ትውልድና ዕድገት
ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ የኪነ ጥበብ ዘርፍ እንቁ በመሆን በዘርፉ ዕድገት ላይ ታላቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ በሁለገብ አርቲስትነት ተሣትፎው ሥኬትን የተላበሰ የጥበብ ሰው ነው። የኪነጥበብ ሙያን አውቆ በማሣወቅ ብዙ ጥበበኞችን አፍርቷል፤ መንገድ በማሣየት አያሌ የጥበብ ቤተሰቦችን ፈጥሯል፡፡
አዲስ አበባ ልዩ ሥሙ ቀጨኔ መድሀኒዓለም በመባል የሚታወቀው ሠፈር እትብቱ የተቀበረበትና አይረሴ የልጅነት ጊዜውን ያሣለፈበት ነው።ፈረንሣይ ለጋሲዮንም አድጎበታል፤ ተምሮበታል።
አምሐ ደስታና ተፈሪ መኮንን በቀለም ትምህርት ከፊት ሆኖ፣ በመምህራንና በተማሪዎች ተወዶና ተመስግኖ፣ በጉብዝናው ተሸላሚ ሆኖ ዕውቀት የቀሰመባቸው ትምህርት ቤቶቹ ናቸው። በትምህርት ቤት ሕይወቱ በተለያዩ የኪነ ጥበብ ክበቦች በመካፈልም ይወደው የነበረውን የኪነ ጥበብ ሙያ ይለማመድም ነበር። መክሊቱ ኪነ ጥበብ መዳረሻው ትወና ሆኖ እሱን ከፍ አድርጎ አስገኘው እንጂ የልጅነት ሕልሙ በፓይለትነት ሠልጥኖ የአየር ሀይል አብራሪ መሆን ነበር። በትምህርት ውጤቱ ተመርጦ ለሌሎች እውቀት ያስተላልፍ ዘንድ ለመምህርነት ታጭቶ ጅማ መምህርን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ገብቶ በመምህርነት ሙያ ሠልጥኗል፤ የተማረውንም ለሌሎች አሣውቋል – አርቲስት ችሮታው ከልካይ።
የኪነ ጥበብ ጅማሮ
በ1970 አካባቢ በማስተማር ላይ ሣለ የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ መልካም ስላልነበር የሚያውቃቸው የቅርብ ሰዎች ሲጎዱ በመመልከቱ ያስተምርበት ከነበረው የጨቦና ጉራጌ አውራጃ ወልቂጤ ከተማ ማስተማሩን በመተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። አዲስ አበባ በገባ በመጀመሪያው ቀን በውስጡ ያለውን የጥበብ ጥማት
ለማስታገስ ቤተሰብ ከማግኘቱ በፊት ሲኒማ ኢትዮጵያ በመግባት ፊልም ማየቱ አይረሴ ገጠመኙ ነው። ያ የጥበብ ፍቅር ግን መሰዋዕትነት አስከፍሎታል። የዚያኑ ቀን ከሲኒማ ቤት ሲወጣ ከሌሎች ጋር ታፍሶ ዘብጥያ ወረደ።
ታፍሶ ከታሰረበት በሰዎች ዕርዳታ ንፁህ መሆኑ ታውቆ ከወጣ በኋላ አገር ፍቅር ቲያትር ቤት በወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሮ በ142 ብር ደመወዝ ተቀጠረ።ከዚያን ቀን አንስቶ በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ መድረኮች ነግሶ ዛሬ ድረስ አለ – አርቲስት ችሮታው ከልካይ። በቲያትር፣ በፊልም፣ በራዲዮና ቴሌቪዥን ድራማ ዎች፣ በማስታወቂያና በልዩ ልዩ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች በመሣተፍ በብዙዎች ዘንድ በሚታወስ ጥበባዊ ችሎታው ዝናና ክብር ተጎናፅፏል፤ እውነተኛ የጥበብ ሰው መሆኑንም አስመስክሯል።
የዝነኛው ዕረፍት ጊዜ ውሎ
ተዋናይ ነውና ለጥበብ ልዩ ፍቅር አለው።አብዛኛውን የዕረፍት ጊዜውንም የሚያሣ ልፈው የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በመመልከት፣ በማድመጥና የራሱን በመገምገም የተሻሉትን ለመከወን በማለም ነው። ቤተ ክርሲቲያን አዘውትሮ ይሄዳል፤ መንፈሣዊ ተግባራት ላይ ንቁ ተሣትፎ ማድረግ የአርቲስት ችሮታው ከልካይ የዕረፍት ጊዜ ቆይታው ተግባሩ ነው።
ተዋናዩ ስለ እምነቱ የተፃፉ ድርሣናትን አብዝቶ ያነባል።በጥሩ ፀሐፊያን የተዘጋጁ ልቦለዶችና ታሪካዊ መፅሀፍት ደግሞ ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ ማንበብ የሚመርጣቸው ዓለማዊ መፅሀፍት ናቸው። ፊልሞችን መመልከት ሌላኛው የዕረፍት ጊዜውን የሚያሳልፍበት ልምዱ ነው። ድርጊታዊና ታሪክ ቀመስ የሆኑ ልቦለዳዊ ፊልሞች ምርጫዎቹ ናቸው።
አካባቢው ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን በማስተባበር ሰዎችን መርዳትና ማገዝ የታመሙትን መጠየቅ ከማህበረሰቡ ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ በመምከር ማህበራዊ ችግሮችን በመፍታትም ያሣልፋል። አብዛኛው የዕረፍት ጊዜውን በቤተክርስቲያናትና የዕምነት ቦታዎች ማሣለፍ ይወዳል። አርቲስት ችሮታው ከአራት በላይ ቤተ ክርስቲያናትን ህብረተሰቡን በማስተባበር አንዲገነቡ አድርጓል።
በሥራና በዕረፍት ጊዜው በሚዘዋወርባቸው ቦታዎች ሁሉ በኪነ ጥበቡ ባደረገው አስተዋፅኦ ከማህበረሰቡ የሚያገኘው ፍቅርና አክብሮት ልዩ ደስታን ይፈጥርለታል። ህብረተሰቡ በእረፍት ጊዜው ታላቅ ትምህርት ማግኘትና ለማህበራዊ ለውጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ለሚቻልበት ኪነ ጥበብ ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ይጠቁማል።
የዝነኛው መልዕክት ለኢትዮጵያ ሕዝብ
“ቤተሰብ በልጆቹ አስተዳደግ ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።ልጆች ላይ ከተሠራ አገራቸውን እንዲወዱ፣ ሰውን ሰው በመሆኑ ብቻ እንዲያከብሩ ተነገሯቸው ካደጉና ከተገሩ ያኔ ሁሉም መልካም ይሆናል። “ሕዝቡ እርስ በርሱ መፋቀርና ሀይማኖቱ የሚያዘውን በጎ ተግባር ማዘውተር ይገባዋል” ሲል ተዋናዩ ይገልጻል።
ልዩነት ብቻውን ገኖ እንዲወጣ የሚደረግበት ሁኔታ በእጅጉ ያሳስበዋል።ይህ ተግባር ለመነጣጠል የሚደረግ በጎ ያልሆነ ልምድ ነውና መቆም እንደሚገባው ተዋናዩ ያስገነዝባል፤ ሁሉም የሰው ልጅ ነውና እርስ በርስ ሊከባበርና ይህቺን አገር ለመለወጥ በጋራ ሊቆም ይገባል።እውቀት ሠማይ ቢደርስ ሰብዓዊነት ካልታከለበት ይናዳል ይላል።
‹‹ይህች ዓለም የኮንትራት ናት።ሁሉም ለቀጣዩ ትውልድ በጎ ሠርቶ ሊያልፍ ይገባል፡፡” ይህ ታላቅ መልዕክት የፅሑፋችን ማሣረጊያ ነው።አበቃን፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም