንኳን ቤት ኪራይ ሊከፍል ይቅርና የሁለቱን ልጆቿንና የእሷን ቀለብ የመሸፈኑም ነገር አጠራጣሪ እየሆነ ይመጣል።
ያ ደግሞ የሚያዛልቅ አልነበረም ከምታገኛት ገቢ ላይም የልጆች ጠባቂ መቅጠር ለአበባ ህልም ነበር፤ በመሆኑም ከልጆቿ ሳትርቅ የራሷን ስራ መስራት እንዳለባት ወስና መንቀሳቀስ ትጀምራለች።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ነበር የደረሰባትን መከራና ያለችበትን ሁኔታ በሙሉ ላለችበት ወረዳ አሳውቃ ስለነበር የከተማው አስተዳደር ሴቶችን በሚያደራጅበት ወቅት ያገኛትና ሰልጥናና ተደራጅታ እንድትሰራ ያለችበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባትና ቅድሚያ በመስጠት የእድሉ ተጠቃሚ እንድትሆን ያመቻችላታል።
የብድር አገልግሎትም ከወለድ ነጻ አስር ሺ ብር እንድታገኝ የተደረገ ሲሆን አበባ ከጎዳና ህይወት የታደገኝ የምትለውንና የምትሰራበትም የምታድርበትም የአንገት ማስገቢያ ቤት ለጊዜውም ቢሆን የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ እንዲኖራት ያደርጋል።
ለአምላክ ምስጋና ይግባው የምትለው አበባ ተመሳሳይ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ በልጅነት መንደሯ የነበሩ አሁን ላይ በልመና ህይወት ውስጥ መሆናቸውን በማስታወስ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ሴቶች ጉዳይ ያደረጉላትን ድጋፍ ከጭንቅ የታደገኝ ትልቅ ሲሳይ በማለት ትገልጸዋለች።
አበባም የተመቻቸላትን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአንድ ወገን በሽታዋን እያስታመመች በሌላ በኩል ስራዋን አጠናክራ መስራቱን ትቀጥላለች። መቼም ቢሆን ለችግር ተንበርክኬ እጄን ለልመና አልዘረጋም የምትለው አበባ ልጆቿን ለቁም ነገር ለማብቃት ያላትን አቅምና ወኔ ሁሉ አሰባስባ ሻይ ቡናና ሌሎች ራዎችን በመስራት ላይ የምትገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሁለት ልጆቿን ራሷን ችላ አብልታ አጠጥታና አልብሳ ትልቁን ልጇን ስምንተኛ ክፍል ትንሿን ደግሞ ስድስተኛ ከፍል እያስተማረች ትገኛለች። ከዚህም አልፋ ከተረፋት ሳይሆን ካላት ላይ እየቆጠበች እንደ ቴሌቪዥንና ፍሪጅ ያሉ የቤት እቃዎችንም ለማሟላት በቅታለች።
በዚህ የተስፋ መንገድ ላይ እያለች ደግሞ አበባ የዓለምም የሀገራችንም ትልቅ ፈተና የነበረው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እሷንም ሁለተኛ ፈተናና ስጋት ሆኖባት ነበር። ደህና ስራ ጀምራ ልጆቿን መሰብሰብና መንከባከብ እንዳቅሟም ጥሪት መቋጠር ንብረት ማፍራት በጀመረችበት ወቅት የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአበባን ስራ በቀጥታ ከጨዋታ ውጪ እንዲሆን አድርጎት ነበር።
ነገር ግን አለሁ ብሎ ያስቀመጣትና ህይወቷን የታደገላት የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር በዚህ ወቅትም ከጎኗ በመቆም የሚበላውንም፣ የጽዳት እቃውንም በማቅረብ ያንን ክፉ ቀን አሳልፎ ለዛሬ እንዳበቃት አበባ ትናገራለች። አበባ የጥሪቱ ነገር አልሟላ አላት እንጂ ዛሬም የበለጠ አስፋፍታ ሰርታ በተመረቀችበት የምግብ ዝግጅት ብዙ ውጤቶችን ለማምጣት የረጅም ጊዜ እቅድም ተስፋም ሰንቃ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።
የተደረገላት ድጋፍ ብቻ ሳይሆን የእሷም ብርታትና ጽናት ከጠንካራው ችግር አላቆ ለዛሬ ቀን አብቅቷታል የሚሉት የደብረ ማርቆስ ከተማ ቀበሌ ዜሮ አንድ የጥቃቅንና አነስተኛ አንድ ማእከል አገልግሎት አስተባባሪ የነበረውን ነገር በሙሉ እንዲህ ያስታውሱታል። ለአበባ የተደረገው ድጋፍ ሙሉ ቤተሰቡን ከረሀብና ከጎዳና ህይወት የመታደግ ነበር።
ካለምንም ገቢ ሁለት ልጆቿን ይዛ እናቷን ቀብራ ለተቀመጠች የጤና ችግር ላለባት ልጅ ህይወት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን ማንም የሚረዳው ሀቅ ነው። በመሆኑም መጀመሪያ የተሰራው ስራ ማረፊያ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበር።
እንዲህ አይነት ስራዎችን ከዚህ ቀደምም ስንሰራ የነበረ ቢሆንም የእነ አበባ ጉዳይ ግን የተለየ ነበር፤ በመሆኑም በሁሉም ነገር ቅድሚያ እንዲያገኙ ለማድረግ ተገደናል። በዚህ መልኩ በተሰራው ስራም አበባንም ሆነ ሁለቱን ልጆቿን ከጎዳና ህይወትና ሌሎች ችግሮች በመታደግ ለዛሬ ቀን እንዲበቁ ማድረግ ተችሏል።
አበባ ህመሟ ስለሚይዛት እንጂ ስራ የማትንቅና ለጉልበቷ የማትሳሳ በመሆኗ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ከቀጠለ የበለጠ ለውጥ እንደምታስመዘግብ ግልጽ ነው። እነዚህ ሁላ ድጋፎች ውጤታማ እንዲሆኑ ደግሞ የከተማዋ ሴቶችና ህጻናት ቢሮም ሙሉ ትብብር ያደርግ ነበር።
የአካባቢው ሰውም ከተጋገረ እንጀራ ጀምሮ የሚለበስና ሌሎች ቁሳቁሶችንም በመስጠት ጥሩ ትብብር ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይ በኮሮና ወቅት እንደ አበባ ላሉ ድጋፍ ፈላጊዎች የአካባቢው ተወላጅ ሆነው ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩትም ብዙ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።
ተመሳሳይ ችግር የነበረባቸው አስር የሚደርሱ ዜጎችም የማቋቋሚያ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን ሴተኛ አዳሪዎችን ጨምሮ በርካቶች በተቻለ አቅም እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል ያሉት ቡድን መሪው እንደ አበባ ያሉት ጠንካራ ሴቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም እየተረፉ መሆኑን በመጠቆም የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ እንደዚህ ውጤታማ የሚሆኑ ሴቶችን በመደገፍ የቤተሰብ መፍረስና የልጆች መበተን እንዳይገጥም በርካታ ስራዎችን የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013