በአገራችን “ምሁራኖቻችን የሚጠበቅባቸውን ያህል ለአገራቸው እያበረከቱ አይደለም”፣ “ሳይማር ያስተማራቸውን ህዝብ በማገልገል ፋንታ ምንም ወዳላደረገላቸው ባእድ አገር በመኮብለል እውቀታቸውን እዛ ያፈሳሉ” ወዘተ ሲባል መስማት እንግዳ አይደለም።
“ምሁሩ በሆዱ ተሰንጓል”፣ “ምሁራዊ አድር ባይነት ተንሰራፍቷል”፣ የምሁርነት መለኪያው ፖለቲካዊ ማንነት ሆኗል”፣ “ምሁር ድሮ ቀረ . . .”፣ “ፊደላዊያን እንጂ ምሁራን የሉም” እና የመሳሰሉት ወቃሽ አገላለፆች የእለት ተእለት አፍ/ብእር ሟሟሻ ከሆኑ ቆዩ።
በተለይ ድህረ 1983 የተደረገውን የመንግስት ልውውጥ ተከትሎ በነፃ ፕሬሱ አማካኝነት ከሚሸነቆጡት የህብረተሰብ ክፍሎች አንዱ ምሁሩ (በኢህአዴግ ሰነድ “ጥገኛው” የሚባለው) እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው።
በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ስራዎችን ለንባብ ያበቁት ዶክተር አለማየሁ ረዳ በስፋትና ጥልቀት እንደፈተሹትና እንደደረሱበት ማጠቃለያ የምንረዳው ከላይ ከጠቀስናቸው አስተያየቶች የተለየ አይደለም። ዶክተሩ እንደሚሉት ምሁሩ የሚጠበቅበትን እየሰራ፤ የማህበራዊ አንቂነት ሚናውን ሁሉ እየተወጣ አይደለም። ያለው ሁኔታ “የሰጎን ፖለቲካ” አይነት ነው።
የዚህ ጽሑፍ መነሻ ሀሳብ የመነጨው ሰሞኑን በ”የኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ካውንስል ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ጥር 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም” ከመካሄዱ ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ አላማው “የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ካውንስሉን ሲመሰርት ዋና ዓላማው ኢትዮጵያውያን ባለሙሉ ፕሮፌሰር ምሁራን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመቀናጀት የሳይንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ግቦችን ለማሳካትና በአገር ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ ለመፍጠር” ሆኖ መስፈሩም እንደዛው። እዚህ ላይ አንድ ሀሳብ እናንሳ፤ “ሳይማር ያስተማረንን ህዝብ” የሚለውን።
በመሰረቱ “ሳይማር ያስተማረን” የሚለው ዝም ብሎ ከመሬት የተነሳ ሀሳብ አይደለም፤ እውነትና እውነቱም ከሚታይና ተጨባጭ ከሆነ ተግባር የተገኘ ነው። ይሁን እንጂ አባባሉ በአንድ ወቅት ያልተማሩት ያስተማሯቸውን ይሉኝታ ለማስያዝ፤ አገራዊ፣ ዜግነታዊ፣ ምሁራዊ ሀላፊነታቸውን በቅንነትና ታማኝነት እንዲወጡ ለመገፋፋት፣ ለማበረታታትና ወደ ውጪ የሚደረግን ኩብለላ ሁሉ ለማስቀረት ሲባል አገልግሎት ላይ በመዋል ከፍተኛ ጠቀሜታን አስገኝቷል። ይህ ግን ዛሬ፤ አሁንም ይሰራል ማለት አይደለም።
ዛሬ ላይ ምሁሩ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ሆነ እንዳይወጣ ያደረጉት ጉዳዮች በርካታ ሲሆኑ አንዱም ግን ከ”ሳይማር ያስተማረን” ጋር የሚገናኝ አይደለም። በአብዛኛው ፖለቲካዊ፣ ዝቅ ሲልም ኢኮኖሚያዊ ነው።
ችግሮቹ “ፖለቲካዊ፣ ዝቅ ሲልም ኢኮኖሚያዊ” ናቸው ካልን “ሳይማር ያስተማረን”ን እንደ መፍትሄም ሆነ እንደ ችግር ማንሳት ጉንጭ ከማልፋትና ምናልባትም መፍትሄውን ከመደበቅ ያለፈ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም። ወደ ጉባኤው እንመለስ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ድረ-ገፅ እንዳሰፈረው ከሆነ ጉባኤው “ካውንስሉ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ግቦች ስኬት ከፕሮፌሰሮች ካውንስል በሚጠበቁ ድጋፎች ላይ ይመክራል።
በመድረኩ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአካዳሚክ፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሳይንስ ባህል ግንባታና ማህበረሰብ ተሳትፎ፣ በአስተዳደርና አመራር ጉዳዮች፣ በዓለማቀፋዊነትና ሀብት ማፈላለግ ላይ የሚያስፈልጉ የተለዩ ድጋፎች የሚቀርቡ ሲሆን የካውንስሉ አባላትም ሃሳባቸውን ይሰጡባቸዋል።
ይህም የኢትዮጵያውያን ምሁራን እውቀትና ልምድ በመጠቀም የተሻሻሉ የአሰራር ሂደቶች ለመፍጠርና ውጤት ለማስመዝገብ” ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረው ሲሆን ለአገርና ህዝብም እስከዛሬ አጥተውት የኖሩትን ከምሁራን የሚገኙ ትሩፋቶችን መቋደስ እንዲችሉ እድሉን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ የ”ፕሮፌሰሮች ካውንስል” ለዚህ ጽሑፋችን መነሻ ሆኖ እንጂ እሱ እራሱ ርእሰ ጉዳያችን ባለመሆኑ በሌላ ጽሑፋችን እንደምንመለስበት ጠቅሰን ወደ አጠቃላዩ እንሸጋገር።
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሁሌም ሲያከራክሩ የሚታዩ ፅንሰ ሀሳቦች አለ። “ምሁር”፣ “የተማረ”፣ “ሊቅ”፣ “ሊቃውንት” . . . የሚሉት። “አለ/የለም” የሚለውም እንደዛው። ከዚሁ ከ”አለ/የለም” ጋር ተያይዞ ደግሞ “ፊደላዊያን ናቸው ያሉት እንጂ . . .” የሚል እሰጥ እገባ ደሞ መጣ። እያለ እያለ ጣት መቀሳሰሩ እዚህ ደርሷል።
እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር እውነት ነው። እሱም ዩኒቨርሲቲዎች “ሁለት ብቻ” ነበሩ በተባለበት በዚያ ወቅት፤ ዶክተርና ፕሮፌሰር ብርቅ በሆነበት በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ለአገርና ለወገን የሚጠቅሙ፣ ዛሬም ድረስ አብዝተው የሚጠቀሱና “ድንቅ” የሚባሉ ስራዎች እንዳልነበሩ ሁሉ፤ ዛሬ የመንግስት ብቻ ከ50 (በላይ) ዩኒቨርሲቲዎች (ሌሎች ተቋማትን ሳንጨምር) እና ከቁጥር በላይ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች፣ ዝቅ ያሉትን ትተን) ባሉበት በዚህ ዘመናዊ ዘመን ለአገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ስራዎች የሉም። ይህ ማንም የማይከራከርበት የወቅቱ የአገራችን ተጨባጭ እውነት ነው።
በተለይ ቀደም ባሉት ስርዓታት፣ በተለይም በንጉሥ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግስት እሳቸው እራሳቸው አደራ ብለው ከመላካቸው ጋርም ተያይዞ፣ ለትምህርት ወደ ውጪ አገር የተላከ ሰው ሄዶ ተምሮ በመምጣት አገሩ ላይ አንድ ነገር ሰርቶ ለውጥ ለማምጣት የነበረው ችኮላ ነው። ይህ ችኮላም ከተመረቁ በኋላ እንኳን የተወሰኑ ቀናትን ጠብቆ ዲግሪን ለመውሰድ ድረስ እንኳ ጊዜ የማይሰጥና “በፖስታ ቤት በኩል ይላክልኝ” በማለት የፖ.ሳ.ቁ. ሰጥቶ በፍጥነት ወደ አገር ቤት መመለስ ነበር።
ሄዶ መቅረትማ? እንዴት ሆኖ? (የንጉሱ ስርአት እስከ ወደቀበት ዘመን ድረስ አንድም ኢትዮጵያዊ በውጭ አገር ጥገኝነት ጠይቆ አያውቅም። ይህም ሊሆን ይችላል በርካታ በውጪ አገር የሚደረጉ ጥናቶች ኢትዮጵያዊያንን “ኢትዮጵያ-አሜሪካዊ” (Ethiopian Americans) እንጂ በ”ዲያስፖራ” ምድብ ስር ሲያካትቱ የማይታዩት፤ ከሌሎች አፍሪካዊ ወንድም እህቶች ነጣይነቱ አኳያ ጥሩ ባይሆንም።) ይህን እውነት የሚነግሩን የነበሩ ሲሆን እየነገሩን ያሉም የአይን ምስክሮችና እራሳቸው የዛ አካል የነበሩም አሁንም አሉና አያከራክርም።
በመሰረቱ በብዙ አገራት ማህበራዊ “አንቂነት” (activism እና ተግባሪው “activist”) የምሁራን ተግባርና ሀላፊነት ነው። ማንም፣ የራበና የጠማው፣ ኪሱ የሳሳበት፣ የስልጣን ጥም እርር ድብን ያደረገው ወሸነኔ ሁሉ ጦሩን ሰብቆ፣ ቢላውን ስሎ የሚገባበት ማህበራዊ ሀላፊነት አይደለም። ለዚህ ደግሞ የሶቅራጥስን ህይወትና ስራዎች ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማስታወስ ይገባል።
“አንቂነት” ወይም አክቲቪዝም ማለት ሳይከበቡ “ተከብቤአለሁ” ማለት አይደለም። “አንቂነት” ተከብቦም ቢሆን እውነቱን ማስተማር፣ መብትና ግዴታን ማሳወቅ፣ ጭቆናንና ጨቋኝን ማጋለጥና ማውገዝ፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ይገነባ ዘንድ ሳይታክቱ ማሳወቅ ማለት ነው። በዚህ ተግባራቸው ዓለም የሚያውቃቸውም ሆኑ በቅርብ የተፈጠሩት ለዚህ የበቁት በዚሁ ሰብአዊ ተግባር እንጂ በሌላ አይደለምና ነው።
ጋንዲ፣ ማንዴላ፣ ሉተር ወዘተ ሁሉ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ላይ ሲሰሩ (እየደረሱባቸው በነበሩ አደጋዎች ሁሉ ውስጥ ሆነው) የነበሩት እነዚሁ መሰረታዊ ሰብአዊ ጉዳዮች ላይ በመሆኑ እነሆ አስተምህሯቸው ዛሬም ድረስ ዓለምን እያገለገላት ይገኛል፤ ሰሚ ባይኖርም ቅሉ።
ወደ ፈላስፋዎቹም ስንሄድ የምናገኘው ያውና ተመሳሳይ ሆኖ በይዘትና ቅርፁ ግን ልቆ ነው የምናገኘው። (ወደ እንደዚህ አይነቱ ጽሑፍ ስንመጣ ዓለምን በሁለት ጎራ ከፍሎ ማየት የተገባ አሰራር ሲሆን ጎራዎቹም ብሉይ (ጥንታዊ)ና ዘመናዊው ዓለም ናቸው፤ እዚህም ከዚሁ አኳያ ማየት ያስፈልጋል።)
በተለይ ከ18ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ በዓለማችን ከፍተኛ የሽግግር ወቅት እንደ ነበር ተመዝግቦ ይገኛል። ይህም ሽግግር ከነባሩ የሰው ልጅ አኗኗር ወደተሻለውና ዘመናዊው ለመምጣት የተደረገ ሲሆን ይህም በሳይንሳዊ አስተሳሰብ፣ በኢንዱስትሪ እድገትና የመሳሰሉት ዘርፎች ከፍተኛ እመርታ የታየበት ወቅት ነበር።
ይህ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ የተደረጉ ፍልስፍናዎች ወደ መድረክ ወጥተው እጅግ አወዛጋቢ፣ አነታራኪና አከራካሪ የሆኑበት ጊዜ ሲሆን ከእነሱ በኋላም ለተፈጠሩ ፈላስፎችና ፍልስፍናዎቻቸው መሰረት ለመሆን የበቃ ነው።
ከ18ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ያለው ወቅት በተለይ እነ እንግሊዝን የመሳሰሉ አገራት በከፍተኛ ደረጃ በኢንዱስትሪ አብዮት የተስፈነጠሩበት ወቅት ሲሆን ለዚህም ከእነ ማርክስና መሰሎቹ ፍልስፍናዎች ጀምሮ ለመስፈንጠራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገውላቸዋል።
ለሰዎች እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትህ ማግኘት ከማንም በፊት ሀሳብ ያፈለቁት ምሁራን ሲሆኑ በተለይም የሰዎችን የመናገር ነፃነት መከበርን በተመለከተ በቀዳሚነት ሃሳብ ያመነጩት በአብርሆት ዘመንና ከዛ በኋላ የመጡ የፖለቲካ ፍልስፍና አቀንቃኞች ናቸው። ይህም ለዲሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት መጣል የራሱን አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን ለሊብራል ዲሞክራሲ መፈጠርም የእነዚሁ ወገኖች ፍልስፍና በእርሾነት አገልግሏል። የዘመነ-አብረኸት ልሂቃኑ አስተሳሰብ ቶማስ ጀፈርሰን አስተሳሰብ ለወግ ያበቃው የነፃነት አዋጁ፤ የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም መሰረቱ ካርል ማርክስም እዚህ ሊጠቀሱ የግድ ነው።
ዓለማችን በየአቅጣጫው ለማህበረሰብ ይጠቅማል፤ ከነበረበት የጉስቁልና ህይወትና አኗኗር ያላቅቀዋል፤ እንደ አንድ መሸጋገሪያ ድልድይ ይሆነዋል ወዘተ በማለት አዳዲስ ሀሳቦችን ያፈልቁ የነበሩ ፈላስፎች በየአቅጣጫው ነበሯት። ከዚህ አኳያ በተለይ 18ኛው ክ/ዘ ተጠቃሽ ነው።
አሜሪካዊው ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ ሩሲያዊው ሎሞኖሶብ፣ እንግሊዛዊው ኒውተን፣ ፈረንሳዊው ዴካርቴ እና መሰሎቻቸው ከየአገሮቻቸው ባለፈ ለዓለም የኢኮኖሚ አስተሳሰብና እድገት ያበረከቱት አስተዋፅኦ እንዲሁ ዝም ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። የዛሬዎቹ የበለፀጉ የሚባሉት አገራት የተሃድሶ (Reformation) ወይም (እና) የሽግግር (Transition) ዘመን መሰረቶች በመሆናቸውም እነሆ ዛሬም ድረስ “ህያው” ናቸው።
በደምሴ ሀይሌ እና ግርማ ተረፈ በተዘጋጀው “የአሁኑ ዘመን የኢኮኖሚ አስተሳሰብ መነሻዎች” ድንቅ መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው ዊሊያም ፔቲ፣ ፍረንሷ ኬኒ እና የመሳሰሉት ሊቃውንት ለስነ ኢኮኖሚ ሂደቶች አሀዛዊ ትንተና መሰረት የጣሉ ሲሆኑ ስራዎቻችውም ዘመን ተሻጋሪ በመሆን ዛሬም ድረስ ትኩስ እንደሆኑ አሉ። ሁሉንም እምነቶች በእኩል ዓይን የሚያየው (pluralist) ቤንጃሚን ፍራንክሊንም በባለውለታነቱ ሁሌም ሳይነሳ ውሎና አድሮ አያውቅም፤ ከአሜሪካ መስራች አባቶችም አንዱ ነው።
ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ “ሰዎች የማይገሰስ ተፈጥሯዊ ሰብአዊ መብት አላቸው”፣”መንግስት መቋቋም ያለበት የዜጐችን መብት ለመጠበቅ ነው”፤ “የመንግስት የስልጣን ምንጭ የዜጐች ነፃ ፍቃድ ነው፡፡”፣ “ኢ-ፍትሐዊ መንግስትን የማስወገድ መብት አላቸው” እና ሌሎች በርካታ አንኳር አንኳር የሰው ልጅ የማይገሰሱ መብቶች የልሂቃኑ አዕምሮና ፍልስፍናዎቻቸው ውጤቶች ናቸው።
ይህ ሁሉ የሚያስረዳን በአንድ አገር የተረጋጋ ሁለንተናዊ እድገትና ብልፅግና፣ የአገራት ዘመን ተሻጋሪ ተምሳሌትነት (ለምሳሌ የአሜሪካ ሕገ-መንግስት) ሊኖር የሚችለው በዛች አገር ጉዳይ ላይ የምሁራን ያልተገደበ ተሳትፎ ሲኖር ነውና “የኢትዮጵያ ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች ካውንስል”ንም ከዚሁ አንፃር ማየቱ ተገቢ ነው ለማለት ነው።
ለግማሹ ሴይጣን ለግማሹ መልአክ የሆነውና ዓለምን በሁለት (ካፒታሊዝም እና ሶሻሊዝም) ጎራ የሰነጠቀው ማርክስና ፍልስፍናው፤ እስከ አሁን ድረስ ለተፈጥሮ ሳይንስ (በተለይም ለፊዚክስ) የጥናት መስክ የደም ስር የሆነውን፤ የኒውክለር ቀመር ቀማሪውና ለአገሩ ብልፅግና ተኪ የሌለው አስተዋፅኦን ያበረከተው አልበርት አንስታየን (“ከትላንት እንማራለን፣ ዛሬን እንኖራለን፣ ስለነገም ተስፋ እናደርጋለን” በሚል ቋሚ አመለካከቱም ይታወቃል።)፤ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎቻቸው የሚታወቁት በሥነ-ጽሑፍ እና በፖለቲካ ፍልስፍና እድገት፣ እንዲሁም በአሜሪካ አብዮተኞች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ጆን ሎክ (1632-1704) በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም ዋና ትኩረቱን መንግስትና ህግ ላይ ማድረጉ በተለይ የሚታወቅለት እንግሊዛዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ (1588-1699) እና በ17ኛ ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ18ኛው ክፍለ ዘመን ከልማድ ወይም ከባሕል ይልቅ በሕሊና ወይም በማስተዋል ብቃት (reason) ላይ ትኩረት የሚያደርገውን «ኢንላይትመንት» የተሰኘ የአውሮፓ ምሁራን ንቅናቄን ከሚያቀነቅኑት ፈላስፎች አንዱ የሆነው ዢን-ዣክ ሩሶ (1712-1778) እና እጅግ ብዙዎቹ ለዛሬዋ ውብ (አነሰም በዛ) ዓለም መሰረቶች ናቸው።
እያወራንለት ያለው ካውንስል አባላት ባንዴ እንዲህ እንዲሆኑ ሳይሆን አገራችን ካለችበት ምስቅልቅል ህይወት ውስጥ እንድትወጣ፣ የአገሪቱ ፕሬዝዳንትና የካውንስሉ የበላይ ጠባቂ ሣህለወርቅ ዘውዴ ከላይ በጠቀስነው ጉባኤ መክፈቻ ላይ እንዳሉት “የኢትዮጵያ ሙሉ ፕሮፌሰሮች ዕውቀታቸውንና እምቅ አቅማቸውን ለሀገር ልማት በማዋል ረገድ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ” ይገባል፤ ቢያንስ ለመጪው ትውልድም መደላድሉን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
ይህ “ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካውንስሉን ሲመሰርት ዋና ዓላማው ኢትዮጵያውያን ባለሙሉ ፕሮፌሰር ምሁራን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመቀናጀት የሳይንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ግቦችን ለማሳካትና በአገር ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ ለመፍጠር” መሆኑ በሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተነግሯል።
ፕሮፌሰር አፈወርቅ እንደተናገሩት “ምሁራኖቻችን ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ግቦች” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው እና “በአካዳሚክ፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሳይንስ ባህል ግንባታና ማህበረሰብ ተሳትፎ፣ በአስተዳደርና አመራር ጉዳዮች፣ በዓለማቀፋዊነትና ሀብት ማፈላለግ ላይ የሚያስፈልጉ የተለዩ ድጋፎች” እና የመሳሰሉት ግዙፍ ሀሳቦች ተነስተው ጥልቅ ውይይት የተካሄደበት ጉባኤ ነበር።
ምንም እንኳን እስከዛሬ ያልነበረን (በቀይና ነጭ ሽብር የጨነገፈ) መሆኑ ቢቆጭም ከአሁን በኋላ አገራችን እስካሁን ስናወራላቸው እንደመጣነው አገራት ሁሉ በምሁራኖቿ ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጤና፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች እየሰሩ ያሉ 236 ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች ያሏት መሆኑ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።)
“በሃገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያው ትኩረት በተደረገባቸው ማዕድን፣ ግብርና፣ ቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” የተባሉት እነዚሁ ምሁራን “ለሃገራቸው ልማት የዕውቀት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ” ታስቦ ካውንስሉ መቋቋሙንም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ማስታወቁም ከላይኛው አንቀፅ ሀሳባችን ጋር ተያያዥ ነው። ወደ ማጠቃለያው እንሂድ። ከመሄዳችን በፊት ግን በዚሁ ጉዳይ ላይ ላባቸውን ጥንፍፍ አድርገው የሰሩትን እጓለ ዮሀንስ (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ)፣ መስፍን ወልደማርያም (አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ)፣ አለማየሁ ረዳ (የሰጎን ፖለቲካ) እና ሌሎችንም መመልከትና ማስታወስ ተገቢ ነው።
ሲጠቃለል፤ ኢትዮጵያ በብዙ ወሳኝ ጉዳዮች ቀዳሚ ነች። ከዚህ ጽሑፍ አንፃር ብንመረምር እንኳን በዘርዓያዕቆብ አማካኝነት ለዓለማችን ዘመናዊ ፍልስፍና (ሞደርን ፊሎሶፊ) መሰረት የጣለች (ክላውድ ሰመር እንዳጠኑት) ነች።
ይሁን እንጂ አሁን ያለንበት ደረጃም ይሁን ይዞታችን እንዳነሳሳችን አይደለም። ወደ ኋላ ተንሸራትቶ . . .። ከዚህ ከተንሸራተትንበት ለማውጣትና ለመውጣት ነው እንግዲህ የአሁኑ ወቅት ግብ ግብ። ለፕሮፌሰሮቻችን መልካሙን ሁሉ እንመኝላቸዋለን!!!
አዲስ ዘመን ጥር 18/2013