
አንዲቷን ጣፋጭ የሙዚቃ ስንግ ለማጣጣም የበቃነው ምናልባትም በምንም ትዝ ሊሉን የማይችሉ ብዙዎች ደክመውበት ነው። ከዚህቹ አንዲት ሙዚቃ ጀርባ የምናውቃቸውም፣ የማናውቃቸውም ጥበባቸውን አዋጥተውበታል። ተጨንቀው፣ ተጠበው፣ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ የምናደንቀውን፣ የምንወደውን እውቁን ድምጻዊ ሠርተውታል። በልተን የማንጠግበውን፣ አጣጥመን የማንረካውን ሙዚቃ እንካችሁ ብለውናል፤ ከድምጻዊው ድምጽ ውስጥ ሆነው። ስንቶች ግን ከምንወደው ሙዚቃ ውስጥ እኚህን ድምጾች እንሰማለን? ከምንወዳቸው ሙዚቃዎች ጀርባ የማናስተውላቸው፣ ያልሰማናቸው ብዙ ድምጾች ይገኛሉ። ይህን እንደ ሳንድዊች ግምጥ የሚደረግ ግጥምን ማንስ ጻፈው? የአዕዋፋት ዝማሬን የሚያስታውስ ውብ ዜማ ማንስ ቀመረው? የውስጥ ስሜትን የሚፈነቅሉ የሙዚቃ መሣሪያ ድምጾች በማንስ እጅ የተዳሰሱ ናቸው? እንደ ወተትና ስኳር የተዋሃደ፣ እንደ ውሃና ማር ተቀይጦ ብርዝን የሠራ ያህል በአንድነት ኩልል ብሎ እንዲወርድ ያደረገ የሙዚቃ አቀናባሪስ የትኛው ነው?
ከዛሬ ሠላሳና አርባ ዓመታት በፊት ተሞዝቀው እያደር እንደወይን ጣፍጠው ዛሬም እልፍ የሙዚቃ ዓይነቶችን እናጣጥማለን። ታዲያ ግን “…እስቲ በዚያን ጊዜ እነማን ነበሩ?” መቼም ድምጻውያኑን መጥራት ለአብዛኛዎቻችን ቀላሉ ነገር ነው። ከባዱ ነገር ግን ‹የዚያን ሰው ሙዚቃ ማን ሠራው፣ ማንስ አቀናበረው?› የምትለዋን ጥያቄ የሚመልስን ሰው ማግኘቱ ላይ ነው። ገጠር ከተማው ላይ “ፈልጌ አስፈልጌ…” እያሉ በዘፈን የዚህን ዘፈን ጠማቂ የሚነግረን ብናጣ “ምን ታደርጊዋለሽ” ብሎ “ችሎ ማለፍ ጥሩ” ነው። እንዲያም ይሁን እንዲህ ግን “መርሳት አይገባም” ይለናል የዛሬው ዝነኛችን። ከላይ በተጣቀሱት አንዳንድ ሙዚቃዎች ውስጥ ጥላሁን ገሠሠ ቢዘፍን ከጀርባ ግን ብቻውን እንዳይመስለን። ያለው ማሩን ለሙዚቃ ጠጅ፣ ማሩን ለብርሃን ጧፍ እያደረገ የምንወዳቸውን ብዙ ድምጾች የሠራው ኦርጋኒስት፣ አቀናባሪው ሻለቃ መላኩ ተገኝ ነው።
ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ በወጡ በአብዛኛዎቹ ልብ አርስ ሙዚቃዎች ውስጥ ሻለቃ መላኩ አለ፤ ቅሉ ስለመኖሩ እምብዛም ባይታወቅም። ዛሬ እንደዘበት የምናጣጥማቸውን ሙዚቃዎች ለማስደመጥ ሲል ምናልባትም ብዙ ሌት ማዕልትና ንጋት ራሱን ጥሎ ነበር። ምናልባትም ደግሞ እንቅልፉን ብቻ ሳይሆን ጤናውንም አጥቶ ጭምር። ‹ወርቃማው ዘመን› ከምንለው ውስጥ ለሙዚቃ ነብስን ሲዘሩ ከነበሩት መካከል ሻለቃ መላኩ አለ። የምንወዳቸውን ብዙዎችን ያደመጥነው በዋዛ ሳይሆን ከአንደኛው ጅምር ሴኮንድ እስከ መጨረሻዋ ድረስ በእያንዳንዱ እንጥፍጣፊ ሴኮንድ ውስጥ የአቀናባሪው ጠብታ አለበትና እርሱን አለማሰብ ከንፍገትም የባሰ ነገር አለው። ፍለጋ በወጣንበት የዚያን ዘመን የሙዚቃ አቀናባሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ሻለቃ መላኩ ተገኝ የሌለበት እንደሆን ‹ያልተሳካ ፍለጋ› ቢባል ስህተት አይሆንም።
“አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ
በዘፈን አንደኛ ጥላሁን ገሰሰ” ያስባለና እንዲባል ምክንያት የሆነው ሻለቃ መላኩ፣ ሌላኛውን የሙዚቃ ነበልባል “እሳቱ ተሰማ፤ ድምጹ የተስማማ” አላስባለም እንዴ? እንዲያው ለነገሩ እንጂ እርሱ በስም ላይ ስም ያላስደረበለት ማን አለና…ወንዶቹንም ሆነ ሴቶቹን ድምጻውያን በሥራው ስራቸውን ከማይረሳ የጥበብ አፈር ጋር አስማምቶ አጣብቆታል። ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ባለው ብቅ ያሉትን ዛሬም የምንዘምራቸውን ስሞችና ዛሬም የምናዜማቸውን ሙዚቃዎች አስጊጦ ሰጥቶናል። ግጥም ከዜማ፣ ምቱን ከጨዋታ አዋዶ የሠራቸው ሙዚቃዎች ሁሉ እያደር እንደወይን መጣፈጥ ይዘው አሁንም ልንጠግባቸው አልቻልንም። ‹የወርቃማው ዘመን ወርቃማ ትሩፋቶች› ከዘመናት በኋላም እንደተትረፈረፉ ናቸው።
ከጥላሁን ገሠሠ እስከ ታምራት ሞላ፣ ከማህሙድ አህመድ እስከ ብዙነሽ በቀለ፣ ከመስፍን ከበደ እስከ ጥላዬ ጨዋቃ፣ ከሀምሳ አለቃ ሲሳይ ገሠሠ እስከ ዓባይ በለጠ… ዘርዝረን የማንችላቸው አንጋፋ ድምጻውያን ዙሪያ ሞልቶ የሚታይ አንዱ ሻለቃ መላኩ ነበር። አውጥቶ አውርዶ፣ ደምሮ ቀንሶ፣ ከላይ ታች እየቀመረ ሙዚቃዎቻቸውን እያዋደደ የሙዚቃን ጥበብና ውበት በደማቁ ያሳየ የዚያን ዘመን ምርጥ አቀናባሪ ነበር።
በ1937 ዓ.ም የተጀመረው የሻለቃ መላኩ ሕይወት፣ ከልጅነት እስከ ዕለተ ሞቱ ከሙዚቃ ተለይቶ አያውቅም ነበር። ከሙዚቃ ጋር ቁርኝት የፈጠረው ገና በ12 ዓመት ዕድሜው ነበር። ‹አቀናባሪ› ወይንም ‹ኦርጋኒስት› የሚለውን የሙያ ማዕረግና ችሎታውን ያገኘው የኋላ ኋላ ቢሆንም፤ የልጅነት ሕይወቱ ግን ከሙዚቃ መሣሪያዎች ንክኪና እንጉርጉሮ ጋር አብሮ ያደገ ነው። የሙዚቃ መሣሪያዎቹን ባገኘበት አጋጣሚ ሁሉ በጣቶቹ እየዳሰሰ፣ በድምጹ የማንጎራጎር ልምድ ነበረው። ከሁሉም የሙዚቃ መሣሪያዎች ለኪቦርድ የነበረው ፍቅር ይለያል። ከአንጋፋዎቹ ጀርባ አቁሞ ምን ጊዜም የማይረሱት ዝነኛ ሙዚቀኛ ያደረገው የቅንብር ሥራው ይሁን እንጂ ለብዙ ጊዜ ያሳለፈበትና ለዚህ ደረጃ ያበቃውም ይኸው የኪቦርድ ተጫዋችነቱ ነው። ለሻለቃ መላኩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም አቀናባሪዎች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ኪቦርድ ባለውለታው መነሻቸው ነው።
ጎበዝ የኪቦርድ ተጫዋች ናቸው የምናላቸው፣ ጎበዝ የሙዚቃ አቀናባሪ ሆነው የምናገኝበት አጋጣሚ የሰፋ ነው። ምክንያቱም ከየትኛውም የሙዚቃ መሣሪያዎች ኪቦርድ ተጫዋችነት በባህሪው ከቅንብር ጋር የሚመሳሰልና ተያያዥነትም ስላላቸው ነው። በአንድ የመድረክ ሙዚቃ ላይ ከጅምር እስከ ፍጻሜው፣ የድምጻዊውን ድምጽ ጨምሮ ሁሉንም የሙዚቃ መሣሪዎችን እየመራ አንድ ውህደት በመፍጠር የባንዱን ሙልእነት የሚሠራው ኪቦርዲስቱ ነው። እያንዳንዱን ጠብታ ምጣኔ የሚወስነው እርሱ ነውና ለአቀናባሪነቱ ወሳኝ የሆነውን የሰላ ጆሮና የሙዚቃ አሠራር ጥበብን እንዲይዝ ያደርገዋል። ለአንድ አቀናባሪ ኪቦርድ መነሻው ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም ከአቀናባሪው ፊት የማይጠፋ መዳረሻውም ጭምር ነው። ኪቦርዲስቱ ሻለቃ መላኩ ተገኝ በአቀናባሪነት ተገልጦ እኚያን ሁሉ ግሩም የሙዚቃ ሥራዎችን እንዲያበረክትልን መነሻ የሆነለትም፣ እንዲህ ባለ መልኩ የተጓዘበት መንገድ ነው። ሙዚቃን ከመጫወት ባለፈ ሳይንሱንም ጠንቅቆ የሚያውቅና በአንድ ወቅት የሙዚቃ አስተማሪ የነበረም ጭምር ነው። በእነዚህና በሥራ ልምዶቹ ያገኛቸው ግብአቶቹ ተደማምረው፣ አንድ የሙዚቃ አቀናባሪ ሊያውቃቸውና ሊያልፋባቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ ብቁ ባለሙያ ያደርጉታል።
ሁለቱ ወርቃማ ባንዶች (የክብር ዘበኛ እና የፖሊስ ሠራዊት) በሁለት ጎራ እሳት አንድደው የተፈታተሹበትን ወርቃማውን ዘመን ከማምጣታቸው ጀርባ የአቀናባሪዎቹ አቅምና ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ከአየለ ማሞ፣ እና ከኮለኔል ሳህሉ ደጋጎ በነበረው በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ ሻለቃ መላኩ ተገኝ የፍልሚያ ሜዳው ድምቀት ነበር። የመድረክ ካልሆነ በስተቀር በባንዶቹ ለሚሠሩ ነጠላም ሆኑ ካሴቶች፣ አቀናባሪዎቹ የአንበሳውን ድርሻ ይዘው ይሰለፋሉ። የችሎታቸው ወሳኝነት ደግሞ አያጠያይቅም። እናም የክቡር ዘበኛን የኋላና የፊት መስመርን ድንቅና ውብ አድርገው ከሠሩት የጊዜው ፈርጦች መካከል ሻለቃ መላኩ ግንባር ቀደሙ ነው።
ኦርጋኒስቱ ትልቁን ሙዚቃዊ ጥበቡን ያገኘበትና ታላቅም ሆኖ የታየው በክብር ዘበኛ ቤት ውስጥ ነበር። ለበላይነት በወዲህና በወዲያ ተወጥሮ የነበረው ገመድ መስፈንጠሪያ ከሆናቸው መካከል አንዱ ሻለቃ መላኩ ነው። ትንቅንቁ እሳት ቢመስልም፣ እሳቱ ግን ፈትሾ ብዙ ወርቆችን አውጥቷል። ለመላኩ የችሎታው ማዳበሪያና የብቃቱ ማሳያ ነበር። ከክቡር ዘበኛ ከወጡ ወርቃማ ሥራዎች ጋር አብሮ እርሱም ብቅ አለ። በክብር ዘበኛ ውስጥ ከነበሩ ድምጻውያን መካከል ምርጡን በመሥራት ችሎታውን በኩራት ያሳረፈበት የመጀመሪያው ጥላሁን ገሠሠ ነበር። በችሎታው የጊዜውን ታላቁን ድምጻዊ አሳምኖ፣ በእርሱ ድምጽ ውስጥ ራሱን መግለጥ መቻል ለመላኩ ትልቅ ስኬት ነበር። ከሁሉ የሚበልጠው ስኬት ደግሞ ያቀናበራቸው ሙዚቃዎቹ ከአድማጭ ዘንድ ሲደርሱ እልል! የተባለላቸው መሆናቸው ነበር። ከእኚሁ የጥላሁን ገሠሠ ሥራዎችም “የ13 ወር ጸጋ” በተሰኘው አልበም ውስጥ ገኖ የወጣው የሻለቃ መላኩ ስም ከሁሉም በተለየ ነበር። “ፈልጌ አስፈልጌ” እና “ምን ታደርጊዋለሽ” ደግሞ ሌላኛዎቹ የዝና ካቦርቶች፣ የክብር ጋቢዎቹ ናቸው።
አቀናባሪው ሻለቃ መላኩና የክብር ዘበኛ የፊት ድምጻውያን ተያይዘው፣ የሙዚቃ ደምስራቸውን አያይዘው የወርቁን እሳት አቀጣጠሉት…”ጭንቅ ጥብብ” የተሰኘውን የብዙነሽ በቀለን ካሴት አስደመጡ። በአድማጩ ዘንድም “እንዳንቺ አላየሁም” የተባለችበት የሚመስለውን ይህንን ሥራም በትዝታው አባት፣ በማህሙድ አህመድ ድምጽ ተደመጠለት። “ቀበጥባጣ ወጣት”፣ “አለሙሽ አሰቡሽ” በሲሳይ ገሠሠ ተፋፍሞ በዓባይ በለጠ እና በሌሎችም ሥራዎች ውስጥ ‹መላኩ አበጀህ!› ተባለለት። ሻለቃው የሙዚቃ ቡልኮውን ደርቦ፣ በአቀናባሪነትና በኪቦርዲስትነት ረዥም ዓመታትን ያሳለፈው በክብር ዘበኛ ቤት ውስጥ ይሁን እንጂ፤ የታየባቸው ስፍራዎች በርካታ ናቸው። በሐረር ሦስተኛ ክፍለ ጦር የሙዚቃ ክፍል ውስጥ ኦርጋኒስቱ መላኩ ታይቷል። የምድር ጦር የሙዚቃ ክፍልም ችሎታውን ለክቶ ካሳየባቸው መካከል አንደኛው ነው። ከእነዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ በኢትዮ-ስትሪንግ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ሙዚቃን በመጫወት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ያካበተውን ልምድና ተሞክሮውን ለወጣት ሙዚቀኞች በማቋደስም ጭምር ከ15 ዓመታት በላይ ዘልቋል። ሙዚቀኛውን፤ ኦርጋኒስት፣ ኪቦርዲስት ሻለቃ መላኩ ተገኝን ያፈራች ግን ‹የክብር ዘበኛ ናት› ይባልላታል።
ሻለቃ መላኩ ተገኝ የድምጻውያኑን በማቀናበር ብቻ ሳይሆን፣ የራሱን ረቂቅ ሙዚቃዎች በማስደመጥም የሚያስደምም ነበር። ነፍሱ ከሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር በፍቅር የወደቀች ነበረችና ድፍን 16 ዓመታትን ውሎ አዳሩን ከእነርሱው ጋር ብቻ አድርጎ ኖሯል። በወቅቱ ቫዮሊናቸውን ይዘው ሲያጅቡትና አብረውት ሲጫወቱ የነበሩትም ፀሐይ ተስፋዬ፣ ፍቅርተ ተሰማ እና ሠናይት ደጀኔ የተባሉት ሦስቱ የቫዮሊን ተጫዋቾች ናቸው። ከሦስቱ ሴቶች በተጨማሪ ባለ ሳክስፎኑ ጴጥሮስ የሻለቃ መላኩ አራተኛው ረዳት ነበር። ከእነዚሁ ጋር ተጣምሮ የቆየባቸው ጊዜያት የራሱን አዳዲስ ሥራዎች በመፍጠር የተጠመደባቸው ነበሩ። ከሌላ የሙዚቃ ግብሮቹ ገለል ብሎ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በመጫወትና ልሳን አልባ ቅንብሮችን በመፍጠር ቆይቷል። በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበሩ አምስት አልበሞችንም ማስደመጥ የቻለ ነው። “ቀበጥባጣ” ፣ “ትዝታዬ ነሽ” ፣ “ምነው ተለየሽኝ”፣ “እንዳንቺ አላየሁም”፣ “ልቤ ደጅ ይጠናል”፣ “ቦቡ ፍቅርሽ” እና “ችሎ ማለፍ ጥሩ” በጣም ከመተወደዱለት ብዙ ሥራዎቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው። እንዲያውም አንዳንዶች “ቦቡ ፍቅርሽ” የሚል ቅጽል ስም ይሰጡታል።
በ1970ዎቹ የነበረው የሻለቃው የሙዚቃ ሕይወት ገሚሱ በቅንብር፣ ገሚሱ ደግሞ ከእስካሁን በተለየ መንገድ ድምጻዊነትም የተቀላቀለበት ነበር። የሌሎችን ግጥምና ዜማ አዋዶ ሙዚቃን እንደሠራላቸው ሁሉ፣ የራሱን ግጥምና ዜማ ፈጥሮ የራሱን ሙዚቃም አስደምጧል። ከሠራቸው ሙዚቃዎቹ ውስጥም “መርሳት አይገባም” እና “መዓዛ መዓዛ” የሚሉት ሁለቱ ተጠቃሾች ናቸው። በኢትዮ-ስትሪንግ ባንድ ውስጥ ደግሞ “ሰው ማማት አልወድም” የምትል አንዲት ነጠላ ዜማ ተቀነባብራለታለች።
1983ዓ.ም አብዮቱ ጓዙን ጠቅልሎ ከስልጣን ሲወርድና ሌላኛው ሲወጣ አብረው ላይና ታች የሆኑ ነገሮች ብዙ ናቸውና ለውጡ በሻለቃ መላኩም ዘንድ ነበር። ጥበብን የያዘ በለውጥም ሆነ በነውጡ የሚጨመርለት ወይንም የሚቀነስበት ባይኖርም በአጋጣሚዎች የዚህ አካል መሆን ግን ያለ ነው። ቅሉ በዚህ ባይሆንም ሻለቃ መላኩም ከቅንብር ሥራው ወደ መጀመሪያው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነቱ ብቻ ገባ። በአንድ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ቦታዎች እየተገኘ ከአመሻሽ ጀንበሩ ፊት ይቆም ነበር። በጣይቱ እና በኢምፔሪያል ሆቴል ኪቦርድ በመጫወት ጥሩ የሚባል ጊዜ አሳልፏል። እንዲሁም በጋዜቦ እና በለንደን ካፌ ያንኑ ውብ የሙዚቃ አጨዋወቱን ደግሞባቸዋል።
ከሙዚቃ ሕይወቱ ጀርባ ሻለቃ መላኩ ተገኝ ከአሥር አለቃ አልማዝ መንገሻ ጋር የውትድርናን ግንባር ብቻ ሳይሆን የትዳር ጎጆውንም ቀልሶ፣ የአብራካቸውን ሦስት ልጆችንም ስመዋል። ሦስት የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል። ከመካከል አንዱንም የእነርሱን ባንዲራ አስይዘው ዱካ ፈለጋቸውን አስከትለው ነበር። ይሁንና ሀገር በመስዋዕት የምትቆም የሰማእታት አደባባይ ናትና ይህንኑ ጽዋ ጠጥቷል። የሻለቃው ቤተሰብ በሙዚቃውም ኢንዱስትሪ፣ በጦሩም አውድማ ለሀገሩ መስዋዕት ሆኖ የኖረ ድንቅ ቤተሰብ ነው። በየዘርፉ ሀገራዊ ተጋድሎ ካደረጉና እያደረጉ ካሉ ጥቂት ቤተሰቦች መካከል ምናልባትም አንደኛው ይህ ቤተሰብ ነው። “የምኮራበት ትልቁ ታሪኬ ይህ ነው። ሁሌም ደስተኛ ነኝ። ለሀገሬ ከነቤተሰቦቼ ዋጋ ከፍያለሁ፤ አሁንም ከሀገር በላይ ለኔ ምንም የለም” በአንድ ወቅት የሻለቃው ባለቤት አሥር አለቃ አልማዝ ያለችው ነበር።
“የማያልፉት የለም፤ ያ ሁሉ ታለፈ…” የሚባል ብዙ ነገር ቢኖርና ቢባል ቅሉ የማያልፉት ደግሞ አንድ ነገር አለ፤ እርሱም የሰው ልጆች መጨረሻ የሆነው ‹ሞት› ነው። ሁላችንም ሟቾች ብንሆንም፣ ሁላችንም ግን የምንሞተው አንድ ሞት አይደለም። ሁላችንም ካለመኖር ወደመኖር መጥተን ተወልደናል። ነገር ግን የአብዛኛዎቻችን ሞት ከመኖር መልሰን ወደ አለመኖር እንሄዳለን። እንደ ሻለቃ መላኩ ተገኝ ያሉ ጥቂቶች ደግሞ፤ ሲሞቱ የሚሄዱት ከመኖር ወደ ሌላ መኖር ነው። ከስድስት ዓመታት በፊት ሞት በሻለቃው ኦርጋኒስት የሆነው እንዲሁ ነበር። ሻለቃ መላኩ ተገኝ ለብዙ ጊዜያት በፍቅር ክሊኒክ ውስጥ ነበር። የክሊኒኩ የዕለት ተዕለት አብይ ግብርም እርሱን መርዳት፣ ስጋውን ማከም፣ ነብሱን ማቆየት ነበር። አፍጥጦ ከመጣው እርጅና ጋር የገጠመው የጤና እክል ግን ለመሻር አዳጋች እየሆነ ሄደ። ሞት የማያልፉት ሆነናም ጥር 24 ቀን 2012ዓ.ም ልክ ከሌሊቱ በ9 ሰዓት የእስትንፋሱ ቃጭል እየደወለች ከማሰሪያው ላይ ተበጠሰች። የዘለዓለም ዕረፍትን አደረገ። ከ55 ዓመታት በላይ ለሙዚቃ ደክሞ፣ በ75 ዓመቱ ሞተ።
የሻለቃው የሕይወት አጨራረስ ጥሩ የሚባል አልነበረም። ለ55 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጠብ እርግፍ እያለ ዘመን አይሽሬ ሥራዎችን እንዳበረከተ ሰው ሳይሆን፤ ምንም እንዳልሠራ እንደዘበት ቸል ተባለ። በሕይወቱ መጨረሻ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱ እንዳለፈም የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታዎች መመልከት ቅስምን የሚሰብር ነበር። እንኳንስ ሳር ቅጠሉ ጭንቅላቱን በሀዘን እየወዘወዘ ለሚሰናበተው እውቅ ሰው ይቅርና ለተራውም ግለሰብ ቢሆን ቀብሩን በማድመቅ የማንታማ ቢሆንም፤ የሻለቃ መላኩ ግብአተ መሬት የተፈጸመው ከ50 በማይዘሉ ሰዎች ነበር። የሆነው በወቅቱ በነበረው ወረርሺኝ ሳቢያ ነው እንበለውና ስለ አኗኗሩና አጨራረሱ ግን እዳ አለብን።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም