
አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ ከ500 ሺ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት ከተማ አቀፍ ፌስቲቫል እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ የባሕል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የኪነጥበብ ሀብቶች ልማት መድረኮችና ኪነቶች ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደኑ ዝግጅቱን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ቢሮው በየዓመቱ ላለፉት 15 ዓመታት የተለያዩ ፌስቲቫሎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፤በተለይ ላለፉት አምስት ዓመታት የኪነጥበብ ዘርፉ ራሱን ችሎ የራሱን መሪ ቃሎችን በመቅረፅ እና በኪነጥበቡ ትኩረት ሊሰጠው በሚገባ ጉዳይ ላይ መሠረት በማድረግ እየሠራ ነው።
ፌስቲቫሉ በዋናነት ከወረዳ እስከ ማዕከል የሚገኙ አማተር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ተማሪዎች እንዲሁም ፕሮፌሽናል የሚባሉ አንጋፋ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በእዚህም መሠረት በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት የተለያዩ ልምምዶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ከሰኔ ሰባት እስከ ሰኔ ዘጠኝ 2017 ዓ.ም ድረስ በመስቀል አደባባይ እና በኤግዚቢሽን ማዕከል የኪነጥበብ ፌስቲቫል ይደረጋል ሲሉ አመላክተዋል።
ፌስቲቫሉ ላይ ከ500 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚታደሙ በመግለጽ፤ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሠራራት በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበር እንደሆነ ጠቁመው፤ዋና ዓላማው በዘርፉ የሚሠማሩ ተተኪ ባለሙያዎች ማፍራት አስፈላጊ በመሆኑ እና የከተማዋ ገፅታ ለከተማው ማህበረሰብ እንዲሁም ለክልሎች በማሳየት በወጣቶች፣ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ስሜት መፍጠር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ዝግጅቱ ላይ በ21 ዘርፎች ከ3ሺ በላይ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ውድድሮች የሚያቀርቡ ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ በመጥቀስ፤ትምህርት ቤቶች አማተር ጥበባት እንዲሁም በግል የሚንቀሳቀሱ ተወዳዳሪዎች እንደሚገኙ አመልክተው፤ ዝግጅቱ ላይ ከሚከናወኑ ዋናዋና ክዋኔዎች መካከል በሥነ ጽሑፍ ዘርፎች የሚቀርቡ ውድድሮች፣የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ዓውደ ርዕይ እና የዕይታዊ ጥበባት ሥራዎች እንዲሁም የፎቶ ግራፍ እና የስዕል ኤግዚቢሽኖች ይገኙበታል ብለዋል።
ፌስቲቫሉ ላይ ወጣቶች፣ሴቶች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች በአካል በመገኘት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተጋብዘዋል።
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም