ለምለም መንግሥቱ
ኢትዮጵያ ቀጣይት ያለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲስፋፋ፣የህዝቦችዋ ኑሮ እንዲሻሻል ከውጭም ከሀገር ውስጥም ባለሀብቶች በተለያየ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እንዲሰሩ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ ጭምር ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች።በተለይም የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ለማሳደግ ያላትን የመሬት ሀብት፣ምቹ የአየር ፀባይና የሚሰራ የሰው ኃይል ለውጭ ባለሀብቶች በማስተዋወቅ ያደረገችው ጥረት ይጠቀሳል። በትላልቅ ኩባንያዎች ውስጥ በመሳተፍ የጎላ ሚና ባይኖራቸውም በአቅማቸው በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ በተለያየ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እራሳቸውንም ሀገርንም በመጥቀም በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሚና ቀላል አይደለም።
ኢንቨስትመንት በመሳብ እንደሀገር ተጠቃሚ ለመሆን ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ባለሀብቶቹ ወይንም ኢንቨስተሮቹ በሚሰማሩበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተስማሚ የሆነ፣ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ የማያስከትል፣በባለሙያ የታገዘ ጥራት ያለው ግንባታ ማከናወናቸውን ማረጋገጥ ይገባል።በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት መልካም ተሞክሮ አለው።
በጽህፈት ቤቱ የግንባታ ቁጥጥርና ዲዛይን አጽዳቂና ግንባታ ፈቃድ ሰጭ አቶ ካሳ ንጉሱ እንዲህ ያስረዳሉ።በክልሉ በከብት ማድለብ፣በዶሮ እርባታ፣በፋብሪካ ደረጃ ደግሞ እንደ ፓስታና ማካሮኒ፣ዱቄት የመሳሰሉ የምግብ ፋብሪካዎች በማቋቋምና በሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ።አምራች ኢንዱስትሪዎቹ እስከዛሬ ባለው ተሞክሮ አብዛኞቹ ባለሀብቶች ለሥራ የወሰዱትን ቦታ አጥረው በማስቀመጥ ጥቅም ላይ አያውሉትም።ይህ ደግሞ የአካባቢው አርሶ አደርም አርሶ እንዳይጠቀምበት እንቅፋት ፈጥሯል። ከብት ለማድለብ ፈቃድ ወስደው የእርሻ ሥራ የሚያከናውኑም ጥቂት አልነበሩም። ሥራ የጀመሩትም ቢሆኑ ለሥራቸው የሚያከናውኗቸው ግንባታዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ስለመሆኑ አይጨነቁም። የግንባታ ሙያ የሌለውን በአነስተኛ ገንዘብ በማሰራት ነው ወደ ሥራው የሚገቡት። ይህ ደግሞ በዘርፉ የተዘበራረቀ አሰራርን አስከትሏል።
እንደ አቶ ካሳ ማብራሪያ ባለሀብቱ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲሰጠው አብሮ የግንባታ ፈቃድም መያዝ እንዳለበትና ሥራውንም ከመጀመሩ በፊት ግንባታው በዲዛይን የተደገፈና በግንባታው ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ብቃት አለመታየቱ ነው። ይህ አለመሆኑ ደግሞ ባለሀብት ለግንባታ ትኩረት እንዳይሰጥ ከማድረጉ በተጨማሪ ለሥራ የወሰደውን ቦታ እንደፈለገው እንዲያደርግም መንገድ ከፍቷል።የተሰሩትም ግንባታዎች ቢሆኑ በባለሙያ የታገዙ ባለመሆናቸው ጥንካሬ በማጣት ሲፈርሱና የተለያየ ችግር ሲያስከትሉም ቆይተዋል።ግንባታዎቹ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ተጽዕኖም ግምት ውስጥ አለመግባቱ ችግሩን አባብሶታል።ለጽህፈት ቤቱ መቋቋምም ምክንያት ሆኗል። ጽህፈት ቤቱም ከ2009ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ገብቶ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ለመፍታት ጥረት አድርጓል።
ችግሩ ታውቆ ሥር እስኪሰድ ድረስ እንዴት የሚቆጣጠር አካል አልነበረም ተብሎ አቶ ካሳ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የክልሉ ከተማ ልማት ቢሮ ነበር ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርግ የቆየው።ነገር ግን በቢሮው ብቻ የሚከናወነው የዲዛይንና መፅደቅ እንዲሁም የክትትል ሥራ ውጤታማ ለማድረግ አላስቻለም።ሥራውን በአንድ ቢሮ ብቻ ማከናወንም ከፍተኛ የሥራ ጫና አስከትሏል።ተገቢውን ሥራ መሥራትም ሆነ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ባለማስቻሉ ሥራውን ብቻ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ጽህፈት ቤት የማቋቋም ውሳኔ ላይ ነው የተደረሰው።
ጽህፈት ቤቱ ከተቋቋመ በኋላ ስለተሰሩ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም በሥራው ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንም አንስተው አቶ ካሳ እንዳብራሩት፤ የግንባታ ሥራው ባለሙያ የማብቃትና የሥራ ዕድል መፍጠር በመሆኑ በቅድሚያ በዘርፉ ባለሙያ ያለው ስለመሆኑ እና የብቃት ማረጋገጫ ፈተና (ሲኦሲ) ወስዶ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያለውና ያሟላ ማስረጃ ይታያል።በግንባታ ዘርፉ በግንበኝነት፣ በአናፂነትና በሌላም ዘርፍ የሚሰማራው ባለሙያ ሥራውን በብቃት እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን ወደ ወረቀትም እንዲቀይር የሚረዳ በመሆኑ በትምህርት የታገዘ ባለሙያ እንዲሆን ያስችላል። ግንባታው በታወቀና ብቃት ባለው የተማረ ኮንትራክተር እንዲሰራ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል።በዚህ መልኩ የሚከናወነው የግንባታ ሥራ የበቃ ባለሙያን ማሳተፍ ብቻ ሳይሆን ተተኪም ለማፍራት ያግዛል።
የኢንቨስትመንት ሥራውም በግንባታ በኩል ጥራት ይኖረዋል።ኢንቨስተሩም በዚህ በኩል ተባባሪ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን በዚህ መልኩ መከተል ግዴታም አለበት።የሥራ ፈቃድ ይዞ ወደ ጽህፈት ቤቱ ሲሄድ ካርታና ፕላኑን ይዞ መቅረብ ይኖርበታል።ጽህፈት ቤቱም መረጃው የተሟላ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ነው ወደ ሥራ የሚገባው። ባለሙያውን ማሟላት ብቻ ሳይሆን ለግንባታ የሚውለው አሸዋ፣ድንጋይና ሌሎችም ግብአቶችና ግንባታው የሚከናወንበት መሬት ህንፃ የሚገነባበት ከሆነ መሬቱ ወይንም አፈሩ ህንፃ መሸከም እንደሚችል ከግንባታው በፊት ቀድሞ የሚከናወን ተግባር ነው።
ለግንባታ የሚውለው ብረትም እንዲሁ ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑ ይታያል።በተመሳሳይ ከብት በማድለብና ዶሮ በማርባት ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችም እንስሳቱን የሚያቆዩበት፣ ከእንስሳቱ የሚወገደው ቆሻሻ በአካባቢ ላይ ብክለት እንዳያስከትል ቆሻሻ የሚያስወግዱበት ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም የቆሻሻ ማስወገጃ(ሴፍቲንክ ታንክ)እንዲገነቡ ይደረጋል።እንስሳቱም በተሻሻለ አያያዝ ጤንነታቸው ተጠብቆ የእርባታው ሂደት እንዲሆኑ ማቆያቸው በዲዛይን ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ይደረጋል።
በበሽታ የተጠቁ፣ለገበያ የደረሰና ገና በማድለብ ወይንም በርቢ ሂደት ላይ የሚገኝ እንስሳት አብረው በአንድ ቦታ ሳይሆን ተለይተው መቀመጥ ስላለባቸው የግንባታ ዲዛይኑ ይሄን ሁሉ ባካተተ ሁኔታ ነው የሚከናወነው።
ለእንስሳቱ የሚሆን ጤና ጣቢያም የዲዛይኑ አካል መሆኑን አቶ ካሳ ያስረዳሉ።እስካሁን ባለው ተሞክሮ የእንስሳት እርባታው ባህላዊ የአረባብ ዘዴን የተከተለ እንደነበርም አስታውሰዋል። ከብት ለማድለብ ፈቃድ ወስደውም እነርሱ ቀጥታ በሥራው ውስጥ ሳይሳተፉ የደለበ ከብት ከገበያ በመግዛት እያተረፉ በመሸጥ ላይ የተሰማሩ እንደነበሩም ጠቁመዋል።የዲዛይን ሥራው ይህን ሁሉ ክፍተት እንደሚያስቀርም ይናገራሉ።
ጽህፈት ቤቱ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ ደረጃውን የጠበቀ የከብት ማድለቢያ በመሥራት ችግሩን በመቅረፍ ላይ እንደሆነም ገልጸዋል።ሉሜ ወረዳ ቢዮሲቄ፣ ሸራ ዲባዲባ አካባቢዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩና በቅርቡ ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩትንም በተመሳሳይ ከዘመናዊ የአረባብ ዘዴ እንዲከተሉ በማድረግ በዲዛይኑ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ ሥራ መሰራቱን አመልክተዋል።
የግንባታ ዘርፉን ለማሻሻል በተወሰደው እርምጃ ከዚህ ቀደም ኢንቨስተሩ ፈቃድ ያገኘበትን ትቶ ለሌላ ተግባር ያውለው የነበረውን መሬት በማስቀረትና ያለሥራ የተቀመጠ መሬትም እንዳይኖር አግዟል።በግንባታ ዘርፉ እየተከናወነ ባለው ሥራም ዓላማውን ደግፈው ወደሥራ ያልገቡ ኢንቨስተሮችን ጽህፈትቤቱ ከምሥራቅ ሸዋ አስተዳደር ጋር በመተባበር ውላቸው እንዲቋረጥም ተደርጎ መሬቱ መሥራት ለሚችል ባለሀብት እንዲሰጥና ለሌላ ልማት እንዲውል ማድረግ ተችሏል።በብዛት ያጋጠመውም መሬት ወስዶ ወደ ሥራ ያለመግባት ችግሮች ናቸው።በግንባታ ዘርፉ ደግሞ ብቃት በሌላቸው ባለሙያዎች ተገንብተው በአካባቢ ላይ የተለያየ ጉዳት ሲደርስ የነበረ ችግርን ማቃለል ተችሏል።
በጽህፈት ቤቱ በሙያና በተለያየ መንገድ በተደረገ ድጋፍ እንዲሁም የግንባታ ሥራ ክትትልና ቁጥጥር በተለያየ የኢንቨስትመንት መስክ ላይ የተሰማሩ ወደ 98 የሚደርሱ ባለሀብቶች ሥራ ጀምረዋል። ሥራ ከጀመሩትም በምሥራቅ ሸዋ አዳማ ወረዳ አዱላላ በሚባል አካባቢ በፓስታና መካሮኒ እንዲሁም በዱቄት በማቋቋም፣ሞጆ ጆጎጉዴዶ በሚባል መንደር በከብት እርባታና ማደለብ ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች ይጠቀሳሉ።
በግንባታ ዲዛይኑና እየተወሰደ ስላለው እርምጃ በኢንቨስተሩ በኩል ስላለው ተቀባይነት አቶ ካሳ እንዳስረዱት፤ በጽህፈት ቤቱ ክትትልና ቁጥጥር ሥር የሚያልፉት ባለሀብቶች አሰራሩን መቀበል ግዴታቸው እንደሆነ ተገንዝበውና አምነውበት እየሰሩ ይገኛሉ።ለሥራ ከባንክ የተበደሩትን ብር ምዕራፍ በምዕራፍ የሚለቀቅላቸው ደረጃውን የጠበቀ የሥራ ግንባታ ማከናወናቸው እየታየ በመሆኑ የግድ ነው። ጽህፈት ቤቱ ህጉን ተከትለው የማይፈጽሙትን ኢንቨስተሮች የማስቆም ሥልጣን ስላለው እና ባለሀብቱ በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ ስለሚደርስበት ችግር ውስጥ ከመግባት ይቆጠባል።
ጽህፈት ቤቱ የኢንቨስትመንት ዘርፉን በግንባታ ወደተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የበለጠ ጥረት እንዳያደርግ ተዘዋውሮ ለመሥራት የመጓጓዣና ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች(ሎጂስቲክ) ያለመሟላት ተግዳሮት አለበት።ያልተሟሉ ነገሮች ቢኖሩም እንደ አመችነቱ በወር፣በሁለትና በሶስት ወር በተቀመጠለት የግንባታ ደረጃ ሥራወን ማከናወኑን የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን በማከናወን ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።
የክልሉ መንግሥት በዚህ በኩል ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይኖርበታል።በኢንቨስተሩ በኩል ደግሞ የሚስተዋለው ችግር የግንባታ ፈቃድ ወስዶ በወቅቱ ወደ ሥራ አለመግባት ነው።ለመጠየቅ ሲኬድ ባለሀብቱ ሀገር ውስጥ ላይኖር የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል።በአድራሻቸው የማይገኙም ያጋጥማሉ።ይሄ ደግሞ እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ ሆኗል።
ግንባታውን በራሳቸው ጀምረው ለባንክ ብድርና ለተለያየ ድጋፍ ማስረጃ ለመጠየቅ ወደ ጽህፈት ቤቱ የሚቀርቡም ጥቂት አይደሉም።ይሄ አይነቱ አካሄድ ቅጣት ስላለው ጉዳዩን በማሳወቅ እንዲመለሱ ይደረጋል። በአሁኑ ጊዜ የግብአት መወደድም ሌላው ማነቆ በመሆኑ ዘርፉን አስቸጋሪ አድርጎታል። ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ የራሱ ተጽዕኖ ቢኖርም በተለይ ቫይረሱን እየተከላከሉ ሥራው እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል። በአንድ በኩል ኢንቨስትንትን ማስፋፋት በሌላ በኩል ደግሞ በተግዳሮች ውስጥ የሚገኝ ግንባታ ማከናወን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ቢታወቅም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት የተጀመረውን የግንባታ ደረጃ ማጠናከር የግድ እንደሆነ አቶ ካሳ ያስረዳሉ።
በጽህፈት ቤቱ የሚከናወነው ግንባታ ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ የገጠሩንም መኖሪያ ቤት ያካትት እንደሆን አቶ ካሳ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ፤ እስካሁን የተቀመጠ ደረጃ የለም።አብዛኞቹ አርሶአደሮች በይዞታቸው ላይ ነው ግንባታ የሚያከናውኑት።በተጨማሪም ደረጃውን ጠብቀው ለመሥራት የገንዘብ አቅም ውስኑነት አለባቸው።በሂደት ግን ወደ ደረጃ መገባቱ አይቀርም። በአካባቢ ግብአት ወይም ሀብት ቤቶቹ እንዲገነቡ የኦሮሚያ መንግሥት አቅዷል።በክልሉ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ደረጃውን የጠበቀ ዲዛይን በመሰራት ላይ ይገኛል።ሥልጠናዎችም ለባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ናቸው።ስልጠናው ሙቀታማና ቀዝቃዛ የሆኑ አካባቢዎችን ባገናዘበ ወጭ ቆጣቢ በሆነ ግብአት ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት እንዴት መገንባት እንደሚቻል መሰረት ያደረገ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ከኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቢሮ ፈቃድ የወሰዱ ወደ 65 የሚጠጉ የአካባቢው አርሶአደሮች ወደ ሥራ ገብተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2013