ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት የሁነት ዝግጅቶች ሚና

ቱሪዝም ለአንድ ሀገር ብሔራዊ አርማ ተደርጎ የሚታሰቡበት ዘመን ላይ ተደርሷል። ከሁለንተናዊ ፋይዳው አንጻር ሲቃኝ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የቱሪዝም ዘርፉን ከማሳደግ አኳያ ብዙ ሥራ ተሰርቷል። ከነዚህ ሥራዎች መካከል የሁነት ዝግጅት አንዱ ነው። ይሄን አስመልክቶ በቱሪዝም ሚኒስትር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ሁነቶች ሲዘጋጁ እየታየ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን እንድታስተናግድ የሆነችው ምን ብትሠራ ነው? የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው የሚከተለውን ብለውናል። ዓለም አቀፍ ሁነቶች ከአንድ ሀገር የሚፈልጉት ብዙ ነገር አለ። ከዚያ ውስጥ መሰረተ ልማት አንዱ ነው። ለአብነት አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬክሽን፣ አድዋ መታሰቢያ ሙዚየም፣ እንደስካይ ላይት ያሉ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሆቴሎች እንዲሁም መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ሀገሪቷን ለዓለም አቀፍ ሁነቶች ተመራጭ እንድትሆን እንዳደረጓት አብራርተዋል።

በመንግስት፣ በግል ባለሀብቶች እና በከተማ መስተዳደሩ እየተሠሩ ያሉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች፤ በተለይ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ አይነተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን አንስተዋል። እነዚህ ቀድመው ከነበሩ ትላልቅ ሆቴልች እና መሰረተ ልማቶች ጋር ተዳምረው ኢትዮጵያ እንደሀገር አዲስ አበባ ደግሞ እንደ ዋና ከተማ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ቀጣናዊ እና አለም አቀፋዊ ሁነቶችን እንዲያስተናግዱ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

በእዚህ ዓመት እስከ አሁን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን አንስተው፤ በበጀት ዓመቱ ከዘጠና በላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶች መስተናገዳቸውን ጠቁመዋል። የሁነቶቹ ይዘት እንደሁነቱ አይነት በተሰብሳቢ ደረጃ የተለያዩ መሆናቸውን የጠቆሙት ሃላፊው፤ አንዳንዶቹ እስከ ሁለት ሺ ሰዎች ሲገኙበት የቀሩት ከዛ በታች እንግዶች የተገኙበት እንደሆነ አንስተዋል።

በዚህ የሁነት ዝግጅት እና በተሠሩ ሌሎች ሥራዎች እስከ አሁን ምን ያህል ቱሪስቶች በሀገሪቱ እንደተስተናገዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ስራ አስፈፃሚው፤ አሁን ላይ በቁጥር ደረጃ እንደማይታወቅ ይሁንና በዓመታዊ ማጠቃለያ ሪፖርት ላይ እንደሚገለጽ በማመላከት ምላሽ ሰጥተዋል።

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሁነት የሚመጡ እንግዶችን ለቱሪዝም ከመጠቀም አኳያ እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ የሁነት ተሳታፊዎች የቢዝነስ ቱሪስት መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለስብሰባ፣ ለምክክር እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎቶች የሚመጡ ናቸው። እንደሆቴል ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ምቹ ማድረግ፤ ለኤግዚብሽን የሚሆኑ ስፍራዎችን ማዘጋጀት እና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል። እንደዚሁም በሚኖራቸው ትርፍ ሰዓት በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ቦታዎችን እንዲጎበኙ በማድረግ፣ እንደቆይታቸው መጠን የኢትዮጵያ የአየር መንገድን በመጠቀም ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ለማድረግ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

ለሁነት ወደ አዲስ አበባ የመጣ አንድ ቱሪስት ለጉብኝት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች በሄደበት አካባቢ እንደ መኝታ፣ ምግብ ያሉ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ የቱሪዝም ምርቶችን ሊገዛ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። እነዚህ እድሎች የሁነት እንግዶችን ለቱሪዝም መጠቀም በደንብ ሊሰራበት እንደሚገባ ጥቁምታ የሚሰጡ መሆናቸውን አብራርተዋል። ከዚህ በዘለለ ከሱቅ በደረቴ፣ ከሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች፣ ከተለያዩ የንግድ ቦታዎች እንደየፍላጎቶቻቸው የፈለጉትን መሸመት የሚችሉበት እድል በመኖሩ፤ ከቱሪዝሙ ባለፈ ማህበረሰቡ የሚጠቀምበት አጋጣሚ በመኖሩ እድሎችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ቱሪዝምን በተመለከተ የቱሪዝም ሚኒስቴር በዋናነት ኢትዮጵያን እንደሀገር በተለያዩ ደረጃ ላይ የሚገኙ የቱሪስት ሀብቶችን፤ በመዳረሻ ቦታ ላይ የሚገኙ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማስተዋወቅ ሃላፊነቱ እንደሆነ አመላክተዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስር የሚገኙትን ጨምሮ የአስጎብኚ ድርጅቶች፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እነማን ናቸው? ምን ምን መዳረሻ ቦታዎች እንዳሉ? ፓኬጅ እንዲያዘጋጁ ይደረጋል ብለዋል።

ፓኬጁ የኮንፍረንስ እንግዶች ገና ከሀገራቸው ሳይነሱ ቀደም ብሎ በተዘጋጁ ዌብሳይቶች፣ ሊንኮች፣ ኢንስታግራሞች እና የመረጃ አማራጮች እንደሚለቀቅላቸው ያነሱት አቶ አለማየሁ፤ በኢኮኖሚ አቅማቸው፣ እንዳላቸው የቆይታ ጊዜ፣ እንደየፍላጎታቸው እና ምርጫቸው ፓኬጅ ገዝተው በአስጎብኚ ድርጅቶች በኩል በሚፈልጉት የቱሪስት መዳረሻ መስተናገድ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።

በቀጣይ ሁነቶችን ከማስፋት፣ ከማስቀጠል እና የቱሪዝም ዘርፉን ከማጠናከር አኳያ ምን ሊሰራ እንደታሰበ የተናገሩት አቶ አለማየሁ፤ አሁን ላይ ዘርፉ እያደገ ከመምጣት አልፎ ተወዳዳሪ ወደመሆን መሸጋገሩን አንስተዋል። ለዚህ የለውጥ ሂደት ወሳኝ የሚባሉ እንደአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያሉ ሁኔታዎች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አስረድተዋል። የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቃት ማረጋገጥ እና ደረጃ መስጠት ለቱሪዝም ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው፤ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ሂደቱን መከታተል አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

ሆቴሎች ከምግብ እና መኝታ አገልግሎት ባለፈ እንደደረጃቸው የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ሁነት መከወኛ ስፍራዎቻቸውን የደረጃ እና የጥራት ሁኔታ ቢያስተውሉ መልካም መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት እንደነበረው ከትራንስፖርት አቅራቢዎች ጋር በመነጋገር ቱሪዝሙን ሊደግፍ በሚችል መልኩ ሥራዎች መሰራታቸው አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ባለሙያዎችን በማሰልጠን ፤ለስብሰባ የሚመጡ እንግዶች በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያላቸውን ርካታ እና ቅሬታ የሚገልጹበት እድል በቀጣይ የሚሠራበት እንደሚሆን ገልጸዋል።

አያይዘውም ከኢትዮጵያ ባለፈ የውጪ ሀገር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማግባባት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እና ምክክሮች እንዲበዙ በማድረግ የኢንቨስትመንት እድሎችን በማስፋት ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ እድሎች በመፍጠር ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል። በተቀመጡ አቅጣጫዎች እና ፖሊሲዎች መሰረተ ልማትን በመሥራት፣ የአገልግሎት ተቋማትን በማላቅ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ ባለፈ እንደአፍሪካ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

ከዚህ ሰፊ አላማ በመነሳት መስህቦችን የሚያስተዳድሩ አካላት በቀጣይ ዘርፉ ላይ ምን አይነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ አለማየሁ፤ መስህብ ለአንድ ሀገር ብዙ ትርጉም ያለው ነው። በኢኮኖሚ፣ በተፈጥሮ ውበት፣ በታሪክ፣ በማንነት፣ በስልጣኔ ሊገለጽ ይችላል። ሀላፊነት የተሰጣቸው እነዚህ አካላት የሚያስተዳድሯቸውን መስህቦች በመጠበቅ በተሻለ ከፍታ ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ምቹ ማድረግ ሲባል የቋንቋ ችግር ያለባቸውን ጨምሮ የአካል ጉዳት ሰለባ የሆኑ ጎብኚዎች ወደመስህብ ስፍራዎች የሚመጡ በመሆኑ፤ እነዚህን ጎብኚዎች ያማከለ አገልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል። ለዚህም የተለያዩ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አንስተው፤ ቋንቋን በሚመለከት በቅርብ የቻይና ዜጎችን የጉብኝት ችግር ለማቅለል አዲስ አበባ ተቀማጭ ከሆኑ የቻይና ዜጎች ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ሳምንታት የቻይና ቋንቋ ስልጠና ለአስጎብኚ ባለሙያዎች መሰጠቱን አሳውቀዋል።

ሁሉንም ጎብኙ ባማከለ ደረጃ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ የመስህብ አስተዳዳሪ አካላት ሀላፊነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አለማየሁ፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚና እንዳለ ሆኖ የነዚህ አካላት ሚናም ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል። የቱሪዝም ዘርፍ ቅንጅት እና ውህደት እንደሚፈልግ ጠቁመው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በዘርፉ ላይ ካሉ ከሁሉም አካላት በጋር ትብብር እየሠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ፍቃድ በመስጠት፣ የቱሪስት ጋይድ ቡክ በማዘጋጀት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከሁሉም አካላት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። አስጎብኝ ማህበራት፣ መስህብ አስተዳዳሪ አካላት እንዲሁም ሁነት አዘጋጅ ማህበራት ለቱሪዝም እድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ አንስተው፤ ከሁሉም ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳላቸው ጠቁመዋል።

አያይዘውም በቅርቡ ለተሻለ የቱሪስት መነቃቃት ‹‹የሁነት አዘጋጆች ብቃት ማረጋገጫ›› በሚል ዝግጅቶች እንዳሉ አንስተው፤ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በቱሪዝም ላይ ለተጀመረው ወሳኝ ሥራ አንድ አካል መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሀገሪቱ ሁነቶችን ለማስተናገድ በቂ አቅም እንዳላት ያነሱት ሀላፊው፤ ብቁ ሆና በመገኘቷ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ መብቃቷን ገልጸዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ዝግጁነቷን የሚያረጋግጡ በርካታ ሁነቶችን አድርጋለች ብለዋል። እየተሠሩ ያሉ ዘመኑን የዋጁ መሰረተ ልማቶች ለእነዚህ ምላሽ የሚሆኑ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል። ለአብነት አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከልን አንስተዋል።

ኮንቬንሽኑ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ በብዙ ቴክኖሎጂዎች የተደገፈው አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መሆኑን በማመላከት፤ ሀገሪቱ ለጀመረችው አህጉር አቀፍ ሁነት እንደአብነት የሚነሳ ነው ብለዋል። በተመረቀ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፍ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ለመጪዎቹ አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ሁነቶችን ለማስተናገድ ስምምነት የወሰደ እንደሆነም ሀላፊው ጠቁመዋል። እንደአጠቃላይ ሀገሪቱ ለሁነት አዘጋጅነት ተመራጭነቷ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል ሲሉም ተናግረዋል።

የሁነት ቱሪዝም ለአንድ ሀገር ያለው ሁለንተናዊ ፋይዳ የላቀ እንደሆነ በማንሳት፤ ከሀገር እስከ ማህበረሰብ የሚደርስ የተጠቃሚነት ሰንሰለት እንዳለ አንስተዋል። በባዛር፣ በኤግዚብሽን እንዲሁም እንደመስቀል እና ኤሬቻ ባሉ የአደባባይ በዓላት ሰሞን የሚሰሩ ስራዎች ህዝብን ከግለሰብ፣ ግለሰብን ከሀገር ያያያዙ መሆናቸውን በመጠቆም ፋይዳቸው የጋራ መሆኑን አመላክተዋል። አያይዘውም እንደታላቁ ሩጫ ባሉ ዓመታዊ ዝግጅቶች ላይ ያሉ እድሎች ቱሪዝሙን ጠቅመው፤ ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ እንደሆኑ የተለያዩ ምሳሌዎችን በማንሳት ገልጸዋል።

ሁነትን ከሀገርና ህዝብ ለይቶ ማየት አይቻልም። ሁሉንም ያያያዘ፣ ያነካካ የጋራ ተጠቃሚነት ነው ያሉት ሀላፊው፤ ሰፊ እድሎችን እና ትስስሮችን በመፍጠር ረገድ ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ የተዘረጋ መሆኑን አንስተዋል። ሀገሪቱ መጪውን ቃኝታ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ወሳኝ አቅጣጫዎችን ተልማለች። መስህቦችን ከሀብትነት ባለፈ የገቢ ምንጭ የሚሆኑበት መንገድ ጥርጊያ ላይ እንደምትገኝ በማመልከት፤ በቀጣዮቹ ጊዜያት ሀገሪቱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷ የሚረጋገጥበት እድል የሰፋ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደእሳቸው ማብራሪያ፤ ሁነቶችን ጨምሮ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ከዚህ በፊት ያልነበሩ በርካታ ለውጦች ታይተዋል። ከዚህ በፊት ቱሪዝም የማህበራዊ ዘርፍ አንዱ አካል በመሆን ከባህል ጋር ሆኖ ሲሠራበት ነበር። ይሁንና አሁን ላይ ቱሪዝም ከአምስቱ የኢኮኖሚ አመንጪ ዘርፎች አንዱ በመሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል። በዚህም መሰረት ባለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ የቱሪዝም ሥራዎች ተሠርተዋል። ፡

ሀላፊው አክለውም በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፣ በቱሪዝም መስሪያ ቤት፣ በግል ባለሀብቱ፣ በክልል ባሉ መስተዳድሮች እንዲሁም በክልል በሚገኙ የቱሪዝም ተቋማት ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት በማድረግ ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት እንዲውል ከፍተኛ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል። በዘርፉ በተሰራ ሥራ ምቹ እድልን የሚፈጥሩ በአይን የሚታዩ ተጨባጭ ሁነቶችን ማስተናገድ፤ መዳረሻ ቦታዎችን ማስፋፋት እና ማልማት ተችሏል። በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ትብብርን በመፍጠር ረገድ ሰፋ ያሉ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You