አስቴር ኤልያስ
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ብቁና አስተማማኝ ለማድረግ የህንጻ ዲዛይንና የግንባታ ጥራትን ማስጠበቅ የግድ ይላል። በተለይም ዘርፉ የሚያሻው የህግ ማዕቀፍ በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ የሚባክን ጊዜንም ሆነ ገንዘብን ሊታደግ ይችላል። በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደረግ ጥንቃቄ ደግሞ ከጊዜም ሆነ ከገንዘብም ሌላ የህዝብን ጤንነትና ደህንነት እንዲጠበቅ የማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለውም እሙን ነው።
በዚህ ረገድ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት አማካሪዎችና አርክቴክቶች እንደመሆናቸው በጉዳዩ ዙሪያ ምን መደረግ አለበት ስንል ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ከነበሩትና የኢትዮጵያ አማካሪ አርክቴክቶችና መሃንዲሶች ማህበር የቦርድ አባል ሆነው ከሰሩት፤ የአዲስ መብራቱ አማካሪ አርክቴክቶችና መሃንዲሶች ድርጅት ባለቤት እንዲሁም ሙያ ነክ ስልጠናዎችንና የሐሳብ ልውውጥ መድረኮችን የሚያዘጋጅ የቀበና ሃውስ ዳይሬክተር ከሆኑት ከዋና አርክቴክት አዲስ መብራቱ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧልና መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራበት ያለው የባለሙያዎች ምዝገባ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነው ማለት ይቻላል?
አርክቴክት አዲስ፡- የባለሙያ ጉዳይ ሲነሳ በዲዛይንና በኮንሰልታንሲ እንዲሁም በኮንስትራሽን ዘርፍ ውስጥ ሁሌ የሚታሰበኝ ነገር ቢኖር የባለሙያን ብቃት ወይም ጥራት ላይ ያላተኮረ ኢንዱስትሪ በአሸዋ ላይ ቤቱን እንደሰራ ሰው ይመሰልብኛል። ይህ ሲሆን ደግሞ የጥራት ጉድለት ያጋጥማል እንደማለት ነው፤ በእኛ አገር በተወሰነ ደረጃ የማስተውለውም ይህን አይነት አካሄድ ነው። ስለዚህ በእኔ አስተያየት በእኛ አገር የባለሙያ ምዝገባ ወይም ደግሞ የባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጥ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ፈጽሞ የተከተለ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ምን መደረግ አለበት ይላሉ? እንዴትስ ነው መስተካከል የሚገባው?
አርክቴክት አዲስ፡– የባለሙያ ምዝገባን የተመለከተ የዓለም አቀፍ ልምድ የሚያሳየን በተለያየ አገር እንደየአገሩ ሁኔታ ልዩነት ቢኖረውም በጥቅሉ ግን አንድ መለየት ያለበት የተለዩ ሙያዎች ለምሳሌ የአርክቴክቸርና የስነ ህንጻ ባለሙያ የተለየ አይነት የምዝገባ ስርዓት ሊከተል እንደሚገባው ይታወቃል። የሰው ልጆች ደህንነት ላይ ተጽዕኖ ያደርጋሉ ከሚባሉት ማለትም የባለሙያው የግሉ ውሳኔ የሰው ልጆችን ደህንነት ይነካሉ የሚባሉ አምስት ያህል ዘርፎች አሉ።
ከእነዛ ውስጥ አንዱ የአርክቴክት ሙያ ሲሆን፣ የእነዚህ ዘርፎች ከሌላው ሙያ ምዝገባ የተለየ ነው። እከሌ ይህ ሙያ አለው ተብሎ ተመዝግቦ መቀመጥ ሳይሆን ብቃቱ፣ ክህሎቱና እውቀቱ መመዘን አለበት። ይህ ሊደረግ የሚችልበት አሰራር እየተከናወነ ነው። በኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር የፖሊሲ ረቂቅ ጸድቆ ለመንግስት ቀርቧል።
ይህም ረቂቅ የሚጠቅሰው አንድ የስነ ህንጻ ወይም የከተማ ዲዛይን የሚሰማራ በዘርፉ የተመረቀ ባለሙያ እንደተመረቀ ፍቃድ መስጠት ሳይሆን ቢያንስ ሁለት ዓመት በተመዘገበ ወይም ፈቃድ ባለው ባለሙያ ስር ሆኖ ልምድ ማግኘት አለበት። ሁለት ዓመት ከሰራ በኋላ ፈተና የሚዘጋጅለት ሲሆን፣ ሙያውን ሊመዝኑ የሚችሉ ፈተናዎች ናቸው የሚዘጋጁለት። ማህበሩ እነዚህን ዝርዝር ጉዳዮችን በማካተት ነው ለመንግስት ያቀረበው። ስለዚህም በዚህ መንገድ የባለሙያዎች ምዝገባ ቢደረግ የተሻለ ውጤት እናገኛለን ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ካልሆነ መንግስት ትኩረት ሊያደርግ የተገባው ነገር ይኖር ይሆን?
አርክቴክት አዲስ፡- በቅርቡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ስር የተቋቋመ አንድ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አለ፤ ይህ ባለስልጣን ይህንን አይነት ስራ መስራት አለበት። እንዲህም ሲባል በቀጥታ ለባለሙያዎች ምዝገባ የሚያስፈልገውን ቅደም ተከተል ከሙያ ማህበራቱ ግብዓቶቹን ወስዶና አስፈላጊውን ዶክመንት አዘጋጅቶ ወደስራ መግባት ማለት ነው። የባለሙያዎችን ምዝገባ በተመለከተ መመሪያዎችን አዘጋጅቶ ተግባሩን መጀመር ነው ያለበት።
እስካሁን ያለው ችግር ምንድን ነው ቢባል የሙያ ማህበራት ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነቱን ሐሳብ ለመንግስት አካላት ሲያቀርቡ ከርመዋል። ይህ ስልጣን የተሰጠው ደግሞ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ነው። ተቆጣጣሪው ባለስልጣንም በእሱ ስር ነው።
የሌላው አገር ተሞክሮ የሚያሳየው በዚህ ዘርፍ ውጤታማ መሆኑን ነው። እነዚህ አገሮች ከባለሙያ ምዝገባ ጋር ተያይዞ መመሪያው ምን መሆን አለበት የሚለውን የሚያወጡት የሙያ ማህበራት ናቸው። ነገር ግን የመንግስት አካል ምዝገባ ነው የሚያካሄደው። አሁን እያደረገ ያለው ግን መመሪያውንም ለማውጣት ስለሚሞክር በቂ የሆነ መመሪያ ማውጣት ስላልቻለ ነው።
በእርግጥ አሁን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የሚባለው ተቋም ኮንሰልታንት ቀጥሮ ይህን ያልኩሽን ዶክመንት እያዘጋጀ ነው። ስለሆነም የምዝገባ ስርዓቱ ምን መምሰል አለበት የሚለውን በዝርዝር እያዘጋጀው ነው። በዛ ዝግጅት ላይ የአርክቴክቶች ማህበር፣ የኮንሰልቲንግ አርክቴክቶችና መህንዲሶች ማህበር፣ የኤሌክትሪካል መህንዲሶችና የሜካኒካል መሃንዲሶች ማህበርና ሌሎችም መሰል ማህበራት አሉ። እኔም በዚሁ ውስጥ ያለሁ ሲሆን፣ አንድ ዶክመንት እየተዘጋጀ እንደሆነ መረጃው አለኝ።
ይህ ዶክመንት ተጠናቆ በእነዚህ የሙያ ማህበራት ተገምግሞ ትክክል ነው ተብሎ ከተረጋገጠ ቀጥታ ወደስራ ነው መገባት ያለበት። የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጥናት ያጠናል እንጂ ተግባሪ አይደለም። ይህን ተግባራዊ የማድረግ ስልጣን ያለው የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ነው። ዶክመንቱ ተጠንቶ ሲያልቅ ወደስራ መለወጥ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡- ዶክመንቱ በተያዘለት ፍጥነት እየተጓዘ ነው ማለት ይቻላል? አሁን ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለጻል?
አርክቴክት አዲስ፡- በጣም ዘገምተኛ ነው፤ ትልቁ እድገት የሚባለው የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከብዙ ዓመት የሙያ ማህበሮች ውትወታ በኋላ ይህ ሐሳብ ተጠናቅሮ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በተለያየ መልክ ዶክመንቱ ሲቀርብ ነበር፤ ነገር ግን ማንም ሰው አንስቶ አልተከታተለውም።
አሁን ግን ቢያንስ በጀት በጅቶ ጥናት ለማስጠናት መነሳቱ ተስፋ ሰጪ እድገት ነው። የሚያሰጋው ግን ተጠንቶ የጥናቱ ውጤት ሼልፍ ላይ እንዳይቀመጥ የሚል ነው። ስለዚህ ይህ እንዳይሆን በቶሎ ወደትግበራ መግባት የግድ ይላል። የሌሎች አጋራት ልምድ የሚያሳየው ይህን ኃላፊነት የሚወስዱት የሙያ ማህበራቱ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ጥናቱ ተግባራዊ ቢሆን ፋይዳው ምን ያህል ነው?
አርክቴክት አዲስ፡– ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልሽ የዲዛይን፣ ኮንሰልታንሲና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንዲኖረን ያደርጋል፤ እሱ ከሌለ ቤትን አሸዋ ላይ እንደመገንባት ይቆጠራል። ምክንያቱም ብቃቱ ያልተረጋገጠ ባለሙያ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየሰራ ጥራትን ማምጣት በጭራሽ አይታሰብም።
አዲስ ዘመን፡- ልምድ ያለው ባለሙያ ከጀማሪው የሚለየው በምን አግባብ ነው?
አርክቴክት አዲስ፡- ጀማሪው የተመረቀበት ወረቀት ይኖረዋል፤ ግን እሱ ወረቀት የባለሙያውን ብቃት ይገመግማል የሚል እምነት የለኝም። ከተለያዩ ተቋማት ልምድ ሊያጽፍ ይችላል፤ ምናልባትም የሚጻፈው ልምድ በእርግጥም ትክክል ላይሆን ይችላል፤ ስለዚህም በተጻፈለት ልምድ ብቻ ተነስተን ባለሙያው ብቁ ነው ልንለው አንችልም። የሚገመገምበት የራሱ የሆነ መስፈርት ሊኖር ይገባል። በእርግጥ እዚህ አገር ላይ የፕሮጀክቶችም ታሪክ አይመዘገብም፤…
አዲስ ዘመን፡- እንዴት?
አርክቴክት አዲስ፡– ለምሳሌ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ፕሮጀክቶችን ጠበቅ አድርጎ ይዟል። እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ድረስ የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም መገምገም ተጀምሯል። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ካለ በብቃት የተሰሩ ፕሮጀክቶች ይታወቃሉ፤ ችግር ያለባቸውም ይለያሉ። ችግር ያለባቸው የየትኛው ባለሙያ ችግር ነው የሚለውም ተለይቶ ሊታወቅ ይችላል። ነገር ግን ምንም መረጃ በሌለበት ሁኔታ ልምዳችንን በወረቀት ብቻ አጽፎ መያዝ ብቃትን ለመገምገም አስተማማኝ ነው ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ከባለሙያው አመዘጋገብና ብቃት ሌላ የአንድ አርክቴክት የአገልግሎት ክፍያስ የሚከናወንበት መንገድ እንዴት ይገለጻል?
አርክቴክት አዲስ፡- ይኸኛው ደግሞ የዘርፉ ሁለተኛው ራስ ምታት ነው፤ የመጀመሪያው የዘርፉ ዋና መሰረት የባለሙያ አመዘጋገብ ነው ካልን ይህ የአገልግሎት ክፍያ ደግሞ ምሰሶ ነው ማለት እንችላለን። አንድ ብቃት ያለውን ባለሙያ ከያዝን በኋላ የባለሙያው የክፍያ ስርዓትስ እንዴት ነው የሚለው በኛ አገር በአሁኑ ሰዓት ህጋዊ የሆነ ሰነድ የለም። ይህ በመሆኑ ምክንያት የተለያዩ ግዥዎች በሚፈጸሙበት ጊዜ የተለያዩ ተወዳዳሪዎች የተለያየ ዋጋ ይሰጣሉ። አንዳንዱ ስራው ከሚጠይቀው ዋጋ በታች ስለሚያስገባ ስራውን ለመወጣት እንቅፋት ይሆንበታል። የሚያስፈልገውንና ጥራት ያለው ባለሙያ ለመመደብ አያስችለውም።
ይህ የመነጨው ከምንድን ነው ቢባል እንደሚታወቀው ባለፈው አስር ዓመት ውስጥ ዋና አልሚ የነበረው በንጽጽር ሲታይ መንግስት ነው።
መንግስት ደግሞ ሲከተል የነበረው ስርዓት ቅናሽ የሰጠውን ባለሙያ ነው። ወይም በጣም ጥሩ ከተባለ ደግሞ ቴክኒካልና ፋይናንሻል (ኳሊቲ ኤንድ ኮስት) አድርጎ ነው የሚሄድበት የነበረው። ስለዚህም ተቋሞች ወይም ባለሙያዎች ስራ ለማግኘት በሚል ሲወዳደሩ መንግስትም ያስቀመጠው መመሪያ ስሌለለ በአንድ ብርም እሰራለሁ የሚል ባለሙያ ከመጣ መንግስት ተቀብሎ ይፈራረማል። ይህ ማለት የአስር ብር እቃ በአንድ ብር እሸጥልሃለሁ ብሎ ሲመጣ እንደመቀበል ማለት ነው። ይህ ትልቅ ችግር ነው።
እዚህ ላይ ትኩረት እንዲደረግበት የምፈልገው ነገር ቢኖር አሁንም በኢትዮጵያ አማካሪ መሃንዲሶችና አርክቴክቶች ማህበር እና በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ትብብር ገንዘቡን ኢንስቲትዩቱ ከፍሎ ፕሮጀክቱን ግን በኢትዮጵያ አማካሪ መሃንዲሶችና አርክቴክቶች ማህበር የተጀመረ እና እኔም በቦርዱ ውስጥ ያለሁበት ስራ አሁን ላይ 95 በመቶ የተጠናቀቀ የባለሙያዎች ክፍያ ጥናት ተዘጋጅቷል። ይህ ጥናት ለጊዜው የተዘጋጀው ለህንጻና ለመንገድ ፕሮጀክቶች ተብሎ ዓለም አቀፍ ልምዱንም በመቃኘት የተዘጋጀ ዝርዝር ጥናት ነው። ለማጽደቅም ቀርቦ ነበር።
ይህ ጥናት የተሰራው በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የፋይናንስ ምንጭ ነው። ስለዚህም የመንግስት አካል ተሳትፎበታል ማለት ነው። አሁንም ችግር ነው ብዬ ደጋግሜ የምናገረው ኢንስቲትዩቱ ተግባሪ አለመሆኑን ነው። አስጠንቶ የሚሰጠው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ለተቆጣጣሪ ባለስልጣኑ ነው።
እንደዚህ አይነት ጥናቶች የዛሬ አስርና አስራ አምስት ዓመት ገደማ ተጠንተው ያውቃሉ። ነገር ግን የሚወስን አካል ጠፍቶ ሼልፍ (መጽሐፍ መደርደሪያ) ላይ ቀርተው ነው። ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለመራመድ መዘጋጀትና ወደትግበራው መግባት አለብን የሚለውን የሚወስን የመንግስት አካል ነው የጠፋው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ለመወሰን የተቸገረበት ምክንያት ምንድን ነው? ወይስ አስገዳጅ ችግር ኖሮበት ነው?
አርክቴክት አዲስ፡- እኔ የሚመስለኝ ለምሳሌ ክፍያን የመደራደር ስልጣን ለመንግስት ሰራተኞች መስጠት አይፈልግም። ለምሳሌ የሚከተላቸው ፖሊሲዎች አነስተኛውን ክፍያ ከሆነ ዝቅተኛ የሰጠውን መሸለም ነው ማለት ነው። ነገር ግን መሆን ያለበት ለምሳሌ ለአንድ ፕሮጀክት አንዱ አንድ ቢሊዮን ብር ሌላው ደግሞ ሃምሳ ሺህ ብር ቢጠይቅ ሃምሳ ሺውን አይሆንም ብሎ መመለስ አለበት።
አይሆንም ለማለት እዛ ቦታ ያለው ባለሙያ ነው የሚወስነው። ግን ያ ሲሆን አይታይም፤ በቦታው ያሉ የመንግስት አካልም ውሳኔ ለመወሰን ፍራት አለበት። በዝቅተኛ ዋጋ መዋዋሉ መንግስትን እንደሚጠቅመው ከማሰቡም በላይ ትልቁን ዋጋ መዋዋል ስጋት ስለሚሆንበት ከነገሩ ጾም ይደሩ አይነት ስራ ሲሰራ ይስተዋላል።
ምክንያቱም ዝቅተኛ ዋጋው ፕሮጀክቱን የማይመጥነውና ጥራቱም እንዳይጠበቅ የሚያደርገው ነው። ቀደም ሲል የጠቀስኩልሽ የኢንስቲትዩቱ እና የባለስልጣኑ ጥናት የሚያሳየው ይህንን ነው። ዋጋ በመስበር አንድ ሰው ስራ ማግኘት እንደማይችል የሚያሳይ ነው። በመንግስት በኩል ስጋት እንዳለ ቢታወቅም እኛ እንደ ባለሙያ ግን ጥራት ያለው ስራ እንዲሰራ ምኞታችን በመሆኑ አንፈራም።
ከደከመና ከሞተ ኢንዱስትሪ ወደተሻለ እንደሚሄድም ስለምንረዳ ነው። አሁን ይህ ነገር የመጨረሻው ደረጀ ላይ ነው ያለው። መንግስት ለዲዛይን ጭማሪ ገንዘብ ቢያወጣ በመቶ ቢሊዮንና ትሪሊዮን በሚቆጠር ፕሮጀክቶች ላይ ጥራትን ለማስጠበቅ ዋስትና የሚሰጥ ነገር ነው። ምክንያቱም በዲዛይን የተሰራው ነገር ነው መሬት ላይ የሚወርደው።
ደግሞም መታሰብ ያለበት ስለአንድ ህንጻ መገንባት ብቻ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፤ ህንጻዎች ተደምረው ነው ከተማ የሚሆኑትና ለጥራቱ መጠበቅ ለዲዛይን የሚሰጠው ክፍያ የእነቶሎ ቶሎ ቤት አይነት አሰራር እንዳይሆን ትኩረት ቢሰጠው የተሻለ ነው የሚሆነው።
አሁን ግን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልሽ ሁለት ሰነዶች ተጠንተው ተዘጋጅተዋል፤ ይህን ሰነድ ግን በመከታተል አንድ ውሳኔ ላይ መደረስ አለበት። የ100 ሺህ ብርን እቃ በአንድ መቶ ብር እየገዛን ነው በማለት እንደጉብዝና ተቆጥሮ መደነቅ አይገባም። የመቶ ሺህ ብር እቃ በመቶ ሺህ ብር ነው መገዛት ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- የሰነዶቹ መጽደቅ ከጥራት በተጨማሪ ፋይዳቸው ምንድን ነው?
አርክቴክት አዲስ፡– በፕሮጀክቶች አካባቢ መንግስት ከሚያጋጥሙት ችግሮች አንዱ የስራ መዘግየት ነው። የገንዘቡን ነገር ተይውና መንግስት በገነባቸው ፕሮጀክቶች ሊሰጥ የነበረውን አገልግሎት በሰዓት ሊሰጥ አይችልም። በዚህ ውስጥ ምን ያህል ኪሳራ እንዳለ ግልጽ ነው።
ሌላው የዋጋው ጉዳይ ነው፤ ፕሮጀክቱ በአንድ ሚሊዮን ብር ያልቃል ተብሎ ውለታ ይገባና ስራ ይጀመራል። ከቆይታ በኋላ ፕሮጀክቱ ሁለት ቢሊዮን ብር ይሆናል። መንግስት የበጀተው አንድ ቢሊዮን ከነበረ እንደገና በጀት ፍለጋ ታች ላይ ይባላል። ስለዚህ በእቅድ መመራት አይቻልም ማለት ነው። ግን ለትክክለኛ ባለሙያ ትክክለኛ ክፍያና ጊዜ ከተሰጠው ስራው በአግባቡ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡- የግዥ ስርዓቶች የሚካሄዱት በዘርፉ ያሉትን ህጎች በጣሰ መልክ ነው ይባላልና የትኛውን አይነት የግዥ ስርዓት መከተል አዋጭ ነው ይላሉ?
አርክቴክት አዲስ፡– በኛ አገር ፌዴራል ፐብሊክ ፕሮኩዩርመንት ኤንድ ፕሮፐርቲ ኤጀንሲ (የፌዴራል መንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ) የሚባለው ጠንካራ የሆነ መንግስታዊ ድርጅት ነው። የትኛውንም አይነት የግዥ ፖሊሲዎችን እያወጣ ስራ ላይ የሚያውል ነው ማለት ነው። እንደተቋም ብዙ ስራዎችን ሰርቷል። ነገር ግን እንደ ኮንሰልታንሲና በተለይ እንደ አርክቴክቸራል ዲዛይን የሙያ አገልግሎት ግዥን በተመለከተ ቁርጥ ያለ ፕሮኩዩርመንት (የአገልግሎት ግዥ) ሰነድ የለውም።
ለምሳሌ እኔ አርክቴክት ነኝ፤ የአርክቴክቸራል አገልግሎት ግዥ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ተሞክሮው የሚያሳየው የአርክቴክቸራል አገልግሎት ግዥ ጥራት ላይ የተመሰረተ መሆን ያለበት የሚል ነው። እኛ አገር ግን ዝቅተኛውን ገንዘብ የሰጠ ሰው ነው ማለት ነው። ስለዚህም ኤጀንሲው ወረድ ብሎ የእያንዳንዱን ባለሙያ ክፍያ በዝርዝር ማየት አለበት።
ስለዚህ ማድረግ ያለብን የግዥ ኤጀንሲው ለምሳሌ የአርክቴክትን ሙያ በተመለከተ ፕሮክሪዩመንት ኦፍ አርክቴክቸራል ሰርቪስ የሚል ቴለርድ የሆነ ነገር ማስቀመጥ ነው፤ ምንም ያንን ሊጠቀምበት ይችላል ማለት ነው። ጥቅል ነገሩን ከሚወስድ ከዋናው ላይ ወስዶ ማስተካከል ነው፤ ይህን ሲያደርግ ጥራት ላይ መሰረት ማድረግን ማስገደድ አለበት። እንዲህም ሲባል የባለሙያው፣ አማካሪውና የዲዛይነሩ መረጣ መቶ በመቶ በሚያስብል ደረጃ በጥራት ላይ መሆን አለበት ነው።
ለምሳሌ የአንድ ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ቢሰራ፤ ትልቅ ተቋም ነኝ፤ ብዙ ባለሙያዎችን መድቤ እሰራለሁ ቢል ያ ባለሙያ ጥራት ላይ የተመሰረተ ስራ ለመስራት የፕሮጀክቱን አስር በመቶ ይጠይቃል ብንል መቶ ሚሊዮን ብር ይሆናል ማለት ነው። እኛ አገር ግን የዲዛይን ክፍያ እንደተጨማሪ ወጪ ነው የሚታየው። ይህን ችግር ግን የጠቀስኩት ሰነድ ወደትግበራ ከገባ ይፈታዋል የሚል እምነት አለኝ።
ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፕሮኩዩርመንት ህግ የአርክቴክቸራል ዲዛይን ውድድር በውስጡ አይጠቅስም፤ አስራ አምስት ያህል የዲዛይን ውድድር የሚል በዶክመንታችሁ ውስጥ አካቱ ሲል የፌዴራል ፕሮክሪዩመን ኤጀንሲ ጠይቋል። ለምን ቢባል ውለታ ከተካሄደ በኋላ ችግር እየተፈጠረ ስለሆነ ነው።
እንደሚታወቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአጼ ኃይለስላሴ ጀምሮ የዲዛይን ውድድር ተካሂዷል። በቅርቡ ብሄራዊ ትአትር ቤት አካባቢ የተገነቡት የፋይናንስ ተቋማት ሁሉ የተገነቡት በዲዛይን ውድድር ነው። ነገር ግን ወደ ውለታ ሲመጣ ችግር ይገጥማል። የፌዴራል ፕሮኪዩርመንት ኤጀንሲ እነዚህን ነገሮች ከዓለም አቀፍ ህግ ጋር ሊያካትት ይገባል፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ቀላል የሆነው መንገድ ስለእያንዳንዱ ሙያ ሲፈልግ የየሙያው ማህበራቱ ስላሉ እነሱን ጠይቆ የፕሮኪዩርመንት (የአገልግሎት ግዥ) ህግ ምን አይነት ቢሆን ነው በማለት ግብዓት ወስዶና ከአገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አገናዝቦ ወደህግ ለውጦ ቢያመጣው አንዴ ህግ ሆኖ ስለሚወጣ ሁሉም ይከተለዋል። ስለዚህም ለዲዛይንና ለኮንሰለታንሲ በዚህ መልኩ ትኩረት የሚሰጠው ከሆነ ዲዛይን ላይ ያለቀን ንድፍ መገንባት ቀላል ይሆናል።
አማካሪዎችና አርክቴክቶች የሚነፈጉት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጊዜንም ጭምር ነው። ለምሳሌ መንግስት አንድ ፕሮጀክት ለመገንባት ሲያስብ ለዲዛይን ጊዜ ያስፈልገዋል ብሎ አያስብም። ወደፕሮጀክቱ ለመግባት ሶስት ወር ያህል ሲቀረው ዲዛይኑን በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ አምጡ ይላል። በሌላው ዓለም ያለው ልምድ ብዙ ፕሮጀክቶች ሲታዩ አንድ ዓመት ተኩል ያህል ዲዛይን ይሰራና ግንባታው ከዛ በኋላ አንድ ዓመት አሊያም አንድ ዓመት ከመንፈቅ ያህል ጊዜ ነው የሚፈጀው። ይህ ማለት ምንም እንኳ ከፕሮጀክት ፕሮጀክት ቢለያይም ለዲዛይን የሚሰጠው ጊዜና ለግንባታ የሚሰጠው ጊዜ ተቀራራቢ ነው ማለት ነው።
በኛ አገር ዲዛይኑ በሶስት ወር ይሰራ ይባላል፤ ከዛ በሶስት ዓመት እንዲጠናቀቅ የታቀደው ፕሮጀክት ስድስት ዓመት ይፈጅበታል። ለዚህ ፕሮጀክት መጓተት ምክንያት የሚሆነው ለዲዛይን የተሰጠው ጊዜ ውስን ስለሆነ ነው። ስለዚህ ዲዛይንና ኮንሰልተንሲ ላይ ይበልጥ ትኩረት ቢደረግ ኮንስትራክሽን ላይ ያሉ ብዙ ችግሮች ይፈታሉ።
አዲስ ዘመን፡- የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለሙስና የሚያጋለጥበት ዋናው ነገር ምንድን ነው ይላሉ? መፍትሄውስ?
አርክቴክት አዲስ፡– የሙስና አሰራር የሚጀምረው ቀደም ሲል ከጠቀስኩልሽ ጉዳይ ነው። ይኸውም የባለሙያ አመዘጋገብ፣ የአገልግሎት ክፍያና የባለሙያው አገልግሎት ግዥንም የሚመለከት ነው። በነገራችን ላይ ሙስና የሚባለው ችግር ስለመኖሩ የሚያሳይ ምልክት ነው። ለምሳሌ ጠንከር ያለ በሽታ ሆኖ ምልክቱ ራስ ምታት ሊሆን ይችላል፤ ሙስናም ትክክለኛው በሽታ ሳይሆን የዋናው ችግር ምልክት ነው። እኔ የማየው በዚህ ረገድ ነው።
የባለሙያ አመዘጋገብ ላይ ያለን ድክመት እንዲሁም የባለሙያ ክፍያ ላይም ግልጽ የሆኑ መመሪያዎች አለመኖር እና የባለሙያው አገልግሎት ግዥ ላይም ጥራትን መሰረት ያደረገና ጥራትን መሰረት ያደረገ ዋስትና ያለመኖር ችግሮች ተደማምረው ሙስና እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ እገምታለሁ። በእርግጥ የሙስናው ችግር አንዱ ከአንዱ ይለያያል።
ለምሳሌ ሁለት የባለሙያ ድርጅቶች አማካሪዎች ናቸው ብንል፤ ጨረታ ይወጣል፤ አንደኛው ለስራው የሚያስፈልገውን ባለሙያ አቅርቦ ክፍያው ይህን ያህል ነው ብሎ ይገልጻል። አንደኛው ደግሞ ስራውን የማይመጥን ዝቅተኛ ክፍያ ያቀርባል። ዝቅተኛ በመሆኑ ክፍያው ያሸንፍና ስራውን ይጀምራል፤ ግን ማጠናቀቅ አይቻለውም። የሚፈጠረውን የገንዘብ ክፍተት ለመሸፈን መንገድ ይፈልጋል። እዚህ ላይ እንግዲህ ሁለት አይነት ሙስና ይመጣል።
አንደኛው ውለታ ከተገባለት የተገባለት ስራ ሳይቀርብ ክፍያው የሚሸፈን ይሆናል። ገንዘቡ ስራውን ለመጨረስ ስለማይበቃ ከኮንትራክተሮች ጋርና ከሌሎች ጋር መርህ አልባ ግንኙነት መፍጠር ይመጣል። በዚህም አካሄድ አንዱ ችግር ወደሚቀጥለው ችግር እያመራ ነው የሚሄደው ማለት ነው።
ሌሎቹም በጥራትና በተሻለ ሁኔታ የሚሰሩትም ወደዚህ አይነት እንዲሄዱ ከማድረጉም በላይ ልምድ ሁሉ ይሆንና እንደባህል መቆጠር ይጀምራል። መንግስት ራሱ በሚዋዋልበት ክፍያ ስራው መጠናቀቅ እንደማይችል እያወቀ ነው ውጤት የሚጠብቀው። ይህ ደግሞ ብርቱካን ተክሎ ሙዝ እንደመጠበቅ የሚቆጠር ነው። ስለዚህ ገንዘቡ የሚፈለገውን አይነት ባለሙያ መቅጠር ስለማያስችል ጥራቱ ይጓደላል፤ ለሙስናም ይጋለጣል።
መፍትሄውም ቢሆን አንድ ቤት ሲሰራ ዋናው መሰረቱ ነው። ቤቱን በአሸዋ ላይ ሳይሆን በዓለት ላይ ለመመስረት ባለሙያው ላይ ማተኮር ፋይዳው ትልቅ ነው። የባለሙያ አመዘጋገብ ስርዓታችን ብቃትን በአግባቡ የሚመዝን መሆን አለበት። አሁንም ደግሜ እንደመፍትሄ የምጠቅሰው የግዥ ስርዓቱንና አከፋፈሉን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መመሪያ በአገር ደረጃ ሊኖረን ይገባል።
ይህን አስመልክቶ የተጠኑ ጥናቶች ወደተግባር እንዲገቡ ጫና መፍጠር ያሻል። እነዚህ ከተስተካከሉ ሙስና ምልክት እንጂ ቀጣይ በሽታ ሆኖ አይቀመጥም። የሌላ በሽታ ምልክት የሆነው ራስ ምታት በፓራሲታሞል ለማከም ብትሞክሪ ሊጠፋ አይችልም፤ ሙስና እንዲሁ ነው።
ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን መንግስት ሊያይ ይገባቸዋል። እነዚህም እንዳልኩሽ የባለሙያው ምዝገባ፣ የባለሙያው የአገልግሎት ክፍያና የግዥ ስርዓቱ ወጥነት ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሶስቱ ላይ በትኩረት ከተሰራ ሙስና ሙሉ ለሙሉ ይጠፋል ባይባልም በእጅጉ ይቀንሳል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አርክቴክት አዲስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2013