
የሰው ሠራሽ አስተውሎትና የሰው ልጆች ፊት ለፊት የተፋጠጡበት ጊዜ ላይ መሆናችን ገሀድ የምንመለከተው ሀቅ ነው:: በአንዳንዱ ጉዳይም ተፈጣሪ ከፈጣሪው ጋር ግብግብ የገጠመበት ጊዜ ላይ ነን:: ቴክኖሎጂው የሰው ልጆችን ሕይወት ማቅለሉ ብቻ በቂና ሁሉንም አሳማኝ ለመሆን አልቻለም:: እንደ አመጣጡ፣ እንደየ አቀባበሉ፣ እንዳረዳዱና እንዳመለካከቱ በእያንዳንዱ ዘንድ ያለው ስሜት የተለያየ ነውና እኛም ጥሩ ወይንም መጥፎ ብለን ፍርድ ለመስጠት ሳይሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በኪነ ጥበብ መንደር ውስጥ እየተስተናገደ ያለበትን ሁኔታ ግን አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት መልካም ነው:: ምክንያቱም ያለነው ዓለም ውስጥ ነውና ‹ነግ በኔ› ማለትም ይኖራል:: ከተማረ ሁሉም ሰው ሊማር ይችላል፤ ነገር ግን የሚማረው ‹ሞኝ ከራሱ፣ ብልጥ ከጎረቤቱ› መሆኑ ላይ ነውና ከዚህ አንጻርም መቃኘታችን አይከፋም::
ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) አሁን አሁን በብዙ ጉዳዮች ላይ ዙሩን እያከረረው ነው:: የኤ አይ ሮህቦት የሰው ልጆችን የአኗኗር ዘዬ ሲቀይር፣ በአንድ በኩል ሕይወት የሚያቀልና መልካም ነገሮችን የሚያመጣ የተባለለት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹እስቲ ትደርስና!› ሲሉ በጥርጣሬ ዓይን ያፈጠጡበት ሆኗል:: ለብዙዎች ምቾትን፣ ለአንዳንዶች ስጋትን የፈጠረ ሆኖ ይታያል:: አዳዲስ ነገሮች ብቅ ባሉ ቁጥር መሰል ሁኔታዎችን እንደሚያስተናግዱ የታወቀ ቢሆንም፤ በተለይ ኪነት አካባቢ ያሉ ነገሮችን ግን እንዲህ ብለን ብቻ የምናልፋቸው አይደሉም:: ጥበብ ስስ ብልቷንም ሆነ ሥሯን አላግባብ የነኳት እንደሆን ጽጌረዳ አበባ ማለት ናት፤ በቀላሉ የምታገግም አትሆንም:: ስለ ኤ አይ የምናነሳቸው ሀሳቦችም ኪነ ጥበቡን ብቻ የሚመለከቱ ይሆናሉ::
በቅድሚያ ግን ለዋናው ሀሳባችን ረዳት እንዲሆነን ጥበብ መንደር ውስጥ ስለ ኤ አይ ቴክኖሎጂ ጥቂት እውነታዎችን እንጫር:: ለኢንዱስትሪው ያመጣቸውና የታዩ መልካም ነገሮች መኖራቸው የማይካድ ነው:: ለምሳሌ የአዕምሮና ተዛማጅ መብቶች ቅጂ (ኮፒራይት) ጉዳይን ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ለመቆጣጠር ችሏል:: በማኅበራዊ ሚዲያዎች እና ከአድማጭ ተመልካች ጋር በሚያገናኙ መተግበሪያዎች ውስጥም ኤ አይ’ን እንመለከተዋለን:: ለአብነት በስልኮቻችንም ሆነ በኮምፒውተር ወደ አንደኛው የማኅበራዊ ሚዲያ ከመግባታችን በግላችን የምንፈልጋቸውና የምንወዳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ከፊት ለፊት ገጽ ላይ ገጭ ሲሉ አስተውለን ይሆን?
