
አዲስ አበባ፦ በተደጋጋሚ ለ20 እና 30 ዓመታት ከ50 እና ከ100 ጊዜ በላይ ደም በመለገስ ሕይወት ለታደጉ በጎ ፍቃደኛ ለጋሾች እውቅናና ሽልማት እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።
በአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ታረቀኝ፤ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ሰኔ ሦስት የዓለም የዕይታ ቀን ተከብሮ ውሏል። የፊታችን ሰኔ ሰባት ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን ይከበራል። እነዚህን ዓለም አቀፍ በዓላት ታሳቢ በማድረግ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም እንደ ሀገር “የደምና የዓይን ብሌን ለጋሾች ቀን” በሚል ደምና ዓይን ብሌናቸውን በመለገስ የወገኖቻቸውን ሕይወት ለታደጉ እና ለወገኖቻቸው ብርሃን ለፈነጠቁ በጎ ፍቃደኞች በጠቅላላ እንደ ሀገር ክብርና ምስጋና ይሰጣል።
በእዚሁ ቀን በልዩ ሁኔታ ደግሞ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ ከተቋሙ ጋር አብረው የሚሠሩ አጋር አካላትና ሌሎች በተገኙበት በተደጋጋሚ ለ20 እና 30 ዓመታት ከ50 እና ከ100 ጊዜ በላይ ደም በመለገስ ሕይወት ለታደጉ በጎ ፍቃደኛ ለጋሾች እውቅናና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ጠቁመው፤ እንዲሁም በደምና ሕብረ ህዋስ ማሰባሰብ ሂደቱ ከፍተኛ አበርክቶ ለተወጡ ተቋማት፣ ማህበራት፣ ቡድኖች እንዲሁም ግለሰቦች እውቅናና ሽልማት ተቋሙ ያበረክታል ብለዋል።
አንድ ሰው 450 ሚሊ ሊትር ደም በመለገስ የሦስት ሰዎችን ሕይወት መታደግ እንደሚችል አቶ አለማየሁ አመላክተው፤ ከእዚህ አኳያ በተደጋጋሚ ለ20 እና 30 ዓመታት ከ50ና ከ100 ጊዜ በላይ ደም የለገሱ በጎ ፍቃደኞች በሚተካ ደም የማይተካ የበርካቶችን ሕይወት መታደጋቸውን ተናግረዋል።
የወገኖቻቸውን ሕይወት የሚታደግና ወገኖቻቸውን ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚመልስ ስጦታ ላበረከቱ በጎ ፍቃደኞች ውለታቸውን በምንም ነገር መክፈል ባይቻልም፤ ለሠሩት በጎ ሥራ እውቅናና ምስጋና መስጠት ይገባል ያሉት አቶ አለማየሁ፤ የሰው ልጅ ለሠራው፣ ላደረገው በጎ ነገር ተገቢው እውቅና ሲሰጠው የበለጠ እንዲተጋ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።
እውቅናና ሽልማቱ ዜጎች በደምና ሕብረ ህዋስ ልገሳ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ይበልጥ እንዲሳተፉ የሚያነሳሳና የሚያተጋ መሆኑን ገልጸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ እውቅናና ምስጋና የሚያገኙ በጎ ፍቃደኞች ለሌሎች አርአያ በመሆን፤ ዜጎች እንዲለግሱ መነሳሳትን ይፈጥራሉ ብለዋል።
አቶ አለማየሁ፤ ዜጎች ግንዛቤውንና እውቀቱን አግኝተው ደም ከለገሱ በኋላ፤ ደግመው እንዲለግሱ ወይም ቋሚ ለጋሽ እንዲሆኑ የተለያዩ የማትጊያ ስልቶችን ተቋሙ እንደሚጠቀም አመልክተው፤ እውቅናና ክብር ለለጋሾች መስጠት አንዱ የማትጊያ ስልት ነው። ይህም ቋሚ የደም ለጋሾች ቁጥር እንዲበራከት እና እንደ ሀገር በቂ የደምና ሕብረ ህዋስ ክምችት እንዲኖር ያስችላል ሲሉ ሥራ አስፈጻሚው አቶ አለማየሁ አስገንዝበዋል።
ከደምና ሕብረ ህዋስ ልገሳ ጋር ተያይዞ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ የተዛቡ አመለካከቶች አሉ። ለመለገስም ስጋት የሚገባቸው ሰዎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ አለማየሁ፤ ከእዚህ አንጻር ከ100 ጊዜ በላይ ደም የለገሱ አካላት ደም መልሶ እንደሚተካ፣ ደም መለገስ የጤና ጠቀሜታና የሕሊና እርካታ እንደሚያስገኝ ሁነኛ ማሳያ ናቸው። እንዲሁም ማህበረሰቡ በዘልማድ የሚገምታቸው ጉዳቶች ወይም የተዛቡ አመለካከቶች በተጨባጭ እንደሌሉ የሚያስረዱ ምስክሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
እውቅናና ሽልማት የሚገባቸው ቢያንስ ሦስት በጎ ፍቃደኞችን እያንዳንዱ ክልል በተላከላቸው መስፈርት መሠረት አወዳድረው እንዲልኩ አቅጣጫ መሰጠቱን ሥራ አስፈጻሚው አቶ አለማየሁ ጠቁመው፤ ከየክልሉ ተመልምለው የሚመጡ በጎ ፍቃደኞች በፌዴራል ደረጃ ሰኔ 07 ቀን 2017 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚካሄደው ደማቅ የእውቅናና ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተሸላሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል።
አቶ አለማየሁ፤ ማናቸውም ከተቋሙ ጋር መሥራት የሚፈልጉ አካላት አብረው በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ በመሳተፍ በጎ ፍቃደኛ ለጋሾችን እንዲያበረታቱ አሳስበዋል።
እንዲሁም ማህበረሰቡ በዕለቱ ከ2 ሰዓት ተኩል (30) ጀምሮ ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እንዲሁም ወደ ዋና መሥሪያ ቤቱ፣ ቀይ መስቀል ግቢ እና 54ቱ የክልል ደም ባንኮች ጎራ በማለት የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብሩ ተካፋይ ከመሆን ባሻገር ደም እንዲለግሱና ከሕልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ በቃል ኪዳን ሰነዱ የክብር ፊርማቸውን እንዲያኖሩ በእዚህ አጋጣሚ ሥራ አስፈጻሚው አቶ አለማየሁ ጥሪ አቅርበዋል።
በሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም