ራስወርቅ ሙሉጌታ
ቤተሰብ የህብረተሰብ መሰረት ነው፡፡ ያለ ህብረተሰብ ደግሞ ሀገር ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሀገርን ሀገር ለማለት መሟላት ካለባቸው መስፈርቶች ውስጥ የህብረተሰብ መኖር አንዱ ስለሆነ ነው፡፡ አንድ ማህበረሰብ ትውልድን እየተካ እንዲቀጥል ደግሞ ጋብቻ ጉልህ አስተዋፆኦ አለው፡፡
ቤተሰብ የህብረተሰብ የተፈጥሮ መነሻ በመሆኑ በሕብረተሰብና በመንግስት ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ ይታመናል፡፡ በመሆኑም የመንግስት ጥበቃ የሚገለፅበት አንዱ መንገድ የቤተሰብ ግንኙነትን በህግ መደንገግና መግዛት ነው፡፡
በቤተሰብ ውስጥ የሚነሱ ክርክሮችን ፍትሃዊ በሆነና በተቀላጠፈ ሁኔታ ብቃት ባለው አካል እንዲዳኙ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለፌደራሉ መንግስት በሆኑ መስተዳድሮች ተፈፃሚነት የሚኖረው የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ በስራ ላይ ውሏል፡፡
የቤተሰብ ህግ በፍትሀ ብሄር ህግ ከሚካተቱ ህጎች አንዱ ነው፡፡ የቤተሰብ ህግ በቤተሰብ መካከል የሚኖሩ ፍትሀ ብሔራዊ ጉዳዮችን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ በሰዎች መካከል የሚኖሩ ግላዊና ቁሳዊ ጉዳዮች የሚዳኙበት ህግ ማለት ነው፡፡
ግላዊ ከሚባሉት ውስጥ እንደምሳሌ ብንመለከት በጋብቻ ውስጥ በባልና ሚስት መካከል ሊኖር ስለሚገባ የመከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ፣ ቤተሰብን በጋራ መምራት፣ አብሮ መኖርና የመኖሪያ ቦታን በጋራ መወሰን፣ የመተማመን ግዴታን እናገኛለን፡፡ ቁሳዊ ጉዳዮች ደግሞ የባልና ሚስትን የንብረት ባለቤትነት ሁኔታዎች በቀጥታ የሚመለከት ይሆናል፡፡ በተጨማሪ የተወሰኑ ክልሎች እንደ ማህበረሰባቸው የባህል፣ልማድና እንደየአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ የራሳቸው የቤተሰብ ህግ አውጥተው በስራ ላይ እያዋሉ ይገኛሉ፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የህግ አግባብና የመንግስት ሃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የተመሰረቱ ቤተሰቦች እንዳይፈርሱና ውጤታማ እንዲሆኑም በህጉ ባይካተቱም ቀጥሎ የተጠቀሱት ምክረ ሀሳቦች የተሳካለት ቤተሰብ ለመመስረት ወሳኝ መሆናቸው ይነገራል።
ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር
ደስተኛ ቤተሰብ ለመመስረት ጠንካራ ግንኙነት መኖር በተለይም በሁለቱ ጥንዶች (ባልና ሚስቶች) መካከል መኖር መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የተሳካ የቤተሰብ ግንኙነት መኖር የጠንካራና የጤናማ ቤተሰብ መገለጫ ነው፡፡ ባላደጉ ሀገራት ጥንዶች በጋብቻ ህይወት ውስጥ ሰዎች ሲኖሩ ውስጣዊ ፍላጎቶቻቸውን በግልፅ መነጋገር እምብዛም የተለመደ ባይሆንም ለስኬታማና ደስተኛ ህይወት ግን በግልጽነት መነጋገር እርስ በርስ መናበብ፣ መደናነቅና ፍቅራቸውን መገላለጽ ደስተኛ ቤተሰብን ለመፍጠር የሚረዱ ናቸው፡፡
ቤተሰብ በእለት ተእለት ግንኙነት ውስጥ በሀሳብ፣ በቃላትና በድርጊት መግባባታቸው ብሎም የእያንዳንዱን ግለሰብ የግል አመለካከትና አቀባበል መረዳት ይጠበቃል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ መግባባትን መፍጠር የሚችለው የሰው ልጅ በማስተዋል በአትኩሮት ነገሮችን ሲመለከትና ሲያዳምጥ እንቅስቃሴዎችንም ሲገነዘብና ምላሽ ሲሰጥም ነው፡፡
ጥንዶች ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው ከሚያስችለው መንገድ መካከልም አንደኛው ለውይይት የሚሆን ግዜ መስጠት ነው። ለምሳሌ አብዛኛውን ግዜ በስራ የሚያሳልፉ ባልና ሚስቶች ከተጣበበውም ሰአታቸው ቀንሰው ቢሆን በቋሚነት በመገናኘት ስለትዳራቸው ስለቤታቸው ስለልጆቻቸውና አጠቃለይ ሁኔታዎች የሚወያዩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።
እንደዚህ አይነት ግንኙነቶች በአንድ ወገን በሁለቱ ጥንዶች መካከል መቀራረብን የሚያዳብሩ ሲሆን በሌላ በኩል ችግሮች ካሉ እንኳን ሳይባባሱና ስር ሳይሰዱ በወቅቱ እንዲፈቱ እድሉን ይሰጣል። በውይይት ወቅትም በአክብሮት መያዝ ማለት አንድ ባል ወይም ሚስት የተሰማቸውን ስሜት ለመግለጽ ሲሞክሩ እስከመጨረሻው ሀሳባቸውን እንዲገልጹ እድል መስጠትና ማስጨረስ ማለት ነው፡፡
ሀሣባቸውን አለማጣጣል እና አለማቋረጥ እነሱ በቀጥታ ምን ሊነግሩን እንደፈለጉ ለማወቅ ይረዳናል፡፡ ይህም ጥንዶች በመደበኛነት ከሚያደርጓቸው ውይይቶች ባለፈ ካለ ምንም ንግግርና ጥያቄ የተጓዳኛቸውን ፍላጎት በማንበብ የማይፈልጉትን ነገር አለማድረግ በአንጻሩ የሚፈልጉትን ማድረግ ማለት ነው።
ጣልቃ ገብነትን ማስወገድ
በጥንዶች መካከል በጓደኛና በቤተሰብ የሚፈጠሩ ጣልቃ ገብነቶች ለበርካታ ትዳሮች መፍረስ ምክንያት እንደሆኑ ይታወቃል። ምንም እንኳን እንደማንኛውም ጉዳይ ከቤተሰብም ሆነ ከጓደኛ ጋር ስለ ትዳር ህይወት መወያየትም ሆነ ምክር መውሰድ የተለመደ ቢሆንም ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ግን ለትዳር አጋር ብቻ ሊሆን ይገባል።
ከቤተሰብና ከጓደኛ የሚሰጡ ምክሮች በሙሉ ስህተት ናቸው ማለት ባይቻልም ጉዳዩ የሚመለከተውና በተግባራዊነቱም ላይ በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆኑት ሁለቱ ጥንዶች በመሆናቸው ሀሳቡን እንደ ሀሳብ ተቀብሎ ማቅረቡ ችግር ባይኖረውም ለሚወሰነው ውሳኔ ግን የትዳር አጋር ሙሉ ፈቃደኝነት ሊታከልበት ይገባል።
በዚህ ረገድ ጥንዶች በጋራም ሆነ በተናጥል ከየቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙባቸው የተለያዩ ሀይማኖታዊ በአላት እንደ ሰርግና ለቅሶ ያሉ ማህበራዊ ክንዋኔዎች መኖራቸው ግልጽ ነው። በመሆኑም እነዚህና ሌሎች መሰል አጋጣሚዎች የሚፈጥሯቸውን ግንኙነቶች ለትዳር በጎ ግብአት የሚሸመትባቸው እንዲሆን ማድረግ ከጥንዶች የሚጠበቅ ይሆናል።
በዚህ አይነት ሰላማዊ ከተጽእኖ ነጻ የሆነ ቤተሰብ ለመመስረት ደግሞ ጥንዶች ገና የትዳር ህይወታቸውን ሶስት ጉልቻ አቁመው መመስረት ሲጀምሩ አንስቶ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጓደኞቻቸው ሊመጡ የሚችሉትን ተጽእኖ ፈጣሪ ግንኙነቶች ገደብ ሊያበጁላቸው ይገባል።
ይህንንም እንደየሁኔታው አንዳንድ ግዜ በሁኔታዎች የሚገለጽ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በቀጥታ በመናገር ከጣልቃ ገብነታቸቸው እንዲታቀቡ ማድረግ ተገቢ የሚሆንበት አጋጣሚ ስለሚኖር ለሀሳብ ለተግባርም ቅድሚያ የሚሰጡት ትዳር አጋራቸው መሆኑን በግልጽ መናገርና ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።
በገቢና ወጪ ላይ ተወያይቶ ከስምምነት መድረስ
እንደ ጣልቃ ገብነት ሁሉ በቤተሰብ ውስጥ ገቢና ወጪን በተመለከተ የሚፈጠሩ አለመስማማቶች በርካታ ትዳሮች ላይ የሚፈጥሩት ተጽእኖ አለ። በተለይ አሁን ባለንበት የኑሮ ውድነት በየቀኑ እየጨመረ ባለበት ወቅት በትዳር ውስጥ የሚኖሩ ጥንዶች ለገንዘብና ለቁጠባ የሚኖራቸው አተያይ ጠንካራ ሊሆን ይገባል።
የገቢ ማነስ የራሱ ችግር ያለው ቢሆንም በእጅ ያለውን ገቢ በአግባቡ በስምምነት መጠቀም መቻል ግን ገንዘቡ ከሚያመጣው ጥቅም ባለፈ የሚደረጉት ነገሮች በመሉ በስምምነት የተደረጉ ስለሚሆን በቤት ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ አላስፈላጊ ጭቅጭቆችን ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ ይረዳቸዋል።
ይህም ሆኖ በተለያዩ ውስጣዊም ሆነ ውጪያዊ ምክንያቶች በንግግራቸው መሰረት አንዳንድ ሁኔታዎችን ማካሄድ አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል እንደ ማንኛውም ጉዳይ ስህተቶች ቢፈጠሩ ነገሮችን በትእግስት ማለፍ ከሁለቱም ተጓዳኞች የሚጠበቅ ይሆናል። ይሄ ግን በተለይ በአንድ ወገን ተደጋጋሚነት ሲኖረውና በአማካኝነት ደረጃ ሲሆን ለትዳር መፍረስ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ የሚፈለግለት ጉዳይ መሆን አለበት።
የልጆች አስተዳደግን በተመለከተ የጋራ ኃላፊነት መውሰድ
አንድ ቤተሰብ ውጤታማ መሆኑ ከሚገለጽባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ልጆችን አስተምሮና የጥሩ ስነ ምግባር ባለቤት አድርጎ ለወግ ለማእረግ ማብቃቱ ላይ ነው። በእርግጥ ለልጆች ሁለንተናዊ ማለትም የአካል የስነ ልቦናና የጸባይ መብቃት በርካታ አካላት ሃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም ቀዳሚዎቹ ግን ቤተሰብ በተለይ እናትና አባት ወይንም አሳዳጊዎች ናቸው።
ይህም ሆኖ በሀገራችን ብዙ ግዜ ለልጆች አስተዳደግ ሀላፊነት ወሳጅ ተደርገው የሚወሰዱት እናቶች ናቸው። በእርግጥ በተፈጥሮ ሂደት ልጆችን የመንከባከቡ ጉዳይ ከወንዶች ይልቅ ለሴቶች የቀረበ ቢሆንም ጤነኛ ሆነው እንዲያድጉም ሆነ የተስተካከለ ስነ ምግባር እንዲኖራቸው የአባቶች ሃላፊነትም ከፍተኛና ወሳኝ ነው።
ይሄ ደግሞ ግዜ ከመስጠት የሚጀምር ይሆናል። ሁሉም አባት ቢቻል በየቀኑ አልያም በቀናት ልዩነት በአጋጣሚ ሳይሆን ሆን ብሎ ከልጆቹ ጋር የሚያሳልፈው ግዜ ሊኖረው ይገባል።
በዚህ ግዜም በአንድ ወገን በትምህርትም ሆነ በህይወት ተሞክሮ ያገኛቸውን ልምዶች የሚያካፍልበት ፤ እንዲhuም ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እንዴት መሆን እንዳለበት መስመር ለማስያዝ የሚያስችለው ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ልጆቹ ያለባቸውን ችግር ያሰቡትንና አጠቃለይ ያሉበትን የአመለካከትም ሆነ የተግባር ሁኔታ ለማወቅና መቀጠል ያለባቸውን እንዲቀጠሉ ማስተካከል ያለባቸውን እንዲያስተካክሉ በወቅቱ እርምጃ ለመውሰድ እድሉን ይሰጠዋል። ልጆች በትምህርት ውስጥ ያሉ ከሆነ ደግሞ በተመሳሳይ ግዜ በመስጠትና እቅድ በማውጣት ከመምህራኖቻቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት መፍጠርና መወያየት በቅርበት ልጆች ያሉበትን ሁኔታ ለመገንዘብ ይጠቅማል።
ለትዳር አጋር ተገቢውን አክብሮት መስጠት
ለትዳር አጋር አክብሮትን መስጠት ለአብሮነት ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ለሰው ልጅ አክብሮት መስጠት በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ቢሆንም ለትዳር አጋር የሚሰጡ አክብሮቶች ግን የተጓዳኝን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ሊሆን ይገባል። ለትዳር አጋር የሚሰጠው ክብርም ከልብ የመነጨ በንጹህ ፍቅር የሚገለጽ ሲታይ የሚደረግ ሳይታይ የሚተው መሆን የለበትም።
በዚህ በኩል ወደ ሌላ መሄድ የሚለው በቅድሚያ የሚነሳ ይሆናል። አንድ ሰው ከትዳር አጋሩ ውጪ ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት ሊፈጥርና ሳይታወቅበት ረጅም ግዜንም ሊያሳልፍ ይችላል። ነገር ግን የዚህ ሰው ትዳርም ሆነ ማህበራዊ ግንኙነት ሁሌም አደጋ ውስጥ እንዳለ ብሎም አንድ ቀን የትዳር መፍረስ መለያየትና የቤተሰብ መበተን እንደሚገጥመው መገንዘብ አለበት። በመሆኑም በአንድ ወገን እንዲህ አይነት ችግሮች የተፈጠሩ ካሉ ያለምንም ማመንታት እንዲቆሙ ማድረግ የሚጠበቅ ሲሆን የራስን ጸባይ መሰረት በማድረግም ከዚህ በኋላ እንዳይፈጠሩ ሁኔታዎችን እየዘጉ መሄድ ይጠበቃል።
ለምሳሌ አንድ ባል ለዚህ ነገር የሚዳርገው መጠጥ በመጠጣቱ ከሆነ ራሱን ከመጠጥ በማራቅ ሊሆን ይችላል። ይህ ለትዳር አጋሩና ለልጆቹ ያለውን ክብር የሚያሳይ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ባል ሚስቱ ማምሸቱን እንደማትወድ የሚያውቅ ከሆነ ይህንን ሀሳቧን በመቀበል ሳያመሽ የሚገባ ሲሆን ለሚስቱ ክብር አለው ማለት ነው።
በሌላ በኩል አንዳንድ ግዜ ጥንዶች ተጓዳኛቸው ለእነሱ ያለውን ክብር የሚለኩት የእኔ ለሚሉት ቤተሰብ በሚሰጠው ክብርና እውቅና ይሆናል። ለምሳሌ አንዲት ሚስት ባሏ ለእሷ ከሚያደርገው ባልተናነሰ ለእናትና አባቷ ብሎም ለወንድሞቿ ክብር እንዲኖረው ልትፈልግ ትችላለች። እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲገጥሙ የራስንም ሆነ የቤተሰብን ጥቅም በማይነካና ጣልቃ በማያስገባ ሁኔታ አስፈላጊውን ክብር መስጠት አንዳንድ ግዜም ስለ ባለቤቱ ቤተሰቦች ጤንነትና ያሉበትን ሁኔታ መጠየቅ የትዳር አጋርን ለማስደሰት ይጠቅማል።
መቻቻል
በትዳር መካከል የሚኖር መቻቻል እንደሌሎቹ ማህበራዊ ግንኙነቶች ሁሉ ጠንካራ ስፍራ ያለው ነው። የሰው ልጅ በባህሪው ጥፋት አብሮት ያለ በመሆኑ ማንም ሰው ቢሆን ፍጹማዊ ሆኖ ሊኖር አይችልም ትዳርን ያህል ትልቅ ተቋም ውስጥ ሲኖሩና በበርካታ ምክንያቶች በየቀኑ ከሰዎች ሲገናኙ ደግሞ የሚፈጠሩ ብዙ ችግሮችና አለመግባባቶች ይኖራሉ።
መቻቻል የሚያስፈልገውም እነዚህ ችግሮች እንዳይባባሱና ለሌላ መሰረታዊ ችግር (ለቤተሰብ መፍረስ) ብሎም ለልጆች መበተን ምክንያት እንዳይሆኑ ለማድረግ ነው። መቻቻል ሲነሳ ደግሞ ይቅር ባይነት አብሮ ይነሳል ይቅር ሲባል ግን ለሁለቱም ወገኖች አደራን የሚያስተላልፍ መሆን አለበት። በአንድ ወገን በደል ተፈጽሞበት አልያም የማይፈልገው ነገር የተደረገበት ሰው ይቅር ብያለሁ ሲል ይህንን ጉዳይ ዳግም በማንሳት (በማቄም) ሌላ ግዜ ንትርክ ላለመፍጠር ሲሆን፤ በሌላ በኩል ይቅር የሚደረግለት ሰው ደግሞ ያንኑ ተመሳሳይ ጥፋት ደግሞ ላለመስራት ቃል የሚገባበትና የሚተገብረውም መሆን አለበት።
አንዳንድ ሰዎች ነገሮችን በዝምታ የሚያልፉት በሌላ ግዜ አንስተው ለመውቀስ በመሆኑ አንድ ችግር ሲፈጠር ከአመታት በፊት የተደረጉ ነገሮችን ሳይቀር በማስታወስ በችግር ላይ ችግር ሲደራርቡ ይታያሉ። የዚህ አይነቱ የቂም አካሄድ ለሁለቱም ወገን ጉዳት ያለው በመሆኑ ነገን በማሰብ በንጹህ ልብ ይቅር በመባባል «በደልን መርሳት እንኳን ባይቻል» መተው እንደሚቻል ጥንዶች ሊረዱትና ሊተገብሩትም ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2013