ኃይለማርያም ወንድሙ
የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ላይ ያየናቸው በ19 60 አዲስ ዘመን ያስነበባቸውን የችሎትና ሌሎች ወጣ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል።
ሐሰተኞቹ ዳኞች ተቀጡ
አርባ ምንጭ (ኢ.ዜ.አ)፤ በጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት በገሙ አውራጃ በምዕራብ ዓባያ ወረዳ በሸንገሌ ቀበሌ የዳኝነት ሥልጣን ሳይኖራቸው ዳኝነት እየተሰየሙ ሕዝቡን ሲያጭበረብሩ የተገኙት አራት ሰዎች ምዕራብ ዓባያ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሰው ቀርበው አድራጎታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው በ፮ ወር እሥራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል።እነዚህም ሐሰተኞች መኩሪያ ካሱ፣ አቦይ ሐይካ፣ቶሃ ቶምባርና በፈሌ ቀልሐ የተባሉ መሆናቸውን የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ መኰንን አበበ ገልጠዋል።
ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ
በሐያ ሳንቲም ጭማሪ አምሳ ብር ተቀጡ
አቶ በቀለ ገብሬ ተወድዷል እያሉ በኒያላ ሲጋራ መደበኛ ዋጋ ላይ ሐያ ሳንቲም እየጨመሩ ለሕዝብ በመሸጣቸው በጉዳዩ ተከስሰው በትናንትናው ዕለት ስድስተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ፶ ብር መቀጫ ሲወሰንባቸው ፤ለኤግዚቢት የቀረበው ሸቀጥ ደግሞ ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ ክፍል በሰጠው መግለጫ ስድሳ ሳንቲም ይሸጥ የነበረውን ኒያላ ሲጋራ ሰማንያ ሳንቲም ሲሸጡ የተገኙት አቶ በቀለ የዋጋ ተቆጣጣሪዎች ሲጠይቋቸው ስሜ “ንዳ ነሪ” ነው ብለው ነበር። የንግድ ፈቃዳቸውንም ለማሳየት አስቸግረው እንደነበር ምስክሮቹ ለፍርድ ቤቱ ባሰሙት ቃል ገልጠዋል።በመጨረሻም የንግድ ፈቃዳቸው ቁጥር ፲፩ሺ፯፻፲፰ ሲታይ ስማቸው እንደተባለው ሳይሆን በቀለ ገብሬ መሆኑ ተረጋግጧል።ይህንንም ተከሳሹ አምነዋል።
ሦስቱ ምስክሮች ሰፊ ማስረጃ ቃላቸውን ሲያሰሙ ” አቶ በቀለ ይህንን ሲጃራ በሰማንያ ሳንቲም ሲሸጡልን ለዋጋው ከፍ ማለት የሰጡን ምክንያት ተወድዷል የሚል ነበር። ግን በፓኬቱ ላይ የተጻፈው ዋጋ አልተለወጠም ።
እንዲያውም ለእናንተ ብዬ ነው እንጂ ዋጋው አንድ ብር ገብቷል ብለውን ነበር።በማለት ለፍርድ ቤቱ ዘርዝረው አቅርበዋል።በመጨረሻ ሲያስረዱም ተመሳሳይ ችግር የሚያጋጥመን በሲጃራ ላይ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ዓይነት የንግድ ሸቀጥ ዋጋ እየተዘዋወርን ከተወሰነው በላይ እንዳይሸጥ ነጋዴዎችን በምንቆጣጠርበት ጊዜ ሁሉ ነው። የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ከፈጸሙ አንከሳቸውም” ብለዋል።
የፍርድ ቤቱ ዳኛም ነጋዴዎች ከመንግሥት ጋር መተባበር እንዳለባቸው አስረድተዋል፤አቶ በቀለም ከእንግዲህ ከዚህ ዓይነቱ ተግባር ወጥተው ንጹህ የንግድ ሥራ እንዲያካሂዱ መክሯቸዋል ።ሕዝቡን ከመበደል መቆጠብና መወገድ እንዳለባቸው በማስጠንቀቂያ መልክ ነግሯቸዋል።
እንደዚሁም አቶመሐመድ አህመድ የተባሉ ተሰማ አባቀማው መንገድ ላይ የሚገኙ ነጋዴ ፤ጥሪ ደርሷቸው ተግድደው እንዲቀርቡ ታዘው ስለነበር በተባለውም ቀን ስላልተገኙ ፤ለሁለተኛ ጊዜ በጥብቅ ተገድደው በአስቸኳይ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት አዟል።አንድ ሌላ ከፍተኛ የመጠጥ ክስ ጉዳይ በፖሊስ ጣቢያው በኩል ያለው ምርመራ ተጣርቶ ስላላቀ በዚሁ ቀን ከአውራጃው ፍርድ ቤት መቅረቡም ታውቋል።
ላሟ ፲ ጥጃዎች ወለደች
አሰላ(ኢ.ዜ.አ)፤ አንዲት ላም በአንድ ጊዜ አሥር ጥጃዎች ወለደች።ከተወለዱት አሥር ጥጃዎች መካከል አንዱ በተፈጥሮው ትክክለኛ ጥጃ ሲሆን ፤ዘጠኙ ደግሞ መጠናቸው በጣም ትንንሽ ነበር። እነዚህ መጠናቸው አነስተኛ የሆኑት ጥጃዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ መጠኑ ከነርሱ ከፍ ይል የነበረው 10ኛው ጥጃ ስድስት ቀን ቆይቶ ሞቷል። ባለላሚቷ አቶ ወትዩ ድልበቶ የሚባሉት
ሲሆኑ ፤በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በጭላሎ አውራጃ ከፈሌ ወረዳ ቆሬ ሁዲጎ በሚባለው ቀበሌ የሚኖሩ መሆናቸው ተገልጧል።
(መጋቢት 15 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
በሐይቅ ባሕር የዓሣ ማዳቀል ተጀመረ
ደሴ (ኢ-ዜ-አ)፤ በወሎ ጠቅላይ ግዛት በአምባሰል አውራጃ በሐይቅ ባሕር ውስጥ የሚገኘው አምባዛ የተባለው ዓሣ ለምግብነት ይበልጥ ተወዳጅነት ስላለው ፤ከነጭ ዓሣ ጋር አዳቅሎ ዘሩን ለማሻሻል በታቀደው መሠረት ፤የጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴ ክቡር ፊታውራሪ ማሞ ሥዩምን ከማዴ ወንዝ ዓሣ አስመጥተው በሐይቅ ወንዝ አስገቡ ።ይኸው ነጭ ዓሣ በሐይቅ ወንዝ ውስጥ ወደፊት በብዛት የሚረባ ከመሆኑም በላይ ፤የጠቅላይ ግዛቱን ሕዝብም ፍላጎት የሚያረካ መሆኑ በተደረገው ጥናት ለማወቅ ተችሏል።
(መጋቢት 10 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013