ሰላማዊት ውቤ
ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በየቀኑ ወደ መዲዋ አዲስ አበባ የሚጎርፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ናቸው። ከእነዚህም የተወሰኑት ጉዳያቸውን ፈፅመው የሚመለሱ ሲሆኑ፤ አብዛኞቹ ደግሞ ሥራ ፍለጋ ብለው የሚፈልሱ ናቸው። ይብዛም ይነስም ሁለቱም ከተሜነት ለወለደው ችግር የመጋለጣቸው ዕድል ሰፊ ነው።
በተለይም ከሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች የሚመጡ ዜጎች ለከተማዋ አዲስ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በእጅጉ ይቸገራሉ፤ ይጭበረበራሉ፤ በአብዛኛውም ከበድ ላለ ዝርፊያና ችግር ሲጋለጡ ይታያሉ። እንደሚባለው የአብዛኛው የከተማው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ገፈት ቀማሽም እነሱ ናቸው። በሌላ በኩል ችግር ፈጣሪ፣ በመሆንም አስተዋፆዋቸው ከፍተኛ ነው የሚሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችም አሉ።
ቅቤ ላይ ሙዝ፥ እንጀራ ላይ ጄሶ ከመቀላቀል ጀምሮ የማጭበርበርና የተለያዩ ወንጀሎችን የመፈፀም፣ የኑሮ ውድነት ምንጮች ተደርገውም ይታያሉ። ከሴት አዳሪነት መስፋፋትና ከፅዳት ጋር የተያያዘ እንዲሁም የከተማ ችግር ምንጮችና መንስኤዎች መሆናቸውም ይነገራል። ለክልሎች በፍጥነት ያለ ማደግ ዋንኛ ምክንያት የነዚሁ ሰዎች የማያቋርጥ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት ነው።
የደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት ፍልሰት የሚለውን ቃል ሲተረጉመው መፍለስ፣ መፍረስ፣ መሰደድ፣ ተማርኮ መኼድ፣ መዞር፣ መባከን፣ ወደ ሌላ ሕዝብ መጠጋት ይለዋል። በነገራችን ላይ የማህበራዊ ጠበብቶች እንደሚሉት በተለይም እኛ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳገኘነው መረጃ ፍልሰት ለአንድ ከተማ ጥሩም መጥፎም ጎን አለው። በተለይ እንደ ማዕድናትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ላላቸው እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማነት በመሸጋገር ላይ ለሚገኙ ከተሞች የዕድገት ምንጭ ነው።
እነዚህ አካባቢዎች ፈጥነው እንዲያድጉና እንዲመነደጉ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋሉ። እንደ አዲስ አበባ ላለችውና ፈጣን ግንባታዎችና ሌሎች ሰፋፊ የማያቋርጡ የልማት እንቅስቃሴዎች ለሚከናወኑባት ከተማ ደግሞ ፍልሰት ጭራሽ አያስፈልግም ተብሎ መደምደም ደረጃ ላይ ባይደርስም ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑን የማህበራዊ ጉዳይ ጠበብቶቹ ይናገራሉ።
እነሱ እንደሚሉትም ወደ መዲናችን አዲስ አበባ ዕለት በዕለት የሚደረገውና የማያቋርጠው ፍልሰት ሕዝቡን ሞልቶ አትርፎ ከተማዋን አጨናንቋት በግልፅ ይታያል። እንደ መኖሪያ ቤት እጦት፣ እንደ ሥራ እጦት ያሉ የኑሮ ውድነቶችንም ሲፈጥር እየታየ ነው። በአራቱም የከተማዋ አቅጣጫዎች በየቀኑ እስከ 15 ሺህ ሰው ወደ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ የሚገመት እንደሆነም ይነሳል።
ይሁንና በአራቱም አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚፈልሰው ትክክለኛውን የህዝብ ቁጥር ለማወቅ ለማዕከላዊ ስታስቲክ ኤጄንሲ ጥያቄ ያነሳን ቢሆንም፤ ኤጄንሲው ለጊዜው ያጠናከረው መረጃ የሌለው መሆኑን ተረድተናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ተገንዝቧል። በእርግጥ አዲስ አበባ አሁን ባለችበት ሁኔታ ባይመከርም ፍልሰት ለከተሞች በጎም ክፉም ጎን እንዳለው ኤጄንሲው ያምናል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ስለፍልሰቱ ለመመርመር ያሚያስችል ጥናት ለማጥናት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ለጥናቱ የሚረዳ ስልጠናም ሰጥቶ አጠናቅቋል። ጥናቱ ከሳምንት በኋላ ይጀመራል። ሆኖም ፍልሰት በመዲናችን አዲስ አበባ ዕድገትና በነዋሪዎቿ ላይ የሚያሳድረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በቁጥር ለመግለጽ የሚቻለው ደግሞ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ይሆናል።
እኛም ጥናቱ ተጠናቅቆ የተሟላ መረጃ እስክናገኝ በከተማችን አዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ዞር ዞር ብለን በተለይ በአራቱም አቅጣጫ ወደ ከተማችን የገቡትንና የተቀላቀሉትን የሕብረተሰብ ክፍሎች አመጣጥ፣ አኗኗርና ሌሎች መሰል ሁኔታዎችን ለመቃኘት ሞክረናል። ከከተማዋ ነዋሪዎችም በፍልሰት ስለሚገቡት ዜጎች ያላቸውን አስተያየት ጠይቀናል።
ጊዜው ብርሃኑን ለጭለማ ቦታውን ለቆ ለዓይን ደንገዝገዝ ሲል ነው። በዚህ ሰዓት ብዙ ሴቶች በየትኛውም ሰው በሚበዛበት የመዲናችን አዲስ አበባ አካባቢዎች ወጥተው መቆማቸው የተለመደ ነው። እነዚህ ሴቶች ትራንስፖርት ወይም ታክሲ ሳይሆን የዕለት ጎርሳቸውን ነው የሚጠብቁት። የዕለት ጉርሳቸውን እስኪያገኙ ቆመው ያድራሉ።
ተዋበች ጫካን ያገኘናት ከነዚህ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ቺቺኒያ አካባቢ ነው። በመንገድ መብራት ታግዘን አየናት። ከንፈሯን ቀይ ሊፕስቲክ ተቀብታለች። አቀባቧ የአፏን አካባቢ ያለቃለቀው በመሆኑ ለሥራው አዲስ መሆኗ አያጠራጥርም። ጥብቅ ያለ ታይት ለብሳ ረጅም ተረከዝ ያለው የድሮ ፋሽን ጫማ ተጫምታለች።
የተጫማችውም ቢሆን ለሥራው አዲስ መሆኗን ያረጋግጣል። ገጽታዋ የዋህና ገራገርነት የተላበሰ ነው። እንደ ሌሎቹ የገበያ ጊዜዬን አታባክኑብኝ አላለችንም። ልናነጋግራት የፈለግንበትን ጉዳይ ስንነግራትም ክፍያ አልጠየቀችንም።
እንደነገረችን ከክፍለ ሀገር የመጣችው በቅርቡ ነው። አመጣጧ ሥራ ፍለጋ ነበር። ከነበረችበት ክልል ለሥራ የወሰደቻት ሴት ሀብሲቱ ጓጎለ ብላ በ15 ቀኗ ማለዳ ነው ያባረረቻት። ትምህርት አልተማረችም። እናም እንደ ልማዷ ሰው ቤት እንዲያስቀጥራት ከአንዱ ደላላ ቤት ሄዳ ነበር። አጋጣሚ ሲጠያየቁ የሀገሯ ልጅ ሆኖ አገኘችው። ቆንጆ ነሽ ቢዝነስ (ሴት አዳሪ) ስሪ አላት።
በእርግጥ እኛም ስናያትና ሥሪ ያላት ሥራ ባይበረታታም አሣ የመሰለች ጠይም ተብላ የምትገለፅ ቆንጆ ናት። ለሥራው ያመቻት ዘንድ የለበሰችውንም ገዝቶ ሰጣት። ቀን ቀን ለኔ ምግብ ታበስይልኛለሽ፣ ቤት ታፀጅልኛለሽ አላት።
ማታ ማታ ቢዝነስ ስለምትሰሪና በዛው ከወሰደሽ ወንድ ጋር ስለምታድሪ ቤት መከራየት አያስፈልግሽም። ሥራ ካጣሽ ከኔ ጋር ታድሪያለሽም አላት። እንዳጫወተችን አዳሩን ሥራ ፍለጋ ብላ ወደ እሱ የሄደች ዕለት ጀምራዋለች። ደግነቱ ማይወስዳት ሰው አጥታ አታውቅም።
ገንዘብ ያለው ባለመኪና ካጋጠማት ለአዳር አምስት መቶ ብር እንድትቀበል መክሯታል። የሌለው ካጋጠማት ከ100 እስከ 200 ብር ተቀበይ ብሏታል። የዋህነት በተላበሰ ቅላፄ እንደነገረችን አዲስ አበባ ውስጥ ቤት ውድ ስለሆነ እሷ እሱን በማግኘቷ ዕድለኛ ነች።
ከሲዳማ ክልል ይርጋዓለም ከተማ ትምህርቱን ከሰባተኛ ክፍል አቋርጦ የመጣው ወጣት ወንድሙ ካማንጎ ይባላል። ከመጣ አምስት ዓመቱን ይዟል። የመጣው ከእንጀራ እናቱ ጋር ባለመግባባቱ ሥራ ፍለጋ በሚል ነው።
ይርጋ ዓለም ከተማ ላይ በጫኝና አውራጅ የሥራ ልምድ ነበረው። አሁን ላይ እየተዳደረ ያለውም መስቀል አደባባይ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ባለው የእኛ ባስ ጫኝና አውራጅ ሆኖ ነው ።
ሥራውን የሚሰራው በክፍለ ሀገር መታወቂያ በመሆኑ የሚኖርበት አካባቢ የከተማ ነዋሪነት መታወቂያ እንዲሰጠው ይፈልጋል። እንዳጫወተን አሁን ላይ የሚያድረው በቀን ለብቻው ከሆነ 60 ብር ለሁለት ከሆነ ደግሞ ላይና ታች ባለው ተሰካኪ አልጋ 30 ብር ከፍሎ ነው። ፍራሹ የሣርና የቃጫ ነው። ሥራ ከሌለ ግን እንኳን ለመኝታ ለምግብም አያገኝም ። ቢሆንም ሁሉም ጫኝና አውራጆች በዚህ አጋጣሚ ከአከራዮች ችግሩን የሚያልፉበት ስምምነት አላቸው።
ስምምነቱ በሚያገኙበት ጊዜ ውዝፋቸውን አንዴ መክፈል የሚችሉበት ነው። ይሄ የአዲስ አበባ ከተማ ተዛዝኖ መኖር ያስደስተዋል። ለዘለቄታው ኑሮውን አዲስ አበባ ላይ ለማድረግም እንዲያቅድ አድርጎታል። የነዋሪነት መታወቂያ የሚፈልገው ለዚህ ነው። ሌላው ቀርቶ አዲስ አበባ ላይ መሸወዱ ሁሉም ነገር ዘና ያደርገዋል። በዚህ አጋጣሚ እንደመጣ የተሸወደበትን ሁኔታም በፈገግታ አጫውቶናል።
እንደመጣ ከይርጋለም በቋጠረው ገንዘብ ሞባይል በሦስት መቶ ብር፣ 16 ጂቢ ሚሞሪ እንዲሁም በዋሌት ቦርሳ 400 ብሩን ዕቃ በሚያወርድበት ጊዜ በአካባቢው ቁጭ ብሎ ሲሰራ ላገኘው ሊስትሮ አንዴ ያዝልኝ ይለዋል። ሥራውን ጨርሶ ቀና ሲል ሊስትሮው በአካባቢው የለም።
ሙሉ ቀን ይሄን አሁን ድረስ ሳያገኘው የቀረውን ይሄን ሊስትሮ ፍለጋ ሲባክን ይውላል። ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ይሆንበታል። የሥራው አካባቢም ያሳረፈው ልጅ ቤት ይጠፋዋል። በዚህ ሁኔታ አሁኑ የሚያድርበትና በቀን 30 ብር የሚከፈልበት ቤት ማደር ጀምሯል።
እንዳስተዋልነው ከጠመንጃ ያዢ ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ ያሉትና በጀብሎ ወይም በሡቅ ደረቴ ንግድ የሚተዳደሩት በአብዛኛው ከአንድ ክልል የመጡ የአንድ አካባቢ ልጆች ናቸው። እድሚያቸውም ቢሆን ተመሣሣይ ነው። ሁሉም ደግሞ ትምህርታቸውን አቋርጠው የመጡና አዲስ አበባ ላይ ትምህርታቸውን መቀጠል ያልቻሉ ናቸው።
ከነዚህ ታዳጊ ወጣቶች አንዱ ወንድሙ ኩሩቼ ይባላል። እንደነገረን የመጣው ከወላይታ ዞን ዳሞተ ሶሪ ወረዳ ደምበዛሜ ቀበሌ የስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ነው። ሦስት ዓመቱን ይዟል። እዚህ አዲስ አበባ ዘመድ ስላለው ሥራውን የጀመረው በመጣ ማግስት ነው። ሆኖም ከመጣ ማግስት ጀምሮ ዘመዱ ጋር አያድርም። ለሦስት አንድ ሺህ 500 ብር እየከፈሉ የሣር ፍራሽ እየጣሉ በወለል ላይ ነው የሚያድሩት።
አባቱ አርሶ አደር ቢሆኑም ከአራቱ ልጆቻቸው አንዱ የበኩር ልጃቸው እሱ በመሆኑ ቢያንስ እራሴን ልቻል በማለት ነው የመጣው። በቀጣይ ዓመት ወደ ሀገሩ ተመልሶና ቤተሰቡ አጠገብ ሆኖ ሥራ እየሠራ ትምህርት ቤት ገብቶ ያቋረጠውን ትምህርቱን የመቀጠል ዕቅድ አለው። በቀን ገበያ ካለ መቶ ብርና በላይ ከሌለ 50 ብር ያገኛል። የዕለት ወጪውን ሸፍኖ ቁጠባውን እየቆጠበ 30 ሺህ ብር አድርሶታል።
በዚህ ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ከብት ገዝቶ እያረባ ትምህርቱን የመቀጠል ሀሳብ ሰንቋል። እዚሁ መስቀል አደባባይ መድን ድርጅት አካባቢ ያገኘናቸው አቶ ባዬ አየለ መድን ድርጅት አካባቢ ነው የሚሠሩት። እንደሰጡን አስተያየት የባስ ማቆሚያም ሆነ መጫኛ ያለው ሜክሲኮ ሸበሌ አካባቢ ነው። ሆኖም ከገጠር ለተለያየ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ከዛ መጥተው ማታ ላይ ሀዋሳ ሀዋሳ በሚሉና በተለያዩ ባስ ረዳቶች አማካኝነት በአካባቢው ትኬት ይቆርጣሉ።
መሣፈሪያ እዛው እየመሰላቸው ወደ እነሱ መሥሪያ ቤት ሰተት ብለው የሚመጡም አሉ። ሆኖም በአካባቢው ጀብሎ ከሚሸጡት በተጨማሪ ከተለያየ አካባቢ ፈልሰው ለመጡ ዘራፊዎች ይዳረጋሉ። ቦርሳቸውና ሻንጣቸው ይቀማል። እናሳያችሁ በሚልም ተታለው ይወሰድባቸዋል።
እሳቸው በሚሰሩበት ሳሪስ ባለው ሁለተኛ መሥሪያ ቤታቸው አካባቢ ደግሞ መስቀል አደባባይ ጭምር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ፈልሰው የመጡ ታዳጊዎች አሉ። እነዚህ ታዳጊዎች ሚዛን መመዘን ነው የሚሰሩት። የዘጠኝ ዓመት ሴት ልጅ ሁሉ ሥራውን ትሰራዋለች። የሚያሰሯቸው ደግሞ ሌሎች ሰዎች ትንሽ ሳንቲም እየከፈሉ በመሆኑም ለጉልበት ብዝበዛና በተለይም ሴቶቹ ለመደፈር የተጋለጡበት ሁኔታም አለ።
ብዙዎቹ ሴቶቹ ጎዳና ላይ ነው የሚያድሩት። የአፍና አፍንጫ ጭንብል አያደርጉም፣ ምግብ የሚበሉትም ትርፍራፊ ነው። በዛ ላይ አብዛኞቹ የመጡት ከደቡብ በመሆኑ ደቡብ ላይ ቀባሪና የተማረ እንዳይጠፋ ከክልል ጋር በቅንጅት መሠራት አለበት የሚል እምነት አላቸው።
ወጣት አብዱል ጀዋድ ሀሰን እንደነገረን እንደሚያየው ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ ፍልሰት በርትቷል። ቀላል ቢመስሉም አንዳንድ ከንጥቃቄና ከዘረፋ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ሲፈፀሙ ይታያል። ሌላው ቀርቶ ከገጠር የሚመጣው ወጣት ስልጣኔ ስለሚመስለው ከፀጉር አቆራረጥ ጀምሮ ቀዳዳ ይለብሳል።
ከከተማው ይኮርጃል። ስለዚህ መላ መፈለግ ግድ ይላል። እሱ በአስመጪ ሥራው እንዳየው እንደ ዱባይ፣ ታይላንድና ሳውዲ ዓረቢያ አገራት ሰው ከየትም አካባቢ የመጣው የሚለይበት የአሻራ አሰራር አለ። ወንጀል ሲሰራ መቼ፣ ማንና በምን ዓይነት ሰው እንደተሰራ ይታወቃል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ፕላን የህንፃ ኮንስትራክሽንና የአርትኬቼር ባለሙያው ዶክተር ጥበበ አሰፋም የሕዝብ ብዛትና የቦታ ጥበትን ከከተማ ፕላን እንዲሁም አኗኗር ዘይቤ ጋር ማስታረቅ እንደሚገባ ይመክራሉ። እኛም ጥናቱ ይሄን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ ከፍልሰት ጋር የተያያዘውን የአዲስ አበባን ችግር ይፍታ በማለት ጽሑፋችንን ደመደምን።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013