ውበታም ኮቴዎች

ጥበቃ ሆኜ ልቀጠር ከሰዓት እስኪሆን እየጠበኩ ነው..የድርጅቱ ሕንፃ ደረጃ ላይ ቁጭ ብዬ።

በሕይወቴ ተመኝቼ የተሳካልኝ ምን እንደሆነ አላውቀውም። እኔ የነካኋቸው ነገሮች ሁሉ እንዳይሆኑ ሆነው የተበጁ ናቸው። ነገሮች ለምን ሌላው ጋ ሰምረው እኔ ጋ ሲደርሱ እንደማይሳኩ ይገርመኛል። ግን በዕድለ ቢስነቴ ያዘንኩበት ቀን የለም። በእርግጥ የምፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ሳጣ የኖርኩ ሰው ነኝ ግን ያጣኋቸው ነገሮች እንዳያሙኝ ሆኜ የቆምኩ ነኝ።

ይሄን ብርቱነቴን እንዴት እንዳገኘሁት አላውቅም። ምናልባት ምርጡ አንተ እንዴት ያለው ነው ተብዬ ስጠየቅ ‹ያ ብዙ ነገሮች አልሳካ ብለውት በሳቅ ውስጥ የቆመው እኔ ነኝ› ብዬ እንድመለስ እግዜር ከርህራሄው ትንሽ ቦጭቆ የሰጠኝ ይመስለኛል።

በሕይወቴ ዕድሌን ሁለት ጊዜ ረግሜዋለሁ..በብዙ ሳቅ ውስጥ ቆሜ እንባ የተናነቀኝ ያኔ ነው እላለሁ። የመጀመሪያው አባቴን በሞት ሳጣው ነው። አባቴ ታሞ አልጋ ላይ እያለ ዩኒቨርስቲ ልገባ የሁለት ቀን እድሜ ነበር የቀረኝ። የሕይወቴ ትልቁ ጸሎቴ አባቴ ድኖ ማየት ነበር። ግን ዩኒቨርሲቲ በገባሁ በማግስቱ አባቴ ማረፉ ተነገረኝ። አባቴ ከመሞቱ ከደቂቃዎች በፊት የኔን ስም እየጠራ..‹ልጄን ጥሩት፤ አይቼው ልሙት› እያለ እንደነበር ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው እናቴ የነገረችኝ። አባቴ ሳያየኝ..የነፍሱን የመጨረሻ ሰዓት ሳላስተውል ተለየኝ።

አባቴን ቀብሬ መቼም ይደርስብኛል ብዬ ባላሰብኩት ብቸኝነትና መከራ ተከብቤ ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመለስኩ። በዛ ስብራቴ ውስጥ ሂሩት ከምትባል ልጅ ጋር ተዋወኩ። ዕድሌን የረገምኩበት ሁለተኛው ምዕራፍ ከዚህ ይጀምራል። ከአባቴ ሞት በኋላ ለብቻዬ የምቀመጥበት አንድ የብቸኝነት ዓለም ነበረኝ። እዛ ዓለም ላይ እኔ ብቸኝነቴና ዕድለቢስነቴ ብቻ ነበርን። በዚህ መከራ ውስጥ የሚጎዳኝ ሌላ ሰው ይገባል ብዬ አላሰብኩም ነበር።

በዚህኛው እኔ ውስጥ የምትገባ ሌላ ነፍስ ትኖራለች ብዬ አልገመትኩም ነበር። ሕልምና እውኔ ተደበላልቀውብኝ ከሰው ልጅ ሁሉ ሌላ ነበርኩ። የምድር ቆይታዬን አጠቃላይ ጉዳት እያስተናገድኩ እንደሆነ ስለማምን ከዚህ በኋላ የሚጎዳኝ ሰውም ሆነ የምጎዳበት አጋጣሚ የለም ብዬ በማመን ውስጥ ነበርኩ። ግን ሂሩት የምትባል ሴት ገባችበት።

የብቻዬ ዓለም ውስጥ ሽንጠ ረጅሙን ሕንፃ ተደግፌ፣ ዛሬም ድረስ በማስታውሳት እንዴት ከወዳጆቿ ተለይታ እዛ ቦታ ብቻዋን እንደቀረች እርግጠኛ ባልሆንኩባት ብሎኬት ላይ ተቀምጬ፣ እኔ አባቴና እናቴ የነበርንበትን የወዲያ ዓለም እዳስሳለሁ። ከዛ ዕምባ..ከዛ ስብራት..

በዚህ የቀን ሙሉ ትካዜዬ ውስጥ ከተደገፍኩት ሕንፃ አናት የተማሪዎች ኮቴና ድምፅ፣ ሳቅና ቧልት ይሰማኝ ነበር። የሆነ ሰዓት ላይ፣ በሆነ በተመጠነ ርምጃና እንቅስቃሴ ወደዚያ ወደዚህ ስል የምሰማው አንድ ኮቴ ነበር። በሆነ ሁናቴ የሚራመድ ሰበር ሰካ..ማቅ በለበሰች በነፍሴ ነፍስ ውስጥ የሚያረብብ ዳና አንዱ ትውስታዬ ነበር። ይሄ ኮቴ ጠዋት ወደ ክፍል ሲገባ ረፋድ ከክፍል ሲወጣ እንደገናም ከሰዓት ክፍል ገብቶ ሲወጣ ለነፍሴ እጅግ የቀረበ ዜማ ሆኖ ተለማመድኩት።

አንድ ቀን..ተክዤ በተቀመጥኩበት ይሄው ኮቴ ካለሁበት መጣ። ምንም እንዳይማርከኝ ሆኜ ለመኖር የተሰናዳሁ ሰው ነበርኩ…ለዛ ኮቴ ቀና ስል ከአንዲት ጠይም ሴት ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጨሁ። ምንም አይነት ቅጥያ ሳትጨምር ‹ሂሩት እባላለሁ› ስትል እጇን ዘረጋችልኝ።

‹ናሆም› ስል እጆቿን በመጨበጥ መለስኩላት። እውነት እላችኋለሁ በዛ ቅጽበት የተሰማኝ አዲስነት ነበር። የአንዲት ሴት እጅ በዘላለሜ ውስጥ በትካዜ ላኖረው ቃል የገባሁለትን እኔን ሲቀይረው መኖር ትርጉሙ ጠፋኝ። በዛ ቅጽበት ከእንግዲህ አትረባም ያልኩት እኔ ተስፋ ሲያለመልም ሕይወት ድንግርግር አለችኝ። ያ እጅ ሁሌ የምሳለመው የካህን እጅ ሆኖ ልቤ እንዲቀመጥ ለራሴ ቃል ገባሁ። ያ እጅ እንዳይጥለኝ..ከአባቴ እጅ ቀጥሎ በመተማመን ወደሕይወት ደባለኩት።

እንዲያ ባለው አጋጣሚ ከሂሩት ጋር ተዋወቅን። እኔ ከተወችኝ ለሞት በሚያበቃ ስሜት ወደድኳት..እሷ ግን እንዲያው ነበረች። መሻሬን ስታውቅ ችላ አለችኝ። ልቧን ካራራው ብዬ አንድ ቀን እንደማፈቅራት ነገርኳት። ለምን እንደቀረበችኝ ግልጽ ባለ አማርኛ እንዲህ ስትል አስታወቀችኝ..‹የቀረብኩህ አሳዝነህኝ ነው..ሁሌ ወደክላስ ስገባና ከክላስ ስወጣ ብቻህን አዝነህ ሳይህ የሆንከው ነገር እንዳለ በመረዳት ነው የቀረብኩህ..እኔ አሁን ላይ ለፍቅር ዝግጁ አይደለሁም› አለችኝ። ከአባቴ ሞት ቀጥሎ በሂሩት ተሰበርኩ። አባቴንና ሂሩትን ሳስብ ሁለት ሞትን ሞቼ ሰው የሆንኩ ያህል ይሰማኛል። ከዛ በኋላ ባሉት ጊዜያቶች ውስጥ ዕድሌ እየካበ ሲንደኝ፣ እየጠገነ ሲሸርፈኝ አሁን ካለሁበት ደረጃ ላይ አድርሶኛል።

ከተመረኩ ሦስት ዓመት አልፎኛል..የሄድኩባቸው አንዳቸውም ድርጅቶች ስሜን ለጥፈውት አላየሁም። በእርግጥ ውጤቴም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ ግን ደግሞ ከኔ ያነሰ ውጤት ያላቸው ወዳጆቼ ሥራ ተቀጥረው አይቻለሁ። ከኔ በቀር ሁሉም ጓደኞቼ በሥራ ዓለም ላይ ናቸው። ሁለት ጓደኞች ብቻ አሉ እንደ እኔ በጡረታ የተገኘ የእናታቸውን እንጀራ እየበሉ ቤት የተቀመጡ። እኔስ በዕድለ ቢስነቴ ነው ሥራ ያጣሁት የእነሱ ግን ጥጋብ ነው..አዲስ አበባ ውስጥ ያልገቡበት የሥራ ቦታ የለም። ግን ከወር በላይ መቆየት አይችሉም። መጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል..ከዛ በሳምንቱ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል በዛው ሳምንት መሰናበቻ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል። አመላቸው ጉድ ነው። እነሱን ሳይ ከኔም የባሰ ዕድለቢስነት አለ እንዴ እላለሁ። ሁሉም በራሱ አጋንንት ውስጥ ነው..

ከሦስት ዓመት ሥራ ማጣት በኋላ ጥበቃ ሆኜ ልቀጠር ከሕንፃው መግቢያ ደረጃ አንዱ ላይ ተቀምጬ ከሰዓት እስኪሆን እጠብቃለሁ። ጥበቃ ሆኜ ማለፌም ይገርመኛል..ዕድለ ቢስነቴ ከላዬ ላይ ጮሆ ሊወጣ እያጣጣረ ይመስለኛል። አባቴን ያሳጣኝና ሂሩትን የነጠቀኝ ዕድለ ቢስነት ከዚህ በኋላ ቢወጣ ባይወጣ ምን ሊጠቅመኝ ስል በውስጤ እመልሳለሁ። ደረጃው ላይ ተቀምጬ ኮቴ ሰማሁ.. ቁልቁል የሚወርድ ኮቴ። የጫማው ኮቴ ደረጃው ላይ ሲያርፍ የሚፈጥረው ስሜት ዕድለ ቢስነቴን አስረሳኝ። የማን እግር ይሆን እንዲህ በተዋበ እርምጃ የሚረግጥ? የማን ጫማ ይሆን እንዲህ ባማረ አካሄድ ዜማ የሚፈጥር? እያልኩ ወንድ ይሁን ሴት በማላውቀው ሰው ርምጃ ተደነቄ መጠበቅ ጀመርኩ።

ኮቴው እየቀረበኝ መጣ..ከላይ የሚወርድ የሆነ ሰው እንደሆነ ተገለጠልኝ። ኮቴው እኔ በተቀመጥኩበት የደረጃ መረማመጃ ላይ ሲደርስ ሴት መሆኗን ተረዳሁ..ደስ የሚል ጠረን የቀላቀለ ሴትነት ከላይ ወደታች ተዋሓደኝ። ለመተላለፊያ እንዲሆናት ስል ሰፋ አድርጌ ከያዝኩት ቦታ ነቅነቅ ብዬ ጥጌን ያዝኩ። ደስ በሚል እርምጃ በአጠገቤ አለፈች። ዓይኔ ጀርባዋ ላይ አረፈ..ሂሩት ነበረች ብል ማን ያምነኛል? አዎ ሂሩት ነበረች..

እንዳልከተላት የሚያደርግ ለሦስት ዓመት የታመቀ ቅያሜ ነበረኝ..ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መጨረሻዋን አየሁት። መጨረሻዋ ውጪ ቆማ ከምትጠብቃት ቀይ መኪና ውስጥ መግባት ነበር። በመኪናዋ ስትሄድ አየኋት..

ድርጅቱ የአባቷ ነበረ..ለጥበቃ ከተወዳደሩት ስም ዝርዝር ውስጥ የኔን ስም ተመልክታ ልታገኘኝ እንደመጣች ተነገረኝ..

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ነበረች..የመጀመሪያ ቀን ዩኒፎርም ለብሼ በጥበቃነት በር ላይ እንደቆምኩ ከሳምንት በፊት ያየኋት ቀይ መኪና ወደግቢው ስትገባ በር ከፈትኩ። ሂሩት ናት..አላወቀችኝም። አንድ ዓይነት ለብሼ፣ ኮፍያ አድርጌ..አላየችኝም።

ነፍሴ ተጨነቀች..ሥራውን ልተው አልተው በሚል ሀሳብ ቀን ሙሉ ዋልኩ። ለማፈቅራት ሴት ድርጅት ጥበቃ ሆኖ መሥራት..ምንም ይሁን እሠራለሁ ስል ወሰንኩ።

የሆነ ቀን ሂሩት አወቀችኝ..

ወንድነቴ ውስጥ እኔ የማላውቀው ዲያቢሎስ ያለ ይመስለኛል።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You