ለምለም መንግሥቱ
ወፎች ወይንም አዕዋፋት ክንፍ ያላቸው፣ ደመ ሞቃት፣ የጀርባአጥንት ያላቸው፣ ዕንቁላል ጣይ ነፍሳት ናቸው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በምድራችን ላይ ከ10ሺ በላይ የአዕዋፋት ዝርያዎች ይገኛሉ።
ወፎች ከመሬት ላይኛው ጫፍ (አንታርክቲካ) ድረስ ባለው ቦታ የሚኖሩ ሲሆን፣ መጠናቸው ከአምስት ሳንቲ ሜትር (ሁለት ኢንች)፣ የምትረዝመው ትንሽ ወፍ፣ ሶስት ሜትር አስር ጫማ) የምትረዝመው ሰጎን ድረስ ይለያያል።አዕዋፋት ባላቸው ቀለም፣ መጠንና ባህሪያት የሰውን ቀልብ ይስባሉ።
ሁሉም አዕዋፋት በማንኛውም ጊዜ የሚገኙና በአንድ ሥፍራ ብቻ የሚገኙ ሳይሆኑ፣ ጊዜንና ወቅትን ጠብቀው ከአካባቢ አካባቢ በመዘዋወር የሚኖሩም አሉ። በአንዳንድ አካባቢ ብርቅዬ ተብለው የሚጠሩ አዕዋፋትም እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ድንበር ዘለልና ድንበር የማይዘሉ አዕዋፋት መኖራቸውም አይዘነጋም።በቀለም፣በመጠንና በባህሪ የተለያየ ዝርያ ያላቸው አዕዋፋት የቱሪስት መስህብም ሆነው በጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ሚና አላቸው።ጥቂት የማይባሉ ቱሪስቶችም አዕዋፋቱን ብቻ ለማየት ከሀገር ሀገር ይዟዟራሉ።አዕዋፋቱ በጎ ነገር በማድረግም ጉዳት በማድረስም ስማቸው ይነሳል።የአካባቢ ሥነምህዳርን በመጠበቅና በበጎ ተጽዕኗቸው የሚጠቀሱ መኖራቸው ይነገራል።
በቅድሚያም ከብዙዎቹ መካከል ስለጥቂቶቹ አዕዋፋት ባህሪ እናውሳ። ሰዎች በተሳሳተ መንገድ የሚረዷቸውና በፍርሀት ከሚታዩት አዕዋፋት መካከል የሌሊት ወፍ ይጠቀሳል።ዝርያው መርዛማ ኬሚካል ወይም ጀርሞች ተሸካሚ እንደሆነ ወይም በባህላዊው አስተሳሰብ የመጥፎ ዕድል ምልክት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።የሌሊት ወፍ ብቸኛ መብረር የሚችል አጥቢ እንስሳት ሲሆን፣‹‹ቺሮፔትራ›› ተብለው ከሚጠሩ የእንስሳት ዝርያ ውስጥ የሚመደብ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የሌሊት ወፍ በሥጋት እንደሚታየው ብቻ አይደለችም። ጥቅም ያለው አገልግሎትም ይሰጣል። የሚመገበውን አዝርዕት ከቦታ ቦታ በማሰራጨት ተክሎች እንዲራቡ እና በአዳዲስ ቦታዎች እንዲበቅሉ በማድረግ የሚያከናውነው ተግባር ይጠቀሳል። ለአብነትም የአቮካዶ፣ሙዝ፣ማንጎ እና የመሳሰሉ የፍራፍሬ ተክሎች ናቸው። የሌሊት ወፍ የክብደቱን ግማሽ ያክል ነፍሳትን በአንድ ጊዜ ይመገባል።ይህም በሽታ የሚያመጡ እንደ ወባ ትንኝ ያሉ ነፍሳቶችን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ስለዝርያው ከተጻፉ መረጃዎች ከተጻፉት ጥቂቶቹ ባህሪያቶች ናቸው።
ሌላው ስሙ በብዙዎች ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሳላት አዕዋፍ የመስቀል ወፍ ነው። ሰዎች ረጅም ጊዜ ተጠፋፍተው ሲገናኙ ‹‹ምነው እንደ መስቀል ወፍ በአመት አንዴ የምትታየው ወይንም ምትታይው›› ይባባላሉ። በተለምዶ የመስቀል ወፍ እየተባለ የሚጠራው የወፍ ዘር ግን እንደሚባለው ለብዙ ጊዜ ተሰውሮ በመስቀል የበዓል ወቅት ብቻ ብቅ የሚል ሳይሆን ዘወትርም የሚገኝና አራት አይነት ዝርያ ያለው እንደሆነ ይነገራል።
ምናአልባትም ሰዎች በተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚያዩት የወፍ ዝርያ ብቻ የሚመስላቸው የመስቀል ወፍ በሰዎች እይታ ውስጥ የሚገባው የክረምት ወራት አብቅቶ የበጋው ወቅት በሚጀምርበት ጊዜ ነው። የመስቀል ወፍ ሰብል ስለሚመገብ በዚህ ወቅት ደግሞ ሰብል ስለሚደርስ የመራቢያ ጊዜው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቅሳሉ። በመሆኑም በሰው ዕይታ ውስጥ የመግባት ዕድሉ ሰፊ ነው።
የመስቀል ወፍ ተብለው ከሚጠሩት መካከልም ትናንሾቹ ወይንም ዲንቢጦቹ እንደሆኑም ይገለጻል። የመስቀል ወፍ በኢትዮጵያና በአካባቢው የሚገኝ ዝርያም እንደሆነ ይነገራል። ክንፈ ነጭ ዓሳ አዳኝ ወፍ የሚባለው ደግሞ በመጠናቸው አነስተኛ የሆኑ አሳዎችን በማደን ይታወቃል። መንቆሩ አጠር ብሎ ደንዳና ሲሆን፣ ከሰሜን አውሮፓ የሚመጣ ዘላን ወፍ ነው። በኢትዮጵያ በዋነኝነት በሐይቆችና ትላልቅ ኩሬ አካባቢዎች በብዛት ይታያል። ይህ የወፍ ዝርያ በባህር ውስጥ ሀብት ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ከተግባራዊ ባህሪው መረዳት ይቻላል።
እንዲህ የጥቂቶቹን አዕዋፋት አፈጣጠርና ባህሪዎች ከነገርናችሁ፤ አዕዋፋት ከአካባቢ ጋር ያላቸው ቁርኝትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ስላላቸው ሚና ደግሞ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ላይ ባለሙያ የሆኑት አቶ አሉላ ገብሩ የነገሩንን እንዲህ አቅርበንላችኃል።
እንደ አቶ አሉላ ማብራሪያ አዕዋፋት የየራሳቸው ሥም ያላቸው ሲሆን፣ የኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እና የአካባቢ ሥነምህዳር በመጠበቅ ጉልህ ሚና አላቸው። አዕዋፋት በባህሪያቸው ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ በመሆናቸው የተለያየ ዘር ከቦታ ወደ ቦታ በማዘዋወር ምድረበዳ የሆነ አካባቢ እንዲያገግም በማድረግ የበጎ ተጽዕኖ ሚና አላቸው።ለአብነትም የውሃ ላይ አዕዋፋት በሚኖሩበት የውሃ አካባቢ መኖሪያቸውን ይሰራሉ። ለቤት መስሪያ የሚጠቀሙበት ግብአት በውሃው አካባቢ ተስማሚ የሆነ ሥነምህዳር እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
እንደ አምበጣ ነፍሳትን በመብላት የሚታወቁት የአዕዋፋት ዝርያዎች ደግሞ ሰብል የሚበሉ ተባዮችን በመቆጣጠር ሰብሉ እንዳይጎዳ በመታደግ ሚና ይወጣሉ። ሰብል የሚያጠቁትን ተባዮች ለማጥፋት ሲባል ፀረተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ወይንም መድኃኒት በመጠቀም አካባቢ ላይ ጉዳት ከማስከተል በተፈጥሮ መንገድ አዕዋፋትን በመጠቀም ችግሩን ማስወገድ የጎላ ጠቀሜታ አላቸው።
የተለያዩ ዕጽዋትን የሚመገቡ አዕዋፋት ደግሞ በሚጸዳዱበት ስፍራ የበሉት ዘር መልሶ ስለሚበቅል በዚህ ረገድም የአካባቢውን ሥነምህዳር በመቀየር አወንታዊ ሚና ይወጣሉ። የአዕዋፋቱ ኩስ ለማዳበሪያም በማዋል ጥሩ ምርትና ምርታማነት እንዲሰጥ ያስችላል።
በተለምዶ ጥንብ አንሳ ተብሎ የሚጠራው የወፍ ዝርያ ደግሞ አካባቢን በማጽዳት ይጠቀሳል።ይሁን እንጂ ይህ አዕዋፍ በሰዎች ዘንድ ሲወደስ አይሰማም። ግን ጥቁሙ የጎላ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ተሞክሮዎች የሚያሳዩት ለበአላትና ለተለያዩ ዝግጅቶች በየአካባቢው ዕርድ ይከናወናል። የሥጋ ተረፈ ምርትም በየአካባቢው ይጣላል።ጥንብ አንሳ አዕዋፋት ደግሞ እነዚህን ቆሻሻዎች ያፀዳሉ።አካባቢው እንዳይቆሽሽ ብቻ ሳይሆን፤በቆሻሻው ምክንያት የማህበረሰብና የእንስሳት ጤና እንዳይጎዳ በማድረግ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው።
እንደ አቶ አሉላ ገለጻ አዕዋፋት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውም የጎላ ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በአዕዋፋት ቱሪስቶችን በመሳብ ተጠቃሽ ሀገር ናት። እንደሀገር የአዕዋፋት ሀብት ብቻ ሳሆን ኢትዮጵያ የመሬት አቀማመጧ፣ የዝናብ ሁኔታ፣ የአፈር ልዩነቱ በአጠቃላይ ተስማሚ የሆነ ብዝሃህይወት ያላት መሆኗ ልዩ ያደርጋታል። በመሆም ኢኮኖሚን በማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።
በመዝናኛነት ከሚውሉት አዕዋፋት መካከል ፓሮት፣ ፒኮክ የተባሉት አዕዋፋት የሚጠቀሱ ሲሆን፣በፓርክ ውስጥ ተይዘው ለጎብኝዎች ይዘጋጃሉ። ጥቅሙ በመታወቁ ገበያ ላይ በማቅረብ ብዙዎች ገቢ ያገኙበታል። ተመራማሪዎችም በአዕፋት ሥነባህሪና በመሳሰሉት ላይ ጥናት የሚያደርጉ በመሆናቸው አስፈላጊነታቸው የጎላ ነው። አዕዋፋት ከእምነት ጋርም ቁርኝታቸው ከፍተኛ ነው።
አንዳንድ ሀገራት የአዕዋፋትን ምስሎች ለብቻቸው፣ከሰውና ከተለያየ ነገር ጋር በማድረግ ይጠቀማሉ። በተረት ተረት፣ በምሳሌያዊ አነጋገርና ሥነቃል አዕዋፋት በሥነጽሁፍ ውስጥም ይጠቀሳሉ። በአሜሪካን ሀገር ንስር በጣም የተከበረ እንስሳ ሲሆን፣ እንደ መለያም ተደርጎ ይወሰዳል። በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ አዕዋፋት ለምግብነት ይውላሉ።
አዕዋፋቱን መመገብ ጤናማ ተደርገው እንደሚወሰዱና መድኃኒት እንደሆኑ ይነገራል። አዕዋፋት ለአልባሳትም ይውላሉ።በተለይም ላባቸው ለትራስ በመዋል ተስማሚ እንደሆነ ይነገራል።
አቶ አሉላ እንደሚሉት በዚህ ምድር ላይ አስፈላጊ አይደሉም የሚባሉ አዕዋፋት የሉም። ስለአዕዋፋቱ ጥቅምም ሆነ ጉዳት የሚነሳው ወይም የሚለካው ከሰዎች አንጻር እንጂ በያንስ የአንዱ አዕዋፍ መኖር ለሌላው ጥቅም አለው በመሆኑ አይጠቅምም የሚባል ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም። ከጉዳት አንጻር ሊነሳ የሚችለው ከአካባቢ ስነምህዳር አንጻር ተስማሚ ሆኖ ሳይገኝ ብቻ ነው። ለምሳሌ እምቦጭ አረም ለኢትዮጵያ ሥነምህዳር ተስማሚ ባለመሆኑ ነው ጉዳቱ የከፋ የሆነው።
አዕዋፋትም እንዲሁ በተመሳሳይ ከሌላ አካባቢ በመምጣት ጉዳት ሲያደርስ ነው ችግሩ የሚነሳው። አዕዋፋት ከሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚ ይኖራል። አንዱ አጋጣሚ በኤርፖርቶች አካባቢ የሚስተዋለው ከአውሮፕላኖች ጋር በመጋጨት ጉዳት ያደርሳሉ። እነርሱም ይጎዳሉ። ከመኪናና ከፎቅ ጋር በመጋጨትም ይሞታሉ። ከአካባቢ ሥነምህዳር አንጻር ሲታይ እነርሱ ወደ ሰው ሄደው ሳይሆን፣ ሰው ነው ወደ እነርሱ የሄደው።
ሥነምህዳርን በመጠበቅ በጎ ተጽዕኖ ያላቸውን አዕዋፋት እንዴት መጠበቅና መንከባከብ እንደሚቻል አቶ አሉላ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ግን ያልተነገረላቸው አዕዋፋት መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። የአዕዋፋት ጥቅም በጥናት ተደግፎ መከናወን ይኖርበታል። በዚህ ረገድ አካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ከፍተኛ ሚና አላቸው። ተቋማቱ አዕዋፋቱ መኖራቸው ስለሚያስገኙት ጥቅምና ባይኖሩ ስለሚያደርሱት ጉዳት በማህበረሰብ ውስጥ በቂ የሆነ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
አዕዋፋት ወደ አንድ አካባቢ ሲሄዱ ምግብና መጠለያ ፈልገው ስለሆነ ማህበረሰቡ ይህን ተገንዝቦ በማሟላት ረገድ ድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ይገባል።ሰዎች በግንዛቤ እጥረት አዕዋፋቱ የፈልጉትን እንዳያገኙ ሊያደርጉ ይችላሉ። ለአብነትም የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለእርሻ በመጠቀም ምግብ እንዳያገኙ፣የሚጠጡትን ውሃም ለመስኖ በመጠቀም ውሃ እንዳይጠቀሙ ሊያደርጓቸው ይችላሉ።
ለመጠለያ የሚገለገሉበትን ዛፎች በመቁረጥም መኖሪያ ያሳጧቸዋል። ነገር ግን ማህበረሰቡም አዕዋፋቱም ሳይጎዱ እኩል ተጠቃሚነትን በሚያሰፍን መልኩ መሥራት እንዲሁም የአዕዋፋት መኖር ለማህበረሰቡ ህልውና እንደሆነ በማስገንዘብ ከአዕዋፋቱ የሚገኘውን ጥቅም ማጎልበት ይቻላል። የመገናኛ ብዙኃንም በዚህ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ አቶ አሉላ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2013