
ዜና ሀተታ
መሽቶ በነጋ ቁጥር አዳዲስ ገጽታዎችን መመልከት የአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች የቅርብ ጊዜ መገለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይም ሰፋፊ ጎዳናዎች ዳርና ዳር የሚተከሉት የመንገድ ዳር መብራቶች፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ ለምለም ሳርና አበባዎች ለመንገዶቹ ፈርጥ፤ ለዓይናችን ማረፊያ ሆነዋል፡፡
የመንገዶቹ መስፋት የትራንስፖርት ፍሰትን ከማሳ ለጥም ባለፈ አዲስ አበባ የስልጡን ከተሞችን መልክ እንድትይዝ አድርጓታል፡፡ በስልጡኖቹ መንገዶች የምን ጠቀም ተገልጋዮችስ ከመንገድ አጠቃቀማችን አንጻር ስልጡን መሆን ይኖርብናል፡፡
መንገድ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የምናከናውንበት እና ሥራችንን አቀላጥፈን ለመሥራት የሚያስችለን ነው። መውጫ መግቢያችን መንገድ ነው፡፡ ለእዚህም ነው “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” የሚባለው። በእርግጥም እንጓዝ በመኪና መንገድ ጊዜያችንን እና ነዳጃችንን ሳይበላ ያሰብነውን አሳክተን እንድንመለስ የተመቻቸ መሆን ይኖርበታል፡፡
የተመቻቸ መንገድ ማለት መኪኖች ሳይጨናነቁ የሚፈሱበት፣ የእግረኞች ግራና ቀኙን እየተመለከቱ ዘና ብለው የሚሄዱበት መንገድ ፣ ዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገጃ፣ የመኪና ማቆሚያ እና የትራፊክ ምልክቶች፣ የመንገድ ዳር መብራቶች እናም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን የያዘ ሊሆን ይገባል፡፡ በእዚያው ልክ ዘመናዊነትን በአግባቡ ተቀብሎ የሚተገብር ኃላፊነትን በአግባቡ የሚወጣ ተገልጋይ ሊኖር ይገባል፡፡
እስቲ ከአንበሳ ጋራዥ- ጃክሮስ – ጎሮ አደባባይ የተዘረጋውን የኮሪዶር ልማት መንገድ በምናብ ላስቃኛችሁ፤ ይህ መንገድ ከሦስት አቅጣጫ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች የሚገለገሉበት ዋና መስመር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል በከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ ሲያስተናግድ የነበረ ነው፡፡
መንገዱ በኮሪዶር ልማት ተሠርቶ ለአገልግሎት ክፍት ከሆነ በኋላ የትራፊክ መጨናነቁ አብቅቶ የተሳካ የትራፊክ ፍሰት እያስተናገደ ይገኛል፡፡
የኮሪዶር ልማቱ 13 የታክሲ መጫኛና ማውረጃ (ተርሚናሎች)፣ አራት ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ፣ ስድስት የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ ከስምንት ኪሎ ሜትር በላይ ደረጃውን የጠበቀ የእግረኛ መንገድ ፣ ሦስት የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ ቦታዎች፣ 872 ሱቆች እንዲሁም ሰባት ፕላዛዎችና የሕጻናት መጫወቻ ቦታዎች አካቶ የያዘ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነት አስገራሚ ለውጥ በማየታቸውም የአካባቢው ነዋሪዎችና የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ሰዎች ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ቢኒያም ዋለልኝ፤ የጎሮ መስመር ተርሚናል አገልግሎት ሠራተኛ ነው፤ መንገዱ ከመሠራቱ በፊት የነበረው የታክሲ አገልግሎት እጅግ የተጨናነቀ እና ለአደጋ የሚያጋልጥ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ታክሲዎች መንገድ ዳር እንደፈለጉ ተራ ሳይጠብቁ ሰዎችን ሲጭኑ እርስ በራስ በመገጫጨት እንዲሁም ከሌሎች ተሽከርካሪዎች ጋር በመጋጨት ተደጋጋሚ አደጋ ያስከትሉ ነበር ይላል፡፡
አሁን ላይ አዲሱ የጎሮ የኮሪዶር መንገድ በቂ የእግረኛ መንገድ፣የታክሲ ማቆሚያ ተርሚናሎች እንዲሁም የተለያዩ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ማካተቱ፤ ታክሲዎች ሥርዓት እንዲይዙ አድርጓል፤ ተገልጋዩም ሥርዓት ይዞ ለመጠቀም አመቺ ሆኗል፤ ይህም የትራፊክ ፍሰቱን የተመቸ እንዳደረገው እና መንገድ ዳር የተደረጉት አዳዲስ የትራፊክ ምልክቶችም በፊት ያጋጥም የነበረውን አደጋ እና መጨናነቅ በጣም ይቀንሱታል ሲል ይገልጻል፡፡
ከአንበሳ ጋራዥ ወረድ ብሎ በሚገኝ አነስተኛ ቤት የሻይ ቡና አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ተስፋነሽ ከበደ በበኩላቸው፤ቀደም ሲል መንገድ ዳር የነበሩ የንግድ ሱቆች ወደ መንገዱ የተጠጉ ነበሩ፤ በተጨማሪም መኪኖች መንገድ ዳር ይቆማሉ፤ አሁን ላይ ሁለቱም ተስተካክለዋል፤መንገድ ዳር መኪና እንዳይቆም የትራፊክ ምልክቶች ተደርገዋል፤ ሱቆችም በኮሪዶሩ ምክንያት ገባ ብለው ተሠርተዋል፡፡
ነገር ግን ሰፊውን የእግረኛ መንገድ ትቶ በፊት በለመደው መንገድ ከመኪኖች ጎን እየተጠጋ የሚራመድ እግረኛ በርካታ ነው፤ በመሆኑም ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲጠቀም እና ለአደጋ እንዳይጋለጥ በልማድ መጓዙን ትቶ የአዲሱን መንገድ ባሕሪ ተላምዶ በአግባቡ ሊጠቀም ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
የሜትር ታክሲ ሹፌር የሆነው ወጣት ኢብራሂም ማንድዮ በበኩሉ፤ “የጎሮ መስመር በፊት በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ በተለይም ወደ ሥራ መግቢያና ከሥራ መውጫ ሰዓት ላይ እና ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እንዲሁም የግጭት አደጋዎች ይከሰቱበት ነበር፡፡
አሁን መንገዱ ለትራፊክ ፍሰት በጣም አመቺ ከመሆኑ ባሻገር በቂ የእግረኛ መንገድ ማካተቱ ለተገልጋይ እጅግ የተመቸ አድርጎታል፤ ሆኖም ግን የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ውስን ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተለይ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ስንሰጥ ተንቀሳቅሰን ለመሥራት ያስቸግራል፤ ይህ በሂደት ታይቶ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ቢጨመር መልካም ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የከተሞች መዘመን ትርጉም የሚኖረው ሰዎችም አብረው ሲዘምኑ ነው፤ የሚዲናዋ ለውጥ የበለጠ የሚጎላው የተሠሩትን የኮሪዶር ልማቶች በአግባቡ መጠቀም የሚችል እና አሮጌ አሠራሮችን ትቶ በፍጥነት ከአዲሱ ለውጥ ጋር የሚራመድ ማህበረሰብ ሲፈጠር ነው በማለት እንደ ጋዜጠኛ ምልከታችንን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም