ምህረት ሞገስ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የሚገኝ የመጀመሪያውና ትልቁ የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ስም የኢትዮጵያን የትምህርት ዕርምጃ እንዲያሳይ ታኅሣሥ 9 ቀን 1954 ዓ.ም. ተመስርቷል። የዘውዳዊው መንግሥት ሥርዓት ካከተመ በኋላ፤ ደርግ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚል ስም ሰይሞታል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና አስተዳደሩን ስድስት ኪሎ በሚገኘው በዋናው ግቢ ያደረገ ሲሆን፤ በስድስት ኪሎ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ እንዲሁም የኢንፎርማቲክስ ፋኩልቲ፣ በአምስት ኪሎ የቴክኖሎጂ ፋኩለቲ፣ በአራት ኪሎ የሳይንስ ፋኩልቲ፣ በጥቁር አንበሳ የህክምና ፋኩልቲ ፣ በልደታ የቴክኖሎጂ ፋኩለቲ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ፣ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት፣ የጥርስ ህክምና ትምህርት ቤት፣ እንዲሁም በደብረዘይት ከተማ የእንስሳት ህክምና ፋኩልቲን ያስተዳድራል።
በስሩ የያዛቸው ፋኩልቲዎች እና ኢንስቲትዩቶች ሲታሰቡ፤ የዩኒቨርሲቲውን ትልቅነት እና የመምህራኑን ቁጥሩን ብዛት እንዲሁም ይህ ተቋም በአገር ግንባታ ላይ የሚኖረው ሚና ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
ለአገር መልካም በማድረግ እና ህዝብን መስመር በማስያዝ በኩል ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ይኸው ዩኒቨርሲቲ ብዙዎች እንደሚገልፁት፤ እንደስያሜው እና እንደአንጋፋነቱ የሚጠበቅበትን ያህል ሀላፊነት እየተወጣ አይደለም። ለዚህ ዋነኛው ችግር በዩኒቨርሲቲው ጠንካራ የመምህራን ማህበር አለመኖሩ ነው።
‹‹የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ማህበር ለመመስረት ቢፈለግም አልሆነም፤›› በማለት ዝግጅት ክፍሉ ድረስ በመምጣት የጠቆሙት በዩኒቨሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋ እና ባህሎች አካዳሚ መምህር እና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዓለማየሁ ዶጋሞ ናቸው።
ዶክተር ዓለማየሁ እንደሚናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ለአገር ዕድገት ሊወጣ ከሚገባው ሚና ባሻገር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከመማር ማስተማር እና ከምርምር ጋር ተያይዞ ሰፊ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አሉ። አሁን ባለው የዩኒቨርሲቲው አመራር ደግሞ ጥያቄዎች እየተመለሱ አይደሉም። እንደውም ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲቀርቡ በመምህራኖች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። አምባገነንነት አለ።
ለዩኒቨርሲቲው በግለሰብ ደረጃ ከሚቀርበው ጥያቄ በተጨማሪ በተለያየ መልኩ በደል የሚፈፀምባቸውን መምህራን ለመጠበቅ የመምህራን ማህበር ይቋቋም የሚል በቡድን የቀረበ ጥያቄ ነበር። ታዲያ የመልካም አስተዳደር ችግር ለማቃለል ጠንካራ የመምህራን ማህበር በማቋቋም ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሀላፊነት ይወጣ።
በመምህራኖች ላይ የሚደርሰውን በደልም ለመቆጣጠር ጥረት ይደረግ በማለት፤ ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ‹‹ማህበር ለማቋቋም የውይይት መድረክ እናዘጋጅ›› የሚል ማመልከቻ አቅርበዋል። ነገር ግን ለቀረበው ጥያቄ መልስ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ። ‹‹ያሉም ሆነ አዳዲስ የሚሾሙ ሚኒስትሮች ዩኒቨርሲቲውን መንካት አይፈልጉም።›› ያሉት ዶክተር አለማየሁ፤ ‹‹ላሚቷን ያጠቃል ተብሎ የተጠበቀው በሬ የላሚቷን ወተት ጠባው›› ይባላል ካሉ በኋላ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ፕሬዚዳንቶችም ሆኑ የትምህርት ሚኒስትሮች ሲሾሙ ዩኒቨርሲቲውን ከብልሹ አሰራር ይጠብቃሉ ተብለው ሲጠበቁ ሙሰኛ የሚሆኑበት አጋጣሚ በስፋት መኖሩን ያብራራሉ።
ሚኒስትሮች የዩኒቨርሲቲው መምህር ሳይሆኑ የዩኒቨርሲቲው ደመወዝ ስለሚሻል ፔሮል ውስጥ ስማቸው ተካቶ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሁኔታ እንደነበር እና ከፕሮጀክቶች እና ከምርምር ገንዘቦች ጋር ተያይዞ የጥቅም ትስስር በመፍጠር፤ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን ብልሹ አሰራር እንደማስተካከል ተንበርክከው ለዩኒቨርሲቲው ብልሹ አሰራር እጅ የሚሰጡበት ሁኔታ መኖሩንም ያመለክታሉ።
ዶክተር አለማየሁ፤ ቀድሞ ጠንካራ የመምህራን ማህበር ነበር። የመምህራንን ጥቅምን በሚመለከት ጥሩ የሚታገል ከመሆኑም ባሻገር የአገሪቱን የትምህርት የፖሊሲ አቅጣጫን የሚያመላክት በእነዶክተር ታዬ ወልደሰማያት የሚመራ ታዋቂ የዩኒቨርሲቲው የመምህራን ማህበር ነበር። ነገር ግን ከቆይታ በኋላ ባልታወቀ ሁኔታ ማህበሩ ታግዷል። አመራሩ እና ማህበሩ እያለ ቢሮው ታሽጎ ህልውናው ጠፍቷል። ይህ ከሆነ አስራ አምስት ዓመት አልፏል። ነገር ግን ማህበሩ ሳይኖር አሁንም ድረስ ከመምህራን የማህበር አባላት የገንዘብ መዋጮ ከደመወዛቸው ይቆረጣል።
እንደዶክተር ዓለማየሁ ገለፃ፤ አሁን ግን በፈቃደኝነት በመንቀሳቀስ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለውጥ እንዲኖር ማህበሩ እንዲቋቋም ጥረት እያደረጉ ነው። በቅድሚያ የነበረው ማህበር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፈልገው ነበር።
ነገር ግን የነበሩት የቀድሞ የማህበሩ አባላት ማህበሩን በድጋሚ ማቋቋም በመፍራታቸው አፈግፍገዋል። እነርሱ ግን ምንም እንኳ በዩኒቨርሲቲው ያለው አመራር አምባገነን ቢሆንም፤ የሚመጣ ነገር ካለም ለመቀበል ዝግጁ በመሆን ማህበሩ እንዲቋቋም የሚፈልጉ መሆኑን ገፍተው ጥያቄውን በማቅረብ ላይ ናቸው።
‹‹ማህበሩን ማቋቋም ከባድ አይደለም። አሁንም ድረስ ተቆርጦ የት እንደሚገባ የማይታወቅ ገንዘብ ለመምህራን ማህበር በሚል እየተቆረጠ ነው። የቀድሞ ቢሮ ለሌላ ጥቅም ውሏል። ድሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በር ላይ የመምህራን ማ።ህበር የሚል ፅሁፍ ነበር። አሁን ምንም የለም። የሚጠይቀው ይህንን ማስተካከል ብቻ ነው›› በማለት፤ አሁን በቀላሉ በአዲስ መልክ ማህበሩ እንዲቋቋም ይደረግ።
ውይይት ይካሄድበት እና በቀጣይ በአጠቃላይ በመምህራኑ ሙሉ ተሳትፎ መግባባት ላይ መድረስ እንዲቻል የተወሰኑ መምህራኖች በፈቃደኝነት እሸቱ ጮሌ አዳራሽ መድረክ ለማዘጋጀት አቅደው የውይይት መድረኩን ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረባቸውን ይገልፃሉ። ነገር ግን የታሰበውን የውይይት መድረክ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ግልባጭ ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ ማመልከቻ የተሰጠ ቢሆንም፤ ተቀባይነት አለማግኘቱን ያብራራሉ።
እንደዶክተር አለማየሁ ገለፃ፤ ላለመቀበላቸው ማሳያው በዩኒቨርሲቲው አሰራር ለእያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮግራሙ ይገለፅ ነበር። በተጨማሪ ጥያቄ አቅራቢዎቹ የመድረኩን ዝግጅት በሚመለከትም ዩኒቨርሲቲው የራሱን አማራጭ ወስዶ ሊሄድበት ይችላል። ወይም ለማዘጋጀት ‹‹ሀላፊነቱን እንወስዳለን›› ብለው በታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለጥር 1 ቀን ውይይቱ እንዲካሄድ ጥያቄ አቅርበዋል።
‹‹በተለያየ መልኩ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ። ይህ ማህበር ቢቋቋም መምህራን እየደረሰባቸው ያለ ብዙ በደል አይደርስባቸውም ነበር።›› በማለት ለምሳሌ እርሳቸው ላይ የደረሰውን በደል ይናገራሉ። ዶክተር ዓለማየሁ እንደሚገልፁት፤ አንድ ጊዜ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ቦርዱ ባለበት ጠንከር ያለ ሃሳብ በማቅረባቸው ምክንያት ተፈልጎ ያለአግባብ የሶስት ወር ደመወዝ ተቀጥተዋል።
የተቀጡት የመምህራንን ዕድል ያለአግባብ ተወስዷል በማለታቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ሰበብ የተደረገው ደግሞ በዲፓርትመንት ስብሰባ ላይ ‹‹ስልክ ወጥተህ አነጋግረሃል፤ ስብሰባ ረብሸኻል›› በሚል ነበር ይላሉ። ይህ ሁሉ የመምህራን ማህበር ቢኖር ሊከላከሉት እና ሊደግፋቸው ይችል እንደነበር ጠቁመው፤ መምህራን ላይ ለሚፈፀም በደል ሁሉ የመምህራን ማህበሩ መኖር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ያብራራሉ።
ደመወዝ ከመቁረጥ ጀምሮ ያለበቂ ምክንያት የተባረሩ መምህራኖች አሉ። ካሉ በኋላ ለምሳሌ ‹‹የጉስቁልና ጌቶች ሞገሱን የገፈፉት ዩኒቨርሲቲ›› በሚል መፅሀፍ የፃፈው ብርሃኑ ደቦጭ ሁለት እና ሶስት ጊዜ ተባሯል ይላሉ።
የጥቁር አንበሳ ዲን ዶክተር ዳዊት ወንድምአገኝ ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት ሳይቀር ተፎካካሪ ሆነው የተወዳደሩ ብቃት ያላቸው ቢሆንም፤ ከሀላፊነቱ አስነስተዋቸው አሁን በመምህርነት ብቻ በመስራት ላይ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
ማህበሩ የመምህራንን በደል ከመከላከል ባሻገር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥመውን የትምህርት ጥራት ችግር ለማቃለል እና ትልልቅ የትምህርት ዘርፉ ስህተቶች ለመከላከል እና ለመቀነስም የራሱን ሚና ይጫወት እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር አለማየሁ፤ ለምሳሌ ሁለት ጊዜ የተሰረቀው ብሔራዊ ፈተና ራሱ የዩኒቨርሲቲ መምራን ማህበር ቢኖር በእንዝላልነት ችግሩ የሚፈጠርበት ዕድል እንደሚቀንስ እና ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ተደባብሶ ከመቅረት ይልቅ እንዳይደገም ተጠያቂነት የሚኖርበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር ይላሉ።
‹‹የመጀመሪያው የ12ኛ ክፍል ፈተና ሲሰረቅ በተማሪዎች ስነልቦና ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም። በእርግጥ የተሰረቀው ፈተና ተሰርዞ ሌላ ፈተና ተዘጋጅቷል።›› ያሉት ዶክተር ዓለማየሁ፤ በዛ ጊዜ ለተፈፀመው ድርጊት ተገቢው እርምጃ ባለመወሰዱ በድጋሚ ፈተናው ለሁለተኛ ጊዜ ለመሰረቅ በቅቷል።
ፈተናው የሚዘጋጀው በዩኒቨርሲቲው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለው የትምህርት ጥናት እና ምርምር ተቋም ላይ በማህበሩ በኩል ተፅዕኖ በመፍጠር ፈተናውን የሚያዘጋጁት ሰዎች በጥንቃቄ ሥራውን እንዲሰሩ ስህተትም ከፈጠሩ የሚጠየቁበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር ይላሉ። ከፈተናዎች ድርጅት ጋር ሲሰሩ ከመልስ መስጫ ጋር ተያይዞ ክፍተት እንዳይኖር፤ ክፍተት ቢኖር እንኳ ትውልዱ እንዳይጎዳ በአጭሩ መቆጣጠር የሚቻልበትን ዕድል ማህበሩ ይፈጥር ነበር ይላሉ።
ሌላው ችግር በተቋሙ የሚሾሙ ፕሬዚዳንቶች በተደጋጋሚ ወደ ውጭ የሚሄዱበት ሁኔታ መኖሩ በመምህራኑ ላይ ተፅዕኖ ከማሳደሩም በላይ የኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሚና እንዳይጫወት አድርጓል። በዚህ ሳቢያ አንዳንዴ ፕሬዚዳንት አልባ ዩኒቨርሲቲ የሚባልበት ሁኔታ አለ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንቶች ጉዞ ለህክምና እና ለሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም ተደጋጋሚ ከሆነ ዩኒቨርሲቲውን እንደሚጎዳ አያጠራጥርም። ተወካይ ቢኖርም ተወካዩ ተክቶ የሚሰራው የተወሰነ ሥራ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ሥራው የማይሰራበት ጊዜ ብዙ ይሆናል። ማህበሩ ቢኖር ኖሮ በዚህ ላይም ችግሩ እንዲቃለል ጫና መፍጠር ይችል ነበር ይላሉ።
የማህበሩ መቋቋም መምህራን ላይ የሚፈፀመውን በደል ለመከላከል ያግዛል ሲባል፤ አለመግባባት ሲኖር ተነጋግሮ እንደመፍታት በአምባገነንነት ስልጣንን በመጠቀም መምህራን በዩኒቨርሲቲው ጊቢ እንዳይገቡ ለጥበቃዎች ደብዳቤ በመበተን መምህራን ባስተማሩበት እና በሰሩበት ጊቢ እንዳይገቡ እስከመከልከል ድረስ የሚፈፀም በደልን ለመከላከል ማህበሩ የሚያግዝ መሆኑንም ይገልፃሉ።
እንደዶክተር ዓለማየሁ ገለፃ፤ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ነው። ከመሳሪያ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ከባድ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ችግሩን የሚፈጥሩትን ለመከታተል እና ለማቃለል መሳሪያ ለማሰራት ቢፈልግም አልተቻለም።
የመምህራን ማህበሩ ቢኖር በቀላሉ በጥገና ስም የሚሰረቁ መሳሪያዎች ላይ ጥብቅ ክትትል ለማድረግ ይቻል ነበር። በተጨማሪ እንደአሁኑ አይነት አገር አቀፍ ምርጫ ሲካሄድ፤ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ በመሆኑ ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ በምሁራኖች አወያይነት ፓርቲዎች በዩኒቨርሲቲው የሚወያዩበትን መድረኮችን በማዘጋጀት በመሪነት ተሳትፎ ለማድረግ የሚችልበት ዕድል ይፈጠር ነበር ይላሉ።
እርሳቸው በቆዩባቸው የተወሰኑ ዓመታት የመምህራን ማህበር ሲሰራ አይተው እንደማያውቁ የሚናገሩት ደግሞ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ጌታሁን ዳና ናቸው። እንደርሳቸው ገለፃ፤ በዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ለመምህራን የሚሟገት ማህበር የለም።
የበፊቱ ማህበርም ቢሆን ንቁ ሆኖ የሚንቀሳቀስ ካለመሆኑም ባሻገር የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነበረበት። ገለልተኛ እና ነፃ ማህበር ቢኖር መምህራን የሚጎድላቸውን ለማሟላት ለምሳሌ፤ የመብት ጉዳይ፣ የማስተማር ነፃነት፣ የሚያስቡትን ጉዳይ በቀጥታ ሃሳብን የማስተላለፍ እና በአጠቃላይ ይሟላልኝ የሚሉትን ለማሟላት ይቻል ነበር።
እንደአቶ ጌታሁን ገለፃ፤ ቀደም ሲል ጠንካራ ማህበር እንደነበር ሰምተዋል። የማህበሩ ዋና ዓላማ የመምህራንን መብት እና ጥቅም ማስከበር ነው። ለምሳሌ የብዙ መምህራን ራስ ምታት የቤት ችግር ሊሆን ይችላል። ይህንን ችግር ለማቃለልም ማህበር ቢኖር የተሻለ ዕድል ነበር። አሁንም ለመምህራን ማህበር በሚል የሚቆረጥ ገንዘብ አለ። በሺ የሚቆጠር መምህር አለ። እስከ አሁን ተቆርጦ የነበረው ብር የት እንደደረሰ አይታወቅም። ያም ሆነ ይህ አሁን ላይ ማህበሩ ቢቋቋም ጥሩ ነው። ነገር ግን ማህበሩን ለማቋቋም በቂ ድጋፍ እየተገኘ አይደለም።
እዚህ ላይ ከአመራሩ ፈቃደኝነት አንፃር ብቻ ሳይሆን በመምህራን በኩልም ክፍተት መኖሩን የሚያመለክቱት አቶ ጌታሁን፤ ብዙ ሰው መምህራን ማህበር ይቋቋም የሚለውን ሃሳብ ቢደግፍም በተለያዩ ምክንያቶች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ግፊት መፍጠር ላይ ክፍተት መኖሩ የሚታበል አለመሆኑን ያብራራሉ።
አቶ ጌታሁን ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አገሪቱ ትልቅ ውስብስብ ችግሮች ያሉባት በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስለማህበር ማሰብን እንደተራ ጉዳይ ማየት አንደኛው ሊሆን ይችላል ይላሉ። ሁለተኛው በኢኮኖሚው ላይ ያለው ውጣ ውረድ ማለትም መምህራን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስለኢኮኖሚ እያሰቡ ሲወጠሩ ማህበር ማቋቋምን እንደቅንጦት በማየታቸው ነው የሚል ግምት አላቸው።
በተጨማሪ በሥራ መጠመድ እና እስከ አሁን የመምህራን መብትን አስመልክቶ የሚታጋል አካል አለመኖሩ መምህራኑ ተስፋ እንዲቆርጡ ስላደረጋቸው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ በችግር ውስጥ መኖር ከተለመደ ከዛ መውጣትን ብዙ ሰው የማያስበው በመሆኑ አሁንም ማህበር ስለማቋቋም የሚያስቡ እና በሀላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀሱት ውስን መሆናቸውን ይናገራሉ።
በሌላ አገር ውስጥ ትልልቅ ለውጥ የሚያመጡ ጠንካራ ማህበራት ሲኖር ነው በማለት ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ያለውን ጠንካራ የሰራተኛ ማህበር በመጥቀስ፤ እነርሱ ተሰሚነት እንዳላቸው እና መንግስት ለእነርሱ ምላሽ የሚሰጥ እነርሱም ምላሽ የሚቀበሉ ናቸው ይላሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር ነፃ ማህበር የለም። የበፊቱ ማህበር ሙሉ ለሙሉ ጠፍቶ እንደአዲስ ከመጀመር ይልቅ የነበረውን ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ ማህበሩን ማጠናከር እና ነፃ ሆኖ እንዲሰራ ማድረግ የተሻለ ነው ካሉ በኋላ፤ ማህበር ሲኖር ትልቁ ጉዳይ ሰዎች በማህበሩ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ማስቻል መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ጌታሁን ገለፃ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የዩኒቨርሲቲውን መምህራን በመሰብሰብ አነጋግረው ነበር። በጊዜው ከመምህራን ‹‹የመኪና እና የቤት ችግር አለብን›› በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹መኪናን ያለ ግብር ለማስገባት በቂ መንገድ የለም።
የቤቱን ችግር ለመቅረፍ ግን ተደራጅታችሁ ቅረቡ እና መንግስት መሬት ያቀርብላችኋል›› የሚል መልስ ሰጥተው ነበር። ነገር ግን የነበረው የመምህራን ማህበር በእኔ በኩል ተደራጁ ሲል ሰዎች ማህበሩን ባለማመን አንመዘገብም ብለው ጉዳዩ ተጨናገፈ። ሰዎች በማህበሩ ላይ እምነት ከሌላቸው ዋጋ የለውም በማለት በወቅቱ የነበረውን ያስታውሳሉ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ አንፃር እንኳን ሲታይ ለመምህራኖቹ ቤት ያልሰጠ ብቸኛ ዩኒቨርሲቲ ነው። ይህ አሁን በጣም ተራ ነገር ነው። አዲስ አበባ ውስጥ በትራንስፖርት እየተቸገሩ በቤት ኪራይ እየተጉላሉ ከህይወት ጋር ግብ ግብ ማድረግ ከባድ ነው። ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለምሳሌ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የዲፓርትመንት ሰብሳቢ የነበረው ሰው ዲን ሲሆን ለየት ያለ ቤት ይሰጠዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ግን ብዙም ደረጃውን ያልጠበቀ በጣም ጥቂት ቤት ለመምህራን ተሰጥቷል። አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለመምህራኖቹ የጋራ መኖሪያ ቤት ገዝቶ ሰጥቷል።
ትናንት የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ይህን ሲያደርግ፤ ይኽኛው አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲስ ለምን ይህንን አያደርግም ሲባል ጥያቄውን በተናጥል ከማቅረብ ይልቅ ጠንካራ ማህበር ቢኖር ኖሮ ምላሽ ያገኝ ነበር። ሆኖም ያ አልሆነም። ነፃ የሆነ የዩኒቨርሲቲ ማህበር ማቋቋም መልካም መሆኑ መዘንጋት የለበትም ይላሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ አቶ ሰብስብ በላይ እንደሚናገሩት፤ ከ1997 ዓ.ም በኋላ በዩኒቨርሲቲው የገቡት ሰዎች በተለያየ መልኩ የፖለቲካ ሰዎች ናቸው።
ቀበሌ ሲሰሩ የነበሩ የሁለተኛ ዲግሪ እንዲማሩ እየተደረገ ይገቡ ነበር። ተማሪዎች ራሳቸው ተመርጠው ሥልጣን ከያዙ በኋላ፤ በዩኒቨርሲቲው የደህንነት ሥራ ይሰራሉ። እንደገና ማደሪያ ተሰጥቷቸው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይሰራሉ። የዩኒቨርሲቲ መምህራኑ ራሱ አንድ የሚያደርገው ጉዳይ ውስን ነው።
ዩኒቨርሲቲው ከፖለቲካ ድርጅት ጋር ተጣብቋል። ይህ ከላይ እስከ ታች ከፕሬዚዳንት ጀምሮ እነርሱን የሚገዳደር እና ጥያቄ የሚያቀርብ ጠንካራ ማህበር እንዲቋቋም አይፈልጉም።
ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በመምህርነት ከማገልገል ባሻገር የምርምር ሥራንም እንደሚሰሩ የሚናገሩት አቶ ሰብስብ፤ ‹‹የኮንትራት ተቀጣሪ ነህ›› በሚል በመባረራቸው መምህር ብሎ ኮንትራት የለም በሚል በፍርድ ቤት ሰበር ድረስ ተከራክረው አሸንፈዋል። ሆኖም በዚህ ላይ መምህራኖች ሊደሰቱ እና ሊደግፏቸው ሲገባ ቤቱ በብሔርተኝነት የተጨማለቀ በመሆኑ አንዳንዶች ‹‹ለምን አማቻችንን ከሰስክ?›› እንዳሏቸው ይገልፃሉ።
‹‹ አንድ ትልቅ ዝሆን በትንሽ ገመድ ታሰረ፤ አሳሪው ገመዱን ፈቶ ዝሆኑን ቢለቀውም ዝሆኑ መታሰር የለመደ በመሆኑ አልሄደም።›› የሚሉት አቶ ሰብስብ፤ መምህራኖቹ ራሳቸው እንቅፋት የሚሆኑበት አጋጣሚ መኖሩን በማስታወስ ፤ አንዱ በጎሳ ሌላው በጥቅም አንዳንዱ ‹‹ከደሙ ንፁህ ነኝ›› ብሎ እየሸሸ አንድ አድርጎ ነፃ እና ጠንካራ ማህበር ማቋቋም ከባድ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ።
‹‹ሙስና ላይ ያለውን ችግር ስናገር፤ ግዢ ላይ ችግር አለ።›› ሲሉ ከጎናቸው ከመቆም ይልቅ፤ ‹‹ስለሰው አትናገር፤ እንቶኔን አትንካ ›› የሚሏቸው መምህራኖች ብዙ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
አቶ ሰብስብ እንደሚናገሩት፤ እርሳቸው ግልፅ ናቸው። መጀመሪያ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው በዩኒቨርሲቲው ቅርንጫፍ ተቀጠሩ። ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ በተመራማሪነት ነበር። ቀጥለው ወደ አቃቂ የሄዱ ሲሆን 2004 ላይ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው የአገር ልማት መካነ ጥናት ኢንስቲትዩት (IDPR) ገቡ። 75 በመቶ ምርምር 25 በመቶ ደግሞ በመምህርነት እንዲሰሩ ተቀጠሩ። ከእርሳቸው በኋላ ሁለት ሰዎች ተቀጥረዋል። ሁለት ዓመት ሲሆናቸው ቅጥሩ ኮንትራት ነው በሚል ያባርሯቸዋል።
በማሰናበቻው ደብዳቤ ላይ ‹‹ በፕሮጀክት የተቀጠሩ በመሆኑ የምንከፍለው የለንም የሶስት ወር ደመወዝ ተሰጥቷቸው ተሰናብተዋል›› የሚል ሲሆን፤ እነርሱም ለሁለት ዓመት ተሟግተው ለማሸነፍ በቅተዋል። ፍርድ ቤቱ ቢወስንም በዩኒቨርሲቲው ባለው አምባገነንነት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አንቀበልም እስከማለት ተደርሶ እንደነበር አስታውሰው፤ ‹‹ታስረው እንዲቀርቡ›› ሲባል ግን አሸንፈው በመምጣታቸው ያስገቧቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደአቶ ሰብስብ ገለፃ፤ ሰራተኛውን አሰባስቦ ለመብቱ ማቆም እና በተለይ ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ማህበር ማቋቋም ከባድ ነው። ምክንያቱም በተለያየ መልኩ ጠንካራ አስተማሪ እና ተመራማሪዎች አይፈልጉም። ይህ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ችግር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ችግር ነው። ከላይ ካልጠራ ችግሩ ሊቀረፍ አይችልም። መጀመሪያ ከላይ እስከ ታች ፍቃደኝነቱ መኖር አለበት። ለትክክለኛ ዓላማ እና ለእውነት የሚሰራ አካል ቢኖር ጥሩ ነው።
ጠንካራ ማህበር ቢቋቋም በአገር ደረጃ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻል ነበር። ነገር ግን ጠንካራ ከፍተኛ አቅም ያላቸው መምህራን ሸሽተዋል። ብቃት ያላቸው ሰዎች ዲን ለመሆን እንኳ ተወዳደሩ ሲባሉ አይወዳደሩም። አሁን ላይ ስለትልቂቱ ኢትዮጵያ ማሰብ ያስፈልጋል። አፍሪካ ውስጥ ተቋማትን ነፃ ማድረግ እና ነፃ ማህበራትን ማቋቋም ከባድ ነው። ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥማል። ነገር ግን ትልቁን የአገርን ሥዕል አይረሱም። ስለዚህ እርሳቸውም ትልቅ ሥራ ሊሰራ የሚችል ነፃ ማህበር እንዲመሰረት ፍላጎት አላቸው። ሆኖም ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ያመለክታሉ።
ከላይ ሃሳባቸውን የገለፁልንን ከዶክተር አለማየሁ ውጪ ያሉትን አቶ ጌታሁን እና አቶ ሰብስብን በዛው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሄደን ያገኘናቸው ሲሆን፤ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለቃለ መጠይቅ በሄድንበት ወቅት ‹‹ከዩኒቨርሲቲው በተለይም በመምህራን ዲኖች ፈቃድ ሳታገኙ እና ደብዳቤ ይዛችሁ ሳታስፈቅዱ ለኢንተርቪው መግባት የለባችሁም›› በሚል ከጥበቃዎች ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ የተገባ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ለማናገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
በስልክ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናን ያገኘናቸው ቢሆንም፤ ከእርሳቸው ጋር ምንም አይነት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ይመስረት የሚል ሃሳብ አለመቅረቡን ገልፀው፤ ንግግራችንን በዛው ዘግተውታል። ከመምህራኑ በቀረቡት ጥያቄዎች ዙሪያ በሰፊው ለመወያየትም ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
በዚሁ ጉዳይ ላይ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር አካልም ሆነ መምህራን እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አካላት ማንኛውንም ሃሳብ መሰንዘር የሚችሉ ሲሆን፤ እኛም ለማስተናገድ ዝግጁ ነን።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2013