
ዜና ትንታኔ
መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንዲሁም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማዳበር ባወጣው መመሪያ መሠረት አስፈላጊውን መስፈርት ላሟሉ አምስት ባንክ ላልሆኑ የግል ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛትና በመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሪ በማመቻቸት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ለማስፋፋት የሚረዳ ሚና እንዳላቸው በመመሪያው ላይ ተመላክቷል።
የውጭ ምንዛሪ ግኝት አማራጭን ከማስፋት እና በጥቁር ገበያውና በመደበኛው ገበያ መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ ልዩነት ከማጥበብ አንጻር የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እያበረከቱ ያለውን ፋይዳ በሚመለከት የኢትዮ ፎሬክስ ቢሮን እና የሀሮን ፎሬክስ ቢሮን አነጋግረናል።
የኢትዮ ፎሬክስ ቢሮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ኢትዮ ፎሬክስ መስከረም 27 ቀን 2017ዓ.ም የመጀመሪያ ቢሮውን በኢትዮጵያ ሆቴል ከፍቷል፤ በአሁኑ ጊዜ አራት ቅርንጫፎች አሉት፤ ለ16 የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችም የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡
የጥቁር ገበያ ገንዘብ የሚመነጨው ከጥቁር ኢኮኖሚ ነው። ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች፣ ኮንትሮባንዲስቶች፣ ሕገ-ወጥ መድኃኒት አስመጪዎች እና ሀብት የሚያሸሹና ግብር የሚሰውሩ አካላት የጥቁር ኢኮኖሚ ተዋናዮች ናቸው። እነዚህ አካላት በሌላ የሕግ ማሕቀፍ መስመር እስካልተያዙ ድረስ ተጽዕኗቸው ቀጣይነት ይኖረዋል ይላሉ። ከባንኮች ጋር ሄዶ የውጭ ምንዛሪ ያጣ ሰው በቀላሉ ከኢትዮ ፎሬክስ ማግኘት ይችላል። በተለይ ከባንክ የተሻለ ምንዛሪ መኖር፣ ሰዎች ከጥቁር ገበያው ተቀራራቢና ሕጋዊ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቻላቸው ቢሮውን ተመራጭ ማድረጉን ገልጸው፤ በየእለቱ የቢሮ የገበያ ድርሻ እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮ ፎሬክስ ባለፉት ሰባት ወራት ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ አንቀሳቅሷል። በእዚህም ከ17 ሺህ 500 በላይ ደንበኞች መስተናገዳቸውን አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፤ ይህ የሚያሳየው በፊት በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙና የሚመነዝሩ ሰዎች ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እየመጡ መሆኑን ነው። ይህን ማጠናከር ከተቻለ ከተወሰነ ዓመታት በኋላ ጥቁር ገበያ ምናልባት ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ አቶ ኤፍሬም ያስረዳሉ፡፡
የውጭ ምንዛሪ ቢሮው አሠራር ቀልጣፋና የክፍያ ሥርዓቱ በደንበኛ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ ባንኮች ደንበኝነትን እና የቁጠባ ደብተርን የሚጠይቅበት ሁኔታም እንደሌለ አቶ ኤፍሬም ይገልጻሉ፡፡
ቢሮው ሰባቱንም ቀን 24 ሰዓት የሚሠራ መሆኑም ለተጠቃሚዎች ጥሩ እድል እንደሆነና ይህም የጥቁር ገበያን እንቅስቃሴ ለማቆም የሚረዳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጥቁር ገበያ ሙሉ ለሙሉ ላይጠፋ ይችላል ያሉት አቶ ኤፍሬም፤ ይሁንና ቀደም ሲል በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያሳድር የነበረውን ተጽእኖ እንደሚቀንስ አስረድተዋል፡፡
አሁን በመደበኛው ገበያው እና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን የተረጋጋ ነው። ይህም በፍላጎት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የምንዛሪ ተመኑ እንደሁኔታው ሊጨምርና ሊቀንስ ይችላል። የጥቁር ገበያ ተዋናዮች ወደ መደበኛ ሥርዓት ሲገቡ በሁለቱ ገበያዎች ያለውየሀሮን ፎሬክስ ቢሮ ዳይሬክተር አቶ መሳይ ሲሳይ በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ባንክ ያደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ገበያ መካከል ያለው ልዩነት ተቀራራቢ እንዲሆን አድርጓል። ይህም አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረገና የሕገ ወጥ ምንዛሪ ሥርዓቱን ያደናቀፈ መሆኑን ገልጸዋል።
ጥቁር ገበያው ሕጋዊ አይደለም፤ ደረሰኝ አይሰጥም እንዲሁም ደግሞ የደህንነት ጥያቄ ያለበት ነው። ነገር ግን አንድ ሰው ጥቁር ገበያውን ትቶ በውጭ ምንዛሪ ቢሮ ቢስተናገድ ሕጋዊ ደረሰኝ እና ከጥቁር ገበያው የማይተናነስ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማግኘት ይችላል። ከእዚህም በላይ ገንዘቡን ወዲያውኑ ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ሥራ መጀመር ለምንዛሪ ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄደውን ሰው ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እያስገባ መሆኑን የገለጹት አቶ መሳይ፤ አሁን ላይ ጥቁር ገበያው እየተዳከመ መምጣቱንም ጠቅሰዋል፡፡ ሰዎችም በውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እየመነዘሩ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ የውጭ ምንዛሪ ገበያው የተረጋጋ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የሀሮን ፎሬክስ ቢሮ ባለፉት ሰባት ወራት ከበርካታ ሰዎች የውጭ ምንዛሪ እንደገዛና ለብዙዎችም እንደሸጠ የተናገሩት አቶ መሳይ፤ ይህንን አገልግሎት ለማግኘት ፓስፖርት፣ ቪዛና የጉዞ ደረሰኝ አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዶላር የሚሸጥ ሰውም መታወቂያ መያዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም