ዳንኤል ዘነበ
በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉባቸው ክብረ በዓላት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት የባህል ወጉን በጠበቀ መልኩ በጥቂት ሰዎችም ቢሆን ተከብሯል። በየበዓላቱ አዳዲስ ዲዛይን የታከለባቸው የባህል አልባሳት ታይተዋል። ለመሆኑ ዛሬ ላይ የባህል አልባሳት በብዛት ለመለበሳቸው ምክንያቱ ምን ይሆን?
የባህል አልባሳቱን በማዘመን ረገድ ከሚጠቀሱት መካከል የፋሽን የዲዛይን አሰልጣኝ ሚኪያስ ታደለ አንዱ ነው። ለኢትዮጵያውያን ጥሩ ምስል የሚከስቱና በተለያዩ አልባሳት ላይ በአንድ ላይ ተጋምደውና ውበት ሰርተው የሚገኙ አዳዲስ ዲዛይኖች መምጣታቸው የባህል አልባሳት በብዛት እንዲለበሱ አድርጓል ይላል።
በአራዳ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የፋሽን ዲዛይን አሰልጣኝ የሆነው ሚኪያስ እንደሚለው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ በበዓላት ወቅት በርከታ የባሕል አልባሳትን የሚያዘወትር ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፋሽን ኢንዱስትሪው አልባሳቱን በተለያየ ስልት ሸምኖ ሲያቀርብ በርካቶች እንደ ፍላጎቶቻቸውና እንደምርጫቸው መልበስ ጀምረዋል። በቅርቡም በዓመታዊው የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ በእነዚህ ባሕል አልባሳት ተውበው የታዩ የተለያዩ ግለሰቦች ተስተውለዋል።
ፋሽን ዲዛይን በውስጡ ሁለት ነገሮችን እንደሚይዝ የሚጠቅሰው ሚኪያስ፤ ይህም ከኋላ የመጣ ዲዛይንና አዳዲስ ፈጠራዎች እንደሆኑ ያብራራል።ዲዛይን ሲደረግ የነበረን የማይለቅ፤ አሊያም የበፊቱ ላይ የሚጨመር ነው ይላል።በአዲስ መልክ የሚፈጠሩም እንዳሉ ገልጾ፤ በዚህም ፋሽን ዲዛይን የኋላውን ሳይረሳ አዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ይዞ የሚመጣ መሆኑን፤ ይህ ደግሞ ጊዜ ተኮር፣ ሁኔታዎችን ሊያመለክት የሚችልና ታሪክን የሚያስታውስ እንደሆነ ያስረዳል።
እንደ አሰልጣኝ ሚኪያስ ማብራሪያ፤ ፈጠራ የሚባለው ነገር መነሻው ብዙ ነው።ፋሽን ዲዛይነር የሆነ ሰው አዳዲስ የዲዛይን ፈጠራዎችን ካየው፣ ከታሪክ፣ ከራሱ ባህሪ አንጻር ሊሠራ ይችላል። ለዚህም የራሱን በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። ሂደቱን ተከትሎ ሙሉ የፈጠራሥራውን ማከናወን ይችላል። ዝግጅት የጎደለው ከሆነ ሙሉ ፈጠራውን አያሟላም።
አሰልጣኝ ሚኪያስ አክሎ እንደሚያስረዳው፤ ከባህል አልባሳት አኳያ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ።በአሁኑ ወቅት የባህል አልባሳት በስፋት ሲለበሱ ይስተዋላል።ብዙ ፈጠራዎች ተጨምረውባቸው ሰው በዘመናዊ መንገድ ሳይቀር የትም ቦታ ሊለብሳቸው በሚችል ሁኔታ ውስጥ ነው።
በፊት በሃይማኖታዊ ተቋማት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን አስታከው ይለበሱ የነበሩ አልባሳት በአሁኑ ወቅት በሁሉም አውድ ውስጥ ባህላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ሁኔታዎችንም ባገናዘበ መልኩ በብዛት ይለበሳሉ።ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ አዳዲስ የዲዛይን ፈጠራ ውጤቶች መታየታቸው ነው።
ፋሽን «ክላሲክ ፋሽን ትሬንድ» እና «ፋድ ፋሽን ትሬንድ» የሚባሉ ሁለት ዓይነት ሂደቶች እንዳሉት የሚናገረው ሚኪያስ፤ «ክላሲክ ፋሽን ትሬንድ» የሚባለው አንድ ፋሽን ዲዛይን ሲመጣ ሂደቱን የማያቆም መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ይገልጻል። ለምሳሌ ቲሸርት ሁልጊዜም የሚለበስ በመሆኑ ክላሲክ ፋሽን ትሬንድ ውስጥ ይመደባል።
ከገበያው ላይ የማይወጡት አልባሳት በዚህ ሂደት ውስጥ ይካተታሉ። «ፋድ ዲዛይን» የሚባለው ደግሞ ወቅቱን ጠብቀው የሚለበሱትን የሚያሳይ ነው።ሃይማኖታዊ አልባሳት በብዛት ክላሲክ ትሬንድ ውስጥ ይካተታሉ።ይቆማሉ የሚባሉ አይደለም።ባህል ደግሞ ከዚህ ጋር ይያያዛል።
በአሁኑ ወቅት አዲስ እየመጡ ያሉ ዲዛይኖች በፊት ከነበሩት የፋሽን አልባሳት ዲዛይኖች ለየት ያሉ በመሆናቸው ትኩረትን እንደሳቡ አሰልጣኝ ሚኪያስ ይናገራል።«ይህ አንዳንድ ጊዜ ጫና ሊያሳድር ይችላል። ምክንያቱም ፋሽን ስለተባለ ብቻ ባህልን ይወክላል ማለት አይደለም።በዚያው ልክ ደግሞ ይዞት የሚመጣው እሴት አለ።
ሃይማኖታዊ ትውፊትን የሚገልጹ አልባሳትና ባህላዊ ትውፊትን የሚገልጹ አልባሳት በተወሰነ መልኩ ተመሳስሎ ስላላቸው እሴቶችን በመጨማመር ለይቶ መስራት ከዲዛይነሩ ይጠበቃል» ሲል ይገልጻል።
በአሁኑ ወቅት የባህል አልባሳት በሁሉም የሁነት አውድውስጥ መለበሳቸው የፈጠራው ሥራ ስፋት ምን ያክል ፋሽን ዲዛይነሮች ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው ሲልም አሰልጣኝ ሚኪያስ ይናገራል።
አኩሪ የሆነውን የባህል አልባሳት ጥበብን ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ዲዛይነሮች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውና ባህሉን በማክበር ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታገኘውን ፋይዳ ከፍ ማድረግ እንደሚችሉም ያመላክታል።
አሰልጣኝ ሚኪያስ እንደሚለው፤ ሃይማኖትም ባህልም የሚፈቅዱ አልባሳትን አጣጥሞ ነው ዲዛይነር መስራት ያለበት። ፋሽን ዲዛይነሩ ይሄንን አገናዝቦ የመስራት ግዴታም ይኖርበታል። ባህልን ሃይማኖትን ጊዜውንም ያገናዘበ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ሂደት መስራት ፈጠራው እየተጠናከረ እንዲሄድ ያግዛል።
ዘመን ተሻጋሪም ይሆናል።ነገር ግን በዘፈቀደ የሚሰራ ዲዛይን ባህሉን እያበላሸው ይሄዳል።እንደ ኢትዮጵያ ባህል በአልባሳት በኩልም ጥንቃቄን የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ በተቻለ መጠን ማንኛውም ፋሽን ዲዛይነር ባህልን ወግንና ታሪክን፤ የማህበረሰቡን ሕግጋቶች ጠብቆ መስራት ይጠበቅበታል።
በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ዲዘይን በገበያ ላይ መምጣታቸው የባህል አልባሳት በስፋት እንዲለበሱ አዎንታዊ ተጽእኖ መፍጠራቸውን የተለያዩ በዓላት ላይ የሚለበሱ አልባሳትን አብነት አድርጎ ይጠቅሳል። አዲስ ልብስ ሲባል ከጨርቁ፤ ከዲዛይን፤ ከቀለማትና መስመሮችን በአዲስ መንገድ ከማስቀመጥ እንዲሁም ይዘው ከሚመጡት እሴቶች አንጻር ሊታይ እንደሚችልም አንስቷል።
ከዚህ አኳያ የሽንሽን አልባሳት፣ እጀ ጠባቦች፣ በወንድም በሴትም የሚለበሱና ዲዛይነሮች የራሳቸውን እሴት ጨምረው በብዛት እያመረቱ መሆናቸውን አመላክቷል።
ሰዎች የባህል አልባሳትን በማዘወተር የበለጠ በማንነታቸው እየኮሩ መምጣታቸውን የሚናገረው ሚኪያስ፤ የባህል አልባሳትን ምስል በአግባቡ ሰንዶ ማስቀመጥ ተገቢ እንደሆነና እነዚህ ባህል አልባሳትም ከበዓላት ቀናት ውጪ ሰርክ የሚለበሱ እንዲሆኑ ምኞቱን ይገልጻል።
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013