ፖለቲካ ለምንወድ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ደርድሮልን እናያለን:: መዝናኛ ለምንወድ አዝናኝ የሆኑትን ያስቀምጣል:: ስለ ዝነኞች፣ ከዝነኞችም ብዙ ጊዜ የእኛ ምርጫ ስለሆነው ዝነኛ አዲስ ነገር በወጣ ቁጥር ሁሉ እንዳያልፈን ከፊት ያደርገዋል:: ለማየትም ሆነ ለማንበብ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን በምናስብባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ወሳኝ ነገር ስለመኖሩ በማሳወቂያ (ኖትፊኬሽን) ሳይቀር ይልክልናል:: የፊልም መተግበሪያዎችን የምንጠቀም ከሆነ፣ ባለፉት ጊዜያቶች ባየናቸው ፊልሞች ውስጥ የተወኑ ተዋንያን የተውኑባቸው አዳዲስ ፊልሞች ሲለቀቁ አምጥቶ ፊት ያስቀምጥልናል:: በሙዚቃው ደግሞ ባለፈው የሰማነውን ሙዚቀኛና ከእርሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ብቻ ሳይሆን ትዝታ፣ ሬጌ፣ ብሉዝ፣ እንቅጥቅጥ ምርጫችንን ለይቶ ያውቀዋል:: ታዲያ ይህ ሁሉ ጥንቆላ ወይንስ? ይህን አድራጊው ኤ አይ ነው:: ሲያደርግ ደግሞ በጥንቆላ ሳይሆን በ‹አልጎሪዝም› ነው:: ስልካችንን ከፍተን ላይ ታች እየጫርን ስናነብና ስንመለከት የነበራቸውን ሲሰልል ነበርና ምርጫችን ምንና ማን እንደሆነ አበጥሮ ያውቀዋል::
በእነዚህም ሆነ በቀጣዮቹ ረቂቅ ግብሮቹ ውስጥ የኤ አይ ስጋና ደም፣ ጥበብና መንፈስ ‹አልጎሪዝም› ነው:: የዕውቀትና የጥበብ ማዕከል አንጎል ጭንቅላቱ እሱ ላይ ነው:: ያለዚህ አደርገዋለሁ ብሎ ሊያሳየን የሚችል ምንም ዓይነት ጥበብ አይኖረውም:: ሮህቦቶቹ የሚከውኑት ከሰው ልጅ የሚማሩትን ነውና ትምህርት ቤቱም ሆነ አስተማሪው ይሄው የአልጎሪዝም ስልት ነው:: ከኢንተርኔት መረብ እስከዛሬ ድረስ በሰው ልጆች ተሠርተው የተለቀቁ ፊልሞች፣ የተጻፉ መጻሕፍትና ሌሎችም ጽሁፎች፣ የተሞዘቁ ሙዚቃዎች፣ የተነገሩ ንግግሮች…ከሁሉም አንድም ሳይቀረው እንደ ‹ሀ ሁ› ይማረዋል:: አንድ ሰው ጎበዝ ደራሲ ለመሆን ብዙ ማንበብ እንደሚኖርበት ሁሉ አንድ ሮህቦትም ከመጻፉ አሊያም ከመሞዘቁ በፊት በተመሳሳይ ይከውናል:: ይህን የሚያደርግበት ግዙፍ የአልጎሪዝም ላይብረሪው የኢንተርኔት ክምችቶች ናቸው:: ‹እስቲ እንደ እገሌ ሆነ ተውን ጻፍ› ስንለው ‹እገሌ ምን ዓይነት›እንደሆነ መንገር ማስተማር ብቻ ነው::
ከፈረንጆቹ 2022 ወዲህ የጥበብ መንደር በኤ አይ ቴክኖሎጂ፣ በባሕርዛፍ አሊያም በወይራ ጪስ ታጥናለች:: ምስጋናውም ቅሬታውም፣ ሙገሳውም ሀሜቱም መሳ ለመሳ እየሄዱ ናቸው:: መነሻቸውም በአሁኑ ሰዓት እዚሁ መንደር ውስጥ የሚወነጨፉ ሁለት የኤ አይ ፈጠራዎች ናቸው:: “DALL-E” እና “Discord, Midjourney” የተባሉ:: እነዚህ ሁለቱ የኤ አይ ጥበበኞች ከትንሹ ምስል እስከ ድምጾችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ እንዲሁም ከእነዚህም ውስብስብ የሚባሉ ነገሮችን ሁሉ ያለምንም ረዳት ጥንቅቅ አድርገው መሥራት ችለዋል:: በነሐሴ 2022 ‘Midjourney’ በተባለው ኤ አይ አማካኝነት “ዲ‘ኦፔራ ስፓሻል” የተሰኘ ቲያትር ተሠርቶ ሽልማት ሳይቀር አግኝቷል::
የኤ አይ ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ዓይን ኪነ ጥበብ ላይ ማነጣጠሩ፣ እንደ ማንኛውም ዘርፍ ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂውን ለማስጠቀም በማሰብ ብቻ አይደለም:: ከዚያ ጀርባ ኤ አይ ራሱን የመሸጫ ማስታወቂያ አድርጎ ለመጠቀም ይፈልጋል:: በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በቀላሉ የመዋሃድ አቅም ያላቸውን እንደ ፊልምና ሙዚቃ ያሉትን ጥበባት በመጠቀም ልብ መርቻ ሊያደርገውም ይፈልጋል:: በጦፈው መንገድ ውስጥ ግራና ቀኝ ሁለት ጎራ ይዞ የሚገኘውን የጥበብ ቤተሰብ ለማስታረቅና ከኤ አይ ጋር ትውውቅ ፈጥሮ ለማስማማት አሸማጋይም ሽተዋል:: የኪነት ወገንን ወክለው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይ የሚሳተፉና ቴክኖሎጂውን በተመለከተም የመደራደሪያ ሀሳቦችን እስከማቅረብ ደርሰዋል:: ፕሮጀክቶችን እየቀረጹ ጥናታዊ ጽሁፎችን ሳይቀር እያቀረቡ፣ ኤ አይ በጥበብ ፈጠራዎች ውስጥ የሰው ልጆች ከሚደርሱበት ምናባዊ ረቀቂነት ለመድረስ እንደማይቻለው በመግለጽ፣ በጥበብ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ለኤ አይ መስጠት አያስፈልግም የሚል መከራከሪያዎችንም ያነሳሉ::
በ2024ቱ የዓለም ኢኮኖሚይ ፎረም ላይ አርቲስቶች፣ በዋናነትም ሙዚቀኞችን የሀሳብ ፈጣሪዎች ተሳትፈው ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ ከጥበብ ኢንዱስትሪው ድንበር ላይ ለወረራ እያኮበኮበ ያለውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጉዳይን በተመለከተ ነበር:: በእርግጥ የአርቲስቶቹም ሆኑ የፈጠራ ሀሳብ አፍላቂያኑ እንቅስቃሴ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመቃወም ሳይሆን ‹እንዴት አብሮ ለመዝለቅ ይቻላል?› ዓይነት ማስታረቂያ መንገድ ፍለጋ ነበር:: ነገሩ ከኛ ዘንድ ገና ውሀውም ያልሞቀ በመሆኑ ምንም ላይመስለንና ወሳኝነቱን ላንገነዘበው እንችል ይሆናል፤ ባደጉት ሀገራት ዘንድ ግን በአሁኑ ሰዓት የከረረ አብዮት ውስጥ ናቸው::
የቴክኖሎጂውም የጥበብ ኢንዱስትሪውም መናኸሪያ የሆነችው አሜሪካ የውዝግቡ ዋና አደባባይም እርሷ ሆናለች:: ለርሷም ለዓለምም ትልቁ የፊልም መንደር የሆነው ሆሊውድ የኤ አይ ላብራቶሪም ጭምር እየሆነ መጥቷል:: በአንድ በኩል ጥሩ ሆኖ ሳለ በሌላ በኩል ደግሞ በተዋንያንና በሀሳብ አፍላቂያኑ ላይ ተጽእኖው ከፍ ያለ ሆኗል:: ሆሊውድን ጨምሮ በአሜሪካ የፊልምና የቴሌቪዥን መስኮቶችም የቀድሞ ተዋንያኑን ቦታ ኤ አይ ተተክቶ በርካታ ሥራዎችም ተሠሩ:: ተዋንያኑ ግን ይህን አሜን ብሎ ለመቀበል አልወደዱምና ቅሬታና አቤቱታቸውን ማስተጋባት ጀመሩ:: ቀጥሎም ለ118 ቀናት የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ:: በዚህ አድማ ምክንያት 6.5 ቢሊየን ዶላር ለማጣት ተገደዋል::
ከዚህ በኋላ ነበር የአሜሪካ የፊልምና ቴሌቪዥን መስኮት ተዋንያን ማኅበር (SAG-AFTRA) የአባላቱን ቅሬታ ይዞ ለድርድር የቀረበው:: ጉዳዩ ወደ ኢኮኖሚይ ፎረሙ መዝለቁ አልቀረም ነበር:: የSAG ዋና ተደራዳሪ የነበረው ዱካን ካርባትሪ በንግግሩ ውስጥ “ኤ አይ ለእኛ አስፈላጊ ነገር ነው:: ነገር ግን፤ እንዲህ ባለው የፈጠራ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሥራዎቻችን ሰዋሰው ተኮር የማናደርግና የነበረውን ነቅለን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን የምንተክል ከሆነ የምንሄደው የፈጠራ ሥራን ልብና ነብስ ወደማጣት ነው” ብሎም ነበር:: ከዚህ በተጨማሪ አርቲስቶቹን ያስቆጣው ጉዳይ፣ ከመሪ እስከ አጃቢ ተዋንያን ቦታ በኤ አይ ተወስዶ ወደ አውላላ ሜዳ እያመሩ እንደሆነ ስለታያቸው ነበር:: የቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች ግን በፈረንጆቹ 2045 በረቂቅነቱ የለየለትን ገና “አቫተር” የተሰኘውን ሮህቦት ስለማምጣት ያስባሉ:: በቅርቡ ከወደ ሙዚቃው መንደርም ዝነኞቹ ኒኪ ሚናጅ፣ ቢል ኤሊሽ እና ጆናስ ብራዘርስን ጨምሮ ወደ 2 መቶ የሚጠጉ ሙዚቀኞች ለኤ አይ ቴክኖሎጂ አበልጻጊዎችና በኤ አይ ቴክኖሎጂ ልዩ ልዩ የጥበብ ሥራዎችን ለሚሠሩ ጥሪ አድርገዋል:: ይህም ቴክኖሎጂው በሙዚቃ የግጥምና ዜማ ደራሲያን እንዲሁም በሌሎችም እያሳደረ ያለውን ጫና እንዲረዱት ለማድረግ ነበር::
ይህ ጉዳይ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ሰጥቶ ዘላቂ መፍትሄ እንዳይገኝለት ችግሩን ውስብስብ ያደረገው ደግሞ በእነዚሁ የጥበብ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ሆነው በተቃራኒው ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የሚደግፉ መኖራቸው ነው:: ኤ አይ ከሰው ልጆች በበለጠ ከስህተት የራቀ ነው:: ኤ አይ አንድን የጥበብ ሥራ ሲያከናውን በብዙ እጥፍ ከሰው ልጅ ይፈጥናል:: ብዙ የጥበብ ባለሙያዎች የሚያስፈልጉበትን ቦታ አንድ ሮህቦት ብቻውን ይፈጽመዋል:: ከገንዘብ አንጻር ለሰው ኃይል የሚወጣውን ወጪ ይቀንሳል:: ብዙ ነገሮቹ ምቾት አላቸውና ከላይ ሥራውን በባለቤትነት የሚያሠሩ ባለገንዘቦችና ሌሎችም ይህ እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ:: የእነርሱ ዓላማ ብዙ ገንዘብ፣ ብዙ ትርፍ ማግኘት እስከሆነ ድረስ የኤ አይ እጅ ስመው የማይቀበሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም:: ውዝግቡ እንዲህ ካለውም ጋር ጭምር ነው:: ማን አስታራቂ፣ ማንስ ዳኛ ይሁን?
ኤ አይ በኪነ ጥበብ ሥራዎች መነጽር ውስጥ፤ ምርጡን ተዋናይ ሆኖ ፊልም ቢሠራ አይገርመን ይሆናል፣ የራሱን ድምጽ፣ የራሱን መልክና ገጽታ ይዞ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ዝግጅቶችን ሲያቀርብም እንሰማውና እንመለከተው ይሆናል፣ ሙዚቀኛም ሆኖ ሲያቀነቅን መስማታችን አይቀርም:: ነገር ግን ደራሲ ሆኖ የርሱን መጽሐፍ ስናነብስ? አለም “ዊሊያም ሼክስፒር፣ ጀምስ ብሩስ” እንደምትለው፣ እኛም በሀገራችን “ሀዲስ አለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ፣ ስብሐት…” ብለን እንደምንጠራው ሁሉ ‹ሚስተር ኤ አይ›የሚሉት ደራሲ የሚመጣበት ጊዜው ሩቅ አይደለም:: አሁንም ቢሆን ጫፍ ጫፉን ይዞታል::
“በአርቲስት ሰዎች ያልተፈጠሩ ፈጠራዎች ጥበብ ነው ለማለት ይቻላል?” ሲል ገጹ ላይ ያሰፈረው ዘ ሀርቫርድ ጋዜጣ ነበር:: ጋዜጣው ባወጣው ጽሁፍም ከታዋቂው የአጫጭር ታሪኮች ጸሀፊና የልቦለድ ደራሲ፣ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር የሆነውን ዳፍን ካሉታይን፣ ኤ አይ በሥነ ጽሁፍ ምን አንደምታ ሊኖረው እንደሚችል ጠይቆትም ነበር:: “በበኩሌ ኤ አይ በሰው ልጆች የሚጻፈውን ያህል በጥሩ አጻጻፍ ይከውነዋል ብዬ አላስብም:: በሰው ልጅ የሚጻፉትን መሳጭ እንዲሆኑ የሚያደርጉት ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ:: አንደኛ/ ደራሲያን ዓለምን የሚመለከቱበት ልዩ እይታ ነው:: ሁለተኛ/ የቋንቋዎቹ ቱባነት ነው:: ሦስተኛ/ በሰው ልጆች ብቻ ሊገለጹ የሚችሉ ከባህሪ፣ ከልምድ፣ ከሁኔታዎችና አጋጣሚዎች የሚገኙ ዝርዝር ነገሮች አሉ:: እናም በኤ አይ የተጻፉ ነገሮች ቢኖሩም እስካሁን እነዚህን ሦስት ነገሮች ማምጣት ግን አልተቻላቸውም” በማለት ይገልጻል:: ዛሬም ሆነ ነገ ኤ አይ መጻሕፍትን ጽፎ የማሳተም አቅም ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በታሪኮቹ ውስጥ ሥነ ጽሁፋዊ ስሜቶችን ከመፍጠር አንጻርም የሚሆንለት አይመስልም::
ታዲያ ይህ ሁሉ ለኛ ምናችን ነው? ከዚህ ሁሉ ጀርባ ልንማረው የሚገባ ቢያንስ አንድ ነገር አለ፤ ግን ምን? የኤ አይ ሮህቦቶች ብቻ ሳይሆኑ ራሷ ዓለም እየሄደች ያለችበት መንገድ አንዱን ከሌላው ደምስር ለመቅዳት ከሚደረግ የአልጎሪዝም ሥርዓት ጋር ነው:: የአኗኗር አልጎሪዝም፣ የፖለቲካ አልጎሪዝም፣ የኢኮኖሚ አልጎሪዝም፣ የእርምጃዎች ሁሉ አልጎሪዝም…ማላመድ፣ መለማመድና መላመድ ነው:: ስለዚህ ዓለም እያስተናገደቻቸው ያሉ እያንዳንዱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ነገ ወደኛ የሚመጡ ናቸው:: ሲመጡ ግን በምን መልኩ ተቀብለን፣ እንዴትስ ነው የምናስተናግዳቸው? የጥበብ ኢንዱስትሪዎቻችንስ ስለነገ ምን ያስባሉ?
የነበረንና ያለንን ማወቅ፣ የሚያስፈልገንን ደግሞ ከሁለቱም መቀመር ግዳችን ነው:: አሊያ ግን ነገር ለማቅለል ያልነው እኛኑ ያቀለናል:: የጎሪጥ ያየነውም በአፍጢም ይደፋናል:: ከዚያ ይልቅ ምን ዓይነት ነን፣ ምንስ ዓይነት ይበጀናል? ማለቱ ነው ጥሩ:: በዘመናዊው የሙዚቃ ቅንብር ውስጥ ለመድረክ የሚያቅር ድምጽ ሁሉ በቴክኖሎጂ ተሞርዶ ሲወጣ እንኳን ለምንተች ለኛ፣ እንዴት ነው የድምጻዊውን ‹የሚስተር ሮህቦትን› ሙዚቃ የምናጣጥመው? የማኅበረሰባችን የአኗኗር ዘዬ ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው:: ውበትን የሚለካው እንኳን በተፈጥሮ እይታ ውስጥ ነው:: ለዛም ነው እኮ…‹አፈሩ፣ ወንዙ፣ ተራራ ሜዳው፣ ጋራ ሸንተረሩ…› ከማለት አልፈን የሰውን ልጅ ውበት ለመግለጽ እንኳን ‹የዘንባባ ማር፣ የጥንቅሽ ፍሬ፣ ሎሚ ብርቱካን መሳይ፣ ሩብ ግማሽ ጨረቃ…› ማለት የምናዘወትረው::
ለሀገራችን የጥበብ ኢንዱስትሪ ኤ አይ ያስፈልገናል:: ባንፈልገውም መምጣቱ የማይቀር ነው:: ጥያቄያችን መሆን ያለበትም ስለ አስፈላጊነቱና አላስፈላጊነቱ ወይንም ስለ መምጣቱና ስላለመምጣቱ ሳይሆን፤ ስለሚመጣበት መንገድና የአስፈላጊነቱን መጠን ስለመመጠን መሆን አለበት:: ጣፈጠ ተብሎ ስኳርን ቢሞጅሩት አያስጠጣም፤ አያስበላም:: በራሳቸው ባደጉ ሀገራት ዜጎች ውስጥ እንኳን ስጋትን የፈጠሩ ጉዳዮች እንደኛ ሲሆን ደግሞ የባሰው የእቶን እሳት ነው:: የራሱ የሆኑ የጎንዮሽ ችግሮች ቢኖሩም ኤ አይ በሕክምናው ዘርፍ የሚያስፈልገንን ያህል ለጥበብ ኢንዱስትሪ እናውለው ብንል ቀጥሎ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነትና ውጤት አንድ አይሆንም:: ለሳይንስና ፈጠራ በዘገነው መጠን ለጥበብ እናድርገው ካልን ድሮም ‹መንገድ መንገድ›ያሰኘው ኪነታችን ‹እልም በባቡሩ› ማለቱ ነው:: ለዓለምም ሆነ ለኛ፤ የኪነ ጥበብን ልጓም ለአርቴፊሻል ኢንትለጀንስ መስጠት፣ ውስጡ ያለውን የሰው ኃይል እንጀራውን የማሳጣት ጉዳይ ብቻ አይሆንም:: ነገን ግን ሳትቆምርብን ዛሬ እንቀምራት
በሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም