
-በክረምቱ 23 ሚሊዮን ያህል ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ ታቅዷል
አዲስ አበባ፡– በበጀት ዓመቱ 10 ወራት በተከናወነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ57 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በክረምት ወራትም 23 ሚሊዮን ያህል ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡
በሚኒስቴሩ የወጣቶች ብሔራዊ የዜግነት አገልግሎት እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስፋፊያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዐቢይ ኃይለመለኮት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት 10 ወራት ከ23 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፈዋል፡፡ በእዚህም ከ57 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል። በአገልግሎቱም መንግሥት ሊያወጣ የሚችለውን ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መንግሥት ሊሸፍናቸው ያልቻላቸውን ተግባራት መድረስ አስችሏል ያሉት አቶ ዐቢይ፤ በአረንጓዴ አሻራ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ በችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ፣ የግብርና ልማት፣ ትምህርትና ልማት ሥልጠና አገልግሎት፣ የጤና አገልግሎት፣ የመሠረተ ልማቶችን ማልማትና ማጠናከር፣ ሰላምና ደህንነት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች የተከናወነ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የሂሳብ ሥራ፣ የምህንድስናና የሥነ-ልቦና ምክር አገልግሎትንና ሌሎችንም የሙያ አገልግሎቶች የሚያካትት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በቀጣዩ የክረምት ወራትም ካለፈው ዓመት ከፍ ያለ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የዝግጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ያመለከቱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በክረምት ወራት ብቻ 23 ሚሊዮን የሚደርሱ ወጣቶችን ለማሳተፍ እቅድ ተይዟል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሕል እንዲሆን በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲሰርጽና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ፈጠራ እና የንቅናቄ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ባለድርሻ አካላትን የማወያየት እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በተያዙ በጎ ፈቃድ እቅዶች ላይ እንዲወያዩ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመልክተው፤ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የግብዓት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በያዝነው ሰኔ ወር አጋማሽ ሀገር አቀፍ የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መክፈቻ እንደሚደረግ አንስተው፤ በተከታታይ ዓመታት እየተከናወነ ያለው የወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም