አስቴር ኤልያስ
የተወለዱት በቀድሞው ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ይርጋለም ከተማ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት አዲስ አበባ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የአግሪካልቸር አግሪቢዝነስ አግኝተዋል።
የቡና ቀማሽነት ኪውግሬደር የሚባል ሰርተፊኬትም አላቸው። ባስገኙት ውጤትም የተለያዩ የምስክርና ወረቀት በበጎ አድራጊነታቸው፣ በቡና ጥራት ባስመዘገቡት ሥራ እንዲሁም በትጉህ ግብር ከፋይነታቸው ከአገር ውስጥም ሆነ ከተለያዩ የዓለም አገራት ካሉ የተለያዩ ተቋማት ተሰጥቷቸዋል።
እኚህ የዛሬው የምጣኔ ሀብት እንግዳችን አጠቃላይ የቀርጫንሼ ካምፓኒ ሥራ አስፈፃሚ አቶ እስራኤል ደገፋ ሲሆኑ፣ አዲስ ዘመን በቡናው ዘርፍ ስላለው እንቅስቃሴን አስመልክቶ ከእርሳቸው ጋር ቃል ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሯልና መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- ትኩረቱን በቡና ላይ ያደረገው ቀርጫንሼ በቡናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው ተግባር እንዴት ይገለፃል?
አቶ እስራኤል፡- ካምፓኒው የሚሠራ አጠቃላይ የአገራችን ኢኮኖሚ በሚፈልግበት ዘርፍ በግብርና ዘርፍ እና ማኑፋክቸሪንግ ላይ ነው። አጠቃላይ በግብርናው ላይ ወደ 26 ሺህ የሥራ እድሎችን በመፍጠር እንዲሁም ደግሞ ከ56 ሺህ አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር በማድረግ የተሻለ ገበያን በመፍጠርና የተሻለ የኤክስቴሽን ድጋፍ በማድረግ የቡናን ምርትና ምርታማትን በማሳደግ ላይ ነው። እንዲሁም በውጭው ገበያ የተሻለ እድል በማፈላለግ የሚሠራ ድርጅት ነው።
ላለፉት ተከታታይ አራትና አምስት ዓመታት ትልቁን የአገሪቱን የቡና ኤክስፖርት ከሁለት አኃዝ በላይ ድርሻ በመውሰድ የሚልከው ይኸው ኩባንያ ነው። በየትኛውም የኢትዮጵያ ቡና አብቃይ ክልሎችም ሆነ ወረዳዎች ይገኛል።
አጠቃላይ ወደ 57 ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ደግሞ ወደ አምስት ፋርሞች (እርሻዎች) በቡናው ሴክተር ላይ ማኔጅ እናደርጋለን። በተጨማሪም በማኑፋክቸሪንግ ላይ በቀጣይ አምስት ዓመታት በአንድ ጊዜ ወደ 11 የኢንዱስትሪ ማኑፋክቸሮችን እየገነባን ነው ያለነው። ከ11ዱ ደግሞ ሦስቱ ወደ ሥራ ገብተዋል።
አብዛኛው ትኩረታችን የአገራችንን ኢኮኖሚ መደገፍ ላይ ነው። ይህንንም ድጋፍ የምናደርገው በግብርናውና በማፋክቸሪንግ ሴክተሩ ነው። በዚህ ሴክተር የጎላ ሚና በመጫወት የሥራ እድሉንም ፈጥረን ይበልጥ ደግሞ የግብርና ሥራ ላይ በማተኮር ይሆናል። በተለይ በግብርና በኩል ከኢንዱስትሪው አንፃር ሲተያይ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል ሴክተር ነው ብለን እናምናለን። በመሆኑም በዛ ላይ የበለጠ ጊዜ ሰጥተን አስፍተን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። የአፍሪካ ትልቁ የግብርና ኩባንያ ሆኖ መቀጠል ነው ዋና ግባችን።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ኩባንያችሁ በቡሌ ሆራ ያለውን እንቅስቃሴ ለመንግሥት ኃላፊዎች አስጎብኝቷልና ምን ነበር ለማሳየት የተሞከረው?
አቶ እስራኤል፡– ጉብኝት የተደረገበት አባያ የሚባለው የደበቃ እርሻ ጣቢያ ሲሆን፣ ኩባንያው ካሉት እርሻዎች ሁሉ አነስተኛው ነው። ነገር ግን እንዴት አድርገን ግብርናን ከተለምዶ አሰራራችን መቀየር እንዳለብን ሁሌም ይቆጨኝ ነበር። ቡና ማብቀል የጀመርነው ከሁሉም አገሮች በፊት ነው። እኛ ለዓለም ቡና እናበረክታለን። ነገር ግን የመጨረሻው ደግሞ ምርታማ ያልሆነ ግብርና ያለን በዓለም ደረጃ እኛው ነን።
እናም ከሰው ቀዳሚ የሆነች አገር በምርትና ምርታማነት ደግሞ ከሁሉ ወደኋላ ስንቅር ውስጤን ይሰማዋል። አርሶ አደሩም የሚያገኘው ጠቀሜታ እየተሻሻለ ሳይሆን የበለጠ ፈተና ውስጥ እየገባ ያለበት ወቅት ስለመሆኑ እያስተዋል ነው። ስለሆነም ምን ብናደርግ ይሻላል በሚል አንድ ዲፓርትመንት በማቋቋም ነው ግብርናውን ትራንስፎርም እናደርጋለን በሚል በዛ ስፍራ የተንቀሳቀስ ነው።
በቡናው ፋርም ላይ ትልልቅ ኢንቨስትመንት ሰርተው ትልቅ ደረጃ ላይ ከደረሱ ከእነ እሥራኤልና ብራዚል ጋር በጋራ ወደመስራቱ መጣን፤ በጋራ ሆነን እንዴት አድርገን ማሳደግ እንደምንችል ከእኛ ቡድን ጋር የተለያየ ጉብኝት አድርን አማካሪዎችን በመቅጠር የደበቃ ፋርምንና እዛው ምዕራብ ጉጂ ዞን የሚገኘውን ሌላኛውን ገላና የሚባልበት ወረዳ ላይ እንደዚሁ ወደ750 ሄክታር ላይ በሰፊው እያለማን ነው የምንገኘው። ይህ የወሰድነው ተሞክሮ ድሪፕ ኢሪጌሽን ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ የመጨረሻው የሚባለው በግብርናው ዘርፍ የተገኘና ውጤታማ የሆነ የመስኖ ሲስተም ነው።
ከዚህ ቀደም ስንጠቀምበት የቆየው የመስኖ ሲስተም ከመቶ ዓመት በፊት በፊት የተጀመሩ የመስኖ ሲስተም ነው። በፈጠራው ሂደት ውስጥ ድሪፕ መስኖ ግን ውጤታማ ነው። ለእጽዋቱ የሚሰጠው የውሃ መጠን የተመጠነ ነው። የውሃ ብክነት አይኖርም። ውሃ ደግሞ ሀብት ነውና መባከን የለበትም። እጽዋቱ ደግሞ መጠጣት ያለበት የሚበቃን ያህል ነው። ቴክኖሎጂው በሶፍትዌር የተደገፈ ነው። የትኛውም እጽዋት ውሃ እንደፈለገ፤ የትኛው ደግሞ እንዳልፈለገ ራሱ ሶፍትዌሩ ሠርቶ ነው የሚያቀርበው። ከዚህ ከዚህ አንፃር በደበቃ ያለው የተሻለው ቴክኖሎጂ ነው የሚያሰብለው ነው። በዚህም ውጤታማ ነው።
አርሶ አደሩ በተለምዶ በሄክታር ቡና የሚያገኘው ከስድስት ኩንታል የዘለለ አይደለም። እኛ በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅመን በሄክታር እስከ 35 ኩንታል ቡና ማሳካት ችለናል። ይህ ሙከራ ደግሞ የመጀመሪያው ነው። የሚጠበቀው በሄክታር እስከ 65 ኩንታል ድረስ ነው ብለን በመሥራ ላይ ነው ያለነው። ያንን ማሳካት ከቻልን የአገር የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ እንዲሁም የአርሶ አደሮችን ገቢ ከፍ ማድረግ ይቻላል። በተጨማሪም በእኛ ኢንቨስትመንት ዙሪያ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ትልቁ ገበያችን ቡና ነው፤ ቡና ደግሞ ለመቶ ዓመት ያህል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እዚህ ድረስ አምጥቶናል። ይህ ዘርፍ አሁን ከምናገኘው መቶና መቶ ሃምሳ እጥፍ አሳድጎ ወደውጭ መላክ የሚቻልበት ሂደት ቀላል ነው።
ሁሉም በዚህ አይነት ቴክኖሎጂ ቢሰራና አርሶ አደሩንም ቢያሳትፍ ውጤታማ መሆን ይቻላል። የእኛ ትልቁ እቅዳችን የራሳችን ማሳ ላይ ትልቁን ምርት ማምረት ላይ ብቻ አይደለም። በአቅራቢያው የሚገኙ የአርሶ አደሮችን ማሳዎችንም ወደእኛ ቴክኖሎጂ በመቀየር እነሱም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መሰረት ማደላደልና በፋይናንስም በመደጎም በዛ ልምምድ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ዲዛይን አድርገን ጨርሰናል። ይህ ሲሆን ምርትና ምርታማትን ማሳካት ይቻላል። የአርሶ አደሩንም የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ኩባንያና አርሶ አደሩ ትስስራቸው ምን ያህል ነው? ከጠቀሱት በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ የሚያደርገው እገዛ እንዴት ይገለፃል?
አቶ እስራኤል፡- እኛ የቆምንበትና መሰረት የሆነን አርሶ አደሩ ነው ብለን እናምናለን። አርሶ አደሩን ይዘን ካልተነሳን ያስቀመጥነው ዓላማ ግቡን ይመታል የሚል እምነት የለንም። ይህንንም ጠንቅቀን እናውቀዋል። ደግሞም የወጣነው ከዚሁ ማህበረሰብ ከመሆኑም በላይ ያደግነውም ሆነ የኖርነው በዚሁ ማህበረሰብ ውስጥ እንደመሆኑ ለራሳችን ችግር ራሳችን መፍትሄ ሆነን ካልተገኘን በስተቀር ከሌላ ቦታ የሚመጣን አካል መጠበቅ ለእኛ ማህበረሰብ ልክ መሆን አይችልምና ከዚህ ተነስተን የምንስራው ከልብ ነው።
ካለን ዓመታዊ ትርፋችን ላይ አስር በመቶ የሚሆነውን ለበጎ አድራጊ ድርጅት የምንሰጠው ሲሆን፣ ይህም በጎ አድራጊ ድርጅ ‹ቡና ቀላ›› በሚል ስም የሚጠራ የራሳችን ድርጅት ነው። በቡና አብቃይ አርሶ አደር ዙሪያ የተለያዩ መሰረታዊ የሆኑ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንገኛለን። ከእነዚህም መካከል ትምህርት ቤቶችን እንገነባለን፤ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እናጎለብታለን።
በየዓመቱ ከአምስት ሚሊዮን ችግኝ በላይ እናከፋፍላለን። እንዲሁም እኛ ገብተን የምንሰራባቸው ከመሰረተ ልማት በጣም የራቁ አካባቢዎች አሉና በዛ አካባቢ ህብረተሰቡን ሊጠቅም የሚችል ተግባራት እናከናውናለን። ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ቡና በማብቀል የማይታወቁና ከባህር ጠለል በላይ የሆኑ አካባቢዎች ዘልቀን በመግባት ቡና በማብቀል ላይ በመሆኑም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ እያመቻቸን እንገኛለን። በተለይ ደግሞ በቡናው ዘርፍ ያለውን ቴክኖሎጂ በማስፋፋ ጭምር እየሰራን ነን።
አዲስ ዘመን፡- አካባቢዎቹ የት የት እንደሆኑ ሊጠቅሱልን ይችላሉ?
አቶ እስራኤል፡- ለምሳሌ አማሮ አካባቢ ገላና የሚባልበት ስፍራ ምንም አይነት እርሻ የለም፤ ህዝቡ የሚተዳደረው ከብት በማርባት ነው። ከዚህም የተነሳ አርብቶ አደሩ በከብት ግጦሽ ሳቢያ ሲጣላ ይስተዋላል። በመሆኑም ግጭቶች በአካባቢው ይከሰታሉ። በእነዛ አካባቢዎች በመግባት አካባቢውን ወደግብርናው በመቀየር ላይ ነን።
እኛ የቀየርነው ብቻም ሳይሆን ማህበረሰቡም ወስዶ እንዲተክልና እንዲያመርት እንዲሁም ያመረተውን ምርት ለእኛ እንዲሸጥ ከማደረግም በላይ እየገዛነው ያለነው በተሻለ ዋጋም ጭምር ነው። አርሶ አደሩም ጥቅሙን በመረዳቱ ጠንክሮ በመሥራት ላይ ነው።
ሌላኛው አካባቢ ደግሞ አናሶራ ነው፤ አናሶራ ደግሞ እጅግ በጣም ደጋ ከመሆኑ የተነሳ ምንም ቡና ነገር አይበቅልበትም ተብሎ የሚታሰብ ቦታ ነው። በዚያ ቦታ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ቡና እንዲተከልና እንዲበቅል ያደረግነው እኛ ነን። በአካባቢው ኢንዱስትሪም ተክለናል። በአሁኑ ወቅት የእዛ አካባቢ አርሶ አደር ቡናም በማምረት የተሻለ ህይወት መኖር እንደሚቻል አምኗል።
ከዚህ በኋላ ቡናን አስፍቶ በማምረት ላይ የሚገኘው ራሱ ነው። በአሁኑ ወቅት እያከፋፈልን ያለው ችግኝ ነው። ከዚህ ቀደም ቡና የሚበቅልባቸው አካባቢዎች ጫካ ያለበት ነው ተብሎ ነበር የሚታሰበው፤ አሁን ግን በተለያዩ አካባቢዎች ሌላው ቀርቶ አያበቅሉም የተባሉ ቦታዎች ሁሉ በመስፋት ላይ ነው። ዓለም እየተጠቀመበት ያለውን ቴክኖሎጂ መጠቀም እስከተቻለ ድረስ የማይቻል ነገር የለምና እኛ ያንን እያረጋገጥን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የአገራችንን ኢኮኖሚ በማሳደግ ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ቀርጫንሼ ብራዚልንና እሥራኤልን በቡናው ዘርፍ ያላቸውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ላይ እንደሆነ ይታወቃልና ኩባንያው ምን ያህል ቶን ቡና ወደየትኞቹ አገሮች ነው የሚልከው? ምን ያህልስ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ላይ ይገኛል?
አቶ እስራኤል፡- ቡና ከሚያበቅሉ አገራት ውጭ ቡናችንን ለሌላው የዓለም ክፍል ሁሉ እናቀርባለን።መዳረሻን ያልሆነ አገር የለም ማለት ያስደፍረኛል። በዚህ ዓመት ወደ 35 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና ለመላክ ነው አቅደን እየሰራን ያለነው። በእቅዳችን መሰረት አሁን ወደ 45 በመቶ ማሳካት ችለናል። ከዚህ በኋላ በቀሩት ጊዜያት ደግሞ የቀረውን 55 በመቶ እንደምናሳካ እርግጠኞች ነን። አምና 28 ሺህ ሜትሪክ ቶን ነበር የላክነው፤ አቻምና እንዲሁ ተመሳሳይ የቡና መጠን ነበር ወደተለያዩ አገራት የላክነው።
የዚህ ዓመቱ የቡና መጠን ከፍ ያለበት ምክንያት በቅርቡ የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታዋ፣ የቡና እና ሻይ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርና ሌሎችም እንግዶች የጎበኙት በምዕራብ ጉጂ ዞን የሚገኘው የቡና ማዘጋጃና ማከማቻ መጋዘን ቡሌ ሆራ ላይ እየሰራን ነው ያለው። በተመሰሳይ በጅማ ዞንም እንዲሁ በመስራት ላይ እንገኛለን። የቡና መጋዘኖችን ለመስራት የታሰበበት ዋነኛ ምክንያት አርሶ አደሩ ምርቱን የሚሸጠው ለትክክለኛው ቡና ላኪ ወይም ለዓለም ገበያ ለሚያቀርበው ባለመሆኑ ነው።
በአርሶ አደሩና በቡና ላኪው መካከል ከፍተኛ የሆነ ክፍተት አለ። ያ ሁሉ ከአርሶ አደሮቹ የሚወስደው ትርፍ ነው። የአቅርቦት ሰንሰለቱ አርሶ አደሩን ያማከለ ባለመሆኑ ልክ አይደለም በማለት ለረጅም ጊዜ ስንናገር የነበረው ይህንን ነው። አርሶ አደሩ ያለው ታች በመሆኑ አዲስ አበባ መጥቶ ቡና ለመሸጥ የሚያስችል አቅም የለውም። አዲስ አበባ አይደለም በቅርቡ ወዳለችው ከተማ እንኳ የሚሄደው በፕሮግራም ነው። ስለዚህም እኔ አዲስ አበባ ተቀምጬ አርሶ አደሩን ያማከለ ገበያ መፍጠር ስለማልችል የግድ አርሶ አደሩ ወዳለበት ስፍራ መሄድ ግድ ይለኛል።
በሁለተኛ ደረጃ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ አለው። አዲስ አበባ ድረስ ተሸክመን የምንመጣው ቆሻሻ ቡናን ነው። ወደ 800 ኪሎ ሜትር አዲስ አበባ ድረስ ተጉዞ መጥቶ የቡና ጥራት እንዲጠበቅ ለማድረግ ሌላው ፈታኝ ሥራ ነው። ስለዚህ ይህን አይነቱን አካሄድ ማሳጠር መቻል አለብን። እንደሚታወቀው አገሪቱ ነዳጅ የምትገዛው በዶላር ነው። በመሆኑም ወጪው ተደምሮ የሚያርፈው አገር ላይ ነው። ያንን ወጪ ማስቀረት ከተቻለ እሰየው ነው። 45 በመቶ ያህሉን ከቡና ዋጋ ውስጥ የሚወስደው የሎጂስቲክ ወጪ ነው።
ቡሌ ሆራ ላይ ያለው ቡና ተዘጋጅቶና ጥራቱ እዛው ተለክቶ ወደ አዲስ አበባ አሊያም አዲስ አበባ መምጣት ሳያፈልገው ወደወደብ በዛው ማስኬድ ነው የሚጠበቅበት። ጅማ ላይም የተዘጋጀው እንዲሁ ወደ ወደብ የሚሄድ ከሆነ ብቃታችን ይጨምራል። የአርሶ አደሩ የገበያ ቅርበት እጅግ ትርፋማ ያደርገዋል።
አርሶ አደሩ ምርቱን ባልሆነ ዋጋ እንዲነጠቅ አያደርገውም። ምክንያቱም ከርቀት ገበያ ይልቅ እዛ በአቅራቢያው ባለው ገበያ ለመሸጥም ሆነ ለመደራደር አቅም ይኖረዋል። ዋጋው ሳይስማማው ቀርቶ አልሸጥም ብሎ ወደቤቱ ቢመለስ ወጪ የለበትም። አዲስ አበባ ከመጣ ግን የሚያርፈው ሆቴል ነው፤ ወጪ አለው።
ለአንድ አርሶ አደር አንድ ቡና ላኪን ከማግኘት ይልቅ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ መሄድ ይቀላል። ነገር ግን ወደ አዲስ አበባ ሳይመጣ ባለበት አካባቢ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚቻል ከሆነ እንደ አገርም ሚናው የጎላ ነው። በመሆኑም ይህ ተበረታትቶ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው። አሁን የመጣው ለውጥ እነዚህንም ነገሮች በማየት መምጣት ያለበት ሪፎርም መምጣት ይኖርበታል።
ደግሞም አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። እኛም ይህንን አይነት ሥራ በቡሌ ሆራም ሆነ በጅማ ጀምረናል። ሁሉም ቦታ መዳረሻችንን እያሰፋን ቆሻሻው እዛው ቀርቶ የመጨረሻው ምርት ወደውጭ ገበያ የሚላክበትን ሂደትን ነው እያሰፋን ያለነው። ለዛም ነው ዘንድሮ 35 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና እንልካለን ብለን እቅዳችንን ሰፋ አድርገን እየተነሳ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ በቡና ገበያ እና በግብይቱ ላይ የሚያጋጥሙ ዋና ዋና ችግሮች የሚባሉ ችግሮችና መፍትሄ ይሆናሉ የሚሉት ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ እስራኤል፡– የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ለአርሶ አደሩ አሊያም ለአምራች የተሻለ የገበያ ዋጋ መክፈል ነው። የተሻለ ዋጋ ለመክፈል ደግሞ በቡና ገበያ ስርዓት ውስጥ እሴት የማይጨምሩ ወይም ለሴክተሩ ምንም ዋጋ የሌላቸው አካላት ከውስጡ እየወጡ አምራችና ላኪው በቀጥታ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻለ ገበያን በመክፈት አርሶ አደሩን የተሻለ ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እድል ይፈጥራል። ከዚህ አኳያ በቡሌ ሆራም ሆነ በጅማ ወርደን እየሠራን እንገኛለን።
ልክ በዛ ልክ በቡና ሴክተሩ የተሰማሩ ሌሎች ድርጅቶች ወርደው መስራትን ይጠይቃቸዋል። በዚህም ስራቸው አምራቹን ኃይል መደገፍ ይገባቸዋል። ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚደረግ ከሆነ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ከምታመርተው ምርት በቅርብ ጊዜያት ወደ 200 በመቶ እጥፍ አድጎ መቀየር ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ጠንክሮ መስራትና የአቅርቦት ሰንሰለቱንና የግብይት ስርዓቱን መቀየር ግድ ይላል፤ በዚህ ጉዳይ በጅምር የተያዙ ነገሮች አሉ። ይህ አካሄድ ደግሞ ጠንክሮ ከቀጠለ አርሶ አደሩ ምርታማነቱ እጅግ በጣም እያደገ ነው የሚሄደው።
አዲስ ዘመን፡- የቡና ጥራት ላይ የሚቀመጥ ደረጃ አለና ከአርሶ አደሩ ቡና ስትገዙ የቡና ጥራቱ ምን ይመስላል?
አቶ እስራኤል፡- እኛ ከአርሶ አደሩ ጋር ዓመቱን ሙሉ ነው የምንሰራው። እንዲህም ሲባል ቡናው ከማበቡ ጀምሮ የእኛ ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስለሚከታተሉ ጥራቱ የሚጀምረው ከዛ ነው። ቡናው በቅሎ ዛፉ ላይ ከተበላሸ በኋላ እንከኑን ይቀንሰው ይሆናል እንጂ ምሉዕ ሊሆን አይችልም። አንዴ በቅሏልና ችግሩን ለማስወገድ ከመሰረቱ ካልሆነ ብዙም ውጤታማ ሊያደርገው አይችልም። በመሆኑም መሰራት ያለበት ኤክስቴንሽን ላይ ነው። ከዚህ በኋላ የሚኖረው የደረጃ አሰጣጥ የልፋት ውጤት የሚያስገኘው ነው ማለት ይቻላል። እኛ በዚህ መልኩ ነው ከአርሶ አደሩ ጋር ከመሰረቱ የምንሰራው።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ አተያይ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተፈላጊነቱ ምን ያህል ነው?
አቶ እስራኤል፡– ቡናችን ተፈላጊ ነው። ነገር ግን ምርታማነቱ ማደግ ባለመቻሉ የፈላጊዎቹን ፍላጎት ማሟላት አልቻለም። ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ስለመሆኗ ዓለም ሁሉ ስለማወቁ ምንም ጥያቄ የለውም። በቡናው ሴክተር ላይ የተሳተፉ የትኞቹም ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ቡና ማግኘት ይፈልጋሉ። ነገር ግን ሰፊ ምርት አግኝተው ይህን የኢትዮጵያ ምርት ብቻ ይዘው ለመሄድ በቂ አቅርቦት እያገኙ አይደለም። እጥረት አለባቸው። ስለሆነም ምርታችንን ማስፋት ጥራቱንም ማስጠበቅ የግድ ይለናል።
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? ከመንግሥት ጋርስ በልማቱ በኩል ተሳስራችሁ ስለመሥራታችሁ ያለው ግንኙነት እንዴት ይገለፃል?
አቶ እስራኤል፡– የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲቋቋም ለግብርና ምርቶች ሲሆን፣ ተጣርተው ያለቀላቸውን ምርቶች እንዲያገበያይ ተፈልጎ ነው፤ ነገር ግን እያገበያየ ያለው ጥሬ ምርቱን ነው። ሁለተኛ ደግሞ የአቅራቢዎች ሰንሰለት ውስጥ ለምርቱ ምንም እሴት የማይጨምሩ
ተደጓሚዎችን ይፈጥራል። ያ ማለት ከላኪውም የሚወስድ ጥቅም እንዲሁም ከአቅራቢና ከእነሱ በታች ደግሞ ሌላው አርሶ አደሩም አለና የእርሱንም ጥቅም ይወስዳል። ምንም እሴት ሳይጨምር ነገር ግን እያካበተ ትርፍ የሚያገኘው በመቶኛ እያሰላ ነውና ያንን ብቻ እየሰበሰበ የሚሄድበት ስርዓት ነበር።
አሁን ግን ጊዜው ያበቃ ይመስለኛል። መንግሥትም ደርሶበት አይኑን ገልጦ አይቶ አማራጭ የገበያ ሂደት አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት በኩል ፀድቆ አዲስ የገበያ ሕግ (ቨርቲካል ኢንቲግሬሽን) የሚለውን አቋቁሞ በስራ ላይ አውሏል። ለዚያም ነው እኛ ወርደን እየሰራን ያለነው። እዛው በእርሻ ላይ እያሉ ደረጃዎች ወጥተው ከዛው ወደውጭ የሚላክበት ሂደት ላይ እየሰራን ነው ያለነው። ሁሉም ቦታዎች ማለት ይቻላል ላቦራቶሪዎችን ገንብተን ጨረሰን ወደስራ ገብተናል። ባለሙያዎችም ዝግጁ ሆነው ስራቸውን ጀምረዋል። ስለዚህም አሁን የተሻለ በሚባል ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።
በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ከመንግሥት ጋር ባለን ግንኙነት ያየነው ለውጥ አፍሪካ ውስጥ ነው ወይ ያለሁት ብለን ራሳችንን እስከምንጠይቅ ድረስ ነው መልካም ነገር ያየነው፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል የለመድነውና ያደግንበት ሂደት የተለየ ነበር። ምክንያቱም መንግሥትን ፈላጭ ቆራጭ፣ ተፈሪ እንዲሁም የሩቅ አድርገን ነበር የምናየውና አሁን ላይ ባለው ለውጥ ግን መንግሥት እጅግ የህዝብ አገልጋይ እንደሆነና ለህዝብና ለለውጥ እንደሚሰራና እንዲሁም የእኛ አገልጋይ እንደሆነ ነው እየተረዳን ያለነው።
በአገሪቱ ትክክለኛ የኢኮኖሚ ችግሮች ላይ በጣም ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። ችግሮችን ዳስሶና አጥንቶ ነው የተነሳው። ለግብርናው እየተደረገ ያለው ድጋፍ በጣም ከፍ ያለ ነው። ድሮ ትራክተር ስናስገባ ቀረጥ ከፍለን ነው። በመስኖው ዘርፍ ያለውን የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ከውጭ አገር ስናስገባ ቀረጥ እንድንከፍል እንገደዳለን። አሁን ላይ ግን ይህ ነገር ተነስቶልናል።
አልፎ ተርፎ አይዞችሁ፤ በርቱ፤ ቀጥሉ፤ ይህን አስፉ፤ በጣም ብዙ የሥራ ዕድል መፍጠር አለባችሁ፤ ምርታማነታችሁ መጨመር አለበት በሚል በልባችን ያለውንና እኛ የምንፈልገውን በግሌ ደግሞ እኔ የምቆጨትበትን ነገር ያገኘሁት አሁን ነው። በዚህም የገጠመን ትልቅ እድል ነው ብዬ አምናለሁ። እንደ አገር ደግሞ ይህንን እድል ከተጠቀምንበት ኢትዮጵያ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ትቀየራለች። እነቻይናም የሃያ ዓመት ታሪክ ነው የቀየራቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማትቀየርበት ምንም ነገር አይኖርም።
እኛ ስንፈጠር ድሃ ሆነን አይደለም። ብዙ ሀብት አለን፤ ነገር ግን ሀብታችንን እንዳንጠቀም በብዙ ነገር የፍጥኝ ተይዘን ስለታሰርን ነው። ይህም በድህነት እንድንማቅቅ አድርጎናል። ከዚህ በኋላ በድህነት የመማቀቁ ጉዳይ ያበቃለት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ ባለሀብት መንግሥት በጀመራቸው የልማት ሥራዎች ምን ያህል ተሳታፊ ነዎት?
አቶ እስራኤል፡– እኛ አገራችንን በጣም እንደግፋለን። ገበታ ለሸገርም የተጫወትነው ሚና ትልቅ ነው። እንደ አንድ ኩባንያ አስር ሚሊዮን ብር እገዛ አድርገናል። አልፎ ተርፎ ግን እኔ በግሌ የቡና ላኪዎች ማህበር የቦርድ አባል ስለሆንኩ ከአባላቱ አሰባስበን ሌሎቹም በዚሁ እንዲሳተፉ በማድረግ ወደ 400 ሚሊዮን ብር ሰብስበን እንዲገባ አድርገናል።
ኮቪድም ተከስቶ በነበረበት ወቅት እንዲሁ፤ ገበታ ለአገርም ይፋ ሲደረግ ወደ 20 ሚሊዮን ብር ነው ድጋፍ ያደረግነው። ከዚህ ቀደም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም እንዲሁ አድርገናል። በዚህ በዚህ ከመንግሥት ጋር ለመሥራት ወደኋላ ያልንበት ጊዜ የለም። አገርን ለማሳደግና ለመለወጥ የሚመጣ የትኛውም ሐሳብ ቢሆን ድርጅታችን ይደግፋል።
አዲስ ዘመን፡- ወጣቱ ከእሰዎ ህይወት መማር ያለበት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ እስራኤል፡- እኔ እንደ ዕድል ሆኖ የወጣንበት ቤተሰቦቻችን ለፍተውና ደክመው የተቀየሩ ቤተሰቦች ናቸው። በዕድል አይደለም ወደዚህ የመጣሁት። ሠርቶ መብላት፤ ለለውጥ መድከም ከቤተሰቤ የተማርኩት ነው። በተለይ እናቴ ገበያ ቆማ ቸርችራ ነው እኛን ያስተማረችን። የሰው ልጅ ለዓላማ በመቆም ለፍቶ ከሰራ ያለመመበት ቦታ ከመድረስ የሚያግደው ነገር አይኖርም።
ዓላማን ለማሳካት በሚደረግ ሂደት ተስፋ መቆረጥ መታሰብ የለበትም። አብሮ ዋጋ መክፈል እንዳለ ከወዲሁ መረዳት አስፈላጊ ነው። እናቴ ጠንካራ ሴት ስለነበረች ይህን ከእርሷ ተምሬያለሁ። እኛን ታስተምራለች፤ እንዲሁም ራሷም ትማራለች፤ ትነግዳለችም። እኛ የተሻለ ነገር እንዲኖረን የተሻለ ትምህርት ቤት ታስገባናለች። አባታችን እንዲሁ ጠንካራ ስለሆነ በቡናው ዘርፍ አምስተኛ ላኪ ነው። እናም ከቤተሰቦቼ የተማርኩት ሥራንና ጠንክሮ ለዓላማ መቆምን ነው።
ሩቅ አገር ተሰድጄ ያልፍልኛ ማለት እምብዛም አዋጭ አይደለም። ያደጉ አገራት ያላቸውን ሀብት ጨርሰው ተጠቅመው ነው ያደጉት። አሁን የማደግ እድልም አማራጭም ያለው እዚህ በአገራችን ውስጥ ነው። ብዙ ሀብት አለ። ገና አልተነካም። ያንን ሀብት ማየት ያስፈልጋል። ወርቅ ወርቅነቱ የሚታወቀው አጥበሽ ጭቃውን ከላዩ አራግፈሽ ደክመሽ ነው ማንፀባረቁን የምታዪው። ህይወትም እንደዛው ናት። መልፋትና መድከምን ይጠይቃል። በአጭር መንገድ ሄዶ የመበልፀግ ሂደት አሳሳቾች ናቸው፤ ሲያሳስቱም ኖረዋል። ይህ ደግሞ አዋጭ አይደለም። በአጭር የሚያስቀጭ እንጂ ረጅም የሚያስጉዝ አይደለም።
እኔ ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቼና እህቶች በሙሉ የምመክረው አጠገባችሁ ያለውን ነገር ተመልከቱ በሚል ነው። አጠገባቸው ያለው ሀብት ከሰሩበት ወደገንዘብ ይቀየራል። ያለውን ሀብት በመጠቀም ጠንክረው የሚሰሩ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ሊደርስ የሚችል አገር አይኖርም። ያሉትን ፈተናዎች እንደ እድል መውሰዱም ብልህነት ነው። የፈተናው ጊዜ አጭር ስለሚሆን ያንን ዋጋ ለመክፈል ቁርጠኞች መሆንን ይጠይቃል።
እኛ ያደግንበት ባህል ጥበቃን የሚበዛው አይነት ነው። ቤተሰብም ልጁን ሲያሳድግ ጥንቃቄ ያበዛል። ይህ አያያዝ ከፍቅር የመነጨ ስለመኑ እሙን ነው፤ ግን ደግሞ ሰው ራሱን እንዳያሳድግ ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነውና መስበር ያስፈልጋል። አንድ ወጣት ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ከእናት አባቱ ቤት በመውጣት የራስን ህይወት ለመምራት ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል እንጂ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣም በኋላ ተቀጥሮ ደመወዝ ለመውሰድ ብቻ ማሰብ የለበትም። ለመለወጥ ደግሞ ዋጋ መክፈል ግድ ነው። ያለምንም ዋጋ መክፈል የሚመጣ ውጤት የለምና ወጣቱ በአቅራቢያው ያለውን ነገር በመመልከት እሱን ወደሀብት ለመቀየር መትጋት አለበት። ብዙ ጊዜ ገንዘብ ሊሆን የሚችለው ሐሳብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ እስራኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013